የሕዳሴ ግድቡ – ቀጣናዊ ፋይዳ

በድል እና በፈተና ውስጥ ያለፈ ግድብ ነው – ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ፡፡ ኢትዮጵያውያኑንና የኢትዮጵያን መንግሥት ድሉ እንዳላስታበየው ሁሉ ፈተናውም ለአፍታ እንኳን ቢሆን አላስጎነበሰውም፡፡ ሕዝቡም ሆነ መንግሥት ፈተናው በጸናበት ጊዜ ሁሉ አንድነቱን ይበልጥ አጠናክሮ እያንዳንዱን ሴራ እና ዓይን ያወጣ ተጽዕኖን በብቃት መወጣት ችሏል፡፡

ትናንት የነበረው የኢትዮጵያ ታሪክ ያለመሸነፍ ነው፤ ዛሬም የተስተዋለውና የተደገመው ይኸው ያለመሸነፍ ታሪኩ ነው፡፡ የሕዳሴ ግድቡ የመሠረት ድንጋይ ከተቀመጠለት ጊዜ ጀምሮ ሕዝቡና መንግሥት ምንም እንኳ የተጋረጣቸው ፈተናዎች በርካታ ቢሆኑም፤ ፈተናዎቹ ብርታት ሆነውት የሕዳሴ ግድቡን ከጫፍ አድርሶታል፡፡ አለመሸነፉንም በዓለም አደባባይ አስመስክሯል፡፡

በቅርቡ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በሚገኝበት ጉባ ተከስተው ሁለት ተርባይኖች ኃይል ወደ ማመንጨት መሸጋገራቸውን አብስረዋል፤ በወቅቱ እንደተናገሩትም፤ በአሁኑ ጊዜ በነበሩት ሁለት ተርባይኖች ላይ ሁለት በመታከላቸው አራት ተርባይኖች ኃይል በማምረት ላይ ይገኛሉ፡፡ ምናልባትም ቢበዛ እስከ ታኅሣሥ ወር ላይ ተጨማሪ ሦስት ተርባይኖች ሥራ ይጀምራሉ። በጥቅሉ ኢነርጂ የሚያመርቱትን የተርባዮኖች ቁጥር ሰባት ያደርሰዋል ማለት ነው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ “ውሃው የጋራ ሀብታችን ነው፡፡ የእኛ ኃላፊነት እንደ ሀገር እና እንደ ሕዝብ የሚገባንን ያህል ተጠቅመን የሚገባቸውን ያህል ደግሞ ለወንድሞቻችን ማካፈል ነው፡፡” ሲሉ በወቅቱ ተናግረዋል፡፡ እናካፍል ያልነው ውሃ ነው ያሉት ዐቢይ (ዶ/ር)፣ ከዚህ ቀደምም ግሪን ሌጋሲን እናካፍል ብለናል። ችግኞችን በነፃ እንስጥ ብለናል። ነገ በጣም በቅርቡ ስንዴ እናካፍላለን።” ሲሉ ማብራራታቸውም የሚታወስ ነው፡፡ እናም ይህ ለታችኛው የተፋሰስ ሀገራት ትልቅ በረከትና ሲሳይ ነው ሲሉም ያስረዳሉ፡፡

ምንም እንኳን ዛሬ ግብጽ ጦሯን ሰብቃ ዘገር ነጥቃ ለጦርነት ብትጋበዝም፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጉባ ሆነው ያስተላለፉት መልዕክት፣ “የሱዳን ወንድሞቻችን እንኳን ደስ አላችሁ፡፡ ተጨማሪ ውሃ አግኝታችኋል፡፡ ይህም ውሃ የጋራችን ነው፤ ትጠቀሙበታላችሁ፡፡ የግብጽ ወንድሞቻችን እንኳን ደስ አላችሁ፡፡ ተጨማሪ ውሃ ዛሬ ጨምረንላችኋል፡፡ አረንጓዴ ዐሻራ በቂ ዝናብ ስላመጣ አፍስሰንላችኋል፤ ወደፊትም ይቀጥላል፡፡” የሚል ነው፡፡

እርሳቸው እንዳሉትም፤ ተባብረን ተጋግዘን ቀጣናችንን እናሳድጋለን ነው፡፡ በትብብር መንፈስ መሔድ ከተቻለም ውሃው ለሁሉም ጠቃሚና የሚበጅ እንደሚሆን ያላቸውን ተስፋም ገልጸዋል፡፡ እኛም በርግጥ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ መጠናቀቅ ለቀጣናው ያለው ፋይዳ ምንድን ነው? ስንል የዘርፉን ምሁራን አነጋግረናል፡፡

የምጣኔ ሀብት ባለሙያው እና የቀድሞው ዲፕሎማት አምባሳደር ጥሩነህ ዜና እንደሚሉት ከሆነ፤ የሕዳሴ ግድብ መጠናቀቅ ከሁሉም አስቀድሞ ለኢትዮጵያ ትልቅ ፋይዳ ያለው ነው፤ ከዚህ በተጨማሪ ለቀጣናው ያለው ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊም ሆነ ፖለቲካዊ ፋይዳው ሰፊ ነው፡፡

ኢትዮጵያ በምታካሂደው ልማታዊ እንቅስቃሴም ሆነ ሰላም በማስከበሩ ረገድ ቀጣናውን እስከ መምራት ምሳሌ መሆን የምትችል ናት፡፡ አሁንም የሚጠበቅባት ይህንኑ ተግባር እየፈጸመች መሆኑን፣ በተለይም ቅኝ ገዥዎች ያስቀመጡት የውሀ ሕግ ከግብጽና ከሱዳን በስተቀር ሌሎቹን የተፋሰሱን ሀገራት የሚበድል ሲበድልም የኖረ መሆኑን አስታውሰዋል፤ ይህ እንዴት ተቻለ? በሚያስብል ሁኔታ ግን ኢትዮጵያ ታላቁን ግድብ ሰርታ ማስመስከር ችላለች ብለዋል፡፡

ቅኝ ገዥዎቹ ያስቀመጡት ሕግ ኢትዮጵያን ሲበድል የኖረ ነው፤ ነገር ግን ኢትዮጵያ 85 በመቶ የውሀው አመንጪ ሀገር ሆና እንዲሁም ለተፋሰሱ ሀገራት የምትሰጥ ሀገር ጭምር ሆና ሳለ ሕጉ ውሀውን እንዳትጠቀም አድርጎ የኖረ ነው ያሉት የምጣኔ ሀብት ባለሙያው፣ ከዚህ በኋላ ግን ሕግና መርህን በመከተል እንደዚህ ቀደሙ ሁሉ ኢትዮጵያ ለብዙ የአፍሪካ ሀገሮች አርአያ ትሆናለች ሲሉ አብራርተዋል፡፡ ኢትዮጵያ በብዙ መንገድ ቀዳሚ ናት፤ ብዙዎችም አርአያዋን ተከትለዋል፡፡ ምክንያቱም ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደምም ፈረንጅን ማሸነፍ ችላለች፡፡ በዚህም ነፃነቷን ማስከበር ችላለች፡፡ ብዙዎችም ለነፃነታቸው ሲሉ ኢትዮጵያን ተከትለዋታል ይላሉ፡፡

ኢትዮጵያ ለቀጣናው ያላት አበርክቶ ከፍ ያለ ነው ሲሉ የሚናገሩት አምባሳደር ጥሩነህ፣ “የአፍሪካ ኅብረትም ሲቋቋም ኢትዮጵያ ቀዳሚ ነበረች ብለዋል። በዚህ ረገድ የታየው እንቅስቃሴዋ የኢትዮጵያን የመምራት አቅም ያሳየ ነው፡፡ ስለዚህ ዛሬም የተደገመው ይኸው የመምራት አቅም እንዳላት ሲሆን፣ ይህንንም በሕዳሴ ግድብ በተግባር ማሳየት ችላለች ሲሉ ተናግረዋል፡፡

የሕዳሴ ግድብ መጠናቀቅም ኢትዮጵያውያንንም ሆነ የቀጣናውን ሀገራት የሚያበረታታ ነው፡፡ ልክ በዓድዋ ጦርነት ነጮች በኢትዮጵያ እንደተሸነፉና አፍሪካውያንም የኢትዮጵያን ማሸነፍ አስተውለው ጠፍንጎ ከያዛቸው የባርነት ቀንበር እንዴት መውጣት እንደሚችሉ ምሳሌ ሆናለች፡፡ አሁንም በዚህ ጉዳይ ላይ በውሀችን የመጠቀም መብት አለን እንዲሉ ያደረገ ተግባር ኢትዮጵያ አከናውናለች ሲሉ አስረድተዋል። ምክንያቱም አፍሪካውያኑ፣ ‘እኛም ማሸነፍ እንችላለን፤ ምክንያቱም ኢትዮጵያ አሸንፋለች’ ብለው እንደተንቀሳቀሱ ሁሉ የሕዳሴ ግድብ መጠናቀቅ በመቻሉ፤ ‘እኛም ባለን ሀብት መጠቀም እንችላለን’ የሚል ስሜት ይፈጥርባቸዋል፡፡ ይህ ደግሞ ለቀጣናው ትልቅ ነገር ነው ሲሉ አመልክተዋል፡፡ ስለዚህም በቀላሉ የሚታይ አይደለም ባይ ነኝ ይላሉ፡፡

በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ መምህር የሆኑት አለምሰገድ ደበሌ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የኢትዮጵያን መንግሥትና ሕዝብ ጥንካሬ ያሳየ ግድብ ነው ይላሉ፡፡ ካለፉት አስራ ሶስት ዓመታት ጀምሮ ያለ አንዳች መሰልቸት ሲሰራበት የቆየና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ በተለይ ባለፉት አራት ዓመታት ከፍተኛ ጥረት ታክሎበት ውሀ መያዝ የቻለ፤ ተጨባጭ ለውጥም ማሳየት መጀመሩንም አስረድተዋል፡፡

አለምሰገድ (ዶ/ር)፣ የዓባይ ወንዝ መነሻው ከእኛ ነው ይላሉ፡፡ በመሆኑም የመጠቀም ሙሉ መብት እንዳለን ሊዘነጋ አይገባም በማለት ያመለክታሉ፡፡ ይህ መብታችን ከንግግር ባለፈ በሥራ የተገለጠ በመሆኑም ግድባችንን ሰርተን ማሳየት የቻልን ሕዝብ ነን ሲሉም ያረጋግጣሉ፡፡

እርሳቸው እንደሚናገሩት፤ ልክ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እንዳሉት የሕዳሴ ግድቡ ለቀጣናው ሀገራት ፋይዳው የጎላ ነው፡፡ የመጀመሪያ የቀጣናውን ሀገራት ማስተሳሰር የሚችል ግድብ መሆኑ ነው፡፡ ትልቁና ዋናው ነገር የኃይል ጉዳይ ሲሆን፣ ከዚህ የተነሳ የሕዳሴ ግድቡ መጠናቀቅ ተፈላጊውን ኃይል ማግኘት የሚያስችል ነው፡፡

የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በእስካሁኑ ሂደት አራት ተርባይኖች ኃይል ወደ ማመንጨት ሂደት እንዲገቡ አድርጓል፤ በቀጣይ ደግሞ በጥቂት ጊዜ ውስጥ ተጨማሪ ተርባይኖች ኃይል ያመነጫሉ። ሙሉ በሙሉ ወደ ሥራ ሲገባ ደግሞ የተፈለገውን ያህል የኃይል አቅርቦት ስለሚኖር በቀጣናው ላይ ያለውን ኃይል ማሳደግ ይችላል ሲሉ ያብራራሉ፡፡ በአካባቢያችን ያሉ ጎረቤት ሀገሮች የኃይል ምንጫችንን መጠቀም ይችላሉ፡፡ የሕዳሴ ግድብ መጠናቀቁ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦትን ከማሳደግ ጎን ለጎን ይህን ጠቀሜታ ለማግኘት እንቅስቃሴ ውስጥ በጋራ መሥራት እና መተባበርን ይጠይቃል፡፡ በጋራ መሥራት ውስጥና በትብብር ውስጥ ደግሞ ኅብረት ይኖራል ይላሉ፡፡

አለምሰገድ (ዶ/ር) እንደሚናገሩት፤ የሕዳሴ ግድቡ መጠናቀቅ ሌላኛው ቀጣናዊ ፋይዳው የጋራ እድገት እንዲመጣ በር መክፈቱ ነው፡፡ እርሱን ተከትሎ የተለያዩ ፕሮጀክቶች ወደ ሥራ የሚገቡ ስለሚሆኑ ድህነትን ለመቀነስ ያግዛል፡፡ አስተማማኝ የኃይል አቅርቦት ስለሚኖርም ኢንቨስትመንትን ያሳልጣል፡፡ የኃይል አቅርቦት አለ ማለት ኢንቨስተሮች ከኃይል ጋር ተያይዞ የሚመጣ ተግዳሮት አይኖርባቸውም እንደማለት ነው፡፡

አምባሳደር ጥሩነህ፣ በበኩላቸው፤ የሕዳሴ ግድቡ መጠናቀቅ ከኢኮኖሚው አንጻር ሲታይ ከፍተኛ ጥቅም አለው ይላሉ፡፡ ልክ እንደ አለምሰገድ (ዶ/ር) ሁሉ ኃይል በአሁኑ ጊዜ በጣም ወሳኝ ነው ይላሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት ቴክኖሎጂው እጅግ እየተራቀቀ መሔዱን ተያይዞታል ሲሉ ጠቅሰው፤ ለዚህ የቴክኖሎጂ መሳለጥ ኃይል ከፍተኛ ድርሻ አለው ሲሉ ያስረዳሉ፡፡

አምባሳደሩ እንደሚሉት፤ ኢትዮጵያ ለአፍሪካ የሚበቃ ኃይል አላት፡፡ ያንን አቅሟን አሁን ማሳየት ጀምራለች፡፡ ይህ ብቻ አይደለም፤ ኢትዮጵያ አሁን እያመረተች ያለው ካላት አቅም አስር በመቶ ሊሆን ይችላል፡፡ ሙሉ አቅሟን ስትጠቀም አሁን ለሚመጣው ቴክኖሎጂ በጣም አስፈላጊ ስለሆነ ያንን ቴክኖሎጂ ለማስፋፋት የሚፈልጉ ሀገሮች ወደ ኢትዮጵያ ሊመጡ ይችላሉ፡፡

ኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድቡ እንኳ ገና ሳይጠናቀቅም ጎረቤት ሀገሮችን ስትጠቅም ቆይታለች፡፡ አሁንም ሊጠናቀቅ ከጫፍ የደረሰው ግድብ ከሚያመርተው የኤሌክትሪክ ኃይል ምርት እየተጠቀመች ያላቸው ለራስዋ ብቻ አይደለም፤ ካላት ሀብት ለአካባቢ ሀገሮች ማቋደስ ጀምራለች፡፡ ወደ ኬንያ፣ ወደ ሱዳን፣ ወደ ደቡብ ሱዳን እና እስከ ደቡብ አፍሪካ ድረስ ለመሔድም ፍላጎት አላት፤ ፍላጎት ብቻ ሳይሆን የሕዳሴ ግድብ ወደመጠናቀቁ ምዕራፍ መቃረቡ ፋይዳው ብዙ ነው የሚሉት አለምሰገድ (ዶ/ር)፣ ለቀጣናው ሀገራት የተሻለ የውሃ አጠቃቀም ሥርዓት እንዲኖረን የሚያደርግ ነው ሲሉ ያመለክታሉ፡፡ እንዲህ ሲባል ደግሞ ፍትሃዊ የውሀ ሀብት አጠቃቀምን የሚያካትት ነው ይላሉ፡፡

በናይል ተፋሰስ ሀገራት ላይ ፍትሃዊ የሆነ የውሃ አጠቃቀም አስተዳደር እንዲኖር ያደርጋል፡፡ ኢትዮጵያ አሊያም ግብጽ ብቻ የምትጠቀምበት ወይም ሱዳን ብቻ የምትጠቀምበት ሳይሆን ሁሉም የናይል ተፋሰስ ሀገራት እኩል በሆነ መልኩ የተፈጥሮ ሀብታችን በሆነው ውሃ መጠቀም እንዲችሉ የሕዳሴ ግድቡ በር የሚከፍት ነው፤ በዚያ ዓይነት መልኩ ቀጣናዊ ትስስርን በምስራቅ አፍሪካና በአፍሪካ ቀንድ ሊያመጣ ይችላል፡፡ በተጨማሪም የሕዳሴ ግድባችን ታዳሽ ኃይል እንደመሆኑ አሁን የምናያቸው በዓለም ላይ የሚታየው ዓይነት የአየር ንብረት ለውጥን የሚያስከትል አይደለም።

ከዚህ ባሻገር የሕዳሴው ግድብ መጠናቀቅ መሰልጠንን ጭምር የሚያመጣ ነው ይላሉ፡፡ አለምሰገድ (ዶ/ር) ለዚህ በምክንያትነት የጠቀሱት ስልጣኔዎች በአብዛኛው የመጡት ውሀ ባለበት አካባቢ ነው ሲሉ ያስረዳሉ፡፡

እንደ አለምሰገድ (ዶ/ር) ገለጻ፤ ለማደግ አብሮነት ትልቅ ድርሻ አለው፤ በጋራ መሥራት ደግሞ አብሮነትን ያጠናክራል፡፡ አብሮ ለመሥራት በሚደረግ ጥረት ውስጥ በቀጣናው ሀገራት ውስጥ ትስስርን ይፈጥራል። በሰላሙ ዙሪያም ለውጥን ማምጣት የሚችል ነው፡፡ በእነዚህ ጉዳዮች ላይ ከተግባባን እንዲህ ዓይነት ጥቅም አለው ከተባባልን አሁን እየተደረጉ ካሉት የቃላት ልውውጦች መውጣት እንችላለን፡፡ ያሉብን ችግሮች ተፈቱ ማለት ደግሞ ተግባባን ማለት ነው፡፡ ተግባባን ማለት ደግሞ ካለንበት ድህነትም ቀስ በቀስ መውጣት እንችላለን ማለት ነው፡፡

እንደ ዘርፉ ባለሙያዎች አባባል፤ ቀጣናዊ ትስሰር ቢኖረንና ብንግባባ ከግብጽ ጋር ያለን ግንኙነት መልክ ይይዛል፡፡ ከሌሎቹም እንደ ሱዳን ዓይነት ካሉ ጎረቤት ሀገራት እና ከናይል ተፋሰስ ሀገራት ጋር ያለን ግንኙነት ከቀደመው የተሻለ ይሆናል ማለት ነው፡፡ ይሁንና በዚህ ጉዳይ ላይ ብዙ መሥራት ይጠበቅብናል፡፡ የናይል ቤዚን ኢንሼቲቭ የሚባሉ ድሮ ሲሰራባቸው የነበሩ ዓይነቶች ላይ የተለያዩ መድረኮችን በመፍጠር መንቀሳቀስም ጠቃሚ ነው፡፡ መወያየትም እንዲሁ መልካም ነው፡፡ ዲፕሎማሲው ላይም መሥራት ጠቀሜታው የጎላ ነው።

ባለፉት ዓመታት በዲፕሎማሲው ላይ በመሠራቱ ብዙ ለውጦች መመዝገብ ችለዋል፡፡ እንደ እሱ ዓይነት ስኬት መምጣት የቻለውም ስለተሠራበት ነው፡፡ በዘርፉ ያሉ ምሁራንንም አሁንም ማሳተፉ ጠቀሜታ አለው። በተለይም ሙያዊ አበርክቷቸውን እንዲያበረክቱ ማድረግ አስፈላጊ ነው፡፡

ከዚህ ጋር በተያያዘ ውሀ እና ሰላምን አያይዞ መደረግ ያለባቸው ውይይቶች ካሉ ውይይት በማድረግ ቀጣናዊ ትስስሩንና ሰላምን ማምጣት እንዲችሉ ማድረግ ብልህነት ነው፡፡ ሁሉም የየራሱን እኩል የሆነ ጥቅም ካገኘ ወደ ሰላሙ ይሄዳልና በዚያ ላይ መሥራት አዋጭ ነው፡፡

ኢትዮጵያ ፈር ቀዳጅነቷ ተጠናክሮ እንዲቀጥል በሕዳሴ ግድብ ላይ ብቻ መወሰን አይኖርባትም፡፡ ሌሎች ግድቦችን መሥራት ኢትዮጵያ ኃይል የማምረትና ለሌሎች ማከፋፈል የምትችል ሀገር እንድትሆን የሚያደርጋት ነው፡፡ ይህ ደግሞ ለኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ጉልበት ይሰጣታል፡፡ በሀገር ውስጥ ያለውን የሥራ አጡን ቁጥር ለመቀነስና ኢኮኖሚን ይበልጥ ለማጠናከር ዓባይ ላይ ብቻ ሳይሆን ሌሎቹም ላይ መሥራት ያስፈልጋል፡፡ ትናንት እና ዛሬ የተገለጠው ትጋት ነገም ሊደገም ይገባል፡፡

አስቴር ኤልያስ

አዲስ ዘመን መስከረም 7/2017 ዓ.ም

 

Recommended For You