የዛሬው የዘመን እንግዳችን ከሥራ ፈጣሪ ሴቶች መካከል አንዷ የሆነችው ወይዘሪት ሳምራዊት ፍቅሩ ናት። እንግዳችን ተወልዳ ያደገችው አሰላ ከተማ ውስጥ ነው። የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን የተከታተለችው እድገት በሥራ በተባለ እና ጭላሎ ተራራ በሚባል ትምህርት ቤት ነው። በማይክሮሊንግ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ኮሌጅ በሶፍትዌር ኢንጅነሪንግ ዲፕሎማ እንዲሁም ሂልኮ በተሰኘ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ኮሌጅ ደግሞ በኮምፒዩተር ሳይንስ የመጀመሪያ ዲግሪ አግኝታለች። ገና በወጣትነቷ ጀምሮ ተቀጥረው ለሚሰራበት ሙዚቃ ቤት የራስዋን የሽያጭ ሪፖርት የሚያቀርብ ሶፍትዌር ከመስራት ጀምሮ የተለያዩ ሥራዎችን የሚያቀላጥፉ ቴክኖሎጂዎችን ለኢትዮጵያ በማስተዋወቅ ግንባር ቀደም ሆናለች።
ለሽንፈት እጅ የማትሰጠው እንግዳችን በሴትነቷና በወጣትነቷ ምክንያት በተደጋጋሚ የሰራቻቸው የምርምር ሥራዎች ተቀባይነት ባያገኙም ለኢትዮጵያ አዲስ የሆነና በቴክኖሎጂ የታገዘ የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጥ ሥርዓት በመፍጠር ረገድ ፈር ቀዳጅ መሆን ችላለች። በአሁኑ ወቅት ከ40ሺ በላይ ለሚሆኑ አሽከርካሪዎች የሥራ በር በከፈተው በራይድ የትራንስፖርት አገልግሎት ከ500 ለማያንሱ ዜጎችም ቋሚ የሥራ እድል ፈጥራለች። ከሰሞኑ ደግሞ የምርጥ አፍሪካዊ ቢዝነስ ባለራዕይ ሽልማት አሸናፊ ሆናለች። አዲስ ዘመን ጋዜጣም ወጣቷን ሥራ ፈጣሪ የዛሬው የዘመን እንግዳ አድርጎ እንደሚከተለው ይዞ ቀርቧል።
አዲስ ዘመን፡- ወደ ቴክኖሎጂ ፈጠራ የገባሽበትን አጋጣሚ አስታውሺንና ውይይታችንን እንጀምር?
ወይዘሪት ሳምራዊት፡- እንደሚታወቀው ተወልጄ ያደኩባት አሰላ ለአዲስ አበባ ቅርብ፣ አንባቢና ንቁ ማህበረሰብ ያለባት ትንሽ ከተማ ብትሆንም ለቴክኖሎጂ ግን ነዋሪዎቿ የዚያኑ ያህል ቅርብ አልነበሩም። እኔ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት በምማርበት ጊዜ እቅዴ የነበረው ሜዲካል ዶክተር መሆን ነው። ምክንያቱም ደግሞ የነበረው አንድ ሆስፒታል ብቻ ስለነበር ብዙ ህብረተሰብ አገልግሎት ማግኘት ሲቸገር እመለከት ስለነበር ነው። አንዲት አጋጣሚ ግን የልጅነት ህልሜን የሚያስቀየር ነገር ፈጠረች። ይኸውም አንድ ቀን ከእናቴ ጋር ገበያ እየሄድኩ ሳለ አንድ የኮምፒዩተር ማሰልጠኛ ማዕከል ጋር በአጋጣሚ እናቴ ቆማ ሰው ሰላም እያለች ባለችበት ቅስበት እኔ ማዕከሉ ውስጥ ባለው ኮምፒዩተር ላይ አይኖቼ አተኩረው ቀሩ። ሰዎች ቁጭ ብለው በኮምፒዩተሩ ሲፅፉና የተለያዩ ሥራዎችን እየሰሩ ተመለከትኩኝ። በተለይ የሚንቀጠቀጠው እስክሪኑ የበለጠ ጥያቄ አጫረብኝ እናቴን ስለምንነቱ ስጠይቃት እንደማታውቀው ነገረችኝ። ቀጠልኩና ኤሌክትሪክ ኢንጂነር ወደሆነውና አዲስ አበባ የሚኖረው ወንድሜ ጋር ደወልኩና ስላየሁት ነገር ጠየኩት። እሱም ኮምፒዩተር መሆኑንና ስለምንነቱ አብራራልኝ።
ክረምት ላይ ወንድሜ ጋር ስመጣ የበለጠ በተግባር በታገዘ ሁኔታ ስለኮምፒዩተር ማወቅ ቻልኩኝ። እኔም በዚህ ቴክኖሎጂ እጅግ ስለተመስጥኩኝ ብዙ ጥያቄዎች መጠየቅና መመራመር ጀመርኩ። ብዙም ሳልቆይ ደግሞ ስለኢንተርኔት አስረዳኝና ለእህቴ ደብዳቤ እንድፅፍ ነገረኝ። ከዚያ ደግሞ ደብዳቤ እንዴት በፍጥነት ሊደርሳት ቻለ? የሚል ጥያቄ ፈጠረብኝ። በመጨረሻ ይህ ቴክኖሎጂ ሁሉንም ዘርፍ የሚነካና የሚገባ መሆኑን ተረዳሁ። ስለዚህ ኮምፒዩተር ብማር የበለጠ ጠቃሚ መሆኑን ተገነዘብኩኝ። በዚያ መሰረት ማይክሮሊንክ ኮሌጅ በሶፍትዌር ኢንጅሪንግ እንዲሁም ሂልኮ በተባለ ኮሌጅ በመግባት ኮምፒዩተር ሳይንስ አጠናሁኝ። ከዚሁ ጎን ለጎን ግን በተለያዩ ኩባንያዎች ውስጥ ተቀጥሬ ስሰራ ነበር።
አዲስ ዘመን፡- በኮምፒዩተር ሳይንስ ከተመረቅሽ በኋላ በቀጥታ በተማርሽበት ሙያ ለምን ነበር መስራት ያልቻልሽው?
ወይዘሪት ሳምራዊት፡– በቀጥታ በተማርኩበት ዘርፍ ሥራ መስራት ያልቻልኩባቸው በርካታ ምክንያቶች ነበሩ።ከሙያዬ ውጭ ተቀጥሬ ስሰራ የነበረው እኔ ወደፊት እደርስበታለሁ ብዬ ላመንኩበት ነገር መሳካት የብዙ ሙያ እውቀት ያሻኛል ብዬ አስብ ስለነበረ ነው። ለዚህ ደግሞ የሚጎድለኝን ክህሎት ማሳደግ ነበረብኝ። አንድን ነገር ሰርቶ ለመሸጥ የመግባባት ክህሎት ያፈልጋል። ስለዚህ ሽያጭ ያለበት ቦታ ላይ ግዴታ መቀጠር አለብኝ ብዬ ወሰንኩኝ። በዚያ መሰረት አንድ ሙዚቃ ቤት ተቀጥሬ ካሴቶችን መሸጥ ጀመርኩኝ። መጀመሪያ ላይ ትንሽ ከባድ ነበር። በተለይም እንደእኛ ሃገር ዝምተኝነትን የሚያበረታታ ማህበረሰብ ባለበት ሀገር ውስጥ ሰዎችን አግባብቶና አሳምኖ እቃን መሸጥ ፈታኝ ነበር። ሆኖም ሽያጭ እየሰራሁ ሲስተም አናሊስት ሆኜ ለሌላም ድርጅት እሰራ ነበር። በዚያ መልኩ ነው አቅሜን ያጎለበትኩት።
የሚገርምሽ በሙዚቃ ቤቱ እየሰራሁ በነበርኩበት ጊዜ የቀኑ በጣም ከፍተኛ የሆነ ሽያጭ እንፈፅም የነበረ ቢሆንም በወረቀት ፅፈን ነበር የምናስገባው። በየቀኑ የሸጥኩትን ስደምርና ስቀንስ ረጅም ጊዜ ይወስድብኝ ነበር። ለባለቤቱ ደግሞ እንዲሁ በእጅ ጽፌ ነበር ሪፖርት አደርግ የነበረው። በተለይም በምደምርበት ጊዜ ብዙ መሳሳቶች ያጋጥሙኝ ነበር። ሁለተኛ ደግሞ ደምበኞች የሚፈልጓቸውን ሙዚቃዎች ያሉና የሌሉ መሆናቸውን የምናረጋግጥበት ስርዓት አልነበረንም። ቶሎ የምናስተናግድበት ሲስተም ባለመኖሩም አንዳንድ ጊዜ ደንበኞቻችንን እናበሳጭ ነበር። በመሆኑም ሁልጊዜ ደምበኞቻችንን እያበሳጨን መዝለቅ የለብንም፤ መፍትሄ መፈለግ አለብኝ የሚል ድምዳሜ ላይ ደረስኩኝ። የሽያጭና የገቢ ዝርዝር ስርዓት በሶፍትዌር መዘርጋት እንደሚገባ አመንኩኝ። እንዳውም ይሄ ለእኔ መልካም አጋጣሚ ነው ብዬ አሰብኩኝ። በወቅቱ ታዲያ ዲግሪዬን እየተማርኩኝ የራሴን ሶፍትዌር ሰርቼ ጨረስኩኝ።
ይህ ሶፍትዌር ኦዲዮና ቪዲዮ ያለው የሽያጭ ስርዓት ነበረው። ስለዚህ ሽያጭ ሲካሄድ ከኢንቨንተሪው ላይ እየቀነሰ ይሄዳል። በተመሳሳይ ሰዓት ደግሞ ምንያህል እንደተሸጠ ሪፖርቱን ማየት ያስችላል። ከዚህም ባሻገር ከስልክ ጋር አገናኘሁትና ባለቤቱ ሲደውል አጠቃላይ የሽያጭ መጠንን ለማወቅም ሆነ ሌሎች ዝርዝር መረጃዎችን የስልኩን ቁጥሮች በመጫን ማወቅ የሚያስችል ነበር። ለምሳሌ 1 ቁጥርን ሲጫን ‹‹ የዛሬው ሽያጭዎ 100ሺ ብር ነው›› ብሎ ማሽኑ በድምፅ ያነብሎታል። ይህንን ሶፍትዌር ሰርቼ ለባለቤቱ ሳቀርብለት በጣም ነው ደስ ያለው። እናም ያቺን የመጀመሪያዬን ሶፍት ዌር በስድስት ሺ ብር ነው ለሙዚቃ ቤት ባለቤቱ ሸጥኩለት። በዚህ ግን በጣም ደስተኛ ነበርኩኝ። ምክንያቱም ለኮሌጅ የምከፍለውን ገንዘብ ማግኘት ችያለሁ፤ ደግሞም በወቅቱ ያ ብር ብዙ ነበር።
በመቀጠልም ለሁለት ኩባንያዎች ሌሎች ሶፍትዌሮችን አዘጋጅቼ ሸጥኩኝ። ከዚያ በኋላ ግን የሚጎሉኝ ክህሎቶች ስለነበሩኝ ወደፊት መቀጠል አልቻልኩም። በእድሜዬም ደግሞ ገና በጣም ወጣት ነበርኩኝና ከብዙ ሰዎች ጋር መተዋወቅ ባለመቻሌ ደግሞ ምርቶቼን ማሳየት አልቻልኩም። ያም ሆኖ ግን የሰራኋቸው ሶፍትዌሮች እግርጌ አድራሻዬን እየፃፍኩ ስለነበር እሸጥ የነበረው ያንን የተመለከተው የሲመንስ ሶፍትዌር ቴክኖሎጂ ባለቤት ደወለልኝ። በዚያ ጊዜ እሱ ብቻ ነበር እንደዚያ አይነት ሶፍት ዌር እየሰራ ይሸጥ የነበረው። ከተቀጣጠርንበት ስፍራ ደርሼ ስደውልለት እንደእኔ አይነት በእድሜም ሆነ በአካል አነስ ያለች ልጅ ስላልጠበቀ ነው መሰል ሲመለከተኝ በጣም ነው የተገረመው። ቢሮው ወስዶ አስጎበኘኝ። የተደራጀና በርካታ ሰራተኞች ያሉት የሶፍትዌር ኩባንያ ሆኖ አገኘሁት። በመሆኑም የፈለከውን ያህል ክፈለኝና ከአንተ ጋር ልሰራ አልኩት።
የሚገርምሽ በወቅቱ እኔ የሰራሁትን ሲስተም ለማሳየት ስመጣ ላፕቶፕ ስላልነበረኝ ትልቁን ሲስተም ዩኒት ተሸክሜ ነው የሄድኩት። እሱ ግን ትጋቴን ስላየ በጣም ተደስቶ ቀጠረኝ። እናም ዲግሪዬን እየተማርኩኝ ጎን ለጎንም እዛ ኩባንያ ውስጥ ተቀጥሬ መስራት ጀመርኩኝ። ቀስ እያልኩኝ ክህሎቴን እያዳበርኩኝ ሌላም ድርጅት ተቀጥሬ ሰራሁ። ተቀጥሬ እየሰራሁ ሳለ ካሜሮን ሃገር ለሰባት ወራት ሄጄ የመስራት እድሉን አግኝቼ ነበር። ከዚያ ስመለስ ግን የራሴን ኩባንያ መክፈት እንዳለብኝ ወሰንኩኝ። ደግሞም እንደተመለስኩኝ በጣም ብዙ ሰዎች ሶፍትዌር እንድሰራላቸው ይጠይቁኝ ነበር። በዚያም በጣም ብዙ ገቢ ማግኘት ጀመርኩኝ። ደመወዜንም አጠራቅሜ ስለነበረ የራሴን ሥራ ለመስራት ዝግጅቴን አጠናቀቅኩኝ። በዚያ ጊዜ ነው ሃይብሪድ ዲዛይንን ያቋቋምኩት።
አዲስ ዘመን፡- ታዲያ ‘ራይድ’ የተባለውን የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጥ ድርጅት ለማቋቋም የተነሳሽበት አጋጣሚ ምን ነበር?
ወይዘሪት ሳምራዊት፡- የራሴን ሥራ ስጀምር የትኛውም ሶፍትዌር ኩባንያ የሚሰራውን ሥራ ላለመስራት ለራሴ ቃል ገብቼ ነበር። ምክንያቱም በጣም በርካታ እድሎች እንዳሉኝ በመረዳቴ ነው። በተለይም የማያቸውን ችግሮች መፍትሔ የሚሆኑ ቴክኖሎጂዎችን ማፍለቅ ዋነኛ ትኩረቴ መሆን እንዳለበት ነው ያመንኩት። በመጀመሪያ ደረጃ አዲስ ምርት ማውጣቴ በራሱ ትልቅ እድል ነው። በሌላ በኩል የያዝኩትን ቴክኖሎጂ ለህብረተሰቡ ለማስተዋወቅና ህብረተሰቡ እስከሚረዳው ድረስ ሌላ ቴክኖሎጂ ለማምጣት ፋታ የሚሰጥ ሥራ ነው። ስለዚህ ከራይድ በፊት ሁለት ምርቶችን ለገበያ አቅርቢያለሁ። አንደኛው የጥገና ማኔጅመንት ሲስተም ነው።
ይህንን ሲስተም ለመስራት ምክንያት የሆነኝ የተለያዩ አምራች ኢንዱስትሪዎችን በጎበኘሁበት ጊዜ የነዚህ ፋብሪካዎች የጀርባ አጥንት የሆነውን ማሽን ለማስጠገን የሚያወጡት ጊዜ ወጪና ሁኔታን ለመረዳት ሞክሪያለሁ። እነዚህ ኢንዱስትሪዎች በዓመት አንድ ጊዜ ከወጣላቸው የጥገና መርሐ ግብር ውጭ ማስጠገን የማይችሉ መሆኑንም ለመታዘብ ሞክሪያለሁ። ዓመት ጠብቀው ጥገናውን የማያካሂዱ ከሆነ የምርት መቋረጥና አላስፈላጊ ወጪ ያጋጥማቸዋል፤ ባዘገዩ ቁጥር በደምበኞቻቸው ዘንድ ያላቸውም ተቀባይነት እየቀነሰ ይመጣል። ለምሳሌ በወቅቱ ቆዳ ፋብሪካዎች በየቀኑ ያጡት የነበረው እስከ 40ሺ ዶላር የሚደርስ ገንዘብ ነበር። ስለዚህ ይህንን የጥገና ጊዜ የሚያስታውሳቸው ሲስተም ያስፈልጋቸዋል።
ሌላው ችግር ደግሞ አንዱ ጠጋኝ በምን መንገድ? እንዴትና ምን አይነት ግብዓት ተጠቅሞ ጠገነው? የሚለው የጥገና ታሪክ የመፃፍ ልምዱ ያለመኖሩ ነው። ሌላኛውም መጥቶ ሲጠግን ተመሳሳይ ሁኔታ ነው ያለው። የጥገና ታሪኩ ቢኖር ግን ችግሮች በፍጥነትና ወጪ ቆጣቢ በሆነ መንገድ መፍታት ይቻላል። ይህ ሶፍትዌር መሰራቱ ድርጅቶቹ ለጥገና የሚያወጡትን ወጪ እስከ 75 በመቶ ድረስ ሊቀንስላቸው ይችላል። በተጨማሪም በእነዚህ ፋብሪካዎች ብዙ ጊዜ የውጭ ምንዛሪ እጥረት ስላለ ብቻ አስቀድሞ የግብዓት ግዢ ይፈፀማል። ጥገና በሚደረግት ጊዜ በማከማቻ ውስጥ ያለውን ግብዓት መጠንና አይነት የሚያስታውሳቸው ሲስተም የላቸውም። በዚህ ምክንያት ብዙ አላስፈላጊ ወጪ የሚያወጡ ድርጅቶች መኖራቸውን ታዝቢያለሁ። እኔ የሰራሁት ሶፍትዌር እነዚህን ሁሉ ችግሮች የሚፈታላቸው ነበር።
ይህንን ችግር ይፈታል ብዬ የሰራሁትን ሶፍትዌር ለተወሰኑ ኩባንያዎች በነፃ ሁሉ ሰጥቼ ነበር። ብዙዎቹ ሲስተሙን ቢወዱትም ግን እኔን ማመን ከበዳቸው። ደግሞ ሶፍትዌሩ ጀምሮ በሽያጭም ሆነ ውል የምፈርመው እኔ መሆኔ ብዙ አላስደስታቸውም ነበር። አንዳንዶቹም ቅድሚያ ክፍያ ከከፉሉኝ በኋላ የምጠፋባቸው መስሏቸው የሰጉም ነበሩ። የሚገርምሽ ግን ባሉኝ ጊዜ እያቀረቡክ፤ ሲስተሙም በተሳካ ሁኔታ እየሰራና ምንም ሳያጎድል ህጋዊ ሰብዕና ኖሮኝ ሳለ ውል እንፈራረም ስላቸው ያፈገፍጉ ነበር። ልክ ሲስተሙ ሁለት ወር ሲሞላው ሲቋረጥባቸው ያለስምምነት መቀጠል እንደማልችል አሳወኳቸው። ያንን ደግሞ አቋርጬ ወደ ሌላ ምርት ማምረት ፊቴን አዞርኩኝ። ይህንን ሥራ ስጀምር ግን ተጨማሪ የሰው ኃይል የማይፈልግ በራሱ ገቢ የሚያመነጭ መፈለግ አለብኝ ብዬ አስብኩኝ። በዚያ መሰረት በአራት ወራት ውስጥ የአጭር መልዕክት የሎተሪ ሲስተም ዘረጋሁኝ። በነገራችን ላይ ሲስተሙን መሰረት በማድረግ ታላቁ ህዳሴ ግድብን ለማስተዋወቅ ጥያቄ አቅርቤ ነበር። ግን በአባይ ስም ምንም አይነት ሎተሪ መስራት አይቻልም ተባለና ተውኩት። በመቀጠል ደግሞ ብዙ የሴቶች ማህበራት ጋርም ሄጄ ነበር። አንዳንዶቹ ወንበርና ጠረጴዛዎቻቸው አቧራ የመታቸውና ሥራ የማይሰሩ ነበሩ። ለዚህ ምክንያት ደግሞ የበጀት ችግር እንደሆነ ነገሩኝ። በአጭር የስልክ መልዕክት ሎተሪ ድርጅታቸውን በማስተዋወቅ እኔ መንግሥት ከሚሰጠኝ 10 በመቶ ድርሻ አምስቱን ብቻ ወስጄ አብረን እንድንሰራ ብጠይቃቸውም አብሮኝ ለመስራት የደፈረ አልነበረም።
በመጨረሻ በሱባ መናገሻ ላይ ከጓደኞቼ ጋር ችግኝ በተከልኩበት ወቅት በአጋጣሚ ከመናፈሻው ሥራአስኪያጁ ጋር ስንነጋገር ድርጅቱ የሚተዳደረው እንጨትና ችግኝ እየሸጠ ብቻ መሆኑን፤ ከመንግሥትም ምንም አይነት ድጋፍ እንደማያገኙ ነገሩኝ። ይህ ሰው ስለአጭር የስልክ መልዕክቱ ሎተሪ ሳጫውተው አብሮኝ ለመስራት እንደሚፈልግ ነገረኝ። የዚያኑ ቀን አብሮኝ አዲስ አበባ መጥቶ ውክልና ሰጥቶኝ አብረን ለመስራት ተስማማን። በወቅቱ የሚያምንብኝ አንድ ሰው መገኘቱ ብቻ እጅግ አስደስቶኝ ነበር። ፕሮፖዛሉን ለብሔራዊ ሎተሪ ካስገባን ከአንድ ሳምንት በኋላ ጠርተውን ሁሉም ነገር ተጠናቆ ለህዝብ ሊለቀቅ ሲል በተመሳሳይ ሰዓት የህዳሴ ግድቡ ሎተሪ ይፋ ሊደረግ ስለሆነ ያንን ሎተሪ ማካሄድ እንደማንችልና ፍቃድ ሊሰጡን እንደማይችሉ ነገሩኝ። መጀመሪያም ቢሆን የአባይ ሎተሪ ሃሳብ አቅርቤ አልተቀበሉኝም፤ እንደገና አሳምኜ የሱባውን ፕሮጀክት ይዤ ስመጣ መከልከሌ እጅግ በጣም አሳዝኖኝ ነበር። ምክንያቱም ለእኔ በጣም ከባድ ነበር።
ከዚያ እንደወጣሁ ግን ከመንግሥት ጋር የማያገናኘኝና ፈቃድ የማይፈልግ ሌላ ሥራ መስራት እንዳለብኝ ራሴን አሳመንኩኝ። በመቀጠል ችግሮችን መፈለግ ጀመርኩኝ። አብረውኝ የሚሰሩትን ሁሉ በየዕለቱ የሚያጋጥማቸውን ችግር እንዲነግሩኝ እወተውታቸው ስለነበረ የታክሲው ችግር ጎልቶ ወጣ። እኔ ራሴ ማታ አምሽቼ ስወጣ ትራንስፖርት ማግኘት በጣም ነበር የምቸገረው። ከሌሊቱ ስድስትና ሰባት ሰዓት ላዳ ተከራይቶ መሄድ በጣም ያስፈራል። ብዙዎቻችን ደግሞ ታርጋ ይዘን አንገባም፤ በዚህ የተነሳ ብዙ ችግር የደረሰባቸው ሰዎች እንዳሉ እናውቃለን። አንዳንዱም የትራንስፖርት አገልግሎት ለመስጠት ሳይሆን ለሌላ አላማ የሚንቀሳቀስ ይሆናል። ያ ሁኔታ ብዙዎቻችንን ያስጨንቀን ነበር። በተለይ እኔ አምሽቼ ስሄድ በየደቂቃው የደረስኩበትን ስፍራ ለቤተሰቦቼ መልዕክት እልክ ነበር። ልክ እኔ የነበረኝን አይነት ስጋት ጓደኞቼ ላይ ነበር።
ከዚህ በመነሳት ሰውን የሚያስጨንቀውን ነገር የሚፈታ አንድ ኩባንያ ያስፈልጋል የሚል ድምዳሜ ላይ ደረስኩኝ። በተለይ አገልግሎቱን የሚሰጡት ሹፌሮች አድራሻና ማንነት በትክክል ታውቆና ሲስተም ውስጥ እንዲገባ አድርጎ ህብረተሰቡ አስተማማኝ የሆነ የትራንስፖርት አገልግሎት መስጠት አንድ ትልቅ እፎይታ ነው ብዬ አመንኩ። ምክንያቱም ችግር ቢፈጠር እንኳን ተጠያቂ የሚሆን ህጋዊ ተቋም መኖሩ ትልቅ ተቀባይነት ይኖረዋል። አዲሱን የራይድ ፕሮጀክቴን ለመስራት አራት ወር ገደማ ነው የፈጀብኝ። ሥራ ስጀምርም በ40ሺ ብር ይዤ ነው የተነሳሁት። ከአራት ወር በኋላ ራይድን ለህዝብ ይፋ ያደረግነው በአጭር የስልክ መልዕክት ነው። መጀመሪያ ላይ እኔ ፊት ለፊት አልወጣሁም። በስልክ ሰይፉ ፋንታሁን ጋር ደውዬ ስለሥራችን ነገርኩት። በስልክ ብቻ ታክሲ ጠርቶ አስተማማኝና ደህንነቱ በተረጋገጠ መልኩ አገልግሎት ማግኘት እንደሚቻል አስረዳሁት። በጣም ደስ አለውና ፕሮግራሙ ላይ አቀረበው።
ወዲያውኑ ደንበኞች የአገልግሎት ጥያቄ እየተበራከተ መጣ። እውነቱን ለመናገር መጀመሪያ ላይ አሽከርካሪው አይመዘገብም ብዬ ነበር የሰጋሁት። መጀመሪያ ቀን ሰባት ተሽከርካሪ ሲገባ በሶስተኛው ቀን 400 ተሽከርካሪ ደረሰ። በዚህ መልኩ ራይድ አሁን ከ43ሺ በላይ ተሽከርካሪዎችን ተጠቃሚ ማድረግ ችሏል።
አዲስ ዘመን፡- የትራንስፖርት አገልግሎቱ አዲስ ከመሆኑ ጋር ያጋጠመሽ ችግር ምን ነበር?
ወይዘሪት ሳምራዊት፡- እንግዲህ ራይድ ቶሎ ተቀባይነት ቢያገኝም በመሃል ግን ተግዳሮቶች አልነበሩም ማለት አይደለም። የመሰረተ ልማት ችግር ነበረ፤ በተለይ የኢንተርኔት አገልግሎት መቆራረጥ ጉዳይ ሥራችን ላይ ትልቅ እንቅፋት ፈጥሮብናል። በወቅቱ ከነበሩት ከኢትዮ-ቴሌኮም ሥራአስፈፃሚ ጋር ከተነጋገርን በኋላ ግን በአፋጣኝ ጥገና ተደርጎልን ሥራችንን በተቀላጠፈ ሁኔታ ማካሄዳችንን ቀጥለናል። ከሁሉ በላይ ግን በመገናኛ ብዙሃን ድርጅታችንን ለማስተዋወቅ የምንከፍለው ክፍያ ከፍተኛ መሆኑ እንደጀማሪ ድርጅት እጅግ ተፈታትኖን ነበረ። ለረጅም ጊዜ ደግሞ ለአሽከርካሪዎች ለማስተዋወቅና ስልጠና ለመስጠት ከፍተኛ ወጪ እያወጣን ስለነበርና ገቢም እያገኘን ስላልነበር የግድ ባለሃብቶችን ማሳተፍ እንደሚገባን አመንን። ግን በሥራው አምኖበት ከእኛ ጋር ተባብሮ ለመስራት የሚፈልግ ባለሃብት ማግኘት ሌላው ፈታኙ ጉዳይ ነበር።
በተለይ ሌላ ጀማሪ ኩባንያ ላይ ኢንቨስት የማድረጉ ባህል በእኛ ሃገር አልተለመደም። ሁለተኛ ደግሞ ቴክኖሎጂ ላይ ኃላፊነቱን ወስዶ መዋለንዋዩን ማፍሰስ የሚፈልግ ሰው ማግኘት ከባድ ነበር። ምክንያቱም ቶሎ ትርፍ የሚገኝበት ዘርፍ ባለመሆኑ ነው። ባንኮች ሳይቀሩ በኮላተራልም ቢሆን ማበደር አይፈልጉም። ማይክሮ ፋይናንሶችንም ስንጠይቅ ከ70 ሺ ብር በላይ ሊያበድሩን እንደማይችሉ ነው የነገሩን። ይህ ብር ደግሞ ለእኛ ምንም ሊሰራልን አይችልም። የሚገርምሽ ትልልቅ ኩባንያዎች ሳይቀሩ ቶሎ ትርፍ የሚሰጣቸው ካልሆነ አብረው ለመስራትም ሆነ ለመደገፍ አይፈልጉም። ስለዚህ ውጭ የሚኖሩት የተለያዩ ሰዎች ጋር በመፃፃፍ ስለኢንቨስትመንቱ ማስረዳትና አብረውኝ እንዲሰሩ ወደ መጠየቁ ገባሁ። ከፃፍኩላቸው ሰዎች ውስጥ አንድ ካናዳ ውስጥ የሚኖሩ ሰው ብቻ ነበር ምላሽ የሰጠኝ። እኚህ ሰው ደግሞ በቴክኖሎጂ ላይ 25 ዓመት የሰሩ መሆኑንና ሃሳቤን እንደወደዱት ገለፁልኝ። ወደ ኢትዮጵያ እንደመጡ ተገናኝተን አወራን፤ ከጥቂት ቀናት በኋላ ግለሰቡ ቃላቸውን ጠብቀው ያለምንም ህጋዊ ስምምነት በአካውንቴ የተወሰነ ገንዘብ አስገቡልኝ። እኔም ከብዙ ጥረት በኋላ እምነት የሚጥልብኝ ሰው በማግኘቴ የዚያኑ ቀን ራይድን ትልቅ ድርጅት አድርጌ ሰዎቹን ተጠቃሚ ለማድረግ ለራሴ ቃል ገባሁኝ።
ሁለተኛውም ኢንቨስተር በተመሳሳይ መልኩ ድጋፍ አደረገልንና በጣም በትንሽ ብር ትልቅ ድርጅት አደረግነው። ለዚህ ስኬት የበቃሁት በራሴ ብቻ ሳይሆን እንዳልኩሽ የእነዚህ ግለሰቦች ድጋፍ በመታከሉና ጠንካራ የሆኑ ሰራተኞች ስላሉኝ ጭምር ነው። በተለይ ከትንስፖርት ሚኒስቴር ጋር በነበረው ውዝግብ ቢሯችን ሲታሸግ በረንዳ ላይ ሁሉ ቁጭ ብለው ነበር ሲሰሩ የነበሩት። አሁን ከእኛ በኋላ በርካታ የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ ድርጅቶች ተበራክተዋል። በዚህ ደስተኛ ነኝ።
አዲስ ዘመን፡- አሁን ላይ የድርጅትሽ አቅም ምንላይ ደርሷል? ለምን ያህል ዜጎችስ የሥራ እድል መፍጠር ተችሏል?
ወይዘሪት ሳምራዊት፡- ራይድ ዛሬ ለ43ሺ ተሽከርካሪዎች የሥራ እድል ፈጥሯል። 500 ቋሚ ሰራተኞች አሉን። አብዛኞቹ ሴቶች ሲሆኑ ቁጥራቸው ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ደግሞ ገና ከዩኒቨርሲቲ እንደተመረቁ የገቡ ናቸው። ይህ ሁሉ በሰባት ዓመታት ውስጥ የተከሰተ ነገር ነው። ይሄ ሁሉ የሆነው ደግሞ ቴክኖሎጂን በማቀላጠፍ ነው። ለእነዚህ ሁሉ አሽከርካሪዎች የሥራ እድል ተፈጠረ ማለት በሥራቸው የሚተዳደሩ የቤተሰብ አባላትን በሙሉ ነው ተጠቃሚ የሚያደርገው። ብዙ አሽከርካሪ ኑሮውን ከመደጎም አልፎ ተጨማሪ ሃብት አፍርቷል፤ ሌላ መኪና ገዝቷል፤ የራሳቸውን ድርጅት ከፍተዋል። ከሁሉ በላይ በዚህ ድርጅት ውስጥ የሚሰራው አብዛኛው ወጣት መሆኑ ለሌላውም ወጣት መነሳሳት ፈጥሮለታል ብዬ አምናለሁ። ማንኛውም የሥራ ፈጠራ ሃሳብ ያለው ወጣት ከዜሮ ተነስቶ መለወጥና ማደግ እንዲችል አርዓያ ሆነዋል። በአጠቃላይ ራይድ የብዙዎችን አይን ገልጧል ብዬ አምናሁ። ከዚህ ባሻገር ማህበረሰቡ የሥራ ፈጠራ አማራጮችን እንዲመለከት የተለያዩ ስልጠናዎችን እንሰጣለን።
አዲስ ዘመን፡- የእናንተ ድርጅትን ተከትሎ ተመሳሳይ አገልግሎት የሚሰጡ ኩባንያዎች መከፈታቸው ለእናንተ ድርጅት ስኬት ነው ወይስ ተግዳሮት?
ወይዘሪት ሳምራዊት፡- ለእኔ ተመሳሳይ ድርጅቶች መከፈታቸው ተግዳሮት ወይም ስጋት ሊሆንብኝ አይችልም። ምክንያቱም ራይድ አሁን ያለበት ቦታ ላይ ለመድረስ ብዙ መንገድ መጓዝ ጠይቆታል። ይህም በመሆኑ አሁን ለሚከፈቱት ድርጅቶች መንገድ ጠርገናል። በተለይም ከመንግሥት ድርጅቶች ጋር መጋጨት ቀላል ነገር አይደለም። በመሰረቱ እኔ ይህንን ሥራ ስንጀምር ከመንግሥት ትልቅ ድጋፍ አገኛለሁ ብዬ ነበር። ምክንያቱም ወጣት ሥራ ፈጣሪዎችን ያበረታታሉ፤ ሴቶችም ይደገፋሉ የሚል መርህ ስላለ ነው። ወይዘሪት ሳምራዊት ከዚህ አንፃር ሁለቱንም ታሟላለች። ስለዚህ እንዲህ አይነት ፈታኝ ሁኔታ ያጋጥመኛል ብዬ አልገመትኩም ነበር። ሲመጣ ግን በዚህ ምክንያት ተስፋ ቆርጬ ለመቀመጥ አላማ አልነበረኝም። የእኔ ራዕይ በቴክኖሎጂ ገና ኢትዮጵያን ማስተዋወቅ ነው።
በአሁኑ ወቅት ወደ ምስራቅ አፍሪካ ሥራችንን በማስፋት የሃገራችን ገፅታ መገንባት ነው አልመን እየሰራን ያለነው።እኛ ኢትዮጵያውያን በሩጫና በቡና ብቻ ሳይሆን በዓለም ላይ መታወቅ ያለብን በቴክኖሎጂም መታወቅና የሃገራችንንም ስም ማስጠራት መቻል አለብን። በአጠቃላይ የእኔ ራዕይ ገና በአፍሪካ ጭምር ገናና የሆነ የቴክኖሎጂ ኩባንያ መፍጠር በመሆኑ አሁን ላይ ተመሳሳይ ድርጅቶች መከፈታቸው ለእኔ ስጋት አልሆነብኝም፤ ከአላማዬም ወደኋላ አያስቀረኝም። ገና በጣም ትንሽ ነገር ነው የሰራነው፤ ብዙ አዳዲስ የፈጠራ ሥራዎችንና ቴክኖሎጂዎችን እያሻሻልን ነው የምንሄደው።
በነገራችን ላይ አዲስ አበባ ውስጥ ካለው ችግር ውስጥ ገና 15 በመቶውን ነው ተደራሽ እያደረግን ያለነው። ይህም ቢሆን አውቶብስና ሌሎችም ታክሲ አገልግሎት የሚሰጡትንም ጨምሮ ነው። ስለዚህ ቀሪውን 85 በመቶ የሚሆነውን ህዝብ እንዴት ማገልገል እንዳለብን ነው ማሰብ ያለብን። የምፈልገው ግን ጤናማ የሆነ የሥራ ውድድር እንዲኖር ነው።
አዲስ ዘመን፡- ግን ከእናንተ በኋላ የተፈጠሩ አንዳንድ ድርጅቶች በአገልግሎት በቅልጥፍናም ሆነ በቴክኖሎጂ ሥራቸውን አስፍተው የያዙ አሉ፤ በዚህ ረገድ ራይድ ምን አስቧል?
ወይዘሪት ሳምራዊት:- በመሰረቱ አሁን ላይ ሌሎቹ ኖሯቸው ራይድ የሌለው አሰራርም ሆነ ቴክኖሎጂ የለም። ልክ እንደሌላው ሁሉ እኛም የኮርፖሬት ወይም የብድር አገልግሎት የምንሰጣቸው ድርጅቶች አሉን። አሁን ላይ ከ500 በላይ የሚሆኑ የኮርፖሬት አገልግሎት ተጠቃሚዎች አሉን። ለምሳሌ ብጠቅስልሽ የእስራኤል፤ የእንግሊዝ ኤምባሲን፤ መሬት አስተዳደር ማንሳት እንችላለን። ይሄ ቀድሞም የምንሰጠው አገልግሎት ነው። ክፍተት አይቶ መፍትሄ የሚሆን አሰራር ይዞ መምጣት የቢዝነሳችን መርሆም ስለሆነ በዚህ ረገድ ስጋት የሚሆንብን ነገር አለ ብዬ አላምንም። እርግጥ ነው ከኑሮ ውድነቱ፤ የነዳጅ ዋጋ በየእለቱ ከመጨመሩና መንግሥትም ለዘርፉ ድጎማ የማያደርግ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ አሽከርካሪዎቹ ላይ የሚፈጠር ጫና መኖሩን እንገነዘባለን። የእነሱን ተጠቃሚነት ለማሳደግ ከመንግሥት ጋር ከመከራከሩ ጎን ለጎን ገቢያቸው የሚጨምርበት መንገድ እየሰራን ነው ያለነው።
ከሰሞኑ እንዳያችሁት ደግሞ ከኢትዮ-ቴሌኮም ጋር በመተባበር የሲም ካርድ ሽያጭ እንዲሰሩ ማድረግ ጀምረናል። ሲም ካርድ በሸጡ ቁጥር የሚያገኙት ገቢ በተጨማሪ ኮምሽን እንዲያገኙ አድርገናል። ከዚህም ባሻገር የቴሌ ብር ወኪል ናቸው፤ ወኪል በመሆናቸው ትራንዝአክሽን በተካሄደ ቁጥር የሚያገኙት ኮምሽን አለ። ከአስር በላይ በሚሆኑ ሆስፒታሎች የጤና አገልግሎት በቅናሽ እንዲያገኙም ምቹ ሁኔታ ፈጥረናል። በሥራ ላይ አደጋ ቢያጋጥማቸው ቅድሚያ ክፍያ ሳይጠየቁ የጤና አገልግሎት የሚያገኙበትም እድል ተመቻችቶላቸዋል። አንድ ዓመት ያህል የቆጠቡ አሽከርካሪዎች መኪና የሚገዙበት ስርዓት ከባንኮች ጋር በመግባባት ተበጅቶላቸዋል። ግብር መክፈል የተቸገሩትንም እኛ እናግዛለን።በቅርቡ እቁብ የተሰኘ ፕሮጀክት ይፋ እናደርጋለን። ይህንን የቁጠባ ዘዴ ተጠቅመው ራሳቸውን እንዲለውጡ የሚደረግ ነው የሚሆነው። ይህም የሚያሳየው አሽከርካሪዎቻችን ምቹ ሁኔታ ተፈጥሮላቸው እንዲሰሩ የተደረገውን ጥረት ነው። ከሁሉ በላይ በኮድ ሶስት የታክሲ አገልግሎት ህጋዊ ማዕቀፍ እንዲኖረው በማድረግ ራይድ ያበረከተው አስተዋፅኦ ከፍተኛ ነው። ከመንግሥት ጋር ታግለን ህጋዊ አሰራር ባይዘረጋ ኖሮ ዛሬ ላይ እኛም ሆነ ሌሎቹ ትራንስፖርት ሰጪ ድርጅቶች ባልኖሩ ነበር።
አዲስ ዘመን፡- እንዳአንቺ እውቀት ኖሯቸው መንገዱ ለጠፋባቸው ሴቶች ምን መልዕክት ማስተላለፍ ትፈልጊያለሽ?
ወይዘሪት ሳምራዊት፡– የእኛ ባህል ሴትን በጣም የሚጫን ነው። እኔ ግን ፈጣሪ ይመስገን በጣም ከጎኔ ሆነው ሲረዱኝ የቆዩ ቤተሰቦች ናቸው ያሉኝ። ግን ሁሉም ነገር ቤተሰብ ጋር ይቀራል ማለት አይደለም። ወጣ ስትይ ማህበረሰቡ ቶሎ ሊቀበልሽ ይቸግረዋል። እኔም እንዳልኩሽ ምርቴን ይዤ ስወጣ ያለማመን ነገር ነበር። ይህ በራሱ አንድ ተግዳሮት ነበር፤ ግን አንድ የራሴ የሆነ መርህ አለኝ፤ ይኸውም ችግርን በራሱ እንደአንድ እድል መጠቀም ነው። ችግር ከመጣ ራሴን ሞግቼ ካሸነፍኩም ሆነ ከተሸንፍኩኝ ተምሪያለሁ ነው የምለው። የሕይወት ተሞክሮዬም እያደገ ነው የሚመጣው። ይህ ማለት ግን ሁልጊዜ ችግር እያጋጠመኝ እቅዴ እየከሸፈ መኖር አለብኝ ማለት አይደለም። ግን የሰራኋቸውን ስህተቶች ደግሞ እንዳልሰራ ጥንቃቄ አደርጋለሁ፤ ተምሬበት ነው የማልፈው። በሌላ በኩል ለራሴ ግልፅ መሆን እንዳለብኝ አምናለሁ፤ ራሴን አልዋሸውም፤ ጥንካሬዬን እንደማውቀው ሁሉ ጉድለቴንም ጠንቅቄ ነው የማውቀው። ከእኔ በተሻለ ጠንካራ ስብዕና ያላቸውን ሰዎች አናግራለሁ፤ እጠይቃለሁ። በየቀኑ ራሴን እያሳደኩ ነው የምመጣው።
ሌላኛው ትልቁ ነገር ደግሞ ሁለቱም ፆታ እኩል ነው ብዬ አምናለሁ። እኛም እንደወንዶቹ የሚያስብና የሚሰራ ጭንቅላት አለን። ስለዚህ ከእነሱ እኩል የፈለግነው ቦታ ለመድረስ የሚያግደን ነገር አይኖርም። አስቀድሜ እንዳልኩሽ ቀደም ብዬ በሰራኋቸው ሁለት ሥራዎች ማህበረሰቡ አልተቀበለኝም፤ ሶስተኛውን ስጀምር ግን ለተወሰነ ጊዜ ራሴን ደብቄ ነበር። ያ ደግሞ የስትራቴጂ አካል ነው እንጂ ሽንፈት አይደለም። ምርቴ ከታወቀና ከተለመደ በኋላ የእኔ ማንነት ሲታወቅ ማህበረሰቡ ለመቀበል አላዳገተውም፤ እኔም አልታገልኩም። ስለዚህ የተለያዩ ስትራቴጂዎች እየሞከርን ራሳችንን ማሳደግ አለብን። በሥራችን ስኬታማ ለመሆን ራዕያችን ላይ ግን ሁልጊዜ ትኩረት ማድረግ አለብን።
አዲስ ዘመን፡-ለነበረን ቆይታ በአንባቢዎቼና በዝግጅት ክፍሉ ስም ከልብ ላመሰግን እወዳለሁ።
ወይዘሪት ሳምራዊት፡- እኔም አመሰግናለሁ።
ማህሌት አብዱል
አዲስ ዘመን ግንቦት 27/2014