ቢላዋ ሲፈበረክ ለህይወት ጠቃሚ የሆነውን ምግብ ለማዘጋጀት እንዲጠቅም ታስቦ ነው። ይሁንና ሰዎች ከዚህ ዓላማ ውጪ ሰዎችን ለማጥቃት ሲጠቀሙበት ስለሚስተዋል ቢላዋ የሚባለው ስም ሲጠራ ነፍስ ማጥፋት፣ ጥቃትና ፍርሃትም አብሮ ይታሰባል። ለቅዱስ ዓላማ ታስበው የተፈጠሩና ለእርኩስ ዓላማ ውለው ምነው ባልተፈጠሩ ያልናቸው ብዙ ነገሮች እንዳሉም ሳይታለም የተፈታ ነው።
ለሰው ልጆች ጥቅም ተብሎ የተፈጠረው ቦምብ ለበርካቶች ህይወት መጥፋትና ለሰው ልጆች የስጋት ምንጭ ሆኖ ሲታይ አጠቃቀሙን ካላወቅንበት ወይም ደግሞ ሆን ብለን ካዛባነው ለልማት ያልነው መሳሪያ ለጥፋት ውሎ ስቃይና መከራን እንደሚያበራክትና እልቂትንም እንደሚያስከትል ግልጽ ያደርግልናል።
ከላይ በጠቀስነው ጉዳይ የተንደረደርነው ከሰሞኑ እጅግ አነጋጋሪ ጉዳይ በሆነውና ለቅዱስ ዓላማ ተፈጥሮ ለሰይጣናዊ ተግባርም እየዋለ ስላለው ማህበራዊ ሚዲያ ትንሽ ለማውሳት ፈልገን ነው። በማርክ ዙከርበርግ የተወለደው ማህበራዊ ሚዲያ መነሻ ዓላማው በህዝቦች መካከል መቀራረብን ማስፈን፣ አንድነትን ማጠናከር፣ ፍቅርን ማጎልበትና የዕውቀት ሽግግርን ማፋጠን ነበር። ይህንንም ተከትሎ በርካቶች ፍቅርና ሰላምን ሰብከውበታል። ርቀት ሳይገድባቸውም ከአንዱ የዓለም ጫፍ ወደሌላው ተዋውቀውበት አንድነታቸውን አጠንክረውበታል። ዕውቀት አስተላልፈው ዕውቀትም ሸምተውበታል። ተዋውቀውበት እስከጋብቻ የደረሰ ግንኙነት የመሰረቱም ብዙዎች ናቸው።
«በጥባጭ እያለ ማን ጥሩ ይጠጣል» ሆነና ነገሩ ለቅዱስ ዓላማ የተፈጠረው ይህ ማህበራዊ መገልገያ ለእኩይ ተግባር ውሎ የሀሰት ወሬ ማራገቢያ፣ የስም ማጥፊያ ፣ ሰላም ማደፍረሻና እልቂትን መስበኪያ ሲሆን እየተስተዋለ ነው። ከምንጊዜውም ይልቅ አሁን የጥላቻ ወሬዎች ማህበራዊ ሚዲያውን ተቆጣጥረውት በዘር፣ በብሄር፣ በሃይማኖትና በፖለቲካ አመለካከት ላይ የተመረኮዘ የጥፋት መልዕክት እየተሰበከበት ይገኛል። ይህ ጉዳይ በዓለም አቀፍ ደረጃም እጅግ አሳሳቢ ደረጃ ላይ በመድረሱና ስጋት በመደቀኑም በተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባዔም ሳይቀር የመነጋገሪያ አጀንዳ ሆኖ እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው።
በማህበራዊ ሚዲያ የሚተላለፉ የጥላቻ መልዕክቶች ለሀገራት መፈራረስ መንስዔ የሆኑበት ሁኔታ እንዳለና በብዙ ሀገራት ሰላምና ደህንነታቸው ላይ ስጋት መደቀኑም የአደባባይ እውነት ነው። አሁን ከሰሞኑ እንኳን አፍሪካዊቷ አገር ግብጽ ማህበራዊ ሚዲያ በሰላሟና በህዝቦቿ ደህንነት ላይ የደቀነውን አደጋ በመገንዘብ እስከ ከ5000 በላይ ተከታይ እያላቸው የአገር ደህንነትን አደጋ ላይ የሚጥሉ የማህበራዊ ትስስር ገጾች ለመዝጋት መወሰኗ ችግሩ አሳሳቢና ዓለም አቀፋዊ እንደሆነ የሚያሳይ ነው።
በፖለቲካ ሽግግር ላይ ላይ በምትገኘው አገራችንም በማህበራዊ ሚዲያ እየተላለፉ ያሉ የሀሰት ወሬዎች፣ ሥም ማጥፋቶች፣ ህዝብን ከህዝብ የሚያጋጩና የአገርን ሰላም የሚያደፈርሱ መልዕክቶች ወዘተ እጅግ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሳቸውን ከሰሞኑ ከተላለፈው የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓብይ አህመድ ድንገተኛ መልዕክት መረዳት ይቻላል።
ምንም ዓይነት በዓል ወይም ሁነት በሌለበት ሁኔታ ባልተጠበቀ ጊዜ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን መሰል የስጋት መልዕክት ማስተላለፋቸው ማህበራዊ ሚዲያው በአገራችን ሰላምና በህዝቦቿ ደህንነት ላይ ከፍተኛ ስጋት መደቀኑን ያመላክታል። ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልዕክታቸው የጥላቻ መልዕክትን በማስተላለፍ የሚገኝ ምንም ዓይነት ጥቅም እንደሌለ አስምረውበታል። አሁን አይመስለን እንጂ በጥላቻ አዕምሮ ታውረን ያለምንም የኃላፊነት መንፈስ የምንለቃቸው የጥፋት መልዕክቶች ጦስ በዚሁ ተግባር ላይ ለተሳተፉ አካላትና ቤተሰቦቻቸውም የሚተርፍ ነው።
ልዩነታችንን እንደ ፀጋ ተቀብለን ትልቋን ግንድ ኢትዮጵያን መመልከት ካልቻልንና ቅርንጫፎችን ብቻ እያሰብን ልዩነትን የምናሰፋ ከሆነ ቁጭ ብለን የምንወቃቀስባት አገር እንዳትኖረን እስከማድረግ እንደሚያደርሰን ቆም ብለን ማሰብ ይኖርብናል።
መረን የለቀቀ ነጻነት አገርን ያፈርሳል። ሃሳብን በነጻነት መግለጽ መከበር ያለበት ዴሞክራሲ መብት ነው። ይሁንና ይህ መብት በተግባር ላይ ሊውል የሚችለው የአገርንና የህዝብን ደህንነት አደጋ ላይ የማይጥል ሲሆንና የሌሎችን መብት የማይጋፋ ሲሆን ነው። ከዚህ ውጪ በማህበራዊ ትስስር ገጾች እየተላለፉ ያሉ የጥላቻና እልቂት ቀስቃሽ መልዕክቶች ምንም ዓይነት መደበቂያ የዳቦ ስም ሳይሰጣቸው ወንጀል ተብለው ሊፈረጁና የህግ ተጠያቂነት ሊኖርባቸው ይገባል። ስለሆነም ማንኛውም የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚ ከምንም በፊት በቅድሚያ ለራሱ፣ ለአገሩና ለህዝቡ ያለበትን ኃላፊነት በማሰብ ጥንቃቄ ሊያደርግ ይገባል እንላለን።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ መጋቢት 14/2011