ኢትዮጵያ የዜጎቿን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ እያከናወነቻቸው ካሉ የልማት ሥራዎች ጎን ለጎን የምግብና ሥነ-ምግብ ሥርዓቱን (ኒውትሪሽን) ትራንስፎርም ለማድረግ ርብርብ እያደረገች ትገኛለች። በተለይም ደግሞ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን ዘላቂ የልማት ግቦች ለማሳካትና የፓሪሱን የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ስምምነት በተቀመጠው የጊዜ ገደብ ለማከናወን ያስችላት ዘንድ ከመቼውም ጊዜ በላይ ከሚመለከታቸው አጋር አካላት ጋር ተቀናጅታ እየሠራች ነው።
ከኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ያገኘነው መረጃ እንደሚያመለክተው፤ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በምግብ ሥርዓት ላይ መሥራት የ2030 ዘላቂ ልማት ግቦች ትግበራን ለማፋጠን እና ለውጥ ለማምጣት ትልቅ እድል ነው ብሎ ያምናል፤ ለእዚህም እ.ኤ.አ በመስከረም 2021 የምግብ ሥርዓት ጉባኤ በኒውዮርክ አካሂዷል። የጉባዔው ዓላማ ጤናማ፣ ዘላቂ እና ፍትሐዊ የሆነ የምግብ ሥርዓትን ለማሳካት ሀገራት የምግብ ሥርዓታቸውን መቀየር እንዳለባቸው የሚያስገነዝብ ነው።
ኢትዮጵያም የመንግሥታቱ ድርጅት አባል እና የጉባኤ ተሳታፊ እንደ መሆኗ ይህን የቤት ሥራ ወደ ሀገር ቤት በማምጣት ከተባበሩት መንግሥታት የምግብ ሥርዓት ማሕቀፍ እና ከዘላቂ ልማት ግቦች ጋር የተጣጣመ አጠቃላይ የምግብ ሥርዓት እና ኒውትሪሽን Ethiopian Food System and Nutrition (EFSN) ፍኖተ ካርታ አዘጋጅታ በመተግበር ላይ ትገኛለች።
ይህ ፍኖተ ካርታ የኢትዮጵያን ሕዝብ የሚጠቅም በንጥረ-ምግብ የበለፀገ፣ ተደራሽ እና ተፈጥሯዊ የምግብ አሠራርን ለማጎልበት ያለመ ነው። የኢትዮጵያን የምግብ ሥርዓት ትግበራ እና ስኬታማነት በቅርቡ የተቀላቀለውን የሥራና ክህሎት ሚኒስቴርን ጨምሮ 16 ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶችን የያዘ ምክር ቤት ተቋቁሟል፤ መሥሪያ ቤቶቹም የሥራ ድርሻ የተከፋፈሉ ሲሆኑ፤ ምክር ቤቱን የግብርና እና የጤና ሚኒስቴር በጋራ ይመሩታል። የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ደግሞ የምክር ቤቱ ሴክሬታሪያት ሆኖ እየሠራ ይገኛል።
የኢትዮጵያ የምግብ ሥርዓትና ኒውትሪሽን መርሀ ግብር አስተባባሪ ዶክተር ከፈለኝ ጌታሁን እንደሚናገሩት፤ የኢትዮጵያ ምግብ ሥርዓትና ኒውትሪሽን ትልቅ አጀንዳ ነው። ሀገሪቱ ለአየር ንብረት የማይበገር የምግብ ሥርዓት በመዘርጋት ረገድ ከአፍሪካ ሀገራት አንፃር ብዙ ርቀት ተጉዛለች።
ከተጀመረ አራት ዓመታት በሆነው በእዚህ መርሃ-ግብር ለዘርፉ የተለየ ትኩረት በመስጠትና በተለያዩ መንግሥታዊ ተቋማት ሲከናወኑ የነበሩትን ሥራዎች ወደ አንድ በማምጣት በጋራ ተጨባጭ ውጤታማ ሥራ እየተሠራ ይገኛል። በተለይም በአረንጓዴ አሻራ፣ በሌማት ቱሩፋትና በስንዴ ልማት ሥራዎች እየተመዘገበ ያለው ውጤት፣ የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ ባለፈ ለዜጎች የተመጣጠነ ምግብ ተደራሽነት ወሳኝ ሚና እየተጫወተ ነው።
ይኸው የኢትዮጵያ ምግብ ሥርዓት ትራንስፎርሜሽን እና ኒውትሪሽን መርሃ-ግብር በሰባት ክላስተሮች ተከፋፍሎ እየተሠራ መሆኑን የሚናገሩት ዶክተር ከፈለኝ፤ ክላስተሮቹ በተለይም ደህንነቱ የተጠበቀ እና የተመጣጠነ ምግብ ስለመኖሩ እና ተደራሽነቱን የማረጋገጥ ሥራ በዋናነት እንደሚሠሩ ያስረዳሉ። ይህም ሲባል የሰብል ምርታማነትና ተደራሽነትን ከማሳደጉ ጎን ለጎን ሁሉንም ዜጎች ደህንነታቸው የተጠበቀ እና በንጥረ-ነገሮች የበለጸጉ ምግቦችን ተጠቃሚ ማድረግ ላይ እንደሚያተኩር ያስገነዝባሉ። ይህም ክላስተር በአምስት ለውጥ አምጪ የመፍትሔ ሃሳቦች ላይ በመመስረት አቅርቦት እና ተደራሽነት ላይ ለውጥ እንዲመጣ እንደሚሠራ ይናገራሉ።
ከእዚህም ባሻገር የኢትዮጵያን ብሔራዊ የምግብ ደህንነት አያያዝና ቁጥጥር ሥርዓት ማጠናከር፣ የአነስተኛ ይዞታ፣ የግሪን ሃውስ እና የጓሮ አትክልት ምርቶችን በማስፋፋት የተመጣጠነ እና በንጥረ-ነገር የበለፀገ ምግብ (ከእንስሳት እና ከዕፅዋት የሚገኝ) አቅርቦትን ለመጨመር መደገፍ፣ በኢንዱስትሪ የሚመረቱ ምግቦች ባዮ ፎርቲፊኬሽን በመጠቀም አልሚ ንጥረ ነገሮችን እንዲይዙ ማድረግ ሌላኛው በክላስተሩ ትኩረት ተደርጎ የሚሠራ ሥራ መሆኑን አመልክተዋል። እነዚህም ምግቦች አመራረት እና ፍጆታ ማሳደግ፤ ለአየር ንብረት ተስማሚ የእንስሳት እሴት ሰንሰለትን ማጠናከር እና የሀገር በቀል የምግብ ምርትና ሂደትን ማዘመን እና ማሻሻል መሆናቸውን ይጠቅሳሉ።
‹‹እነዚህ ለውጥ አምጪ የመፍትሔ፤ ሃሳቦች የምግብ ደህንነትን ለማሻሻል፣ የምግብ ምንጮችን ለማብዛት እና የተመጣጠነ ንጥረ ነገር አቅርቦትን በማጎልበት በኢትዮጵያ የሚስተዋሉትን የሥነ ምግብ ተግዳሮቶች ለመፍታት ያለሙ መሆናቸውንም ያስረዳሉ። ስልታዊ ትንተና እና አቀራረብን በማጠናከር፣ አዳዲስ አሠራሮችን በማስተዋወቅ እና የመንግሥትን ቁርጠኝነት በማጎልበት፣ ብሔራዊ የአመጋገብ መመሪያዎችን በማውጣት አስተማማኝ እና ቀጣይነት ያለው ግንዛቤ ለሕዝብ በማስጨበጥ ደህንነቱ የተጠበቀ እና የተመጣጠነ ምግብን ለማሻሻል እንደሚሠራ ያስገነዝባሉ።
ሦስተኛው ክላስተር ደግሞ በተቀናጀ ፖሊሲ እና ሥርዓት የግብርና ትራንስፎርሜሽንን ለማበረታታት ጥረት እንደሚረግ ዶክተር ከፈለኝ ያስረዳሉ። የመሬት አቅርቦት እና ባለቤትነት ገደብን፣ የፋይናንስ አገልግሎት ተደራሽነት እና ሌሎች ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ጉዳዮች በመፍታት ፈጣን የምግብ ሥርዓት ለውጥን ለማመቻቸት የተቀናጀ እና ወጥ የሆነ ፖሊሲን ለመተግበር ያለመ እንደሆነም ያብራራሉ።
እሳቸው እንዳስታወቁት፤ በአብዛኛው ፖሊሲዎች የሚዘጋጁት በመንግሥት በኩል ሲሆን፤ የሚስተዋለውን አነስተኛ የባለሙያዎች መስተጋበር ለማስፋት ይሠራል። የምግብ ሥርዓት አስተሳሰብ ለውጥን በኅብረተሰብ ዘንድ ለማምጣት በተለያዩ ፖሊሲዎች ለጋራ ጥቅም በጋራ መሥራት ያስፈልጋል። በጋራ መሥራት ፖሊሲ አውጪዎች የሚያወጧቸውን ፖሊሲዎች ተግዳሮቶችን እና እድሎችን አስቀድሞ ለማወቅ ያስችላል።
እንደ እርሳቸው ማብራሪያ፤ ሜካናይዜሽን ማፋጠን፣ የተሻሻለ ዲጂታል ቴክኖሎጂ እና ፈጠራን ማሳደግ ሌላኛው የመርሃ ግብሩ ትኩረት ነው። የኢትዮጵያ ምግብ ሥርዓት ትራንስፎርሜሽን እና ኒውትሪሽን ክላስተር የግብርና ምርታማነትን ለማሳደግ በሚያስችሉ የተሻሻሉ የዘር አይነቶች፣ የተሻሻሉ የእንስሳት ዝርያዎች፣ ማዳበሪያ፣ አግሮ ኬሚካሎች እና ረቂቅ ተህዋስያን አጠቃቀም ላይ ያተኩራል። በተጨማሪም በግብርና ሥራ ውስጥ ፈጠራን፣ የግብርና ማሽኖችን እና የመረጃ አገልግሎቶች ቴክኖሎጂዎችን መቀበልን ያበረታታል።
በተጨማሪም የሰብል ስፔሻላይዜሽን እና የምርት ኮሪደሮችን በመመስረት የግብርና ግብይትን ለማስፋፋት የአቅርቦት ሰንሰለት አስተዳደርን፣ የገበያ ተደራሽነትን እና የገበያ መረጃ ሥርዓትን ማሳደግ ላይ እንዲሁም በማህበረሰብ ላይ የሚደርስ አደጋ አመራር እና ዝቅተኛ ገቢ ያለው ማህበረሰብ ክፍል ጥበቃ ላይ ትኩረት ያደረጉ ክላስተሮችም አሉት። ይህም በኢትዮጵያ የምግብ ሥርዓት ውስጥ ያለውን ስጋት በብቃት በመቆጣጠር በመላ ሀገሪቱ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ አጋዥነቱ ከፍተኛ ነው።
ዶክተር ከፈለኝ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እና የምግብ ሥርዓት ባለድርሻዎች በተለይም አርሶ አደሮች ለአደጋ የተጋለጡ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ ‹‹ኮቪድ-19 ወረርሽኝ በሀገር አቀፍ ደረጃ በምግብ ሥርዓቱ ላይ የተመሰረቱ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ገቢ አደጋ ላይ ጥሎ ማለፉን በማስረጃነት መጥቀስ ይቻላል›› ይላሉ። በተጨማሪም የአንበጣ መንጋ በአርሶ አደሮች ገቢ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ የሚያሳድርበት ሁኔታ መኖሩን ያስገነዝባሉ። የክህሎት ልማትን፣ የቴክኖሎጂ ፈጠራ ማዕከላትን፣ የገጠር ኤሌክትሪፊኬሽን እና የከተሞች መስፋፋትን በማጠናከር ቀጣይነት ያለው እድገት ማምጣት ደግሞ በሰባተኛው ክላስተር ትኩረት ተደርጎ የሚሠራበት ስለመሆኑንም ያብራራሉ።
እነዚህ ስትራቴጂያዊ ጉዳዮች እድገትን ለማሳለጥ፣ ማህበረሰብን ለመደገፍ እና ለትልቅ ለውጥ ለማዘጋጀት የተነደፉ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ በተለይም ለአካባቢ ተስማሚ እና አየር ንብረትን ያገናዝቡ ቴክኖሎጂዎችን ለማስተዋወቅ የገጠር ኤሌክትሪፊኬሽን ማስፋፋት ሥራ ትልቅ ትኩረት እንደተሰጠው ይጠቁማሉ።
በተጨማሪም ያልተማከለ ከተሜነትን፣ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገሩ የበለፀጉ የከተማ ማዕከላትን፣ ተመጣጣኝ የመሬት አጠቃቀም እቅድን እና ዘላቂ ከተሞችን ለማፍራት የሚያስችሉ ስትራቴጂዎችን ማውጣት ሌላው እንደ መፍትሔ የተቀመጠ ጉዳይ መሆኑን ዶክተር ከፈለኝ ያብራራሉ። ዘርፈ ብዙ ክህሎቶችን ለመገንባት የሚያስችሉ ፈጠራዎችን ማጎልበት፣ ቴክኖሎጂዎችን ማፍለቅ እና የሙያ ማሰልጠኛ ማዕከላትን በማቋቋም ሀገሪቱ ዘላቂ የልማት ግቦችን በተቀመጠው የጊዜ ገደብ ለማሳካት ያስችሏታል ተብለው ከተለዩ ሥራዎች መካከል ዋነኞቹ እንደሆኑ ነው ያስገነዘቡት።
ዘላቂ የልማት ግቦችን ለማሳካትም ሆነ የፓሪሱን የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ስምምነት ተግባራዊ ለማድረግ በሚደረገው ጥረት የኢትዮጵያ የሥርዓተ ምግብ ሽግግርና ኒውትሪሽን መርሃ ግብሩ ወሳኝ ሚና እንዳለው በመገንዘብ ፈጣንና ቅንጅታዊ ሥራው ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ ያስገነዝባሉ። በእዚህ ረገድ እንደ ሀገር ከ16 ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶችና አጋር ድርጅቶች ጋር በቅንጅት የሚሠራው ይኸው የኢትዮጵያ ምግብ ሥርዓት እና ኒውትሪሽን የልማት መርሃ ግብር ሁሉም አካላት ተዋናይ ሆነው በኃላፊነት የሚሠሩት መሆኑን ተናግረው፤ ግቡን ለማሳካት አስቻይ ሁኔታ እንደሚፈጥር ያመለክታሉ።
ቀደም ሲል በተናጠል ይሠራ የነበረውን ሥራ ወደ አንድ በማምጣት ይባክን የነበረውን ሀብትና ጉልበት በመታደግ ረገድ ሚናው የጎላ እንደሆነ ይናገራሉ። በተጨማሪም ከሁሉም መንግሥታዊ ተቋማት ጀምሮ እስከ አርሶ አደሩ ድረስ በምግብና በተመጣጣነ ምግብ ሥርዓት ላይ የነበረውን የተዛባ ግንዛቤ በመቀየር ሥራቸው በእዚሁ መልክ የተቃኘ እንዲሆን ያደርጋልም ብለዋል።
በሌላ በኩል ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የግብርና ሥርዓት ግንባታ ሥራው የእርሻ መሬትን ከማዘጋጀት ጀምሮ ተጠቃሚው ዘንድ እስከማድረስ ዘላቂና ተከታታይነት ያለው ሥራ እንደሚያሻው ያመለክታሉ። ምርታማነትን ለማሳደግ ከሚደረገው ጥረት ጎን ለጎን እርሻን ለማስፋፋት ሲባል የሚደረጉ የደን ምንጣሮዎችን፣ የውሃ ሀብትን አላግባብ የመጠቀሙ ልማድና በድኅረ ምርት ወቅት ያሉ የምርት ብክነቶችን ጭምር በማስቀረት እንዲሁም ለበካይ ጋዝ ልቀት ምክንያት የሆኑ አሠራሮችን በማስቀረት ውጤታማ ሥራ መሥራት ከሁሉም ባለድርሻ አካላት ብዙ እንደሚጠበቅ አስገንዝበዋል።
ማህሌት አብዱል
አዲስ ዘመን ሰኞ መጋቢት 8 ቀን 2017 ዓ.ም