
በ21ኛ ክፍለ ዘመን ያለነው ትውልዶች እያደገ ባለው ሳይንስና ቴክኖሎጂ ውስጥ እንዲሁም እየተፈጠሩ ባሉ አዳዲሲ ፈጠራዎች እየተደመምን የምንኖር ብቻ ሳንሆን የቴክኖሎጂው ተዋናዮችም እየሆንን ነው::
ከዘመኑ ጋር ለመጓዝ እና ስልጡን ለመሆን፤ ‹‹ግሎባል ፓወር›› ከሚባለው ዓለም አቀፍ ኃይል ጋር መዋሃድ ይኖርብናል:: ያለንበት ዘመን ዓለም ለሳይንስና ቴክኖሎጂ ትልቅ ትኩረት የሰጠችበትና ትንግርት የሚመስሉ ፈጠራዎች እየተሠሩ ያሉበት ነው::
በተለይም ባለንበት ዘመን የሰው ልጆች የምርምርና ፈጠራ ውጤት የሆነው አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ (AI) መልሶ ለሌሎች ፈጠራዎች ጥቅም ላይ የመዋሉ ነገር አሠራሮቻችን አቅልሎልናል:: የዊኪፒዲያ ኢንይክሎፒዲያ መካነ ድር በዚህ ዙሪያ ባወጣው መረጃ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ (ሰው ሠራሽ አስተውሎት) በትምህርት ዘርፍ መሠረቱ የተጣለው እ.ኤ.አ በ1956 ሲሆን ዘርፉ በታሪኩ በብዙሃን ብሩህ ተስፋ ሰጪ ዑደቶች ውስጥ ያለፈ ነው:: ይሁን እንጂ በወቅቱ ዘርፉ በደረሰበት ነቀፌታ ፈንድ የሚያደርገው አጥቶ ነበረ ::
ፈንድ ማድረግና ዘርፉን ማጥናት በስፋት የጨመረው ግን እ.ኤ.አ ከ2012 ወዲህ ነው:: ቀስ በቀስ ጥቃቅን ጥሬ መረጃዎችን (ዳታዎችን) ጉልህ መረጃ በማድረግ ቀይሮ ማሽኑ እንዲያውቀው በማድረግ፣ ቪዲዮው አርትኦት እንዲደረግ እና ለጨዋታ ትግበራዎች መጠቀም ተችሏል:: በ2020ዎቹ ሰው ሠራሽ አስተውሎት በፍጥነት እየበለጸገና እያበበ የመጣበት ወቅትና አመንጪ ሰው ሠራሽ አስተውሎት (generative AI) ብቅ ያለበት ነው::
ሀገራችንም በዘርፉ ላይ መሥራት የጀመረችው ከአምስት ዓመት በፊት የኢትዮጵያ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩትን በማቋቋም በወሰደችው ታሪካዊ እርምጃ ነው:: በዚህም ሀገሪቱ የቴክኖሎጂ አጠቃቀምን በማሳደግ በርካታ ሥራዎች ከማከናወኗም በተጨማሪ አብዛኛው ሕዝብ የብሮድባንድና የኪስ ስልክ አገልግሎት ተጠቃሚ ሊሆን የቻለበት ነው::
በሀገሪቱ ባለፉት አምስት ዓመታት የዲጂታል መሠረተ ልማቶችን በመዘርጋት፣ በማስተዳደርና ጥበቃ በማድረግ የቴክኖሎጂውን ሥነ ምኅዳር ለማስፋፋት በርካታ ሥራዎች ተሠርተዋል:: ይህም ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ የተለያዩ መሠረተ ልማቶች መገንባታቸው መንግሥት ለዘርፉ የሰጠውን ትኩረት የሚያሳይ ነው::
ዲጂታል ማኅበረሰብ በመገንባት ረገድ ኢትዮጵያ የ5 ሚሊዮን ኮደርስ ኢንሼቲቭ ቀርጻ ወደ ተግባር ገብታለች:: በዚህም እስከ አሁን አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች የኮደርስ ሥልጠና እንዲወስዱ ተደርጓል:: አሁንም ዜጎች የዲጂታል ዕውቀት እንዲያገኙ በማድረግ ረገድ በትኩረት እየተሠራ ይገኛል:: በኢትዮጵያ ከ15 ሚሊዮን በላይ ነዋሪዎች ዲጂታል መታወቂያ የያዙ ሲሆን ክፍያዎችን ከጥሬ ገንዘብ ወደ ዲጂታል መቀየርም ተችሏል::
Artifical Intelgence Of Ethiopian And African ድረ ገጽ በአፋን ኦሮሞ ባወጣው መረጃ ሀገራችን ከሳይንስና ቴክኖሎጂ ወደ ኋላ የቀረች ብትሆንም ይህንን ቴክኖሎጂ በትክክል ሰው ሁሉ ተገንዝቦ ቢተገብረው በግብርናው ዘርፍ፣ በጤናው፣ በመከላከያው፣ በሳይንስና ቴክኖሎጂ፣ በኢኮኖሚክስ እና በመሳሰሉት ዘርፎች አጃኢብ የሚያሰኝ ብዙ ዕድገት እንደሚገኝ ስለምናምን ነው ይላል:: በተለይም ተማሪዎች ፣ መምህራን እንዲሁም ማኅበረሰቡ በሰው ሠራሽ አስተውሎት ላይ ጠንካራ ግንዛቤ እንዲኖሯቸው ታስቦ እየተሠራ እንደሆነም ያስረዳል::
ሰው ሠራሽ አስተውሎት ወይም አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ የኮምፒውተር ሳይንስ ቅርንጫፍ ሆኖ በስፋት እሱ ላይ ትኩረት የሚሰጡ ስማርት ማሽኖችን ቀጣጥሎ መሥራት ነው:: ቢሆንም ግን ትኩረትን ወይም የሰው ልጆችን ችሎታ የሚፈልጉ ነገሮችን የሚተገብር ነው:: ይህም ማለት የሰው ልጅ ፕሮግራም ካሲያዛቸው ውጪ የማይሠሩ ናቸው:: ብዙ ጊዜ ሰው ሠራሽ አስተውሎት ምንነቱ በዚህ ላይ ተመሥርቶ ‘‘machine learning’’ (ማሽንን መማር) እና ‘‘ deep learning (በጥልቀት መማር) ነው ሲል ድረ ገጹ ያስረዳል::
ሀገራችን በሳይንስና ቴክሎጂ ወደ ኋላ የቀረች ብትሆንም ይህንን ቴክኖሎጂ በትክክል ሰው ሁሉ ተገንዝቦ ቢተገብረው በግብርናው ዘርፍ፣ በጤናው፣ በመከላከያው፣ በሳይንስና ቴክኖሎጂው፣ በኢኮኖሚው እና በመሳሰሉት ዘርፎች አጃኢብ የሚያሰኝ ብዙ ዕድገት እንደሚገኝ ይታመናል ይላል:: በተለይም ተማሪዎች ወይም መምህራን እንዲሁም ማኅበረሰቡ በሰው ሠራሽ አስተውሎት ላይ ጠንካራ ግንዛቤ እንዲኖሯቸው ታስቦ እንደቀረበም ነው የሚያስረዳው::
ከነዚህ ቴክኖሎጂዎች መካከል ባለንበት ክፍለ ዘመን ውስጥ በጣም ወሳኝ የሆነው እና ‹‹ግሎባል ፓወር›› ሆነው ለመገኘት ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶት በዚህ ላይ እየተሠራበት ካለው መካከል ከፍተኛ ሰው ሠራሽ አስተውሎት የሚሉት አንዱ ነው::
የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን በአንድ ወቅት እንደተናገሩት ‹‹ባለንበት ክፍለ ዘመን ውስጥ አንድ ሀገር ‹‹ግሎባል ፓወር›› ሆኜ እገኛለሁ ብላ የምታስብ ከሆነ ሰው ሠራሽ አስተውሎት ላይ መሥራት አለባት፤ በትክክል ከፍተኛ ሰው ሠራሽ አስተውሎት (AI ‘advance’) ደረጃ ከደረሰች እና ካደገች አንዲት ሀገር ብታምንም ባታምንም
በዓለም ላይ የሚገዳደራት ወይም ጐንዋ የሚደርስ ሀገር አይኖርም::›› በማለት ጠቁመው ነበር ሲል Artifical Intelgence Of Ethiopian And African ድረገጹ ላይ በአፋን ኦሮሞ (ትርጉም በራሴ) ካወጣው መረጃ ለመረዳት ተችሏል::
‹‹How artificial intelligence is transforming the world›› በሚል ርዕስ ዳረል ኤም ዌስት እና ጆሃን አር አለን ባወጡት ጥናታዊ ጽሑፍም አብዛኛው ሕዝብ ከሰው ሠራሽ አስተውሎት ጽንሰ ሃሳብ ጋር ዝምድና የሌለው ወይም እንግዳ የሆነ ነው:: እ.ኤ.አ 2017 በዩናትድ ስቴትስ 1ሺ 500 ከፍተኛ የቢዝነስ መሪዎች በዚሁ ሰው ሠራሽ አስተውሎት (AI) ዙሪያ ተጠይቀው 17 በመቶው የሚሆኑት ብቻ ነበሩ እንደሚያውቁት የተናገሩት:: አብዛኞቹ ግን ስለጉዳዩ በትክክል ምን እንደሆነ የማያውቁ ወይም እንዴት ልዩ ኩባንያዎቻቸው ላይ ተጽዕኖ እንደሚያሳድርም እርግጠኛ አልነበሩም:: የንግድ ሂደቶችን ለማነቃቃት እምቅ አቅም እንዳለው የተገነዘቡት ዘግይተው ቢሆንም በድርጅታቸው ውስጥ ሰው ሠራሽ አስተውሎት እንዴት ማሰማራት እንደሚችሉም ግልጽ አልሆነላቸውም::
በዘርፉ ላይ የግንዛቤ እጦት በስፋት ቢስፋፋም፤ የሰው ሠራሽ አስተውህሎት ቴክኖሎጂ እያንዳንዱን የሕይወት ፍኖት (walk of life) እየለወጠው ይገኛል:: ሰው ሠራሽ አስተውሎት ግንዛቤን የሚያሰፋ መሣሪያ ሆኖ ሰዎችን እንደገና አስበው፤ እንዴት መረጃ እንደሚያቀናጁ፣ ጥሬ መረጃ እንዴት እንደሚተነትኑ እና የውሳኔ አሰጣጥን በማሻሻል የተገኘውን ግንዛቤ እንዲጠቀሙ የሚረዳ ነው:: በተለይ ሰው ሠራሽ አስተውሎት የፖሊሲ አውጪዎች፣ የሃሳብ መሪዎች ፍላጎቱ ያላቸው ታዛቢዎች የሚታደሙበት እንደመሆኑ መጠን፤ ዓለምን እንዴት እንደሚያነቃቃና እንደሚቀይር የሚያሳይ እንዲሁም በማኅበረሰቡ ምጣኔ ሀብትና አስተዳደር ላይ አስፈላጊ ጥያቄዎችን የሚያነሳ ነው::
ከሪፐብሊክ ኦፍ ፍራንስ ድረ ገጽ የወጣ አንድ መረጃ እንደሚሳየው ሰው ሠራሽ አስተውሎት የቴክኖሎጂ ዘርፉን የሚያናውጥ ብቻ ሳይሆን የወደፊቷን አፍሪካ እንደገና የሚቀርጽና የሚለውጥ ነው ይላል:: ከጤናው ዘርፍ እስከ ትምህርት እንዲሁም ከግብርና ለሚመነጩ ለአፍሪካ ዋና ዋና ማኅበራዊ ኢኮኖሚያዊና አካባቢያዊ ተግዳሮት ሁነኛ መፍትሔ የሚሰጥ ነው:: ይህም ልዩ ክህሎት የአህጉሩን ጨዋታ ቀያሪ ማሽን ሊያደርገው እንደሚችል ነው መረጃዎች የሚያሳዩት::
በያዝነው ግንቦት ወር የመጀመሪያዎቹ ሳምንታት በአዲስ አበባ ‹‹የኢትዮጵያ ቴክኖሎጂ ኤክስፖ ETEX-2025›› ‹‹አርተፊሻል ኢንተለጀንስናን ለአፍሪካ ብልጽግና እና ትብብር ›› በሚል መሪ ሃሳብ በአፍሪካ ሰው ሠራሽ አስተውሎት መድረክ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ባደረጉት ንግግር ኢትዮጵያ በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስና በዲጂታል መሠረተ ልማት አርአያ እየሆነች እንደሆነ ገልጸው ነበር::
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመድረኩ እንደተናገሩት ኢትዮጵያ በሰው ሠራሽ አስተውሎት፣ በዲጂታል መሠረተ ልማት እና በክህሎት ማበልጸጊያ ሥራዎች ግንባር ቀደም እየሆነች መጥታለች:: በኢትዮጵያ የተጀመሩ የአርተፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት፤ ዲጂታል መታወቂያ እንዲሁም አምስት ሚሊዮን ኮደርስ ሥልጠና የኢትዮጵያን ዲጂታል ሕልሞች ወደ ተጨባጭ ለውጥ የሚቀይሩ ናቸውም ብለዋል ::
በወቅቱ አፍሪካ ሀገር በቀል የሰው ሠራሽ አስተውሎት የተመራ አካታች ብልጽግና በማምጣት የአጀንዳ 2063 ግቦችን ለማሳካት እየሠራች መሆኑን የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ አፍሪካ በ2030 አርተፊሻል ኢንተለጀንስን በሥነ ምግባርና በአካታችነት መርሕ በአኅጉራዊ መልክ ልትገነባ እንደሚገባ ተናግረዋል:: አርተፊሻል ኢንተለጀንስ ለዜጎች ሕይወት መሻሻል፣ ለተቋማት መለወጥና የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም ሞተር መሆኑን ገልጸዋል::
አሁንም ዜጎች የዲጂታል እውቀት ባለቤት እንዲሆኑ በማድረግ ረገድም በትኩረት እየተሠራ መሆኑን አመልክተዋል። ከ 15 ሚሊዮን በላይ ኢትዮጵያውያን እና ነዋሪዎቿ የዲጂታል መታወቂያ መያዛቸውን እንዲሁም ክፍያዎችን ከጥሬ ገንዘብ ወደ ዲጂታል መቀየር መቻሉን ጠቁመዋል። በኢትዮጵያ አብዛኛው የመንግሥት ተቋማት አገልግሎታቸው ዲጂታል እንዲሆን መደረጉን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸው፤ በቅርቡ በተመረቀው የመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት 12 ተቋማት 41 አገልግሎቶችን በአንድ ጣሪያ ሥር ለሕዝብ እየሰጡ ነው ብለዋል።
የአገልግሎት አሰጣጥን ለማዘመንና የዜጎችን ኑሮ ለማሻሻል የዲጅታል የክፍያ አማራጮችን ማስፋፋትን ጨምሮ ድጂታል ኢኮኖሚ ለመገንባት በርካታ ሥራዎች እየተሠሩ መሆናቸውን አስታውቀዋል። በቀጣይም በ2030 የኢትዮጵያን የቴክኖሎጂ ትራንስፎርሜሽን እውን በማድረግ በቴክኖሎጂ የበለጸገች ሀገር እንድትሆን በትኩረት እንሠራለን ነው ያሉት። የቴክኖሎጂ አካታችነትን ለማሳደግ በትብብር መሥራት እንደሚገባ አስገንዘበዋል።
የዘርፉ ባለሙያዎች ሰው ሠራሽ አስተውሎት እ.አ.አ በ2035 ፣ በ2045 ወይም በ2075 የሰው ልጆች የሚሠሩትን ሊከውን ይችል ይሆናል በሚል የተለያየ አቋም ይዘዋል። አሁን ያለው ሰው ሠራሽ አስተውሎት ወደ አርቴፊሻል ሱፐር ኢንተለጀንስ ወይም አርቴፊሻል ጄነራል ኢንተለጀንስ ሲሻገር ነው የሰው ልጆች የሚከውኑትን በአጠቃላይ መሥራት እንደሚችል ከቢቢሲ አማርኛ ድረገጽ የተገኘው መረጃ የሚያሳየው። እዚህ ላይ ከዲጂታል አገልግሎቶች የብሔራዊ ሎተሪን፣ ዲጂታል ቲኬትና የኢትዮጵያ ዲጂታል መታወቂያን ወይም ፋይዳ መታወቂያን ማንሳት ወደድን ::
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሎተሪ አገልግሎት ከወረቀት ቲኬት ሎቶሪ በተጨማሪ የዲጂታል ሎቶሪ የተጀመረው ኢትዮ ቴሌኮም እና የብሄራዊ ሎተሪ አስተዳደር በቴሌብር የዲጂታል ሎተሪ ለመጀመር ሐምሌ 8 ቀን 2014 ዓ.ም ባደረጉት የስምምነት ፊርማ ነው:: በሚያዝያ 2017 ዓ.ም ደግሞ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሎተሪ ራሱን ችሎ የዲጂታል ሎተሪን ይፋ አድርጓል:: ይህ ዘመናዊ ሎተሪ ከወረቀት ሎተሪ በተጨማሪ በዲጂታል መላ በሞባይል መተግበሪያ አማካኝነት ለኅብረተሰቡ አገልግሎት የሚሰጥ ነው::
ለረጅም ዓመታት በመፋቅ እድለኛ የሚያደርጉት የፈጣን እና የቢንጎ ሎተሪዎችም በዲጅታል መንገድ ተካተውበታል። ከሀምሳ ሚሊዮን ብር ሽልማት አንስቶ በርካታ የጨዋታ አማራጮች የቀረቡበት ሲሆን በኢትዮጵያ በስምንት የሀገራችን ቋንቋዎች መዘጋጀቱ ታውቋል። አገልግሎቱ በኢትዮጵያ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ከቲኬት ሎተሪ ወደ ዲጅታል ሎተሪ በተጨማሪ በሃምሳ ሺህ ብር ሽልማት የከፈተውን የእድል በር ወደ ሃምሣ ሚሊየን ብር ከፍ አድርጎታል። ዲጂታል ሎተሪ በሃምሳ ሚሊየን ብር መጀመሩ ወደፊት የሽልማት ጣሪያው እንደሚያድግና በተደራሽነቱ ብዙ ሰዎች ዕድላቸውን ለመሞከር እንደሚታደሙበት ይጠበቃል::
በዘመናችን ከ90 በላይ ሀገሮች የዲጂታል መታወቂያ አገልግሎት እየተጠቀሙ ነው:: እስካለፈው የፈረንጆቹ ዓመት መጨረሻ በዓለም 5 ቢሊዮን ሰዎች ዝቅተኛና መካከለኛ ገቢ ያላቸው የአፍሪካና የእስያ ሀገሮችም የዚሁ ፋይዳ መታወቂያ ተጠቃሚዎች እንደሆኑ “Digital Watch Observatory” ያወጣው መረጃ ያሳያል።
በኢትዮጵያ ፋይዳ (ዲጂታል) መታወቂያ ከተጀመረ ስድስት ዓመት ሆኖታል። ፋይዳ መታወቂያው በሙከራ ደረጃ ሲተገበር ቆይቶ መጋቢት 21 ቀን 2015 ዓ.ም. በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የወጣውን አዋጅ ተከትሎ በይፋ ተግባራዊ መሆን ጀምሯል።
ፋይዳ ዲጂታል መታወቂያን ከሌሎች መታወቂያዎች የሚለየው አንድ ወጥ መሆኑ ነው። ሰዎች የቀበሌ ነዋሪነት፣ የትምህርት ቤት፣ የመሥሪያ ቤት መታወቂያ ይኖራቸዋል። በዘመናችን ቀድሞ ስንገለገልባቸው የነበሩ ብዙ የወረቀት መታወቂያዎች የነበራቸውን የዲፕሎማቲክ ግንኙነት እያቋረጡ ነው።
ከኢትዮ ቴሌኮም ድረገጽ የተገኘ መረጃ እንደሚያሳየው፤ የዲጂታል መታወቂያ የነዋሪዎችን የባዮሜትሪክ (የጣት ዐሻራ፣ የዓይን ዐሻራ እና የፊት ምስል) እንዲሁም የግል መረጃዎችን በመሰብሰብ አንድን ግለሰብ ልዩ በሆነ መልኩ እንዲታወቅ የሚያስችል ነው። ኢትዮ ቴሌኮም መሪ የዲጂታል መፍትሄ (ሶሉሽን) አቅራቢ ድርጅት በመሆኑ የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያን ራዕይ በአጋርነት ለማሳካት እና ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን የማድረግ ራዕይ ለማፋጠን በዲጂታል መታወቂያ ምዝገባ፣ በመታወቂያ ሕትመትና ሥርጭት፤ ማንነትን በማረጋገጥ (Authentication) ሥራዎች ላይ በትኩረት እየሠራ ይገኛል።
የሰው ሠራሽ አስተውሎት ሚናው እያደገ ያለበት አንዱ ምክንያት ለኢኮኖሚ ልማት እጅግ በጣም ጥሩ አማራጮች ማቅረብ መቻሉ ነው:: ሰው ሠራሽ አስተውሎት ዓለም እንዴት ይለወጣል? በሚል የቀረበ አንድ ጥናታዊ ጽሑፍ ላይ እንደተጠቀሰው፤ በ‹‹Price Water house Coopers›› ድርጅት በተሠራ አንድ ፕሮጀክት እንደተገመተው ‹‹በሰው ሠራሽ አስተውሎት ቴክሎጂዎች በዓለም ደረጃ የሀገር ውስጥ ምርት በ15 ነጥብ 7 ትሪሊዮን ዶላር ጨምረው፣ በ2030 14 በመቶ ማድረስ እንደሚቻል ነው::››
ይህም የእድገት ትንበያ በየክፍለ አኅጉራቱ ስናየው በቻይና 7 ትሪሊዮን፣ በሰሜን አሜሪካ 3 ነጥብ 7 ትሪሊዮን፣ በሰሜን አውሮፓ 1 ነጥብ 8 ትሪሊዮን፣ በአፍሪካና በኦሽኒያ 1 ነጥብ 2 ትሪሊዮን፣ ከቻይና ውጪ ባለችው እስያ 0 ነጥብ 9 ትሪሊዮን ዶላር፣ በደቡብ አውሮፓ 0 ነጥብ 7 ትሪሊዮን እና በላቲን አሜሪካ 0 ነጥብ 5 ትሪሊዮን ዶላር ሊጨምር እንደሚችል ነው ::
ቻይና በዚህ ምክንያት በፍጥነት እየተስፈነጠረች እንደሆነና ለዚህም በሰው ሠራሽ አስተውሎት ብሔራዊ ግብ ላይ 150 ቢሊየን ዶላር ፈሰስ (ኢንቨስት) እንዳደረገች በዚህም እ.ኤ.አ በ2030 ዓለም አቀፍ መሪ ለመሆን እየሠራች መሆኑን ሰው ሠራሽ አስተውሎት ዓለምን እንዴት ይለውጣል? በሚል Darrell M. West እና John R. Allen ያወጡት ጥናታዊ ጽሑፍ ያሳያል::
በሀገራችን የዲጂታል አገልግሎቶች ሲጀመሩ በመተግበር ከአፍሪካ ግንባር ቀደም ነች:: ነገር ግን ፋይዳ መታወቂያ፣ ዲጂታል ሎተሪ እንዲሁም ሰው ሠራሽ አስተውሎት እንዲተገበሩ ሲደረግ ለጋዜጠኞችም የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና መስጠትን ባሕል ማድረግ ይገባል:: የሚመለከታቸው አካላት በዚህ ረገድ የማዝገም አዝማሚያ ይታይባቸዋል:: የሙያው ማኅበራት በዚህ ረገድ ፈር ቀዳጅ ቢሆኑ ግንዛቤ የጨበጠው ጋዜጠኛ ለማኅበረሰቡ ግንዛቤውን በማስጨበጥ የበለጠ አገልግሎቱን ተደራሽ እና ተጠቃሚ ማድረግ ይቻላል::
ኃይለማርያም ወንድሙ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ግንቦት 30 ቀን 2017 ዓ.ም