ፋሪድ ዘካሪያ፣”The Future of Freedom” በተሰኘው ማለፊያ መጽሐፉ ፤ “በ1980ዎቹ ስለ ቴክኖሎጂና መረጃ ዝግጁና ተደራሽ መሆን (ዴሞክራታይዜሽን)በተደጋጋሚ አንብበናል። ክስተቱም በአንጻራዊነት እንግዳና አዲስ ነበር። ከዚህ በፊት የነበረው ቴክኖሎጂ ግን ማዕከላዊነትንና ስልጣንን የሚያጠናክርና የሚያደላድል ነበር ። በ1920ዎቹ የፈነዳው የመጀመሪያው የመረጃ አብዮት ማለትም ሬዲዮ ፣ ቴሌቪዥን ፣ ፊልምና ድምጽ ማጉያ እንደተባለው ማዕከላዊነትን የማጠናከሪያ መሳሪያ ነበር ። እነዚህን የመገናኛ ዘዴዎች የተቆጣጠረ ግለሰብ ወይም ቡድን ሕዝቡን በቀላሉ ይደርሳል ። ለዚህ ነው በዚያ ዘመን መፈንቅለ መንግስት ሲደረግ ተሯሩጦ የሬዲዮና የቴሌቪዥን ጣቢያን መቆጣጠር የተለመደ የነበረው ።
ህወሀት/ኢህአዴግ አዲስ አበባን እንደተቆጣጠረ የተሯሯጠው የኢትዮጵያ ሬዲዮንና ቴሌቪዥንን ለመቆጣጠር እንደነበር ያስታውሷል ። ዳሩ ግን የዛሬው የመረጃ አብዮት በሺህዎች የሚቆጠሩ የዜና ማሰራጫዎችን ቀፍቅፏል ። የእጅ ስልክ ያለውን ዜጋ ሁሉ መረጃ አቀባይና ተቀባይ አድርጎታል። ለዜና የግድ ኢቲቪን ወይም የኢትዮጵያ ሬዲዮን አልያም ቪኦኤን ደጅ አይጠናም ። በመሆኑም መቆጣጠርን አዳጋች ሲያደርገው መቃወምን ደግሞ በተቃራኒው ቀላል አድርጎታል ። በይነመረብ ይህን ሒደት ፍጹም ወደተለየ ምዕራፍ አሸጋግሮታል ። ለዚህ ነው ቶማስ ፍሬድማን፣’ ሁሉም ተገናኝቷል ፤ የተገናኘውን ሁሉ መቆጣጠርን ግን አዳጋች ነው።’ያለው”
ዛሬ በሀገራችን እንደ ድረ ገጽ ፣ ፌስቡክ ፣ ቲዊተር፣ ቴሌግራም ፣ ዩቲውብ ያሉ ማህበራዊ ሚዲያዎች እንደ አሸን ቢፈሉም መቆጣጠር ግን አዳጋች እየሆነ ነው። የማህበራዊ ሚዲያው (የፕላትፎርሙ)ተፈጥሮና ባህሪ ስድ ለቋቸዋል ። ጥላቻንና ልዩነትን የሚጎነቁሉ ተበራክተዋል ። ሀሰተኛ ፣ የተዛቡና የፈጠራ ትርክት መረጃዎች መልካዓውንና አየሩን በመቆጣጠራቸው ሕዝብ እየተወናበደና እየተደናገረ ይገኛል ። ሀገራዊ አንድነትና ኢትዮጵያዊነት እየተሸረሸረ ፤ ግጭትና ቀውስ እየተቀሰቀሰና እየተለፈፈ እየሰለጠነ ነው ።
ጦር ከፈታው ወሬ የፈታው እንዲሉ ፤ ዲጂታል ወያኔ፣ ጦፈኞቹ ፣ ጥቅም እስካገኙ ድረስ ሕዝብ ቢጫረስ፣ ሀገር ቢፈርስ ደንታ የሌላቸው ዩቲውበሮች ሀገራችንን ለዘመናት ያቆሙ ምሰሶዎችን እየነቀነቁ ፣ እኩያንንና እባያንን እያደነቁ በህልውናችን ላይ የማያበራ አደጋ እየደቀኑ ይገኛሉ ። ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት ሀገርን የመበተን ፣ ሕዝብን የማጫረስ መብት እስከመሆን ተደርሷል።
ሕገ መንግስቱም ሆነ የመገናኛ ብዙኃን አዋጁ የሰጣቸውን መብት እየጨለጡ ፤ ግዴታቸውን ግን ሆን ብለው ዘንግተዋል ። አስታዋሽ ያስፈልጋቸዋል ። ዳተኛውና አባባዩ መንግስት ሕጋዊ እርምጃ መውሰድ ሲጀምር ደግሞ እዚህም እዚያም ጩኸቱ እየበረከተ ነው ። ሌት ተቀን የጦርነትን ፣ የጥላቻንና የልዩነት ድቤ የሚደልቁ አብዛኛዎቹ ዩቲውበሮች የሞራልም ሆነ የሕግ ግዴታቸውን ወደ ጎን ያሉ አጉራ ዘለል መሆናቸውን ዘንግተው በሕግ አምላክ እያሉ ነው። ምርጫቸው እንዳስጠየቃቸው የተገነዘቡ አይመስልም።
ጣታቸውን በመንግስት ላይ ከመቀሰራቸው በፊት ራሳቸውን ሊመለከቱ ይገባል። ይሄን ስል መንግስት ፍጹም ነው ማለቴ አይደለም ። በተለይ ማህበራዊ ሚዲያው የጉዳቱን ያህል በርካታ ሲሳይ ይዞልን የመጣ ቢሆንም ላልተገባ አላማና በአቋራጭ ጥቅም ማባረሪያ አድርገነዋል። ዊኒስተን ቸርችል ተጠያቂነት የስኬት ንጉስ እንዳለው ፤ ያለ ግዴታ መብቱን እየጨለጠ ያለው ዩቲዊበር ተጠያቂነት እንዳለበት ሊገባው ይገባል ።
ባለፈው ሳምንት የፌደራል ፖሊስን ጠቅሶ የኢትዮጵያ ፕሬስ ኤጀንሲ እንደዘገበው ፤ ምንም ዓይነት የብሮድካስት ፍቃድ ሳይኖራቸው የህዝቡን ሰላምና ደህንነት የሚያናጉ ግጭት ቀስቃሽ መረጃ የሚያሰራጩና በሀሰተኛ ፕሮፓጋንዳ መንግስትና ህዝብን ለመለያየት የሚሰሩ 111 ህገ-ወጥ የበይነመረብ መገናኛ ብዙሃን ሲኖሩ፤ በመገናኛ ብዙሃን አዋጅ ቁጥር 1238/2013 መሰረት ምንም ዓይነት የብሮድካስት ፍቃድ ሳይኖራቸው የህዝቡን ሰላምና ደህንነት የሚያናጉ በብሄር እና በሀይማኖት ጉዳዮች ላይ ግጭት ቀስቃሽ መረጃ የሚያሰራጩ እንዲሁም በሀሰተኛ ፕሮፓጋንዳ መንግስትና ህዝብን ለመለያየት ሌት ተቀን የሚሰሩ ናቸው ።
ከዚህ ውስጥ በጣም ወጣ ያሉ ብሄርን ከብሄር ሃይማኖትን ከሃይማኖት በማጋጨት የሀገርን ሰላምና ደህንነት ለማደፍረስ የሚንቀሳቀሱትን ለይቶ 10 ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ሥር አውሎ ምርመራ እያጣራባቸው ይገኛል ። እነዚህ ግለሰቦች የተለያዩ ግጭት ቀስቃሽ አጀንዳዎችን በመቅረጽ የሀገራችንን ሰላምና ደህንነት እንዳይረጋጋ የጥላቻ ንግግር በማሰራጨት በብሄር እና በሀይማኖት መካከል ጥርጣሬ እንዲፈጠር ሲያደርጉ የቆዩ ናቸው ።
የፌደራል ፖሊስ ጉዳዩን ለማጣራት ባደረገው ክትትል ግለሰቦቹ ምንም አይነት ህጋዊ ፍቃድ የሌላቸውና በመገናኛ ብዙሃን አዋጅ መሰረት ያልተመዘገቡ መሆናቸውን ከኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ባሰባሰበው መረጃ ማረጋገጥ ችሏል። ግለሰቦቹ የሚዲያ ተከታዮቻቸውን በመጠቀም ሐሰተኛና ግጭት ቀስቃሽ መረጃዎችን የሚያሰራጩት በክፍያ እንደሆነም በምርመራ ደርሶበታል። በየትኛውም ሚዲያ ተጠቅመው መረጃን ለህዝብ ተደራሽ የሚያደርጉ ግለሰቦች የሀገሪቱን ህግና ሥርዓት አክብረው መንቀሳቀስ እና ህጋዊ መስመር በመከተል በተጠያቂነት መንፈስ መስራት ይኖርባቸዋል ።
ፖሊስም ህግን አክብረው በማይሰሩት ላይ የጀመረውን ምርመራ አጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን በዚህ አጋጣሚ ማሳሰብ ይወዳል ። በመጨረሻም ህብረተሰቡ ያገኘውን መረጃ ሁሉ ከመጠቀም በመቆጠብ በጥንቃቄ መርምሮ ማየትና ማገናዘብ እንዳለበት እያሳሰበ በህገ-ወጥ መንገድ በበይነመረብ መገናኛ ብዙሃን አማካኝነት አጀንዳ ቀርፀው በሀይማኖት፣ በብሄር ህብረተሰቡን ለማጋጨት የሚሰሩ አካላትን በማጋለጥና ለህግ አሳልፎ በመስጠት ሀገራዊ ግዴታውን መወጣት ይኖርበታል ሲል የፌዴራል ፖሊስ ያሳስባል ። ዛሬ ሩዋንዳውያንና ኬንያውያን ማህበራዊ ሚዲያን ለበጎ ዓላማ በማዋል ራሳቸውንና ሀገራቸውን በመጥቀም ለአህጉሩ በአርዓያነት እየተጠቀሱ ሲሆን እኛ ግን በተቃራኒው እየሄድን ነው ።
ቀደም ባለ አንድ መጣጥፌ እንደገለጽሁት የኢንፎርሜሽን ኮሙኑኬሽን ቴክኖሎጂን በአግባቡ ለተጠቀመበት ደግሞ የሰው ልጅን ህይወት ቀላል ያደርጋል ። ማህበራዊ ተራክቦንና ገብያን ያሳልጣል። ሎጂስቲክስን ያቀላጥፋል። የስራ እድል ይፈጥራል። ኢኮኖሚን ያስመነድጋል። ሆኖም ቴክኖሎጂውን አበክሮ በጥበብና በማስተዋል ለበጎ አላማ መጠቀምን ግድ ይላል ብዬ ነበር ። ዛሬ በአለማችን ቀዳሚ ከሆኑ 20 የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ኩባንያዎች 15ቱ በአሜሪካ ይገኛሉ። የአሜሪካው ሲሊካን ቫሊ የአለማችን ባለ ምጡቅ አእምሮ የፈጠራ ሰዎችና ባለሀብቶች ሁል ጊዜ የሚቃጠሩና የሚገናኙበት ነው ።
በሲሊካን ቫሊ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ዘርፍ በየ6 ደቂቃው አዲስ ነገር ይፈጠራል ። በሰዓት ሲሰላ10 ፣ በቀን ሲመታ 240 ፣ በአመት 87ሺህ 600 አዳዲስ ፈጠራ ማለት ነው ። ( እዚህ ላይ ለአፍታ ሀገራችን የምትገኝበትን ተጨባጭ ሁኔታ በምናብ አብራችሁኝ አንሰላስሉና በመንፈሳዊ ቅናት እንድትጨረጨሩ በአክብሮት እጋብዛለሁ …!? ) ታዲያ … ! አሜሪካ የቴክኖሎጂ ፈጠራ ምድረ ገነት ብትባል ይበዛባታል !? እረ ! በጭራሽ ።
በአለማችን የመጀመሪያው የትሪሊዮን ዶላር ጥሪት አፕል መሆኑንም ይገነዘቧል ።
ሆኖም አሜሪካ እነዚህ ኩባንያዎቿ የገመና* መብት the right of privacy እና የገበያ ውድድርን እንዲያከብሩም እየሰራች ነው ። ሴናተር ኤልዛቤት ዋረን ፌስ ቡክ ገበያውን በበላይነት ስለተቆጣጠረ ወደ ትናንሽ ካምፓኒዎች መከፋፈል አለበት በማለት የምርጫ መቀስቀሻ እስከማድረግ ደርሳ ነበር ።
የአውሮፓ ሕብረትም እጁን አጣጥፎ አልተቀመጠም። በ50ዎቹ IBM ፣ በ80ዎቹ Micro Soft በምዕራባውያን ገብያን በበላይነት በመቆጣጠር monopoly እንደከሰሳቸው ሁሉ ፤ ባሳለፈው ጉግልን የማስታወቂያ ነፃ የገበያ ውድድርን በማስተጓጎል የአውሮፓ ህብረት የ1 ነጥብ 7 ቢሊዮን ዶላር ቅጣት አከናንቦታል ። ሕብረቱ በዚህ አያበቃም። በቀጣይ የቅጅ መብትን Copy Right ፣ ዜጎች የግል መረጃቸው ባለቤትና የጥቅም ተጋሪ እንዲሆኑም እየሰራ ነው ። ስፓቲፍ Spotify በአፕል Apple ላይ የመሰረተው የቅጅ መብት ክስን እዚህ ላይ ማስታወሱ ተገቢ ነው ።
የማህበራዊ ሚዲያው ሌላው ገጽታው ደግሞ፤ በመላው አለም በሀሰተኛ ፣ በተሳሳተ መረጃ ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን በማናጋት ክፉኛ እየተከሰሰና እየተብጠለጠለ ይገኛል ። እዚህ ላይ ማህበራዊ ሚዲያው አይደለም እንደኛ ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት እና ለነፃና ገለልተኛ መደበኛ ሚዲያ ግንባታ አርፋጅ ለሆኑ ሀገራት ለምዕራባውያንም አደጋ መደቀኑን ያሳያል ። ዶናልድ ትራምፕንና ሒላሪ ክሊንተንን ባፋጠጠው ፣ ባወዛገበው የ2016ቱ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ፣ በእንግሊዝ ከሕብረቱ የመነጠል BREXITE ሕዝበ ውሳኔ ፣ በፈረንሳይ፣ በጀርመን፣ በጣሊያን፣ በዩክሬን ፣ …፤ ምርጫ በማህበራዊ ሚዲያው ይራገቡ የነበሩ የደባ ፣ የሴራ ፣ የጥላቻ እና ሀሰተኛ መረጃዎች የዴሞክራሲያዊ ተቋማት ነፃና ገለልተኛ መሆንና አጠቃላይ ስርዓቱን አደጋ ላይ ጥለውት እንደነበር ያጤኑአል ።
በEBS ቴሌቪዥን “ Teck Talk “ አዘጋጅነት የምናውቀው ሰለሞን ሙሉጌታ ፤ “ ግርምተ ሳይቴክ “ በሚል መፅሐፉ ገፅ _ 154 ላይ ፤ “ እንደፌስቡክና ትዊተር ባሉ የማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ የሚናፈሱ በርካታ የሀሰት ወሬዎች በርካቶችን ግራ ከማጋባት አልፈው የአንድ ሀገር ማህበራዊና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ላይም አሉታዊ ተፅዕኖ ያሳድራሉ ። …” ሲል ተፅዕኖአቸው ከፍ ያለ መሆኑን ያረጋግጣል ። ባለፉት ሁለትና ሶስት አመታት ማህበራዊና መደበኛ ሚዲያው የሀገራችንን ገጽታ ለማጠልሸት የሄደበትን ርቀት ያስታውሷል ።
ሆኖሞ በተለይ ፌስ ቡክ የሀሰት ወሬ ስርጭትን ለመከላከል “ fake news story “ ብሎ ለመፈረጅ እንዲሁም ፤ የዜናዎችን እውነተኝነት መጣራት ሲያስፈልግ ደግሞ “ disputed “ የሚል መለያ የሚያስቀምጥ አሰራርን ስራ ላይ ቢያውልም የሚፈለገውን ያህል ውጤታማ አለመሆኑን በሀገራችንም በመላው አለምም እያስተዋልን ነው ። ለዚህ ነው ማህበራዊ ሚዲያው ያለተጠያቂነት፤ ዛሬ በአለማችን ቀዳሚ የሆኑ አምስት የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ማለትም የአልፋቤት ፣ አማዞን፣ አፕል ፣ ፌስ ቡክና ማይክሮሶፍት ሲሶ ( 25 በመቶ ) ገበያ በሆነው አውሮፓም ሆነ አሜሪካ ፣ እስያ ፣ ላቲን አሜሪካ ፣ አፍሪካ ይህን አደጋ ለመከላከል እየሰሩ ሕግ እያረቀቁ ባሉበት መንግስት ሕግ ይከበር በማለቱ አቧራ ሊነሳ አይገባም ።
እንደ ኮሎምቢያ ጆርናሊዝም ሪቪው መፅሔት የቅርብ ጊዜ ጥናት ከሆነ ከአሜሪካውያን 60 በመቶው ዜና የሚያገኙት ከፌስቡክ ወይም ከቲዊተር ነው ። ከ200 አመታት በላይ የዳበረ ፣ የጎለበተ ፣ የደረጀ ዴሞክራሲና ልምድ ያለው መደበኛ ሚዲያ ባለበት ሀገር ከ10 ሰው ስድስቱ ዜና የሚያገኙት ከማህበራዊ ሚዲያ ከሆነ ፤ የዳበረ ነፃና ገለልተኛ የሆነ መደበኛ ሚዲያ በሌላት ሀገራችንማ ቁጥሩ ወደ 80 ፣ 90 በመቶ ከፍ ሊል ይችላል።
ሎሬት አማኑኤል አብዲሳ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የጋዜጠኝነትና ተግባቦት ረዳት ፕሮፌሰር ቀደም ባለ ጊዜ ‘ በኢትዮጲስ ‘ ጋዜጣ ላይ “ ነፃነት ያለ ኃላፊነት ጥፋት ነው “ በሚል ያስነበቡን ፁሑፍ ይሄን ጥሬ ሀቅ የሚያረጋግጥ ነው ። “…በሀገራችን በማህበራዊ ሚዲያዎች የሚሰራጩ መረጃዎች ሁሉ ትክክልና እውነተኛ እንደሆኑ አድርጎ የሚቀበለው ሰው ቁጥር ብዙ ነው ። ይህ አጠቃላይ ከሀገሪቱ ዕድገት ጋር የተያያዘ ነው ። …” ፤ ቀደም ባሉት አመታት በተለይ በመንግስት መደበኛ መገናኛ ብዙኃን አመኔታ መታጣቱ አብዛኛው ዜጋ ማህበራዊ ሚዲያን በመረጃ ምንጭነት እንዲመርጥ መግፋት ሆኖታል ።
ማህበራዊ ሚዲያው ህጸጽ ስመለስ፤የዘረኝነት፣ የጥላቻ እንዲሁም ሀሰተኛ መረጃዎች በማህበራዊ ሚዲያው በፍጥነት በአጭር ጊዜ ለሕዝብ ይደርሳሉ ። ከላይ የጠቀስሁት The Economist መፅሔት በእማኝነት የጠቀሳቸው ጁሊያን ዮርክን የተባሉ የሚዲያ ጎምቱ ተመራማሪ ፤ “…ከእንግዲህ መደበኛው ሚዲያ በሚገዛበት ሕግ ማህበራዊ ሚዲያውን ማስተናገድ አይቻልም ::” ብለዋል ፤ ለነገሩ ጉግል ፣ አፕል ሜት እና ፌስቡክ እንደ አልቃይዳ ፣ ታሊባንና አይሲስ ያሉ አሸባሪዎች ማህበራዊ ሚዲያዎችን በመጠቀም የፕሮፓጋንዳ ፣ የጥላቻ መልዕክት እንዳያስተላልፉ ፤ አባል ፣ ተከታይ እንዳያፈሩ ለመከላከል ከመንግስታት ጋር እየሰሩ ናቸው ።
ከሶስት አመታት በፊት አንድ የአውስትራሊያ ዜግነት ያለው አክራሪ በኒውዚላንድ ክራይስት ቸርች ከተማ በሚገኙ ሁለት መስጊዶች ላይ ተኩስ ከፍቶ 50 ንፁሀን ገድሎ በርካቶችን ሲያቆስል በፌስ ቡክ ቀጥታ ይተላለፍ ስለነበር ፤ ሀገሪቱ የሽብር ጥቃቶችን የሚያበረታቱ፣ የጥላቻና ሀሰተኛ መረጃዎች በማህበራዊ ሚዲያ እንዳይሰራጩ የሚገድብ ሕግ ለማውጣት እየሰራች ሲሆን ፤ የእንግሊዙ “ ዘ ኢንዲፔንደንት “ ጋዜጣ በበኩሉ የፌስቡክ ገፁን ቀኝ አክራሪዎች እንዳይጠቀሙ ማገዱን ተዘግቧል ።
ሰሞኑንም በሀገራችን እየተወሰደ ያለው እርምጃ የተለያየ ስም ቢሰጠውም የፕሬስ ነጻነቱን ለማነቅ ሳይሆን የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ እንደሆነ አምናለሁ ። ጠንካራና ሕጋዊ የመገናኛ ብዙሀን ለመንግስት አይንና ጀሮ በመሆን ስለሚያገለግል ።
የሕግ የበላይነት በሁሉም ዘርፍ ይረጋገጥ !
/በትናንት የነፃ ሀሳብ ገጻችን የተስተናገደው “መኀልዬ መኀልዬ ዘ ኢትዮጵያ ህዝብ “የሚለውበቁምላቸው አበበ ይማም(ሞሼ ዳያን) ጽሁፍ የተጻፈው በቁምላቸው አበበ ይማም(ሞሼ ዳያን) መሆኑን እየገለጽን ለተፈጠረው ስህተት አዲስ ዘመን ይቅርታ ይጠይቃል፡፡
በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን) fenote1971@gmail.com
አዲስ ዘመን ሰኔ 2 ቀን 2014 ዓ.ም