የለማች ኦሮሚያን ለማየት ምኞት ብቻ ሳይሆን ታክስና ግብርን በአግባቡ በመክፈል ሀላፊነትን መወጣት እንደሚገባ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ለማ መገርሳ ዛሬ በአዳማ ከተማ በተጀመረው የታክስ ንቅናቄ ላይ ተናግረዋል፡፡
ግብርን መክፈል የልማቱን እርምጃ ለማፋጠን ስለሚረዳ ሁሉም ዜጋ ትኩረት ሰጥቶት መስራት እንደሚገባ መስተዳድሩ አሳስበዋል፡፡
በኦሮሚያ ክልል በየአመቱ የሚሰበሰበው ታክስና ግብር እየጨመረ ቢመጣም ክልሉ ከሚያገኘው ገቢ ጋር ሲነፃፀር አነስተኛ እንደሆነ በመግለፅ የክልሉ ማህበረሰብ ትኩረት በመስጠት የሚጠበቅበትን ታክስና ግብር በአግባቡ በመክፈል ክልሉን ወደ ላቀ ልማት ማምጣት አለበት ሲሉ መስተዳድሩ ተናግረዋል፡፡
ይህ ‹‹ግዴታዬን እወጣለሁ መብቴን እጠይቃለው ›› በሚል መሪ ቃል የተጀመረው የታክስ ንቅናቄ እስከ አንድ አመት የሚቆይ ሲሆን በዚህም ከፍተኛ ለውጥ ይገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅ የኦሮሚያ ገቢዎች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ጫልቱ ሳኒ ገልፀዋል፡፡
በ2011 ዓ.ም በተደረገው እንቅስቃሴ በዕቅድ የተያዘው 15.5 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ የታቀደ ሲሆን በእነዚህ 6 ወራት ውስጥ በመደበኛ 15 ቢሊዮን፣በማዘጋጃ ቤት 3.5 ቢሊዮን ብር የተሰበሰበ ሲሆን በአጠቃላይ 108 ፐርሰንት መሰብሰብ መቻሉን ወ/ሮ ጫልቱ ተናግረዋል፡፡
ይህን የታክስ ንቅናቄ ቀልጣፋ ለማድረግ ከአባ ገዳዎች፣ከሀይማኖት አባቶች፣ከአትሌቶች፣ከአርቲስቶችና ከባለሀብቶች የተለያዩ አምባሳደሮች ተመርጠዋል፡፡
በዚህ ለአንድ አመት በሚቆየው የታክስ ንቅናቄ መክፈቻ ፕሮግራም ላይ የተለያዩ የፌዴራልና የክልል ባለስጣናት ተገኝተዋል፡፡
በወይንሸት ካሳ