በሰሜኑ የአገራችን ክፍል አሸባሪው ሕወሓት ከከፈተው ጦርነት ጋር ተያይዞ የጦርነቱ ሰለባና የሰብዓዊ መብት ተጎጂ የነበሩት ሁሉም የህብረተሰቡ ክፍሎች ተጎጂ ቢሆኑም በተለይም ሴቶች፣ ህጻናትና አረጋውያን ደግሞ የአስከፊው ጦርነት ገፈት ቀማሽ ነበሩ። ከታዳጊ ህጻናት ጀምሮ እስከ አዛውንት መነኩሴ ድረስ የዚሁ አረመኔያዊ ድርጊት ሰላባ ነበሩ። ልጆች በወላጆቻቸው ፊት፣ እናቶች ደግሞ በልጆቻቸውና በባለቤታቸው ፊት እጅግ አስከፊ በሆነ መልኩ ተደፍረዋል። በዚህም አንዳንዶቹ አካላዊ ጉዳት ሲገጥማቸው ሁሉም የስነልቡና ስብራት ደርሶባቸው ከአንገታቸው ቀና ማለት ተስኗቸዋል።
ከዚህ ጦርነት ጀምሮ ጥቃቱ እንደ ቀድሞው ጊዜ ሁሉ እንደ አንድ ድንገት የሚፈፀም የጦርነት የጎንዮሽ ጉዳት ተደርጎ መታየቱ አክትሞለታል። ሕግ በማስከበር ስም በወጡ አንዳንድ አካላት ጭምር ሲፈፀም በግልፅ ተሰምቷል፣ ተስተውሏል። አዝማሚያው በሴቶችና ልጃገረዶች ላይ የሚፈፀም ወሲባዊና ማንኛውም ጥቃት ታስቦበት ወደሚፈፀም የበቀል ጥቃት መሸጋገሩንም እንዳንድ ዓለምና አገር አቀፍ ሰነዶች ያመለክታሉ። በተጨማሪም ጾታዊ ጥቃቱ በተለይ ለጥፋት ቡድኑ ኃይሎች በአስከፊና አስነዋሪ ሁኔታ ሆን ተብሎ እንደ ጦር መሣሪያ እንዲያገለግል መደረጉም ይነሳል።
በሕግ ማስከበሩ ወቅት በነበረው ጦርነት በኢትዮጵያ በተለይም በትግራይ ክልል በጥፋት ኃይሎች አማካኝነት በሴቶችና ልጃገረዶች እንዲሁም ህፃናት ላይ የደረሱ ጾታዊ ጥቃቶችን ተከትሎ የሰብዓዊ እርዳታ ቢሮ (ኦቻ) ጾታዊ ጥቃቱ እንደ አንድ መደበኛ የጦር መሳሪያ እያገለገለ መገኘቱን በዘገባው መግለፁን ዋቢ ማድረግም ይቻላል። አስገድዶ መድፈር መደበኛ በሆነ መንገድ እንደ ጦር መሣሪያ እየዋለ መሆኑን የተባበሩት መንግስታትም እ.ኤ.አ በ2008 ባወጣው ሰነድ ጠቁሟል።
በአፍሪካ ከተቀሰቀሱና ከተካሄዱ የእርስ በእርስ ጦርነቶች ጋር በተያያዘ ጥቃቱ አንድ መደበኛ የጦር መሳሪያ ለማገልገሉ ብዙ ማሳያዎችም አሉ። ለአብነት በዚያው ሰሞን ሂውማን ራይትስዎች ባወጣው አንድ ዘገባ እንዳመለከተው በምዕራብ አፍሪካዊቷ ሴራሊዮን ከ10 ዓመታት በላይ በቆየው የእርስ በእርስ ጦርነት በአገሪቱ ከነበሩት ሴቶች መካከል አንድ አራተኛ (1/4ኛ) የሚሆኑት በዚሁ መልኩ ተደፍረዋል። እ.ኤ.አ በ2011 በኮንጎ በነበረው የእርስ በእርስ ግጭትም በየአንዳንዱ ሰዓት ውስጥ 48 ሴቶች አስገድዶ መድፈር ወንጀል ይደርስባቸው እንደነበር ተጠቁሟል። በሩዋንዳም እንዲሁ ለዓመታት በዘለቀ የእርስ በእርስ ጦርነት ከ250 ሺህ በላይ ሴቶች የአስገድዶ መድፈር ጥቃት የተፈፀመባቸው መሆኑንም ሰነዱ ይጠቅሳል።
በተበታተነ መልኩ ይሁን እንጂ በኢትዮጵያም በሰሜኑ ክፍል በተከሰተው ግጭት በርካታ ልጃገረዶች፣ ሴቶችና ህፃናት እንዲህ ዓይነቱ አስከፊ ጾታዊ ጥቃት የደረሰባቸው ለመሆኑ በተለያየ መንገድ ሲገለፅ ቆይቷል። በትግራይ ክልል አክሱም ከተማ የአስገድዶ መድፈር ወንጀል ምርመራን አስመልክቶ የፌዴራል ጠቅላይ አቃቢ ሕግ ባወጣው ዘገባ 116 ተበዳዮች ለፖሊስ ቃላቸውን መስጠታቸውን መግለጹ ይታወሳል።
በእርግጥም እንዲህ ዓይነቱ ተግባር በሰራዊቱ ላይ ጥቃት ከተፈፀመና መንግስት ሕግ ማስከበር ከጀመረ እንዲሁም የተኩስ አቁም አድርጎ ከትግራይ ክልል ከወጣ በኋላ በተጨማሪም ሕወሓት ወደ አማራና አፋር ክልሎች ከተስፋፋ በኋላ ተባብሶ የቀጠለበት ሁኔታ መኖሩን የሚያመላክቱ መረጃዎች አሉ። ቢሆንም ይሄን ያህል ሴቶችና ልጃገረዶች እንዲሁም ህፃናት እንዲህ ዓይነት ጥቃት ደርሶባቸዋል ብለው መጠናቸውን የሚገልፁ ሳይሆኑ የተበታተኑ ናቸው።
ይሄንኑ በሰሜኑ ክፍል የተከሰተውን ግጭት አስመልክቶም መንግስት በጦርነቱ ምክንያት በአፋር፣ በአማራና በትግራይ ክልሎች በሴቶችና ልጃገረዶች ላይ የተፈፀሙ ጥቃቶችን ወንጀል ለማጥራት የሚያስችል ከፍተኛ እንቅስቃሴ ሲያደርግ ቆይቷል። የሚኒስትሮች ግብረ ኃይል ጽሕፈት ቤት የተቋቋመበት ሁኔታም መኖሩ የሚታወስ ነው። ጽሕፈት ቤቱ ሲቋቋም ዋነኛ ዓላማው ያደረገው በሰሜኑ የአገራችን ክፍል በተከሰተው ግጭት አውድ የተፈፀሙ ወንጀሎችን ማጥራት እንደነበርም ይታወቃል። በዚሁ ጽሕፈት ቤት ሥር አራት ኮሚቴዎች መዋቀራቸውና የጥቃት ወንጀሉን የማጥራት ሥራው ሲከናወን መቆየቱም እንዲሁ ይታወሳል። በነገራችን ላይ ከአራቱ ኮሚቴ አንዱ የምርመራ እና ክስ ቡድን ነው።
ከዚሁ ጋር ተያይዞ ከግንቦት 13 እስከ ግንቦት 17 ቀን 2014 በቢሾፍቱ ከፍተኛ የአቅም ግንባታ ስልጠና መርሐ ግብር ተካሂዷል። ስልጠናው ዓለም አቀፋዊ ደረጃዎችን እና የተመረጡ ልምዶችን መሰረት ያደረገ ሲሆን አዘጋጆቹ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴርና የኢፌዴሪ ፍትህ ሚኒስቴር ነበሩ።
በመድረኩ ላይ በፍትህ ሚኒስቴር የጠቅላይ አቃቢ ሕግ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ፍቃዱ ጸጋ ተገኝተዋል። ሚኒስትር ዴኤታው እንደገለፁት፤ በሰሜኑ የአገራችን ክፍል በተከሰተው ግጭት አውድ የተፈጸሙ ጾታዊ ጥቃቶች ዓይነት ወንጀሎች ሲከሰቱ መንግስት ዜጎችን ከጥቃቱ የመጠበቅ ኃላፊነት አለበት። የዜጎችን ሰላምና ደህንነት ከማስጠበቁ ባሻገርም ጾታዊ ጥቃቶችን የማስቆሙን ኃላፊነት ይወስዳል። ተፈፅመው ሲገኙም ቢሆን ጉዳዩን መርምሮ ወንጀለኞችን የማስቀጣቱ ዋነኛ ድርሻ የመንግስት ነው።
በየደረጃው ያሉት የፍትህ አካላትም እንደ አገር የተቋቋሙት እንዲህ ዓይነቱን አስከፊና አፀያፊ ተግባር ለመከላከል ነው። በመሆኑም ለወሲባዊ፣ አካላዊና ኢኮኖሚያዊ እንዲሁም ስነ ልቦናዊ ጉዳት የተዳረጉ የወንጀሉ ሰለባዎች ተገቢና ሁሉን አቀፍ ፍትህ እንዲያገኙ ከማድረግ አንፃር ዓይነተኛ ሚና እንደሚጫወቱ እምነታቸው ነው።
በምርመራው ሂደት የሚሳተፉ ባለሙያዎችን አቅም ለመገንባት የተሰጠው ከፍተኛ ስልጠና ዓላማም ይሄው ነው። ስልጠናው ዓለም አቀፋዊ ደረጃዎችን እና የተመረጡ ልምዶችን ቀምሮ እንዲካሄድ የተፈለገበትም ከዚህ የተለየ ምክንያት የለውም። ዓላማው በምርመራው ብሎም በክስ ሂደቱ የሚሳተፉ ባለሙያዎችን አቅም በተገቢው መንገድ በመገንባት ማብቃት ነው። ይሄ ደግሞ ባለሙያዎቹ የተለየ ባህርይ ያላቸውን የጾታ ጥቃት ወንጀል ምንነት በቀላሉ እንዲረዱ ያስችላል። የጾታ ጥቃት ወንጀል ምርመራዎች በሚያካሂዱበት ሳይንሳዊ እና ህጋዊ አግባብ ላይ ጥልቅ ግንዛቤ እና ዕውቀት በማስረጽ መርማሪዎች የተሻለ ሥራ የሚሰሩበትን ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል።
የጾታ ጥቃት ምርመራዎች የተሳኩ እንዲሆኑ በማድረጉ ረገድ እገዛው የጎላ ይሆናል። እንደ ሚኒስትር ዴኤታው አቶ ፍቃዱ ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ጥበቃ ስርአትም ተጠያቂነትን ከማረጋገጥ አንፃር ከባድ ኃላፊነት ተጥሎበታል። ስልጠናው የደቡብ ሱዳንን እና ኮንጎን ጨምሮ አገራችን በሰሜን ኢትዮጵያ ባለፈችበት ዓይነት ችግር ያለፉ ሌሎች አገራት ተጨባጭ ተሞክሮዎችን በመቀመር እንዲካሄድ የተፈለገበት ዓላማም በዋናነት ተጠያቂነትን ለማስፈን ያለመ ነው ብለዋል።
‹‹ተጠያቂነትን ለማስፈን ምርመራዎች በፍጥነት ተጠናቀው ክስ መመስረት አለበት›› ሲሉ በመድረኩ ባደረጉት ንግግር ያሳሰቡት ደግሞ በተባበሩት መንግስታት ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን አገራዊ ጽሕፈት ቤት ምክትል ተጠሪ ቻርለስ ንዴማ ናቸው። የጥፋት ኃይሉ በአማራና በአፋር ክልል ከተስፋፋበት ጀምሮ የደረሰውን ጥቃት ጨምሮ በጦርነቱ የወደመውን ንብረትና ሕይወት እንዲሁም የጾታዊ ጥቃት ሪፖርት ማየታቸውን ያወሱት ንዴማ በእርግጥ ተጠያቂነትን የማስፈን ሂደቱ ጾታን መሰረት አድርገው የተፈፀሙትና የሚፈፀሙት ጥቃቶች በጣም ውስብስብ በመሆናቸው እንዲህ እንደሚጠበቀው ቀላል ላይሆን ይችላል።
በግጭት ወቅት የሚከሰቱ ጥቃቶች ከሰው ባህርይ ወጣ የሚሉ እንዲሁም እጅግ ሰዋዊ ክብርና ስብዕናን የሚነኩ አዋራጆች ከመሆናቸው አኳያ እጅግ ከባድ የሚሆን ይመስላቸዋል። አልፎ አልፎ እንደ ጦርነት ግብ ማስፈፀሚያ ስልት ጥቅም ላይ የሚውሉ መሆናቸው ተጠያቂነት የማስፈን ክብደቱን አብዝቶ ያጎላዋል ይላሉ። እንደ ንዴማ ክስ ለመመስረት የሚያስችል የተጎጂዎችንም ሆነ የሌሎች ሰዎችን ምስክርነት ማግኘቱ በተለይ እጅግ አስቸጋሪ እንደሚሆን ይገምታሉ። ምክንያቱም ደግሞ በጾታዊ ጥቃቱ የተሳተፉ ሰዎች ድርጊቱን ላለመፈፀማቸው በተለያየ መንገድ ማስተባበሪያዎችን ሊያቀርቡ ይችላሉ። ለምሳሌ፤ በወሲብ ሥራ የተሰማሩ ሴቶች የፆታዊ ጥቃቱ ሰለባ ሊሆኑ ይችላሉ። አጥቂዎቹ በወሲብ ሥራ ላይ ከተሰማሩ ሴቶች ጋር ነው ድርጊቱን የፈፀምነው ብለው ሰበብ የሚፈጥሩበት ሁኔታ ሊኖር ይችላል። ወይም እንዲህ ዓይነቱ የሀሰት ማስተባበሪያ ሊኖር አይችልም ብሎ መገመት ያዳግታል። ጾታዊ ጥቃቱ የደረሰባቸው ሴቶችም መጠቋቆሚያ መሆንን በመፍራትም ሆነ በዛቻና በተለያየ መንገድ ጥቃት እንደደረሰባቸው ለመናገር ላይደፍሩ ይችላሉ። ሆኖም የውጭ ተሞክሮ የተቀመረበት የአቅም ግንባታ ስልጠና እንዲህ ዓይነቶቹን ውስብስብ ችግሮች የመፍታት አቅም ስለሚፈጥር የማጥራት ሂደቱ ስኬታማ እንደሚሆን አይጠራጠሩም።
አሁን ላይ የሚኒስትሮች ግብረ ኃይል ጽሕፈት ቤት እስከ ማቋቋም በመድረስ በጾታዊ ጥቃቱ ወንጀል ላይ እየተካሄደ ያለውን ጠንካራ ምርመራና መፍትሄ የማቅረብ ሂደትም አብዝተው የሚያደንቁ መሆናቸውንም ንዴማ በመድረኩ ለተገኙት ተሳታፊዎች ገልፀዋል። ይሄ እንደተጠበቀ ሆኖ ለስኬታማነቱ የተለየ ኃላፊነት ያለበት የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር በጥቃቱ ሰለባዎች ላይ ትኩረት አድርጎ መሥራት እንደሚገባው በማሳሰብ ነው ተጠሪው ቻርለስ ንዴማ ንግግራቸውን የቋጩት።
‹‹በዓለም አቀፍ ደረጃ ከሶስት ሴቶች አንዷ በሕይወት ዘመኗ አካላዊ ወይም ወሲባዊ ጥቃት ይደርስባታል›› ሲሉ በተወካያቸው በኩል የተናገሩት ደግሞ ትኩረቱን ሴቶችን በማብቃትና በሴቶች እኩልነት ላይ አድርጎ እየሰራ የሚገኘውና በኢትዮጵያ የተባበሩት መንግስታት የሴቶች ጉዳይ ተወካይ የሆኑት ሚስ አና ሙታቫቲ ነበሩ። ሚስ አና በዚሁ መድረክ ለስልጠናው ተሳታፊዎች በጥቃቱ ዙሪያ ያለውን ልምድ አካፍለዋል። የኢትዮጵያን ስነ ሕዝብ ዳሰሳ ጥናት ዋቢ አድርገውም 23 በመቶ የሚሆኑት ዕድሜያቸው ከ15 እስከ 49 የሆኑ ሴቶች አካላዊ ጥቃት ያጋጥማቸዋል ብለዋል። 10 በመቶዎቹ ደግሞ የወሲባዊ ጥቃት ሰለባዎች እንደሆኑም አስምረውበታል።
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ዓለሚቱ ሁመድ እንዳሉት፤ በሴቶች፣ ልጃገረዶችና ህፃናት ላይ የደረሰው ጥቃት በተበዳዮቹ ሕይወትና በአገር ኢኮኖሚ ላይ የሚያሳድረው ተፅዕኖ እጅግ የከፋ ነው ብለዋል። ሆኖም የጉዳቱን መጠን ከማስረዳት አኳያ በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽንና በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ጽሕፈት ቤት ከግንቦት እስከ ነሐሴ 2013 ዓ.ም በጋራ የተካሄደው ጥናት በግጭቱ አውድ ስለተፈፀሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችና የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ሕግ ጥሰቶች ላይ ጠቃሚ መረጃ ለመሰብሰብ ችሏል።
የጥናቱ ግኝትም ከጾታዊ ጥቃት ጋር በተያያዘ አስገድዶ መድፈርን ጨምሮ የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶችና የሰብዓዊ ሕግጋቶች ጥሰት መፈፀማቸውንና ተጨማሪ ምርመራ የሚሹ መሆናቸውን አሳይቷል። በመሆኑም መንግስት ከግጭቱ ጋር ተያይዞ የተፈፀመውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት ለመፍታትና ተግባራዊነቱን ለማረጋገጥ የሚደረገውን ጥረት የሚቆጣጠር የፍትህ ሚኒስቴር፣ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን፣ ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር እንዲሁም ከሌሎች ዘርፍ መሥሪያ ቤቶች የተወጣጡ አባላት ያሉት የሚኒስትሮች ግብረ ኃይል አቋቁሞ ወደ ሥራ መግባቱን አውስተዋል።
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን ግንቦት 23/2014