የወጣት ሴቶች ማቋቋሚያ ማህበር ከተመሰረተ ሦስት አሥርት ዓመታትን ማስቆጠሩን መሥራቾቹ ይናገራሉ። የተመሰረተበት ዋና ዓላማ ወጣት ሴቶችን የተለያዩ ሙያዎች ባለቤት በማድረግ የየራሳቸውን የገቢ ምንጭ በመፍጠር ኑሯቸውን እንዲደግፉ ማድረግ ነው። አስገድዶ መድፈር በደረሰባቸው ሴት ወጣቶች ላይም ትኩረት አድርጎ በመስራት ላይ ይገኛል።
ይሁንና ማህበሩ ቀስ በቀስ የተመሰረተበትን ዓላማ ሳይለቅ የተለያዩ የአካል ጉዳት ያለባቸውን ወጣት ሴቶችና ወንዶች በዚሁ ቅኝት መደገፉን ቀጥሎ 30 ዓመታትን አስቆጥሯል። ካለፈው ግንቦት 22 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ ለ10 ተከታታይ ቀናት በሚቆየው የቀርከሃ ሥራ ስልጠና 34 መስማት የተሳናቸውን ወጣቶች ካዛንቺስ፣ ባንቢስ የገበያ ማዕከል አካባቢ በሚገኘው የስልጠና ማዕከሉ ውስጥ እያሰለጠነ ይገኛል።
ወጣት እስክንድር መንግስተአብ መስማት ከተሳናቸው ሰልጣኝ ወጣቶች መካከል ሲሆን እሱ በአስተርጓሚው በኩል እንደነገረን ከአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 6 ነው ተመልምሎ የተላከው። ከዚህ ቀደም በምልክት ቋንቋ ስልጠና ወስዶ መስማት የተሳናቸውን፣ ግን ደግሞ በምልክት ቋንቋ የመግባባት ምንም ዓይነት ችሎታ የሌላቸውን የሕብረተሰብ ክፍሎች በምልክት ቋንቋ እንዲግባቡ የሚያስችል ስልጠና ሲሰጥ ቆይቷል። ሆኖም ሥራው ኮንትራት በመሆኑ ሲጠናቀቅ ለአንድ ዓመት ያህል ሥራ ፈትቶ ለመቀመጥ ተገዷል።
በዚህ መካከል አሁን እየሰለጠንኩበት ያለው የወጣት ሴቶች ማቋቋሚያ ማህበር ቀድሞ ኮንትራት እሰራበት ለነበረው ተቋም መስማት የተሳናቸው ሥራ አጥ ወጣቶችን መልምላችሁ ስማቸውን ላኩልኝ ሲል እኔን በወረዳ በኩል አቀረበኝ ይላል። ወጣቱ እንደሚለው ”ከስምንተኛ እስከ 12ኛ ክፍል የትምህርት ደረጃ ያላቸው” የሚለውም ከምልመላው መስፈርት አንዱ ነበር።
ወጣቱ ካዛንቺስ በሚገኘው የማሕበሩ ስልጠና ማዕከል መሰልጠን ከጀመረ ሁለተኛ ቀኑን አሰራር ላይ እንደሆነ ነግሮናል። ስልጠናውን እየወሰዱ ያሉት በቡድን በቡድን ሆነው ነው። አንዱ ቡድን ስድስት አንዳንዴም ሰባት አባላት ይኖሩታል፤ እንደ ሁኔታው ነው ማለት ነው። ይህ ደግሞ ሥራውን ተጋግዘውና ፈጥነው ለመልመድ እያስቻላቸው ይገኛል። በቀጣይ ቀናት የመጽሐፍ መደርደሪያዎችንና ወንበሮችን ጨምሮ ከቀርከሃ በሚሰሩ በተለያዩ ቁሳቁሶች ለመስራት የሚያስችል ስልጠና ይወስዳል። ከስልጠናው በኋላ በቡድን እንደሆኑ በቀርከሃ ሥራ ላይ በተሰማራ ተቋም ተቀጥረው ወይም የራሳቸውን ሥራ በመፍጠር ለመሥራትና ዘላቂ የገቢ ምንጭ ለማግኘት እንዳሰቡ አጫውቶናል።
ሌላዋ የስልጠናው ተሳታፊና መስማት የተሳናት ወጣት ሊዲያ በልሁ ተመልምላ የመጣችው ከነፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ 3 ነው። ወጣቷ በ2003 ዓ.ም ከእንጦጦ ቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ በሥዕል ሙያ በዲፕሎማ ተመርቃ ነበር። በሥዕል ሙያዋም በመካኒሳ መስማት የተሳናቸው ትምህርት ቤት በመምህርነት ለአራት ዓመታት አገልግላለች። በርካታ መስማት የተሳናቸውን ወጣቶች በሥዕል ሙያ ማሰልጠን ችላለች። ለጠቅ አድርጋም ቢዲአይኤ የተባለ ድርጅት በመቀጠር እንዲሁ ለአራት ዓመታት ሰርታለች።
ነገር ግን ሥራው ቋሚ ባለመሆኑ ሥራ ፈትታ ከተቀመጠች ዓመታትን አስቆጥራለች። ቋሚ ገቢ የሚያስገኝ የመንግስት ወይም ሌላ ሥራ ለማግኘት ጥረት ብታደርግም አልተሳካላትም። ያለ ሥራ መቀመጡ አሁን በአገራችን ካለው የኑሮ ውድነት፤ በቅርቡ ትዳር መስርታ ከወለደቻቸው ሁለት ልጆች ጋር ተዳምሮ ሲያስቸግራት በቆየችበት ወቅት ይሄ ስልጠና በቴክስት ደረሳት። ሥራው ከሥዕል ጋር ግንኙነት ያለው ቅርፃ ቅርፅ እንደመሆኑ ወደ ማህበሩ መጥታ ተመዘገበችና ስልጠናውን መውሰድ ጀመረች። በአሁኑ ሰዓት ከቀርከሃ ወንበርና ጠረጴዛ፣ የመጽሐፍ መደርደሪያ እንዲሁም የተለያዩ ቁሳቁሶችን በመሥራት እየሰለጠነች እንደምትገኝ ገልፃልናለች።
‹‹በየቤቱ እኔ ያገኘሁትን ይህን ዕድል ያላገኙ በርካታ መስማት የተሳናቸው ሥራ አጥ ወጣቶች አሉ›› የምትለው ሊዲያ ከስልጠናው በኋላ በሙያው ተቀጥራ ወይም የራሷን ሥራ ፈጥራ ዘላቂ የገቢ ምንጭ ከመፍጠር ባሻገር እነዚህን ወጣቶች በቀርከሃ ሥራ ሙያ የማሰልጠን ዕቅድም እንዳላት አውስታለች። ሁሉም ባይሆንም አንዳንዱ የህብረተሰብ ክፍል መስማት የተሳናቸው ሥራ መሥራት አይችሉም በሚል የተሳሳተ ግምት እንዲህ ባለው ስልጠና እንዲሳተፉ አያደርግም። ከግንዛቤ እጥረት ቤተሰቦቻቸውም ከቤት እንዳይወጡ ሁሉ ይከለክሏቸዋል። በመሆኑም ዕድሉን አያገኙም። እነሱን ማሰልጠን ያሰበችውም ለዚህ ነው።
አቶ ታደሰ ተስፋዬ የዛሬ 30 ዓመት የወጣት ሴቶች ማቋቋሚያ ማህበርን ከመሰረቱት አንዱ ናቸው። እኛ ያገኘናቸው መስማት ለተሳናቸው ወጣቶች የቀርከሃ ሙያ ስልጠና ሲሰጡ በመሆኑም የቀርከሃ ሙያ አሰልጣኝ እንደሆኑም ነግረውናል።
እንደ አቶ ታደሰ ለ10 ቀናት በሚቆየው ስልጠና የሚሳተፉት 34 ወጣቶች በሙሉ መስማት የተሳናቸው ናቸው። ቁጥራቸው 34 ያህል ሲሆን ከነዚህ መካከል 16ቱ ሴት መስማት የተሳናቸው ወጣቶች ናቸው። ወጣቶቹ በአሁኑ ወቅት ሙሉ በሙሉ ሥራ አጥ ሲሆኑ ከተለያዩ ክፍለ ከተሞች በዚሁ ሥራ አጥነታቸው ተመልምለው በመምጣት ነው ስልጠናው ላይ መሳተፍ የቻሉት። ማህበሩ ስልጠናውን መስማት ለተሳናቸው ወጣቶች ሲሰጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።
እየሰለጠኑ የሚገኙት ከቀርከሃ በሚሰሩ የተለያዩ ቁሳቁሶች ሙያ ነው። ለአብነት የቀርከሃ ወንበር፣ የመጽሐፍ መደርደርያ፣ የአንፑል ማቀፊያና ሌሎች ቁሳቁሶች ይጠቀሳሉ። ማህበሩ ስልጠናውን እየሰጠ ያለው መስማት ለተሳናቸው የሕብረተሰብ ክፍሎች ጥበቃ ከሚያደርገው ”ተሀድሶ መስማት የተሳናቸው ማህበር” ጋር በመተባበር እንደሆነም ይናገራሉ።
እንደ አቶ ታደሰ ማብራሪያ ድርጅቱ በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው መስማት የተሳናቸው ወጣቶች በተለያየ ምክንያት የሥራ ዕድል ባለማግኘታቸው ዕድሉን እንዲያገኙ ለማድረግ ረጅም ስልጠናዎችን ሊሰጣቸው ዝግጅት እያደረገ ይገኛል። ዋና ዓላማው ወጣቶቹ የነዚህ ሙያዎች ባለቤት ከሆኑ በኋላ የየራሳቸውን የገቢ ምንጭ በመፍጠር ከሥራ አጥነት ተላቅቀውና ራሳቸውን ችለው የተሻለ ኑሮ እንዲኖሩ ማድረግ ነው። በመሆኑም ተመስርቶ ወደ ሥራ ከገባ ጀምሮ ባለፉት 30 ዓመታት በልብስ ስፌት፣ በቆዳና በተለያዩ ሙያዎች፤ እንዲሁም በስነ-ተዋልዶ 2ሺህ 200 ሴቶችን ማሰልጠንና በሰለጠኑበት ሙያ የየራሳቸውን ሥራ በመፍጠር የገቢ ምንጭ እንዲያገኙ ማድረግ ችሏል። ከነዚህ መካከል 30 ያህሉ አስገድዶ መድፈር የተፈፀመባቸው ናቸው። በተለይ ኤች.አይ.ቪ/ኤድስ በአገራችን በከፍተኛ ደረጃ ተስፋፍቶ በነበረበት ሰዓት 600 ወጣቶችን በስነ-ተዋልዶ አሰልጥኖና አደራጅቶ በ“ቡና ጠጡ” መርሐ ግብር በሰፊው ወደ ሥራ ያስገባበት ወቅት ነበር።
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን ግንቦት 25/2014