የመጽሐፉ ስም፡- መሐረቤን ያያችሁ ደራሲ፡- ሙሉጌታ አለባቸው የገጽ ብዛት፡- 215 ዋጋ፡- 71 ብር ወጣቱ ደራሲ ሙሉጌታ አለባቸው በበርካቶች ዘንድ የሚታወቀው ለሕትመት ባበቃቸው «መሐ ረቤን ያያችሁ» በሚለው የልብ ወለድ መጽሐፍ ነው።ወጣቱ ደራሲ ከዚህ ቀደም «በአዲስ አድ ማስ» ጋዜጣ በቀድሞ «አዲስ ጉዳይ» መጽሄት በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ከሚታተሙት የህት መት ውጤቶች መካከል «በዘመን መጽሔት» እንዲሁም ቃና የቴሌቪዥን ፕሮግራም ተርጉሞ ከሚያስተላልፋቸው የውጭ ፊልሞች በተርጓሚነት በመስራት አሻራውን ያኖረ ወጣት የብዕር ጀብደኛ ነው።
ሙሉጌታ የመጀመሪያ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በወልዲያ፤ የከፍተኛ ደረጃ ትምህርቱን በሃዋሳ እና በአዲስ አበባ ተከታትሏል። በጋዜጠኝነት ፣ በተርጓሚነት ፣ በአርታዒነት እና በህዝብ ግንኙነት ዘርፍ እያገለገለም ይገኛል። በትርፍ ጊዜውም ስነጽሁፋዊ መጣጥፎችን እና ድርሰቶችን እንካችሁ ለንባብ ይለናል።
መጽሐፉ ምን ይዟል?
«መሐረቤን ያያችሁ» በ«ሕጽናዊነት» የአጻ ጻፍ ስልት በአሥራ ሁለት ምዕራፎች የተዘጋጀ የአጫጭር ልቦለዶች ስብስብ ነው። ሕጽናዊነት የአዳም ረታ ፈጠራ የሆነ ፍጹም ኢትዮጵያዊ የአጻጻፍ ስልት ሲሆን፤ ደራሲው አዳም ረታ ይህንን ስልት ለመፍጠር እንደ ሞዴልነት ተጠቅሞበታል። ስለ ሕጽናዊነት በጣም በአጭሩ ስንናገር ህጽናዊነት የአንዱ ከሌላው መያያዝ ማለት ነው። አንድ ገጸ ባህሪ ከሌላው ገጸ ባህሪ፤ አንዱ ሁነትም እንደዚሁ ከሌላው ሁነት በቀጫጭን መስመር የተያያዘ እንዲሆን አድርጎ የፈጠራን ሥራ የመስራት መንገድ ነው።
በገሃዱ ዓለም ሁሉ ነገር በግልጽ የሚታይ እና በስውር በተቀመጠ የግንኙነት መስመር በጥልፍልፎሽ የተሳሰረ በመሆኑ እውነታንበፈጠራ ሥራ ለመወከል ከሕጽናዊነት የተሻለ መንገድ ሊኖር እንደማይችል ደራሲውን ጨምሮ ብዙዎች ይስማማሉ። የመጽሐፉ ዘውግ አጭር ልቦለድ ቢሆንም እያንዳንዱ አጭር ታሪክ ከሌላው ጋር በቀጫጭን የታሪክ መስመሮች የተሳሰረ ስለሆነ የረጅም ልቦለድ ባህሪ አለው ማለት ይቻላል። አተራረኩ በተከሸኑ ገላጭ ቃላት በቦታው እና በሁነቱ ውስጥ ገብተን እንድንሳተፍ የሚያደርግ ነው። ስነ ጽሑፋዊ አጻጻፉ በጉልህ ይታይበታል።
ደራሲው ጋዜጠኛ ስለነበር ሁነቶችን ሲተርክ ልንም ሆነ ሲያሳይ ምንም ዓይነት የምንጭም ሆነ የታሪክ መዛባት እንዳያደርግ ረድቶታል። ምክንያቱም የአጻጻፍ ስልቱም ለእንዲህ ዓይነቱ ስህተት አይጋብዝም። በዚህ መጽሐፍ ውስጥ የደራሲው ሀሳብ ፣አቋም ወዘተ ብዙም አይታወቅም። የጽሑፉ አብዛኛው ክፍል ሀቅ በገላጭ ቃላት የተንሰላሰሉ ታሪክ እና ሁነቶችን ማስቀመጥ ብቻ ነው። እንዲያውም በዓይኑ ያያቸውን ነገሮች ራሱ በአንደኛ መደብ እኔ እያለ ይገልጻቸዋል። የደራሲው አቋም ምንም ይሁን ምን በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ገለልተኛ መሆኑ ለታሪክ ሆነ ለልብ ወለድ ጸሐፊዎች ጥሩ ትምህርት ይሆናል።
እንደሚታወቀው ሙሉጌታ አለባቸው ደራሲ ነው። ደራሲም ጋዜጠኛም ነበር። በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሲጽፍ ግን ከራሱ አተያይ ነጻ መሆኑ መጽሐፉን ሚዛናዊ ያደርገዋል። በመጽሐፉ ውስጥ ያለው እያንዳንዱ አጭር ታሪክ ከሌላው ምዕራፍ አጭር ታሪክ ጋር የሚያገናኝ ነገር ቢኖረውም ለእያንዳንዱ ታሪክ ያሰመረለት የሁነት የታሪክ እና የመቼት መስመር አስገራሚ ነው። ልቦለድ መሆኑ እንደተጠበቀ፤ በየትኛውም ምዕራፎች የታሪክ የጊዜም ስህተት አይታበትም፤ ከልቦለድ ጸሐፊ ደግሞ እንዲህ አይነት አድሎ አይጠበቅም። ትውልድን ማሳሳት ነው። በሌላ በኩል ደግሞ ሌላም ሰው ሊጽፈው ስለሚችል የሚጣረሰው ነገር ይበዛል።
ያኔ የታሪክ፣ የሁነት እና የመቼት ግጭት ይፈጠራል ማለት ነው። ሙሉጌታ አለባቸው የጣልናቸውን መልካም እሴቶቻችንን እንድናነሳ ባማሩ ቃላት በአስገራሚውየአጻጻፍ ስልቱ እንድናነሳም፤ እንድንነቃ ሸንቆጥ ያደርገናል። ዋቢ የሚሆኑ ሀሳቡን ለማንሳት ሽማግሌዎች በህብረተሰቡ ዘንድ ያላቸውን ተቀባይነት እና ከፍ ያለ ማህበራዊ ሚና፣ የፍቅር ኃያልነትን፣ የአብሮነት ብርታትን፣ የአገር እና የወገን ፍቅርን… ደራሲው እያዋዛ እንደጣልናቸው እና እንድናነሳቸው ይነግረናል። ከአንዳንድ የተውሶ ቃላት እና ሀሳቦች በቀር የቋንቋ አጠቃቀሙ እጅግ አስገራሚ ነው። በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ያለው እያንዳንዱ ታሪክ አሃድ ወይም አጭር ታሪክ በተከለለት ገጽ ወይም «ቴሪቶሪ» ተዘግቶ አይቆምም። እሱን ለመሰሉ ሌሎች አሃዶች ምኞት ክፍት ነው።
ከእያንዳንዱ አሃድ እየበረረ የሚወጣው የግንኙነት ዘሃ ከቁጣ፣ ከሳቅ፣ ከሃዘን፣ ከቃላት ዘዬ እንካሰላንቲያ ወዘተ የተፈተለ ነው። ለብቻው ፈዞ የሚቀር አሃድ፤ ለብቻው የሚጠናቀቅ አንድ ወጥ ታሪክ የለም። እያንዳንዱ ታሪክና አሃድ ደርዝ ነው። በዚህ መጽሐፍ ላይ ሙሉጌታ አለባቸው ከደራሲ አዳም ረታ ተዋስኩ ስለሚለው አጻጻፍ ስልት እራሱ አዳም ረታ «ይህ መጽሐፍ ነፍስ ያለው የአጻጻፉ ቅርጽ እና ይዘት «የብዕሩ አንደበት» ከፍቅር እስከ መቃብሯ ዲማ ጊዮርጊስ ከሕሊና ደውሏ ሱጴ ቦሩ ጎን ትቆማለች።
የሙሉጌታ ቋንቋ ውብ ነው። ይህ መጽሐፍ ሊናቅ የማይችል የአንድ ወጣት የስነ ጽሁፍ ጀብደኛ ዘራፍ ነው።» እንዲል አስገድዶታል። ሃሳቤን ከመቋጨቴ በፊት ስለዚህ መጽሐፍ አንድ ነገር ልበል። እንደማሳሰቢያም ጭምር ያዙት! መጽሐፉ የሁነት እና የታሪክ ሰነድ መጽሐፍ ነው። ደራሲው ከልጅነት ህይወቱ ከአደገበት አካባቢ እንዲሁም በዚያን ወቅት የነበሩ ሁነቶችን በቀንና በቦታ ግልጽ አድርጎ የሚያሳውቅ። እኔ እያለ ህይወትን፣ ባህልን፣ ታሪክን በምልሰት የሚያስኮመኩመን የደራሲው ሃሳብና ስሜት እንድንጋራው ያደረገበት ድንቅ የስነጽሁፍ ምሳሌ መሆን የሚችል ነው። ስለዚህ በዚህ መጽሐፍ ላይ ዳሰሳ ሳደርግ ከመጽሐፉ ገጽና ምዕራፍ እየጠቀስኩ ማስቀመጡ ምቹ አልነበረም።
ምክንያቱም የቱ ተጠቅሶ የቱ ይተዋል? በሌላ በኩል ደግሞ ይህ ሙያዊ አስተያየት ሳይሆን አስተውሎት ነው። በዚህ መጽሐፍ ላይ ውብ የሆነ የቋንቋ አጠቃቀም፣ ጥልቅ የሆኑ የሃሳብ እና የስሜት ትስስሮሽ፣ ከፍ ያለ ስነ ጽሑፍ ይዘት ያለው የቋንቋ መማሪያ መጽሐፍ ሊባል ይችላል። ስለዚህ ማለት የሚቻለው መጽሐፉ በተከሸኑ ገላጭ ቃላት የተጻፈ የደራሲው የበኩር ሥራው ነው፤ ስለዚህ መጽሐፉን እንዲያነቡት ጋበዝኩ። ሰላም!
አዲስ ዘመን መጋቢት 15/2011
በአብርሃም ተወልደ