አዲስ አበባ፡- መንግሥት ለዓመታት ከእንግሊዝ መንግሥት ጋር ባደረገው ዲፕሎማሲያዊ ድርድር ከ151 ዓመት በኋላ ወደ አገሩ የተመለሰው የአፄ ቴዎድሮስ ጉንጉን ፀጉር (ቁንዳላ) የኢትዮጵያ ብሄራዊ ሙዚየም በአደራተቀበለ፡፡ ‹‹የአንድነት ገመድ›› እንደሆነ በብዙኃን የሚታመንበት ታላቅ ቅርስ ወደ አገሩ ሲገባ ደማቅ የአቀባበል ሥነሥርዓት ተካሂዶለታል፡፡
ትናንት በቅርስ ጥናት እና ጥበቃ ባለሥልጣን በተካሄደው የአቀባበል ሥነ ሥርዓት ላይ ከአገረ እንግሊዝ በቀጥታ የአፄ ቴዎድሮስ ቁንዳላ ይዘውየገቡት የባህል እና ቱሪዝም ሚኒስትር ዶክተር ሂሩት ካሳው ቅርሱ ወደፊት በሚዘጋጅለት ትክክለኛ ቦታ እስኪያርፍ ድረስ በአደራ ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ሙዚየም አስረክበዋል፡፡
በርክክብ ሥነሥርዓቱ ላይ እንደተናገሩት፣ የአፄ ቴዎድሮስ ፀጉር ከረጅም ዓመታት በኋላ መመለሱ ለኢትዮጵያውያን እና ለመንግሥት ኩራት ነው፡፡ መንግሥት ለአገረ እንግሊዝ ካቀረበው በርካታ ጥያቄዎች ውስጥ የመጀመሪያው የሆነውን አዎንታዊ ምላሽ በመስጠት ቅርሱን መልሷል፡፡
ከዚህ በኋላም ምላሽ የሚያገኙ ጥያቄዎች እንዳሉ ገልጸው፤ በታሪክ አጋጣሚ ከአገር የወጡ ቅርሶችን የዲፕሎማሲ ግንኙነቱን በማጠናከር ለማስመለስይሠራል ብለዋል፡፡ እንደ ዶክተር ሂሩት ገለፃ፣የአፄ ቴዎድሮስ የኢትዮጵያ አንድነት እንዲሁም ራዕይ በሁሉም ኢትዮጵያውያን ውስጥ አለ፡፡
ይህ ቅርስ መመለሱ ራዕዩ እንዲታደስ እና ብዝሃነትን የምታስተናግድ አንድ ጠንካራ ኢትዮጵያ እንድትገነባ የሚያግዝ ነው፡፡ ታላቅ የመንፈስ ጥንካሬንም በአገሪቷ ላይ ያሰፍናል፡፡ ‹‹አፄ ቴዎድሮስ ኢትዮጵያዊ ናቸው›› ያሉት ሚኒስትሯ፤ ከዚህ ውጪ ሌላ ዘር የላቸውም ብለዋል፡፡
‹‹ እንግሊዞች 151 ዓመት የአፄ ቴዎድሮስን ፀጉር ለምን ጠብቀው አቆዩት?›› የሚል ጥያቄ በማንሳትም፤ የታሪክ እና የቅርስ አያያዝ ሥርዓቱን በተመለከተ ሁሉም ኢትዮጵያዊ እራሱን መጠየቅ እና መመርመር ይኖርበታል ብለዋል፡፡ የጥንታዊ ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር ፕሬዚዳንት ልጅ ዳንኤል ጆቴ በበኩላቸው ፣ የአፄ ቴዎድሮስ ጉንጉን ፀጉር ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያን አንድነት አስተሳስሮ የያዘ ታላቅ ቅርስ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
መጪው ትውልድም እንደ ዓይኑ ብሌን ሊጠብቀውና ሊንከባከበው ይገባል፡፡ የአፄ ቴዎድሮስ ቁንዳላ በብሄራዊ ሙዚየም በአደራ ከሌሎች በጥብቅ ከተያዙ መሰል ቅርሶች ጋር በጊዜያዊነት እንደሚቀመጥ ታውቋል፡፡
ትክክለኛው ማረፊያው ሲዘጋጅለት ወደዚያው ያመራል፡፡ ንጉሱ በኢትዮጵያ ታሪክ ትልቅ ቦታ የነበራቸውና እስካሁንም በጀግንነታቸው የሚጠሩ ናቸው። ከስማቸውና ከአልበገር ባይነት ስሜታቸው በተጨማሪ ደግሞ እስከዛሬ ብዙዎች የሚያነሷቸው በፀጉር አሠራራቸው ጭምር ነው። ይህ ታላቅ ቅርስ ወደ አገሩ መመለሱ በአገረ ጀርመን፣ፈረንሳይ፣ ጣሊያን፣ እንዲሁም ሌሎች አገራቶች የሚገኙትን መሰል ቅርሶች ለማስመለስ ትልቅ ዕድል እንደሚከፍት ተገልጿል፡፡
መረጃዎች እንደሚያመለክቱት በእንግሊዝ ሙዚየሞች ውስጥ ብቻ 11 ታቦቶች እንዲሁም ከ300 በላይ የብራና መጽሐፍትን ጨምሮ በርካታ ቅርሶች ይገኛሉ፡፡ በአቀባበል ሥነሥርዓቱ ላይ ‹‹አምጡ ቆርጣችሁ ከሹሩባው ላይ፤ሚዛን እንሰር እንዳንለያይ›› በሚለው የአፄ ቴዎድሮስ ሙዚቃ እና በሌሎች ሥራዎቹ የሚታወቀው ተወዳጁ አርቲስት ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮን) ጨምሮ በርካታ ታዋቂና ተፅዕኖ ፈጣሪ እንግዶች ታዳሚ ሆነዋል፡፡
አዲስ ዘመን መጋቢት 15/2011
በዳግም ከበደ