“የዕድሜን ችግር ለመፍታት እንደ ኬንያ መወሰን አለብን” – ዶክተር አያሌው ጥላሁን

– ዶክተር አያሌው ጥላሁን የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የሕክምና ባለሙያ

በዕድሜ ገደብ የሚካሄዱ ውድድሮች ዋነኛ ዓላማ ወጣትና ተተኪ አትሌቶችን ማፍራት ነው። ታዳጊና ወጣት አትሌቶች ወደ ትልቅ መድረክ የሚሸጋገሩበትን ዕድል የሚያገኙትም በእንዲህ አይነት መድረኮች መሆኑ አያከራክርም። ይሁን እንጂ መሰል ውድድሮች ሁሌም ከዕድሜ ተገቢነት ጋር በተያያዘ ከችግር ፀድተው አያውቁም። ይህ ችግር በአፍሪካ አትሌቲክስ ላይ ጎልቶ የሚታይ ቢሆንም በስፖርቱ ትልቅ ስም ያላቸው እነ ኬንያ በወሰዱት ርምጃ መሻሻል እያሳዩ ይገኛሉ። በአትሌቲክስ ገናና ስም ያላት ኢትዮጵያ ግን ይህ የዕድሜ ተገቢነት ጉዳይ በወጣቶች መካከል በሚካሄዱ ውድድሮች ሁሉ የዘወትር ጥያቄና የብዙዎች እሮሮ ሆኖ ቀጥሏል። በዚህም ኢትዮጵያ ተተኪ አትሌቶችን እያጣች ትገኛለች። ይህ የአትሌቶች የዕድሜ ተገቢነት ጥያቄ በቅርቡ በድሬዳዋ በተካሄደው የኢትዮጵያ ከ18 እና ከ20 ዓመት በታች አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ ተባብሶ ታይቷል። ይህ ችግር ያለባቸው ብዙዎቹ ሀገራት ጨከን ብለው በወሰዱት ርምጃ በተጨባጭ የሚታይ ለውጥ እያስመዘገቡ ቢሆንም፣ ኢትዮጵያ የዚህ ችግር ገፈት ቀማሽ ከሆኑ ሀገራት ግንባር ቀደም እንደመሆኗ የተጣመመውን ለማቅናትና ስፖርቱን ገዝግዞ እየጣለ የሚገኘውን ነቀርሳ ነቅሎ ለመጣል የረጅሙን መንገድ ጉዞ የጀመረች አይመስልም።

ለሰባት ቀናት በድሬዳዋ ሲካሄድ ቆይቶ ባለፈው እሁድ የተጠናቀቀው የኢትዮጵያ ከ18 እና ከ20 ዓመት በታች አትሌቲክስ ሻምፒዮና ስያሜው ባጭሩ ሀገር አቀፍ የወጣቶች አትሌቲክስ ሻምፒዮና ተብሎ ሊጠራ ይችላል። በተግባር ግን ፈፅሞ የወጣቶች ሻምፒዮና መሆን አልቻለም። እንደ አጠቃላይ ይህ ሻምፒዮና ከዓላማው አኳያ ከሽፏል ማለት ይቻላል። ይህንንም ከባለሙያዎች እስከ አሠልጣኞችና ራሳቸው አትሌቶች እንዲሁም የውድድሩ ባለቤት በሆነው አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የታመነበት ነው።

በዚህ ሻምፒዮና በጣት የሚቆጠሩ (በተይም በአጭር ርቀት ሴቶች) ወጣቶች ተወዳዳሪ ሆነው ከመቅረባቸው ባሻገር በአጠቃላይ በሁሉም የውድድር አይነቶች በተገቢው ዕድሜ ላይ የሚገኙ ወጣቶችን ማየት አልተቻልም። ገና ሻምፒዮናው ከመጀመሩ አስቀድሞ የፌዴሬሽኑ የሕክምና ባለሙያ ሆነው ለረጅም ዓመታት ያገለገሉት ዶክተር አያሌው ጥላሁን “ይህ ሻምፒዮና ከሽፏል” በማለት ነበር የሚዲያ ባለሙያዎች ከዕድሜ ተገቢነት ጋር በተያያዘ ስላለው ችግር ለመጠቆም የሞከሩት።

ከስምንት ኦሊምፒኮች በላይ በዚህ ሙያ ማገልገል የቻሉት ዶክተር አያሌው በወጣት ውድድሮች ላይ ለዓመታት የተጋነነ የዕድሜ ተገቢነት ችግር ምክንያቱና መፍትሔውን በተመለከተ ለአዲስ ዘመን የሰጡት ሀሳብ እንደሚከተለው ይነበባል።

አዲስ ዘመን:- የዘንድሮው ሻምፒዮና የዕድሜ ተገቢነት ጉዳይ ጎልቶ የታየበት ምክንያት ምንድነው፣ የፌዴሬሽኑ የሕክምና ክፍልስ ቀድሞ የማጣራት ሥራ ሠርቷል?

ዶ/ር አያሌው:- በፌዴሬሽን በኩል ምንም ማጣራት አላደረግንም ማለት ይቻላል። ምክንያቱም ካጣራን ከግማሽ በላይ የሆነው አትሌት ሳይሳተፍ ስለሚመለስ። መጀመሪያም ስህተት ስለተሠራ መነካካቱ ብዙ ችግር ያመጣል።

አዲስ ዘመን:- ችግሩ የማነው?

ዶ/ር አያሌው:– ጥፋተኛው አትሌቱ አይደለም። አሠልጣኙ፣ ቡድን መሪው፣ ክለቦችና ክልሎች ናቸው። በፍፁም ሕግ አያከብሩም፣ በተለይ አሠልጣኞች በሚያሳዝን መልኩ እየሠሩ ያሉት ወንጀል ጭምር ነው። ለሀገር የሚጠቅሙ የተማሩ አሠልጣኞች ናቸው ያሉን፣ ግን ወንጀሉን ለመሥራት ቀዳሚዎቹ እነሱ ናቸው። ልጆቹ ከመመረጣቸው በፊት በሕክምና አስመርምረናል ብለው ነው ይዘው የሚመጡት፣ እኛ በዚያ እርግጠኛ መሆን ባንችልም።

አዲስ ዘመን:- ክለቦች ተገቢ ነው ብለው ያመጡትን አትሌት ፌዴሬሽኑ የውድድሩ ባለቤት እንደመሆኑ በራሱ የሕክምና ባለሙያዎች አጣርቶ ተገቢ ያልሆነውን ለምን አላገደም?

ዶ/ር አያሌው:- አንድ ሐኪም ትክክል ነው ያለውን ሌላው መንካት አይችልም፣ እኔ ላደርግ የምችለው የእነሱ ሐኪም ትክክል ነው ያለውን አትሌት በመታወቂያ እሱ መሆኑን ማረጋገጥ ነው። ብዙዎቹን አትሌቶች ስለማውቃቸው የጎሉ ችግሮችን ለማውጣት ሞከርኩኝ፣ ግን ውድድሩ ላይ ለመሳተፍ ከመጣው ሁለት ሦስተኛው አትሌት ከውድድር ውጪ ሊሆን ነው። አስደናቂ ወጣቶችን በተገቢው ዕድሜ ያመጡ አሠልጣኞች አሉ፣ ግን ሁለት ሦስተኛውን ካገድን ውድድሩ ላይካሄድ ነው፣ ውድድሩም ሊሰረዝ ሆነ፣ ስለዚህ አትሌቱን ሳይሆን ችግሩን የሚፈጥረውን አካል ነው መቅጣት ያለብን፣ ያጠፋው እያለ ያላጠፋውን መቀጥቀጥ የለብንም። በዚህ ምክንያት ፕሬዚዳንቱን አነጋግረን “ይሄ ነገር አያዋጣም” ወደ ግብግብ ልንሄድ ነው ብለን ውድድሩ ተካሂዷል።

አዲስ ዘመን:- ችግሩ የአሠልጣኞች፣ ክለቦችና ክልሎች ብቻ ነው ብሎ መደምደም ይቻላል?

ዶ/ር አያሌው:– በዋናነት ችግሩ ያለው እኛው ፌዴሬሽን ውስጥ ነው፣ ሕጎቹ በሙሉ ልክ አይደሉም። ስለዚህ ባልሠራነው ሥራ የተለየ ነገር መጠበቅና ሌላው ላይ ጣት መቀሰር የለብንም። በዚህ መሠረት ውድድሩ ከሚሰረዝ የመጣው ሁሉ ተወዳድሮ በኋላ በጉዳዩ ዙሪያ ተቀምጠን ብንነጋገር የተሻለ ነው ብለን ቀጥሏል። ይህ ችግር ስለሚያመጣው መዘዝ ለአሠልጣኞች፣ ክለቦችና ክልሎች የሰጠነው ሥልጠና ቁጥር ስፍር የለውም፣ የተነጋገርንበትም ጊዜም በተመሳሳይ። ከ2014 ዓ.ም ጀምሮ ብዙ ጊዜ መክረንበታል፣ በነዚህ ዓመታት ወንጀል ነው የተሠራው፣ ጭራሽ ብሶባቸው ነው የሚመጡት። የተማረ ነገር ግን በፍፁም መሻሻል የማይፈልግ ሰው ነው እየመጣ ያለው። ሰብስበን ስንነጋገር ተገቢ ያልሆነውን አባር ይልሀል፣ ግን ውድድር ላይ ተገቢ ያልሆነውን ይዞ የሚመጣው ራሱ እንደዚህ የሚለው ነው። እንዲህ አይነት የአሠልጣኞች ቡድን ነው የተፈጠረው፣ ይህ ማለት ግን ጥረት የሚያደርጉ መልካም አሠልጣኞች የሉም ማለት አይደለም። እነዚህ ጥሩ ነገር ይዘው የሚመጡ አሠልጣኞች ግን ተገቢ ያልሆነውን ይዘው በሚመጡት እየተዋጡ በዚህም ተስፋ እየቆረጡ ተመልሰው እዚያው ችግር ውስጥ ይገባሉ።

አዲስ ዘመን:- ይህን ችግር የሚፈጥሩት አሠልጣኞች፣ ክለቦች ወዘተ ለመታረም ፍቃደኛ የማይሆኑበት ምክንያት ምን ሊሆን ይችላል?

ዶ/ር አያሌው:- ዓላማቸው አትሌቲክሱን ማጥፋት ነው ብዬ አምናለሁ፣ እንጂ ከፈለጉ ማስተካከል ይችላሉ። በዋናው ሻምፒዮና የተወዳደሩ፣ በዓለም መድረኮች የተሳተፉ አትሌቶች ተመልሰው እዚህ ለመወዳደር ይመጣሉ። ችግሩ ስር ሰደደ፣ በዚህ የሚሰቃዩ የሚጎዱ ብዙዎች ናቸው። እኔ በግሌ ለምን እንዲህ ውጥንቅጡ የወጣ ሕይወት ውስጥ እገባለሁ እስከማለት ደርሻለሁ። አይሆንም ብለን ስንጥል በአሠልጣኞች እንሰደባለን፣ አትሌቶች ይጮሁብናል፣ ለፀብ የሚጋበዝም ብዙ ነው። የሕክምና ሙያ ረክሷል። ይሄ ችግር ከፌዴሬሽኑ ጀምሮ ነው መጥራት ያለበት፣ ደንቡ ልክ አይደለም፣ መታየት አለበት።

አዲስ ዘመን:- ለምሳሌ የትኛው ደንብ ነው ትክክል ያልሆነው?

ዶ/ር አያሌው:አንደኛ የፕሮጀክት ውድድር ለምን ብቻውን አይደረግም፣ የማሠልጠኛ ማዕከላት ውድድር ለምን ለብቻው አይሆንም?

ከ18 ዓመት በታች ለምን ብቻውን አይሆንም?።

ሌላው ክለቦች ከ18 ወይም ከ20 ዓመት በታች የሚባል ነገር የላቸውም፣ በዚህ ረገድ ያስመዘገቡትና ሪፖርት ያደረጉት ነገር የለም፣ ለምሳሌ 2015 ዓ.ም ላይ ከ18/20 ዓመት በታች ፕሮጀክትና አትሌቶች አላችሁ ወይ? ብለን በደብዳቤ ጠይቀን ነበር፣ አንድም መልስ የሰጠ የለም፣ በወጣት ውድድር ላይ ግን ሁሉም ክለብ ይመጣል። ይሄ ምን ማለት ነው?፤ በእኛው ፌዴሬሽን ከላይ ጀምሮ ያለው የቁጥጥር ሥርዓት፣ የውድድር ፕሮግራምና ሕግና ደንብ ፍፁም ችግር አለበት። ሌላው ትልቁ የኛ/የፌዴሬሽኑ ፕሮጀክቶች የትኞቹ ናቸው? ይሄን የሚመልስ ካለ በጣም ደፋር ሰው መሆን አለበት፣ እኛ ፌዴሬሽኑ 39 ፕሮጀክቶች አሉን እንላለን፣ ባህልና ስፖርት ሄደህ ስትጠይቅ 160 ነው ይላል፣ ልዩነቱ ግልፅ ነው፣ የትኛው ነው የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሮጀክት፣ በየትኛው ዕድሜ?

አዲስ ዘመን:- ፌዴሬሽኑ ከሕግና ደንብ በተጨማሪ ከዕድሜ ጋር በተያያዘ ሌሎች ችግሮች የሉበትም ይላሉ፡፡

ዶ/ር አያሌው:- የአሁኑን ሥራ አስፈፃሚ አይመለከትም፣ ትልቁ ችግር በፌዴሬሽኑ አንገመገምም፣ አሁን ይሄ ውድድር እንዲህ ተበላሸ፣ ነገ ርምጃ ወስደን ከማስተካከል ይልቅ ችግሩን እንደያዝን ወደ ሌላ ውድድር ነው የምንሄደው፣ ይሄ ሁሉ የፕሮግራም፣ የትምህርትና ሥልጠና መስመር ሲስተሙ/ሥርዓቱ መውደቁን ነው የሚያሳየው። ስለዚህ አሁንም ይብቃን! እንበል። ቁጭ ብለን እንነጋገር፣ በቃ ይህ ነገር ፈር ስለሳተ አዲስ አካሄድ የተለየ መስመር እንፍጠር፣ ጥገና ሳይሆን አዲስ ሥርዓት እንገንባ፣ በናይጄሪያ የወጣት ሻምፒዮና ባንወዳደርስ? ለምን 2-3 ዓመት የወጣቶቹን ውድድር አንዘጋውምና አዲስ ትውልድ ይዘን አንመጣም?። በአሁኑ ሻምፒዮና ያየሁት ዝቅተኛ ዕድሜ 25 ነው፣ ፌዴሬሽን፣ ክልሎችና ክለቦች ጋር ትልቅ ሥራና ኃላፊነትም ጭምር አለ። ኢትዮጵያን የሚያዋጣት ውድድር ሳይሆን ትምህርትና ሥልጠና ላይ ማተኮር ነው።

አዲስ ዘመን:- የፋይዳ መታወቂያ ምዝገባ በአንዳንዶች ዘንድ መፍትሔ ተደርጎ ቢቆጠርም፣ በሌላው ወገን ምንም አይለውጥም የሚል እምነት አለ፣ እርስዎ ከየትኛው ጋር ይስማማሉ።

ዶ/ር አያሌው:- እኔ ምንም አይለውጥም ከሚሉት ወገን ነኝ። አንድ ሰው የፋይዳ መታወቂያ ለመመዝገብ ሲሄድ ዕድሜውን የሚናገረው ራሱ ነው፣ የተናገረው እድሜ ትክክል አይደለም የሚባልበት ሁኔታ አይኖርም፣ ስለዚህ እንደውም ችግሩን ሊያባብሰው ይችላል፣ የፋይዳ መታወቂያ አንዱ ጥንካሬ አንድ ሰው አንዴ ከተመዘገበ ለሚቀጥለው አምስት ዓመት ዕድሜውን ሊያጭበረብር አለመቻሉ ሊሆን ይችላል። ስለዚህ ብዙ ተስፋ አላረግም። ምክንያቱም ዕድሜ የሚመዘገበው ባለቤቱ በሚሰጠው መረጃ መሠረት ነው።

አዲስ ዘመን:- የፋይዳ መታወቂያ ምዝገባ በትምህርት ቤት ሕፃናት ላይም ተግባራዊ እየተደረገ በመሆኑና የጣት ዐሻራንም ያካተተ እንደመሆኑ ወደፊት አስተዋፅዖ ሊኖረው አይችልም?

ዶ/ር አያሌው:– የተደራጀ መረጃ ስለሚመዘግብ በትምህርት ቤቶችና ፕሮጀክቶች ላይ በትኩረት ከተሠራበት ወደፊት ትልቅ አስተዋፅዖ ይኖረዋል።

አዲስ ዘመን:- ታዲያ ለዚህ ችግር መፍትሔው ምንድነው ይላሉ?

ዶ/ር አያሌው:- ይሄን ችግር ለማቆም እንደ ኬንያ መወሰን አለብን፣ ኬንያ የወጣቶች ውድድሯን ለአራት ዓመት ዘግታ ነው እንደገና የመጣችው፣ ለዚህም ነው ሁሌ አዳዲስ አትሌቶች የምናየው፣ እኛም ከዚህ መማርና ቆራጥ መሆን አለብን። ኢትዮጵያ በወጣት ሀብታም ነች፣ ስፖርቱን የሚመራ ቆራጥ ሰው ብቻ ነው የሚያስፈልገው። አስገራሚ ወጣቶች በውድድሮች ላይ በተገቢው ዕድሜ ይመጣሉ፣ ተገቢ ባልሆኑት ተሸፍነው ግን ሳናያቸው ይመለሳሉ። መድረኩ የእነሱ ቢሆንም በታላላቆቻቸው ተቀምተዋል፣ እነ ስለሺ ስህንና መሠረት ደፋር ወደ ኃላፊነት መጥተዋል፣ በሩጫ ዘመናቸው ቆራጥ ነበሩ፣ ያንን በአመራርነትም መድገም አለባቸው፣ ደራርቱ ልትቆርጥና ልትወስን ነበር፣ በተለያየ ነገር ስትዋከብ አልተሳካላትም እንጂ።

አዲስ ዘመን:- ዶክተር አያሌው ለሰጡን ሀሳብና ጊዜ ከልብ እናመሰግናለን።

ዶ/ር አያሌው:- እኔም አመሰግናለሁ።

ቦጋለ አበበ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ግንቦት 30 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You