ኢትዮጵያ እና ግብርና በእጅጉ የተቆራኙ፤ ለሺህ ዓመታት የቆየው ግብርና ዛሬም ድረስ የሕዝቧን ከ80 በመቶ በላይ እንደ መተዳደሪያ ሆኖ የሚያገለግል፤ ነገር ግን ዛሬም ከጥንቱ ዘመን የአስተራረስ ዘይቤ እምብዛም ፈቀቅ ያላለ መስክ ነው። በዚህም ምክንያት ግብርናው ሳይዘምን፤ ምርትና ማርታማነቱ በሚፈለገው ልክ ሳያድግ፤ ከበሬ ትከሻ ሳይላቀቅ፤ ክረምት ጠብቆ ከማምረት ሳይራራቅ፤… ኖሯል። ይሄም ኢትዮጵያ ለም መሬቷን፤ የውሃ ሃብቷን፤ አምራች የሰው ኃይሏንና እምቅ የተፈጥሮ ሃብቷን ይዛ የምግብ ዋስትናዋን እንኳን ሳታረጋጋጥ ዛሬ ላይ ደርሳለች።
ኢትዮጵያ፣ ግብርናዋን ብታዘምን፣ ምርታማነቷን ብታሳድግ፣ ቴክኖሎጂዎችን በዘርፉ ብትተገብር የምግብ ዋስትናዋን ከማረጋገጥ አልፎ ለሌሎች መመገብ የምትችልበት አቅም ያላት ቢሆንም፤ ለራሷ እንኳን መሆን ሳትችል ስንዴን ከውጭ እያስገባች ሕዝቦቿን ለመመገብ፤ የግብርና ኢንዱስትሪዎቿም ከውጭ በሚገቡ ግብዓቶች ላይ ጥገኛ ሆነው ውጤታማ እንዳይሆኑ፤ በጥቅሉ ውሃ ላይ ተቀምጣ የምትጠማ፤ ለም አፈር ላይ አርፋ የምትራብ፤… የድህነትና ረሃብ መገለጫ ሆና ስንገለጥ ኖራለች።
ይሄን እውነት ለመቀየር ከደርግ ዘመን ጀምሮ የተሞካከሩ የሜካናይዜሽን የእርሻ ልማት ተግባራት ነበሩ። ሆኖም የሚፈለገውን ውጤት ሳያመጡ፤ ምርታማነታቸውን ሳያሳድጉና የአርሶ አደሩን ኑሮ ሳያሻሽሉ የኢህአዴግ ዘመን ተተካ። እሱም በግብርና መር የኢኮኖሚ ፖሊሲ ታግዞ፤ ግብርናውን የማዘመንና የማሳደግ፤ በሂደትም ለኢንዱስትሪው ሽግግር የሚሆን ምቹ መደላድል መፍጠርን ታላሚ አድርጎ ወደስራ ገባ። አልተሳካም እንጂ፣ ግብርናውን ከበሬ አላቅቆ በትራክተር የማከናወን ሂደታዊ ለውጥ፤ ከዝናብ ጥገኝነት አፋትቶ የመስኖ ልማትን የማስፋት ጅማሮ፤ የተቆራረጠውን የእርሻ ልማድ ወደ ኩታ ገጥም የአስተራረስ ዘዬ ለማሻገር ውጥኖች ተይዞም ነበር።
ብሂሉም “ግብርናው እንዲሰጥህ በደንብ ስጠው” ነውና ግብርናው በግብዓትም፣ በቴክኖሎጂም የታገዘ፤ ምርጥ ዘርና ሌሎች ማዳበሪያና መሰል ምርታማነትን የሚያሳድጉ ግብዓቶች ለአርሶ አደሩ እንዲደርሱ ተደረገ። በዚህም ምርታማነትን ማሻሻል ብቻ ሳይሆን፤ ምንም እንኳን በተወራለት ልክ ባይሆንም “ሚሊዬነር” የተባሉ አርሶ አደሮችን ማፍራት የተቻለበት አጋጣሚም ስለመፈጠሩ በየሚዲያዎቹ በስፋት ተዘግቧል። ይሄም ሆኖ ግን አገር የምግብ ዋስትናዋን ማረጋገጥ፤ የአርሰ አደሮቿን ሕይወት በሚፈለገው ልክ ማሻሻል፤ ግብርናዋንም ባሰበችው ልክ ከበሬም ከዝናብም ማላቀቅ ሳትችል፤ ኢህአዴግ ተለውጦ ለውጥ የወለደው ብልጽግና ቦታውን ያዘ።
ከ2010ሩ የለውጥ ማግስትም ግብርናውን ማዘመን በይደር የሚተው የቤት ስራ ባለመሆኑ ዋናው አጀንዳ ተደርጎ ተይዟል። ይህ ደግሞ እንደ ቀደሙት ከውጭ በተቀዱ የፖሊሲ መስመሮች የሚከወን ሳይሆን እንደ አገሪቱ ተጨባጭ እውነታ ሊሰራበት የሚገባ እንደመሆኑ “አገር በቀል የኢኮኖሚ ፖሊሲ” ተነድፎ እና የአስር ዓመት የብልጽግና ልማት ሰንድ ተዘጋጅቶ ወደትግበራ ተገባ። ሲጀመርም የቀደሙ የዘርፉ አፈጻጸሞችና ሂደቶች ተፈትሸው፤ ያሉ መልካም እድሎችና ፈተናዎች ተለይተው፤ የመዳረሻ ግብ ተቀምጦና ሁሉም ባለድርሻ ተሰጥቶት ነው።
ለምሳሌ፣ የነበረውን የዘርፉን አፈጻጸም ተገምግሞ በሰነዱ እንደተቀመጠው፤ ከ2003 እስከ 2012 ባሉት ዓመታት ለፈጣን ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ የተጠበቀው አንዱና ዋናው ዘርፍ ግብርና ነው። ዘርፉ ለጠቅላላ የኢኮኖሚ ዕድገትና ለድህነት ቅነሳ የሚያደርገውን አስተዋጽኦ ከማሳደግ አኳያ በዘርፉ ፈጣንና ዘላቂነት ያለው ዕድገት በማምጣት የግብርናውን ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ፣ የግብርና ግብዓት አቅርቦትን ማቀላጠፍ፣ በዘርፉ የገበያ ትስስርን ማሳደግ፣ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ የግብርና ልማትን ማረጋገጥ፣ የህዝቡን ተጠቃሚነት በየደረጃው ማረጋገጥ እና በዘርፉ መዋቅራዊ ለውጥ እንዲመጣ ማስቻል የዘርፉ ዋና ዋና የትኩረት አቅጣጫዎች ነበሩ።
በዚህ አቅጣጫ መሰረት በተከናወኑ ተግባራት የግብርና አጠቃላይ አገራዊ ምርት ዕድገት ከ2003 እስከ 2012 በጀት ዓመት በአማካይ በየዓመቱ የ5ነጥብ3 በመቶ ዕድገት ያስመዘገበ ሲሆን፣ በዕቅድ ከተያዘው ከ8 በመቶ በላይ አማካይ የዕድገት ምጣኔ ግብ ጋር ሲነጻጸር ዝቅተኛ ነው። ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ የግብርና ምርቶች የውጭ ንግድ ገቢ እንዲሻሻል ምርታማነትን የሚጨምሩ፣ ጥራትን የሚያሻሽሉና፣ የግብይት ሰንሰለቱን የሚያቀላጥፉ ሥራዎች ሲሰሩ ቆይተዋል። በዚህም ባለፉት 10 ዓመታት በአጠቃላይ ከሸቀጦች የውጭ ንግድ ከተገኘው የውጭ የምንዛሪ ገቢ ውስጥ 73ነጥብ8 በመቶ የሚሆነው የተገኘው ከግብርና ምርቶች ነው። አሁንም ድረስ የውጭ ንግድ ገቢ በዋነኛነት በግብርናው ዘርፍ ላይ የተንጠለጠለ ሆኖ ይገኛል።
በአነስተኛ ይዞታ የሚመረተው የዋና ዋና ሰብሎች የመኸር ምርት በ2003 በጀት ዓመት ከነበረበት 222 ሚሊዮን ኩንታል በ2012 በጀት ዓመት ወደ 335 ሚሊዮን ኩንታል ከፍ ብሏል። በተመሳሳይ በ2012 በጀት ዓመት የአገዳና ብርዕ ሰብሎች አጠቃላይ ምርት 297 ሚሊዮን ኩንታል፣ የጥራጥሬ ሰብል ምርት 30 ሚሊዮን ኩንታል፣ እንዲሁም የቅባት ሰብል ምርት 8ነጥብ4 ሚሊዮን ኩንታል ደርሷል። ይህም የምርት ዕድገት የተመዘገበው በዘርፉ በታየው ከ20 በመቶ በላይ አማካይ የምርታማነት ጭማሪ ሲሆን፣ በተለይም በአብዛኛው የአገዳና ብርዕ ሰብሎች ላይ የታየው የምርታማነት ጭማሪ ከፍተኛ ድርሻ ነበረው። በአነስተኛ ይዞታ የሚመረተው የአትክልትና ፍራፍሬ የመኸር ምርት በ2003 በጀት ዓመት ከነበረበት 22 ሚሊዮን ኩንታል በ2012 በጀት ዓመት ወደ 60 ሚሊዮን ኩንታል (አትክልት 10 ሚሊዮን ኩንታል፣ ሥራሥር 42 ሚሊዮን ኩንታል እና ፍራፍሬ 8 ሚሊዮን ኩንታል) ከፍ ብሏል።
በሌላ በኩል፣ ለገጠሩ ህብረተሰብ የሥራ ዕድል በመፍጠር የገጠር የሥራ አጥነትን በመቀነስ በኩል በግብርናው ዘርፍ ባለፉት አምስት ዓመታት 6ነጥብ7 ሚሊዮን የሥራ ዕድል መፍጠር ተችሏል። በከተሞች አካባቢ ወጣቱን ወደ ግብርና ዘርፍ በመሳብ የሥራ ዕድል ከመፍጠሩ በተጨማሪ ለከተሞች በቂ የግብርና ምርት ለማቅረብ ከፍተኛ እንቅስቃሴ ሲደረግ ቆይቷል። በተለይም ወጣቱን ወደ ግብርና ዘርፍ ለመሳብና ተሳትፎው እየጨመረ እንዲሄድ ለማድረግ ግብርናን የማዘመን ሥራዎች ከፍተኛ ድርሻ ስላላቸው በዘመናዊ ቴክኖሎጂ አጠቃቀም፣ በእሴት መጨመር እንዲሁም በግብይት ሰንሰለት ልማት ላይ ሰፋፊ ሥራዎች ሲሰሩ ቆይተዋል።
በአጠቃላይ ለአገሪቱ ኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግር አስተዋጽኦ ከማድረግ፣ የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ እና ለሌሎች ዘርፎች አስተማማኝ ግብዓቶችን ከማቅረብና ለምርቶች ገበያ ከመፍጠር አንጻር የግብርናው ዘርፍ ውስንነት ነበረበት። ዘርፉ የአገሪቱን ሕዝብ የምግብ ፍላጎት ለማሟላት ያልቻለ ሲሆን፤ እስከ 25 ሚሊዮን ያህል ዜጎች በቂ ምግብ እንደማያገኙ ይገመታል። ከ15 ሚሊዮን የማያንሱ ዜጎችም በእለት ደራሽ እርዳታና በልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራም ታቅፈው ይገኛሉ። በዚህም ከ2003 እስከ 2012 ዓ.ም ያሉት አስር ዓመታት አፈጻጸም ዘርፉ በምርትም ሆነ በምርታማነት መሻሻሎች የታዩበት ቢሆንም፤ የአየር ንብረት ለውጥ፣ የግብዓትና የቴክኖሎጂ አቅርቦት ሥርዓት ኋላቀርነት፣ የፋይናንስ ተደራሽነት ችግር፣ ያልዘመነ የምርት ገበያ፣ በቂ ያልሆነ መሠረተ ልማትና ኢንቨስትመንት፣ ተቋማዊ የማስፈጸም አቅም እና የአገር ውስጥ ፖለቲካ ሁኔታ ዘርፉ የተሻለ አፈጻጸም እንዳያሳይ ስትራቴጂካዊ ማነቆዎች እንደነበሩ በጥልቀት ተገምግሞ በሰነዱ ተመላክቷል።
ይሄን የግምገማ ውጤት መነሻ በማድረግ እና አገራዊ እምቅ አቅምን በማገናዘብ የግብርናው ዘርፍ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ በዘላቂነት ለማሳደግ ያለበትን የላቀ ሚና በመገንዘብ የዘርፉን ውጤታማነትን እውን ለማድረግ ወደስራ ተገብቷል። በዚህም ከ2012 ዓ.ም ጀምሮ በሚኖሩት አስር ዓመታት ውስጥ ግብርናው የአገሪቱን ሕዝብ የመመገብ፣ በመካከለኛ ጊዜ የሚያስፈልገውን የውጭ ምንዛሪ የማስገኘት፣ የመዋቅራዊ ሽግግርን እውን የማድረግ፣ ለኢንዱስትሪውና ሌሎች ዘመናዊ ዘርፎች በቂ ምግብ፣ ግብዓትና የሰው ኃይል የማቅረብ፣ ለሌሎች ዘርፎች ምርቶች ገበያ ወይም ፍላጎት የማጎልበትና በስፋት የሥራ ዕድል የመፍጠር ግብ ተቀምጦለታል።
ይሄን እውን ከማድረግ አኳያም የተጠቀሱት ዓመታት የግብርና ልማት የትኩረት አቅጣጫዎች ተብለው ከተለዩት በርካታ ጉዳዮች መካከል የመስኖ ልማት እና የግብርና ሜካናይዜሽን ተጠቃሽ ናቸው። ከመስኖ ልማት አኳያ፣ የኢትዮጵያ የግብርና ምርት በዝናብ ላይ የተመሠረተ በመሆኑ ለዝቅተኛ ምርታማነት የተጋለጠ እንደመሆኑ የመስኖ አቅምን በማጎልበት የግብርናን ዘርፍ ከዝናብ ጥገኝነት ማላቀቅ ዋናው ትኩረት ነው። ምክንያቱም፣ ዘርፉ ከዓመት ዓመት የምርት መጠን ከዝናብ መጠን መዋዠቅ እና በየጊዜው ከሚከሰቱ የድርቅ አደጋዎች ጋር ተያይዞ ከፍተኛ ውጣ ውረዶች ይታዩበታል።
ይህ አካሄድ ደግሞ የሚጠበቀውን የግብርና ትራንስፎርሜሽን ለማረጋገጥ በቂ ስላልሆነ ለመስኖ ልማት ትኩረት መስጠት እጅግ አስፈላጊ እንደመሆኑ ለግብርና ሥራ የሚያገለግሉ አነስተኛ፣ መካከለኛና ትላልቅ የመስኖ ልማቶች በመንግስት፣ በልማት አጋሮች፣ በግሉ ዘርፍ እንዲሁም በማህበረሰቡ ትብብር የሚገነቡ ይሆናል። ይህን የመስኖ መሠረተ ልማቶች ተጠቅሞ በዓመት ውስጥ ያሉንን የምርት ወቅቶች ወደ 3 ወይም 4 ከፍ በማድረግ የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥም በላይ ለኢንዱስትሪና ለውጭ ንግድ በቂ ምርት ከማቅረብ አኳያ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዲኖረው ይደረጋል። የመስኖ ግንባታዎች ኢንቨስትመንት ቅደም ተከትል በሚሰጡት ጥቅምና በመረጃ ላይ የተመሠረተ እንዲሆን ይደረጋል፤ የሚል አቅጣጫ ተቀምጧል።
ይሄን አቅጣጫ መነሻ በማድረግም ላለፉት ሁለትና ሦስት ዓመታት በተከናወነው የመስኖ ልማት ስራ አበረታች ውጤት ተገኝቷል። በዓለማችን እስከ 70 በመቶ የሚሆነው የስንዴ ልማት በቆላማ ቦታዎች የሚካሄድ መሆኑ በዚህ ዘርፍ እንደ አንድ ተሞክሮ የተወሰደ ሲሆን፤ ይሄንኑ ተሞክሮ ወደ ኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ለመለወጥ ተሞክሯል። ኢትዮጵያ ደግሞ ለዚህ የሚሆን ለም አፈር እና ዓመቱን ሙሉ የሚወርዱ ወንዞች ያሉበት፤ ነገር ግን ቆላ ተብለው የመልማት እድሉን ሳያገኙ መሬቱ ልማት እንደናፈቀ፣ ውሃውም በከንቱ እየፈሰሰ የኖረበትን እውነት የሚቀይር ተግባር ተከናውኖባቸዋል።
በዚህ መልኩ በተለይ በቆላማ አካባቢዎች የተጀመረው ስንዴን በመስኖ የማልማት እርምጃ አፋርና ሶማሌ ክልልን ጨምሮ፣ ኦሮሚያ እና ደቡብ ቆላማ አካባቢዎች ላይ በተሰራው ሥራ ውጤት ማየት ተችሏል። በእነዚህ አካባቢዎች በመስኖ የለማው ስንዴም ኢትዮጵያ በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ ድርቅና ጦርነት በተከሰተባት ወቅት አስፈልጓት የነበረውን የምግብ ድጋፍ በራሷ አቅም መሸፈን የቻለችበትን እድል እስከመፍጠር አድርሷታል። ይሄን መሰል ውጤት የተገኘበትን የመስኖ ልማት ስራ የበለጠ የማስፋትና የማሻሻል ተግባራት እየተከናወኑ ሲሆን፤ በሂደት ከውጭ የሚመጣን ስንዴ የማስቀረትና በምግብ ራስን የመቻል ብቻ ሳይሆን፤ ወደ ውጭ በመላክ የውጭ ምንዛሬ የማግኛ ዘርፍ እንዲሆን እየተሰራ ይገኛል።
ከመስኖ ልማት ስራው ጎን ለጎን የሚሰራበትና የግድ ተመጋግቦ መሄድ ያለበት ሌላው የአስር ዓመቱ እቅድ ግብ ማሳኪያ ተደርጎ የተያዘው፤ የግብርና ሜካናይዜሽንን አገልግሎትን ማስፋፋት ነው። ምክንያቱም የሜካናይዜሽን አገልግሎትን ማስፋፋት ግብርናን ለማዘመንና የምርት ጥራትን ለማረጋገጥ፤ ከእርሻ እስከ አጨዳና ውቂያ ባለው ሂደት ውስጥ የግብርና ሜካናይዜሽንን መጠቀሙ ለአርሶ አደሩም ምርታማነት፤ ለምርቱም ጥራት ከፍ ያለ ፋይዳ አለ። ለዚህም የውሃ ፓምፖችን፣ ትራክተሮችን፣ ኮምባይነር ሃርቨስተሮችን እና ሌሎችም ለግብርናው የላቀ ውጤታማነት አቅም የሚፈጥሩ ቴክኖሎጂዎች ለአርሶ አደሩ እንዲደርሱ፤ ባለሃብቱም በስፋት ሥራ ላይ እንዲያውላቸው ይደረጋል። ይሄውም ተጀምሯል።
ይህ ሲሆን ግን ዝም ብሎ መድረስ ስላለባቸው ብቻ እንዲደርሱ የሚደረግ አይሆንም። ይልቁንም ለአገራችን መልከዓ ምድርና አግሮኢኮሎጂ ተስማሚ የሆኑ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ተመርጠው ለአርሶ/አርብቶ አደሩ ተደራሽ እንዲሆኑ እና ጥቅም ላይ እንዲውሉ የሚደረግ ነው የሚሆነው። ከዚህ ጎን ለጎንም የአርሶ/አርብቶ አደሩን አቅም ያገናዘበ አገር በቀል የሜካናይዜሽን ቴክኖሎጂዎች ፈጠራና ስርጭት ሥርዓትን በማጎልበት ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የአርሶ አደሩን ገቢ ትርጉም ባለው መልኩ ማሳደግ ላይ ያተኮረ ነው።
ይህ እንዲሆን እና የግብርና ሜካናይዜሽን አገልግሎት ሰጪ ተቋማትን ለማቋቋም እንዲያግዝም የግብርና ዘርፍ የሚጠቀማቸውን ማናቸውንም የቴክኖሎጂ ግብዓቶችና ማሽነሪዎችን ከግብር ነጻ በማድረግና የሊዝ ፋይናንሲንግ የብድር ሥርዓት በመገንባት ግብርናን ለማዘመን ትኩረት ተሰጥቷል። በዚህም ላለፉት ሁለት ዓመታት በላይ የግብርናውን ዘርፍ በሜካናይዜሽን ለማገዝ የሚያስችሉ ዘርፈ ብዙ ተግባራት ሲከናወኑ፤ ለዚህ እንዲሆንም የኩታ ገጠም አስተራረስ ዘዴዎች በስፋት ሲተገበሩ ቆይተዋል። በዚህ ረገድ ሊጠቀሱ ከሚችሉ አብይ ማሳያዎች መካከል፤ የክልል መንግስታት ለአርሶና አርብቶ አደሩ ተደራሽ የሚያደርጓቸው የውሃ መሳቢያ ጄኔረተሮች፣ የእርሻ ትራክተሮች፣ የማጨጃ ማሽኖች፤ እንዲሁም በስፋት ለምተው ሲጎበኙ የሚታዩት የኩታ ገጠም እርሻ ማሳዎች ተጠቃሽ ናቸው።
ይህን አይነት ድጋፍና እና የኩታ ገጠም እርሻ ጅምር ቀደም ሲል በኦሮሚያና ሌሎችም አካባቢዎች ሲተገበር በመቆየቱ የግብርናው ዘርፍ እድገት ላይ በጎ አብርክቶ እንደነበረው ታይቷል። ይሄ ልምድ ወደ ሌሎች ክልሎች እንዲሰፋ ሲሰራ የቆየ ሲሆን፤ በተለይ የሜካናይዜሽን አገልግሎትን በማስፋፋት ረገድ ድሬዳዋ እና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደሮችን ጨምሮ ለከተማ ግብርናቸውም በዙሪያቸው ላሉ አርሶ አደሮችም በሚሆን አግባብ እነዚህን የሜካናይዜሽን አገልግሎቶች ተደራሽ ሲያደርጉ ቆይተዋል። አሁን ላይ ደግሞ የአማራ ክልል ይሄንኑ ተሞክሮ ወስዶ እየተገበረ ሲሆን፤ ከሰሞኑ የሚስተዋለው የኩታ ገጠም ግብርና ጉብኝቶች እንዲሁም የእርሻ ትራክተሮችን ወደ አርሶ አደሮች ማድረሱ ለሜካናይዜሽን መስፋፋት እንደ በጎ ጅምር የሚወሰድ እርምጃ ነው።
ኢትዮጵያ በብዙ ውስጣዊ ችግሮች በተተበተበችበት፣ በውጫዊ ተጽዕኖዎች እየተፈተነች ባለችበት በዚህ ወቅት፤ እንደ አገር ቢያንስ ራሷን መግባ ማደር ግድ ይላታል። ኢትዮጵያ ታምርት የሚል ንቅናቄ ሲጀመርም፤ በሁሉም መስክ የሚመጣውን ጫና መቀነስና ችግርን በአሸናፊነት መሻገር የሚቻልበትን አቅም መፍጠርን መሰረት ያደረገ ነው። ለዚህ ትልቁን ሚና የሚጫወተው ደግሞ ግብርናው ነው። ግብርናው እንዲያድግና ሚናውን እንዲወጣ እየተሰራባቸው ካሉ ዘርፎች መካከል ደግሞ የመስኖ ልማትና የሜካናይዜሽን አገልግሎትን ማስፋት ነው። እነዚህ ሁለቱም ደግሞ ኢትዮጵያ አምርታ ዜጎቿን እንድትመግብ፤ አምርታ ለራሷም ለሌሎችም እንድትተርፍ በማድረግ ረገድም ከፍ ያለ ሚና ያላቸው የትኩረት አቅጣጫዎች ናቸው።
ይሄን መነሻ በማድረግ በተጀማመሩ ስራዎችም ዛሬ ላይ የመስኖ ልማት ሥራዎች እየበረከቱም ውጤት እያመጡም፤ በትራክተር ማረስም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጎለበተ መጥቷል። ይህ መልካም ተሞክሮ ሲሰፋ እና በየክልሎች በሚደረገው ድጋፍ እንዲጠናከር ሲደረግ ደግሞ በእርግጥም ኢትዮጵያ ማምረት ትጀምራለች፤ አምርታም ራሷን መመገብ ትችላለች፤ ከራሷም አልፋ ለሌሎች መመገብ የሚያስችል አቅምም እምቅ ሃብትም እንዳላት ለዓለም ታሳያለች። ይህ ሲሆን የኢትዮጵያ ትንሳኤ፤ የኢትዮጵያ ከፍታ፤ የኢትዮጵያ ብልጽግና እውን ይሆናል። ለዚህ ግን ጅምሩ በውጤት ታጅቦ መጓዙ ሊቀዛቀዝም፣ ሊቆራረጥም አይገባም።
ማሙሻ ከአቡርሻ
አዲስ ዘመን ግንቦት 23/2014