የናይል ውሃን በፍትሐዊነት ለመጠቀም ኢትዮጵያን ጨምሮ አብዛኞቹ የተፋሰሱ ሀገራት ረጅም ዓመታትን ያስቆጠረ እልህ አስጨራሽ ጥረት ሲያደርጉ ቆይተዋል። ጥረቶቻቸው ከፍ ባሉ ፈተናዎች ውስጥ አልፈው ዛሬ ላይ ታሪካዊ የተባለ የስኬት ምዕራፍ ላይ ደርሷል፤ የናይል ወንዝ የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት ወደ ትግበራ ተሸጋግሯል ።
የናይል ወንዝ ውሃ የተፋሰሱ ሀገራት ሕዝቦች የጋራ ሀብት ነው፤ ይህን ሀብት በፍትሐዊነት ለመጠቀም የሚደረግ የትኛውም አይነት ጥረት በዓለም አቀፍ ሕግ የሚደገፍ እና የሚበረታታ ነው። ይህም ሆኖ ግን አንዳንድ የተፋሰሱ ሀገራት ሲያራምዱት ከነበረው፤ የብቻ ተጠቃሚነት ፍላጎት አኳያ የወንዙ ውሃ የግጭት እና ያለመተማመን ምንጭ በመሆን የተፋሰሱ ሀገራት ሕዝቦች ቤተሰብነትን ሲፈታተን ቆይቷል ።
በተለይም የቅኝ ግዛት ስምምነቶችን እንደ አስገዳጅ ሕግ አድርገው ለማየት የሚሞክሩት የግብፅ መንግሥታት፤ በተለያዩ ወቅቶች በወንዙ ውሃ አጠቃቀም ዙሪያ የሚያነሷቸው ፍትሐዊነት የጎደላቸው ጥያቄዎች፤ ከሁሉም በላይ አፍሪካውያን ለነፃነታቸው ያደረጉትን የመስዋዕትነት ትግል ብቻ ሳይሆን በትግሉ ያገኙትን ድል የሚያሳንሱ ናቸው።
እነዚህ ሀገራት በአንድ በኩል አፍሪካውያን በጋራ ተቋማቸው/ የቀድሞው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት በኩል የትኛውንም የቅኝ ግዛት ስምምነት ውድቅ ማድረጋቸውን ተቀብለው፤ በሌላ በኩል የተፋሰሱን ሀገራት የውሃ ሀብት ባለቤትነት እና የተጠቃሚነት መብት የሚጻረር ስምምነቶችን ለመተግበር ሲንቀሳቀሱ ቆይተዋል።
ይህ ያልተገባ ዘመኑን የማይዋጅ የወንዙን ውሃ የብቻ ባለቤትነት/ተጠቃሚነት ጥያቄ፤ ላለፉት ስድስት አስርት ዓመታት በተፋሰሱ ሀገራት ሕዝቦች መካከል አለመተማመንን ከመፍጠር ጀምሮ፤ በተለይ ግብፅ በተፋሰሱ ሀገራት የውስጥ ጉዳይ ሳይቀር ያልተገባ ጣልቃ ገብነተት እንድትፈጽም፤ በዚህም በሀገራቱ ሕዝቦች መካከል በጠላትነት መፈላለግ እንዲያቆጠቁጥ አድርጋለች፤ እያደረገችም ነው ።
ባለፉት አስር ዓመታት የናይል ውሃ የግጭት እና ያለመግባባት ምክንያት ከመሆን ባለፈ፤ የትብብር እና የጋራ ልማት ምንጭ እንዲሆን ለማስቻል በተደረገው ጥረት ውስጥ የግብፅ መንግሥት፤ ጥረቱ እንዳይሳካ ብዙ ያልተገቡ መንገዶችን መርጦ ሲጓዝ ቆይቷል፤ ለፍትሐዊነት ብቻ ሳይሆን የወንዙ ውሀ በተፋሰሱ ሀገራት መካከል የፈጠረውን ተፈጥሯዊ ወንድማማችነት በሚያሳንስ መንገድ ሲንቀሳቀስ ተስተውሏል።
የናይል ውሃን የተፋሰሱ ሀገራት በኃላፊነት እና በፍትሐዊነት መጠቀም ከቻሉ ለሀገራቱ ሕዝቦች ትልቅ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ፋይዳ እንደሚኖረው ይታመናል። ሕዝቦቹን የበለጠ በማቀራረብ የጋራ ተጠቃሚነትን መፍጠር ያስችላል። የደበዘዘውን ወንድማማችነት በማድመቅም የሚኖረው አስተዋፅዖ መተኪያ የሌለው ነው።
ፍትሐዊነት ዓለም አቀፍ መርሕ በሆነበት በዚህ ዘመን፣ የቅኝ ግዛት አስተሳሰብ ለወለዳቸው ስምምነቶች ትንሳኤ ለመስጠት የሚደረግ የትኛውም አይነት ጥረት፣ በየትኛውም መመዘኛ ተቀባይነት ሊኖረው የሚችል አይደለም። ዘላቂ የሆነ ጥቅም ያስገኛል ብሎ ማሰብም ለዘመኑ አስተሳሰብ ባዳ መሆን ነው።
ይህ ያልተገባ ጥረት የራስን ሕዝብ አሳስቶ ዋጋ ከማስከፈል የማይዘል እና ሕዝብን እንደ ሕዝብ ላልተገባ የሞራል ስብራት የሚዳርግ ኃላፊነት የጎደለው ተግባር ነው። በትናንት ሙት አስተሳሰብ ላይ ቆሞ የማይጨበጥ ተስፋን የመጠበቅ ያህል የሚታሰብ ነው ።
ይህ አይነቱ አስተሳሰብ በቀደሙት ዓመታት፤ በተፋሰሱ ሀገራት ሕዝቦች መካከል የነበረውን ወንድማማችነት ከማቀጨጭ፤ በሀገራቱ ሕዝቦች መካከል አለመተማመንን ከመፍጠር፤ የጋራ ዕጣ ፈንታቸውን የተሻለ ሊያደርጉ የሚያስችሉ ዕድሎች ከማምከን፤ በተለያዩ ሴራዎች ከመደነቃቀፍ ባለፈ በተጨባጭ ተጠቃሚ ያደረገው ሀገር የለም፤ ወደፊትም ሊኖር አይችልም ።
በዚህ ተጨባጭ እውነታ በመነሳት የናይል ወንዝ የትብብር ማዕቀፍ ስምምነትን ያልፈረሙ ሀገራት አሁን ላይ ቆም ብለው ከፍትሐዊነት ተጎጂ የሚሆን ማንም ሊኖር እንደማይችል በአግባቡ ሊያስተውሉ ይገባል። በተለይም የተፋሰሱ ሀገራት ሕዝቦች ለፍትሐዊነት ካላቸው ከፍ ያለ ማኅበረሰባዊ እሴት አኳያ፤ ራሳቸውን ዘመኑን በዋጀው አስተሳሰብ ገርተው ስምምነቱን በመፈረም ሕዝባቸውን ዘላቂ ተጠቃሚ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።
የወንዙን ውሃ በኃላፊነት መንፈስ በፍትሐዊነት ለመጠቀም የተደረሰበት ስምምነት፤ ትናንት አፍሪካውያን አባቶች ብዙ ዋጋ የከፈሉበት የነፃነት ትግል አንድ አካል ነው። ይህንን እውነታ ለመቀበል ፈቃደኝነት ማጣት የትግሉን አባቶች ውለታ ማሳነስ ፤ የከፈሉትን መስዋዕትነት ትርጉም ማቀጨጭ፤ ከዚያም በላይ አጠቃላይ የሆነውን የቅኝ ግዛት ትግልን ዋጋ ማሳጣት ነው።
አፍሪካውያን ከመቼውም ጊዜ በላይ አሁን የራሳቸውን ዕጣ ፈንታ በጋራ የሚወስኑበት ወቅት ነው። በዚህ ወቅት የቅኝ ግዛት ውሎችን ታቅፎ፤ ከውሎቹ ሙቀት ለማግኘት የሚደረግ ጥረት በዚህ አፍሪካዊ ትውልድ ተቀባይነት የለውም። ይህንን በአግባቡ ማሰብ፤ ለዚህ የሚሆን የፖለቲካ ቁርጠኝነት መፍጠር ስምምነቱን ላልፈረሙ ሀገራት ለነገ የሚባል የቤት ሥራ አይደለም።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የስምምነቱን መፈረም አስመልክተው ባስተላለፉት መልዕክት እንዳመለከቱት፤ ሀገራቱ ለፍትሐዊ የውሃ አጠቃቀም በመገዛት “የናይል ቤተሰብን መቀላቀል ይጠበቅባቸዋል“። ለዚህ ደግሞ ከቀደመው ኢ-ፍትሐዊና የቅኝ ግዛት አስተሳሰብ እና አስተሳሰቡ ከወለደው የተዛባ አካሄድ ራሳቸውን ነፃ ሊያወጡ ይገባል። ይህን ለማድረግና ሕዝባቸውን በፍትሐዊነት መድረክ ከፍ ለማድረግ ከዚህ የሚበልጥ ዕድል መቼም አይኖርም፡፡
አዲስ ዘመን ጥቅምት 5 ቀን 2017 ዓ.ም