በ አገር ደረጃ ቋንቋን በተመለከተ የተጠኑ ጥናቶች ቢኖሩም እስከአሁን በፖሊሲ ደረጃ ወጥቶ መጽደቅ አልቻለም። በመሆኑም በቋንቋ አጠቃቀም ዙሪያ ችግሮች እየተከሰቱ መሆኑን ምሁራን ይናገራሉ።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ባህሎች አካዳሚ የቋንቋ ጥናት ኃላፊ ዶክተር ዮሐንስ አድገ እንደተናገሩት፣ እያንዳንዱ ሥራ በህግና በፖሊሲ መመራት እንዳለበት ይታወቃል። በተለይ ልሳነ ብዙ በሆነችው አገር ያለቋንቋ ፖሊሲ መሥራት እጅግ ከባድ ነው።
በዚህም የቋንቋ ፖሊሲ ባለመኖሩ የተነሳ ብዙ ችግሮች ተከስተዋል። በክልል፣ በዞንና በወረዳ ምን ዓይነት ቋንቋ እንዴትና ለምን አገልግሎት ይጠቀሙ? በፌዴራል ደረጃ ምን ዓይነት ቋንቋ ለምን አገልግሎት እንዴት ይዋል? የሚለውም እየተተገበረ አይደለም። በማስታወቂያ በሚሠሩ ሥራዎች ላይም በምን ዓይነት መንገድ ቋንቋው አገልግሎት ይስጥ? ምን ዓይነት ሥነ ልሳናዊ ባህሪ ይኑረው? የሚለው ስላልተለየ ዥንጉርጉርነት አካሄድ ተፈጥሯል።
ይህ ደግሞ በቋንቋ አጠቃቀሙ ላይ ችግሮች መኖራቸውን አመላካች ነው ብለዋል፡፡ ዶክተር ዮሐንስ፤ የፌዴራል የሥራ ቋንቋ፣ የክልል የሥራ ቋንቋ፣ የሚዲያ፣ የገበያና የትምህርት ቋንቋ የትኛው ይደረግና የትኛውን የፅህፈት ሥርዓት እንከተል? የሚለው በህግ የተወሰነ ቢሆንም ለመተግበርና ተጠያቂነትን ለማስፈን ግን እንዳልተቻለ ይናገራሉ።
በማስታወቂያ ሥራም ልሳነ ሳልስ (ሦስት ቋንቋ) ወይም ልሳነ ራብእ (አራት ቋንቋ) መጠቀም ቢፈለግ የትኛው ቋንቋ ይቅደም? ማን ይከተል? የሚለው አይታወቅም። በዚህም አገር የጉራማይሌ ቋንቋ ተጠቃሚ ሆናለች ይላሉ። ተማሪዎች በአፍ መፍቻ ቋንቋ መማራቸው፣ መልክአ ምድራቸውን ማወቃቸው፣ ማስተማርም፣ መማርም፣ መረጃ መለዋወጥም መቻላቸው፤ ቋንቋውን ለትምህርት፣ ለመገናኛ ብዙሃን መጠቀምም እንዲሁ ከፖለቲካ እይታ አንጻር ልክ ሊሆን ይችላል ያሉት ዶክተር ዮሐንስ፤ በአገር አቀፍ ደረጃ እያንዳንዱ ሕፃን በአፍ መፍቻ ቋንቋው ይማር ቢባልም ከዚህ በኋላ የማስተማሪያ ቋንቋው ወዴት ነው መዞር ያለበት የሚለው በቋሚነት አይታወቅም። በዚህም እንደ ቋንቋው ሁሉ ዝብርቅርቁ የበዛ የማስተማር ስርዓት መፈጠሩን ይናገራሉ።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአፍሪካ ጥናትና ምርምር የሦስተኛ ዲግሪ ተማሪና በአገር በቀል እውቀቶች ላይ የተለያዩ ጥናቶችን ያደረጉት አቶ ብሩክ ሸዋአደግ በበኩላቸው እንደገለጹት፤ በፖሊሲው አለመኖር አገራዊ መግባባት እንዳይኖር ሆኗል፤ በህገ መንግሥቱ የተቀመጠው የፌዴራል መንግሥቱ የሥራ ቋንቋ አማርኛ ነው ቢልም ተግባራዊነቱ ግን የተለየ ነው። እንግሊዝኛው በብዛት ሸፍኖታል። ቋንቋው ጽንሰ ሃሳብ የሚሸከሙ ቃላትም እየጠፉ ናቸው። ፖሊሲው ባለመኖሩ የተነሳ ጉራማይሌ በሆነ ቋንቋ መጠቀም ላይ ተደርሷል የሚሉት አቶ ብሩክ፤ ጉራማይሌ ቋንቋ ተናጋሪ እንዲበዛ፤ የቋንቋ ተገዥነት እንዲንሰራፋ፤ እንግሊዝኛን ትልቅ ሌሎች ቋንቋዎችን ትንሽ አድርጎ መመልከት እንዲበራከት ዕድል እንደተመቻቸና ለመመለስ እንደሚያዳግት ይገልጻሉ።
በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የቋንቋና የጋራ ባህል እሴቶች ልማት ዳይሬክተር አቶ አለማየሁ ጌታቸው እንደተናገሩት፤ ፖሊሲ ለህብረተሰቡ ቃል የሚገባበት አቅጣጫን የሚሰጥበት ሰነድ ነው። ሆኖም ይህ ባለመኖሩ የቋንቋዎች የልማት ሂደት፤ ተቋማዊና ቅንጅታዊ አሠራር እንዳይኖር አድርጓል። በተለይ በቋንቋ ልዩነት ብቻ ብዙ ሥራዎች በተደጋጋሚነት እንዲከናወኑ ሆነዋል። ይህ ደግሞ በተለይ በፊልምና ድራማ እንዲሁም ሙዚቃ ዙሪያ መሰራረቅንና ያልተገባ ጥቅም ፍለጋን አምጥቷል። ማህበረሰቡም ሙያው ላይ ያለውን ጥሩ ምልከታ አሳጥቶታል። ከፍተኛ የሆነ የበጀት አቅምንም አዳክሟል።
የመገናኛ ብዙኃን የቋንቋ አጠቃቀም መመሪያ እንዳይኖር የሆነው ፖሊሲው ካለመኖሩ የተነሳ እንደሆነ የሚያነሱት አቶ አለማየሁ፤ የህብረተሰቡን ባህል፣ እሴት በጠበቀ መልኩ የቋንቋ አጠቃቀም እንዳይኖር አድርጓል። የመዝናኛ ኢንዱስትሪውም እንዲሁ በቋንቋው መልዕክት የተነሳ የተለየ ጽንፍ እንዲኖራቸውና በቋንቋው ባለቤቶች ዘንድ ያለው ትርጉምና በሠሪው መካከል ሰፊ ልዩነት በመምጣቱ ለግጭት መንስኤ እየሆነ እንደመጣ ይናገራሉ። እንደ አቶ አለማየሁ ገለጻ፤ የሚጻፈው ጽሑፍ አቀማመጥና የስፋቱ መጠን የተዛባ እንዲሆን፤ አብዛኛው ስያሜም ቢሆን በአገርኛ ቋንቋ እንዳይጻፍ ያደረገው፤የህብረተሰቡን የቋንቋ ፍላጎት መሰረት ያደረጉ አገልግሎቶችም እንዳይሰጡ የሆነው፣ የቋንቋ የፊደል ስርዓት አጠቃቀምና የአረፍተ ነገር መዋቅሮችም ስርዓት እንዳይዙ የተደረገው ፖሊሲው ባለመኖሩ ነው።
የቋንቋውን ስነ ልሳናዊ ባህሪና ሰዋሰዋዊ ስርዓት በጠበቀ መልኩ ለጽህፈት፣ ለንግግርና ለአገልግሎት እንዳይውል አድርጎታል። የፊደላት አመራረጥና የቃላት አሰካክ ጉራማይሌነት የመጣው ቋንቋ ላይ ያለው የስነልሳናዊ እውቀት የጠበበ በመሆኑ ወይም በግዴለሽነት ሊሆን ይችላል የሚሉት ዶክተር ዮሐንስ፤ በቋንቋው አፉን የፈታበት ትልቅ ማህበረሰብና የቋንቋ ምሁር ባለበት አገር ትክክል ያልሆነ የአጻጻፍ ስርዓት መጠቀም ተገቢ አይደለም። ስለዚህ ፖሊሲው በአፋጣኝ መውጣት ይኖርበታል። ሌሎች ቋንቋዎች እንዴት ነው የሚያድጉት፣የሚበለጽጉት እንዲሁም ሌሎች ያንን ቋንቋ ማወቅ ቢፈልጉ እንዴት ነው መማር የሚችሉት የሚለውን መሠረታዊ ጥያቄ በሚመልሱት መልኩም ፖሊሲው ሊዘጋጅ ይገባል ይላሉ፡፡ ቋንቋ በባህሪው ስንጠቀመው የሚያልቅ ሳይሆን የሚያድግ ነው ያሉት አቶ አለማየሁ፤ በዚህም መጠቀም ሲባል ውሳኔዎች ከማግኘታቸው በፊት መልማትን ማስቀደም ነው። እንደ አጋጣሚና ዕድል ወይም በሌላ ጉዳይ እውቅናን ያገኙና ቋንቋዎቹ ሳይለሙ በስሜት ወደ ሥራ ቋንቋነትና ወደ ትምህርት የገቡ በመኖራቸው እነርሱም ላይ መሥራት ያስፈልጋል ባይ ናቸው። ምሁራን ለፖሊሲው ዝግጅት የሚሆን የተለያዩ ሰነዶችን አቅርበዋል። በዚህም በአገር ደረጃ በሁሉም ክልሎች ወደ 11 ቡድን ተዋቅሮ ሁለት አባላት ያሉት ሰዎች በመመደብ አምስት መቶ ገጽ የያዘ 15 ጥናታዊ ጽሑፎችን ያካተተ ረቂቅ የፖሊሲ ሰነድ ተዘጋጅቷል። ይህ ሰነድ ውሳኔ ካገኘ ለዚህ ሁሉ ችግር መፍትሔዎች እንደሚኖር ያነሳሉ። «ቋንቋውን የሚያውቅ ሁሉ መምህር መሆን አይችልም። መምህሩ በቋንቋ ትምህርት የሰለጠነ መሆን ይገባል።
ቋንቋ እንደማንኛውም ትምህርት መልዕክት ብቻ ሳይሆን ክህሎትም ጭምር ይተላለፍበታል። በዚህ ላይ ሊሠራ ይገባል ያሉት ደግሞ አቶ ብሩክ ናቸው። በአንዳንድ ተቋማትና ግለሰቦች ላይ ተናጥላዊ ፍላጎትንም ማጥፋትና ለአገር አንድነት መሥራት እንደሚገባ ይናገራሉ። ቋንቋን ብቻ የሚያለማ አንድ መዋቅራዊ ሥርዓትም ሊኖር ይገባል ይላሉ። በአገር አቀፍ ደረጃ እስከ 1983 ዓ.ም ድረስ ብሔራዊ ቋንቋ ነበር፤ ከዚያ በኋላ ግን የሥራ ቋንቋ እንጂ ብሔራዊ የሚባል ቋንቋ የለም። ከዚህ ጋር ተያይዞም ከ90 በመቶ በላይ የሚሆኑ የኢትዮጵያ ቋንቋዎች የጽሑፍ ቋንቋ አልነበራቸውም።
ከደርግ ዘመን በኋላ በ15 ቋንቋዎች መሰረተ ትምህርት ሲጀመር ኢህአዴግ አዲስ ስርዓተ ትምህርት በመቅረጹ ቆሟል። ይሁንና በምትኩ 52 ቋንቋዎች ወደ ስርዓተ ትምህርቱ ሲገቡ፤ አንዳንዶች በቋንቋ ትምህርትነት፣ አንዳንዶች ደግሞ የጽሑፍም ጭምር እንዲሆኑ ተደርጓል። አገራዊ እውቀቶችና ቋንቋዎች በአገር ላይ በሚፈለገው መጠን አገልግሎት እንዳይሰጡ ይሆናል። ባህላዊ፣ ስነልቦናዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታዎችም ከአገር በቀል እውቀቶች ውስጥ መውጣት አይችሉም። ይህ ደግሞ ማህበረሰቡ የሚያስተሳስረውን ማንነት እንዲያጣ ያደርገዋል። ስለሆነም የቋንቋ ፖሊሲ ሊኖረን የግድ ይላል፡፡
አዲስ ዘመን መጋቢት 15/2011
በጽጌረዳ ጫንያለው