‹‹የኢትዮጵያ እና ህንድ ግንኙነት ከ2000 ዓመታት በላይ ያስቆጠረ ነው››  -ሚስተር አኒል ኩማር ራይ- በኢትዮጵያ የህንድ አምባሳደር እና የአፍሪካ ህብረት ቋሚ ተወካይ

ኢትዮጵያ እና ህንድ ጥንታዊ የስልጣኔ ታሪክ ያላቸው ሀገራት ሲሆኑ ከሰባት አስርት ዓመታት በላይ የዘለቀ የረጅም ጊዜ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት አላቸው። ግንኙነቱ ብዙ ዘርፎችን ማለትም ትምህርትን፣ ጤናን፣ ኢንዱስትሪን እና ንግድን ጨምሮ በጠንካራ መሠረት ላይ ያረፈ ሲሆን አሁን BRICS ሌላው አስፈላጊ የትብብር መድረክ ሆኗል።

የዛሬው ወቅታዊ እንግዳ በኢትዮጵያ የህንድ አምባሳደር እና የአፍሪካ ህብረት ቋሚ ተወካይ ሚስተር አኒል ኩማር ራይ ናቸው። የኢትዮጵያ ሄራልድ በሁለቱ ሀገራት መካከል ስላለው ግንኙነት ያላቸውን አስተያየት ለማግኘት ከአምባሳደር ራይ ጋር አጭር ቆይታ አድርጓል። መልካም ንባብ ይሁንላችሁ!

 ጥያቄ፤- በህንድ እና በኢትዮጵያ መካከል ላለፉት ዓመታት ያለውን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንዴት ያዩታል?

ሚስተር አኒል ኩማር ራይ፡- ኢትዮጵያ እና ህንድ ከታዳጊው ዓለም በጣም ጠቃሚ ሀገራት ሲሆኑ ታሪካዊ ግንኙነታቸው ከ2000 ዓመታት በላይ ያስቆጠረ ነው። ሁለቱም ሀገሮች በሁሉም ዘርፎች ልዩ የሆነ ሞቅ ያለ ግንኙነት አላቸው። እ.ኤ.አ. በየካቲት 2024 በኢትዮጵያ የሕንድ አምባሳደር ሆኜ ከተሾምኩበት ጊዜ ጀምሮ፣ በሁለቱም ሀገራት መሪዎች መካከል ከፍተኛ የዲፕሎማሲ ግንኙነት ሲደረግ ተመልክቻለሁ። እ.ኤ.አ. ኦገስት 17 ቀን 2024 ህንድ የታዳጊ ሀገራት መሪዎች በማደግ ላይ ባሉ ሀገራት የሚያጋጥሟቸውን ተግዳሮቶች ለመቅረፍ የጋራ ጥረቶችን ለማጠናከር ለታዳጊ ሀገሮች ተስማሚ የሆኑ መፍትሔዎች የተወያዩበት ‘An Empowered Global South for a Sustainable Future’ በሚል መሪ ሃሳብ ህንድ ‘3ኛውን የዓለም ደቡብ ስብሰባን አዘጋጅታለች። ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አሊ (ዶ/ር) እና የፋይናንስ ሚኒስትር አህመድ ሺዴ ዶ/ር በመሪዎች ጉባኤ ላይ ተሳትፈዋል። በተጨማሪም በሁሉም ደረጃዎች የቅርብ ግንኙነት እንጠብቃለን፡፡ አሁን ብሪክስ በሁለትዮሽ፣ ክልላዊ እና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ላይ ለቀጣይ፣ የሃሳብ ልውውጥ፣ ትብብር እና ቅንጅት እንደ አዲስ መድረክ ሆኖ ብቅ ብሏል።

ጥያቄ ፡- ኢትዮጵያ ብሪክስን መቀላ ቀሏ ለራሷ፣ ለሌሎች አባል ሀገራት እና አባል ላልሆኑት ጭምር ያለው ጠቀሜታ ምን ይመስሎታል?

ሚስተር አኒል ኩማር ራይ፡- ብሪክስ ህንድ እና ደቡብ አፍሪካን ጨምሮ በ4 ሀገራት የተመሰረተ ድርጅት ነው። ህንድ መስራች አባል በመሆኗ የታዳጊ ሀገራትን ምኞት የበለጠ ውክልና እንዲገኝ የሚያደርግ ነው፡፡ ይህንኑ መሠረት በማድረግም ኢትዮጵያ ህብረቱን ተቀላቅላለች። ኢትዮጵያ በብዙ መልኩ የአፍሪካን ምኞቶች እና ልማት ለማምጣት፣ ለማዘመን እና የሕዝቡን ፍላጎት ለመመለስ የሚያስችል መንገድ ትወክላለች። በዚህች ሀገር ወጣቶች እናምናለን፤ እየተካሄደ ያለው ሁሉን አቀፍ ማሻሻያ የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ገጽታ የመቀየር አቅም እንዳለው እያየን ነው። ብሪክስን በመቀላቀል ኢትዮጵያ የተለያዩ የብሪክስ ሀገራትን በተለያዩ ዘርፎች የተከተሉትን አማራጮችንና የዕድገት ሞዴሎችን ማግኘት ትችላለህ። ኢትዮጵያም ውክልና በማግኘቷ የራሷን እና የምስራቅ አፍሪካን ልማታዊ ፍላጎቶች እና ተስማሚ የሆኑትን ሞዴሎች ተጨባጭ ግምገማ ልታቀርብ ትችላለች።

ጥያቄ፡- ብሪክስ እያደረገ ያለው እንቅስቃሴ እንዴት እየሄደ ነው? ለምሳሌ በቅርቡ የራሱ ዓለም አቀፍ የክፍያ ሥርዓት ጀምሯል።

ሚስተር አኒል ኩማር ራይ፡- የብሪክስ ዋና አላማ የእያንዳንዱን ሀገር ጥንካሬዎች በአግባቡ መጠቀም የሚችሉበት እና በማንኛውም ሥርዓት የማይታሰሩበት የኢኮኖሚ አስተዳደር ሥርዓት ሞዴል እንዲኖር ማድረግ ነው፡፡ ይህም ከአቅማቸው በላይ ነው። የብሪክስ አባል ሀገራት በሀገር ውስጥ ምንዛሬ ለመገበያየት ወይም ወደ ምንዛሪ ልውውጥ ስምምነት ለመግባት እድል ይፈጥራል፡፡ በብሪክስ አባላት መካከልም የንግድ ልውውጥን ያመቻቻል እና የውጭ ምንዛሪ ጥገኝነትን ይቀንሳል፤ ይህም በምንዛሪ አያያዝ ላይ የተሻለ ቁጥጥር እንዲኖር ያደርጋል፡፡ በአጠቃላይ የግብይት ሥርዓቱን ጠንካራ ያደርገዋል። ይህ በሂደት ላይ ያለ ሥራ ነው፣ ወደፊትም ጥሩ እንደሚሆን ይሰማኛል እናም እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ሀገራት በቅርብ ጊዜ ብሪክስን ተቀላቅለው ከእንደዚህ ዓይነት ዝግጅቶች ተጠቃሚ ሊሆኑ ይችላሉ።

ጥያቄ፡- ኢትዮጵያ በተለይ የግሉ ዘርፍ ተሳትፎን መሠረት በማድረግ ንግ ድና ኢንቨስትመንትን ቀላል ለማድረግ ርምጃዎችን እየወሰደች ነው፣ በዚህ ላይ ምን አስተያየት አልዎት?

ሚስተር አኒል ኩማር ራይ፡– የኢትዮጵያ ኢኮኖሚያዊ ነፃነት በጣም ወቅታዊ እና ሁሉን አቀፍ ነው። ሀገሪቱ በክፍያ ሚዛኗ ላይ በተወሰነ ችግር ውስጥ እያለፈች የነበረች ሲሆን፥ በክቡር ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መሪነት ኢትዮጵያ ይህንን እንደ የሕይወት ዘመን እድል በመጠቀም የኢኮኖሚ መዋቅሩንና የአስተዳደር ሥርዓቱን ለማሻሻል ከፍ ያሉ አጀንዳዎችን እንደ ጀመረች አይቻለሁ። እንዲህ ዓይነቱ የተሃድሶ ሂደት ሰፊ ተፅዕኖ ያለው ሲሆን ለሀገር ውስጥም ሆነ ለውጭ ተጫዋቾች አዳዲስ ዕድሎችን ይፈጥራል እናም ውድድሩ ሁሉም ሰው እንዲያድግ እና እንዲሻሻል የሚያበረታታ ይሆናል፡፡ እንደ ግብርና፣ ማኑፋክቸሪንግ፣ ባንክ እና ፋይናንስ፣ ማዕድን፣ የአገልግሎት ዘርፍ ወዘተ. የውጭ ባለሀብቶችን የኢትዮጵያን ገበያ ማራኪነት ለማሳደግ እና የኢትዮጵያን ተወዳዳሪነት ለማሻሻል አቅም አላቸው። ህንድም በ1991 (እኤአ) ተመሳሳይ የተሃድሶ ሂደት ውስጥ አልፋለች፡፡ ዛሬም ቀጥሏል። ስለዚህ ነገሩ እየተንቀሳቀሰ ባለበት መንገድ ለኢትዮጵያ፣ ለኢትዮጵያ ሕዝብ እና ለሀገር ውስጥና ለውጭ ባለሀብቶች ጥሩ ይሆናል የሚል ተስፋ አለኝ።

ጥያቄ፡-የህንድ ባለሀብቶች ከተሃድሶው ምን ያህል ተጠቃሚ ይሆናሉ?

ሚስተር አኒል ኩማር ራይ፡- ህንድ በኢትዮጵያ ኢንቬስት በማድረግ ሁለተኛ ደረጃ ላይ የምትቀመጥ ስትሆን በብዛት የምንሰማራበት ዘርፍ ጨርቃጨርቅ፤ ብረትና ብረታ ብረት፣ ፋርማሲዩቲካልስ፤ ግብርና እና ልብስ ስፌት ናቸው፡፡ የህንድ ቢዝነስ ፎረም የኢንዱስትሪውን እይታ እና የማሻሻያ ሂደቱን ግብዓቶችን ለመስጠት ከኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ጋር በንቃት እየሰራ ነው። ከአዲሱ ሁኔታ ጋር ለመላመድ እና መረጋጋትን ለማግኘት ለፖሊሲ አውጪዎች ጊዜ እና ቦታ መስጠት እንዳለብን ይሰማኛል። እነዚህ ጉዳዮች ከተስተካከሉ በኋላ የፖሊሲ መረጋጋት ይመጣል።

በህንድ ውስጥ በጣም ብዙ ተቋማት ወይም የንግድ ድርጅቶች አሉ፡፡ ከእነዚህም መካከል ትልቁ ታታ ኢንተርናሽናል የግብርና፣ የማዕድን እና ሌሎች የተጠናቀቁ ምርቶችን በተለይም ኢትዮጵያ የዋጋ ተወዳዳሪነት ያላት ዘርፎችን ለመግዛት ይፈልጋሉ። የኢትዮጵያ ምርቶች ወደ ህንድ የሚላኩ ምርቶችን የበለጠ ለማስተዋወቅ «ከኢትዮጵያ ወደ ህንድ ሊላኩ የሚችሉ ምርቶችን›› ለይተናል፡፡ የቅባት እህሎች፣ ጥራጥሬ፣ ጥጥ፣ ጄምስቶን እና ቡና በሚል ርዕስ ጥናት አድርገናል። ጥናቱ የኢትዮጵያን ምርቶች በህንድ ገበያዎች ወደ ውጭ የመላክ አቅምን ለማሳደግ የሚያስችል ስትራቴጂ አስቀምጧል።

ጥያቄ፡- ኢትዮጵያ እና ህንድ በትም ህርት ዘርፍ የሚያደርጉት ትብብር ምን ደረጃ ላይ ደርሷል?

ሚስተር አኒል ኩማር ራይ፡- የትምህርት ሴክተርን በተመለከተ በሁለቱ ሀገራት መካከል በጣም ጠንካራ እና ጥንታዊ ከሆኑ የትብብር መስኮች አንዱ ነው። እና በ1950ዎቹ ከአንደኛ ደረጃ ጀምሮ እስከ ዩኒቨርሲቲ ድረስ ትምህርት በህንድ መምህራን ይመራ እንደነበር ይታወሳል። ኢትዮጵያውያን ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ክህሎት አዳብረዋል፤ አሁን ደግሞ በከፍተኛ ትምህርት ዘርፍ የህንድ ምሁራን ተሳትፎ የተገደበ መሆኑን ሳስተውል በጣም ደስ ብሎኛል። ለአጭር ጊዜ ስልጠና 500 እድሎች ለኢትዮጵያውያን እና ከ70 እስከ 80 በላይ እድሎች እንደ ቅድመ ምረቃ፣ ማስተርስ እና ፒኤችዲ ላሉ የረጅም ጊዜ ትምህርት ፕሮግራሞች እንሰጣለን። ትምህርት በሁለቱም ሀገራት መካከል ያለው የቆየ ግንኙነት እና አስፈላጊ የሕዝብ ለሕዝብ ትስስር ሆኖ ቀጥሏል።

ጥያቄ፡- ኢትዮጵያ ለአስርት አመታት የዘለቀውን የግጭት እና አለመግባባት ችግሮችን ለመፍታት ሀገራዊ ውይይት በማድረግ ሂደት ላይ ትገኛለች። በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ ከህንድ ምን ትማራለች?

ሚስተር አኒል ኩማር ራይ፡– ኢትዮጵያ የሥልጣኔ ሀገር ነች፣ ኢትዮጵያውያን በታሪካቸው ይኮራሉ፣ ሀገር ወዳድ ናቸው። የተሻለው መፍትሔ የሚገኘው በኢትዮጵያ መሪነት እና በኢትዮጵያ የሚመራ የእርቅ ሂደት እንደሆነ እንገምታለን። የሀገር ውስጥ ጉዳዮችን በውይይት ገንቢ በሆነ መንገድ ለመፍታት ምንጊዜም ህንድ ደጋፊ ነች፡፡ እንደዚህ ዓይነት ጉዳዮች ወደተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብት ምክር ቤት በቀረቡባቸው አጋጣሚዎች የኢትዮጵያን አቋም ደግፈናል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ውይይት ሂደት ስኬታማ እንደሚሆን እንጠብቃለን።

ጥያቄ፡- በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን የኢትዮጵያን ሚና እንዴት ያዩታል?

ሚስተር አኒል ኩማር ራይ፡- ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ቀንድ እና ለአፍሪካ አህጉር ቁልፍ የመረጋጋት ምሰሶ ነች። በቀይ ባህር አስፈላጊ የንግድ መስመር ላይ ስለሚገኝ እና በህንድ ውቅያኖስ በኩል ከህንድ ጋር የሚዋሰን በመሆኑ ሰላም እና መረጋጋት ለሁሉም ሰው ጠቃሚ ነው። ስለዚህ፣ የንግድ መስመሮቹ ክፍት፣ በሚገባ የተደራጁ፣ ደህንነታቸው የተጠበቀ እና አስተማማኝ ሆነው እንዲቀጥሉ የሁሉም ሰው ፍላጎት ነው። ኢትዮጵያ፣ የአፍሪካ ህብረት እና የቀጠናው ሀገራት የአፍሪካ ቀንድ ሰላም ሆኖ እንዲቀጥል አስፈላጊ እና ባለድርሻ አካላት ናቸው።

ጥያቄ፡- አፍሪካ በአጀንዳ 2063 የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና (AfCFTA) ዋና ፕሮጀክት ራሷን በኢኮኖሚ ለማዋሃድ እየጣረች ነው። ህንድ በቀጣናው የኢኮኖሚ ቡድን ትግበራ ከኢትዮጵያ እና ከአፍሪካ ጋር እንዴት ትተባበራለች?

ሚስተር አኒል ኩማር ራይ፡- እ.ኤ.አ. በ2023 በህንድ የG20 ፕሬዚዳንትነት ታሪካዊ እና የቆየውን የተዛባ አካሄድ የሚያስተካክል ዲፕሎማሲያዊ ተነሳሽነት በህንድ የተወሰደ ሲሆን ይህም በጂ-20 የአፍሪካ ህብረት ቋሚ አባልነትን የሚያስገኝ ነው። ኢንዶኔዢያ፣ ሕንድ፣ ብራዚል እና ደቡብ አፍሪካ ለመሳሰሉት አራቱ ታዳጊ ሀገሮች የጂ-20 ፕሬዚዳንትነት መስጠቱ እንዲሁ ጥሩ አጋጣሚ ነው። የአፍሪካ ህብረት ይህንን እድል በመጠቀም የአፍሪካ አጀንዳ የ G20 አጀንዳ እንዲሆን እና የአጀንዳ 2063 የአፍሪካ ነፃ ንግድ ቀጠናን ጨምሮ ትክክለኛ የቦታ አቀማመጥ እንዲያገኝ ማረጋገጥ አለበት። ህንድ የG20 አባል ሆና የአፍሪካን ሁሉን አቀፍ ልማት በግብርና፣ በምግብ ዋስትና ጤና፣ በድህነት ቅነሳ፣ በአካባቢ እና በአየር ንብረት ለውጥ አደጋዎችን ማቃለል እና ማስተዳደር እና ሌሎችም ድጋፏን ትቀጥላለች።

ጥያቄ፡- ኢትዮጵያ የአፍሪካ የፋርማ ሲዩቲካል ማምረቻ ማዕከል ለመሆን እየሰራች ነው። የህንድ ኩባንያዎችን ተሳትፎ እንዴት ያዩታል?

ሚስተር አኒል ኩማር ራይ፡- አራት የህንድ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ በማምረት ላይ ይገኛሉ፣ ነገር ግን በውጭ ምንዛሪ እጥረት ምክንያት አፈፃፀማቸው ዝቅተኛ ነበር። ነገር ግን ይህ ሁኔታ ከተረጋጋ እነዚህ ኩባንያዎች በሙሉ አቅማቸው መሥራት የሚጀምሩ ይመስለኛል። የክትባት ማምረቻው ኢትዮጵያ የህንድ ባለሙያዎችን የምትጠቀምበት እና ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካ ክትባቶች የምታመርትበት ዘርፍ ነው። የአቅርቦት ሰንሰለት ለውጥ እና በአፍሪካ አህጉር ውስጥ ያለው የምርት አቅም ጥሩ ይሆናል። ኢትዮጵያ ያገኘችው ጥቅም የአፍሪካ ህብረት የበሽታ መቆጣጠሪያ ማዕከል፣ ወጣት፣ የተማረ እና የሰለጠነ ሕዝብ መኖር ነው። የመድኃኒት ዘርፍ ጥንቃቄ የሚጠይቅ ነው፡፡ ኢትዮጵያ በዚህ ዘርፍ ህንድን ጨምሮ ለኢንቨስትመንት ምቹ መዳረሻ ለመሆን ያላትን ተወዳዳሪነት ለማሳደግ በፖሊሲው እና በኢንቨስትመንት ማዕቀፍ ላይ አንዳንድ ለውጦች እንደሚያስፈልግ አምናለሁ።

ጥያቄ፡- በህንድ እና በኢትዮጵያ መካከል ያለውን ትብብር በህክምና እንዴት ያዩታል?

ሚስተር አኒል ኩማር ራይ፡- በአንፃራዊነት ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር ያላት ሀገር በመሆኗ ኢትዮጵያ መሠረታዊ የጤና መሠረተ ልማት አውታሮች አሏት ይህም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ የመጣ እና ተጨማሪ መሻሻል ያስፈልገዋል። አዳዲስ ሆስፒታሎች እየመጡ እንዳሉ እና የህክምና ኮሌጆች ከፍተኛ ጥራት ያላቸውን ዶክተሮች እና እንክብካቤ ሰጭዎችን እያፈሩ እንዳሉ ብዙ ለውጦችን ማየት እንችላለን። ኢትዮጵያም የአህጉሪቱ ምርጥ የህክምና ኮሌጆች ባለቤት ነች። የጤናው ዘርፍ ትብብርን በተመለከተ የህንድ የህክምና ባለሙያዎች በየጊዜው ወደ ኢትዮጵያ በመሄድ የህክምና ተልዕኮዎችን ያደርጋሉ። በቅርቡ የቻንዲጋርህ የሮተሪ ክለብ ለ12 ቀናት የህክምና ሚሽን ያከናወነ ሲሆን ከ150 በላይ ውስብስብ ቀዶ ጥገናዎችን እና ከ500 በላይ ህሙማንን የበጎ አድራጎት አካል በማድረግ የኦፒዲ አገልግሎት ሰጥተዋል። መሰል ተግባራት ለታካሚዎች ቀጥተኛ እፎይታ ለመስጠት እና የኢትዮጵያን የህክምና ባለሙያዎችን ክህሎት ለማሳደግ በግል አካላትም ይከናወናሉ።

ጥያቄ፤- የጤና ሴክተር ትብብርን ለማሳደግ የህንድ ኤምባሲ ያከናወናቸው ተግባራት ምን ምን ናቸው?

ሚስተር አኒል ኩማር ራይ፡- በህንድ የጂ20 ፕሬዚዳንትነት ጊዜ የህንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ‹‹ለአንድ ምድር፣ አንድ ጤና›› እና በኋላ ላይ “ከድንበር ባሻገር የጤና እንክብካቤ” ጽንሰ-ሃሳብ አስተዋውቋል፡፡ ይህም ከጤና ጋር የተዛመዱ ፍላጎቶችን ጥራት እና አቅምን እያረጋገጠ ዓለም አቀፍ ሥነ-ምህዳርን ለማጠናከር ራዕይ ያለው ነው። እና ከፍተኛ ጥራት ያለው የጤና አገልግሎት ተደራሽነት ለሁሉም የሚል ምርህን የሚከተል ነው። እነዚህ ጽንሰ-ሃሳቦች ከጤና ጋር የተያያዙ ከአፍሪካ ህብረት አጀንዳ 2063 እና የተባበሩት መንግሥታት አጀንዳ 2030 ዓላማዎች ጋር የተጣጣሙ ናቸው።

ከላይ የተገለጹትን ከጤና ጋር የተያያዙ ጽንሰ ሃሳቦችን የበለጠ ለማጠናከር የህንድ ኤምባሲ ሁሉንም ባለድርሻ አካላት በአንድ መድረክ ላይ በማሰባሰብ ሃሳባቸውን እንዲያካፍሉ እና ቅንጅትን ለመፍጠር ለመሥራት የሚያስችል ዝግጅት ጥቅምት 1 ቀን 2024 በአዲስ አበባ እያዘጋጀ ይገኛል። ተሳታፊዎቹ ፖሊሲ አውጪዎች፣ ሆስፒታሎች፣ የባሕል ህክምና ባለሙያዎችን ጨምሮ የህክምና ባለሙያዎች፣ የህክምና ጉዞ ባለሙያዎች፣ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች፣ የሀገር አቀፍ ተወካዮች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ይገኙበታል።

ጥያቄ፡- በህንድ ውስጥ ፖሊሲ አው ጪዎች እና የጤና ባለሙያዎች በጉዳዩ ላይ የተሻለ ግንዛቤ ለማግኘት እና ከህንድ ተቋማት ጋር ግንኙነት ለመፍጠር የሚሳተፉባቸው መድረኮች አሉ?

ሚስተር አኒል ኩማር ራይ፡- በህንድ ውስጥ በመንግሥት እና በኢንዱስትሪ ደረጃ የተደራጁ ብዙ እንደዚህ ያሉ ዝግጅቶች አሉ። መጪው ክስተት ‘Advantage Healthcare India 2024’ በታላቁ ኖይዳ ከዲሴምበር 18 እስከ 20 ቀን 2024 የዴሊ ብሔራዊ ዋና ከተማ አካል በሆነው በታላቁ ኖይዳ የታቀደ ነው። ከህንድ ንግድ እና ኢንዱስትሪ ምክር ቤቶች ፌዴሬሽን (FICCI) ጋር በመተባበር ከዓለም ዙሪያ የተውጣጡ የጤና ባለሙያዎች በዚህ ዝግጅት ላይ ይሳተፋሉ፡፡ እናም የህንድን ዓለም አቀፍ ደረጃ የጤና እንክብካቤ እና ደህንነት አገልግሎቶችን ይመሰክራሉ። ይህ በህንድ የተቀበሉትን የጥራት ደረጃዎች፣ የጤና አጠባበቅ ቴክኖሎጂዎች እና አጠቃላይ የጤና እና ደህንነት አቀራረብን እንዲገነዘቡ እድል ይሰጣቸዋል። ይህ ለኢንዱስትሪ እና ለኢንዱስትሪ ትስስር ትልቅ እድል ይሰጣል። ከኢትዮጵያ ጤና ዘርፍ የተውጣጡ ፖሊሲ አውጭዎች፣ የመንግሥት እና የግል ዘርፍ ከፍተኛ የጤና ተቋማት ኃላፊዎች፣ የህክምና ኢንሹራንስ ኩባንያዎች እና የመገናኛ ብዙኃን ተሳትፎን ሙሉ በሙሉ ስፖንሰር ለማድረግ አቅደናል።

ጥያቄ፡- ህንዳውያን በዓለም ዙሪያ ከፍተኛ የጤና ባለሙያዎች እና ተንከባካቢዎች እንደሆኑ በሰፊው ይታወቃል። በዓለም ዙሪያ የህንድ የጤና ባለሙያዎች እንደዚህ ያለ ታላቅ ስም ያተረፈበት ምክንያት ምንድን ነው?

ሚስተር አኒል ኩማር ራይ፡- የሕክምና ትምህርት ሥርዓት ከመጀመሪያዎቹ ቀናት ጀምሮ በዓለም ላይ ካሉት ምርጥ ከሚባሉት ውስጥ አንዱ ነው። በህንድ ውስጥ ካሉት በሽታዎች ከፍተኛ ጫና አንጻር የሕክምና ተማሪዎቹ እና የጤና ባለሙያዎች ከበሽተኞች ጋር ለመገናኘት የተሻሉ እድሎችን ያገኛሉ።

ይህ ልዩ ተሰጥኦ ለህንድ ዶክተሮች እና የጤና ባለሙያዎች በዓለም ዙሪያ ባሉ ምርጥ እና ትላልቅ ሆስፒታሎች እና የጤና ሥነ-ምህዳሮች ውስጥ እንዲሰሩ እድሎችን ሰጥቷል። በዚህ ምክንያት የህንድ ዶክተሮች እና የጤና ባለሙያዎች እንደ ዩኤስኤ፣ ዩኬ፣ ካናዳ፣ አውስትራሊያ፣ ሲንጋፖር፣ የአውሮፓ ሀገራት እና የባህረ ሰላጤ ሀገራት እና ሌሎችም ከፍተኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ፡፡ የሕንድ ዶክተሮች እና የጤና ባለሙያዎችም እንደ የተባበሩት መንግሥታት፣ የዓለም ጤና ድርጅት፣ ዩኒሴፍ፣ የዓለም ባንክ፣ ድንበር የለሽ ዶክተሮች (የድንበር የለሽ ሐኪሞች)፣ ቢል እና ሜሊንዳ ጌትስ ፋውንዴሽን፣ ዓለም አቀፍ የህክምና ጓድ፣ ቀይ መስቀል እና ቀይ ጨረቃ ማህበራት ባሉ ድርጅቶች ውስጥ በጣም የተከበሩ እና የተወከሉ ናቸው።

ጥያቄ፡- የህንድ ጤና ዘርፍ እንዲነ ቃቃ ያደረጉ ምክንያቶች ምንድን ናቸው?

ሚስተር አኒል ኩማር ራይ፡- በድህረ-ኮቪድ ዘመን፣ ልክ እንደ ህንድ መንግሥት ሁሉ ግለሰቦችም ለጤና ያላቸው ንቃት ጨምሯል። ይህ በህንድ ውስጥ ያለውን ፍላጎት እና ወጪ ቆጣቢ እና ከፍተኛ ጥራት ያላቸውን የጤና አጠባበቅ ተቋማት አቅርቦትን በከፍተኛ ሁኔታ ገፋፍቶታል። ከፍተኛ መጠን ያለው ኢንቨስትመንቱ የተገኘው ከውጭ ባለሀብቶች እንዲሁም ከግሉ ሴክተር ነው። በቅድመ ወረርሽኙ ዘመን እንኳን ህንድ ለውጭ ሀገር ታካሚዎች ተመራጭ መድረሻ ነበረች ምክንያቱም እንደ፡-

  1. ግለሰቦች በዝቅተኛ ወጪ ደረጃ-1 የህክምና አገልግሎት፣ ቴራፒ፣ የቀዶ ጥገና ህክምና ወዘተ ጥቅም ያገኛሉ።
  2. ታካሚዎች በፍጥነት ማገገም እንዲችሉ ባሕላዊ የጤና እና በጎነት እውቀቶች ጥምረት መኖሩ
  3. ህክምናዎቻቸውን ከመዝናኛ እንቅ ስቃሴዎች ጋር በማጣመር የህንድ ማራኪ ውበት፣ የበለፀገ የባሕል ቅርስ እና የተለያዩ መልክዓ ምድሮች ማጣጣም ይችላሉ።

በአሜሪካን ሜዲካል ማኅበር ባደረገው የወጪ ንጽጽር ጥናት መሠረት፣ የጉልበት ምትክ ቀዶ ሕክምና በዩናይትድ ስቴትስ 40,000 የአሜሪካ ዶላር፣ በታይላንድ 10,000 ዩኤስ ዶላር እና በሲንጋፖር 13,000 ዶላር ያስወጣል። ነገር ግን፣ ተመሳሳይ ቀዶ ጥገና፣ በተሻለ የህክምና እንክብካቤ እና አገልግሎት፣ በህንድ 6,500 የአሜሪካ ዶላር አካባቢ ማግኘት ይቻላል። በህንድ ውስጥ ያለው የኑሮ ውድነትም በጣም ተመጣጣኝ ነው፡፡ ይህም ለረጅም ጊዜ ህክምና ለሚወስዱ ታካሚዎች ወጪ እንዳይከብዳቸው ያደርጋል፡፡ ከሁሉም የዓለም ክፍሎች ወደ ህንድ ዘመናዊ ከተሞች የተሻለ ግንኙነት ለህንድ የህክምና እሴት ጉዞ እድገትም አስተዋጽኦ እያደረገ ነው።

ጥያቄ፡- በኦክቶበር 01 ቀን 2024 በህንድ ኤምባሲ የተዘጋጀው የኮንፈረንስ ዋና ይዘቶች ምን ሊሆኑ ይችላሉ?

ሚስተር አኒል ኩማር ራይ፡- ጉባኤው የጤና አጠባበቅ ጉዳዮችን ለመጋራት ሁሉንም ባለድርሻ አካላት በአንድ መድረክ ላይ ለማምጣት ያለመ ነው። ከኢትዮጵያ መንግሥት ተወካዮች፣ ከአፍሪካ ህብረት፣ ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እና በአዲስ አበባ የሚገኙ የተለያዩ ድርጅቶቹ፣ በኢትዮጵያ እና ህንድ የመንግሥት እና የግል ጤና ዘርፍ፣ የፋርማሲ እና የህክምና መሳሪያዎች አምራቾች እንዲሁም የጤና ባለሙያዎችን ለመጋበዝ አቅደናል። ከሁለቱም ሀገሮች በዚህ ኮንፈረንስ በተለያዩ ባለድርሻ አካላት መካከል ቅንጅት በመፍጠር ገንቢ በሆነ መልኩ ለመሰማራት ፍኖተ ካርታ በማዘጋጀት ሁሉም ተጠቃሚ እንዲሆን እንፈልጋለን።

ጥያቄ፡- በጉባኤው ውስጥ ሰዎች እንዴት መሳተፍ ይችላሉ?

ሚስተር አኒል ኩማር ራይ፡- ውይይቱና ምክክሩ ትኩረት ሰጥቶ እንዲሰራና ውጤቱን ያማከለ እንዲሆን ጥሪውን መሠረት በማድረግ ተሳትፎው እንዲቀጥል ተወስኗል። ተሳታፊዎች ዝርዝራቸውን ለጉባኤው በተዘጋጀ የኦንላይን የምዝገባ ፎርም ሊያቀርቡ ይችላሉ (www.eoiaddisababa.gov.in) ምዝገባው እስከ መስከረም 25/2024 (እኤአ) ክፍት ነው። መሳተፍ የሚፈልጉ ድርጅች እና ግለሰቦች ዝርዝር መረጃቸውን በሚከተለው ቅጽ መሙላትና ማመልከት ይችላሉ https://forms.gle/Qf8Lo3KWCxZpCSPx7 ኮንፈረንሱ በህንድ እና በኢትዮጵያ መካከል በጤናው ዘርፍ ለትብብር አዲስ ፍላጎት እንደሚፈጥር እና ለዓለም አቀፍ ተሳታፊዎች ግንዛቤን ይሰጣል ብለን ተስፋ እናደርጋለን።

ለቃለ መጠይቁ ስለተባበሩን እናመሰግናለን!

ሚስተር አኒል ኩማር ራይ፡- እኔም አመሰግናለሁ

አዲስ ዘመን መስከረም 9/2017 ዓ.ም

Recommended For You