ሀገሪቱን ከፊትም ከኋላም በበጎም በክፉም ለመምራት ፖለቲካውን በመግዛትም በመቃወምም የሚዘውሩት ግንባር ቀደም ባለድርሻዎች ኤሊቶች፣ ሊሕቃን፣ አክቲቪስቶችና ምሑራን ናቸው። የእነዚህ መገኛ የት ይሆን ካልን በግለሰብ፣ በቡድን፣ በተቋም፣ በድርጅት እንዲሁም በአማራጭና በገዢ መንግሥት ውስጥ እናገኛቸዋለን። ከዚህ በታች ለሚቀርበው ጽሑፍ ኤሊት፣ ልሒቅ፣ አክቲቪስትና ምሁር በየአንቀጹ በተደጋጋሚ ለአጽንዖት ስለሚቀርብ አንባቢን ላለማስልቸት ከስሞቻቸው የመጀመሪያውን ሆሄ በመውሰድ ኤሊአም በሚል ስያሜ ለመጠቀም ወደድኩ።
ጁሊየን ቤንዳ
ምሑራን በሀገራዊ ድንበርና በጎሳ ማንነት በማይገደብ ዩኒቨርስ ውስጥ የሚኖሩ ናቸው።
መሠረታዊ ሰብዓዊ ፍትሕን በሚመለከት የምትሟገቱ መሆን አለባችሁ። የእናንተ ሀገር ሲሆን ብቻ እየመረጣችሁ የምትሟገቱ ከሆነ የምሑርነትን ነፍስ ታጣላችሁ። መሠረታዊ ችግር ያለው የራስን ማንነት፣ ባሕል፣ ኅብረተሰብና ታሪክ ከሌሎች ማንነቶች ታሪክና ሕዝብ ጋር ለማስታረቅ መቻል ነው።
ፕ.ር ሰይድ
ኢትዮጵያ ከስጋ ዐይናችን በላይ ናት። በንሥር ዐይን የምትነጸር ረቂቅ ሀገር ናት። ናላ ከሰማይ ይሰፋል እንዲሉ እሷን ለማሰብ ሰፊ ሕሊና ግድ ይላል። እፍኝ በምታክል ልባችንም አትመረመርም። በዘመን ብዙ፣ በታሪክ ሰፊ፣ በተፈጥሮ ሀብት በውድ ስጦታ የታደለች ዓለም በተለየ ሁኔታ የሚያያት ልዩ ሀገር ናት።
ይህችን ውድ አገር ለመታደግ ኤሊአም ኃላፊነታችሁ የጎላ ነው። ለአገር ዕድገት፣ ሰላም፣ ብልጽግና ከመድረክ ጀርባ፣ ከጫወታው ሜዳ ዳር፣ ከቀዘፋው ውጪ፣ ከባሕሩ አፋፍ ላይ ትሆኑ ዘንድ አልተጠራችሁም። ሀገር በመገንባት ሂደትም ዜጋው የሥራው አካል እንዲሆንና የድርሻውን እንዲያበረክት እንደ አንድ የተሳካ ተውኔት በጋራ በመጫወት፣ በጋራ በመድመቅ የክብርን ፍሬ ለማሳየት ሀገርን መድረክ ዓለምን ተመልካች አድርጋችሁ የምትጋበዙበት ዕድል መፍጠር የምትችሉት እናንተ ናችሁ።
በተለይም በሀገር ግንባታ ላይ ሰፊ ድርሻ ያላችሁ የመንግሥት ሥራ አስፈጻሚ፣ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ ሕዝባዊ ተቋማት ውስጥ ያላችሁ፣ መምህራን፣ ጋዜጠኞች፣ ደራሲንና የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ሚዛን የደፋ ድርሻ ይጠበቅባችኋል። ለዚሕ “ የሰጎን ፖለቲካ” አስተሳሰብን ወደዳር ማድረግ ይገባል። ከዚሕ አንጻርም በሚገጥሙ ተግዳሮቶች ተሸንፎ ወደኋላ ሳይባል፣ የዛሬ ድኅነቷን ሽሮ በሁለገብ የበለጸገች ሆና ለነገም የምትተርፍ ሀገር ለመገንባት ዕድሉ በእጃችሁ ነው።
ሀገርን የሚቀይሩ ጥቂት ግለሰቦች ናቸው። ዓለምን እንኳን በአንድ ጣት የሚቆጠሩ የበራላቸው ሰዎች ናቸው የቀየሯት። ዓለም መልካም ሰዎች ቁጥራቸው ይነስ እንጂ ነጥፈውባት አታውቅም ይባል የለ። ኤሊአሞች አርቆ አስተዋዮች፣ ለሰው ኖረው፣ ለሰው ሠርተው፣ አገርን ለመለወጥ በሐቀኝነትና በንጹሕ ልብ ደፋ ቀና የሚሉ ናቸው። ባነቁት ሐሳብ፣ በቀመሩት ቀመር፣ በዘረጉት ሥርዓት ሀገርን ይለውጣሉ።
ዛሬ አገር በፊደል ምሑርና በልቡም ቅን የሆነ ኤሊአም ትፈልጋለች። የተማረ፣ በጎ ሐሳብና ቅን ኤሊአም የግል ፍላጎቱን፣ ብሔርተኝነቱንና ጎሰኝነቱን ጥሎ ሁሉም ነገር ከአገር በኋላ የሚልበትን ወኔ አንግቦ የሥራውም ፍሬ በዚህ የሚለካ ሊሆን ይገባል “”””””። በአገራችን ጉዳይ ብዙ የሚቆጩ ነገሮች አሉ። ደግሞ ሁሉም ሰው በዕውቀቱ፣ በጊዜው በጉልበቱ፣ በክህሎቱና በገንዘቡ እንደተለገሰው በሀገር ላይ እንዳለመጠቀም የሚቆጭ ነገር አይኖርም። ሕልምን ለማሳካት፣ ቁጭትን ለመወጣት፣ ጥማትን ለማርካት… የሀገርን ዕድገት፣ ሰላሟ ተጠብቆ፣ ፍትሕና ዲሞክራሲ ሰፍኖ ልትታይ የምትፈለገውን ሀገር በባዶ አትመጣም በጠንካራ ጥረትና ድካም እንጂ።
ጠንካሮች አርቆ አስተዋዮች ሀገርን ይፈጥራሉ። በየትኛውም አገር ሁሉም የታሪክ ክስተቶች በሰው የተፈጠሩ ናቸው። ሀገር በጥረት እንዲገነባ እስራኤል ምስክር ነች። ለብዙ ብዙ ዘመናት ፈርሰው፣ እንደጨው ተበትነው፣ አባቶቻቸው ከተወለዱበት ቀዬ ለቀው፣ ዘራቸውን በሰው አገር ቀጥለው ይኖሩ ነበር። ነገር ግን በጭንቅላትና በልባቸው ውስጥ ያልፈረሰችው አገራቸውን ዳግም ትንሳኤ ሰጥተው ዛሬ የዓለም ቁንጮ አድርገዋታል።
እስራኤላውያን በየሀገሩ እጅግ የሚዘገንን አስከፊ ዘመናትን ተስፋ ከሚያስቆርጥ ሁኔታ ጋር ተጋፍጠዋል። ፍላጎት ካለ፣ ሕልም ካለ በረሃን ገነት ማድረግ ይቻላል። የተበተነውን መሰብሰብ፣ ያልተማረውን ማስተማር፣ የተራበውን ማብላት፣ የተጠማውን ማጠጣት፣ የታረዘውን ማልበስ፣ መጠጊያ ያጣውን ባለቤት ማድረግ፣ ጎዳና የወደቀውን ማንሳት፣ ነዳያንን መርዳት…. ይቻላል። የጠፋው ቅን ልብ፣ በጎ ሐሳቢና መልካም ሕሊና ያለው ኤሊአም ነው።
በሀገራችን ላይ የፍቅር፣ የሰላም፣ የዕድገትና የአንድነት አየር ለማስተንፈስ የችግሯን ሰንኮፍ መንግሎ የሚጥል የበራላቸው የሚፈለጉበት ጊዜው ዛሬ ነው። ዛሬ ለሀገራችን የሚያስፈልጋት በድርሰቱ ልዕልናችንንና አንድነታችንን የሚጻፍበት፣ የታፈነ ዜማ ነጻ ወጥቶ የሕዝብ ልብ የሚያዜምበት፣ በጠቢባን የተሻለ ምስጢር የሚገለጥበት፣ ያላሰብንበትን አኀዝ ሐሳብ የሚቀመርበት፣ የተዳፈነው ሐሳብ ተገልጦ ቅኔ የሚዘረፍበት፣ ሰዓሊያን በተወደሩ ሸራዎቻቸውና በተለወሱ ቀለሞቻቸው የጋራ ምስል፣ የጋራ ገጽታ፣ የጋራ ድምቀት የሚሸከፉበት፣ በየቤተ ተውኔቱ ኅብር እሴት፣ ኅብር ታሪክ፣ ኅብር ሃይማኖት የአንዲት ትልቅ ሀገር የሚመደረክበት ዐውድ በሁሉም የኪነ ጥበብ ዘሮች የጋራ ሀገራዊ መገለጫዎች የሚታይበት እንጂ የምትነቃቀፍበት ጠይመን የምንታይበት“ በአሉታ ብቻ የምንሰለፍበት ሊሆን አይገባም።
ዛሬ እንደሌሎቹ የአደጉ ሀገራት ጥበባትን ለሰው ሀብት ለመገንባት ልንጠቀምበት ይገባል። ሕዝብንና ሀገርን ለመምራት በቅን ልብ፣ በብዕሩ አዕምሮ መዘጋጀትና መብቃት ይፈልጋል። የትናንቷና ገናና ትልቋን ሀገር ወደትልቅነቷ ለመመለስ ከሞቀ ደም ይልቅ ሰፊ ጥበብና ጥልቅ የሀገር ፍቅርን ይዞ መገኘት ግድ ይላል። እርስ በእርስ በመናከስ፣ አንድ ጥግ ላይ ቆሞ የጎሳ ፍላጻ በመወርወር ሰላምን፣ አንድነትና ብልጽግናን ማምጣት አይቻልም። እንደሰላም ማትረፊያ እንደጥላቻ ደግሞ ክፉ ጦርነት የለምና በዚህ አሚነ መሠረት በመታነጽ ዛሬን በአግባቡ ተኑሮ የነገን ፍሬ፣ ዕድልና ተስፋን ለሕዝብ ማሳየት የሚችል ባለቅን ልቦናዎችና ባለብሩህ አዕምሮዎች የሆኑ መንገድ ታላሚ ኤሊአም አገር በስስት ትፈልጋለች።
በኢትዮጵያ ምድር የሰባት፣ የአምስት እንበለው የሦስት ሺህ ገናና ታሪክ ውስጥ ጥቂት ዘመን ብቻ ወደ ኋላ ብንሄድ ተበታትና የኖረችበት ዘመን የቅርባችን ነው። በዘመነ መሳፍንት ዘመን ከትርፍ ይልቅ ኪሳራ፣ ከፍቅር ይልቅ ጥላቻ፣ ከሰላም ይልቅ ጦርነት ከኅብረት ይልቅ መበታተን በመንገሱ የጨለማው ዘመን ተብሎ ተሰይሟል። ዛሬም ዓላማና ግቡ መለያየት በመናፈቅ እኔነትን ብቻ ካቀነቀንን የተያያዝነው ፖለቲካችን ዳግማዊ ዘመነ መሳፍንት ልደቱን ያፋጥንብናል።
ዛሬ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ቆም ብሎ የሚያስብበት ጊዜ ነው። አንዱ የአንዱ ቁስል ሊነዝረው የሚገባበት ጊዜም ነው። ያለመሰልጠናችንና ያለመበልጸጋችን ምክንያት ልንፈትሽ ይገባል። ዛሬ በሥራ ፍሬአቸው የተገለጡ፣ የሕዝብ አፍ ሆነው የልቡን አውቀው የሚያርስ መልስ የሚመልስለትን ልብ ያለው ኤሊአም በብዛት ይፈለጋል። የዜጋውን ተብሰልስሎት የተጋሩ፣ አርቆ አሳቢዎች ኤሊአም መበርከት አለባቸው። በኢትዮጵያ ፍጹም ሰላም በማምጣት ድኅነትን ኋላቀርነትን፣ ጉስቅልናን እንደእርስት የዜጋው ቅጽል ሊሆን አይገባም የሚሉ፣ በአገሪቱ ላይ ድሃ ተበደለ ፍርድ ተጓደለ በማለት የተንሸዋረረውን ሥርዓት መስመር የሚያሲዙ ኤሊቶች ያስፈልጉናል::
ይህቺ ትልቅ ዋርካ፤
ይህቺ ትልቅ ሾላ፤
በገለባ ቀረች ፍሬዎቿን ጥላ። መላኩ ጌታቸው
ተብሎ ስንኝ በተቋጠረላት ሀገር በኩር ፍሬ ሆኖ የዋርካዋን በለስና አበባ ሊመልሱ፣ ስር ሰደው ሊያለመልሙ፣ በቅን ሐሳብ በትሑት ልብ በአፍቅሮተ ሕዝብ ድጋፍና ይሁንታን አንግበው፣ ሀገር ሊመሩ የሙሴን አሰረ ፍኖት ይዘው ሕዝብን ከካራን ወደከነዓን ሊመልሱ የሚችሉ የሕዝብን ልብ የሚያሳርፉ ኤሊአም ያስፈልጋሉ። እንዲህ ሲሆን በአጭር ጊዜ ስኬትና ብልጽግናም ይመጣል። ሕልምም በበጎ ይፈታል። ነገም በጥሩ ይፈከራል። ዛሬ የኢትዮጵያ ስኬት፣ ብልጽግና“ የሰላሟ ባንዲራ የሚውለበለብበት ሰማይ ሁሉም ይናፍቃል። ለዚህም በኤሊአሞቻችን ልብና መንፈስ ውስጥ ለሀገር የሚተርፍ መልካምና ቅን ሐሳብ ሲኖር ብቻ ነው። ይህን ሐሳብ አርክቴክት አሐዱ በላይ አድምቆ ያፀናዋል።
አንድ የእምነት ፍልስፍና ላንሳልህ፣ ጥሩ ነገሮች ምንጭ አላቸው። ፀሐይ ምንጭ አላት። ጨለማ ግን ምንጭ የለውም። የብርሃን አለመኖር ነው የሚፈጥረው። ጨለማን ይዘህ እዚህ ክፍል ውስጥ መግባት አትችልም። ፀሐይ እንዳትገባ ካደረክ ወዲያው ጨለማ ትፈጥራለህ። ጥሩ ነገሮች ምንጭ አላቸው። መሐይምነትን የዕውቀት አለመኖር ነው የሚፈጥረው። ለአንድ ሰው መሐይምነትን ልትሰጠው አትችልም። ዕውቀት ካልሰጠኸው መሐይም ነው። ሀብት እንጂ ድኅነትን ልትሰጥ አትችልም። ፍቅር፣ ቸርነት፣ ታማኝነት ምንጭ አላቸው። ምንጫቸውም እግዚአብሔር ነው። እነዚህን ነገሮች ነፍሳችን ታዳብራለች። የምታደርገውም መልካሙን ነገር ነው። መጥፎው ነገር በጥሩ አለመኖር ነው የሚመጣው።
ለሀገር መልካም መልካሙን ብርሃን ብርሃኑን በመስጠትና በመሥራት የሀገርንና የሕዝብን ሕይወት ማቅናት ይቻላል። ከዛሬ 100 ዓመት በፊት የነበሩ በሙያቸው ሐኪም ቢሆኑም በአጭር የሕይወት ስንቃቸው፣ በሰፊ የንባብ ልምዳቸው፣ በተቀባ የሥነ ጽሑፍ ፀጋቸው ቅርስ የሆነ ጥበብ ፍሬ በመጽሐፋቸው ጥለው ያለፉት ነጋድራስ ገብረ ሕይወት ባይከዳኝ እንዲህ ብለው ነበር። ምስኪኗ ኢትዮጵያ ሆይ የዕድልሽ በር መቼ ይነጋ ይሆን? ይህ ትንቢታዊ ንግግር የመሰለው ሐሳባቸው እውን ሆኖ ኢትዮጵያ ምስኪን ሆና የዕድሏ በር ሳይነጋና ሳይከፈት ለባዕዳን እጇን እንደዘረጋች ከምጽዋት ሳትወጣና የተረጋጋ ሰላም ሳይሰፍንባት በጦርነት፣ በኢ- ዲሞክራሲያዊነት፣ በኢ-ፍትሐዊነትና ሰላም በማጣት የዳጎሰ ሰነድ ሰንዳ አንድ ክፍለ ዘመን በላይ አልቦ ኤሊአም ሆና ተጉዛለች።
የሀገርን ዕድገትና ብልጽግናን ሽተው በለመለመ ታሪክ የተሠራው ሕዝብ ዳዋ ሊውጠው ሲዳዳ በቅንነት መርተው ከወደቀችበት ሊያነሷት፣ የጨለማ መንጦላይቷን ሊገፉላት፣ ስብራቷን ሊጠግኑላት፣ ተስፋዋን የሚመልሱላት፣ የልቧን መሻት የሚፈጽሙላት፣ ሕዝብ አክባሪ፣ በሕዝብ ልብ የሚነግሱ፣ ከሕዝብ ወጥቶ ሕዝቡን የሚዋጁ ኤሊአም ለኢትዮጵያ እንደሚያስፈልጋት ዶ/ር ምሕረት ደበበ ከሥነ ባሕሪ ሐኪምነቱ በተጓዳኝ ከያኒነቱን ተጠቅሞ በጥበብ ብዕሩ እንዲህ ብሏል።
….ወደሕዝብህ ተመለስ፣ ወደሀገርህ ግባ፣ የቆሰለውን የሀገሪቷን ነፍስ እያከማችሁ፣ የተፈረካከሰው ኢትዮጵያ ክብርና ማንነት ፈልጋችሁ ከወደቀበት አንሱት፣ የዚህን ምስኪን ሕዝብ ፍርሃቱና ድንጋጤውን አርግቡለት፣ ጥላቻውንና አለመተማመኑን፣ ጭካኔውና ስግብግብነት …. የበሽታ ምልክቶቹ ናቸው እንጂ የጤነኛ ሰው፣ የሰለጠነ ሰው ኅብረተሰብ ባሕሪያት አይደሉም። አለመደማመጥ፣ ልዩነት፣ መፍራት በኩራት ተውጠው የበታችነት ስሜት መሰቃየት ሌላውን ጥሎ ትልቅ ለመሆን መሞከር ኹሉ የተሸነፈ ማንነት፣ የዘቀጠና የተቀጠቀጠ ሰብዕና መገለጫዎች ናቸው።
ሕዝብ የመረጣቸው፣ በስራ ፍሬ ለውጥን የሚያሳዩ፣ ሀገሪቷ ከተኛችበት ሊቀሰቅሷት፣ ካጎነበሰችበት ሊያቀኗት፣ ከተበታተነችበት ሊሰበስቧት፣ ሥልጣኔዋን ሊመልሱላት፣ ተስፋዋን ሊሰጧት፣ ዳግማዊ የብልጽግናና የሥልጣኔ ትንሳኤዋን ሊያውጁ በሥልጣን ሳይሆን በሥራ፣ ሀገር ሊያገለግሉ የጠየመ ታሪኳን ለማደስ፣ በአዲስ ተስፋ፣ በአዲስ ፍቅር ሕዝብን ደምሮ አንድ ሀገርና ትልቅ ኃይል ያላት ኃያል አገር የሚፈጥሩ ኤሊአም ናቸው።
በንጽሕና፣ በፍቅርና በታማኝነት የሚከወን ነገር ተከታይ ያፈራል። መልካም ዜጋን ይፈጥራል። አስተዋይ ሕዝብ ይሠራል። በዕውቀትና በመረጃ ብቻ ሕዝብና ሀገር አይገነባም። በሰላም፣ በፍቅርና በቅንነትም መዋጀት ግድ ይላል። ለብዙ ጊዜያት አርአያ የሚሆነን ያጣነው የፍቅር ባንዲራ፣ የሰላም ዝማሬ፣ የዕድገት መም፣ የሥልጣኔን ፋና…. ከቅን ልብ ነቅቶ የሚያጎናጽፉንና የሚያመላክቱን በማጣት ነው። ዘመናትን በፈጀው ልማት ችግር አልተፈታም። እውነተኛ ይቅርታ አልመጣም። በጎጥ በስደት፣ በጠላትነት የተፈረጁትን በክብ ጠረጴዛ ክብ ልብ አስፈጥሮ ፍጹም የፍቅር ጽዋን አላስጎነጨም። ለዕድገትና ለብልጽግና በፍቅርና በጋራ መኖር ኪሳራ የሌለው ልዩ ትርፍ ነው።
የራስ በራስ ጥላቻና መለያየት ውጤቱ ቀላል አይደለም። ከድንበር ባሻገር ያለ ጠላት ልኩን፣ ጊዜውን፣ ጉዳትና ጥቅሙ ይታወቃል። ቶሎም መፍትሔ ይሰጥበታል። የራስ በራስ ጠላትነትና መጠላላት ግን ትርፍና አሸናፊነት የሌለው ዝቅጠት ነው። የውስጥ መነቋቆር እንደተዳፈነ ረመጥ ነው። ለዐይን ጎልቶ ሳይታይ ሲቀር የሌለ ይመስላል እንጂ ውስጥ ውስጡን ትውልድ ይፈጃል። ጠፍቶ አይቀርም፣ በትንሹም በትልቁም ትንፋሽ ይቀጣጠላል። ሲነድ አገር ይፈጃል። ደግሞ በረደ፣ ጠፋ ሲሉት በጥቂት ጭረት ከአንዱ ጫፍ ብቅ ይላል። አንዳንዴም ጭካኔው ለጠላት ከተሰበቀው ጦር ይብሳል። በሁለት ወገን እንደተሳለ ሰይፍ ፈጥኖ መትሮ ይፈጃል።
በመልካም ሀገር ገንቢዎች ጥሩ ታሪክ ሰርቶ መልካም ስም ማትረፍ ሸጋ ነው። ከየትኛውም ዜጋ በላይ መማር፣ ማሰብ፣ ትልቅ ደረጃ መድረስ ውጤቱ መሆን የአለበት በተማሩበት የሙያ መስክ፣ በተቆናጠጡት ሥልጣን ጉልበትን፣ ጊዜን፣ ዕውቀትን፣ ክህሎትንና የተፈጥሮ ሀብትን በማስተባበር ዳር ቆሞ ከተመልካችነትና ቅንብብ ካለ ጎሰኝነት ተወጥቶ ለታሪካዊቷና ታላቅ ሀገር አንዲት ጡብ ለማበርከት መጣር ከምንም የበለጠ ታላቅነት ነው።
ከኤሊአም የአደገችና የበለጸገች ሀገር ለመገንባት አዲስና ልዩ የጋራ ርዕዮት በማዘጋጀት ትልቋን ኢትዮጵያ ዳግም ትንሳኤዋን ትመልሱ ዘንድ የሀገሪቷ ዕጣ ፈንታ በእጃችሁ ነው። ሀገር በጥቂት ንጹሓንና አገር ወዳድ አዋቂዎች ልትገነባ ትችላለች። ጋሽ ስዩም ተፈራ እንዳሉት ዓለም በሥልጣኔዋ እዚህ የደረሰችው ምክንያት ያላቸው ሰዎች ስለተፈጠሩ ነው። ከኤሊአም በላይ በጥሩ ምክንያትና ዓላማ ማን ይኑር ማን አገር ይፍጠር በተለይ ዛሬ ሀገር ለመለወጥ ከውስጥም ከውጭም ያላችሁ ኢትዮጵያውያን አንድ አድርጎ ለማድመቅና የችግሯን ሰንኮፍ መንግሎ ለመጣል ሰላምና ዲሞክራሲ ዕድገትና ብልጽግናን ለማጎናጸፍ፣ አገር ለማቅናት ጥሩ ምክንያት ያላችሁ ሰዎች ለአገር ዘብ መቆም ይገባችኋል።
መኩሪያ አለማየሁ
አዲስ ዘመን ሰኔ 3 /2014