የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ችሎት ውሳኔዎች በተካተቱበትና በ2007 ዓ.ም ለህትመት በበቃው መፅሐፍ ቅፅ 16 ላይ በሰነድ መለያ ቁጥር 972ዐ6 ሐምሌ 28 ቀን 2006 ዓ.ም በዋለው ችሎት አምስት ዳኞች ከችሎቱ ላይ ተቀምጠዋል። በዚህም አመልካች አቶ አማረ መልካሙ ራሳቸው በቪዲዮ ኮንፈረንስ አማካኝነት ከመቐለ የቀረቡ ሲሆን፤ በተጠሪ አቶ ካሌብ ሕሉፍ በኩል የቀረበ አልነበረም። ታዲያ ዳኞች ሠዓቱን ጠብቀው ከችሎቱ ተሰይመውና ዳኞች መዝገቡን በጥልቀት መርምረው ፍርድ እነሆ ብለዋል።
ፍርድ
በዚህ መዝገብ በሰበር ችሎቱ ሊወሰን ይገባል ተብሎ የተያዘው ጭብጥ አመልካች የተጠሪ ንብረት የሆነውን በትግራይ ክልል ኮንስትራክሽንና መንገድ ትራንስፖርት ቢሮ ካላቸው ገንዘብ 612ሺ2005 ብር በፍትሃብሄር ሥነሥርዓት ቁጥር 154/ለ/ መሠረት ማሳገዳቸው ከሌሎች የፍርድ ባለገንዘቦች የቀደምትነት መብት ያረጋግጥላቸዋል ወይ የሚለው ነው። አመልካች በተጠሪ ላይ የመሰረቱት ክስ ተከትሎ የፍርድ ባለገንዘብ መሆናቸው ተረጋግጧል።
በአመልካች ጠያቂነት ከላይ በተጠቀሰው ቢሮ የነበረውን ገንዘብም አሳግዷል። አመልካች ገንዘቡን ካሳገዱ በኋላ አሥራ ሰባት የፍርድ ባለገንዘቦች ከተወሰነ ቀን በኋላ በተመሳሳይ መንገድ የተጠሪ ገንዘብ ላይ ዕግድ እንዲሰጥ አመልክተው በፍርድ ቤት ተቀባይነት አግኝቷል። አመልካች በትግራይ ክልል መቐለ ከተማ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመለያ ቁጥር 14044 ባቀረቡት ክስ ያሳገዱትን ገንዘብ በቅድሚያ ለእሳቸው እንዲከፈል ጠይቋል። የሥር ከፍተኛ ፍርድ ቤት በሰጠው ብይን ለክርክር መነሻ የሆነውን ሃብት ገንዘብ መሆኑን መሠረት በማድረግ በፍርድ ቤት ትዕዛዝ የታገደው ገንዘብ ከመሆኑ አኳያ እንደማይንቀሳቀስ ንብረት የማይወሰድ ነው።
በፍርድ ቤት ትዕዛዝ የታገደው ገንዘብ ለፍርድ ባለገንዘቦች ባስፈረዱት መጠን በሬሽዎ እንዲከፋፈል በማለት ብይን ሰጥቷል። አመልካች የሥር ከፍተኛ ፍርድ ቤት ውሳኔ በመቃወም ወደ ክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ያቀረቡ ቢሆንም የሥር ፍርድ ቤት ውሳኔ በማጽናት ወስኗል። አመልካች በሥር ፍርድ ቤት ተፈጽሟል ያሉትን የሕግ አተረጓጎም ስሕተት በመዘርዘር የሰበር አቤቱታቸውን በ26-05-2006 ዓ.ም አቅርበዋል።
የአቤቱታው መሠረታዊ ይዘት የፍርድ ባለዕዳ ገንዘብ ከሌሎች የፍርድ ባለገንዘቦች ቀድመው ማሳገዳቸውን መሠረት ተደርጐ የቀደምትነት መብት እንዲከበርላቸው፤ የቀደምትነት መብት በማይንቀሳቀስ ንብረት ብቻ ሳይሆን በሚንቀሳቀስ ንብረትም ማቋቋም እንደሚቻል፤ የሥር ፍርድ ቤቶችም ክፍያ ማስፈጸም ያለባቸው የፍርድ ባለገንዘቦች ገንዘቡን ባስከበሩበት ቅደም ተከተል ሊሆን እንደሚገባ በመጥቀስ የሥር ፍርድ ቤቶች ውሳኔ እንዲታረም ጠይቋል።
ተጠሪ የአመልካች አቤቱታ ከመጥሪያ ጋር የተላከላቸው ቢሆንም በአድራሻቸው ስላልተገኙ በፍርድ ቤት ቅጥር ግቢ በሚለጠፍ መጥሪያ መሠረት እንዲቀርቡ በተሰጠው ትዕዛዝ መሠረት ባለ መቅረባቸው በጽሑፍ መልስ የመስጠት መብታቸው ታልፏል። ከሥር የክርክሩ አመጣጥና በሰበር የቀረበው የጽሑፍ ክርክር ከላይ የተገለጸው ሲሆን እኛም ጉዳዩን ለሰበር አቤቱታ መነሻ ከሆነው ውሳኔ እና አግባብነት ካላቸው ድንጋጌዎች እና ጉዳዩን ለሰበር ሰሚ ችሎት ሲቀርብ ከተያዘው ጭብጥ አንፃር በሚከተለው መልኩ መርምረናል። ከመዝገቡ እንደሚታየው አመልካች በፍርድ ባለዕዳ ገንዘብ ላይ በፍርድ ቤት ትዕዛዝ ማስከበራቸው የቀደምትነት መብት እንዲሰጣቸው ቢጠይቁም በሥር ፍርድ ቤት ተቀባይነት አላገኘም። ከላይ እንደተገለጸው በፍርድ ቤት ትዕዛዝ የተከበረው ነገር ገንዘብ ነው ይላል በክርክሩ ላይ ከቀረቡት ሃሳብ ውስጥ በግርድፉ ሲገለፅ።
የፍርድ ባለገንዘብ በፍርድ ባለዕዳ ንብረት ላይ የቀደምትነት መብት በሕግ፣ በውል እና በፍርድ ቤት ትዕዛዝ ሊያቋቁም ይችላል። ከማይንቀሳቀስ ንብረት ጋር በተያያዘ የቀደምትነት መብት በጋራ የንብረት ባለሃብቶች፤ በፍርድ ቤት ትዕዛዝ እንደውሳኔውን ለማስፈጸም እንዲሁም ግራ ቀኙ ባደረጉት ሥምምነት ሊቋቋም እንደሚችል ከፍትሃብሄር ቁጥር 3043፣3044 እና 3045 ይዘትና መንፈስ የምንገነዘበው ጉዳይ ነው። በሌላ በኩል በማይንቀሳቀስ ንብረት ላይ የቀደምትነት መብት ሊቋቋም የሚችለው የፍትሃብሄር ቁጥር 2825 በሚያዘው አግባብ የፍርድ ባለዕዳው ንብረቱን ለፍርድ ባለገንዘብ ማስረከቡ ሲረጋገጥ መሆኑን ከሕጉ ንባብ የምንገነዘበው ነው።
አመልካች የቀደምትነት መብት እንዲሰጣቸው መሠረት ያደረጉት የፍትሃብሄር ሥነ ስርዓት ቁጥር 154/ለ/ ነው።
የዚህ ሕግ አንቀጽ መሠረታዊ ይዘትና ዓላማ ስንመለከተው በክርክር ላይ ባሉ ጉዳዮች የፍርድ ባለገንዘብ በመጨረሻ የረታ ከሆነ ፍርዱን ለማስፈጸም የሚያስችል ንብረት ወይም ገንዘብ እንዳይታጣ ቅድመ ጥንቃቄ ለማድረግ ነው። ከፍትሃብሄር ሥነ ስርዓት ቁጥር 154 ርዕስ እንደምንረዳው የማገድ ትዕዛዙ የሚሰጠው ለጊዜው ስለመሆኑ፤ በፍርድ ባለዕዳ ሥር ያለው ንብረት በየትኛውም መልኩ ለሦስተኛ ወገን እንዳይተላለፍ፤ እንዳይበላሽ፤ እንዳይጠፋ ፍርድ እስከሚሰጥ ተከብሮ እንዲቆይ የማድረግ ዓላማ ያለው ነው።
አመልካች ከላይ በተገለጸው አግባብ የፍርድ ባለዕዳ ንብረት ማሳገዳቸው በማይንቀሳቀስና በሚንቀሳቀስ ንብረት የቀደምትነት መብት ማቋቋም በሚያስችል አግባብ ከሕግ ወይም ከውል የመነጨ መብት አግኝቷል ወይ፤ የሚለውን የክርክር ነጥብ በአግባቡ መታየት አለበት። ከሥር ፍርድ ቤት ውሳኔ መረዳት እንደተቻለው አመልካች ከፍርድ በፊት በማይንቀሳቀስ ሆነ በሚንቀሳቀስ ንብረት የቀደምትነት መብት ማቋቋማቸው የሚገልጽ ነገር አላቀረቡም። አመልካች በእጃችን ለተያዘው ጉዳይ አግባብነት ያለው ድንጋጌ ነው በማለት የጠቀሱት የሕግ አንቀጽ 2860 ከላይ በጠቀስነው አግባብ መያዣ/Pledge/ያቋቋሙ የፍርድ ባለገንዘቦች ያላቸውን መብት የሚያመለክት እንጂ ከዚህ ጉዳይ ጋር ተያያዥነት ያለው ሆኖ አልተገኘም።
አመልካች የቀደምትነት መብት በፍርድ ቤት ትዕዛዝ ማቋቋማቸው የገለጹ ቢሆንም የፍትሃብሄር ሥነ ስርዓት ቁጥር 154/ለ/ ከሌሎች አግባብነት ያላቸው ድንጋጌዎች ስንመለከተው ከዚህ የተለየ ትርጉም የሚሰጥ ሆኖ ተገኝቷል። ንብረት ለማስከበር የሚቀርብ ማመልከቻ ሊያሟላቸው የሚገቡ ቅድመ ሁኔታዎች የፍትሃብሄር ሥነ ስርዓት ቁጥር 379 በዝርዝር ደንግጓል። የማይንቀሳቀስ ንብረቱ ዓይነቱን በመለየት ማቅረብ ግዴታ መሆኑን፤ የማይንቀሳቀስ ንብረት ከሆነ ደግሞ ንብረቱን ለይቶ ለማወቅ የሚያስችሉ ምልክቶች መገለጽ እንዳለባቸው ንብረቱ የሚለየው በአካባቢው ውስጥ ወይም ርስተ መዝገብ ከሆነ በተራ ቁጥር በሆነ ጊዜ የወሰኑ ምልክት ወይም በመዝገብ ላይ የተሰጠው ቁጥር መግለጽ እንደሚገባ ተመልክቷል። አመልካች በፍርድ ባለዕዳ ንብረት ላይ የዕግድ ትዕዛዝ እንዲሰጥ ማድረጋቸው ከላይ በተገለፀው አግባብ ከሕግ ወይም ከውል የመነጨ የቀደምትነት መብት አቋቁመዋል ለማለት የሚቻል አይደለም።
አንድ የፍርድ ባለገንዘብ በፍትሃብሄር ሥነ ስርዓት ቁጥር 154/ለ/ መሠረት የንብረት ዕግድ ቢያሰጥ የቀደምትነት መብት የሚያቋቁም ስለመሆኑና አለመሆኑ ከአሁን በፊት የሰበር ሰሚ ችሎት በሰነድ መለያ ቁጥር 29269 እና 27808 የሰጣቸው አስገዳጅ ውሳኔዎች ተመልክተናል። የኢትዮጵያ ንግድ ባንክና የኢትዮጵያ ልማት ባንክ በማይንቀሳቀስ ንብረት መያዣ በማድረግ ብድር በመስጠታቸው ምክንያት የሥር ፍርድ ቤቶች የቀደምትነት መብታቸው የነፈገ ውሳኔ በመስጠታቸው የእነዚህ አበዳሪ ተቋማት መብት የሚያስጠብቅ ውሳኔ መስጠቱ የሚያስረዱ ናቸው።
የሥር ፍርድ ቤት ውሳኔዎች በተናጠል ሲንመለከታቸው በሰነድ መለያ ቁጥር 27808 የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ግለሰቦች ሲከራከሩ በመያዣ የያዘው ቤት በማሳገዳቸው ዕግዱ እንዲነሳ ሲጠይቅ ጣልቃ ገብተህ አልተከራከርክም ዕግዱ አይነሳም የሚል ውሳኔ በመስጠቱ በቀረበው አቤቱታ የሥር ፍርድ ቤቶች ውሳኔ ተሽሯል። በሌላ በኩል በሰነድ መለያ ቁጥር 29269 የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አስቀድሞ ንብረት ማስከበሩ ብቻውን የቀደምትነት መብት አያሰጥም ማለታቸው ከሕግ የመነጨ የቀደምትነት መብት የነፈገ ነው ተብሎ የሥር ፍርድ ቤት ውሳኔ ተሽሯል።
በእነዚህ ሁለት የሰበር ውሳኔዎች አሁን በእጃችን ካለው ጉዳይ ያላቸው ተመሳሳይነት እንደተመለከትነው ከላይ የተጠቀሱ ተቋማት የቀደምትነት መብታቸው በማይንቀሳቀስ ንብረት ያቋቋሙት የቀደምትነት መብት የነበረ መሆኑን የሚያሳይ ሲሆን የአሁኑ አመልካች ያቀረቡት ጉዳይ ግን በፍትሃብሄር ሥነ ሥርዓት ቁጥር 154/ለ/ መሠረት በአንድ የመንግሥት ተቋም የተያዘው የሚንቀሳቀስ ገንዘብ የሚመለከት በመሆኑ ለዚህ ጉዳይ ተፈፃሚነት የላቸውም።
የቀደምትነት መብት በሕግ፣ በውል ወይም በፍርድ ቤት ትዕዛዝ /ውሳኔ/ የሚቋቋም ስለመሆኑ ከላይ በተገለጸው የፍትሐብሄር ሕግ ተመልክቷል። አመልካች በፍርድ ባለዕዳ ላይ አስፈርደው ከሌሎች የፍርድ ባለገንዘቦች ቀድመው የፍርድ ቤት የዕግድ ትዕዛዝ ማግኘታቸው ከሕግ፣ ውል ወይም የፍርድ ቤት ውሳኔ የመነጨ የቀደምትነት መብት አቋቁመዋል ለማለት የሚያስችል የህግ መሰረት የላቸውም።
አመልካች በተጠሪ ገንዘብ የሰጡት የዕግድ ትዕዛዝ ከሌሎች የፍርድ ባለገንዘቦች የተሻለ መብት እንዳላቸው የሚያረጋግጥ አይደለም ከተባለ፤ ቀጥሎ የሚነሳውን ጥያቄ በተራ የፍርድ ባለመብቶች መካከል ያለው የክፍፍል ሥርዓት ምንመሆን አለበት የሚል ነው። ከሥር ፍርድ ቤት መዝገብ መረዳት እንደተቻለው አመልካችን ጨምሮ በተጠሪ ገንዘብ ላይ 18 ግለሰቦች የዕግድ ትዕዛዝ አሰጥቷል። ከአንድ በላይ የፍርድ ባለመብቶች ባሉበት ጊዜ የሀብትና የንብረት ክፍፍል ሥርዓት ምን መሆን እንዳለበት የፍትሃብሄር ሥነ ሥርዓት ቁጥር 403 ያስቀመጣቸው ሁኔታዎች ማየቱ ተገቢ ይሆናል። በዚህ ድንጋጌ መሰረት የፍርድ ባለገንዘቦች ተቀማጭ የሆነውን ሀብት በውሳኔው መሰረት እንዲከፋፈሉ እንደሚያደርግ ተመልክቷል።
አመልካች በተጠሪ ገንዘብ ላይ ቀድመው የዕግድ ትዕዛዝ ማስጠታቸው ግልጽ ቢሆንም ሌሎች የፍርድ ባለገንዘቦችም በተከታታይ ቀናት ይህንን የማሳገድ ተግባር አከናውነዋል። አመልካች ከሌሎች የፍርድ ባለገንዘቦች የቀደምትነት መብት ያልተሰጣቸው ከሆነ ሁሉም የፍርድ ባለገንዘቦች እንደተራ ገንዘብ ጠያቂዎች የሁሉም መብት እኩል እንደሆነ የሕግ ግምት ይወሰዳል። ከላይ እንደተገለጸው አንድ የፍርድ ባለገንዘብ ከሌሎች የፍርድ ባለገንዘቦች አስቀድሞ የባለዕዳውን ንብረት በማስከበሩ ምክንያት ብቻ የቀደምትነት መብት አይሰጠውም። በመሆኑም የፍርድ ባለገንዘቦች እንደተራ የፍርድ ባለመብቶች ተወስደው ደረጃቸው (መብታቸው) እኩል መሆኑን ግምት ውስጥ በማስገባት ባስፈረዱት የገንዘብ መጠን መቶኛ ስሌት በፍርድ ቤት ትዕዛዝ የታገደውን ገንዘብ እንዲከፋፈሉ ማድረጉ የሕግ መሰረት ያለው ስለመሆኑ ከፍትሃብሄር ሥነ ሥርዓት ቁጥር 403 ይዘት ዓላማና መንፈስ የምንረዳው ነው።ከዚህ አንፃር የሥር ፍርድ ቤቶች የፍርድ ባለገንዘቦች በፍርድ ባለዕዳው ላይ ያላቸው የገንዘብ መጠን በመቶኛ (ሬሾዎ) እንዲከፋፈሉ ትዕዛዝ መስጠታቸው መሠረታዊ የሕግ ስሕተት የተፈጸመበት ሆኖ ባለመገኘቱ ተከታዩ ውሳኔ ተሰጥቷል ሲል ሰነዱ አስቀምጧል።
ው ሣ ኔ
- የመቐለ ከተማ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በኮ.መ.ቁ.14044 በ25/04/2006 ዓ.ም የሰጠው ብይን፤ የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በኮ.መ.ቁ. 6365 በ12/05/2006 ዓ.ም የሰጠው ትዕዛዝ ፀንቷል።
- አመልካች እና ሌሎች የፍርድ ባለገንዘቦች ባስፈረዱት መጠን ገንዘብ መቶኛ ስሌት (ሬሽዎ) ድርሻ ድርሻቸውን ይከፋፈሉ ብለናል።
- ወጪና ኪሣራ ግራ ቀኙ ወገኖች የየራሳቸውን ይቻሉ፤ መዝገቡ ተዘግቷል፤ ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ፤ ሲል ውሳኔውን አስቀምጧል ከመቐለ እስከ ፌዴራል ድረስ የተራዘመው ክርክር።
ክፍለዮሐንስ አንበርብር
አዲስ ዘመን ግንቦት 27/2014