አሸባሪው ሕ.ወ.ሓ.ት ወደ ትጥቅ ትግል ከገባ 50 ዓመታትን እያስቆጠረ ነው ። ቡድኑ የብሄር አጀንዳን ይዘው ጫካ የገቡት መሪዎቹ 27 ዓመታት ኢትዮጵያን የማስተዳደር ዕድል ቢያገኙም ዛሬም ድረስ የትግራይን ሕዝብ እርዳታ ጠባቂነት ፍፁም ሊያድኑት አልቻሉም።
በስልጣን በቆዩባቸው 27 ዓመትም ለትግራይ ህዝብ የፈየዱለት ነገር የለም። የትግራይ ሕዝብ ከ1966ቱ ዓ.ም ድርቅ ባልተለየ ሁኔታ ዛሬም በብድኑ እብሪት የተነሳ ብዙ ዋጋ እየከፈለ ነው ። በ27ቱ ዓመታት የስልጣን ዘመኑ ተጠቃሚ የሆኑት የስርአቱ ጥቂት አሽቃባጮች እና የአንድ ቤተሰብ አባላት ናቸው ።
ቡድኑ የማይጨበጥ የቅዠት ነጻነት አጎናጽፋችኋለሁ ብሎ ጦርነት ከጀመረ ሦስተኛ ትውልድ እየመጣ ቢሆንም፤ መሪዎቹ በየጊዜው በሚፈጥሯቸው ችግሮች ምክንያት ትውልዶቹ የቡድኑ መቆመሪያ ከመሆን ያለፈ የተሻለ እጣ ፈንታ አላጋጠማቸውም ።
ለትግራይ ህዝብ እንደገቡለት ቃልም ትግራይን የጦርነት አውድማ እንጂ ምድረ ገነት ማድረግ አልሆነላቸውም። ጭራሽ ዓይጥ እንዳየች ድመት ልጆቹን እያሳደዱ ለማያባራ ጦርነት በመማገድ ስጋት ሆነው ሲያባንኑት ኖሩ እንጂ። ያሉትን ነፃነትም አሁን ድረስ አላጎናፀፉትም ።
‹‹የበሉበትን ወጪት ሰባሪ›› ሆነው ከትግራይ ሕዝብ አልፈው የኢትዮጵያን ሕዝብን ጭምር ለከፋ ችግር ዳርገዋል እሁንም እየዳረጉ ነው። በህዝባዊ አመጽ ከስልጣን ከወረዱ በኋላም የትግራይን ህዝብ መሸሸጊያ በማድረግ ለስልጣናቸው የመቆመሪያ ካርድ አድርገውታል።
ዘንድሮ ህፃን ልጅ እንኳን በቤት እቤት ጨዋታ በማያደርገው በዚህ ሥራቸው ከመረረው የትግራይ ሕዝብ ጋር ተፋጥጠዋል። በነፃነት ስም ምድሩ የጦርነት አውድማ፤ ልጆቹ ጭዳ እየሆኑ ከትውልድ ትውልድ ዕድሜ ብቻ ሲቆጥር መኖሩ ሰልችቶታል። አንዳች ጠብ የሚል ነገር በሌለበት፤ ልጆቹንና ገንዘቡን እነሱ በየጊዜው ለሚያስነሱት ጦርነት ሲገብር መቆየቱም በእጅጉ አስቆጭቶታል።
የእርዳታ እህል ይግባ አይግባ በሚል እንዲሁም በገዛ ነፃነቱ ጉዳይ ጭቅጭቅ አስልችቶታል። ደግሞም አስቆጥቶታልም! ‹‹ሲያዩት ያላማረ ሲበሉት ያቅራል›› እንዲሉ መሪዎቹ ያን ያህል ዓመታት ወስደው ያልጠቀሙት ዛሬ ይጠቅሙኛል የሚል ዕምነቱ ተሟጧል።
መሪ ነን ለሚሉትና በስሙ ሲነግዱ በቆዩት ሕ.ወ.ሓ.ቶች ጠብ በማይል ቁም ነገር ጆሮውን መስጠት አልዋጥ ብሎታል። በማይጨበጥ የቅዠት ዓላማ አወጫብረው በስልጣን እርከን ላይ ለመፈናጠጥና ስልጣንን እርስትና ጉልታቸው አድርገው ለመቆየት የሚያደርጉት እንደሆነ አውቋል።
በዚህ ሁኔታ ከትግራ ሕዝብ ጋር የተፋጠጠው ሕ.ወ.ሓ.ት ዘንድሮ ቅጣ አንባሩ ጠፍቶታል። ከትግራይ ሕዝብ ጋር በመፋጠጡ የሚይዝ የሚጨብጠውን አጥቷል። መላው የኢትዮጵያ ሕዝብም ቢሆን ዛሬ ወደ 1966ቱ ዓ.ም ተመልሶ በረሃብና በቸነፈር የገረጣና የተጎዳ የትግራይ እናቶችን ፊት በፍፁም ማየት አይሻም።
በተለይ የትግራይ ተጎራባች ክልሎች የሆኑት አማራና አፋር ሕ.ወ.ሓ.ት በማያባራ ጦረኝነቱ የትግራይን ሕዝብ መክተቱ ፤ ወጣቱን የጦስ ዶሮ ማድረጉ እነሱም በየጊዜው መተንኮሳቸው ሰልችቷቸዋል።
የአማራ ክልላዊ መንግስት በዚህ ወር ያወጣው መግለጫም ይሄንኑ ነው የሚያመለክተው ። በዚሁ ጉዳይ ላይ የተለያዩ ፖቲከኞችም አስተያየት ሰጥተዋል። መንግስትም የአማራውን መግለጫ በመደገፍ መግለጫ አውጥቷል። ሁሉም መንግስታት በዚሁ ጉዳይ ላይ ምክክር እንዳደረጉና በተጠንቀቅ ላይ እንደሆኑም የገለጡበት ሁኔታ ተስተውሏል።
የትግራይ ሕዝብ ይሄን ሁሉ የመታዘብ ጊዜ አግኝቷል። አመራሮቹ አሁንም በጥፋት መስመር ላይ እንደተሰለፉ እንደሆኑም በሚገባ እያስተዋለ ይገኛል። ቢቢሲ እንደዘገበው ልጆቻቸውን የመጨረሻ ላለው የማያባራ ጦርነት ካልገበሩ ከ20 እስከ 40 ሺህ ብር የደረሰ የቅጣት ገንዘብ እንዲከፍሉ የማስፈራሪያ ማዕቀብ መጣሉም የትግራይን ሕዝብ በእጅጉ አስቆጥቶታል።
ይሄን ማስፈራሪያ የምዕራቦቹ ሚዲያዎችም በማራገብ የሕ.ወ.ሓ.ት አመራሮችን ሲወቅሱበት ሰንብተዋል። አሁን ላይ የሱዳንን በር በማስከፈት ፤ ከታሪካዊ ጠላቶቻችን ጋር ሕ.ወ.ሓ.ት (ወያኔ) ትግራይ ላይ ቁጭ ብሎ አማራና አፋርን ጨምሮ በክልል መንግስታት ዙሯዬን ተከብቤያለሁ ፤ እርዳታ መግባት ፤ አልቻለም እያለ የሚደነፋው ከሕዝቡ ጋር በመፋጠጡ መሆኑም እንኳን ለክልሎች ለሕዝቡም አልጠፋው።
በዚሁ ወር በአፋር በኩል በተከፈተው የእርዳታ ማስገቢያ ኮሪደር 64 እርዳታ የጫነ መኪና ወደ ትግራይ መግባቱን እርዳታዎች ወደ ክልሉ እየገቡ እንደሆነ ትግራይ ህዝብ ቀርቶ ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ የአደባባይ ሚስጥር ከሆነ ውሎ አድሯል።
በተጨማሪም በዚሁ ሰሞን የአለም ባንክ ትግራይን ጨምሮ በጦርነቱ ከአማራና አፋር ክልሎች ለተፈናቀሉ ዜጎች ድጋፍ የሚውል 300 ሚሊዮን ዶላር እርዳታ መስጠቱን የዚሁ እውነታ ማሳያ ነው።
የሕ.ወ.ሓ.ት አመራሮች (ሌቦችና ወንጀለኞቹ) ግን ዛሬም የመጨረሻ በሚሉት የአጥፍቶ መጥፋት ጦርነት ለመግባት እየተዘጋጁ ነው ፤የትግራይንም ወጣት ለከፋ እልቂት ለመዳረግ ሌት ተቀን እየተጉ ነው ። ይህንን እውነታ ለመቀልበስ የትግራይ ህዝብ ግንባር ቀደም ሊሆን ይገባል። ልጆቹን ከቀጣይ እልቂት ለመታደግ ቡድኑን በቃህ ሊለው ይገባል!
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን ሰኔ 1 /2014