ቡና በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ውስጥ ከፍተኛ ድርሻ ያለውና 20 ሚሊዮን የሚጠጋ ሕዝብ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የሚተዳደርበት ዘርፍ ነው። በውጭ ምንዛሪ ረገድም ከሀገሪቱ የውጪ ምንዛሪ ከ35-40 በመቶ ይሸፍናል። ዘርፉ ተገቢውን ትኩረት ካገኘ ከዚህም በላይ በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ውስጥ የጎላ ድርሻ እንደሚኖረው ይታመናል።
ዘርፉ የሀገሪቱ የኢኮኖሚ ዋልታ ሲባል የቆየ ቢሆንም ባለፉት አምስት ዓመታት ያሳየው ለውጥ ግን የሀገር ዋልታነቱን በአግባቡ ያረጋገጠ ይመስላል። በተለይም ሀገር በቀል የኢኮኖሚ መርሐ ግብር እንደሀገር ከተተገበረበት ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ ቡና በሀገር ኢኮኖሚ ውስጥ የሚጫወተው ሚና እያደገ መጥቷል።
መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፤ በ2012 ዓ/ም 270ሺ 035.1 ቶን ለውጪ ገበያ ቀርቦ 854.12 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ተገኝቷል። በ2013 ዓ/ም 243ሺህ 311 ቶን ለውጪ ገበያ ቀርቦ 907 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ተገኝቷል፤ በ2014 300ሺ ቶን ለውጪ ገበያ ቀርቦ 1.4 ቢሊዮን ዶላር ተገኝቷል፤ በ2015 240 ሺ 369 ቶን ለውጪ ገበያ ቀርቦ 1.3 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ሲገኝ ፤ በ2016 ዓ/ም 300 ሺ ቶን ለውጪ ገበያ ቀርቦ 1.43 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ተገኝቷል።
እንደ ሀገር የሀገር በቀል ኢኮኖሚው መተግበር ከመጀመሩ በፊት የቡና ግብይቱ በበርካታ ማነቆዎች የተተበተበ ነበር። በዋናነት የግብይት ሥርዓቱ በጣም የተንዛዛ፤ እሴት የማይጨምር እና ብዙ ችግሮች የነበሩበት ነበር። የሀገር በቀል ኢኮኖሚው ተግባራዊ መሆንም የግብይት ሥርዓቱን በማሳጠር በቡና ልማቱ እና ግብይቱ ላይ ለውጥ ሊመጣ ችሏል። ከዚህ ጎን ለጎንም በዓለም አቀፍ ገበያ ላይ ኢትዮጵያ ቡና የሚሸጥበት ዝቅተኛ የዋጋ ኅዳግ እንዲወሰንና አይነቱ ደረጃ እንዲኖረው መደረጉ የተሻለ የውጭ ምንዛሪ እንዲገኝ በር ከፍቷል።
ባለፉት 6 ዓመታት ከአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ጋር በተያያዘ 8 ነጥብ 5 ቢሊዮን የቡና ችግኞች የተተከሉ ሲሆን ይህም የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር የአካባቢ መራቆትን ከመከላከል ጎን ለጎን ቡናን የመሳሰሉ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸው ምርቶች እንዲስፋፉም የራሱን አስተዋፅዖ አበርክቷል።
የቡና ችግኞችን በስፋት ከመትከል ጎን ለጎንም የቡናን ምርታማነት ሊያሳድጉ የሚችሉ የግብርና ስልቶች ተግባራዊ በመሆናቸውም ባለፈው ዓመት ብቻ 1 ሚሊዮን ቶን ቡና ለማምረት ተችሏል። ለውጭ ገበያ የሚቀርበው የባለ ልዩ ጣዕም ቡና ድርሻ ከነበረበት 30 በመቶ ወደ 60 በመቶ አድጓል።
የአፍሪካ ቀዳሚ የዓለም ደግሞ ሦስተኛ የአረቢካ ቡና አምራች የሆነችው ሀገራችን ባለፈው የበጀት ዓመት በቡና የውጪ ንግድ 1 ነጥብ 43 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር አግኝታለች። ይህም ሀገሪቱ በታሪክ አይታ የማታውቀው የገቢ መጠን ነው። ካለፈው ዓመት ልምድ በመነሳትም በ2017 በጀት ዓመትም ቡና አምና ካስገኘው የ1 ነጥብ 43 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር በመሻገር 2 ቢሊዮን ዶላር ለማስገባት ከወዲሁ ዕቅድ ተይዞ እየተሠራ ነው።
የቡናን ምርታማነትና የገበያ ድርሻ ከማስፋት ጎን ለጎንም የቡና አምራቾች ከዘርፉ ተጠቃሚ እንዲሆኑ የተሠራው ሥራ ውጤት እያሳየ በመምጣቱም በአሁኑ ወቅት ከ1 ሺህ በላይ የቡና አምራች አርሶ አደሮች ምርታቸውን በቀጥታ ለውጭ ገበያ በማቅረብ ጠቀም ያለ ገቢ እያገኙ ነው።
በአምራች አርሶ አደሮች አንድ ኪሎ ግራም ባለ ልዩ ጣዕም ቡና ከ100 ሺህ ብር በላይ እየተሸጠ ሲሆን ከቡና የእሴት ሠንሠለት የሚያገኙት ድርሻም እያደገ መጥቷል። ከአንድ ሺህ በላይ አርሶ አደሮች የላኪነት ፈቃድ በማውጣት የቡና ምርታቸውን በቀጥታ ለውጭ ገበያ እያቀረቡ ይገኛሉ።
ኢትዮጵያ የቡና አምራቾችን ተጠቃሚ ለማድረግ የሠራችው ሥራ ውጤት በማምጣቱ እና በዓለም ላይ የገበያ ድርሻዋም እየሰፋ ስለመጣ የጂ-25 ቡና አምራች ሀገራትን በሊቀመንበርነት የመምራት ዕድል ተጎናጽፋለች። በመምራት ላይም ትገኛለች። የአፍሪካ 2063 ስትራቴጂክ የንግድ ምርት ሆኖ እንዲሰየም ለኅብረቱ ጉባዔ ያቀረበችው ጥያቄም ተቀባይነት አግኝቷል።
የአፍሪካ ኅብረት ቡናን ዋነኛ ስትራቴጂክ ሸቀጥ አድርጎ መውሰዱ ከ70 በመቶ በላይ የሚሆነውን በቡና ላይ ኢኮኖሚውን የመሠረተውን የአፍሪካ ነዋሪ ከመጥቀሙም ባሻገር ኢትዮጵያን የመሳሰሉ ቡና አብቃይ ሀገራት የተፈጥሮ ሃብታቸውን በአግባቡ እንዲጠቀሙ የሚያነሳሳ ነው።
ኢትዮጵያ አሁን ላይ በቡናው ዘርፍ ያሳየችው እምርታ በእጅጉ የሚያበረታታ፤ እንደ ሀገር ተግባራዊ ያደረገችው ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ በየዘርፉ ትርጉም ያለው ውጤት እያመጣ መሆኑን በተጨባጭ ማሳያ ነው። ይህም ሆኖ ግን ሀገሪቱ የቡና መገኛ ከመሆኗ እና ተወዳጅ የሆኑ የቡና ዝርያዎች መገኛ ከመሆኗ አንጻር ለዘርፉ ከዚህ በላይ ትኩረት ከተሰጠው በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ውስጥ የሚኖረው ድርሻ ከዚህም የበለጠ እንደሚሆን ይታመናል!
አዲስ ዘመን ጥቅምት 6/2017 ዓ.ም