በጎ ፈቃድ አገልግሎት በዓለም፣ በአህጉርና በአገር ደረጃ ባህል ተደርጎ መሠራት ከጀመረ በርከት ያሉ ዓመታት ተቆጥረዋል።በተለይም እንደ አህጉር አፍሪካ የተሻለ ሥራ እንደምታከናውን ይጠቀሳል።ከአፍሪካ ደግሞ ቀድሞ ባህሏ ያደረገችው ኢትዮጵያ ድንቅ ብቃቷን እንዳሳየች ሰሞኑን ይፋ የተደረገው ሪፖርት ያመላክታል።በተፈጥሮ ልበ ሩህሩህና አንጀተ እንስፍስፍ በሆኑ ሴቶች መጀመሩ ደግሞ እንድትጎላ ካደረጓት መካከል ይጠቀሳል።
ጅማሮው በአሜሪካን አገር እንደነበር ይወሳል።ምክንያቱ ደግሞ የእርስ በእርስ ጦርነት ወቅት ‹‹የፈቃደኛ ቡድን›› የተሰኘ ስያሜ ያላቸውና ቁጥራቸው የተበራከተ ሴቶች ለወታደሮችና ለጦር ጉዳተኞች ጊዚያቸውን ሰውተው ነፃ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት መስጠታቸው ነው።እኤአ በ1881 ባርተን የአሜሪካ ቀይ መስቀልን ሲመሰርት እኤአ በ1889 ደግሞ በጆንስተውን የውሃ መጥለቅለቅ ለተጎዱ ሰዎች እርዳታዎችን በማሰባሰብ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተጀምሯል። በዚህ ተሳትፎ ከሌሎች የሕብረተሰብ ክፍሎች ይልቅ ሴቶች አይነተኛ ሚና ተጫውተዋልና ነው።ለዚህም ነው በጎ ፈቃድ አገልግሎትን ሴቶች ጀምረውታል የሚባለው።
አሁን ላይ በዓለም ደረጃ በአገልግሎቱ ዙርያ ሴቶች እያደረጉት ያለው አስተዋጾ ብዙ ነው። እሩቅ ሳንሄድ በአገራችን ውስጥ ብቻ ብዙ ሩህሩህና ደጓሚ ሴቶችን በብዛት እንመለከታለን።በለውጡ ዓመታት ብቻም የሴቶችን ድጋፍ ብናይ ከሌላው የማህበረሰብ ክፍል የተለየ እንደሆነ መናገር ይቻላል።ምክንያቱም ሴቶች በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ውስጥ የሚሳተፉት ያለምክንያት አይደለም።በብዛት ተጎጅም ተጠቃሚም ስለሚሆኑ ነው።
በአራዳ ክፍለ ከተማም ሆነ ሠሜን ማዘጋጃ አካባቢ የዶሮ ተራ መንደርተኛ የሆኑት ወይዘሮ ተዋበች አንዳርጌ ለዚህ ትልቅ ማሳያ ናቸው።ምክንያቱም እርሳቸው የዚህ አካባቢ በጎ ፈቃድ አገልግሎት አንቂ ናቸው።ሥራ በማስተባበር አይነተኛ ምሳሌም እንደሆኑ ይነገርላቸዋል።ከዚህ ጋርም ተያይዞ እንዳሉን፤ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ባህሉ ለኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊያን አዲስ አይደለም።ሁልጊዜ በአገር ጉዳይ ማንም ወደኋላ አይልም።ለዚህም ማሳያው የአካባቢያችን ሴቶች በጥፋት ኃይሉ ጉዳት ለደረሰባቸው ሰዎች አለሁላቸሁ ማለታቸው ነው።ለመከላከያም ቢሆን ከልጆቻቸው ጉሮሮ ቀንሰው የሰጡ መሆናቸው በጎ ፈቃደኝነታቸውን ያሳየናል።
‹‹በድንበር ተሻጋሪ በጎ ፈቃድ አገልግሎት እንደ ሶርያ የፈረሱ አገር ዜጎች ጭምር መደገፍ አለባቸው ብዬ አምናለሁ›› የሚሉት ወይዘሮ ተዋበች፤ ከአዲስ አበባ ከተማ አልፈው በሰሜን ሸዋ ዞን ደብረ ብርሃን ከተማ ተጠልለው ለሚገኙና ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉ ወገኖች 14 ኩንታል ምግብና የተለያዩ ቁሳቁሶች በግላቸው አሰባስበው የሰጡ ናቸው። በዚህ ደግሞ እሳቸው የሚኖሩበት ህንፃ (ብሎክ) 81 እማወራዎች በተግባሩ ሲሳተፉ መቆየታቸውንም አውስተውናል።
‹‹ሴቶች በችግር የበለጠ ተጎጂና ተጋላጭ ናቸው›› ያሉን ወይዘሮ ዘሀራ ጀማል በበኩላቸው፤ በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተሳታፊና ተጠቃሚነት ቀዳሚዎቹ ሴቶች መሆናቸውን ያስረዳሉ።ለዚህም በማስረጃነት የሚጠቅሱት በ1967 ዓ.ም የተደረገው የዕድገት በሕብረት ዘመቻን ነው።እርሳቸውም አንዷ እንደነበሩ ያነሳሉ።ምክንያቱም 12ኛ ክፍልን ማጠናቀቅ በጎ ፈቃድ አገልግሎቱን መስጠት ሲቻል ብቻ ነው።በዚህም ወጣቶች ሴቶችን ጨምሮ ወደ ሁሉም የአገሪቱ ገጠራማ ክፍል ተልከው አገልግሎቱን ይሰጣሉ።
እናት አርበኛ የሺእመቤት ምህረቴ ሴቶችን ማበርታት የሚችለው በጎ ፈቃድ አገልግሎት እንደሆነ ይናገራሉ።ምክንያቱም እርሳቸውን በሕይወት እንዲቆዩ ያደረጋቸው ይህ አገልግሎት እንደሆነ ያውቃሉ።እንደውም ‹‹ ይሄን ያደርግልኛል የምለው ልጅም ሆነ ዘመድ የለኝም። ዕድሜዬ በመግፋቱ አቅሜም ደክሟል። ከበሽታው ጋር ተጋግዞ አሁን ላይ ከአልጋዬ መውረድ ተስኖኛል። ሆኖም የአካባቢው ሴቶች ይመግቡና ይንከባከቡኛል። በተለይ ወጣቶች ክረምት በመጣ ቁጥር ቤቴን ይጠግኑልኛል። ዐውድ ዓመትም ሲሆን የሚያስፈልገኝን ያደርጉልኛል።እናም ክረምት የበጎዎች መፍለቂያ ነው፡፡›› ይላሉ።
የሁሉም እናቶች አስተያየት በበጎ ፈቃድ አገልግሎት የበለጠ ተሳታፊም ተጠቃሚም የሆኑት ሴቶች መሆናቸውን ያመላክታል። ሆኖም የመጀመርያው የዓለም በጎ ፈቃድ አገልግሎት በተባበሩት መንግስታት ሥር እ.ኤ.አ ታህሳስ 5 ቀን 2011 በዓለም ዙርያ የሚገኙ 80 አገራትን አቅፎ በአሜሪካ ኒዮርክ ሲቋቋም ዓላማ ያደረገው ጾታ ሳይለይ በአጠቃላይ የሰው ልጆችን መታደግ፣ ማገዝና መደገፍ እንደሆነ ባለፈው ሳምንት ይፋ የተደረገው በአራተኛው የዓለም የ2022 የበጎ ፈቃደኝነት ሪፖርት አስታውሷል።
‹‹እኩልና ሁሉን አቀፍ ማህበራትን መገንባታ›› በሚል መሪ ሀሳብ በአፍሪካ ሕብረተሰብ መካከል እኩልነትና አካታችነትን ታሳቢ አድርጎ የቀረበው ሪፖርት እንደሚያመለክተው፤ አገልግሎቱ የሴቶች ተጠቃሚነትን በጉልህ የሚያረጋግጥ ነው።
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትሯ ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ በመርሐ ግብሩ ላይ እንደተናገሩት፤ ከጥንት ጀምሮ በደቡብ አፍሪካ ኡቡንቱ በኢትዮጵያ ደቦ፣ ጂጌ፣ ወንፈል እየተባለ በእርሻ ወቅት በአረማ፣ በአጨዳ፣ በምርት ስብሰባ በድንገተኛ ተፈጥሯዊ አደጋ ሲከናወን የኖረው በመተጋገዝ መንፈስ የተቃኘ ነፃ አገልግሎት ነው።ይህ ደግሞ የበለጠ ሴቶችን ያሳትፋል።ከ2020 እስከ 2021 በኢትዮጵያ 21 ሺህ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች የተለያዩ የልማት ሥራዎችን አከናውነዋል።
ችግኝ ተከላ፣ ለአንደኛና ለሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች የማጠናከርያ ትምህርት መስጠት፣ ትራፊክ አገልግሎት፣ ስንቅ ዝግጅት፣ በጦርነት ለተጎዱ ወገኖች አልባሳትና ቁሳቁስ ማሰባሰብ፣ የአረጋዊያንን እና የአቅመ ደካሞችን ቤት ማደስ ካከናወኗቸው መካከል ይጠቀሳሉ የሚሉት ሚኒስትሯ፤ ከእነዚህ ወጣቶች ውስጥ በርከት ያለውን ቁጥር የሚሸፍኑት ሴቶች መሆናቸውን ተናግረዋል።
እንደ ሚኒስትሯ ገለጻ፤ እነዚህ ወጣቶች ለ38 ሚሊዮን ሕዝብ አገልግሎት ሰጥተዋል። እዚህም ጋር በጦርነት፣ በአውሎ ነፋስ፣ በሌሎች ሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ አደጋ ክስተቶች የበለጠ ተጎጂና ተጋላጭ የሚሆኑት ሴቶች እንደመሆናቸው በአገልግሎቱ አብዛኛው ተጠቃሚም ነበሩ።አገልግሎቱ በገንዘብ ሲተመን ከሰባት ቢሊዮን ብር በላይ ይሆናልም። ይሄን ያህል ወጪ ማዳን እንደ ኢትዮጵያ በማደግ ላይ ላሉና ብዙ የልማት ሥራዎችን ማከናወን ለሚጠበቅባቸው የአፍሪካ አገራት በቀላሉ የሚታይ አይደለም።
በጎ ፈቃድ አገልግሎት 50 በመቶ አንዳንዴም በላይ ሴቶች ባሉበት በአፍሪካ ሕብረተሰብ መካከል ጾታን ጨምሮ በሁሉም መስኮች እኩልነትንና አካታችነትን በማረጋገጡ ረገድ የጎላ ድርሻ ይኖረዋል። አፍሪካን በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከዓለም የተሻለ ደረጃ ለመድረስ በማስቻሉም በኩል የራሱን ጉልህ ሚና መጫወቱን ሪፖርቱ እንደሚያሳይ አንስተዋል።
ነፃ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በአፍሪካ በተለይም በኢትዮጵያ እንደ ባሕል በመያዝ የተለመደ እንጂ አዲስ አለመሆኑን የጠቀሱት ሚኒስትሯ፤ ይህ አገልግሎት በሕብረተሰቡ ውስጥ በነበረው የተዛባ አመለካከት ሳቢያ ለረጅም ዘመናት ከትምህርት ገበታ ርቀው የነበሩ ሴቶች የትምህርት ዕድል አግኝተው ከመሐይምነት የተላቀቁበት ነው ብለዋል።
እንደ ሚኒስትሯ ማብራሪያ፤ በ1967 ዓ.ም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ከመመረቃቸው በፊት ታላቅ ንቅናቄ በመፍጠር ባደረጉት ዘመቻ ሕዝቡን ከመሐይምነት ለማላቀቅ በነፃ ሲያስተምሩት ቆይተዋል። በዚህም በኢትዮጵያ እስከ 90 በመቶ በመድረስ ተንሰራፍቶ የነበረውን መሐይምነት በአንድ ጊዜ ወደ 37 በመቶ ማውረድ ተችሏል። ይህ ደግሞ የሴቶችን ተጠቃሚነት ያሰፋ ነበርም።
ዶክተር ኤርጎጌ እንደሚሉት፤ በለውጡ ዓመታት በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ አነሳሽነት ችግኝ በመትከል፤ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ለመከላከል እንዲሁም አቅመ ደካሞችንና ገቢያቸው ዝቅተኛ የሆነና ምንም ዓይነት ገቢ የሌላቸውን የሕብረተሰብ ክፍሎች በመንከባከብና በመደገፍ ረገድ አገልግሎቱ ከፊቱ በተሻለ ሁኔታ ላይ ደርሷል። ዘላቂና የተቀናጀ እየሆነም መጥቷል።በተለይ ከጥንት ጀምሮ ሴቶች በጦር ግንባር ከመሰለፍ በተጨማሪ አብዝተው በሚሳተፉበት የጦርነት ወቅት ስንቅ ዝግጅትና ደጀንነት ነፃ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት እንደ አገር ጉልህ ሚና መጫወት ተችሏል።
ዕውቀት፣ ጉልበትና ሀብትን በማቀናጀት አስደናቂና አመርቂ ውጤቶች እያስመዘገበ ያለውን የበጎ ፈቃድ አገልግሎት እንደ አገርም ሆነ እንደ አህጉር አቀናጅቶና ዘላቂ አድርጎ ለማስቀጠል እየተሰራ እንደሆነ ያነሱት ሚኒስትሯ፤ የኢትዮጵያ መንግስት እንደ አህጉር ሕብረተሰቡ እርስ በእርስ በልማትና እድገት ጎዳና የሚያስተሳሰርበትን የወጣቶች በጎ ፈቃድ አገልግሎት ፖሊሲ በ2004 ዓ.ም ማዘጋጀቱን እንደማሳያነት ጠቁመዋል።ሥራው አሁን ላይ አገልግሎቱን ተቋማዊ በማድረጉ ረገድ ያለውን ክፍተት ይሞላልም ብለዋል። እንደ አህጉርም በማስተሳሰር ዕውቅና ወደ የሚያገኝበት ደረጃ እንደሚያሸጋግረው፤ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት አሸናፊነቱንም እንደሚያጎላው ዕምነታቸውን ገልጸዋል።
በተባበሩት መንግሥታት የምስራቅና የደቡብ አፍሪካ አገራት ቀጠና የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ተጠሪ ሉሲ ዱንጉ በበኩላቸው፤ በጎ ፈቃድ አገልግሎት መንግስትና ትኩረት ያልተሰጣቸውን የማህበረሰብ ክፍሎችን የሚያገናኝ ድልድይ ነው። ምክንያቱም የተገለሉ ማህበረሰቦች ጋር በቀላሉ መድረስ ያስችላል ሲሉ የጥናት ግኝታቸውን ለታዳሚው አካፍለዋል።
በጥናታቸው እንዳመላከቱትም፤ አገልግሎቱ በአፍሪካ ሕዝቦች መካከል ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን፤ አካታችነትንና እኩልነትን ማምጣትና ማረጋገጥ የሚያስችል ነው።በተጨማሪም ትኩረት ያላገኙ የማህበረሰብ ክፍሎች በተለይም የሴቶችን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ለመፍታት አይነተኛ ሚናን ይጫወታል።በዚህም በአገልግሎቱ ኢትዮጵያ ከጥንት ጀምሮ ልምድ አላት። የተሻለችም ሆናለች።
ኢትዮጵያ መሐይምነትን በብዙ እጅ ከነበረበት መቀነስ ከቻለው የእድገት በሕብረት ዘመቻ ጀምሮ በሰው ሰራሽና በተፈጥሯዊ ክስተት አደጋዎችና ችግሮች ወቅትም ለሌሎች የአፍሪካና የዓለም አገራት አርአያ የሚሆን ልምድ ማካበቷንና በአገልግሎቱ አፈፃፀምም የተሻለች መሆኗን በጥናት ማረጋገጣቸውን የሚያነሱት ሉሲ፤ የዚህ ሁሉ ምክንያቱ ተግባሩ ከጥንት ጀምሮ በአህጉሩ እንደ ባህል ተይዞ መቀጠሉ እንደሆነም አስረድተዋል።
የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ጠቀሜታን አስመልክተው የተለያየ የዘር ስብጥር፤ አስተዳደግና አመለካከት ካላቸው ዜጎች ጋር አብሮ መሥራትና ልምድ መለዋወጥ ማስቻሉን የጠቆሙት ሉሲ፤ በጎ ፈቃደኝነት በዓለም አቀፍ ደረጃ ሰዎች በአካባቢያቸው የማሕበረሰቡን ሕይወት ለማሻሻል የሚያከናውኑት ተግባር ነው።ስለሆነም በጥናታቸው ተጠቃሚነትን ያረጋግጣልም ብለዋል።
እንደመንግስት ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶት እየተከናወነ እንደሚገኝ የገለፁት ደግሞ የሲቪል ማህበራት ድርጅቶች ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካ ሞላ ናቸው። እርሳቸው እንዳሉት፤ በኢትዮጵያ ውስጥ እንደ ማህበራት የበጎ ፈቃድ ሥራዎች በዓለም አቀፍና በብሔራዊ ደረጃ እየተሰሩ ይገኛሉ። ለአብነት ሮተሪ ኢንተርናሽናልን አንስተዋል። ኪዋንቪስ ኢንተርናሽናል፤ ሊዮን ኪውስ ኢንተርናሽናል፣ ጅብሊንግ ኢንተርናሽናል ድርጅቶች በ20ኛው ክፍለ ዘመን በመጀመርያዎቹ ዓመታት ተመስርተው የበጎ ፈቃደኝነት አውታርን ማስፋፋት የቻሉ ናቸውም ብለዋል።
እንደ አፍሪካ በተለይ በ2018 አገልግሎቱን ወደ ማህበረሰቡ በማውረድ ችግሮቹን እርስ በእርስ በመረዳዳት መቅረፍ የሚችልበትን አቅም መገንባት ተችሏል ያሉት አቶ ፋሲካ፤ እንደ ኢትዮጵያም ድሆችና አቅመ ደካሞችን ከመደገፍ ጀምሮ ደሳሳ ጎጆዎችን መጠገን፣ ችግኞች መትከልና ሰፋፊ እንደ እርሻ ያሉና ሌሎች የልማት ሥራዎችን በበጎ ፈቃድ አገልግሎት መስራት እንደተቻለ አንስተዋል።
ኢትዮጵያም ከአገር አልፎ በአፍሪካ አፈፃፀሟ የተሻለ የሆነውም በዚህ ምክያት እንደሆነ አብራርተዋል።እኛም ተግባሩ አብሮ ከመሥራትና ልምድ ከመለዋወጥ ባሻገር ሕብረተሰቡ በሴቶች ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት ያለውን የተዛባ ግንዛቤ ቀርፎ ለለውጥ ያድርገው በማለት ጽሑፋችንን ቋጨን።
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን ግንቦት 30/2014