ዘመናዊ የአኗኗር ዘዴ ከኤሌክትሪክ ኃይል ውጭ ሊታሰብ አይችልም:: ቤቶች፣ ጎዳናዎች፣ ኢንዱስትሪዎች ብርሃን እና ሙቀት የሚያገኙት ከኤሌክትሪክ ነው። በቤት በቢሮዎች እና በፋብሪካዎች ውስጥ አገልግሎት የሚሰጡ ቁሶችንና ማሽነሪዎችን ያለ ኤሌክትሪክ ማሰብ ከባድ ነው። የኤሌክትሪክ ኃይል ከተለያዩ ምንጮች ሊገኝ የሚችል ሲሆን፤ ከኤሌክትሪክ ኃይል ምንጮች ትልቁ የድንጋይ ከሰል ነው።
የድንጋይ ከሰል መጠቀም ለአየር ንብረት ለውጥ አስተዋጽኦ ስለሚያበረክት ከኃይል ምንጭነት ለማስወጣት ጥረቶች ቢደረጉም ዛሬም የዓለም ትልቁ የኤሌክትሪክ ኃይል ምንጭ ሆኖ ቀጥሏል። የዛሬ ሶስት ዓመት ገደማ የወጡ መረጃዎች እንደሚያሳዩት፤ የድንጋይ ከሰል በአሁኑ ጊዜ በዓለም 36 በመቶ ድርሻ ያለው ትልቁ የኤሌክትሪክ ኃይል ምንጭ ሆኖ ቀጥሏል። እንዲሁም ወደ ኃይል ለመቀየር በአንፃራዊነት ቀላል እና እርካሽ በመሆኑ አገራት ዛሬም የድንጋይ ከሰልን መጠቀማቸውን ቀጥለዋል።
ኢትዮጵያ በዓለም ደረጃ ተወዳዳሪ ሊሆን የሚችል የድንጋይ ከሰል የታደለች አገር ብትሆንም ይህንን ሀብት በሚገባ ሳትጠቀም ቆይታለች። በአገሪቱ ውስጥ ያለውን የድንጋይ ከሰል ፍላጎት ለማሟላት ከውጭ አገራት ስታስገባ ቆይታለች። ከፍተኛ ወጪ በማውጣት የድንጋይ ከሰል ከውጭ አገራት እንደምታስገባ መረጃዎች ያሳያሉ። ይህም በአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ አሉታዊ ጫና ሲያሳድር ቆይቷል። ይህንን ሁኔታ ለመቀየር ካለፉት ጥቂት ዓመታት ወዲህ የከሰል ድንጋይን በአገር ውስጥ ለማምረት እንቅስቃሴዎች ተጀምረዋል።
በቅርቡ 6ኛው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 1ኛ ዓመት የሥራ ዘመን ዘጠነኛ መደበኛ ጉባኤ የማዕድን ሚኒስቴር የ2014 በጀት ዓመት የዘጠኝ ወር የእቅድ አፈጻጸም ሪፖርት አዳምጧል። በማዕድን ዘርፍ በተሰሩ ሥራዎች ዙሪያ የተለያዩ ጥያቄዎችና ማብራሪያዎችን ተጠይቀዋል። በዚህ ወቅት በምክር ቤቱ ሰፊ የመነጋገሪያ ርዕሰ ጉዳይ ከነበሩት አንዱ የድንጋይ ከሰል ልማት ጋር ተያይዘው ያሉ ጉዳዮች ናቸው። የድንጋይ ከሰል ማምረቻ ኢንዱስትሪዎች ግንባታ በምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝ፣ ለኢንዱስትሪው ስኬታማነት ወሳኝ የሆኑ መሰረተ ልማቶች ማለትም ኤሌክትሪክ ኃይል፣ ውሃና መንገድ የመሳሰሉ መሰረተ ልማቶች ለፋብሪካዎቹ ስኬታማነት ወሳኝ በመሆናቸው ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ያለው ቅንጅታዊ አሰራር ምን ይመስላል፣ የድንጋይ ከሰል በሚመረትባቸው አካባቢዎች ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንዳያደርስ አምራቾቹ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ምን አይነት ክትትል እና ድጋፍ እያደረገ ነው፤ ማዕድኑ በሚመረትባቸው አካባቢዎች የሚኖሩ ህዝቦች ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ምን ሥራዎች እየተሠሩ ነው የሚሉ ጥያቄዎች እና ማብራሪያዎች ተነስተዋል።
የሚኒስቴሩ አመራሮችም ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል። የማዕድን ሚኒስትር ኢንጂነር ታከለ ኡማ በሰጡት ማብራሪያ፤ ሚኒስትር አቶ ታከለ ኡማ፤ ባለፉት ዓመታት የኢትዮጵያ ድንጋይ ከሰል ጥራት ይጎድለዋል፣ የአመድ ይዘቱ ከፍተኛ ነው፣ የሰልፈር ይዘቱ ከፍተኛ ነው፣ የእርጥበት መጠኑ ከፍተኛ በሚል የኢትዮጵያ ድንጋይ ከሰል ለኢትዮጵያ ስለማይጠቅም ከውጭ ይግባ የሚል ትርክት ነው የነበረው። በዚህ መሰረትም ለብዙ ዓመታት ኢትዮጵያ ከፍተኛ መጠን ያለው የውጭ ምንዛሪ በማውጣት ድንጋይ ከሰል ከውጭ አገራት ስታስገባ ቆይታለች። ባለፉት ዓመታት ለሲሚንቶ እና ለሌሎች ፋብሪካዎች ግብዓት የሚሆን የድንጋይ ከሰል በዓመት ከ300 ሚሊየን ዶላር በላይ ወጪ እያደረገች ለፋብሪካዎች የሚያገለግል የከሰል ድንጋይ ከውጭ አገራት ስታስገባ ቆይታለች።
ይህንን ሁኔታ ለመቀየር በኢኮኖሚ እና ፖለቲካ ሪፎርሙ ከአምስቱ የብዝሃ ኢኮኖሚ ግንባታ ውስጥ ማዕድን አንዱ ምሰሶ እንዲሆን ተደርጓል። በአገሪቱ ውስጥ ያሉ ማዕድኖችን ማስጠናት፣ ማወቅ እና መጠቀም አስፈላጊ መሆኑ ስለታመነበት በለውጡ ማግስት ነው የተጀመረው። በዚህ ትልቅ ትኩረት ከተሰጣቸው ማዕድኖች አንዱ የድንጋይ ከሰል ነው ይላሉ ሚኒስትሩ።
የኢትዮጵያ ድንጋይ ከሰል ጥራትን በተመለከተ የነበረውን ትርክት ለመቀየር ሥራዎች መሠራታቸውን የሚያነሱት ኢንጂነር ታከለ፤ የኢትዮጵያ ድንጋይ ከሰል ጥራት ለማወቅ ቱርክ፣ ደቡብ አፍሪካ እና ቻይና በመላክ የማወቅ ሥራ ተሰርቷል ይላሉ። በሶስቱም አገራት ላቦራቶሪዎች ውስጥ የተረጋገጠው ኢትዮጵያ ከውጭ አገራት ከምታስገባቸው በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኘው የድንጋይ ከሰል የማቃጠል አቅሙ የተሻለ መሆኑን ማረጋገጥ መቻሉን ጠቁመዋል።
ከውጭ የሚገባው የድንጋይ ከሰል የማቃጠል አቅሙ አምስት ሺ ካሎሪክ አቅም ያለው ሲሆን በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ግን ከስድስት ሺ ኪሎ ዋት አቅም በላይ ያለው መሆኑ ተረጋግጧል። ይህም የሚያሳየው የኢትዮጵያ ድንጋይ ከሰል ኢትዮጵያ ከውጭ ከምታስገባቸው ድንጋይ ከሰሎች በላይ ሀይል የመስጠት አቅም ያለው እና አነስተኛ ጭስ የሚያመነጭ መሆኑን ነው።
እንደ ኢንጂነር ታከለ ማብራሪያ፤ ይህ ከተረጋገጠ በኋላ ስምንት ፋብሪካዎች ድንጋይ ከሰል ማምረት እንዲጀምሩ መንግሥት 25 ሚሊየን ዶላር ለኩባንያዎቹ ሰጥቷቸዋል። መንግሥት ካለው የውጭ ምንዛሪ ክምችት አውጥቶ የሰጠው ፋብሪካዎቹ በፍጥነት ወደ ሥራ መግባት እንዲችሉ ነው። በዚሁ መሰረት አንዳንዶቹ ወደ ሥራ ለመግባት ጥሩ እንቅስቃሴ እያደረጉ ነው። አንዳንዶች የማሽን ግዢ ፈጽመዋል፣ አንዳንዶቹ ጥናታቸውን ጨርሰዋል፣ አንዳንዶቹ የላቦራቶሪ ጉዳዮችን ጨርሰዋል።
በትብብር መሥራት ከተቻለ በቀጣይ ጊዜ ከሰል ከውጭ አገራት ማስገባት ይቆማል። አገሪቱ የድንጋይ ከሰል ከውጭ ማስገባት ስታቆም ለተወሰኑ ወራት የሲሚንቶ ፋብሪካዎች ሊቸገሩ እንደሚችሉ እና የሲሚንቶ ምርት ሊቀንስ ቢችልም የአገር ውስጥ ድንጋይ ከሰል ጥቅም ላይ ማዋል ይገባል ብለዋል።
የአገሪቱ የከሰል ድንጋይ ፋላጎት ሰባት ነጥብ ስምንት ሚሊየን ቶን የከሰል ድንጋይ ሲሆን፤ በቀጣይ ጊዜያት ኢትዮጵያ ውስጥ የድንጋይ ከሰል ማምረት ይጀምራሉ ተብለው የሚጠበቁ የድንጋይ ከሰል ፋብሪካዎች የማምረት አቅም ግን አራት ነጥብ አምስት ሚሊየን ቶን መሆኑን ነው ያነሱት። በአገር ውስጥ የሚመረተው የድንጋይ ከሰል የሁሉንም ፋብሪካዎች ፍላጎት ላያሟሉ እንደሚችሉ ጠቁመዋል። የድንጋይ ከሰል አምራቾቹ ለጊዜው የሲሚንቶ ፋብሪካዎችን ፍላጎት እንዲያሟላ ጥረት ይደረጋል። በቀጣይ ደግሞ የማዳበሪያ ፋብሪካዎች የከሰል ድንጋይ ፍላጎት ለማሟላት የሚያስችል የድንጋይ ከሰል በአገር ውስጥ ለማምረት ጥረት እንደሚደረግ ጠቁመዋል።
ድንጋይ ከሰልን በአገር ውስጥ ለማምረት እንቅስቃሴ መጀመሩ ትርክቶቹ እየተቀየሩ መሆናቸውን አመላካች ቢሆንም፤ ሆኖም እነዚህ የድንጋይ ከሰል የሚመረቱባቸው ክልሎች የየራሳቸው ጥያቄዎች አሏቸው። የድንጋይ ከሰሉ ጥቅም ላይ እየዋለ ሲሄድ የድንጋይ ከሰል የሚመረትባቸው አካባቢዎች የሚኖሩ ህዝቦች ተጠቃሚ እየሆኑ እንደሚሄዱም ጠቁመዋል። በአሁኑ ወቅት ግን ምርት ላይ አልተደረሰም። ምርት ላይ ስላልተደረሰ ብዙ ብዢታዎች አሉ። አንዳንድ ክልሎች ከፋብሪካዎቹ እስከ 30 በመቶ የክልሉ ወጣቶች እንዲይዙ የመፈለግ አዝማሚያ አለ። ብዙ ፋብሪካዎች በሌሉባቸው እና ገና ባለሙ ክልሎች ግን የ30 በመቶ ጥያቄ ማንሳት ተገቢ አይደለም ብለዋል። ክልሎች ከምንም በላይ በዘርፉ የሚሰማሩ ባለሃብቶችን መሳብ ላይ ትኩረት ማድረግ አለባቸው። ከጅምሩ ከፍተኛ ድርሻ ለመያዝ የሚደረገው ሩጫ ባለሃብቶች ወደ ሥራ እንዳይገቡ የሚያደርግ መሆኑንም አብራርተዋል።
በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሁለት ኩባንያዎች የፋብሪካ ግንባታ ላይ መሆናቸውን የጠቆሙት አቶ ታከለ፤ በሚያመርቱ ባለሃብቶች የወጣቶችን ችግር መፍታት ይቻላል። ሌሎች ክልሎችም በተመሳሳይ ይሰራል። ከሚቀጥለው ዓመት ጀምሮ የድንጋይ ከሰል ከውጭ እንደማይገባ የጠቆሙት ኢንጂነር ታከለ፤ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች በአገር የድንጋይ ከሰል እየተጠቀሙ ማምረት ይጀምራሉ።
አገሪቱ የከሰል ድንጋይን ጨምሮ ከሌሎች ማዕድናት ማግኘት ያለባትን ጥቅም ማግኘት እንድትችል ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ ጠቁመዋል። ለድንጋይ ከሰል ልማትና ስኬታማነት ወሳኝ የሆኑ መሰረተ ልማቶች ማለትም ኤሌክትሪክ ሀይል፣ ውሃና መንገድ የመሳሰሉ መሰረተ ልማቶች ለፋብሪካዎቹ ስኬታማነት ወሳኝ በመሆናቸው ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅርበት መሥራት ይገባል።
የድንጋይ ከሰል ልማት በጥንቃቄ ካልተያዘ የእርሻ ቦታ፣ የመጠጥ ውሃ እና ብዝሃ ሕይወት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ የሚያሳድሩ በመሆናቸው በማህበረሰቡ ዘንድ ጉዳት ሊያስከትል የሚችል በመሆኑ፤ በዘርፉ የተሰማሩና የሚሰማሩ ባለሃብቶች ከስራቸው ጎን ለጎን አካባቢውን እንዲያለሙና አሉታዊ ተፅዕኖዎችን እንዲከላከሉ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ድጋፍና ክትትል ሊያደርግ እንደሚገባም ተጠቁሟል።
በአገር ውስጥ የሚመረተው የከሰል ድንጋይ ደረጃው የተለያየ በመሆኑ የጥራቱ ደረጃ ቢቀመጥለት ለተጠቃሚውና ለዋጋ ተመን የሚጠቅም በመሆኑ የማዕድናትን ጥራት ደረጃ ከመወሰን አንጻር ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በትኩረት ሊሠራ እንደሚገባ የጠቆሙት አባላቱ፤ የአካባቢውን ማህበረሰብ እና ወጣቱን ከድንጋይ ከሰል አምራች ባለሃብቶች ጋር በማስተሳሰር የሥራ እድል ከመፍጠር አንጻር አሰራርን በግልጽ ማስቀመጥ ተገቢ መሆኑንም አመላክተዋል።
አንዳንድ ፋብሪካዎች በ2014 ከውጭ የሚገቡ የድንጋይ ከሰል ምርቶችን በአገር ውስጥ ለመተካት የድንጋይ ከሰል አምራቾች ፈቃድ የተሰጣቸው ቢሆንም እስካሁን ይህ ነው የሚባል እንቅስቃሴ ባለመታየቱ የድንጋይ ከሰሉ ይመረትባቸዋል ተብለው ከሚጠበቁ አካባቢዎች ማህበረሰብ ቅሬታዎች እየተነሱ እንደሆነ የጠቆሙት አባላቱ ቢሆንም ወደ ተግባር ከማስገባት ረገድ ያለው እንቅስቃሴ ዝቅተኛ ነው። ኩባንያዎች የድንጋይ ከሰል ወደማምረት እንዲገቡ በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ኩባንያዎቹን ወደ ሥራ ለማስገባት በትኩረት ሊሠራ እንደሚገባም ጠቁመዋል።
የድንጋይ ከሰልን ጨምሮ ሌሎች ማዕድናት በሚመረቱበት አካባቢ የአድሎዊነት፣ የአለመረጋጋት እና የግጭት መንስዔ እንዳይሆኑ ተቋሙ ኃላፊነት መውሰድ እንዳለበት የጠቆሙት የምክር ቤቱ አባላት የተቋሙ የማዕድን ጥናቶች በዳታ ቤዝ መያዝ እንዳለባቸው እና ዓለም-አቀፋዊ ተወዳዳሪ ሊሆኑ እንዲሚገባም አመላክተዋል።
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኢንዱስትሪ እና ማዕድን ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ፤ ሰሞኑን በዳውሮ ዞን የመስክ ምልከታ ያካሄደ ሲሆን ቡድን በዞኑ የሚገኙ የድንጋይ ከሰል ማምረቻዎችን ተዘዋውሮ ከዞኑ አመራሮች፣ ከአካባቢው ማኅበረሰብ እና ከድንጋይ ከሰል አምራቾች ጋር ተወያይተዋል።
የዳውሮ ዞን የድንጋይ ከሰል ሲመረት ለአካባቢ ጥበቃ ትኩረት ከመስጠት ጎን ለጎን ለአካባቢው ማኅበረሰብ አገልግሎት መስጠት የሚችል ጤና ጣቢያ፣ ትምህርት ቤት፣ መንገድ፣ ንጹሕ የመጠጥ ውኃ እና የመሳሰሉትን መሠረተ-ልማቶች በመሥራት፤ የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ እንደሚገባም አስገንዝበዋል። በአካባቢው የከሰል ድንጋይ የማምረት ሥራ ሲጀመር የአካባቢውን ማኅበረሰብ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ከሚሠራው ሥራ በተጨማሪ፣ ቴክኖሎጂን ለማሸጋገር መጣር እንዳለበት የምክር ቤቱ አባላት መጠቆማቸውን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በፌስቡክ ገጹ አስፍሯል።
በምክትል ማዕረግ የዳውሮ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ክቡር ምትኩ መኩሪያ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የድንጋይ ከሰል እስካሁን ያልተሠራበት አዲስ ዘርፍ በመሆኑ የአሠራር መመሪያ (Guideline) ስለሌለው፣ ዘርፉን ለመምራት መቸገራቸውን ገልጸዋል። የፌዴራል መንግሥት ጥናት አካሂዶ ግልጽ የአሠራር መመሪያ ማዘጋጀት እንዳለበትም ጠቁመዋል። ዋና አስተዳዳሪው አክለውም፤ በፌዴራል መንግሥት በኩል ማዕድናትን የሚመለከቱ ሕጎችን ለማውጣት በሚደረገው ውይይት፣ በየደረጃው ያለውን አመራር እና ሕዝብ ማወያየት ቢቻል፣ በዘርፉ የሚታዩ ችግሮችን ለመቅረፍ የሚረዳ ግብዓት ይገኛል ብለዋል።
ለማምረት ፈቃድ የተሰጣቸው የድንጋይ ከሰል አምራቾች በውላቸው መሠረት ወደ ሥራ እንዲገቡ የወረዳው እና የዞኑ አመራር መሥራት እንዳለበትም አሳስበው፤ የፌዴራል መንግሥትም ድጋፍ ማድረግ እንዳለበት ዋና አስተዳዳሪው ጨምረው አሳስበዋል።
መላኩ ኤሮሴ
አዲስ ዘመን ግንቦት 26/2014