በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ እየናረ የመጣውን ዋጋ ለማረጋጋት መንግሥት የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ ነው፤ እንዲያም ሆኖ ግን ችግሩ ቀጥሏል። ይህ ልጓም ያልተገኘለት የኑሮ ውድነት በአገር ውስጥ ብቻ የተከሰተ አይደለም፤ በተለይ በአሁኑ ወቅት በመላው ዓለም እየተስተዋለ ስለመሆኑ መረጃዎች ያሳያሉ።
ኢትዮጵያ ውስጥ ህገወጥ ግብይት እየፈጠረ ያለው ችግር አንዳለ ሆኖ በአገሪቱ ከተከሰቱት የጸጥታና የመሳሰሉት ችግሮች ጋር በተያያዘ የኑሮ ውድነቱ እየጨመረ ይገኛል፤ ለእዚህ የኑሮ ውድነት ምክንያቱ አገራዊ ብቻ አይደለም። በአለም አቀፍ ደረጃ በሸቀጦች፣ በግብርና ምርቶች፣ ሎጂስቲክና ነዳጅ ላይ እየታየው ያለው ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪም ችግሩ ይበልጥ እንዲባባስ እያረገው ነው።
መንግስት ይህን የኑሮ ውድነት እያስከተለ ያለውን ጫና ለመቀነስ የተለያዩ እርምጃዎችን ሲወስድ ቆይቷል፤ እየወሰደም ይገኛል። እየተወሰዱ ካሉ እርምጃዎች መካከል ጤናማ የግብይት ሥርዓትን በማስፈን አምራችና ሸማቹን በቀጥታ ለማገናኘት የሚደረገው ጥረት አንዱ ነው።
ለዚህም ትልቅ ድርሻ እንዳላቸው የታመነባቸውን የህብረት ሥራ ማህበራትን ማጠናከርና የተለያዩ ድጋፎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ በማድረግ መንግስት መሰረታዊ ሸቀጦችን፣ የግብርና ምርቶችን ለህብረተሰቡ ተደራሽ ማድረግን ዋነው ጉዳይ አርጎ እየሰራ ነው፤ በተለይም በከተሞች የሚስተዋለውን የምርት አቅርቦት እጥረትና ህገወጥ ግብይት የወለደውን የግብይት ሰንሰለት መረዘምን ተከትሎ በሸቀጦች ዋጋ ላይ እየታየ ያለውን ንረት ለማረጋጋት ማህበራቱ ከመቼውም ጊዜ በተለየ በአሁኑ ወቅት የጎላ እንቅስቃሴ እያደረጉ ይገኛሉ።
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኅብረት ሥራ ኤጀንሲ አዘጋጅነት ለመጀመሪያ ጊዜ “ኀብረት ሥራ ለሰላምና ለተረጋጋ የገበያ ሥርዓት!” በሚል መሪ ቃል ሰሞኑን ለአራት ተከታታይ ቀናት የተካሄደው ከተማ አቀፍ የኀብረት ሥራ ኤግዚቢሽን፣ ባዛርና ሲምፖዚየምም ይህንኑ ችግር መፍታትን ያለመ አንዱ መድረክ ነው።
መንግሥት ገበያን በማረጋጋት ኢኮኖሚውን ለመደገፍ እየወሰዳቸው ከሚገኙ እርምጃዎች መካከል በአዲስ አበባ ከተማ የምርት አቅርቦትን ለማሻሻል እና ተገቢ ያልሆነ ዋጋ ጭማሪ እንዳይኖር ብሎም በንግድ ስርዓት ውስጥ ተንሰራፍቶ የቆየውን የደላላ ሰንሰለትን ማቋረጥ ትልቁ ሥራ ነው። ለዚህም በአገሪቱ የሚገኙ የኅብረት ሥራ ማኅበራት ገንቢ ሚና እየተጫወቱ እንደሆነ ይታመናል።
በአዲስ አበባ ኤግዚብሽን ማዕከል ከግንቦት 18 እስከ 21 ቀን 2014 ዓ.ም በተካሄደው ኤግዚቢሽንና ባዛር ያገኘናቸው ሸማቾችም መሰል ኤግዚቢሽንና ባዛሮች መዘጋጀታቸው ገበያውን ለማረጋጋት የሚኖራቸው ሚና የጎላ መሆኑን ይናገራሉ።
የጉለሌ ክፍለ ከተማ አዲሱ ገበያ ነዋሪው አቶ ዳዊት አስፋው በኤግዚብሽን ማዕከሉ ተገኝተው ግብይት ፈጽመዋል። አቶ ዳዊት ኤግዚብሽንና ባዛርን ጨምሮ በተለይ የኅብረት ሥራ ማህበራት ያሉበት ቦታ የተሻለ የገበያ ሁኔታ ስለመኖሩ ይናገራሉ። በዚህ ገበያ የሚቀርቡ ሁሉም ምርቶች ውጭ ካለው የገበያ ዋጋ እጅጉን የተሻለ ዋጋ እንዳላቸው ይገልጸሉ።
ማር እየሸመቱ ያገኘናቸው አቶ ዳዊት ከአምስት ወራት በፊት በዚሁ ቦታ የከፋ ቦንጋ ማር መግዛታቸውን ያስታውሳሉ። ማሩ ንጹህ እና ዋጋውም ተመጣጣኝ ስለመሆኑ ይናገራሉ። እንዲህ ባሉ ገበያዎች ጥራት ያለውና ትኩስ ምርት ከማግኘት ባለፈ በተመጣጣኝ ዋጋ መሸመት ይቻላል ነው የሚሉት።
አቶ ዳዊት በዕለቱም አንድ ኪሎ የቦንጋ ነጭ ማር በ260 ብር እና አምስት ኪሎ የበቆሎ ዱቄት በ140 ብር ከሃምሳ ሳንቲም ገዝተዋል፤ ይህም ውጭ ካለው ዋጋ ጋር ሲነጻጸር ሰፊ ልዩነት እንዳለው አንስተው ሌሎች ምርቶችንም ለመሸመት ዝግጁ እንደሆኑ አጫውተውናል።
የኑሮ ውድነቱን በማረጋጋት በኩል የኅብረት ሥራ ማህበራት ትልቅ ድርሻ አላቸው የሚሉት አቶ ዳዊት፣ ማህበራቱ ከዚህ በበለጠ አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ በሚፈለገው መጠን ድጋፍና እገዛ ሊደረግላቸው ይገባል ሲሉም ያስገነዝባሉ። ‹‹እንዲያውም ዘርፉ ሕብረተሰቡ በሚፈለገው መጠን አልተሠራበትም፤ ሊሠራበት ይገባልም›› ብለዋል።
ማህበረሰቡም ማኅበራቱ ባሉበት ቦታ ሁሉ በመሄድ መግዛት ከቻለ የማኅበራቱን አቅም ማጎልበት ያስችላል። አገልግሎታቸውንም በስፋት ለማቅረብ ያስችላቸዋል። መንግሥትም እነሱን በማጠናከርና በመደገፍ ለህበረተሰቡ ተደራሽ እንዲሆኑ መሥራት አለበት። በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ቀደም ሲል የተጀመረው የእሁድ ገበያ አንዱ አማራጭ እንደመሆኑ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል።
በቋሚነት ከዘለቀው የእሁድ ገበያ በተጨማሪ በተለያየ ጊዜ የሚዘጋጀው ባዛርና ኤግዚቢሽንም እንዲሁ ብዙ ሳይቆይ በአንድ ወር አልያም በሁለት ወራት ቢከፈት ገበያውን ማረጋጋት ያስችላል ያሉት አቶ ዳዊት፤ የኅብረት ሥራ ማህበራት ገበያዎች አሉ ከተባለ የትም ይሁን የት ይሄዳሉ። ባይገዙም ቦታው ድረስ በመሄድ ሁኔታውን መመልከት ያስደስታቸዋል፤ ይህ በራሱ ጥሩ ነገር እንደሆነ በመግለጽ ሌሎችም ይህን ቢያደርጉ ይጠቀማሉ ይላሉ።
የአቶ ዳዊትን ሀሳብ የሚጋሩት ወይዘሮ ሀና ማሙዬ በበኩላቸው የህብረት ሥራ ማህበራቱ የተለያዩ ምርቶችን ይዘው በአንድ ቦታ ላይ መገኘታቸው በራሱ ጥሩ እንደሆነ በመግለጽ ገበያውንም ማረጋጋት እንደሚችሉ ይናገራሉ። ምንም እንኳን እርሳቸው ለኤግዚብሽን ማዕከሉ ቅርብ ከሆነው መሿለኪያ የመጡ ቢሆንም ሩቅ ያሉትም ቢሆኑ ተመሳሳይነት ካለው የእሁድ ገበያ መጠቀም እንደሚችሉ ይጠቁማሉ።
በወቅቱ አንድ ኪሎ ኮረሪማ በ100 ብር ሲገዙ ያገኘናቸው ወይዘሮ ሀና፤ በተለይም የጤፍ ዋጋ ውጭ ካለው የተሻለ እንደሆነ ነው የሚናገሩት። ውጭ ላይ በኪሎ ከ50 ብር እስከ 54 ብር የሚሸጠው ጤፍ ከ44 እስከ 46 ብር እየተሸጠ መሆኑን ገልጸዋል።
በዘይት ዋጋ ላይ ብዙ ልዩነት እንደሌለም ተናግረው፣ ገበያው ላይ መገኘቱ በራሱ ትልቅ ነገር ነው ይላሉ። ውጭ ላይ ከአንድ ሺ ብር በላይ የሚሸጠው ከውጭ የሚገባ ዘይት አለ። ነገር ግን በአገር ውስጥ የሚመረተው ኮከብ የሚባል የኑግ ዘይት በ870 ብር መግዛታቸውን ይናገራሉ፤ መንግሥት ይህን አማራጭ ማቅረቡ መልካም እንደሆነ ገልጸው፤ ‹‹የሆነ ሆኖ ዋናው ጤፍ ነው እሱ ብቻ አይጥፋብን ሌላው ትርፍ ነው›› ይላሉ።
በኤግዚብሽን ማዕከሉ እርሳቸው ያሉት ጤፍም ይሁን ነጩ፣ ከቀዩ፤ መካከለኛው ከሠርገኛው በዓይነት በዓይነቱ ገበያው ላይ ቀርቧል፤ አጠቃላይ የግብርናና የኢንዱስትሪ ምርቶችን እንዲሁም የእጅ ሥራ የሆኑ የሸክላ ውጤቶችም ለገበያ ቀርበዋል። በግቢው ውስጥ ለአይን የሚማርኩ ትኩስ አትክልትና ፍራፍሬዎችን ጨምሮ ጥራጥሬዎችም እንዲሁ በገበያው በስፋት ይታያሉ።
የኢንዱስትሪ ውጤቶች ከሆኑት መካከልም የንጽህና አገልግሎት መስጫ የሆኑ ደረቅና ፈሳሽ ሳሙናዎች በተመጣጣኝ ዋጋ መቅረባቸውን ተመልክተናል። ለአብነትም ውጭ ላይ ከ300 ብር በላይ የሚሸጠው አምስት ሊትር የልብስ ሳሙና ከ200 እስከ 250 ብር ሲሸጥ ደረቅ ሳሙና ደግሞ ከ26 ብር ጀምሮ ሲሸጥ ነበር።
ከደቡብ ምዕራብ ከፋ ዞን ከከፋ ጫካ ማር ዩኒየን የመጡት የቦርድ ሰብሳቢ አቶ በዛብህ በቀለ ማርና ኮረሪማ ይዘው ቀርበዋል። ዩኒየኑ 34 ማህበራት ያሉትና ዘጠኝ ሺ አርሶ አደሮችን ያቀፈ መሆኑን በመግለጽ ዩኒየኑ ማርና ኮረሪማን በስፋት እያመረተ ከአገር ውስጥ ባለፈ ለውጭ ገበያም ማቅረብ እንደቻለ ይናገራሉ።
በ2013 ዓ.ም ማር ወደ ጀርመን ልኳል፤ በአሁኑ ወቅት ግን በአገር ውስጥ ማር በከፍተኛ መጠን እየተፈለገ መሆኑን ጠቅሰው፣ ማሩን ለአገር ውስጥ ገበያ ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ይገልጸሉ። ይሁንና በተለይም አዲስ አበባ ከተማን ጨምሮ በተለያዩ የክልል ከተሞች በስፋት ተደራሽ ለማድረግ የገበያ ቦታ ችግር መሆኑን አቶ በዛብህ ጠቅሰዋል።
ለአራት ቀናት ያለምንም ክፍያ በኤግዚብሽን ማዕከሉ ምርቶቻቸውን ለገበያ ማቅረብ እንዲችሉ መደረጉ አስፈላጊና ጠቃሚ መሆኑን በመግለጽ፤ ከሽያጩ ባለፈ የገበያ ትስስር ለመፍጠር ጥሩ አጋጣሚ እንደፈጠረላቸውም ይናገራሉ። ከዚህ ቀደምም ባገኙት ዕድል በቀጥታ ሸማቹን ከማግኘት ባለፈ ሰፊ የገበያ ትስስር መፍጠር መቻላቸውን ይናገራሉ።
የአካባቢውንና የወቅቱን ገበያ በማየት ቦርዱ በወሰነላቸው መሠረት አንድ ኪሎ ማር 260 ብር እንዲሁም አንድ ኪሎ ኮረሪማ በ100 ብር እየሸጡ መሆኑን የገለጹት አቶ በዛብህ፤ በዚህም ሸማቾች ተጠቃሚ እንደሚሆኑና ገበያውንም ማረጋጋት እንደሚቻል ይጠቅሳሉ። በባዛሩ ላይም አስር ኩንታል ማር እና ሶስት ኩንታል ኮረሪማ ይዘው ቀርበዋል።
ለገበያው ይዘው ከቀረቡት የምርት መጠን በላይ በባዛር ገበያው ኮረሪማ ወደ ውጭ ገበያ የሚያቀርብ ላኪ ያገኙ ሲሆን 10 ኩንታል የተፈለፈለ ኮረሪማ እንዲቀርብለት በጠየቀው መሰረት ለማቅረብ በዋጋ፣ በጥራትና በጊዜ ተስማምተው ውል አስረዋል። ለዚህም የቅድመ ዝግጅት ሥራውን ከወዲሁ መጀመራቸውን እና እንዲህ አይነት መድረኮች በተለይም የገበያ ትስስር ለመፍጠር ከፍተኛ ጠቀሜታ አላቸው ብለዋል።
የይርጋጨፌ ገበሬዎች የኅብረት ሥራ ማህበር የተቆላ ቡና ክፍል ኃላፊ አቶ አሻግሬ አድማሱ በበኩላቸው በባዛሩ ላይ የተቆላ ቡና በተመጣጣኝ ዋጋ ለሸማቾች ይዘው መቅረባቸውን ገልጸዋል። በመሆኑም በኤክስፖርት ደረጃ ተቆልቶ የተፈጨ አንድ ኪሎ ቡና 460 ብር ይዘው ቀርበዋል። ይህም ውጭ ላይ ከ570 ብር በላይ የሚሸጥ ነው።
የቡና ልማቱ በይርጋጨፌ ከሚገኙ አርሶ አደር አባላት የሚገኝ እንደሆነ የገለጹት አቶ አሻግሬ፤ በልማቱ ላይ ብቻ ከ40 ሺ በላይ አርሶ አደሮችን ያቀፈ ማኅበር መሆኑን ጠቅሰዋል። ከአርሶ አደሩ የተቀበሉትን ቡናም ቃሊቲ ማሰልጠኛ አካባቢ በሚገኘው ማቀነባበሪያ ፋብሪካ ቆልተው፣ ፈጭተውና አሽገው ለገበያ ያቀርባሉ። ይሄው ቡና ሂልተን ሆቴልን ጨምሮ በተለያዩ ሆቴሎችና ሱፐርማርኬቶችና ሆቴሎች ላይ ይገኛል።
በቋሚነት ካለው ገበያ በተጨማሪ በእንዲህ አይነት የባዛር ገበያ ላይ መሳተፍ መቻላቸው ሰፊ የገበያ ዕድል የሚፈጥርላቸው መሆኑን አቶ አሻግሬ ይገልጻሉ። ይህ ብቻ አይደለም፤ በቀጥታ ሸማቹን ማግኘት የሚቻልበት መሆኑን ይናገራሉ። በተለይም በአሁኑ ወቅት ካላው የኑሮ ውድነት አንጻር ለውጭ ገበያ ከሚያቀርቡበት ዋጋ ባነሰ እያቀረቡ መሆናቸውንም ገልጸው፣ ይህም ኅብረተሰቡን ለመጥቀም እንዲሁም ቡናውን ለማስተዋወቅ ጭምር ትልቅ ዕድል የሚፈጥር ነው ብለዋል።
‹‹የኅብረት ሥራ ማህበራት ችግር ፈቺና መፍትሔ መሆን የሚችሉ ናቸው፤ ለዚህም በጋራ መሥራትና ማበር ያስፈልጋል›› ያሉት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳዳር ኅብረት ሥራ ኤጀንሲ ኃላፊ አቶ ግዛቸው ዓሊ፤ ሰው ሰራሽ የሆነውን የኑሮ ውድነት ለማርገብና የተረጋጋ ገበያ ለማስፈን ታልሞ የተዘጋጀ ኤግዚብሽንና ባዛር መሆኑን ተናግረዋል።
እንደ ሃላፊው ገለጻ፤ ከአቅርቦት ጋር ያለውን ችግር ለመቅረፍም ከአርሶ አደሩ ጋር በመቀናጀት ሰፋ ያለ ውይይት በማድረግ ችግሩን መለየት ተችሏል። ለዚህም የኅብረት ሥራ ማህበራት ለተረጋጋ ገበያ መፍትሔ እንዲሆኑ እየተሠራ ነው። ከእሁድ ገበያ ባሻገር እንዲህ አይነት መድረክ ያለውን ፋይዳ በመረዳትም ከተማ አስተዳደሩ ለኅብረት ሥራ ኤጀንሲው አንድ ቢሊዮን ብር መድቧል።
በመሆኑም ጤፍና የስንዴ ዱቄትን ጨምሮ የተለያዩ ምርቶች በባዛሩ በስፋት መግባታቸውን የገለጹት አቶ ግዛቸው፤ ምርቱን ከስር ከስር እየተተካ እንደሆነና ቀጣዩን ክረምትም ሊያዘልቅ እንደሚችል ነው ያነሱት። አትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም ሌሎች ምርቶችን ደግሞ ከክልል አርሶ አደሮች ጋር በመነጋጋር ለማቅረብ አተየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።
በኤግዚብሽንና ባዛሩ ላይ ከከተማዋ ውጭ ከስድስት ክልሎች የመጡና በተለያየ የኅብረት ሥራ ማህበራት ዘርፎች የተደራጁ እንዲሁም ከኅብረት ሥራ ዘርፍ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያላቸው ተቋማት ተገኝተዋል። በማህበራቱ መካከልም የእርስ በእርስ የልምድ ልውውጥ ማድረግ፣ የገንዘብ ብድር ቁጠባና የኅብረት ሥራ ግንዛቤ እጥረቶችን መቅረፍ፣ ዘላቂነት ያለውን የገበያ ትስስርና መስተጋብር ለመፍጠር እንዲሁም የማኅበራቱን ገጽታ የመገንባት ዓላማ ያለው መሆኑ ተጠቁሟል።
በአራት ቀናትም 178 የኅብረት ሥራ ማህበራትና የተለያዩ ተቋማት እንዲሳተፉ በማድረግ ከ456 ዓይነት በላይ የምርት አይነቶችን በማቅረብ የኅብረት ሥራ ማህበራት ምርትና አገልግሎትን በማስተዋወቅ ከ4 ሺ 656 ኩንታል በላይ የግብርናና የኢንዱስትሪ ምርቶች እንዲሁም የዕደ ጥበብ ውጤቶች በተመጣጣኝ ዋጋ ሽያጭ ማከናወን እንደተቻለና በዚህም 27 ሚሊዮን 912 ሺ 755 ብር እንደተገኘ በመዝጊያ ስነስርዓቱ ላይ የወጡ መረጃዎች ያመለክታሉ።
ሰሞኑን በአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማእከል ለአራት ቀናት በተካሄደው ኤግዚቢሽን 178 የኅብረት ሥራ ማህበራትና የተለያዩ ተቋማት ተሳትፈዋል፤ ከ456 ዓይነት በላይ የምርት አይነቶችም ቀርበዋል። የኅብረት ሥራ ማህበራት ምርትና አገልግሎትን በማስተዋወቅ ከ4 ሺ656 ኩንታል በላይ የግብርናና የኢንዱስትሪ ምርቶች እንዲሁም የዕደ ጥበብ ውጤቶች በተመጣጣኝ ዋጋ ሽያጭ ማከናወን ችለዋል፤ በዚህም 27 ሚሊዮን 912 ሺ 755 ብር መገኘቱን በመዝጊያ ስነስርዓቱ ላይ የወጡ መረጃዎች ያመለክታሉ።
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ግንቦት 24/2014