ይህ ጸሐፊ ከማኅበራዊ ሚዲያ ቱማታ ይልቅ ስሜቱንና ሃሳቡን ሰብስቦ በመጻሕፍት ውስጥ ራሱን ቢሸሽግ ይመርጣል። የስሜትን ወጀብ ጸጥ አድርጎ በተረጋጋ መንፈስ እውቀትን ለመገብየት መጻሕፍት በእጅጉ ተመራጭ ናቸው። ዘመነ ቴክኖሎጂ ግን ሕዝበ አዳምን ከመጻሕፍት ለማፋታት አጠንክሮ በመስራት በልዩ ልዩ አዳዲስ ግኝቶች የማማለሉን ዘመቻ አጧጡፎ የተያያዘው ይመስላል።
ምንም እንኳን ዘመኑ ለሳይንስና ቴክኖሎጂ “እንድንሰግድ” ጫናውና ጠቀሜታው ቀላል ባይሆንም ከመጻሕፍት ንባብ ጋር ፍቺ ፈጽመን እንኑር ማለቱ ግን አግባብም፣ አዋጭም፣ ተገቢም አይደለም። ሰሞኑን እያነበብኩት ብቻም ሳይሆን እያብላላሁት ጭምር ያለው “Die Empty” በሚል ርእስ Todd Henry የተባሉ ደራሲ የጻፉትን ድንቅና ተወዳጅ መጽሐፍ ነው። ምናልባትም በቅርብ ጊዜያት ካነበብኳቸው መጻሕፍት መካከል ይኼኛው በግንባር ቀደምትነት በአንቱታ ያከበርኩት መሆኑን ለአንባቢያን መመስከር እወዳለሁ። እንዲያነቡትም አደፋፍራለሁ።
የመጽሐፉን ርእስ ለዚህ ጽሑፌ ተውሼ ወደ ቋንቋችን ለመመለስ የሳምንታት ትግል ቢፈጅብኝም አልተሳካልኝም። ቃል በቃል በመተርጎም “ባዶ እንደሆንን እንሙት”፤ አይሉት ነገር ትርጉሙ ሌጣና መላ ቢስ ብቻ ሳይሆን ወደ ሌላ ይዘት ጭምር ስለሚያጋድል የሚሞከር አልሆነም። “አውርሰን እንሙት” ለማለት ሞክሬም የቋንቋችን ዐውድ አልፈቅድ ቢለኝና ትርጉም አልባ ቢሆንብኝ እርግፍ አድርጌ ተውኩት። ለማንኛውም ከብዙ ሙከራዎች መካከል ምርጫው አሸንፎ ሳይሆን፤ ይሻላል ያልኩት ተዛማጅ ትርጉም ከላይ በርእስነት የተጠቀምኩበትን ሀረግ ነው – “አሸጋግረን እንለፍ” የሚለውን።
ደራሲው በመጽሐፋቸው ውስጥ ለማስተላለፍ የፈለጉት ዋነኛው ጭብጥ በአንድ ዐረፍተ ነገር ይቅረብ ከተባለ፤ “ነገ ማለፍህ ስለማይቀር፤ የተሰጠህን ችሎታ፣ ፀጋና መክሊት ለተከታዩ ትውልድና ለሀገርህ ሳታሸጋግር የሰነፍ ሰው ሞት እንዳትሞት ተጠንቀቅ” የሚል መልእክትን ነው። ይህንን አንኳር ሃሳብ በብዙ ምሳሌዎችና ማሳያዎች ለመዘርዘር የሞከሩት የተዋጣላቸው በርካታ አሳማኝ ትንታኔዎችን በመጠቀም ነው።
እኔም ከዚህ መጽሐፍ ያገኘሁትን እውቀት ለአንባቢዎቼ ለማጋራት ልቤ የተነሳሳው የአገራችን ወቅታዊና አሳሳቢ ሁኔታዎች በንባቤ መሃል ፍንትው ብለው እየታዩኝ ንባቤን እስከማሰናከል ድረስ ደርሰው እንደነበርም ሳልሸሽግ አላልፍም። ስለዚህም ሙሉውን የመጽሐፉን ሃሳብ ሳይሆን ቁራሹንም ቢሆን ማጋራቱ ይበጅ ስለመሰለኝ እነሆ የንባቤን ማዕድ እንድትጋሩልኝ ይድረስ ብያለሁ።
እንቀጥል…
በቅዱስ መጽሐፍ ውስጥ፤ “መጽሐፍ መክብብ” በሚል ርዕስ የሚታወቅ አንድ ድንቅ መጽሐፍ አለ። “የጥበብ ማዕድን” የሚባሉ እውቀቶችን አምቆ በመያዙ ተወዳጅና ተጠቃሽ ከሆነው ከዚህ መጽሐፍ ውስጥ ጥቂት ስንኞችን በመዋስ እንደ መደላድል ልጠቀምበት። እንዲህ ይነበባል፤ “ከመልካም ሽቱ ይልቅ መልካም ስም ይሻላል። ወደ ግብዣ ቤት ከመሄድ ይልቅ ወደ ልቅሶ ቤት መሄድ ይሻላል፤ እርሱ የሰው ሁሉ ፍጻሜ ነውና፤ ሕያውም የሆነ በልቡ ያኖረዋልና” (ምዕራፍ 7፡1-2)።
የዚህ ጥቅስ መልእክት ባጭሩ “ሞት የሚባል አይቀሬ እዳ እንዳለ አስብ። የደስታህ ውሎ የሞትህን እውነታነት አይጋርደው። ተግባርህ የስምህ ሽቱ ሆኖ በሕያውነት እንዲጠቀስልህ ከፈለግህ ዛሬን በጎ በማድረግ አስተናግደው” የሚል ነው። ከሞት ጋር ሕይወት መታሰቡ፣ ከህልፈት ጋርም የመኖር ጉጉት መጎዳኘቱ የማይቀር እውነታ መሆኑ እንዳይዘነጋ በማስታወስ ጭምር። ከላይ በመንደርደሪያችን ላይ የተጠቀሰው የሚስተር ሄኒሪ መጽሐፍ በዋነኛነት የሚሞግተንም “ሞት በቀጠሮ የማይመጣ ከሆነ ስለምን ለአገርና ለትውልድ በጎ ከማድረግ እንዘናጋለን? ስለምንስ ለመተንበይ ካልሆነ በስተቀር ለመኖር ዋስትና በማይሆነን ነገ በሚሉት ተስፋ እየተታለልን እንሞኛለን። ለምንስ ጠቃሚና በጎ የሆነውን መክሊታችንን ታቅፈን እንቀበራለን” የሚል ግዙፍ ሃሳብን ነው::
ጸሐፊው፤ “ያንተ ቀን ዛሬ ነው። ዛሬ ማድረግ የሚገባህን ለነገ አታሳድር። ለነገ ማሳደር ብቻም ሳይሆን ንፍገትንም አትለማመድ። አንተ ራስህ የብዙዎች ውጤት መሆንህንም አትዘንጋ። በአእምሮህ የተከማቸው እውቀት፣ በእጅህ ላይ የተጠራቀመው መክሊት በብዙዎች ተሳትፎ የተገኘ እንጂ የአንተ ብቻ ጥሪት አይደለም። አንኳን ለነገ አሳድሬያለሁ እያልክ የምተመካበትን ሃብትና እውቀት ቀርቶ እየኖርክባት ያለችው ጀንበር ራሷ የአንተ አይደለችም። ጉዞዋን ጨርሳ በነገ ሌላ ጀንበር ትተካለች። ስለዚህም ነገ የምትለው የተስፋ ዕለት ምን ይዞ እንደሚመጣ ስለማታውቅ አትዘናጋ” እያለ በብርቱ ሃሳቦች ይሞግተናል።
ሙግቱ የሚያፈናፍን አይደለም። የጥበብ ተሰጥኦ ካለህ አቅምህን አሟጠህ በዛሬዋ ጀንበር ለሕዝብህ አስተላልፍ። ሃብት ካለህ ያለ ስስት ዛሬ የምትሞቃት ጸሐይ ሳትዳምን ለትውልድ የሚተላለፍ ፍሬ አፍራበት። የአንተ እውቀት በሚያስፈልግበት ቦታ ንፍገት አሸንፎህ በአእምሮህ ጓዳ ካዝና ውስጥ የተከማቸውን ጥብብ ቆልፈህበት ለነገ አታሸጋግረው። ነገ ያንተ ስለመሆኑ በምን እርግጠኛ ሆነህ ለለጋስነት ትዘገያለህ?” እያለም የራሳችን ከምንለው እምነት ጋር ያፋልመናል።
የመሟገቻዎቹ ሃሳቦች እጅግ በርካቶች ስለሆኑ ለማሳያነት የቆነጠርኩት ጥቂቶቹን ብቻ ነው። አጠቃላይ መንደርደሪያዬን እዚህ ላይ ገታ አድርጌ በራሴ የግል አመለካከት የራሴን አገር እውነታ ወደ መፈተሽ ልሸጋገር።
ኢትዮጵያ ሆይ!
የአገሬን ወቅታዊ ችግሮች በስፋትና በወርዳቸው ልክ ዘርግቼ በማሕበራዊ የሂስ ጥበብ ለመፈተሽ ስሞክር ሁሌም የማርፍበት ዋነኛው ማጠንጠኛ አንድ ጉዳይ ነው – “እኔ ብቻ የሚል ግለኝነት።” ለኢትዮጵያ ፖለቲካ ህመም መድኃኒቱ ያለው እኔ ዘንድ ብቻ ነው። የአገሪቱ ኢኮኖሚ መፍትሔው የሚቀመረው በእኔ የአእምሮ ማሽን ውስጥ ብቻ ነው። የማሕበራዊ ችግሮቻችን የሙቀትና የቅዝቃዜ መለኪያ ቴርሞ ሜትሩ የተያዘው በእኔ እጆች ብቻ ነው። የዕውቀትና የጥበብ ምሥጢራትን ቁልፍ በአደራ የተረከብኩት እኔ ብቻ ነኝ ወዘተ. የሚለው “የራስ ብቻ” የብቃት መፍትሔ ከአሁን ቀደምም ሆነ ዛሬ ምን ያህል የመከራ ዋጋ እያስከፈለን እንዳለ ያየነውና የምናየው እውነታ ነው። “እኔ ብቻ” እያሉ ራሳቸውን አሰላፊና ተሰላፊ ባደረጉ “የራስ ጣኦቶች” አማካይነት እነሆ የምንኖረውን ኑሮ እንድንኖር ተፈርዶብናል፤ ወይንም ፈርደውብናል።
ችግሩ በእኔነት ውስጥ ንፉግነት እንደሚስተዋል ይጠፋናል ማለት ባይቻልም፤ እኔ ብቻ የሚል ሰው “የእኔ ብቻ” የሚለውን በጎ ነገሮች ሁሉ አራግፎ ለመስጠትም እንደማይበረታ የታወቀ ነው። “እኔ” ብሎ መሽቀዳደም ለበጎ ሃሳብ ከሆነና መልካምነትን ለመጋራት መፍጠን ከሆነ እሰየው! ምን ገዶ! ችግሩ ያለው “እኔ ብቻ” ከሆነ የሚመዘዘው መዘዝ ተመጣጣኝ ዋጋ ስለሚጠይቅ ውጤቱ ይበልጥ የከፋ መሆኑ ላይ ነው።
መቼም ይህን መሰሉ ርእሰ ጉዳይ በዋነኛነት ደምቆ የሚሰበከውም ሆነ የሚነገረው አንድም በሃይማኖት ምስባኮች ላይ፣ ሁለትም ሙዚቃን፣ መጻሕፍትን፣ ሥዕልንና ቅርጻ ቅርጽን ወዘተ. አቅፎ በቤተኛነት በያዘው የኪነ ጥበባት ዘውጎች አማካይነት እንደሆነ አልጠፋኝም።
ለፖለቲካውና ለሥልጣን አላሚ ሠፈርተኞች ይህን መሰል መልእክት ከጆሯቸው ቢደርስም ፈጥነው እንደማይቀበሉት ይገባኛል። ስለዚህም የመጽሐፉን ደራሲ መሰል መልእክቶች የተላለፉባቸውን አንድ ሁለት የጥበብ ስራ ማጣቀሻዎችን ላስታውስ።
ተወዳጁ ነፍሰ ሄር ደራሲያችንና መምህራችን ደበበ ሰይፉ “በትን ያሻራህን ዘር” የሚል አንድ ተወዳጅ ግጥም አለው። ይህ አጭር ግጥም አምቆ የያዘው መልእክት እጅግ የገዘፈ ብቻም ሳይሆን የመነሻችንን መልእክትም ለማጉላት ጥሩ ምሳሌ ስለሆነ እነሆ ግጥሙን አስታውሳለሁ።
በጓጥ በስርጓጉጡ፣
በማጥ በድጡ
እንደ ተንጋለልክ – እንደ እንደ ዘመምክ
ትንፋሽህን እንደቋጠርክ
ልል ቀበቶህን እንዳጠበክ
የተልእኮህን አባዜ
የሕይወትህን ቃለ – ኑዛዜ
ወርውር!
የጅህን ዘገር።
በትን!
ያሻራህን ዘር።
ይዘኸው እንዳትቀበር።
ይህ የመምህሬ ግጥም ከላይ ወደ ጠቀስኩት የመክብብ መጽሐፍ እንደገና እንድመለስ ግድ ይለኛል። የመጽሐፈ መክብብ ደራሲ ‹ጠቢቡ ሰለሞን› እንዲህ ይመክረናል። “ይህ ወይንም ያ ማናቸው እንዲበቅል ወይም ሁለቱም መልካም እንዲሆኑ አታውቅምና በማለዳ ዘርህን ዝራ፣ በማታም ጥረትህን አትተው።”
ነፍሰ ሄሩ የሙዚቃ ንጉሥ ጥላሁን ገሠሠም በዚህን መሰሉ ርእሰ ጉዳይ ላይ ብዙ ዜማዎችን እንደተጫወተ እናስታውሳለን።
“ስንት አየሁ ስንት ሰው ያሉ የነበሩ፣
ለመልካም ስራ እንጂ ለራስ የማይኖሩ፣
ከመቃብር በላይ ከታሪክ ኑባሪ፣
ስንት አየሁ ትልቅ ሰው ስንት አየሁ መሠሪ።
ሃሳባችንን ወደመጠቅለሉ እንሂድ። ደራሲው ሄንሪም ሆኑ ሌሎች የጠቀስናቸው ጠቢባን የሚመክሩን አንድና ተመሳሳይ ጉዳይ እንድንከውን ነው። “ነገ! ነገ! እያልን እንዳንሞትና መክሊታችንን እንደተሸከምን እንዳንቀበር።” ዛሬ! አሁን! ለሕዝብና ለአገር በጎነት የሚበጀውን ተሽቀዳድመን እንድናሸጋግር እንጂ ለእምባና ለምሬት በሚዳርጉ ተግባራት ላይ እንዳንረባረብ።” የሁሉም ተማጽኖና የአደራ ቃል ይኼው ነው። ይህ ጸሐፊም ብእሩን ወክሎ በዓመታት ውስጥ ሲቃትት የኖረው ይህንኑ መልእክት ለማስታላለፍ ነው። ሰላም ይሁን!
(ጌታቸው በለጠ /ዳግላስ ጴጥሮስ)
gechoseni@gmail.com
አዲስ ዘመን ግንቦት 24/2014