በኪነጥበብ ዕድገት ላቅ ብለው የሄዱ አገራት ለማህበራዊ ለውጥ ትልቅ አስተዋፅኦ የሚያበረክተውን ኪነጥበብ፤ በተለያየ መልኩ ይገለገሉበታል። ማህበረሰባቸውን ለመቅረፅና የተለያዩ በጎ ተፅዕኖዎችን ለመፍጠር እየተጠቀሙበትም ይገኛሉ። አገራቱ ማህበራዊ ፍልስፍናቸውና አገራዊ አስተሳሰብ ከማህበረሰባቸው አልፎ በሌላው ላይ በማንፀባረቅ ብሎም በማስረፅ የሚፈልጉትን ዓላማ ለማሳካትም ችለውበታል። በዚህም አገራዊ ጥቅማቸውን ማስጠበቅ ቀሏቸዋል።
ኪነ ጥበብ የአስተሳሰብ ለውጥ አንዱ መንገድ መሆኑ ቀድሞ ገብቷቸዋልና ለኪነ ጥበብ እድገት አስፈላጊ ነው የሚሉትን ሁሉ ያደርጋሉ። ከዚህ ማሳያዎች መሀከል በዓለምአቀፍ ደረጃ እጅግ የታወቁ ኪነጥበባዊ ሽልማቶችና ማበረታቻዎች መጥቀስ ይቻላል። በእኛም አገር ዘግይቶም ቢሆን ለኪነጥበብ እድገት ትልቅ ሚና ያለው የኪነጥበብ ባለሙያዎችና ስራዎቻቸው መሸለምና ማበረታታት ከተጀመረ ከረምረም ብሏል።
አሁን ላይ በአገራችን በተለያዩ ተቋማት አዘጋጅነት የኪነ ጥበብ ስራዎች ይበረቱ ዘንድ ለኪነጥበብ ባለሙያዎች የሚሰጡ ሽልማቶች ተበራክተዋል። የኪነ ጥበብ ስራዎች እድገት ከፍ ከሚያደርጉት ተግባራት አንዱ የኪነጥበብ ባለሙያዎች ማበረታታት እና በስራቸው እውቅናና ሽልማት እንዲያገኙ ማድረግ ነው። የኪነጥበብ ባለሙያዎች በስራዎቻቸው እውቅናና የተለያየ ማበረታቻዎችን ማግኘታቸው የሚሰሩት ስራ የተሻለ ለማድረግና በኪነጥበቡ ዘርፍ ጠንክረው በውድድር መንፈስ የተሻሉ ስራዎችን ለመስራት ያስችላቸዋል።
በአገር ደረጃ ለጥበብ ቤተሰቦች ከሚበረከቱ ሽልማቶች ውስጥ ባለፈው ሳምንት ተካሂዶ የነበረው ለዛ ሽልማት አንዱ ነው። የዛሬው የዘመን ጥበብ በዚህ የሙዚቃና የፊልም ስራዎች ተመርጠው የዓመቱ ምርጥ በመሰኘት በተለያየ ዘርፍ የሚሸለሙበት ደማቅ የሽልማት ሥነ ሥርዓት ላይ ያተኩራል።
የለዛ ሽልማት ከጅማሮ
የኪነጥበብ ባለሙያውን ለማበርታት ብሎም በዘርፉ ያውን ኪናዊ እንቅስቃሴ የተሻለ ደረጃ ላይ ለማድረስ በማሰብ በኢትዮጵያ አቆጣጠር በ2003 በአምስት ዘርፎች ሽልማቱን የጀመረው ለዛ አዋርድ በእስከዛሬው ቆይታው ለዘጠኝ ተከታታይ ዓመታት የጥበብ ባለሙያዎችን ሲሸልም ዛሬ ደርሷል። በእርግጥ ከጊዜ ወደ ጊዜ የሽልማት ዘርፎቹን እያሰፋና ተሸላሚዎችንም በየመድረኩ እያቀረበ ሲሸልም የቆየው ለዛ ሽልማት ለፊልምና ሙዚቃ ዘርፍ ዕድገት የራሱን አዎንታዊ ሚና ተጫውቷል።
ሽልማት በጀመረበት በ2003 ዓ.ም የዓመቱ ምርጥ ነጠላ ዜማ፣ ምርጥ ተዋናይት፣ የዓመቱ ምርጥ ተዋናይ፣ የዓመቱ ምርጥ ፊልምና የዓመቱ ምርጥ አልበም በሚሉ አምስት ዘርፎች የመጀመሪያው በሸገር ኤፍ.ኤም 102.1 የለዛ ሬዲዮ ፕሮግራም የአድማጮች ምርጫ ሽልማት ሥነሥርዓት በሚል ስያሜ የሀገራችን የኪነጥበብ ሰዎች በተገኙበት በታሪካዊው የብሔራዊ ቴያትር አዳራሽ በደማቁ ተካሂዶ ነበር።
በወቅቱ በአምስት የተለያዩ ዘርፎች ማለትም ዘሪቱ ከበደ “አርቴፊሻያል” በሚለው ነጠላ ሙዚቃዋ፣ ናትናኤል አያሌው (ናቲ ማን) “Man” ብሎ በሰየመው የመጀመሪያ አልበሙ፣ አበበ ባልቻ በሄሮሺማ፣ ራሱ ሄሮሺማ ደግሞ በምርጥ በፊልምነቱ፣ ሰሃር አብዱልከሪም “ያንቺው ሌባ” በተሰኘ ፊልም ላይ ባሳየችው ትወና፣ በየ ውድድር ዘርፎቹ ቀዳሚ አሸናፊዎች ሆነው በለዛ ሽልማት የመጀመሪያዎቹ ተሸላሚዎች ሆነዋል።
በዚህ መልክ በድምቀት የተጀመረው ለዛ ሽልማት ዘንድሮ አምና በኮሮና ምክንያት ባለመካሄዱ የሁለቱን ዓመት ጥምር ሽልማቶች በአንድ ላይ በማድረግ “10ኛውና 11ኛው ለዛ ሽልማት” በሚል ርዕስ ደማቅ የሽልማት መርሀ ግብር በሂልተን ሆቴል ግንቦት 17 ቀን 2014 አድርጓል። በዚህ ዝነኛና ታዋቂ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ባገናኘው መድረክ የሙዚቃና የፊልም ባለሙያዎች በስራዎቻቸው ተመርጠው የላቀ ክብርና ሽልማት ተቀዳጅተዋል።
በሸገር ኤፍ ኤም የለዛ የአድማጮች ምርጫ ሽልማት በሚል መጠሪያ በአምስት ዘርፎች የኪነ ጥበብ ባለሙያዎችን በመሸለም የጀመረው ለዛ ሽልማት ዛሬ ላይ የሽልማት ዘርፉን አሳድጎ፣ የመምረጫ መስፈርቱንም አሻሽሎና አድማጭ ተመልካቹን አሳታፊ ባደረገ መልኩ የ10ኛና የ11ኛ በ12 የተለያዩ ዘርፎች የሽልማት መርሀ ግብሩን ማድረጉም ተገልጿል።
ከውጤት አንፃር ከዚህ በፊት የተሰጡ የሙዚቃና የፊልም ሽልማቶች የላቀ ፋይዳ አስገኝተዋል ለማለትና በትክክል አዎንታዊ ተፅኖአቸውን ለማወቅ ጥናቶችን ማድረግ ቢያስፈልግም፤ ለአርቲስቶች ወይም ለኪነጥበብ ባለሙያዎች የሚሰጡ ሽልማቶች የኪነጥበብ ስራዎቻቸው በተሻለ መልኩ ለተደራሲው ያደርሱ ዘንድ እንደሚረዳቸውና ጥሩ መነሳሳት እንደሚፈጥርላቸው መገመት አይከብድም። የፊልምና የሙዚቃ ባለሙያዎች የሚሰጡት አስተያየትም ለዚሁ ማሳያ ነው።
በመርሀ ግብሩ ላይ የተገኙ የፊልምና የሙዚቃ ባለሙያዎች አስተያየታቸው የሰጡ ሲሆን በየዓመቱ ምርጥ ስራ ለሰሩና በህዝብ ዘንድ የተወደደላቸው እንዲሁም በባለሙያዎች ተመርጠው በዚህ መልክ መበረታታቸው ለኪነጥበቡ እድገት ትልቅ አስተዋፅዖ እንዳለው ገልፀዋል። መሰል ሽልማቶችና ማበረታቻዎች ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል በማለት አስተያየቱን የሰጠው አርቲስት ይገረም ደጀኔ፤ ሽልማቱ አርቲስቶችን ለተሻለ ስራ ያነሳሳል የሚል እምነት እንዳለውም ገልጿል።
በአገራችን በተለያየ ጊዜ የሚዘጋጁ መሰል ሽልማቶች በተለይም በፊልም ስራ ላይ የራሱ የሆነ አስተዋፅዖ ማበርከቱን እንደሚያምን ገልፆ ባለሙያውም በህዝብ ስራው ተወዶለት የክብር ሽልማት ማግኘቱ ለተሻለ ስራ የሚያነሳሳው እንደሆነ ይጠቁሟል።
ድምፃዊ ጆኒ ራጋ በበኩሉ የኪነ ጥበብ ሽልማቶች በተለይ ለሙዚቃ መነቃቃት አዎንታዊ አስተዋፅዖ እንዳላቸውና በየጊዜ እየተሰጡ ባሉ ሽልማቶች የሙዚቃ ባለሙያዎቹ ተበራክተው በርካታ ስራዎች ከጥራት ጋር ተመልካች ጋር ማድረስ እዳስቻላቸው አስረድቷል። በለዛ ሽልማት ላይ በርካታ ጊዜ እደታደመ የሚገልፀው ድምፃዊ ጆኒ ባለፉት ሽልማቶች የነበሩ የሽልማት ሂደቶች እና መርሀ ግብሮች በጥሩ መልኩ እንደተመለከተው አስተያየቱን ሰጥቷል።
አርቲስት አለማየሁ ታደሰ በበኩሉ መሰል ሽልማቶች ተጠናክረው መቀጠል እዳለባቸው ገልፆ፤ አርቲስቶች በየዓመቱ በሚሰሩት ስራ መሸለማቸው ብርቱና ጠንካራ እንደሚያደርጋቸው አስረድቷል። በተለይ የሰሩትን ስራ ከአድማጭ ተመልካች ስራህን ወደነዋል ለዚህም መበረታታት ይገባሀል የሚል መልዕክት ማድረሻም እንደሚሆን ገልጿል። ባለሙያውም ሙያዊ አደራውን የሚቀበልበት መድረክ እንደሆነና ህዝቡም በስራህ በርትተህ በዚሁ ቀጥል የሚልበት መድረክ መሆኑን አንስቷል።
የዚህ ዓመት የለዛ ሽልማት አሸናፊዎች
እጅግ በተዋበ መልኩ በተሰናዳ መድረክ በልዩና ደማቅ በሆነ መልኩ በተካሄደው የሽልማት ሥነ ሥርዓት ላይ በሙዚቃና ፊልም ስራ አንቱ በተሰኙ አርቲስቶች የዓመቱ ምርጥ ተብለው የተመረጡ ባለሙያዎች በክብር ሽልማታቸውን ሰጥተዋል። በዚህ እጅግ የበረታ ፉክክር ተደርጎበታል በተባለው የባለሙያዎችን ስራ መርጦ መሸለም መርሀ ግብር ተሸላሚዎች ወደመድረክ ወጥተው ሽልማታቸውን ተቀብለው፤ ከብርቱ መልዕክታቸው ጋር አጋሮቻቸውን አመስግነውበታል።
በለዛ አዋርድ የዓመቱ ምርጥ ተሰኝተው ለሽልማት የበቁ ስራዎችና ባለሙያዎች የሚከተሉት ነበሩ። በምርጥ ተከታታይ የቴሌቪዥን ፊልም እረኛዬ ድራማ ሲሆን በዚሁ ድራማ የታጨችው ድርብ ወርቅ ሰይፉ በተከታታይ የቴሌቪዥን ፊልም ምርጥ ተዋናይት በመሰኘት ተሸላሚ ሆናለች። ይህ በሶስት እንስት ደራሲያን ተደርሶ በቅድስት ይልማ የተዘጋጀው እረኛዬ የተሰኘው ድራማ ባለፈው ሳምንት በተካሄደው የጉማ ሽልማት ላይ በተለያየ ዘርፍ አሸናፊ ሆኖ መሸለሙ ይታወሳል።
ሌላኛው ብርቱ ፉክክር ተካሂዶበት አሸናፊነቱ የተለየበት በተከታታይ የቴሌቪዥን ፊልም ምርጥ ተዋናይ ዘርፍ የ9ኛው ሺ ሚሊዮን ብርሃኔ ያሸነፈ ሲሆን የዓመቱ ምርጥ ፊልም እንሳሮ በመሆን የለዛ ሽልማት በክብር ተቀዳጅቷል። እንሳሮ የተሰኘው ፊልም በሌሎች የሽልማት መድረኮች እጩ በመሆን ሽልማቶችን የተቀዳጀ ሲሆን ፊልሙ ለእይታ በበቃ በጥቂት ቀናት ውስጥም ተሰርቆ በህገወጥ መንገድ መሰራጨቱ ይታወሳል።
አማኑዔል ሀብታሙ በእንሳሮ ፊልም የዓመቱ ምርጥ የፊልም ተዋናይ በመሆን የተሸለመ ሲሆን ፤ የዓመቱ ምርጥ የፊልም ተዋናይት ዘርፍ መስከረም አበራ በእንሳሮ ፊልም አሸናፊ በመሆን ሽልማት አግኝታለች። ሌላኛው በመድረኩ ላይ ነግሶ የአሸናፊነት ማዕረግ የተቀዳጀው የለዛ ሽልማት የዓመቱ ምርጥ አልበም የዳዊት ፅጌ “የኔ ዜማ” የተሰኘው ዜማ ነው።
የለዛ ሽልማት የዓመቱ ምርጥ ዘፈን መሰሉ ፋንታሁን “ወይ ልማጣ” አሸናፊ ሆና ሽልማቱን ተቀብላለች። የዓመቱ ምርጥ የሙዚቃ ቪዲዮ የጥላሁን ገሰሰ “ቆሜ ልመርቅሽ” የተሰኘው ስራ ተመራጭ ሆኖ ተሸልሟል። የዓመቱ ምርጥ ነጠላ ዜማ በሮፍናን የተዘፈነው (ሶስት) የተሰኘው ዜማ ተሸላሚ ሆኗል። በሌላ ዘርፍ የዓመቱ ምርጥ አዲስ ድምጻዊ ዳዊት ፅጌ በመሆን ሲመረጥ፤ የዚህ ዘርፍ ስያሜም በእውቁ የሙዚቃ ባለሙያው ኤልያስ መልካ ተሰይሟል። የሽልማት ስያሜውም “የኤልያስ መልካ ሽልማት” እንደሚሰኝ ተገልጿል።
በህይወት ዘመን ተሸላሚ በሙዚቃ ኢንዱስትሪው የላቀ አስተዋፅኦ ያበረከተው የሙዚቃ ባለሙያው ሰላም ስዩም በመሆን ተሸላሚ ሆኗል። ሽልማቱም እውቁ ድምፃዊ ማህሙድ አህመድ መድረክ ላይ በመገኘት ለተሸላሚው አበርክቷል። የዓመቱን ምርጥ የተሰኙ የሙዚቃና የፊልም ባለሙያዎችን ያሸለመው ለዛ አዋርድ ከተሸላሚዎች ጋር በተያያዘ የተለያዩ አስተያየቶችን ማስተናገዱም አልቀረም።
ስለ ሽልማቱ ምን ተባለ?
ባለፈው ዓመት በኮሮና ምክንያት ሳይካሄድ አልፎ ዘንድሮ የሁለቱን ዓመታት ምርጥ የፊልምና ሙዚቃ ስራዎች ብሎ የሸለመው ለዛ ሽልማት በሽልማቱ የተደሰቱትን ያህል ሽልማቱ ከሚገባው አካል ይልቅ የማይገባው ተሰቶበታል የሚል አስተያትም አስተናግዷል። በተለይ የዓመቱ ምርጥ አልበምና የዓመቱ ምርጥ ተዋንያን ዘርፍ የተባሉት በአስተያየት ሰጪዎች የበዛ አስተያየት የተሰጠባቸው ነበሩ።
በእርግጥ መሰል በሆኑ የሽልማት ሂደቶች ውስጥ ከተሸላሚዎች ጋር በተያያዘ የሚሰጡ ሽልማቶች ተገቢነት ላይ የተቃረኑ አስተያየቶች ከህዝብ መቅረቡ የተለመደ ነው። ለዚህ ዋንኛ ምክንያት ደግሞ ተብሎ በባለሙያዎች በተደጋጋሚ የሚነገረው በሸላሚዎቹ የሚወጡ የመምረጫ መስፈርቶች ብዙውን ጊዜ ለታዳሚው አልያም ለህዝብ ይፋ ባለመደረጉ እንደሆነ ይገለፃል። በመሆኑም በጥበብ ዘርፍ የሚሰጡ ሽልማቶች በሙያተኛውና ህዝብ ዘንድ ብዙ የተጣረሱ አስተያየቶች ሲሰጥባቸው ይታያል።
መሰል አስተያየቶችን ማስቆም ባይቻል እንኳን መቀነስ ያስችል ዘንድ የኪነ ጥበብ ባለሙያው በሰራው ልክ ተሸልሞ በልፋቱና በድካሙ ልክ ማበረታቻ ያገኝ ዘንድ በተለያየ መልኩ መሰል የጥበብ ስራ የሚሰሩ ተቋማት የመምረጫ መስፈርታቸው ለህዝብ ግልፅና የማያሻማ አድርገው ማቅረብ ይጠበቅባቸዋል።
በእግጥ በእኛ አገር በጀማሪዎቹ የጥበብ ስራ ሸላሚዎች ብቻ ሳይሆን ከኪነጥበብ ዘርፍ ሽልማትና የተለያዩ ማበረታቻዎች ለኪነጥበብ ባለሙያዎቻቸው የሚሰጡ ዓለምአቀፍ ተቋማትም ቢሆን ከተሸላሚው ማንነትና ብቃት ጋር ተያይዞ ከሚነሳባቸው የአመራረጥ ሂደት ጋር በተያያዘ ብዙ ተቃርኖ ይነሳባቸዋል። ነገር ግን ይሄ አልፎ አልፎ የሚገጥም ጉዳይ እንጂ እንደኛው በአሰራር ግልፅነት ምክንያት በየጊዜው ሽልማት ሲካሄድ የሚነሳ አይደለም።
በለዛ የሽልማት መርሀ ግብር ላይ ብቻ ሳይሆን በሌሎች መሰል የሽልማት መድረኮች ላይም “በምርጫው ሂደቱ ላይ ሊጠራ ይገባል፤ አመራረጡም ልክ አይደለም።” የሚል አስተያቶች ከተለያዩ አካላት አሉታዊ አስተያየት ይሰጣሉ። ይህንን ለማረምና የአሰራር ግልፅነት ለማስፈን ሸላሚ አካላት ጥረት ማድረግ የሚጠበቅባቸው ሲሆን ሸላሚ ተቋማቱ የኪነጥበብ ባለሙያው ለመሸለም እንዲሁም በሙያው ላይ ያሉትን ለማበረታታት በግል እየሰሩት ያለው ጠንካራ ስራ ግን ይበል የሚያሰኝ በመሆኑ ለሽልማቱ አዘጋጆች ከፍ ያለ ምስጋና ሊሰጥም ይገባል።
የኪነ ጥበብ እድገት ማህበረሰባዊ ለውጥን ያፋጥናል። በኪነጥበብ ማስተማር በኪነጥበብ መግራትና ሁለንተናው የአመለካከት ለውጥ ማምጣት ይቻላል። ለማህበረሰባዊ ትስስርና ግንኙነት መጥበቅ ለማህበረሰብ ንቃትና መልከ ብዙ ለውጥ መሰረት የሆነው ጥበብ ዕድገት በቁርጠኝነት መስራት የሚያስልገውም ለዚህ ነው። አበቃን ቸር ይግጠመን።
ተገኝ ብሩ
አዲስ ዘመን ግንቦት 25/2014