የአገሪቱ ከተሞች በውስጣቸው ያለውን እምቅ ሃብት አሟጠው ባለመጠቀማቸው በአብዛኛው ከገጠር በሚቀርቡ የግብርና ምርቶች ላይ ጥገኛ ሆነው ይታያሉ፤ በዚህ የተነሳም የምግብ ዋስትና ችግሮችን በመሰረታዊነት ማቃለል እንዳልተቻለ ይገለፃል። በከተሞች ለከተማ ግብርና ስራ ሊውሉ የሚችሉ በርካታ ቦታዎች እንዳሉ ሲታሰብ ከተሞች በውስጣቸው ያለውን እምቅ ሀብት በሚገባ እንዳልተጠቀሙበት መረዳት ይቻላል።
መንግስትም የከተሞችን እድገት ዘላቂነት ባለው መንገድ ለማስቀጠል ይቻል ዘንድ የከተማ ግብርና ልማትን ተግባራዊ ማድረግ ውስጥ ገብቷል፤ ከዚህ ግብርና ህብረተሰቡን ከዘርፉ ተጠቃሚ ማድረግ እንደሚገባ ታምኖበት እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው። የከተማ ግብርና በከተማ ውስጥና በዙሪያው በአነስተኛ ቦታ ለምግብነትና ለሌሎች ጠቀሜታዎች ሊውሉ የሚችሉ እፅዋትን የማልማት፣ እንስሳትን የማርባት፣ የግብርና ምርት ውጤቶችን የማቀነባበር እና ለተጠቃሚዎች የማቅረብ ስራን ያካትታል።
ከዚህ አኳያም የኦሮሚያ ክልል የከተማ ግብርናን በመተግበር ረገድ በማሳያነት ሊጠቀሱ የሚችሉ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል። በክልሉ ግብርና ቢሮ የከተማ ግብርና አስተባባሪ ዶክተር ኑረዲን መሐመድ ስለክልሉ የከተማ ግብርና ስራዎች በተለይ ለ‹‹አዲስ ዘመን›› ጋዜጣ ማብራሪያ የሰጡትን ማብራሪያ ይዘን ቀርበናል።
የከተማ ግብርና ይዞታ በኦሮሚያ ክልል
አብዛኛው የአገሪቱ ማኅበረሰብ ኑሮው በግብርና ላይ የተመሰረተ በመሆኑ የግብርናውን ዘርፍ አቅምና ምርታማነት ማሳደግ ለጠቅላላ አገራዊ የምጣኔ ሀብት እድገት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ይኖረዋል። ክልሉ የግብርናውን ዘርፍ እድገት ለማሻሻል ብዙ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል። የግብርናው ዘርፍ ተሻሽሎ የአገሪቱን ምጣኔ ሀብት ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ ለማሸጋገር የተከናወኑ ተግባራት የሚፈለገውን ያህል ውጤት ስላላስገኙ ከለውጡ በኋላ የዘርፉን አቅም ሊያሳድጉ ለሚችሉ ዘዴዎች ላይ ትኩረት ተደርጓል።
አገሪቱ በዘርፉ ያላትን አቅም በአግባቡ ያለመጠቀም፣ ዘርፉን በቴክኖሎጂ አለማገዝና ኅብረተሰቡን ስለዘመናዊ ግብርና ተገቢውን እውቀት አለማስጨበጥ ከግብርና የሚገኘው ምርት በብዛትም ሆነ በጥራት በሚፈለገው ልክ እንዳይሆን ካደረጉ ምክንያቶች መካከል ይጠቀሳሉ። በከተሞችና በከተሞች ዙሪያ ያለውን መሬት ለግብርና በአግባቡ ያለመጠቀም የችግሮቹ አንዱ ማሳያ ነው። በተግባር የሚታየው የከተማ ግብርና ስራ ከተሞች ካላቸው አቅም አንፃር ሲመዘን አነስተኛ መሆኑ ተገምግሟል።
አብዛኞቹ የአገሪቱ ከተሞች ‹‹ከተሞች›› ቢባሉም እንዳደጉት አገራት ከተሞች ለመሆን ግን ብዙ ነገሮችን ያሟሉ አይደሉም። ብዙዎቹ የአገሪቱ ከተሞች ለግብርና ስራ የሚውል መሬት አላቸው። ትልቋ ከተማ አዲስ አበባ እንኳ ብዙ የግብርና ምርት ለማምረት የሚያስችል ቦታ አላት።
በከተሞች ውስጥ ከሚኖረው ሕዝብ መካከል ከ25 እስከ 45 በመቶ የሚሆነው ነዋሪ ራሱ በሚያከናውነው የከተማ ግብርና ስራ ተሰማርቶ ምግቡን ማምረት እንደሚችል ዓለም አቀፍ ጥናቶች ይመክራሉ። ትናንሽ መሬት ያላቸው ያደጉ አገራት ከተሞች እንኳ እስከ 45 በመቶ የሚሆነውን የምግብ ፍጆታቸውን የሚሸፍኑት ከከተማ ግብርና ስራ በሚገኝ ምርት ነው። ስለሆነም ከተሞቹ ለአረንጓዴ ልማት ብቻ ሳይሆን ለግብርና ልማት የሚያገለግሉ ሰፋፊ መሬቶችን የያዙ በመሆናቸው መሬቱን ተጠቅሞ ተጨማሪ የግብርና ምርት ማግኘት እጅግ አስፈላጊና ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ አለው።
የኦሮሚያ ክልል ‹‹ከተሞቻችን ሸምተው የሚበሉ ብቻ ሳይሆኑ የሚያመርቱም ጭምር መሆን አለባቸው›› በሚል መነሻና እሳቤ በአገር ደረጃ የተዘጋጀውን እቅድ በክልል ደረጃ ለመፈፀም ድርሻውን ወስዶ እየሰራ ነው። ከክልሉ የከተማ ግብርና ስራ ዋና ዋና ግቦች መካከል ከውጭ የሚገቡ የግብርና ምርቶችን በአገር ውስጥ ምርት መተካት፣ ምርቶችን ለውጭ ገበያ በማቅረብ የውጭ ምንዛሬ ገቢን ማሳደግ እና የሥራ እድል መፍጠር በቀዳሚነት ይጠቀሳሉ።
የኦሮሚያ ክልልም በዚህ ተጨባጭ ሁኔታ ላይ ተመስርቶ ስራውን የሚመራ አደረጃጀት በማዋቀር ወደ ስራ ገብቷል። ኅብረተሰቡ ስለከተማ ግብርና አዎንታዊ አመለካከት እንዲኖረው የግንዛቤ ማስጨበጫዎችን የመስጠት እንዲሁም ዘር እና የእርሻ መሳሪያዎችን የማቅረብ ተግባራት ተከናውነዋል። የከተማ መስተዳድሮች በከተማ ግብርና ስራ ላይ ለሚሰማሩ ግለሰቦች ድጋፍ እንዲያደርጉ አቅጣጫ ተቀምጧል። መሬት ቆጥቦ በብዛት የማምረት አሰራርን ለመተግር ጥረት እየተደረገ ነው። ይህን ለማሳካትም ከንቲባዎች፣ የግብርና ባለሙያዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ስልጠናዎችን እንዲያገኙ ተደርጓል።
19 የክልሉ ዋና ዋና ከተሞችን በመለየት ለከተማ ግብርና ምን ያህል አቅም እንዳላቸው ጥናት እየተከናወነ ነው። እነዚህ ከተሞች ከ40ሺ እስከ 50ሺ ሄክታር የሚታረስ መሬት እንዳላቸው ይገመታል። በ2013/2014 የክረምት ወቅት የምርት ዘመን ከከተማ ግብርና ስራ አንድ ነጥብ ሦስት ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት ታቅዶ ከአንድ ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ማግኘት ተችሏል። የኑሮ ውድነቱን ጫና ለማቃለል ይህንኑ ተግባር በበጋ ወራት በማስቀጠል 650ሺ ኩንታል አትክልትና ፍራፍሬ ለማምረት ታቅዶ 546ሺ 251 ኩንታል ማምረት ተችሏል። በመጀመሪያው ዙር ከተመረተው የአትክልትና ፍራፍሬ ምርት በተጨማሪ በሁለተኛው ዙር ደግሞ ከውጭ የሚገባውን ስንዴ በአገር ውስጥ ምርት ለመተካት የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ አንድ ሺ 126 ሄክታር ማሳ ላይ ከተዘራ ስንዴ 38ሺ 450 ኩንታል ተገኝቷል።
መሬትን በአግባቡ ለመጠቀም በተያዘው እቅድ መሰረት በትምህርት ቤቶችና በሌሎች የመንግሥት ተቋማት ውስጥ የሚገኝ መሬትን መጠቀም ተገቢ ሆኖ ተገኝቷል። በዚህም ለመነሻ ያህል በአዳማ ከተማ የሚገኙና መሬት ያላቸው 33 ትምህርት ቤቶችን በመለየት መሬት በማዘጋጀትና ውሃ የሌላቸውን የውሃ አቅርቦት በመስጠት ለእያንዳንዱ ትምህርት ቤት ዘር እንዲከፋፈል ተደርጓል። በ13 ትምህርት ቤቶች ላይ አትክልት የማልማት ስራ እየተከናወነ ነው። አቅመ ደካማዎችን በማደራጀት በስራው ላይ እንዲሰማሩም ተደርጓል።
በአሁኑ ወቅት በክልሉ ለዚሁ ተግባር የሚውል መሬት ያላቸው ትምህርት ቤቶች ተለይተው እንዲታወቁ ጥናት እየተካሄደ ነው። የመሬቱ መጠን ከማወቅ ጎን ለጎን የውሃ አቅርቦት አቅምም ምልከታ እየተደረገበት ነው። የተማሪዎች የግብርና ክበባት እንዲቋቋሙ በማድረግ ስራውን እንዲያውቁት እየተደረገም ነው።
በሌላ በኩል አርሶ አደሩ ከዚህ ቀደም በነበረው አሰራር ከመሬት ባለቤትነትና ከካሳ ክፍያ አንፃር ተገቢውን ጥቅም ባለማግኘቱ ያን ልምድ መቀየር እጅግ አስፈላጊ ጉዳይ ነው። ስለሆነም አርሶ አደሮቹንና ቤተሰባቸውን በማደራጀትና በማቀናጀት ኑሯቸውን የተሻለ እንዲሆን ለማድረግ የተከናወኑ ተግባራት አሉ። በዚህም የከተማ አስተዳደሮችን በማግባባት 147 ሚሊዮን ብር ተመድቦ በስምንት ከተሞች ላይ 38 ቤቶችን በመገንባት ለከተማ ግብርና ስራ (ለወተት ምርት፣ ለከብት ማድለብና ለዶሮ እርባታ) ተዘጋጅተዋል። ለአብነት ያህልም በአዳማ ከተማ ለወተት ምርት፣ ለከብት ማድለብና ለዶሮ እርባታ የሚሆኑ 10 ቤቶች ተሰርተዋል። በሌላ በኩል የተፈናቀሉ አርሶ አደሮችን በማደራጀት 30 በመቶ እነርሱ እንዲቆጥቡ፣ 70 በመቶውን ደግሞ መንግሥት እንዲመድብ በማድረግ ግብዓቶች እንዲሟሉ ተደርጓል። ይህም የአርሶ አደሮቹንና የከተሞቹን ትስስር በማጠናከር የአርሶ አደሮቹ ሕይወትና የከተሞች እድገት ተመጋጋቢ እንዲሆን ያግዛል።
ከወተት ልማትና ዶሮ እርባታ አንፃር እያንዳንዱ ከተማ ከአንድ በላይ የወተትና ዶሮ ልማት ማዕከላት እንዲኖሩት በማድረግ ከውጭ የሚገባውን ለመተካት እየተሰራ ነው።
የተገኙ ውጤቶች
የከተማ ግብርና ስራው ትኩረት ተሰጥቶት ከተሰራ ትልቅ ለውጥ ማስመዝገብ እንደሚቻል ያመለከቱ ተስፋ ሰጪ ውጤቶች ተመዝግበውበታል። ምርት ሳይመረትባቸው የኖረ መሬትን መጠቀም ተጀምሯል። በዚህም ተጨማሪ ምርት ማግኘትና ለገበያ ማቅረብ ተችሏል።
የከተማ ግብርና ስራው ለስራ እድል ፈጠራም አስተዋፅኦ አበርክቷል። በአንድ ሄክታር መሬት ላይ ከ20 እስከ 30 ሰዎች ስለሚሰማሩ ብዙ ዜጎች የሥራ እድል ተጠቃሚ ሆነዋል።
ስራዎቹን ለመጀመር አርሶ አደሮቹ 30 በመቶውን እንዲቆጥቡ ስለሚደረግ በሚፈለገው ልክ ባይሆንም ከዚህ ቀደም ከነበረው የቁጠባ ልምድ ጋር ሲነፃፀር የተሻለ የቁጠባ ልምድ እንዲኖር ምክንያት ሆኗል። አርሶ አደሮቹ 40 ሚሊዮን ብር እንዲቆጥቡ ታቅዶ 22 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር መቆጠብ ችለዋል።
አርሶ አደሩ ስለከተማ ግብርና ያለው አመለካከት እየተሻሻለ መጥቷል። ከዚህ ቀደም አርሶ አደሩ መሬቱን በመሸጥና በማከራየት ለመኖር ይፈልግ ነበር። አሁን ግን ‹‹አከራይቼና ሸጬ ከማገኘው የበለጠ ራሴ ሰርቼ ማግኘት እችላለሁ›› ብሎ በማሰብ ራሱ ወደማምረት ተግባር እየገባ ነው።
የአርሶ አደሩን ምርት ለገበያ አቅርቦ ተጠቃሚ እንዲሆንም በየከተሞቹ የሽያጭ ማዕከላትን በማደራጀት ምርቱን ያለምንም የገበያ ችግር ለሸማቹ እንዲያቀርብ እየተደረገ ነው። አርሶ አደሮቹ ዘንድሮ ያመረቱትን በጥሩ ዋጋ ሸጠዋል። በአንዳንድ አካባቢዎች አርሶ አደሮቹ በበሬ ከማረስ ወደ ትራክተር ስለተሸጋገሩ ምርታማነታቸው ጨምሯል።
የማኅበረሰቡን ኑሮ የሚያሻሻሉና የአካባቢ ጥበቃን የሚያጎለብቱ የተቀናጁ ስራዎች እየተከናወኑ ነው። ለምሳሌ በአዳማ አካባቢ ከተከናወነው የተፋሰስ ልማት ጎን ለጎን 200 ቀፎዎችን በማዘጋጀት የንብ እርባታ ስራም እየተሰራ ነው። ይህም ከንብ እርባታው የሚገኘው የማር ምርት ለኅብረተሰቡ ከሚሰጠው ጥቅም በተጨማሪ የአካባቢውን ስነ ምህዳር ለመጠበቅም ጥሩ አስተዋፅኦ ያበረክታል።
ስለከተማ ግብርና የኅብረተሰቡ ግንዛቤ
ኅብረተሰቡ ስለከተማ ግብርና የነበረው ግንዛቤ ደካማ ነበር። የኅብረተሰቡ ብቻ ሳይሆን የአመራሩና የባለሙያው አመለካከትም ደካማ ነበር። ኅብረተሰቡ ‹‹የግብርና ስራ ከተማ ላይ ይከናወናል እንዴ? ግብርና ገጠር ላይ የሚሰራ ስራ ነው …›› የሚል አመለካከት ነበረው። ጥናቶች ሲደረጉ፣ ስራው ሲጀመርና ውጤቶች ሲገኙ ግን አሉታዊ የነበረው አመለካከት እየተለወጠ መጥቷል። በስራው የተገኙ ውጤቶች ከተሞቹ ያላቸውን አቅም ያመላከቱ በመሆናቸው በአሁኑ ወቅት የከተሞች ከንቲባዎች የከተማ ግብርና ስራን ለማስፋት ከፍተኛ ፍላጎት እያሳዩ ነው።
ነገር ግን ኅብረተሰቡም ሆነ አመራሩ ስለከተማ ግብርና ያለውን አመለካከት የበለጠ ለማሳደግ ብዙ ስራዎች ይቀራሉ። ስራው ከተጀመረ በኋላ አርሶ አደሮች የሚያገኙት ምርት የተለያየ የሚሆነው አርሶ አደሮቹ ስለስራው በሚኖራቸው የአመለካከት ልዩነት ምክንያት ነው ተብሎ ይታሰባል።
ያጋጠሙ ችግሮች
የአመለካከት ችግር በስራው ሂደት ካጋጠሙና እያጋጠሙ ካሉ ችግሮች መካከል አንዱ ነው። ‹‹ግብርና ሰፊ መሬት ይፈልጋል። ከተማ ላይ የግብርና ስራ ማከናወን አይቻልም …›› የሚል አመለካከት በኅብረተሰቡም ብቻ ሳይሆን በአመራሩም ዘንድ ይስተዋላል። አመራሩን አሳምኖ ውጤታማ ስራ ለማከናወን ብዙ ውጣ ውረዶች ነበሩ። ከከተሞች ይገኛል ተብሎ የታቀደውን ገንዘብ በተገቢው ጊዜ ያለማግኘት ችግር ነበር።
አርሶ አደሩም ከዚህ ቀደም መሬቱን የማሸጥና የማከራየት ልምድ ስላለው ‹‹ አከራይቼና ሸጬ ከማገኘው የበለጠ ራሴ ሰርቼ ማግኘት እችላለሁ›› ብሎ በማሰብ ራሱ ወደ ማምረት ተግባር ለመግባት ሲቸገር ነበር። ለመስራትና ለመለወጥ ፍላጎት ቢኖረውም ፈጣን የአመለካከት ለውጥ በማምጣት ረገድ ችግሮች ነበሩ።
የቁጠባ ባህል ደካማ መሆንም ሌላው ችግር ነው። ስራዎቹን ለመጀመር አርሶ አደሮቹ 30 በመቶውን እንዲቆጥቡ ስለሚደረግ 40 ሚሊዮን ብር እንዲቆጥቡ ቢታቀድም ማሳካት የተቻለው ግን ግማሹን (22 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር) ነው። በእርግጥ በሚፈለገውና በእቅዱ ልክ ባይሆንም ከዚህ ቀደም ከነበረው የቁጠባ ልምድ ጋር ሲነፃፀር ግን የተሻለ የቁጠባ ልምድ ማስመዝገብ ተችሏል።
ዘንድሮ ዝናብ በወቅቱ ባለመጣሉ አትክልቶችን በክላስተር ለማልማት የተያዘው እቅድ እንዳይሳካ እንቅፋት ሆኗል። አሁን ባለው የዓለም የአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የተከሰቱ የአትክልትና ፍራፍሬ በሽታዎችም በምርት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ አሳድረዋል። ከሚቀጥለው ዓመት ጀምሮ የአትክልትና ፍራፍሬ በሽታዎችን ታሳቢ ያደረገ ዝግጅት ለማከናወን ታቅዷል። የዋጋ ንረት በከተማ ግብርና ግብዓት አቅርቦት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ያሳደረ ሌላው ችግር ነው።
ቀጣይ እቅዶች
የከተማ ግብርና ስራው ትኩረት ተሰጥቶት ከተሰራ ትልቅ ለውጥ ማስመዝገብ እንደሚቻል ያመለከቱ ተስፋ ሰጪ ውጤቶች ተመዝግበውበታል። ትናንሽ መሬት ያላቸው ያደጉ አገራት ከተሞች ከከተማ ግብርና ስራ በሚገኝ ምርት እስከ 45 በመቶ የሚሆነውን የምግብ ፍጆታቸውን መሸፈን ከቻሉ፣ ሰፋፊ መሬት ያላቸው የኢትዮጵያ ከተሞች ደግሞ የትምህርት ቤቶች፣ የአርሶ አደሮች ይዞታ ላይ እንዲሁም የኢንቨስትመንት ስራ ያልጀመሩ መሬቶችን ተጠቅመው ከዚህም የበለጠ ማሳካት እንደሚችሉ ግንዛቤ ተወስዷል።
ስለሆነም ከተሞች ያላቸውን የከተማ ግብርና አቅም በመጠቀም ስራውን ስኬታማ ለማድረግ የኦሮሚያ ክልል በከተማ ግብርና ዘርፍ እቅዶችን አዘጋጅቶ እየሰራ ነው። ከእቅዶቹ መካከልም ኅብረተሰቡ ስለከተማ ግብርና ያለው ግንዛቤ እንዲሻሻል ማድረግ፣ ከ50ሺ እስከ 60 ሺ ለሚሆኑ ዜጎች ቋሚ፤ ለ100ሺ ዜጎች ደግሞ ጊዜያዊ የስራ እድል መፍጠር እንዲሁም በአርሶ አደሩ እጅና በመንግሥት ተቋማት የሚገኙ መሬቶችን በመጠቀም ከ25 እስከ 45 በመቶ የምግብ አቅርቦትን ማምረት ዋናዎቹ ናቸው። ይህን ለማሳካትም ክልሉ እውቀትና ልምድ ያላቸውን ባለሙያዎችን በማሳተፍ ስራው የተሟላ አፈፃፀም እንዲኖረው ጥረት እያደረገ ነው።
አንተነህ ቸሬ
አዲስ ዘመን ሰኞ ግንቦት 29 ቀን 2014 ዓ.ም