እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ በቅርስ ጥናት ትምህርት ክፍል ተባባሪ ፕሮፌሰር ሆነው ሲሰሩ ነበር። በነበረው ግጭት ምክንያት ግን እዚያ ማስተማሩን መቀጠል አልቻሉም። ይሁንና ስራውን ሳያቋርጡ በተለይ ሦስተኛ ዲግሪ የሚያጠኑትን በማማከር ላይ ይገኛሉ። ከዚህ በተጨማሪ የሀገር መከላከያ ሙዚየም ለመክፈት የያዘው እቅድ በመኖሩ ለዛ የሚሆን ጥናትና ምርምር በማድረግ ላይ ናቸው። በቅርቡም በአሜሪካ ለስድስት ወር ያህል ቆይተው እግረ መንገዳቸውንም ለሙዚየሙ የሚጠቅሙ መረጃዎችን ይዘው መምጣታቸውን አመልክተዋል። አዲስ ዘመን ከእኚህ የታሪክ ተመራማሪ ከሆኑ ከፕሮፌሰር አየለ በከሪ ጋር ቆይታ አድርጎ እንደሚከተለው አጠናቅሮታል።
አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ በታሪኳ የአገር ውስጥ ትንኮሳም ሆነ የውጭ አገር ወረራ ያጋጠማት ሲሆን፤ እርሱንም በድል መወጣቷ ይታመናል፤ በአሁኑ ወቅት በአሸባሪው ቡድን ያጋጠማት ጦርነት ቀደም ሲሉ በአገር ውስጥ ካጋጠማት ትንኮሳ ጋር ሲተያይ እንዴት ይገለጻል ከሚለው ቃለ ምልልሳችንን እንጀምር?
ፕሮፌሰር አየለ፡- በጣም ጥሩ፤ ሁሌም ቢሆን ታሪክ ጥሩ መመሪያ ይሰጠናልና ወደ ታሪክ መመለሱ መልካም የሚባል ነው። በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ውስጥ እየተካሄደ ያለው ጦርነት ለጊዜው ትንሽ ጋብ ቢልም ሁለት ዓመት ያህል የፈጀ ነው ብሎ መውሰድ ይቻላል። ይህ ጦርነት ደግሞ የሰው ሕይወት የቀጠፈና በጣም ብዙ ንብረትም ያወደመ ነው። እንዲሁም የአገር ቅርስን ያወደመ በመሆኑ በአገር ውስጥ ከተካሄዱ ጦርነቶች የዚህ አይነቱ ታይቶ የሚታወቅ አይደለም።
አብዛኛውን ጊዜ ተስተውሎ ከሆነ ጦርነቶች በአጭር ጊዜ ውስጥ የሚቋጩ ናቸው። ደግሞም ብዙዎቹ ጦርነቶች አሸናፊውን ከተሸናፊ የሚለይ ይሆናል እንጂ የሚጓተት አይነት ጦርነት በታሪካችን ውስጥ የለም። ይህ ጦርነት ይበልጥ እንዲጋጋም ነዳጅ የሚያርከፈክፉበት መኖራቸውም እሙን ነው።
ሕወሓት በአገር ውስጥ ከዚህ ቀደም የመከላከያ ሠራዊት የሰሜን እዝን በማጥቃት የመጀመሪያውን ጦርነት ፈጸመ። ሁለተኛው ደግሞ ቀጥታ አዲስ አበባ ለመግባት ያደረገውን ጦርነት በምናስተውልበት ጊዜ የሚደግፈው የውጭ ኃይል ስለመኖሩ አመላካች እንደሆነ ግልጽ ነው።
በሰኔ 2013 ዓ.ም በአገራችን የተካሄደው ምርጫ ህዝቡ በታሪኩ ስርዓት ያለው ህጋዊ መንግስት ያቋቋመበት ነው፤ በተለይም ከዚህ በፊት ያልነበረውንና ህዝቡ ለመጀመሪያ ጊዜ በፈቃዱ ዴሞክራሲያዊ የሆነ መንግስት ያቋቋመ መሆኑ ከግምት ውስጥ ባለማስገባት በውጭ እና በአገር ውስጥ ያለው አካል ዴሞክራሲያዊ የሆነውን መንግስት አፍርሰው ብሎም ህልውናችንን አሳጥተው አዲስ የፖለቲካ ስርዓት ለመገንባት፣ አዲስ የአገዛዝ ስርዓት ለመፍጠር እየተካሄደ የነበረ ጦርነት በመሆኑ ነው ጦርነቱ ረጅም የሆነው።
አዲስ ዘመን፡- በኢትዮጵያ ውስጥ ተካሂደዋል ከሚባሉ የእርስ በእርስ ጦርነቶች አሁን አሸባሪው ቡድን ካካሄደው ጋር ሲነጻጸር ከጊዜ መርዘም በዘለለ ሌሎቹ ጦርነት የተባሉ አሊያም ግጭቶች ጋር የአሁኑ እንደምን ይገለጻል?
ፕሮፌሰር አየለ፡- እሱን ማየት ካለብን ጥንታዊት እና ዘመናዊት ኢትዮጵያ በሚል ከፋፍለን ነው። በጥንታዊት ኢትዮጵያ የአገዛዝ ስርዓቱ የንግስና ስርዓት ስለሆነ ለረጅም ጊዜ ሚዛኑን ጠብቆ የቆየ ነው። ንጉስ ሊሆን የሚችል ሰው ማን እንደሚሆን የታወቀ ነው። ንጉስ መሆን ያለበት ሰው ማን እንደሆነ የሚያከራክር ቢሆንም እዛው እርስ በእርስ ተከራክረው የሚስማሙበት ሁኔታ ነው የነበረው።
በወቅቱም ህዝቡ ይቃወም የነበረው የንግስና ስርዓቱን አይደለም። እሱን ህዝቡ ተቃውሞም አያውቅም። የቱንም ያህል በመሃላው ሽኩቻዎች ቢኖሩም እርስ በእርስ ስለሚሆን በራሳቸው መንገድ ፈትተው ዘመኑ ወደሚጠይቀው ትክክለኛ መንገድ እንደሚመጡ ነው የሚታወቀው። በዚህ አይነት አካሄድ የንግስና ስርዓቱ ይቀጥላል ማለት ነው። በእርግጥ በዚህ ውስጥ አባት ልጁን እንዲሁም ልጅ አባቱን ለንግስና ሲባል ሊገድል ይችላል፤ በዚህ አይነት መንገድ ነው ኢትዮጵያ እኤአ እስከ 1974 ድረስ የቆየችው።
ይህ በእርግጥ በራሱ የፈጠረው የፖለቲካ መረጋጋት ነበር። በእርግጥ ይህ ስርዓት ኢትዮጵያን አልጠቀመም፤ ጨፍላቂ ነው፤ አሃዳዊ ነው የሚሉም አሉ። ይሁንና በዚህ ስርዓት ውስጥ የረጅም ጊዜ የእርስ በእርስ መባላት የለም። በዚህ ስርዓት ውስጥ የጎጃም፣ የወላይታ፣ የከፋ እና የመሳሰሉ ነገስታትም ነበሩ። በመጨረሻም እነዚህ ነገስታት አንድ ንጉስ የሆኑት ንጉስ አጼ ምኒልክ ነበሩ። በእነዚህ መሃል የተንዛዛ እና ሰፋ ያለ ጦርነት ግን አልነበረም። በእርግጥ ብዙ ግጭቶች ቢኖሩም፤ እነዛ ግጭቶች ቶሎ የሚበርዱ ነበሩ።
ከዚህ አንጻር ሲታይ የአሁኑ ጦርነት በጣም የተለየ ነው። የመጀመሪያው ጉዳይ እርስ በእርስ ነው፤ ሁለተኛ ደግሞ የውጭ ጣልቃ ገብነት አለ። የአሜሪካ ተቋማት የሆኑና ሚዲያዎቻቸው በሙሉ ሁሉም አንድ ላይ ሆነው የኢትዮጵያን ተቀናቃኝ ደግፈው የቆሙበት ጦርነት ነው ማለት ያስደፍራል። በሕወሓት በኩል ለዚሁ ጦርነት ሲባል ህዝቡን አንቀሳቅሰው፣ መስሪያ ቤትና ትምህርት ቤት ዘግተው እንዲሁም መሳሪያ የያዘውንም ሆነ ያልያዘውን አንድ ላይ አድርገው ቀጥታ በማዘመት ተጠምደው ነበር፤ ጉዟቸው የተገታው ደብረ ሲና አካባቢ ነው ማለት ይቻላል።
ይህ ሁሉ ሊሆን የቻለው የአሜሪካ ድጋፍ በመኖሩ ነው። የአሜሪከ ድጋፍ ባይኖር ኖሮ በምንም አይነት ይህን ማድረግ አይችሉም ነበር። በመጀመሪያ ደረጃ ጀርባውን የወጉትን የሰሜን እዝ የአሜሪካ ድጋፍ ባይኖር ኖሮ አያደርጉትም ነበር። እነርሱ ያሰሉት 80 በመቶ መከላከያ ያለው ትግራይ ውስጥ ስለሆነ እሱን ካጠፋንና ከደመሰስነው አራት ኪሎ መግባት ቀላል ነው ብለው ነበር።
የሕወሓት አመራር ለ27 ዓመታት የያዘውን ስልጣን እንደገና መልሶ በእጁ ማስገባት ይፈልጋል። ለዚህ ምክንያት የሚለውም አማራ በድሎናል፤ ገፍቶናል የሚለውም ጭምር ነው። በጥቅሉ በውስጣቸው የአማራ ጥላቻም ስላለባቸው ነው። ራሳቸውን በሚገልጹበት በየትኛውም አጋጣሚ አማራ እንዲህ አድርጎን፤ በድሎን በሚል ትርክት ነው። ከሌላውም ብሄር ጋር ህብረት ለመፍጠር ሲፈልጉም እነርሱ አማራ እንደበደላቸው በመናገር ነው። ለምሳሌ ከኦነግ ሸኔ ጋር የሚያገናቸው ዋና መሰረቱ የሁለታችንም ጠላት አማራ ነው በሚል ስልት ነው። ይህ ግን የፖለቲካ ስልጣኑን ለመጨበጥ እንዲያስችላቸው የሚጠቀሙበት ስልት ነው ብዬ አስባለሁ።
እንዲያም ሆኖ ይህ ሁሉ አካሄዳቸው የትግራይን ህዝብ የሚጎዳ ነው፤ የትግራይ ህዝቦች ራሳቸው አሁን ያላችሁበት ሁኔታ እንዴት ነው ተብለው ቢጠይቁ ፈተና ውስጥ እንዳሉ ነው መናገር የሚችሉት። ሕወሓት ግን ለዚህ መከራ የዳረገህ አማራ ነው ብሎ ነው ሰበብ የሚደረድረው። አመራሮቹ ማንነታቸው የሚገለጸው በራሳቸው ላይ ተመስርቶ አይደለም፤ ‹‹አንተ ማን ነህ?›› ተብለው ቢጠየቁ፤ መልሳቸው ‹‹እኔ አማራ አይደለሁም›› ነው እንጂ፤ ‹‹እኔ ተጋሩ ነኝ፤ ትግራይ ነኝ›› አይደለም። ይህ አሉታዊ ልዕልና በመባል ነው የሚታወቀው።
ሕወሓት ጦርነቱን ለማጋጋም ብሄርን በምክንያትነት አስቀምጠው ያፋጃሉ፤ ብሔር አላዋጣም ካለ ደግሞ ሃይማኖትን መሰረት አድርገው መፋጀት እንዲኖር ያደርጋሉ። ስሜትን የሚያስቆጡ ነገሮች ላይ አጥብቀው ይሰራሉ። ዋና መሰረቱ ግን ያለውን መንግስት አዳክመው በቦታው ለመቀመጥ ነው።
በእርግጥ ስልጣን ከአንዱ ወደሌላ ማለፍ አለበት። ነገር ግን ያ ስልጣን ዴሞክራሲያዊና ሰላማዊ በሆነ መንገድ ሊገምት በሚችል መንገድ ይተላለፍ የሚል ኃይል አለ። በሌላ በኩል ደግሞ የእኛ ታሪክ የሚያሳየን እሱ አይደለም፤ ጠብመንጃ ይዘን በጠብመንጃ እና በጉልበት ስልጣኑን በእጃችን እናደርጋለን የሚል ኃይል ነው ያለው። ሌላው በእነዚህ በሁለቱ መካከል ያለ ነው።
አዲስ ዘመን፡- የውጪው ኃይልስ ለምሳሌ አሜሪካ የምትፈልገው ምንድን ነው?
ፕሮፌሰር አየለ፡- የውጭው ኃይል በሚታይበት ጊዜ ለምሳሌ አሜሪካ ሃያል ስለሆነች እኛ ደግሞ ያለንበት ጂኦፖለቲካዊ አቀማመጣችን በጣም ጠቃሚ ስለሆነ አሜሪካ በቦታው ላይ የእርሷ የበላይነት እንዲኖር ትፈልጋለች። በዚህ ቦታ ደግሞ ጂቡቲ፣ ሱዳን፣ ሶማሊያ አሉበት። በአካባቢያችን ያሉ አገራት የሚያቋቁሙት መንግስት የአሜሪካ ድጋፍ የሚያስፈልገው አሊያም ከአሜሪካ ጋር ትብብር ሊያደርግ ይገባዋል የሚል አተያይ አሜሪካውያኑ አላቸው።
ምክንያቱም 40 በመቶ የመርከቦች እንቅስቃሴ የሚያልፈው በዚሁ በእኛ ቀጣና ነው። ቦታው በኢኮኖሚም ሆነ ጂኦፖለቲካዊ ጠቀሜታ ያለው ነው። አሜሪካውያኑ በቀጥታ እጃቸውን ኢትዮጵያ ውስጥ ለማስገባት የቻሉት ሕወሓትን ብቻ መርጠው ከሕወሓት ጋር ሆነው መንግስት ለመገልበጥ የፈለጉበት ዋናው ምክንያት በ2012 ኢትዮጵያ፣ ኤርትራና ሱማሊያ ያደረጉት ስምምነት አለ፤ ይህ ስምምነት በአካባቢያችን ያለውን ሀብት ተባብረን እናልማ፤ ጂኦፖለቲካዊ ጠቀሜታውን ደግሞ ለልዕለ ሃያላኑ መተው የለብንም። እኛም ተጠቃሚ መሆን አለብን። የእኛም ይሁንታ በአካባቢው መኖር አለበት በሚል መስራት መጀመራቸው ነው።
ይህን ግን አሜሪካ የተረጎመችው በሌላ ነው። ይህ አካሄዳችሁ በተለይ ቻይናን እንዲሁም ራሽያን ለመሳብ ነው፤ እኛን ደግሞ ወደጎን ለማድረግ የተሸረበ ጥንስስ ነው ብላ ያን ስምምት ለማፍረስ 24 ሰዓት ሰርታለች። በቅርቡም አንደኛው ድካሟ ውጤታማ ሆኖላታል፤ እርሱም የሱማሊያ ክልል ፕሬዚዳንት የነበሩትን መሀመድ አብዱላሂ ፎርማጆን አውርደው ሐሰን ሼህ መሀመድ እንዲቀመጡ ማድረጋቸው ነው፤ እኚህ ሰው ደግሞ የእነርሱ ሰው ናቸው። እንደሚታወቀው ጂቡቲ ላይ ካሉ የውጭ ጦር ትልቁ የአሜሪካ ነው። በዚያ አካባቢ ከአምስት ሺህ በላይ ጦር አላቸው። በዚያ ስፍራ አሜሪካንን ጨምሮ ቻይና፣ ጃፓን፣ ፈረንሳይ ጣሊያን በጥቅሉ የሌለ የለም ማለት ያስደፍራል።
ስለዚህም ነው እነ ኢትዮጵያ፣ ኤርትራና ሱማሊያ ባደረጉት ህብረት ጂቡቲ ያለመካተቷ ምስጢር። ጂቡቲ በጥቅሉ በሚባል ደረጃ ከቁጥጥር ውጪ በመሆኗ ነው በቡድኑ ውስጥ ያላስገቧት። ምክንያቱም ሉዓላዊነቷን ከጥያቄ ውስጥ እንዳስገባች የምትቆጠር አገር ሆናለችና ነው። አሜሪካ ደግሞ ዒላማ ያደረገቻቸው ሶስቱን አገራት ነው።
የሱማሊያ ነገር አሁን ላይ ውስብስብ ነው፤ ለምን ቢባል አዲሱ የሱማሊያ ፕሬዚዳንት ሼህ ሀሰን ከሕወሓት ጋር ይሰሩ ነበር። የእርሳቸው መመረጥ ያስደሰታቸውም ለዚህ ነው።
አዲስ ዘመን፡- እንዴት?
ፕሮፌሰር አየለ፡- ምክንያት ካልን 327 የፓርላማ አባላት ብቻ መርጦ የሰጠው ምርጫ ነው። ህዝቡ ድምጽ አልሰጠም። እነዚህ ድምጽ የሰጡት የፓርላማ አባላት ድምጻቸውን የሰጡት አውሮፕላን ማረፊያ ውስጥ ድንኳን ተጥሎላቸው ነው። በተጨማሪም ምርጫውን ያካሄዱት ከአፍሪካ በተወጣጡ የጸጥታ ሃይሎችና በታንክ ተከበው ነው። የፓርላማ አባላቱን የወከላቸው ጎሳው መርጧቸው ነው እንጂ ህዝቡ መርጧቸው አለመሆኑም ልብ የሚባል ነው። ዋናው ነጥብ 327 ሰው ብቻ ድምጽ ሲሰጥ 327ቱ የጎሳ ውክልና ስላላቸው ወይ በአልቃይዳ አሊያም በአሜሪካ ወይም ደግሞ በአውሮፓ ኅብረት በቀጥታ ተጽዕኖ ስር ሆነው ሊገዙ ይችላሉ የሚለው ነው።
ነገር ግን በዚህ ሁሉ መሃል ማየት ያለብን ነገር በሶማሊያ ውስጥ አንደኛ ስጋት የሆነው አልሻባብ ነው። ሼህ ሐሰን፣ ቀደም ሲል ፕሬዚዳንት በነበሩበት ጊዜ ከአልሻባብ ጋር ተዋግተዋል። እኤአ በ2012 እስከ 2016 ስርዓት ያለው የፖለቲካ አካሄድ የሚባለው ነገር የተጀመረውም በእርሳቸው አገዛዝ ዘመን ነበር። አሁንም ቢሆን አልሻባብ ዓላማው ኢስላሚክ መንግስትን መመስረት ነው። ይህንንም መመስረት የሚፈልገው በሶማሊያ ብቻ ተወስኖ ሳይሆን በቀጣናው ሁሉ ነው። ይህ የአልሻባብ ስርዓት ለሼህ ሀሰንም፣ ለፎርማጆም ሆነ ለኢትዮጵያም አይጠቅምም። ይህ ደግሞ የጋራ የሆነ ነገር ይፈጥራል። አሜሪካንን ልብ ብልሽ እንደሆነ ሰውዬው በተመረጠ ማግስት ወደ ሶማሊያ 500 ወታደር እንደገና ልካለሁ አለች፤ የመላካቸውም ምስጢር አልሻባብን ለመዋጋት ለሚደረገው ሂደት ድጋፍ ለማድረግ ነው።
በእርግጥ አሜሪካ ኢትዮጵያ ውስጥ ያላት ተጽዕኖ ገና ሙሉ በሙሉ እነርሱን በሚያረካ መልኩ አይደለም። አሜሪካ የምትፈልገው ሙሉ በሙሉ የኢትዮጵያ መንግስት ከቻይና ወይም ከራሺያ ወይም ደግሞ ከአውሮፓ ህብረት ያለው ተጽዕኖ ከእኛ መብለጥ የለበትም፤ መምራት ያለብን እኛ ነን የሚል ነው። ይህ በሌላ አገላለጽ ኢትዮጵያን በቅኝ አገዛዝ ውስጥ ማድረግ ነው። ፍላጎታቸው የእነርሱ አገልጋይ መንግስት ማድረግ ነው። ያንን ሊያደርግልን የሚችለው ሕወሓት ነው እንጂ ብልጽግና አይደለም ብለው ደምድመዋል።
ባለፈው የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ለፓርላማ ሲናገሩ የተደመጡት ከአሜሪካ ጋር ያለን ተግባቦት ጥሩ ነው በሚል ነው፤ ያስቸገረን ኮንግረንሱ ነው ብለዋል። ይሁንና ኮንግረንሱ ለብቻው ተጽዕኖ ፈጣሪ መሆን አይችልም። በተለይ የውጭ ጉዳይን በሚመለከት ውሳኔው የኋይት ሃውስ ነው። ስለዚህ የኢትዮጵያ መንግስት ከኋይት ጋር ያለውን ግንኙነት እያሻሻለ እስከሄደ ድረስ ችግር የለውም።
አዲስ ዘመን፡- በኢትዮጵያ፣ ኤርትራና ሱማሊያ መካከል የተደረገው ስምምነት የአሜሪካ ከሕወሓት ጋር ባላት ትስስር የተነሳ ምን ያህል ጫና ውስጥ ይወድቃል?
ፕሮፌሰር አየለ፡– እንዳጋጣሚ ሆኖ ያንን ውል ሲያደርጉ የተፈራረሙት መሪዎቹ ብቻ ናቸው። ወደሕዝቡ ዘንድ እንዲሁም ፓርላማም አልደረሰም። በእርግጥ ኢትዮጵያና ኤርትራ ውሉን ወደጎን የሚያደርጉበት ምንም ምክንያት የላቸውም። እንዲያውም አሜሪካ ተጽዕኖዋን በጣም በምታበረታበት ጊዜ ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር ወዳጅነቷን ታጠናክራለች የሚል እምነት ነው ያለኝ። ምክንያቱም አንደኛ ከራሽያ ጋር ውል ተፈራርመዋል። ሁለተኛ ደግሞ አሁን ባለው የፖለቲካ ሁኔታ ኤርትራ እንደበፊቱ ለብቻዋ ልትቀመጥ አትፈልግም።
አዲስ ዘመን፡- ሕወሓት ጦርነት ለመጀመር ነጋሪት እየጎሰመ ስለመሆኑ ይነገራል፤ ይህ አካሄዱ በህዝብ ስም መነገዱን አመላካች ነው እንጂ ከበባው ወይም ድጋፍ ማጣቱ ብቻ አይመስልምና እዚህ ላይ ምን ይላሉ?
ፕሮፌሰር አየለ፡- ሕወሓትን ወደ ጦርነት እንዲገባ የገፋፋው አንዱ አሜሪካ ድጋፍ ስላሳየችው ነው። አሜሪካንን የሚያክል ኃይል የሚደግፈው ከሆነ መኪና እርዳታ ይዞ አልገባም ይላሉ፤ መድሃኒት አልቀረበም ሲሉ ያማርራሉ። ከዚህ ሌላ እኛ በማናውቀው ቴክኖሎጂ አማካይነት ደግሞ ድጋፍ ሊያገኙ ይችላሉ። ስለዚህ ከበባውም ድጋፍ ማጣቱም አይመስለኝም። ከበባው ሐሰት ነው። በህዝብ መካከል ምንም ጥላቻ የለም። እነርሱ የፈጠሩት ችግር እንጂ። በመሆኑም ከበባ ያሉት ከእውነት የራቀ ነው። ከዚህ በፊት መከላከያ መቀሌ ሲገባ የተቋረጠውን መብራት፣ ውሃና መሰል አገልግሎት ለማስተካከል በተገኙ ባለሙያዎች ላይ በተለይ ከመቶ በላይ የሆኑ የኤሌክትሪክ ሠራተኞች ተገድለዋል። የቴሌም ሆነ የውሃ ክፍል ሠራተኞች ተገድለዋል።
በእርግጥ አሁን አሁን ሕዝቡ አመራሩ የራሱን ስልጣን ለማስቀጠል ደፋ ቀና ማለቱን እየተረዳ መጥቷል። አመራሩ ደግሞ ዓላማው መንግስትን ደካማ በማድረግ ቦታውን ለመያዝ ነው። ሕወሓት የአሜሪካ አገልጋይ ሆኗል። አሜሪካም ከፊት ከፊት ሆና እየረዳችው ነው። የአሜሪካንም ዓላማ ሕወሓት የሚባል ድርጅት ወይ ኢትዮጵያ እንዲበታተን አሊያም ስልጣኑን ይዞ የእነርሱ ተላላኪ እንዲሆን ነው። የኢትዮጵያ መንግስት ደግሞ አሜሪካንን አልፈልግም ብሎ አልተወም፤ ከአንዱ ጋር ብቻ መለጠፉን ስላልመረጠ ቻይናንም ራሽያንም ቀርቦ እየሰራ ነው። አልሻባብን ለመውጋት ከአሜሪካ ጋር ይተባበራል። ለሕወሓት ግን ጦርነት ለማካሄድ እውነተኛ የሆነ ምክንያት መኖር አለበትና የእርሱ ምክንያት ሚዛን የሚደፋ ሆኖ አልተገኘም። ጦርነት አፍራሽ መሆኑን በአግባቡ የተረዳ አይመስለኝም፤ ይልቁንም የሕወሓትን ስግብግብነት ነው የሚያሳየው። ከአሜሪካ በሚሊዮንና በቢሊዮን የሚቆጠረውን ብር ነው ያዩት እንጂ ጦርነት የሚያስከትለውን ፈተና አልተረዱትም።
ሕወሓት በአንደኛው እና በሁለተኛው ጦርነት አልተሳካለትም፤ እንደገና ግን ለሶስተኛ ጦርነት እየተዘጋጀ ነው፤ ይህን ሲያደርግ ህዝቡ አሁንም መከራ ውስጥ መኖሩን እያወቀ ነው። ይህ የሚያሳየው በፊትም ቢሆን ሲያሳድዱ የነበረው የራሳቸውን ጥቅም ነው፤ አሁንም እያደረጉ ያለው ይህን ነው ማለት ይቻላል። ለሕወሓት ጥፋት አሜሪካ ደግሞ ተጠያቂ መሆን አለባት፤ ምክንያቱም አሜሪካ ባታበረታታቸው ኖሮ የዚያን ያህል ጥፋት ለማጥፋት ችሎታው አይኖርም ነበር።
አዲስ ዘመን፡- ማን ነው አሜሪካንን ጥፋተኛ ነሽ ሊላት የሚችለው?
ፕሮፌሰር አየለ፡– ልዕለ ኃያል ናት በሚል ብቻ ጥፋተኛ ነሽ ላትባል አትችልም። ሌላው ቢቀር የሰራቻቸውን ጥፋቶች በሰነድ መልክ ታሪክ እንዲያወሳው ጠቅሶ ማለፍ ግድ ይላል። በቅርቡ ያስተዋልነው ጉዳይ አለ። ሲነኳቸው እሪ የሚሉ አውሮፓውያኑም ሆኑ ሌሎች፤ ራሺያና ዩክሬን ወደጦርነት ሲገቡ የኃይል ሚዛናቸው ምን ያህል ውስን እንደሆነ ለማየት በቅተናል።
እነርሱ ለመኮርኮም የሚቸኩሉት እንደኛ ገና በማደግ ላይ ያሉ አገሮችን ነው። አሁን ግን የዩክሬንና የራሽያ ጦርነት በመኖሩ ትንሽ ፋታ ሰጥቶን ሰንብተናል የሚል እምነት አለኝ። ሕወሓትም ምቹ ሁኔታን የመጠቀም የቀደመ ልምድ ያለው እንደመሆኑ አሁንም የሕዝቡን ረሃብ መሰረት አድርጎ ነው ለጦርነት ሲደራጅ የሚስተዋለው። መኪና ወደመቀሌ እንዳይገባ የማድረጉ ምስጢር ሁሉንም ነገር እኛ መቆጣጠር አለብን ከሚል የመነጨ ነው።
በእርግጥ ቀደም ሲል መበደሉና መዋረዱ ምርር ብሏቸው ወደትግል የገቡ እውነተኛ ታጋዮች እንደነበሩ የሚካድ አይደለም። የሕዝቡ ጥያቄ የእኔም ጥያቄ ነው በሚል ወደትግል የገቡ እንደነበሩ ይታወቃል። በዚህም ብዙ መስዋዕትነት የከፈሉ ታጋዮች ነበሩ። ነገር ግን አሁን እሱ ግንባር ራሱን ትራንስፎርም አድርጎ የጥቂቶች መጠቀሚያ ሆኗል። ለዚህም ነው አመራሩ ሊያሸንፈው ወደማይችለው ጦርነት ውስጥ ለመግባት የሚቋምጠው። ዋና ግቡም ራሱን የመጀመሪያ ተጠቃሚ ለማድረግ ነው። ከዚህ በተጨማሪ ይህ ቡድን የትኛውንም የተቀደሰ ቦታ ሆነ መሰረተ ልማትንና ቅርሶችን ማጥፋት ዓላማው ነው።
አዲስ ዘመን፡- በኢትዮጵያና በሱዳን መካከል የሚስተዋል የድንበር ውዝግብ መኖሩ ይታወቃል፤ ይህ ከአሸባሪው ቡድን ጋር አንዳች የተያያዘ ነገር እንዳለ ያመላክት ይሆን?
ፕሮፌሰር አየለ፡– እርግጠኛ ነኝ ሱዳን ይህን የድንበር መግፋት ሁኔታዋን ካላቆመች በእሳት እንደመጫወት ነው የሚቆጠርባት። አንደኛ የእኛን መሬት ነጥቀዋል፤ የነጠቁት ደግሞ እኛ ጦርነት ላይ ሆነን ነው። ይህን ጊዜ ያሰሉት እነርሱን ተጠቃሚ ሊያደርጋቸው በሚችል ሁኔታ ነው። ሁለተኛው ስሌታቸው እኛን ተንኩሰውን የአገር ውስጡን ጦርነት ትተን ወደእነርሱ ፊታችንን እንድናዞርና ሕወሓት አራት ኪሎ እንዲገባም ጭምር ነበር። በወቅቱ መንግስት የወሰነው ውሳኔ ትክክል ነው። ጉዳዩ ምንም እንኳ ከበድ ያለ ቢሆንም በዚህ ስሜታዊ ሆኖ ወዳልተገባ ተግባር አለመግባቱ በሳልነቱን የሚሳይ ነው። ነገር ግን መሬቱን እኛ በምንፈልግበት ጊዜ የግድ የምናስመልሰው ይሆናል። ሱዳንና ሕወሓት የሚያደርጉት ቅንጅት ደግሞ የአሜሪካንን ፖሊሲ ለማራመድ ነው። አሜሪካም ብትሆን ፍላጎቷ ኢትዮጵያ በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካና በሚሊታሪ ጥገኛ አገር ሆና እንድትቀጥል ነው።
አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ እያራመደች ያለውን ዲፕሎማሲያዊ እንቅስቃሴ እንዴት ያዩታል?
ፕሮፌሰር አየለ፡- የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ ደካማ ነው፤ ትልቁ ክፍተታችን እዛ ላይ ነው የሚለውን ሐሳብ አልጋራም፤ አልስማማበትም። ለምሳሌ በጣም ባለብሩህ አዕምሮ የሆኑ በግል የማውቃቸው ዲፕሎማቶች አሉን። ታሪካችንም የሚያሳየው ይህንኑ ነው።
በጣም የሚያስገርመውን ነገር ላስታውስሽ፤ እንደባለፉት ጊዜያት አንዲትን በማደግ ላይ ያለችንና ወደ እድገት ጎዳና የገባችን አገር በመቃረን የተቆመበት ጊዜ የለም ብዬ በድፍረት መናገር እችላለሁ። እኔ በየቀኑ በዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ሲነገሩና ሲሰበኩ የነበሩ ጉዳዮችን ዝርዝር ይዣለሁ። ለምሳሌ ኒዮርክ ታይምስ ኢትዮጵያን በተመለከተ በየቀኑ አርቲክል ያወጣ ነበር። አልጀዚራም ሆነ ሌሎቹ ሁሉ እንዲሁ ሲያደርጉ ነበር።
ከሚዲያዎቹ በተጨማሪ ደግሞ ከኢትዮጵያ ጋር ምንም አይነት ጥላቻ የሌላቸው አገሮች እንዲሁ ከኢትዮጵያ በተጻራሪ ቆመዋል። እንደ አየርላንድ፣ ፊንላንድ ሌላው ቀርቶ ዩክሬን፣ ኢስቶኒያ አይነት ሃገሮች ሁሉ እንዲሁ ነበሩ። ሌላው ቀርቶ በጣም ቅርባችን ናቸው የምንላቸውና እዚሁ ቤተክርስቲያን ያላቸው እነ አርሚኒያ በሙሉ ከአሜሪካ ጎን ቆመዋል። ሀገራችን እንድትበታተን ሁሉም የየራሳቸውን ሚና ተጫውተዋል።
ይህ ሁሉ ጫና ኢትዮጵያ ላይ ሆኖ አገራችን ግን ይህንን የከፋ ጊዜ በጥበብ ከመወጣት በላይ ምን አይነት ዲፕሎማሲ ነው ያለው። ሌላው ቀርቶ በህዳሴ ግድባችን ላይ የነበረውን ጫና ጥበብ በተሞላበት ዲፕሎማሲያዊ አካሄድ ማለፍ መቻልን የመሰለ ነገር ምን አለ። የተለያዩ አጣብቂኞች ውስጥ በገባን ጊዜ ሁሉ እንደየጉዳዩ አይነት በበቂ ሁኔታ ሊያሻግር የሚችል ዲፕሎማሲያዊ አካሄድ በመጠቀም እዚህ ደርሰናል። ስለዚህ በእነርሱ አካሄድ ቢሆን ኖሮ ፍርክስክሳችን ይወጣ ነበር፤ ግን አልሆነም፤ ያልሆነው ደግሞ ዲፕሎማሲያዊ አካሄዳችን ተሽሎ በመገኘቱም ጭምር ነው።
አዲስ ዘመን፡- ፕሮፌሰር ከልብ አመሰግናለሁ።
ፕሮፌሰር አየለ፡– እኔም አመሰግናለሁ።
አስቴር ኤልያስ
አዲስ ዘመን ግንቦት 22/2014