አዲስ አበባ፡- በኢትዮጵያ ውስጥ ከፍተኛ የፖለቲካ ስብራቶች እንዳሉና ለስብራቶቹ ህክምና ማበጀት እንደሚገባ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ ገለፁ፡፡ ቀጣዩ ምርጫ ፍፁም ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚመጣውን ውጤት በፀጋ መቀበል እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል፡፡
አዲስ ወግ በተሰኘውና የጠቅላይ ሚኒስቴር ፅህፈት ቤት በሸራተን አዲስ ሆቴል የአንድ ዓመት የለውጥ ጉዞን አስመልክቶ፤ በተዘጋጀው የሁለት ቀናት መድረክ ማጠቃለያ ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ እንደገለፁት፤ በኢትዮጵያ ውስጥ በብዙ መልኩ የሚገለፁ ከፍተኛ የፖለቲካ ስብራቶች በመኖራቸው ለስብራቶቹ ህክምና ማበጀት ያስፈልጋል፡፡
እንደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገለፃ በኢትዮጵያ ውስጥ እየታዩ ካሉ የፖለቲካ ስብራቶች መካከል ማገናዘብ አለመቻልና ህሊና ቢስነት፣ ልግመኝነት፣ ዋልታ ረገጥነት አስተሳሰብን ማራመድ፣ ጊዜ ታካኪነት፣ ሙያን መናቅ፣ አቅላይነትና የማህበራዊ ድረ ገፆችን ያለአግባብ መጠቀም ናቸው። ከውጭ የሚመጡና ከሀገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ ውጪ የሆኑ ሃሳቦችን በማስወገድና በጋራ በመቆም የፖለቲካ ስብራቶቹን ማከም ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
በተያያዘም ቀጣዩ ምርጫ ፍፁም ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን ማንም አሸናፊ ቢሆን የፖለቲካ ፓርቲ ግን ውጤቱን በፀጋ መቀበል እንደሚኖርበት አሳስበዋል፡፡ ምርጫው አንድ ዓመት የቀረው ከመሆኑ አኳያም ፖለቲካዊ አቋም ያለው ሁሉ ከፈለገ በግሉ ካልፈለገ በፓርቲ በምርጫው አሸናፊ ከሆነ ሌሎች ውጤቱን በፀጋ ሊቀበሉ ይገባል፡ ፡ ከቀጣዩ ሀገራዊ ምርጫ ጋር በተያያዘ ምርጫው በዴሞክራሲያዊ መንገድ እንዲካሄድ መሥራት እንደሚያስፈልግ ጠቅሰው፤ በምርጫው ተፎካካሪ ፓርቲ ቢያሸንፍ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ሥልጣን እናስረክባለን ብለዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎችም በአሁኑ ወቅት ያለው መንግሥት መልካም ነገር ከሠራ መደገፍ ካልሠራ ደግሞ መንቀፍ እንዳለባቸውና ይህም ካልሆነ በምርጫ መጣል እንደሚችሉም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልፀዋል፡፡ የፖለቲካ በሽታና ችግር በልሂቃን፣ በአክቲቪስቶች እና በፖለተከኞች ላይ የሚስተዋል መሆኑንም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ ገልፀው፤ ጊዜን በማሻገርና ትናንት ከዛሬ ጋር በማዛመድ ትውልድ መቅረፅ እንደሚገባም አሳስበዋል። ከወቅታዊው የፖለቲካ ሁኔታ ጋር በተያያዘ የሰከነ ውይይት ማድረግ እንደሚያስፈልግም አስረድተዋል።
«በኢትዮጵያውያን የበዛ ጥላቻ፣ በቀል እና አለመግባባት አለ» ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ብዙ ችግር ተሸክሞ መጓዝ ስለማይቻል ይህን ማራገፍና መቅረፍ ተገቢ መሆኑን አፅንኦት ሰጥተው ተናግረዋል። በመሆኑም ኢትዮጵያ እንድትቆይና እንዳትፈርስ የሚፈልግ ዜጋ ከአፍራሽ ሃሳቦች መራቅ እንዳለበት ተናግረዋል።
በሀገሪቱ በማህበራዊ የትስስር ገጽ በተለይም በፌስ ቡክ አጠቃቀም ዙሪያ ችግር እንዳለ ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ለማስተካከል የሚያግዝ ህግ እየተዘጋጀና ከፌስ ቡክ ኩባንያ ጋር በጉዳዩ ዙሪያ ንግግር እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል።
የማክሮ ኢኮኖሚውን ሚዛናዊነት ማስተካከል የበጀት ዓመቱ ዋነኛ የትኩረት አቅጣጫ መሆኑን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ከዚህ ጋር ተያይዞ የመንግሥት ወጪን ለመቀነስ እየተሠራ መሆኑን ገልፀዋል። በቀጣይ ሀገሪቱ የምትከተለውን የኢኮኖሚ እሳቤ የሚመለከት ዝርዝር ጥናት መዘጋጀቱን እና በአሁን ወቅት ሀገሪቱ ከፍተኛ የእዳ ጫና ስላለባት ተጨማሪ ብድር እንዳትውስድ መደረጉን አስታውቀዋል። የመስኖ ልማትና ቱሪዝምን ማስፋፋት የትኩረት ማዕከል መሆኑንም ገልፀዋል።
የውጭ ግንኙነትን በሚመለከት ባለፈው አንድ ዓመት ብዙ አመርቂ ሥራ መሠራቱን አስታውሰው፤ ከኤርትራ ጋር የ20 ዓመታት የጦርነት እና ፍጥጫ ማርገብ መቻሉን ለአብነት ጠቅሰዋል። ከተለያዩ ሀገራት ጋር በተሠራው የዲፕሎማሲ ሥራ የመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት ኢትዮጵያን በማድመጥ ዜጎቿን ማክበር እንዲችሉ ያስቻለ መሆኑን አመልክተዋል። በሌላ በኩል ቻይና ለአዲስ አበባ የወንዞች ልማት ፕሮጀክት ወጪ ከሚደረገው ገንዘብ ውስጥ አንድ አራተኛውን የሚሽፍን ብድር ለመስጠት ቃል ገብታለች። የመካከለኛው ምስራቅ ሀገራትም መጠኑ ያልተገለፀ የገንዘብ ድጋፍ እናደርጋለን ያሉ ሲሆን፤ ኢትዮጵያውያንም የራሳቸውን ኢንቨስትመንት ያዋጣሉ ብለዋል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 15/2011
በአስናቀ ፀጋዬ