
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የግንባታው መሠረት ድንጋይ ከተቀመጠበት ከመጋቢት 24 ቀን 2003 ዓ.ም ጀምሮ በርካታ ውጣ ውረዶችን አሳልፏል። ለሰማይ ምድሩ የከበዱ ዲፕሎማሲያዊ ጫናዎችን ጭምር ተቋቁሞ የማይቻል የሚመስሉ ችግሮችን ተሻግሯል። ግድቡ በወቅቱ በአምስት ዓመታት ጊዜ ውስጥ በ80 ቢሊዮን ብር ወጪ ይጠናቀቃል ተብሎ እቅድ ቢያዝለትም፣ በተለያዩ ምክንያቶች ዘጠኝ ተጨማሪ ዓመታትን እንዲሁም ለግንባታ ከተያዘለት በጀት በብዙ እጥፍ የሚበልጥ ገንዘብን ጠይቋል።
እንዲያም ሆኖ ክንዳቸው ያልዛለ ኢትዮጵያውያን እጅ አንሰጥም ብለው በተባበረ ክንድ እነሆ ከፍጻሜ ሊያደርሱት ከጫፍ ደርሰዋል። ሪቫን ሊቆረጥለት ከጫፍ ለደረሰው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ኢትዮጵያውያን እንደተጠበቁት ራሳቸው መሃንዲስና የፋይናንስ ምንጭ ሆነዋል።
በብዙ ፈተና ውስጥ ያለፈው ግድቡ ለኢትዮጵያውያን ብዙ ትርጉም ያለውም መሆን ችሏል። ኢትዮጵያውያንን በአንድ ያስተሳሰረ ግዙፍ ፕሮጀክት ነው። ለሀገራዊ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት የላቀ ድርሻ ያለው ስለመሆኑ መንግሥት ብቻ ሳይሆን የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች አስረግጠው ተናግረውለታል፡፡
የኢትዮጵያ ኢኮኖሚክ አሶሴሽን ተመራማሪ ሞላ አለማየሁ (ዶ/ር) ፤ሲያስረዱ፤ ግድቡ ከሚሰጣቸው ብዙ ጠቀሜታዎች መካከል የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት በቀዳሚነት ተጠቃሽ እንደሆነም ያነሳሉ። ኢነርጂ ወይንም ኃይል ለማንኛውም ዘርፍ ማለትም ለአምራች ኢንዱስትሪዎችም ሆነ አገልግሎት ለሚሰጡ ተቋማት ዋና ግብዓት ሆኖ ያገልግላል ይላሉ።
ተመራማሪው እንዳብራሩት፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ደግሞ በምርትና ምርታማነት ላይ የሚነሱ ጥያቄዎችን ማድመጥ ተለምዷል። ለዚህም ዋናው ምክንያት የቆየው የኤሌክትሪክ ኃይል እጥረትና መቆራረጥ ነው። አምራች ድርጅቶች የኃይል አቅርቦት በሚፈልጉት መጠን ካላገኙ በሙሉ አቅማቸው ማምረት አይችሉም። ይህ ሁኔታ ከፍተኛ ቅሬታ ሲነሳበት የነበረ በመሆኑ የግድቡ መጠናቀቅ በዋነኝነት የሀገሪቱን የኤሌክትሪክ ምርት በማሳደግ ችግሩን መፍታት ያስችላል፡፡
‹‹የግድቡ መጠናቀቅ የሀገሪቱን የኃይል አቅርቦት በከፍተኛ መጠን ያሳድጋል›› ያሉት ሞላ (ዶ/ር)፤ የኃይል አቅርቦት አለመመጣጠንና መቆራረጥ በምርትና ምርታማነት ሊያሳድር የሚችለውን አሉታዊ ተጽዕኖ እንደሚያስቀር አስታውቀዋል።
በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎች የኤሌክትሪክ ኃይል እንዲያገኙ እንደሚያስችል ተናግረው፣ የኃይል አቅርቦት የሚያገኙ ዜጎችም ሥራቸውን በተሳካ ሁኔታ በማሳለጥ ተጠቃሚነታቸውን እንደሚያረጋግጥ ተናግረዋል። በቤተሰብ ደረጃ ብቻ ሲታይም የኃይል አቅርቦት በተሟላ ሁኔታ የሚያገኝ አንድ ግለሰብ ሥራውን በቀላሉና በአጭር ጊዜ እንዲያጠናቅቅ በማስቻል ቀሪ ጊዜውን ለሌላ ሥራ በማዋል አምራች ዜጋ እንዲሆን ያደርገዋል ብለዋል።
የምጣኔ ሀብት ባለሙያ ቆስጠንጢኖዮስ (ዶ/ር)በርሀተስፋ ይህንኑ ሃሳብ ያነሳሉ። ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ወደ መጠናቀቅ መድረሱ ለኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት ትልቅ ዕድል መሆኑን ገልጸው፤ ከአፍሪካ አንደኛ ከዓለም ሰባተኛ የሚሆነው ሕዳሴ ግድብ የሚያመነጨው ኃይል ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንዳለው ጠቁመዋል። በዋናነት ይህ ኃይል 60 በመቶ ለሚሆኑና የኤሌክትሪክ ኃይል ላላገኙ ኢትዮጵያውያን ትልቅ እድል ይዞ መምጣቱን አስታውቀዋል።
ግድቡ ከዚህ ባለፈም ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንዳለው ቆስጠንጢኖስ (ዶ/ር)፤ ለአብነትም በርካታ ኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች በግንባታው እየተሳፉ የዕውቀትና የቴክኖሎጂ ሽግግር እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል። ይህም በቀጣይ ለሚሠሩ ግድቦች ትልቅ አቅም መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ቆስጠንጢኖስ (ዶ/ር) እንዳስታወቁት፤ ውሃው በሚጠራቀምበት ጊዜ የአካባቢውን የአየር ሁኔታ በከፍተኛ ደረጃ የሚቀይር መሆኑም ሌላው ፋይዳው ነው። ምክንያቱም የሚተነው ውሃ ለአካባቢው ይጠቅማል።
በአካባቢው ከፍተኛ የዓሳ ሀብት ሊመረትበት ይችላል፤ ከፍተኛ የቱሪስት መዳረሻ በመሆን ሊያገለግልም ይችላል። ከተሞች ያድጋሉ፤ አግሮ ኢንዱስትሪዎች ይስፋፋሉ። በተለይም የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በራሱ ገና ያልተነካ ድንግል አፈር ያለው በመሆኑ በርካታ ኢትዮጵያውያንና የውጭ ባለሀብቶችን መሳብ ይችላል። ከዚህ በተጨማሪም በሃይቁ ዙሪያ የከብት ሀብት ልማት ማስፋፋት ይቻላል።
በሃይቁ ዙሪያ ግብርናን ማስፋፋት የሚቻል በመሆኑ በግብርና ሥራው በኩል ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖራል የሚል እምነትም ቆስጠንጢኖስ (ዶ/ር) አላቸው። የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት በአካባቢው አግሮ ኢንዱስትሪ እንዲስፋፋ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ ጠቅሰው፣ ግብርናው ሲስፋፋ ብዙ ሥራ መሥራትና ከፍተኛ የሥራ ዕድል መፍጠር እንደሚቻልም አመላክተዋል፡፡
በተመሳሳይ፤ የኤሌክትሪክ ኃይል አስተማማኝ ግብዓት መሆኑን የጠቀሱት ሞላ (ዶ/ር)፤ የኢንዱስትሪ እና የግብርናውን ዕድገት ማሳለጥ እንደሚችል ይናገራሉ። እሳቸው እንዳሉት፤ አስተማማኝ የኤሌክትሪክ ኃይል በማቅረብ በኢንዱስትሪውና በግብርናው ዘርፍ የተሻለ ዕድገት በማስመዝገብ የኢኮኖሚውን እንቅስቃሴ ከፍ ማድረግ እንደሚቻልም አመላክተዋል። ኢንዱስትሪዎች የኤሌክትሪክ ኃይል በሚገባ ሲያገኙ በሙሉ አቅማቸው በመሥራት ምርትና ምርታማነትን ያሳድጋሉ። ይህም ምርትና ምርታማነትን ከማሳደግ በተጨማሪ የሰው ኃይል ፍላጎታቸው እንዲጨምር በማድረግ ከፍተኛ የሥራ ዕድል በመፍጠር ትልቅ ድርሻ እንዳለው ተናግረዋል።
ለሀገር ውስጥ አገልግሎት ከሚውለው የኤሌክትሪክ ኃይል ባለፈ ወደ ውጭ በመላክ የውጭ ምንዛሪ ግኝትን ማሳደግ ይቻላል ሲሉ የጠቀሱት ሞላ (ዶ/ር)፤ በአሁኑ ወቅት ኢነርጂ ለአብዛኞቹ ሀገራት ዋና ግብዓት ሆኖ እያገለገለ መሆኑንም አስታውቀዋል። በርካታ ሀገራት ይህንን የኃይል ፍላጎታቸውን ለማሟላት ወደ ተለያዩ ሀገራት እያማተሩ መሆናቸውንም ጠቁመው፤ ይህን መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ኢትዮጵያ ለተለያዩ ሀገራት ኢነርጂ በመሸጥ የውጭ ምንዛሪ እንደምታገኝ ገልጸዋል።
ከውጭ ምንዛሪ ግኝቱ በተጨማሪም ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎችን እንደሚያስገኝ ያመላከቱት ሞላ (ዶ/ር)፣ የኤሌክትሪክ ፍላጎታቸውን በራሳቸው ማሟላት ያልቻሉ ሀገራት ወደ ኢትዮጵያ በመምጣታቸው ኢትዮጵያ ከምታገኘው ገቢ በተጨማሪ ከሀገራቱ ጋር የተሻለ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ግንኙነት መፍጠር እንደምትችልም አስረድተዋል።
‹‹ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ከሚኖረው ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ አስተዋጽኦ አንጻር ዋና የልማት ማዕከል ነው›› ቢባል ማጋነን አይሆንም የሚሉት ቆስጠንጢኖስ ዶ/ር፤ በግድቡ ዙሪያ የተሠሩ ሥራዎች ትልቅ እንድምታ እንዳላቸውም ጠቁመዋል።
በአካባቢው የአግሮ ኢንዱስትሪዎች እንደሚስፋፉ ይህም ወጣቶች በግብርናው ዘርፍ የመሠማራት ዕድላቸው እንዲጨምር በር እንደሚከፍት አስታውቀዋል። ወደፊትም ከሕዳሴው ግድብም ሆነ ከሃይቁ በሚወጣ ውሃ በአነስተኛ የመስኖ ሥራዎች በመሳተፍ ወጣቶች ሥራ ፈላጊ ብቻ ሳይሆኑ ሥራ ፈጣሪ የሚሆኑበት ሰፊ ዕድል ይፈጠራል ሲሉ አብራርተዋል።
ቆስጠንጢኖስ (ዶ/ር) እንዳብራሩት፤ ከግብርና ሥራው በተጨማሪ ኢንዱስትሪዎች ይስፋፋሉ። ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል 64 በመቶ ያህል የአፍሪካ ቀርከሃ የሚመረትባቸው አካባቢ ነው። ይህም የቀርከሃ ኢንዱስትሪ እንዲስፋፋ ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል። ቀርከሃ ጠንካራና ቀላል በመሆኑ በርካታ የቤትና የቢሮ ዕቃዎችን መሥራት ያስችላል። ለአብነትም በከተማ ውስጥ ለሚሠሩ የጋራ መኖሪያ ቤቶች አገልግሎት የሚውሉ የቤት ውስጥ ቁሳቁስን ከቀርከሃ መሥራት ይቻላል። በመሆኑም በአካባቢው የቀርከሃ ኢንዱስትሪዎችን የሚያስፋፉ በርካታ ባለሀብቶችን መሳብ ቀላል ይሆናል።
‹‹ዘርፈ ብዙ አበርክቶ ያለው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በኢትዮጵያ ሕዝብ ተሳትፎ የተሠራ መሆኑ ልዩ ትርጉም አለው›› ያሉት ሞላ (ዶ/ር)፤ በኢትዮጵያ ደረጃ ትልቅና ሜጋ ፕሮጀክት ተብለው ከተነደፉ ፕሮጀክቶች መካከል ዋናው መሆኑን ገልጸዋል። ይህ ፕሮጀክት ሕዝባዊ ተቀባይነት የማግኘቱና በሕዝብም የመገንባቱ ዋናው ምክንያትም በሕዝቡ ውስጥ ታሪካዊ ቁጭት በመኖሩ ነው ይላሉ።
እሳቸው እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ በዓባይ ግድብ ላይ ከ86 በመቶ በላይ አስተዋጽኦ እያደረገች ምንም ሳትጠቀም ኖራለች፤ በዚህ የኢትዮጵያ ሀብት ሌሎች ሲጠቀሙ ኖረዋል። ዓባይ በኢትዮጵያውያን ልብ ውስጥ ቁጭት ፈጥሮ ቆይቷል። ይህን መሠረት ያደረገው ሥራም ትልቅ መነሳሳትን ፈጥሮ በሕዝቡ ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነትን አግኝቷል። በሀገር ውስጥ አቅም መሥራት የተቻለውም በዚሁ ምክንያት ነው።
ፕሮጀክቱ ሕዝባዊ ተቀባይነት ባያገኝ ኖሮ እዚህ ደረጃ ላይ ሊደርስ እንደማይችል ጠቅሰው፣ ወደፊት እንደዚህ አይነት ከጫፍ እስከ ጫፍ ሕዝባዊ ተቀባይነት ሊያገኝ የሚችል ፕሮጀክት ማሰብ እንደሚያስፈልግም ጠቁመዋል፡፡
ግድቡ አስቀድሞም ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታው ታምኖበት የተገባበት ግዙፍ ፕሮጀክት መሆኑን ሞላ (ዶ/ር)ተናግረዋል። ግድቡን ለማጠናቀቅ ከፍተኛ ወጪ መጠየቁን አስታውሰው፣ ግድቡ የቱንም ያህል ጊዜ የፈጀና ከፍተኛ ወጪ የጠየቀ ቢሆንም ከሚያስገኘው ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ጥቅም አንጻር አኩሪና ለኢትዮጵያውያን ትልቅ ትርጉም ያለው ግድብ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ በራሷ አቅም ግድቡን መገንባት አትችልም የሚል የጸና አቋም ይዘው ሲንቀሳቀሱ ለነበሩ አንዳንድ ምእራባውያንና ደጋፊዎቻቸው ትልቅ መልእክት እንደሚያስተላልፍም አስታውቀዋል። እነዚህ አካላት ኢትዮጵያ በውሃ አካባቢ ትልቅ የሚባል ድጋፍ እንዳታገኝ ሲሠሩ እንደነበር አስታውሰው፣ ኢትዮጵያ በራሷ ሀብት፣ ዕውቀት፣ ቴክኖሎጂ ይህን ግዙፍ ፕሮጀክት መገንባት ችላ ማሳየቷ ትልቅ ትርጉም እንዳለው ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላትን ተሰሚነት በከፍተኛ ደረጃ ያሳድጋል ሲሉም ተናግረው፣ በሀገር አቀፍ ደረጃ ከሚያመጣው አዎንታዊ ተጽዕኖ ባሻገር በዓለም አቀፉ ደረጃ የሚያመጣው ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ተሰሚነትም ቀላል ግምት የሚሰጠው አይደለም ብለዋል።
ይህን በተመለከተ የ ሞላን (ዶ/ር) ሃሳብ የሚያጠናክር ሃሳብ የሰጡት ዶ/ር ቆስጠንጢኖስ በበኩላቸው ግድቡ ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ትልቅ ተቃውሞ እንደገጠመው አስታውሰዋል።
እሳቸው እንዳስታወቁት፤ ግድቡ በርካታ ዓለም አቀፍ ጫናዎችን ተቋቁሞ እዚህ ደረጃ ለመድረሱ በዲፕሎማሲው ዘርፍ የተሠራው ሥራ ጠንካራ ለመሆኑ ማሳያ ነው። የግድቡ ሥራ አሁንም ድረስ ዋጋ እየተከፈለበት ያለ በመሆኑ ግብጽ ከኤርትራ፣ ከሶማሊያ፣ ከሱዳን ጋር የምታደርገው ግንኙነት ከግድቡ ጋር በተያያዘ በቀጣይም ጠንካራና ቀጣይነት ያለው የዲፕሎማሲ ሥራ መሥራት እንደሚያስፈልግ ያመላክታል።
የግድቡ ግንባታ እየተጠናቀቀና የውሃ ሙሌትም በተጠናቀቀበት በዚህ ጊዜ ግብጽ የውሃ በጀቷ አልቀነሰም ያሉት ዶክተር ቆስጠንጢኖስ፤ ይህንንም ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ይመለከተዋል ብለዋል። ሚዲያዎች ይህንን ሃሳብ በሰፊው በማስተዋወቅ ግብጽ ኢትዮጵያን በከንቱ ስትከስ እንደኖረች ማሳወቅ እንደሚገባቸውም አመላክተዋል። ምክንያቱም በቀጣይ ለሚሰሩ ሥራዎች እንቅፋት እንዳይሆን ማድረግ እንደሚገባ ጠቁመዋል። ግድቡ ከብዙ ትግል በኋላ ከዳር መድረስ በመቻሉ የተሰማቸውን ደስታ ቆስጠንጢኖስ (ዶ/ር) ገልጸዋል።
ሞላ (ዶ/ር) እስካሁን በተደረገው ርብርብ ግድቡ ስኬታማ መሆኑን ተናግረው፣ ግድቡን ለማጠናቀቅና ከፍጻሜ ለማድረስ ሶስቱ የልማት ተዋንያኖች ማለትም መንግሥት፣ ባለሃብቱና ህዝቡ ከፍተኛ ድርሻ እንዳላቸውም አስገንዝበዋል። እነዚህ የልማት ተዋንያኖች ተቀናጅተው ኃላፊነታቸውን እንዲወጡም አሳስበዋል።
እሳቸው እንዳስታወቁት፤ በተለይም የማስተባበር የመምራትና አቅጣጫ የማሳየት ኃላፊነት ያለበት መንግሥት መረጃዎችን በወቅቱ በማቅረብ የመሪነት ሚናውን ሊወጣ ይገባል። ህዝቡም ገንዘቡን፣ ጉልበቱንና ዕውቀቱን በማቀበል፤ ባለሃብቱም ገንዘቡን በማዋጣት ግድቡን ከዳር ማድረስ ይጠበቅባቸዋል፡፡
‹‹መዘናጋት ብዙ ዋጋ ያስከፍላል›› ያሉት ሞላ (ዶ/ር) አሁን ወደ ፍጻሜው ሲቃረብና አለቀ አለቀ ሲባል መዘናጋት እንዳይፈጠርም አሳስበዋል፡፡
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ መጋቢት 27 ቀን 2017 ዓ.ም