ድሮ ድሮ ሕብረተሰቡ አካል ጉዳተኛን የሚያየውና የሚያስበው መሥራት እንደማይችል። ጤናማ እንዳልሆነ። እንደ ተመጽዋች። ብሎም መንም አይነት ማህበራዊም ሆነ ኢኮኖሚያዊ እንዲሁም ፖለቲካዊ አበርክቶ እንደሌለው አድርጎ ነበር። በዚህ አስተሳሰብም ብዙ አካል ጉዳተኞች ከመገለል ጀምሮ ለተለያዩ ስነ ልቦናዊ ጉዳቶች ሲዳርጋቸው ቆይቷል። ከትምህርት። ከስራ። ከእኩል ተጠቃሚነትና ተሳታፊነት ተገልለው መቆየታቸው ደግሞ ዛሬ ላይ እንደ አገር ያላቸው ተሳትፎ ውስን አንዲሆን አስገድዷል።
ሆኖም ጥቂት የማይባል ቁጥር ያላቸው አካል ጉዳተኞች ይህንን ተጽዕኖ ሰብረው በመውጣታቸው ከፍ ያለ ደረጃ ላይ የደረሱ ሲሆን ሌሎችም አንደነሱ ጠንክረውና የህብረተሰቡን ኋላ ቀር አመለካካት አሸንፈው አንዲወጡ ምከንያት ለመሆን ችለዋል። በዚህም ምክንያት ደግሞ ከጊዜ ወደጊዜ የህብረተሰቡ አስተሳሰብ እየተለወጠ አይችሉም ምንም ጥቅም የላቸውም ከሚለው ወጥቶ ለካ መስራት መማር መምራት ይችላሉ እደል ይሰጣቸው እስከማለት የደረሰ ለውጥ ላይ ተደርሷል። እነሱም በየፊናቸው ጥረት በማድረጋቸው ይሄን ቀላል የማይባል ተፅዕኖ የሚያሳድር አስተሳሰብ አልፈው ትላልቅ ደረጃ ላይ መድረስ ችለዋል።
ወጣት ማርታ ደጀኔ እና ወጣት ሽታዬ አስታወስ የአካል ጉዳታቸውን ይዘው የህብረተሰቡን ጎታች አመለካከት ተፋልመው የራሳቸውን ጥተረት አክለው ስኬት የሚባለው ደረጃ ላይ የደረሱ አካል ጉዳተኞች ናቸው።
ወጣቶቹ አሁንም ሕብረተሰቡ ለአካል ጉዳተኞች ያለው የተዛባ አመለካከት ለውጥ በሚያመጣበት ሁኔታ ላይ መሥራት ይገባል ባይ ናቸው። ምክንያቱ ደግሞ ዛሬም በዚህ ዘመን የአካል ጉዳተኞችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት የሚገድቡ አመለካከቶች ስለሚስተዋሉ ብለዋል።
እነሱ እንደምሳሌ ያነሱትም አካል ጉዳተኞች በዲጂታል ሚዲያው ላይ በባለቤትነት እየተሳተፉ አለመሆኑን ነው።ጋዜጠኝነት ዋንኛ አድሏዊ አሰራርንን መዋጊያ መሣርያ ቢሆንም በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ውስጥ የሚሰሩ ሴቶች በተለይም አካል ጉዳተኞች አሁንም የአድሏዊ አመለካከትና አሰራሮች ሰለባ የሚሆኑበት ሁኔታ ይታያል ይላሉ።በሚዲያው ላይ የሚገለፁበት ቃላትና ዓረፍተ ነገር በራሱ ችግር እንዳለበትም ነው ወጣቶቹ የሚናገሩት። አካል ጉዳተኞችን በሀብረተሰቡ አረዳድ ጤነኛ ብለው ከሚጠሯቸው ሰዎች ጋር እያነጻጸሩ የሚያበረታቱበት አገላለፅም ቅስም የሚሰብርና ሞራል የሚነካ መሆኑን ይናገራሉ።
ሕብረተሰቡ አካል ጉዳተኛን እንደ ተመጽዋች ማየቱን ከማለዳው 11 ሰዓት ቀዝቃዛ አስፋልት ላይ ቁጭ ብለው የሚለምኑ እናት ከለመኑት ውስጥ 50 ሣንቲሙን ለእሷ የመፀወቷት መሆኑን በማስታወስ የምትናገረው ሽታዬ ይሄን ዓይነቱን አመለካከት አልፋ አሁን ለደረሰችበት ደረጃ ለመድረስ መብቃቷን ትገልፃለች። የመጀመርያ ዲግሪዋን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በቋንቋና ስነ ጽሑፍ ሁለተኛ ዲግሪዋንም በዚሁ ዩኒቨርስቲ በስርዓተ ጾታ ጥናት ላይ መሥራት የቻለችው ወጣት ሽታዬ አሁን በአፍሪካን ዲሴብሊቲ ፎረም ውስጥ አድቮካሲና ኮሚኒኬሽን ዳይሬክተር ሆና እየሰራች ትገኛለች።
ይህ በአፍሪካ አህጉር የ 44 አገራት ፌዴሬሽኖችን አቅፎ የያዘ ተቋም ውስጥ መስራት ለእሷ ቀላል የሚባል ስኬት አለመሆኑን ገልጻ ሆኖም ሁሉም ነገር አልጋ በአልጋ ሆኖላት እዚህ አለመድረሷንም ትናገራለች። “የራስን ጥረትና ሕብረተሰቡ በአካል ጉዳተኞች ላይ ያለውን ጥሩ ያለሆነ አመለካከት ለውጥ የሚጠይቅ ነው። እዚህ ቦታ መሥራትና ተምሬ ሁለተኛ ዲግሪ መያዜ ትልቅ ስኬት አድርጎ መውሰድ ይቻላል” ትላለች።
ወጣት ሽታዬ እንደምትለው በትምህርት ቤትም ሆና የሀብረተሰቡ አመለካከት የሚያሳድረው ተፅዕኖ ቀላል አለመሆኑንና ከመገለል ጀምሮ ብዙ ችግሮች እንደገጠሟት ትናገራለች ። ሆኖም ያሰበችበት ለመድረስ የቻለችው ራሷ ባደረገችው ጥረት ቀስ በቀስም ሕብረተሰቡ በአካል ጉዳተኞች ላይ ያለው አመለካከት እየተሻሻለ በመምጣቱ ነው።
ለምሳሌ አካል ጉዳተኛ እንደማይሰራ እና እንደተመጽዋች የመቁጠር አስተሳሰቡ ዛሬ ዛሬ እየተቀየረ ነው። በሕብረተሰቡ ዘንድ አሁን ላይ ከበፊቱ ጋር ሲነፃፀር እንዲህ ዓይነቱ ሁኔታ እየተቀረፈ መጥቷል ።አንደውም ስለ አካል ጉዳተኛው ችግር ያገባኛል ወደ ማለት ደረጃ ደርሷል። በየመድረኩ ሲያቀርብ የሚታየው ሀሳብ ጭራሽ ባለቤቱ አካል ጉዳተኛ ያላየውና መንግስት ትኩረት አድርጎ ሊሳራበት የሚገባውን ነው።
ጋዜጠኛ ማርታ ደጀኔም የአመለካከቱ ሰለባ ነበረች። ‹‹እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ አካል ጉዳተኛ መገለል ደርሶብኛል›› አካል ጉዳት የደረሰባት የሁለት ዓመት ህፃን ልጅ እያለች እንደነበረም ታስታውሳለች። አካል ጉዳቱ ሳይሆን ከዛ በኋላ የሚመጡት አመለካከቶች ጎድተዋት እንዳለፉም ትናገራለች። ‹‹የሕብረተሰቡ አመለካከት የሚፈጠራቸው ነገሮች አካል ጉዳተኞችን ትንሽም ቢሆን ወደኋላ ሳብ ማድረጋቸው አይቀርም›› በሚል ትንሽ አርፍተ ነገር ብትገልፀውም የደረሰባት ብዙ ነበር። መገለሉ ለተወሰነ ጊዜም ቢሆን ከትምህርት ገበታ ሊያርቃት መሞከሩን ገልጻ በተመሳሳይ ከሥራ በተለይም ከምትወደው የጋዜጠኝነት ሙያም ሊያርቃትም ሞክሮ ነበር ። እያንዳንዱ ሰው ላይ ነገ ምን ሊከሰት እንደሚችል አይታወቅም። የተለያዩ ጉዳተኞች በተለይም መገለል በአካል ጉዳተኞች ላይ ሲደርስ የሚታየው እንደዚህ ተብሎ ታስቦ የሚሰራ ሥራ ስለማይኖር ነው። በመሆኑም ከዚህ እሳቤ ጋር ተያይዞ አካል ጉዳት በማንኛውም ሰዓት ሊከሰት የሚችል ነው ብሎ እንደ አገር መሥራቱ እንደሚያስፈልግ ትገልጻለች ።
ዛሬ ለአካል ጉዳተኛ የምንሰራውና የምናመቻቸው ቀና ጎዳና ነገ ለእኛም ይጠቅመናል በሚል ቅኝት ቢታሰብ ጥሩ መሆኑን ገልጻ እሷ በግሏ ባደረገችው ብርቱ ጥረት ቸግሩን አልፋ ትምህርቷን ተምራ የመጀመርያ ዲግሪዋን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በቋንቋና ስነ ጽሑፍ ይዛለች። ቀደም ሲል በተለያዩ ጋዜጦችና መጽሔቶች፣ በሬዴዮ፣ በቴሌቪዥን በመሥራት ከአስር ዓመት በላይ በማገልገል የራሷን አስተዋጾ ስታበረክት ቆይታለች።
ማርታ በአካል ጉዳተኞች ላይ የሚያተኩር ጋዜጣም ታሳትም እንደነበር ትናገራለች። ከኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን የአየር ሰዓት በመግዛት በአካል ጉዳተኞች ላይ ትኩረት ያደረገ የቴሌቭዥን ፕሮግራም ታዘጋጅም ነበር። አሁን ደግሞ ከሴት አካል ጉዳተኞች ጤና እና ስነ ተዋልዶ ጋር በተያያዘ የራሷን በጎ አድራጎት ድርጅት አቋቁማ ድርጅቱን በሥራ አስኪያጅነት እየመራች ትገኛለች ።
በተጨማሪም ከ10 ዓመት በላይ አባል ሆና በቆየችበት በኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ሴቶች ማህበር በቅርቡ በተደረገ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ የሥራ አስፈፃሚ ቦርድ አባላት መካከል አንዷ ሆናም መመረጥ ችላለች። ቀደም ባሉት ዓመታት ሕብረተሰቡ ለአካል ጉዳተኞች የነበረው አመለካከት ዛሬ ላይ በእጅጉ ተሻሽሏል የምትለው ማርታ መመረጧ በራሱ አንዱ መገለጫ እንደሆነም ትናገራለች ። ረጅሙን የሥራ ጊዜዋን በጋዜጠኝነት ሙያ ያሳለፈችው ማርታ ወደ ማህበሩ የአካል ጉዳተኛን የሕብረተሰብ ክፍል ወክላ መምጣቱ በሙያው በአካል ጉዳተኞች ላይ የሚደርሱ ችግሮችን በመፍታት ተሳታፊና ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማስቻል ጥሩ አጋጣሚ እንደሚፈጥርላትም ታወሳለች።
በአገራችን እስከ 20 ሚሊዮን የሚደርሱ የአካል ጉዳተኞች መኖራቸውን የጠቆመው የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ነው። በዚህም ለአካል ጉዳተኞች የሚሰጠው ግምት አሁንም የተዛባ ከመሆኑ አንጻር አካል ጉዳተኞች በራሳቸው ከሚያደርጉት ጥረት ባሻገር የሕብረተሰቡ እገዛና ያለው የተዛባ አመለካከት መስተካከል ይኖርበታል። አመለካከት ለውጥ ማምጣት ላይም ትኩረት ተሰጥቶ ሊሰራ ይገባል።
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን ሰኔ 2 ቀን 2014 ዓ.ም