
የኢራን መንፈሳዊ መሪ አያቶላህ አሊኻሜኒ ኢራን ዩራኒየም የማበልፀግ ተግባሯን እንደማታቆም ተናግረዋል። ኻሜኒ ሀገራቸው ከአሜሪካ ጋር እያደረገችው ባለው የኑክሌር ውይይት አሜሪካ ያቀረበችውን ዩራኒየም የማብላላት ተግባርን የማቆም ጥያቄ ውድቅ አድርገዋል።
ኻሜኒ የእስላማዊቷ ሪፐብሊክ መሥራች በነበሩት አያቶላህ ሩሆላህ ኾሜኒ የመታሰቢያ መርሐ ግብር ላይ ባደረጉት ንግግር፣ ‹‹የአሜሪካ የኑክሌር ፕሮፖዛል ከሀገራችን ራስን የመቻል እና የ‹እንችላለን› መርሕ ጋር የሚቃረን ነው። ራስን መቻልና ነፃነት ማለት የአሜሪካንና መሰሎቿን በጎ ፈቃድ ማግኘት ማለት አይደለም። የአሜሪካ ጥያቄ የእስላማዊ አብዮታችንን መርሕ ሙሉ በሙሉ የሚቃረን ነው›› ብለዋል። ዩራኒየም የማብላላት ጉዳይ ቴህራን በኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ልማት ራሷን ለመቻል ለምታደርገው ጥረት ቁልፍ ግብዓት መሆኑንም ተናግረዋል።
ቴህራን ለውሳኔዎቿ የዋሺንግተንን ፈቃድና ይሁንታ እንደማትፈልግ በአፅንዖት የተናገሩት ኻሜኒ፣ ‹‹አንዳንዶች ምክንያታዊነት ማለት ለአሜሪካ ማጎብደድ እና ለጨቋኝ ኃይሎች እጅ መስጠት ይመስላቸዋል። ነገር ግን ይህ ምክንያታዊነት አይደለም። ጣልቃ ገብተው ኢራን ኑክሌር ማበልፀግ እንዳለባት ወይም እንደሌለባት ለምን ይነግሩናል? እነሱ ሊነግሩን አይችሉም›› በማለት አሜሪካንና አጋሮቿን ወቅሰዋል።
የኢራን ፕሬዚዳንት መሱድ ፔዘሽኪያንም ሀገራቸው ኑክሌር የማብላላት ሥራዋን እንደማትተው ተናግረዋል። ‹‹ኢራንን የሚወቅሱት ኃይሎች ጅምላ ጨራሽ መሣሪያዎችን በማስፋፋት ቀጣናውን እያተራመሱት ነው›› ብለዋል። መንፈሳዊ መሪውና ፕሬዚዳንቱ ስለጉዳዩ ከመናገራቸው በፊት ኢራን በአሜሪካ የቀረበውን ኑክሌር የማበልፀግ ተግባር የመቀነስና የመተው ጥያቄ ውድቅ ለማድረግ እንደተዘጋጀች ‹ሮይተርስ› የዜና ወኪል (Reuters) ዘግቦ ነበር። ሮይተርስ ስማቸውን ያልጠቀሳቸው አንድ ዲፕሎማት፣ የአሜሪካ ሃሳብ ዋሺንግተን በዩራኒየም ማበልፀግ ጉዳይ ላይ ከያዘችው አቋም ፈቀቅ ለማለት ዝግጁ እንዳልሆነች የሚያሳይና የቴህራንን ጥቅም ከግምት ውስጥ ያላስገባ እንደሆነ ገልጸዋል።
የአሜሪካ የመካከለኛው ምስራቅ ልዩ መልዕክተኛ ስቲቭ ዊትኮፍ፣ ፕሬዚዳንት ትራምፕ የኢራንን ኑክሌር የማበልፀግ ተግባር እንደ ‹‹ቀይ መስመር›› እንደሚቆጥሩት እና ኢራን ይህን ተግባሯን እንድታቋርጥ እንደሚፈልጉ ሁለቱ ሀገራት ባደረጓቸው ውይይቶች ላይ በተደጋጋሚ ተናግረዋል።
አንድ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሪፖርት እንዳመለከተው፣ ኢራን ባለፉት ሦስት ወራት የዩራኒየም መሣሪያዎች ምርቷን በ50 በመቶ አሳድጋለች። ይህ መጠን ለኑክሌር መሣሪያዎች ምርት በቂ ባይሆንም ለኃይል ማመንጫ ተግባር ከሚያስፈልገው የዩራኒየም መጠን ግን እጅግ የበለጠ ነው። ኢራን ግን ሪፖርቱን ‹‹ፖለቲካዊ ዓላማን ያነገበና መሠረተ ቢስ ውንጀላ›› ብላ አጣጥላዋለች።
ፕሬዚዳንት ትራምፕ እስላማዊቷን ሪፐብሊክ አጥብቀው በመኮነን ይታወቃሉ። በመጀመሪያው የሥልጣን ዘመናቸው የኢኮኖሚ ማዕቀቦችን ጨምሮ በኢራን ላይ የተለያዩ ርምጃዎችን ወስደዋል። ለአብነት ያህል ሀገራትና ትልልቅ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ከኢራን ነዳጅ እንዳይገዙ አስጠንቅቀዋል፤ የኢራንን አብዮታዊ ዘብ ከአሸባሪዎች መዝገብ አስፍረውታል፤ ከባድ የጦር መሣሪያዎችን ኢራን ወደምትገኝት ቀጣና ልከው አሰማርተዋል፤ አሜሪካን እ.አ.አ በ2015 በኢራንና በስድስቱ የዓለማችን ኃያላን አገራት (አሜሪካ፣ ቻይና፣ ሩሲያ፣ ጀርመን፣ ብሪታኒያ እና ፈረንሳይ) መካከል ከተፈረመው የኢራን የኑክሌር ስምምነት (Iran Nuclear Deal) አስወጥተዋታል።
በኢራንና በስድስቱ የዓለማችን ኃያላን ሀገራት (አሜሪካ፣ ቻይና፣ ሩሲያ፣ ጀርመን፣ ብሪታኒያ እና ፈረንሳይ) መካከል የተፈረመውን የኢራን የኑክሌር ስምምነት ኢራን የኑክሌር ጦር መሣሪያ ግንባታዋን እንድታቆምና በምላሹም በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ በአውሮፓ ኅብረትና በአሜሪካ የተጣሉባት ማዕቀቦች እንዲነሱላት ይደነግጋል። ኢራን ስምምነቱን የማታከብር ከሆነም ቀደም ባሉት ጊዜያት ከተጣሉባት ማዕቀቦች የከፋ ፖለቲካዊና ምጣኔ ሀብታዊ ተፅዕኖ ያላቸው ማዕቀቦች እንደሚጣሉባት፤ ከዚያም አልፎ ጉዳዩ ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት እንደሚቀርብ በስምምነቱ ውስጥ ከተካተቱት ድንጋጌዎች መካከል ይጠቀሳል።
ከስምምነቱ መፈረም በኋላም ኢራን የስምምነቱን ድንጋጌዎች ተቀብላ አንዳንድ ርምጃዎችን ወስዳ ነበር። ከእነዚህም መካከል በናታንዝ እና ፎርዶ ጣቢያዎች የሚገኙ ግብዓቶች እንዲወገዱ መደረጉ፤ በብዙ ቶን የሚቆጠር ዩራኒየም ወደ ሩሲያ መወሰዱ እና የዓለም አቀፉ አቶሚክ ኃይል ተቆጣጣሪ ድርጅት ባለሙያዎች የኢራንን የኑክሌር መሣሪያ ግንባታ በየጣቢያዎቹ ተገኝተው መመልከታቸው ይጠቅሳሉ።
ስምምነቱ ሲፈረም አሜሪካን ሲያስተዳድሩ የነበሩት የወቅቱ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ስምምነቱ እንደትልቅ ዲፕሎማሲያዊ ድል ተቆጥሮላቸዋል። ኦባማን ተክተው ወደ ነጩ ቤት የመጡት ቢሊየነሩ ዶናልድ ትራምፕ ግን ስምምነቱን መቀበል ይቅርና ስለስምምነቱ መስማት አይፈልጉም። ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ‹‹የምንጊዜውም መጥፎው ስምምነት›› እያሉ የሚያብጠለጥሉትን ይህን ስምምነት እንደሚሰርዙት ያስታወቁት ገና በፕሬዚዳንታዊ የምርጫ ቅስቀሳቸው ወቅት ነው።
ትራምፕ ስምምነቱ ኢራንን ለተወሰኑ ጊዜያት ብቻ ከኑክሌር ማበልፀግ ተግባሯ የሚገታ እንጂ ረጅም ርቀት ተወንጫፊ ባሊስቲክ ሚሳይሎችን ከማምረት የሚያግዳት አይደለም ብለው ያምናሉ። እንዲያውም ስምምነቱ ኢራን በውጭ ሀገራት ባንኮች ያላትንና እንዳይንቀሳቀስ ታግዶባት የነበረው በመቶ ቢሊዮን ዶላር የሚቆጠር ገንዘብ እንዲለቀቅላት ስላደረገ ኢራን ገንዘቡን ሽብርተኞችን ለመደገፍ፣ የጦር መሣሪያ ለመግዛት እንዲሁም አክራሪነትን ለማስፋፋት ተጠቅማበታለች ሲሉ ይከራከራሉ።
ፕሬዚዳንት ትራምፕ የኢራን የኑክሌር ስምምነትን የማይቀበሉባቸው ምክንያቶች ብዙ እንደሆኑ በተንታኞች ዘንድ ይገለፃል።
ፕሬዚዳንት ትራምፕ በድጋሚ ወደ ዋይት ሐውስ ከተመለሱ ወዲህ አሜሪካና ኢራን በኦማን አደራዳሪነት አምስት ዙር ውይይቶችን አካሂደዋል። ውይይቶቹ እስካሁን ድረስ ይህ ነው የሚባል ተጨባጭ ውጤት ባያስገኙም፣ ሁለቱ አካላት ለኢራን ጉዳይ ሰላማዊ አማራጭን በተግባር ያሳዩባቸው ርምጃዎች እንደሆኑ ተቆጥረው ተወድሰዋል። የአሜሪካ ዩራኒየም የማበልፀግ ሂደቱን የማቋረጥ ጥያቄና የኢራን ያለማቋረጥ አቋም የሁለቱ አካላት የክርክር ነጥብ ሆኖ ዘልቋል።
አሜሪካ ኢራን ዩራኒም ማበልፀጓን እንድታቆም ትፈልጋለች። የፕሬዚዳንት ትራምፕ አስተዳደር በኢራን ላይ የተጣሉት ማዕቀቦች እንዲነሱ ኢራን ዩራኒየም ማበልፀጓን እንድታቆም አልያም በትንሽ መጠን ብቻ እንድታበለፅግ ይፈልጋል። ኑውክሌሩን የምጠቀመው ለሰላማዊ ግልጋሎት ነው የምትለው ኢራን ደግሞ ዩራኒምን ለኃይል ማመንጫ ማበልፀግ ሉዓላዊ መብቷ እና በዓለም አቀፍ ስምምነቶችም ያልተከለከለ ተግባር እንደሆነ ትገልፃለች። ባለፈው ሳምንት ኢራን ከአሜሪካ ጋር በምታደርገው ድርድር ዩራኒየም የማበልፀግ ተግባሯን ለሦስት ዓመታት ያህል ልታቆም ትችላለች ተብሎ የተነገረውን መረጃም ‹‹ፍፁም ውሸት›› ብላዋለች።
አንተነህ ቸሬ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ግንቦት 30 ቀን 2017 ዓ.ም