አዲስ አበባ፡- ኢትዮጵያ ከገባችበት ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ለመውጣት የፖሊሲ ማሻሻያዎችና መዋቅራዊ ለውጦች እንደሚያስፈልጉ ተገለጸ፡፡ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የተዘጋጀው የኢትዮጵያን ያለፈውን አንድ ዓመት ለውጥ የሚቃኘው «አዲስ ወግ» መድረክ ለሁለተኛ ቀን ትናንት በሸራተን አዲስ ሆቴል ሲካሄድ የዘርፉ ምሁራን እንዳሉት ኢትዮጵያ ከገባችበት ኢኮኖሚያዊ ችግር ውስጥ ለመውጣት የገጠር ልማትና የመሬት ይዞታ ፖሊሲዎች መሻሻል አለባቸው፡፡
ሰላም መስፈንና የህግ የበላይነት መረጋገጥ ይኖርበታል፡፡መንግሥት በኢኮኖሚው የሚያደርገውን ፖለቲካዊ ጫና መቀነስ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ በኢትዮጵያ መሬት ይዞታ ላይ ብዙ ጥናት ያደረጉት አቶ ደሳለኝ ራህመቶ እንዳሉት በኢትዮጵያ የመሬት ይዞታ ተግዳሮት ገጥሞታል።
ዛሬ ከፍተኛ የሚታረስ መሬት እጥረት በመኖሩ በርካታ የገጠር ወጣቶች መሬት የላቸውም፡፡ ወጣቶች ቤተሰቦቻቸውን ከፍላቸው መሬት ስጡን በሚልም በገጠር መሬት የጸብ ምንጭ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በኢትዮጵያ የግብርና ምርታማነት በመጨመር ረገድ ተጨባጭ ለውጦች ቢኖሩም የምርት ዕድገቱ የመጣው ግብርናውን ዕድገት በዘላቂ ለማዘመን ታስቦ ሳይሆን ማዳበሪያ ከውጭ ገዝቶ ማሰራጨት የተውሶ ዕድገት ነው ሲሉ ገልጸውታል፡፡
« የግብርናው ምርታማነት ዕድገት ቢያሳይም ዛሬም አምራቹ የምግብ ዋስትናውን ማረጋገጥ አልቻለም» ያሉት ምሁሩ በድርቅ የሚጠቃውና የምግብ ዋስትና ፕሮግራም ተጠቃሚ የሆነውን አርሶ አደር ቁጥር ባለፉት አስር ዓመታት ከዓመት ዓመት እየጨመረ መምጣቱን ገልጸዋል። ይህንችግር በዘላቂነት ለመፍታት ህዝቡን በማሳተፍ አዲስ የገጠር ልማትና የመሬት ይዞታ ፖሊሲዎችን ማሻሻል ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ በተለይ ከዝናብ ጥገኛ ከሆነ ግብርና ለመላቀቅ ውሃ ልማት ላይ ከፍተኛ ኢንቨስትመንት መድቦ መሥራት ይገባል፡፡
የፈጠራን ባህል ማዳበር ያስፈልጋል፡፡ ለገበሬው የብድር አገልግሎት መመቻቸት ይኖርበታል ሲሉ ምክረ ሀሳብ ሰጥተዋል፡፡ በኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ማህበር ከፍተኛ አጥኝ የሆኑት ዶክተር ሰይድ ኑሩ የኑሮ ውድነት፣ ሥራ አጥነት፣ የውጭ ምንዛሪ እጥረት፣ የዕዳ ጫና የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ችግር ምልክት መሆናቸውን ጠቅሰው፤ ኢኮኖሚው ከገባበት ቀውስ ውስጥ ለማውጣት ለኢንቨስትመንት ምቹ የሆኑ ምህዳር መፍጠር፣ ሰላምን ማስፈን፣ ቀለል ያለ የታክስ ሥርዓት መዘረጋት፣ ፍትሀዊነት ማረጋገጥ እንደሚገባ አብራርተዋል፡፡
ዜጎች በኢኮኖሚው መስክ መገለላቸው፣ ተገልለናል ብለው ማሰባቸው፣ ሀብት የሚገኘው በማጭበርበር መሆኑን ማየታቸውና ማመናቸው ለኢኮኖሚ ዕድገቱ ፈተና መሆኑን አውስተው፤ ዜጎችን ከዚህ አስተሳሰብ በማላቀቅ በልፋታቸው ልክ ተጠቃሚ የሚሆኑበትን የኢኮኖሚ ሥርዓት መዘረጋት እንደሚያስፈልግ ጠቅሰዋል። ኢትዮጵያ ከተለያዩ አገራት ብዙ ብድሮችንና ድጋፍችን ብታገኘም ብድሩን ገንዘብ በሚያመነጩ ውጤታማ ፕሮጀክቶች ላይ አለማዋሉና የሌቦች ሲሳይ መሆኑ ዛሬ እያንዳንዱ ዜጋ በግለሰብ ደረጃ 25ሺ ብር ዕዳ እንዳለበት ገልጸው፤ የተጀመሩ ፕሮጀክቶች ማጠናቀቅ ላይ ትኩረት ተሰጥቶ መሠራት አለበት ብለዋል፡፡
«ግብርና እንደ ሌሎች መስኮች ሁሉ ጥረትና ክህሎትን ይጠይቃል» ያሉት ዶክተር ሰይድ በግብርና ያልተሳካለት ሰው መሬትን ሽጦ ወደ ከተማ መሄዱ ስለማይቀር አማራጭ ሥራ እንዲያገኝ ለማድረግ የመሬት ፖሊሲው መሻሻል እንደሚኖርበት ጠቁመዋል፡፡ ‹‹በአሁኑ ወቅት የፋይናንስ ሴክተሩ ውጥረት ላይ ነው›› ያሉት የኢኮኖሚና የኢንሹራንስ ምሁሩ አቶ ዛፉ እየሱስወርቅ ዛፉ ሰላምና መረጋጋት ለኢኮኖሚው ዕድገት የመሰረት ድንጋይ በመሆናቸው መረጋገጥ አለባቸው፤ መንግሥት በኢኮኖሚው ላይ የሚያደርገው ፖለቲካዊ ጫና መቀነስ፣ በፋይናንሱ ሴክተር የውጭ ባለሀብቶችና ዲያስፖራዎች እንዲሳተፉ መፍቀድና የግል ሴክተሩን ከፖለቲካ ፍጆታ በዘለለ መደገፍ አለበት ሲሉ ገልጸዋል፡፡ በውይይቱ ላይ ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የተወጣጡ አካላትና የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ተገኝተዋል፡፡
አዲስ ዘመን መጋቢት 15/2011
በጌትነት ምህረቴ