መንግስት በነዳጅ ላይ ሲደረግ የነበረው ድጎማ ሊነሳ መሆኑን ማስታወቁ ይታወቃል። የነዳጅ መሸጫ ዋጋን ከህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጭዎች ውጪ በአለም ገበያ ዋጋ ነዳጅ ገዝተው እንዲጠቀሙ ማቀዱንም በቅርቡ ይፋ አድርጓል።
መንግስት የነዳጅ ድጎማውን ለማንሳት በምክንያትነት የጠቀሰው ለአገር ውስጥ ፍጆታ የሚሆነውን ነዳጅ ከፍተኛ ድጎማ በማድረግ በከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ የሚገዛ በመሆኑ ነው፤ ከዚህም በተጨማሪ የውጭ ምንዛሬውም ከጊዜ ወደጊዜ እያሻቀበ በመምጣቱም ጭምር ነው። እንዲሁም የኢትዮጵያ የነዳጅ የችርቻሮ መሸጫ ዋጋ አገሪቱ ካሏት ጎረቤት አገሮች አንጻር ሲታይ ዝቅተኛ በመሆኑ ወደኢትዮጵያ የገባ ነዳጅ በኮንትሮባንድ መልክ ወደጎረቤት አገራት እንዲወጣ ሊደረግ መቻሉንም መንግስት በምክንያትነት የሚጠቀስ ስለመሆኑ አስረድቷል። ይህም አካሄድ በአገሪቱ ያለውን የነዳጅ አቅርቦት እጥረት እንዲኖረው ማድረጉንም ነው ያመለከተው።
መረጃዎች እንደሚያሳዩት፤ የአገሪቱ የነዳጅ ዋጋ፣ ካሏት ጎረቤት አገሮች ጋር በንጽጽር ሲታይ በአፍሪካ ከሚገኙ አገራት ውስጥ ነዳጅ በአነስተኛ ዋጋ ከሚሸጥባቸው መካከል ተጠቃሽ ነች። እንዲህም ሲባል ነዳጅ አምራች ከሆኑ አገሮች ቀጥላ የነዳጅ ምርትን ለህዝቧ በአነስተኛ ዋጋ የምታቀርብ አገር ስለመሆኗም ይነገራል።
መንግስት ለነዳጅ ያደርግ የነበረውን ድጎማ ማንሳት ማቀዱ በእርግጥ የሚያስከትላቸው የኢኮኖሚ ተጽዕኖዎች መኖራቸው እውን ነው። ምክንያቱም ነዳጅ በኢኮኖሚ ዘርፉ ውስጥ ያለው ሚና የላቀ ነውና። ይህ ደግሞ ኢኮኖሚያዊ ጫናውን ከፍ እንደሚደርገው ይታመናል።
በዚህ ጉዳይ ሐሳባቸውን እንዲያጋሩን አዲስ ዘመን ያነጋገራቸው የምጣኔ ሀብት ባለሙያው አቶ ዛፉ ኢየሱስወርቅ ዛፉ፣ መንግስት የነዳጅ ድጎማውን ማድረግ የፈለገበት ዋናው ነገር በውጭ ምንዛሬና በነዳጅ ዋጋው መናር የተነሳ በመሆኑ ነው ይላሉ። አንድ አገር በዚህ መልኩ አልቻልኩም ካለ ደግሞ ለችግሩ መፍትሄ መፈለግ አዋጭ እንደሆነ ነው የሚናገሩት።
የምጣኔ ሀብት ባለሙያ፣ መፍትሄ ነው ካሏቸው ጉዳዮች አንዱ በአገሪቱ ቀደም ሲል ተተግብሮ የነበረውን የተሽከርካሪዎች የመጨረሻ ቁጥር ጎዶሎ እና ሙሉ የሆኑትን ተራ በተራ እንዲሽከረከሩ ማድረግ ነው ሲሉ ይናገራሉ። ይህንኑ ጉዳይ ሲያብራሩም፤ እኤአ 1978 እንግሊዞች ቀጥረዋቸው ወደ ናይጄሪያ ወስደዋቸው እንደነበር የጠቀሱት አቶ ዛፉ ኢየሱስወርቅ ዛፉ፣ እዛ ሲደርሱ አንድ ቪላ ቤት፣ አንድ ሹፌር እና ሁለት መኪናዎች እንደተሰጣቸው ይናገራሉ። የመኪናዎች መጨረሻ ቁጥር አንደኛው በሙሉ ቁጥር፣ ሁለተኛው ደግሞ በጎዶሎ ቁጥር የሚያልቁ ናቸው። ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ በወቅቱ በከተማው ረቡዕና አርብ ጎዶሎ ቁጥር፤ ማክሰኞና ሐሙስ ደግሞ ሙሉ ቁጥር የሚሽከረከሩ መሆናቸው ሲሆን፣ በቀሪዎቹ ቀናት ግን ጎዶሎውንም ሙሉውንም ቁጥር ማሽከርከር ስለሚቻል መሆኑን ነው የተናገሩት።
እርሳቸው እንዳሉት በእኛም አገር መጨረሻቸው ጎዶሎ እና ሙሉ ቁጥር የሆኑ ተሽከርካሪዎች በየተራ እንዲነዱ ቢደረግ አንድ አማራጭ ነው። ቀደም ሲል ሲደረግ የነበረው ተሞክሮ ሊመጣ ይችላል ብዬ አስባለሁ። በአገራችን እንደእሱ እንዲደረግ የተደረገው ግን ከነዳጅ እጥረት ጋር ተያይዞ ሲሆን፣ ናይጄሪያውያን ደግሞ እንዲያ ያደረጉት በነዳጅ ምርት እጥረት ሳይሆን ነዳጅ መንጭቶላቸው ብዙ ዶላር በማግኘታቸውና ብዙ መኪና በመግዛታቸው የመንገድ መጨናነቅ ስላጋጠማቸው ነው ብለዋል።
በሌላ በኩል የምጣኔ ሀብት ባለሙያው፣ የውጭ አገር ላኪዎች የውጭ ምንዛሬውን እውን ወደአገር ውስጥ ያስገባሉ ወይ ሲሉ ይጠይቃሉ። ከባድ የሆነ የውጭ ምንዛሬ እጥረት እያለና የነዳጅ ድጎማ ይነሳል እየተባለ ባለበት በዚህ ጊዜ ላኪዎች በሚያገኙት የውጭ ምንዛሬ በሙሉ መኪና ያስገባሉ። ለዚህ ማሳያ ደግሞ ሰሞኑን ከተማው ውስጥ የሞሉት አዳዲስ መኪናዎች ናቸው ሲሉም ይናገራሉ። ስለዚህም የተናጠል እርምጃ መውሰዱ ብቻ መልስ ሊሆን ስለማይችል ሁሉንም ማየት ያስፈልጋል ብለዋል። ስለዚህም ላኪዎች ወደውጭ የላኩት ዋጋ በትክክል ወደአገር ውስጥ ገንዘቡ መግባቱን ልብ ማለቱም ሌላው አማራጭ እንደሆነ አስረድተዋል።
የነዳጅ ዋጋ እጅግ በናረበት በዚህ ጊዜ የአገር የውጭ ምንዛሬ እጦት አንገብጋቢ ሆኖ አገሪቱ በትራፊክ ጭንቀት ምክንያት መኪናዎች መንገድ ላይ ምን ያህል ነዳጅ ነው የሚያቃጥሉት ሲሉ የሚጠይቁት አቶ ዛፉ ኢየሱስወርቅ፣ ከአዲስ አበባ አንዱ ጥግ ወደመሃል ለመምጣት ሁለትና ሶስት ሰዓት እንደሚፈጅ ተናግረዋል፤ በዚሁ ሁሉ የሚቃጠለው ነዳጅ መሆኑንም ጠቅሰው፤ የተጠየቀውን የነዳጅ መጠን እየከፈሉ ማምጣት ብቻ መፍትሄ ሊሆን አይችልም፤ ስለዚህ የነዳጅ ዋጋ እንዲህ እየናረ ሲመጣ የምንጠቀመውን የነዳጅ መጠን ማሳነሱ እንደ አንድ መፍትሄ መታየት ይኖርበታል ሲሉ ተናግረዋል።
በአገር ደረጃ የውጭ ምንዛሬ ችግራችን እንዲህ አግጥጦ በመጣበት በዚህ ጊዜ ያላስፈላጊ የቅንጦት የሚባሉ አይነት እቃዎች በውጭ ምንዛሬ ተገዝተው ወደ አገር ውስጥ በዚህ ደረጃ መግባታቸው አስፈሪ ነው፤ ስለዚህም በመንግስት በኩል እንዲህ አይነቱ አካሄድ ሊስተዋል እና አንዱን ከሌላው ጋር ማጣጣም የሚቻልበት ሂደት ሊፈጠር ይገባል ብለዋል።
እርሳቸው እንደሚሉት፤ በኢትዮጵያ ለመኪና ታርጋ ለማውጣት እንኳ የታርጋ ቀለም የሚመጣው ከጀርመን አገር ነውና የውጭ ምንዛሬ እጥረት በመኖሩ ለጊዜው መስጠት አቁመናል እስከሚባል ተደርሷል። ነገር ግን የውጭ ምንዛሬ እጥረት በማጋጠሙ ታርጋ መስጠት አንችልም የሚል አገር በሺህ የሚቆጠሩ አዳዲስ መኪናዎች አምጥቶ በአንድ ጊዜ ከተማውን የሚያጥለቀልቅ ሆኖ ነው የታየው። አዳዲስ መኪናዎችን የሚያመጡ አካላት ምናልባትም ከአገር ውስጥ የሚወጡ እቃዎችን በርካሽ የሚሸጡ ሊሆኑ ይችላሉ። ይህ መጥፎ አካሄድ ነው።
የነዳጅ ድጎማ መነሳቱ የሚያሳየው የአቅም ውስንነት መኖሩን ነው። አገር አልቻልኩም ካለች አልቻለችም ነው። በዚህ ላይ ግን የነዳጅ ድጎማው ከተነሳ ከፍተኛ ዋጋ ከፍሎ ሊገዛ የሚችል አካል እንዳለ እውን ነው፤ ነገር ግን ችግር ይሆናል ብዬ የማስበው ዝቅተኛ የኢኮኖሚ አቅም ያለው ህዝብ ለእርሱ የትራንስፖርት መወደድ ትልቅ ትርጉም አለው። መኪና ያላቸው ግን ለመኪናቸው ቤንዚን መግዛት ካልቻሉ መኪናቸውን ማቆም እንደ አንድ አማራጭ ሊወስዱ ይችላሉ በማለት ያስረዳሉ።
ስለዚህም ይላሉ የምጣኔ ሀብት ባለሙያው አቶ ዛፉ ኢየሱስወርቅ፣ የነዳጅ ድጎማው ሲነሳ በአንድ አይነት መልኩ መሆን የለበትም። የሕዝብና የግል ላይ የሚደረገው ውሳኔ የተለያየ መሆን ይጠበቅበታል። በእርግጥ እኔም አንድ አይነት ይሆናል የሚል እምነት አይኖረኝም። የድጎማው መነሳት የኢኮኖሚ አቅሙ ዝቅተኛ የሆነውን የሕብረተሰብ ክፍል የበለጠ ተጠቂ የሚያደርግ ነውና ለዚህ መፍትሄው የድጎማው መነሳት ሁኔታ ሁለት አይነት አካሄድን ሊከተል ይገባዋል። የነዳጅ ድጎማው ይነሳል ሲባል ከትራንስፖርት ተጠቃሚዎች አንጻር የሕዝብ አገልግሎትና የግል አገልግሎት የቱ ነው የሚለው ጉዳይ ከግምት ውስጥ መግባት አለበት።
በቀጣይ ግን አገሪቱ በግብርናው ዘርፍ ያላትን እምቅ አቅም አሟጣ ለመጠቀም ጠንክራ ስራ መስራትና ለውጭ ገበያ በሚውል መልኩ ማምረት የግድ እንደሚላት የምጣኔ ሀብት ባለሙያውም አስረድተዋል። የነዳጅ ድጎማው ብቻ ስለተነሳ አገሪቱ የምትፈልገውን የውጭ ምንዛሬ ማግኘት ያስችላታል ማለት አይቻልም፤ ጎን ለጎን ባላት የተፈጥሮ ጸጋ በመጠቀም ግብርናውን ወደማዘመንና የስራ ፈጠራንም ወደማበረታት መግባት እንደሚያስፈልጋት ተናግረዋል። መንግስት ድጎማውን ማንሳቱ ለጊዜው ሌላ አማራጭ በማጣቱ መሆኑንም ነው የተናገሩት።
መንግስት የነዳጅ ድጎማውን ሲያነሳ መፍትሄዎቹን ተከትሎ የማይተገበር ከሆነ የራሱ የሆነ ችግር ይዞ ሊመጣ ይችላልና በዚህ ላይ ጥንቃቄ ሊያደርግ እንደሚገባውም ባለሙያው ጠቅሰዋል። አገሪቱ አሁን ያለባት ችግር በራሱ ከባድ ነው። ይህ በእንዲህ እንዳለ ድጎማውን ባለው ጊዜ ሙሉ ለሙሉ የሚያነሳ ከሆነ ልትወጣ ወደማትችለው ፈተና ውስጥ ሁሉ ልትገባ እንደምትችል ነው ያመለከቱት።
አስቴር ኤልያስ
አዲስ ዘመን ግንቦት 23/2014