ማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲ የመስከረም ወር 2014 ዓ.ም አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት 34 ነጥብ 8 በመቶ መድረሱን በሪፖርቱ ይፋ ማድረጉ ይታወቃል። ከጊዜ ወደጊዜ እያሻቀበ የመጣው ይህ የዋጋ ግሽበት ከቁጥጥር ውጭ ሆኖ አገሪቱን እንዳይፈትን ደግሞ የምጣኔ ሀብት ባለሙያው መፍትሄ እንዳለ ይናገራሉ።
ከዋጋ ግሽበቱ ጋር ተያይዞ አዲስ ዘመን ያነጋገራቸው የምጣኔ ሀብት ባለሙያውና የኦሮ-ፍሬሽ አትክልትና ንግድ አክሲዮን ማህበር ሥራ አስኪያጅ ዶክተር አደሬ አሰፋ እንደሚናሩት፤ የዋጋ ግሽበት ማለት የምንገዛበት ዋጋ መጨመር ነው። የዋጋ ግሽበት ምን ይመስላል የሚለውን ባደጉ አገራት እና እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ያላደጉ አገራት ብሎ መክፈል ይቻላል።
ባደጉ አገራት የዋጋ ግሽበትን የሚያመላክቱ ብዙ የሚታዩ ነገሮች ቢኖሩም አቅርቦትንና ፍላጎትን ብቻ በማወዳደር እየሔደ ያለው ወዴት ነው? ያለውስ ነገር ምንድን ነው በማለት መለየት ይቻላል። ብዙውን ጊዜ የዋጋ ግሽበት የሚኖረው ፍላጎት ከአቅርቦት ሲበልጥ ነው። ይህ በእኛም አገር አንዱ ችግር ነው። ፍላጎት ደግሞ ከአቅርቦት ያነሰ ከሆነ እሱም የሚፈለግ አይደለም። የሚሸጥበት ዋጋ ከተመረተበት ዋጋ ካነሰ በራሱ ለዋጋ ግሽበት በምክንያነት የሚጠቀስ ነው። ጥሩ የሚሆነው አቅርቦቱና ፍላጎቱ ሚዛናዊ የሆነ ስርዓትን ይዞ መቀጠል ሲችል ነው።
ይህ ግን አቅርቦትንና ፍላጎትን እያወዳደሩ የዋጋ ግሽበቱን ያመጣው ምንድን ነው የሚለውን ለማወቅ ባደጉ አገራት የሚጠቀሙት መንገድ የምርት ሂደቱን፣ የግንባታዎች ወቅታዊ ሁኔታ እንዲሁም የኋሊዮሹንና የወደፊቱን በማወዳደር ነው።
ነገር ግን እንደ እኛ አገር ያሉ ያላደጉ አገራት ላይ ከዚህ ውጭ ብዙ ግምት ውስጥ የሚገቡ ነገሮች ይኖራሉ ይላሉ ዶክተር አደሬ፤ ለምሳሌ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገራት ላይ ያለው የኢኮኖሚ ሁኔታ ያልተረጋጋ ነው። ግብርናችን በጣም ኋላቀር ነው። ያሉን መዋቅሮችም ሆኑ ተቋማት ጠንካራ አይደሉም። በየጊዜው ጦርነቶች፣ ሰላም ማጣቶች እንዲሁም የፖለቲካ አለመረጋጋት የእኛ የዕለትተዕለት ኑሮ በሚመስል አይነት ሁኔታ እየታየ ነው። የውጭ ምንዛሪ ችግር፣ የመንገድ ችግር፣ የቴሌኮሙኒኬሽን ችግር፣ በዝናብ ላይ የተንጠለጠለ እርሻ ፣ አንድ ጊዜ በዝናብ አንድ ጊዜ ደግሞ በድርቅ የምንመታ እንደመሆናችን እነዚህ እነዚህ ነገሮች ግምት ውስጥ ሳይገቡ ስለዋጋ ግሽበት ማውራት አይሆንም ማለት ነው ሲሉ ያብራራሉ።
በኛ ሀገር የዋጋ ግሽበትን ያመጡት ምንድናቸው የሚለውን ለመናገር የተጠቀሱት ችግሮች መነሻ ምንድን ነው? ለምንድን ነው የኖሩት? እነዚህ ችግሮች ደግሞ የዋጋ ግሽበትን ያመጡት እንዴት ነው?ለምሳሌ የዋጋ ግሽበቱ በሁሉም አይነት ምርት ላይ ላይሆን ይችላል። አንዱ ዘንድ ሲከሰት ኢኮኖሚውን እንዴት ነው አንቆ የሚይዘው? የሚለውን ነገር በደንብ ማጥናት እና መተንተን እንደሚያስፈልግ የምጣኔ ሀብት ባለሙያው ያስረዳሉ።
የዋጋ ግሽበቱ እንዲኖር ከሚያደርጉ የመጀመሪያ የአቅርቦትና የፍላጎት አለመመጣጠን ነው ።ይህም ገበያው እንዲሸበር ያደርጋል። ጭማሪ በመኖሩ በገበያው ላይ በድንገት የሚመጣ ፍርሃት ይፈጠራል። እኛም አገር ውስጥ እንደእነዚህ አይነት ሁኔታዎች ታይተዋል፤ እየታዩም ነው ።
ሁለተኛው ደግሞ የግብዓቶች ዋጋ መጨመር ነው። ከዓለም የምግብና የነዳጅ ዋጋ ጋር ተያይዞ የሚመጣ የግብዓት ዋጋ መጨመር የሚያመጡት ምክንያቶች ናቸው። ለምሳሌ በእኛ አገር ነባራዊ ሁኔታ የዛሬ 16 እና 17 ዓመት ወደኋላ ተመልሰን ብናይ አንድ በመጀመሪያ ዲግሪ የተመረቀ ሰው የወር ደመወዙ ከአንድ ሺ ብር በታች ነበር። በዚያ ብር የቤት ኪራዩን ከፍሎ፣ ቤተሰቡን አስተዳድሮ በአግባቡ ይኖር ነበር። ምናልባትም እንደየሰው የሚለያይ ቢሆንም ይቆጥብ ነበር።
ነገር ግን በአሁኑ ወቅት አዲስ ምሩቅ ወደሥራ በሚገባበት ጊዜ የደመወዙን ከፍ ማለት እያስተዋልን ነው። መሬት ላይ ያለውስ ሁኔታ ምንድን ነው ሲባል ልክ የዛሬ 16 እና 17 ዓመት ሲደረግ እንደነበረው አይነት ኑሮ ሰራተኛው ይኖራል። ይህን ያመጣው የዋጋ ግሽበቱ ነው እንጂ የወር ደመወዙ ከዛሬ 16 እና 17 ዓመት በፊት ከነበረው ጋር ሲተያይ በብዙ ጨምሯል። ይህ እንዴት መጣ ሲባል የሰው ጉልበትም ደመወዝም ሲጨምር ዋጋም በዛው ልክ ነው መጨመር ያለበት ይላሉ።
ሌላው ትርፍ ከማግበስበስ የመጣ ነው፤ሰዎች የሚነግዱ ከሆነና ንግድ መኖር ካለበት ማትረፍ መቻል አለባቸው። ነገር ግን ከእኛ አገር ነባራዊ ሁኔታ ጋር አያይዘን የምናይ ከሆነ ስግብግብነት ይጨመርበታል። በአቋራጭ በቶሎ ለመበልጸግ የሚደረግ ሩጫ ይስተዋላል።ማለትም ከሌሎቹ ነጥቆ የመበልጸግ ፍላጎት አሁንም የዋጋ ግሽበቱን ከቁጥጥር ውጭ እንዲሆን አድርጎታል።
በሌላ በኩል ደግሞ እኛ አገር በደንብ አለ ብዬ የማስበው፤ሰዎች በእጃቸው ላይ ያለውን እቃ ለመሸጥ ብሎም ገበያ ለመሳብ ነው ጥረት የሚያደርጉት። በእርግጥም ንግድ መሆን ያለበት እንደእርሱ ነው። ከብዙ ሽያጭ ትንንሽ ትርፎችን እያገኙ ብዙ ትርፍ ነው ማግኘት ያለባቸው። አሁን ግን ሰዎች ለመሸጥ እንኳ እምብዛም አይጨነቁም። በተለይ ለረጅም ጊዜ መቆየት የሚችል አይነት እቃ ከሆነ ብዙ ለመሸጥ አይጨነቁም። ምክንያቱም በአዕምሯቸው ውስጥ ይጨምራል የሚል ግምት አላቸውና ነው። ችግር የለም፤ ይቀመጥ፤ ነገ ይጨምራል የሚል አካሄድ ደግሞ በጣም አደገኛ ነው።
እንደዚህ አይነት አካሄድ ወደባህልነት እየተሸጋገረ ነው፤ ለምሳሌ አንድ እቃ ማታ ከተገዛበት ሱቅ ጠዋት በዛው ዋጋ ለመግዛት ሲጠየቅና ዋጋው ጨመረ ሲባል ምንም የሚሰማን እንግዳ ነገር አይኖርም፤ ጨመረ ደግሞ ብለን ነው የምንገዛው። ምክንያቱም በሰው አዕምሮ ውስጥ ይጨምራል የሚል ግምት ስለነገሰ ነው። በየትኛውም መልኩ የሚባለው ይቀመጥ ይጨምራል ነው፤ ለምን እንደሚጨምርና እንዴት እንደሚጨምር ለማብራራት እንኳ ጊዜ የሚሰጥ የለም ሲሉ ይናገራሉ።ሸማቹ ማህበረሰብም አምኖ የተቀበለው ጉዳይ በመሆኑ ለምን ብሎ አይጠይቅም።በመሆኑም ይህ ሁኔታ የዋጋ ግሽበትን አምጥቷል።
ሌላው ከበቂ በላይ ገንዘብ ወደገበያው የተረጨ መሆኑ በራሱ የዋጋ ግሽበትን አምጥቷል። በኢኮኖሚው ውስጥ የሚዘዋወረው ገንዘብ የተረጨ ነው የሚል አተያይ አለኝ። ይህን ያስባሉኝ ምክንያቶች አሉ።ለምሳሌ ከሚንቀሳቀሰው ገንዘብ ሲታይና ካለው የፋይናንስ ተቋማት እንቅስቃሴም በመነሳት ነው። በተለይ ደግሞ ለምሳሌ የቁጠባና የብድር ወለድ ቢታይ በተለመደው የባንክ ስርዓት የቁጠባና የብድር ወለድ እኩል መሆን የለበትም፤ ነገር ግን እጅግ በጣም የተራራቁ ናቸው።
በአሁኑ ሰዓት ባንክ ነው ማስቀመጥ የምፈልገው የሚል ሰው እጅግ በጣም ትንሽ ነው የሚሆነው፤ ምክንያቱም ባንክ ሲያስቀምጥ እንደሚመስለኝ የሚያገኘው ሰባት በመቶ ነው። ይህ ደግሞ አሁን ካለው የዋጋ ግሽበት ብዙ ብር ባንክ እያስቀመጥን በሄድን ቁጥር ብዙ እያጣን እንሄዳለን ማለት ነው። ስለዚህ ሰው በእጁ ላይ ያለውን ገንዘብ የመጠቀም ሁኔታ ነው ያለው፤ በእጅ ላይ ገንዘብ ማኖር የሚያመጣው ደግሞ ወደ ገበያው ገንዘብ መርጨትን ነው። ወደ ኢኮኖሚው ብዙ የሚንቀሳቀስ ገንዘብ ከገባ ደግሞ በተዘዋዋሪ ለዋጋ ግሽበቱ የራሱን ሚና ይጫወታል ይላሉ።
በሌላ መልኩ ደግሞ የምግብና የነዳጅ አቅርቦት ዋጋ መጨመር በብዙ የእኛ ብር ትንሽ ዶላርን እንዲያባርሩ ማድረግና የእኛ ገንዘብ በየጊዜው የመግዛት አቅሙ እንዲወርድ ያደርጋል። ይህ የብር አቅም መውረድ እንደ እኛ አገር ባሉ አገሮች ላይ ሰው የዶላር ዋጋን ባንክ የሚለውንና በጥቁር ገበያ የሚባለውን እንዲያውቅ አድርጎታል። ሰው ይበልጥ የሚከተለው ደግሞ የጥቁር ገበያውን ሆኗል። ይህ ደግሞ ለምሳሌ ባንክ 50 ቤት ቢገባና ጥቁር ገበያ ላይ ደግሞ 80 ቢገባ ይህን ወዲያውኑ ነጋዴው ወስዶ ሸማቹ ማህበረሰብ ላይ ነው የሚጭነው። ይህም ለዋጋ ግሽበቱ እጅግ በጣም የራሱ የሆነ ድርሻ አለው።
ይህም ሊሆን የቻለው የእኛ በምግብ ላይ በተለይ በግብርና ላይ በተገባን ልክ አለመስራታችንና እርሻችንም በዝናብ ላይ ተንጠልጣይ መሆን ሲሆን፣ ይኸውም አንድ ጊዜ በድርቅ ሌላ ጊዜ ደግሞ በጎርፍ የመመታቱ ጉዳይ አቅርቦትና ፍላጎት ላይ አለመመጣጠን እንዲፈጠር ያደርገዋል። ከዚህም የተነሳ የዋጋ ግሽበቱን በየጊዜው እንድናይ አድርጎናል ሲሉ ያብራራሉ።
ዶክተር አደሬ፣ የመጀመሪያው መፍትሄ ነው ብለው ያብራሩት፤ ሞኒተሪ ፖሊሲ ላይ መንግሥት አሁን እያደረገ ያለውን በደንብ አጥብቆ መቀጠል መቻል አለበት ሲሉ ነው። መንግሥት አሁን ብዙ የገንዘብ እንቅስቃሴዎች በባንክ እንዲሆኑ አድርጓል። ቀደም ሲል ኢ-መደበኛ በሆነ ሁኔታ ሲንቀሳቀስ ገንዘብ ኢኮኖሚው ውስጥ ሲረጭ ነበር። አሁን አሁን ግን መንግሥት ሰዎች በባንክ እንዲጠቀሙ እያበረታታ ነው። ነገር ግን ብዙ ሰዎች ቅሬታ ያሰማሉ። ቅሬታው በፊት ከነበረውና ከምናውቀው ነባራዊ ሁኔታ ስለሚለይ እና ምናልባትም አዲሱ ሊመቸን አይችልም ብለው ከማሰብ የመጣ ነው።
ይሁን እንጂ የገንዘብ እንቅስቃሴዎች በባንክ እንዲሆኑ መደረጉና ያንን መተግበሩ የዋጋ ግሽበትን ለመቆጣጠር የሚረዳ ነው። ይህ ደግሞ በብዙ አገሮች ላይ እየተተገበረ ያለ እንቅስቃሴ ነው። ይህ በእርግጥ በአጭር ጊዜ ውስጥ የዋጋ ግሽበቱን ይቆጣጠራል ማለት ሳይሆን በረጅም ጊዜ ትግበራ የሚያስተካክል ይሆናል የሚል እምነት አለኝ ሲሉ ይጠቁማሉ።
ሁለተኛውን መፍትሄ ሲናገሩ ደግሞ መንግሥት ወጪውን መቀነስ መቻል አለበት ይላሉ።መንግሥት በዚህ ላይ ጥሩ የሚባል እምርታ አሳይቷል። ጥሩ ተሞክሮዎችና ጥሩ እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ ነው። ለምሳሌ መንግሥት ቢሮዎችን ወደ አንድ የማምጣት፤ በውጭ አገር ያሉ አንዳንድ ቆንስላ ጽህፈት ቤቶችን እንደየአስፈላጊነታቸው በከፊል የመቀነስ ነገር ሲያደርግ ወጪዎችን እንደመቀነስ ነው፤ ወጪ ሲቀነስ የትኩረት አቅጣጫው የዋጋ ግሽበቱን ወደማረጋጋት ማስኬድ ነው። ስለሆነም መንግሥት እነዚህን ጉዳዮች በተጠናና በተጠናከረ ሁኔታ ማስቀጠል አለበት፤ አንድ ጊዜ ጀምሮ የሚያቆመው መሆን የለበትም።
ሶስተኛው ደግሞ የቁጠባ ኢንተርስት ሬት ሲሆን፣ የቁጠባ ኢንተርስት ሬት በአንድ ጊዜ ሳይሆን ቀስ በቀስ መጨመር መቻል አለበት የሚል አስተያየት አላቸው። ሰዎች በመቆጠባቸው የሚያጡ ከሆነ ገንዘባቸውን ወደባንክ አምጥተው ከመቆጠብ ይልቅ ወደማጥፋት ነው የሚሄዱት። ስለዚህ ቀስ በቀስ በጥንቃቄ ተግባራዊ መደረግ መቻል አለበት።
በእርግጥ በአንድ ጊዜ ኢንተርስት ሬት የሚጨመር ከሆነ ግን ሰው ያለውን ገንዘብ በሙሉ ባንክ ያስቀምጥና በወለድ መኖር ይጀምራል። ምክንያቱም ገንዘብ ባንክ ሲቀመጥ ለባንክ እዳ ነው፤ በመሆኑም ባንኮቹን ደግሞ ሌላ እዳ ውስጥ እንዳንጥል በጥንቃቄ ቀስ ቀስ በማድረግ ምላሽ መስጠት በሚያስችል መልኩ ተግባራዊ ቢደረግ መልካም ነው።ከዚህ ጋር ተያይዞ የአከፋፈል ስርዓታችን መሻሻል መቻል አለበት፤ በተለይ ከካሽ ወደ መስመራዊ አከፋፈል ስርዓት መሄድ ተመራጭ ነው። አሊያም ገንዘብ በእጃችን ካለ ለማውጣት እንገፋፋለንና መንግሥት እዚህ ላይ የተጠናከረ ሥራ ቢሰራ ጥሩ ነው ብለዋል።
ደክተር አደሬ፣ አራተኛው መፍትሄ ብለው ያስቀመጡት ግብርናችን ላይ መስራት የሚለውን ነው። ምርትና ምርታማነትን እጅግ በጣም ማዘመን አለብን።120 ሚሊዮን ህዝብ የሚመግብና ለብዙዎቹም የሥራ እድል የፈጠረ በመሆኑ ዘርፉ ላይ መስራት በርካታ ነገሮችን የሚቀይር ነው በማለት ያስረዳሉ። መንግሥት የግል ዘርፉንና ግብረ ሰናይ ድርጅቶችን በአንድ ላይ በማስተባበር ምግብ ማከማቸት ላይ መስራት አለበት። ምግብን ማከማቸት የሚቻለውን ማንኛውንም ምግብ ነክ ነገር ማከማቸት ያስፈልጋል። ከተከማቸ ክፍተት ወደታየበት አካባቢ በቀላሉ ማንቀሳቀስ ስለሚቻል የዋጋ ግሽበቱን መቀነስ ይችላል።
በመጨረሻ ግን ይህ ሁሉ ተደርጎ ነገሮች መስመር እስኪይዙ ድረስ በከተማው ይሁን በገጠር ላሉ በጣም ደሃ ለሆኑት የማህበረሰብ ክፍሎች ድጎማ መኖር መቻል አለበት። በተለይ ምግብና ለምግብ የሚውሉ ግብዓቶችን መንግሥት ቢደጉም መልካም ይሆናል ሲሉ ይመክራሉ።
በመፍትሄነት የተቀመጡትን ጉዳዮች ተግባራዊ ለማድረግ የምንቸገር አይመስለኝም የሚሉት የምጣኔ ሀብት ባለሙያው፣ ደግሞም ከእኛ አቅም በላይ አይሁንም የሚል እምነት ስላለኝ የከፋ ነገር አይገጥመንም ብዬ አምናለሁ ብለዋል። እንደ አገር መቀጠል ካለብን መረጋጋት ሰፍኖና ሁሉም ሰው በሰላም መኖር እንዲችል የምንፈልግ ከሆነ ከላይ በተጠቀሱት መፍትሄዎች ላይ የማንሰራበት ምክንያት የለንም ብለዋል።ከእኛ አቅም በላይ የሆኑ ነገሮች አሉ፤ ለምሳሌ የነዳጅ ዋጋ አንዱ ነውና ይህን ለመቋቋም ግን ለምሳሌ ግብርናችን ላይ በደንብ ብንሰራ መለወጥ እንችላለን። በተጨማሪም ሞኒታሪ ፖሊሲያችንም ላይ የምንሰራ ከሆነ የዋጋ ግሽበቱ የማይቀንስበት ሁኔታ የለም ሲሉ አስረድተዋል።
አስቴር ኤልያስ
አዲስ ዘመን ግንቦት 30/2014