የፋሽን ዋንኛ መገለጫ ከሆኑ ጉዳዮች አንዱ ወቅታዊነቱ ነው። ወቅትን እየጠበቁ ሽክ ማለት፣ የአየር ሁኔታንና ተለምዷዊ ጉዳዮችን በማገናዘብ በፋሽን መድመቅ የዘመነኞች የተለመደ ተግባር ነው። እከሌ ፋሽን ተከታይ ነው፣ እገሊት ከፋሽን ጋር ቅርበት አላት የሚባልላቸው ግለሰቦች ወቅትንና ሁኔታን ያገናዘበ አልባሳትን በማዘውተራቸው ነው።
ወቅትን እየጠበቁ ሽክ! ማለት ዛሬ ላይ በስፋት ተለምዷል። ዘመነኞች የዘመናቸውን ግኝቶች፣ ቴክኖሎጂ የፈጠረላቸውን ጥበብ ተጠቅመው በሁሉም የአየር ንብረት ውስጥ በምቾት ሽክ ብለው መታየት እንዲችሉ የሚያደርጓቸውን አልባሳትና መጫሚያዎች ይጠቀማሉ። እንደ አየሩ ጸባይ ለብሶ ማጌጥና መዘነጥ ዛሬ ላይ በብዙዎች ዘንድ ተለምዷል። የሚዘወተር ተግባርም ነው። የክረምት ወቅትን ደረብረብ አድርገን ብርዱን የተከላከልንበት ወፍራም ገበር ያለውና ሙቀትን የሚጠብቅ ልብስ ክረምቱ አልፎ የፀደይ ወቅት ብቅ ሲል መቀየር ያስፈልገን ይሆናል። ይህንን ማድረጋችን ባናውቀው እንኳን ከፋሽን ባህሪያት አንዱን በመተግበራችን ፋሽን ተከታይ ሊያደርገን ይችላል።
ፋሽን ሶስት መሰረታዊ ጉዳዮች ባሟላ መልኩ ሲገኝ ተቀባይነቱ ከፍ እንደሚል ይነገራል። የተጠቃሚዎች ምቾት ውበትንና ዲዛይን ለፋሽን ዋንኛ ጉዳዮች ናቸው። የዘርፉ ባለሙያዎች የሚስማሙት እነዚህ ሶስት መሰረታዊ ጉዳዮች ፋሽንን ፋሽን የሚያደርጉ መሆናቸውን ነው። እነዚህ ሶስት መሰረታዊ ጉዳዮች ደግሞ ሌላ ወሳኝ ጉዳይ ታሳቢ አድርገው ይበጃሉ። እነዚህ መሰረታዊ ጉዳዮች ከሚገኙበት ወቅት ጋር ካልተጣጣሙ የፋሽን ሙሉዕነትን እንደሚያጎድሉ የምትናገረው ዲዛይነር ዳናይት ሳህሉ፤ ወቅት ወይም ዘመን ከፋሽን ጋር ያለውን ከፍ ያለ ቁርኝት ታብራራለች። ከሶስት ዓመት በላይ በፋሽን ዲዛይነርነት ከሁለት ዓመት በላይ ደግሞ በሜካፕ አርቲስትነት ሙያ ለቆየችው ዳናይት ፋሽን ከወቅት ጋር የማይነጣጠል አንዱ በአንዱ ውስጥ የሚከሰትና የተሳሰረ መሆኑን ትገልፃለች።
ሰው ዘመኑን ይመስላል። ይህ ፋሽን የዚህ ዘመንና ወቅት ነው፤ ያኛው ደግሞ የዚያኛውን ዘመን ያስታውሰናል የምንለው በጊዜና በሁነት ውስጥ ተከስቶ ያለፈና የተለወጠ ሂደት በመኖሩ ነው። ድሮ አባቶች የፈሸኑበት ተነፋነፍ በዚያ ዘመን አምረው ደምቀው ‘ዋው’ የተሰኙበት ነበር። ዛሬ የዚህ ዘመን ወጣት አንስቶ ቢለብሰው ምን አልባትም ያን ዘመን ለማሳብ ለበሰው አልያም ታሪክን ለማውሳት አጠለቀው ቢባል እንጂ ከዘመኑ ጋር ስለተላለፈ በተመልካቾች አልያም በዚህ ዘመን ወጣቶች ብዙም ትኩረት ላይስብ ይችላል። የዛሬ ሲኪኒ ሱሪዎችን አልያም አሁን ላይ በወጣቶች የሚዘወተሩ አለባበሶችን ወደ ኋላ መልሰን ለአባቶች የማቅረቡ እድል ቢገጥመን የሚሰጡት አስተያየት ያልተጠበቀ ሊሆን ይችላል።
ከላይ የተገለፁትና ፋሽንን ፋሽን ከሚያሰኙት ጉዳዮች በተጨማሪ በፋሽን እሳቤ ውስጥ ታሳቢ የሚደረገው ወቅታዊነት የፋሽን ትልቁ ጉዳይ ነው። ለክረምት ዲዛይን የተደረገ በጋ ላይ ምቾት ሊፈጥር ከቶም አይችልም። በጋ ላይ ሊለበስ በፍካቱ የተመረጠ አልባስ ክረምት ላይ በዝናብና በጭቃ ለመልበስ ይቸግር ይሆናል።
ለፋሽን ቅርብ የሆኑ ባለሙያዎች የፋሽንን ትርጓሚ ከዚህ ባያርቁትም ከዘመኑ ጋር የታረቀ ጊዜውን የሚመስል፣ ተለብሶ የሚያምር፣ ለለባሹ ምቾት የሚሰጥ አለባበስ ሁሉ ፋሽን እንደሚሰኝ ይገልፃሉ። ዲዛይነር ዳናይት ሳህሉ የፋሽን ትርጓሜው ሰፊና ጥልቅ እንደሆነ ትገልፃለች። አንድ ልብስ ወይም መገልገያ ፋሽን የሚያስብለው ግን የተገኘበት ዘመንና በተጠቃሚዎች ተቀባይነት ማግኘቱ ዋንኛው ጉዳይ እንደሆነ ታስረዳለች። መገልገያው አልያም ልብሱ ፋሽን የሚያሰኘው ደግሞ ከላይ በተገለፁ ሶስት ዋንኛ ጉዳዮች መለኪያነት መሆኑን ታስቀምጣለች።
ሰው በተገኘበት ዘመን ላይ የሚገኝን የአለባበስ ባህል እና ስርዓት ተከትሎ አካባቢውንና ማህበረሰቡን መስሎ በብዙዎች የተመረጠና የተወደደ እንዲሁም ምቹ የሆነ የፋሽን ግብዓትን ይጠቀማል። ይህ ደግሞ ይሰፋና በብዙዎች የሚዘወተር ይሆናል። ያኔ የወቅቱ ፋሽን ሆኖ ይተገበራል፤ ተቀባይነትም ያገኛል። ወቅቱን ጠብቀን የምንጫማው አልያም ገዝተን የምንለብሰው ልብስ አስበን ወይም በአጋጣሚ ብናደርገው መለኪያውን በማሟላቱ ፋሽን ይሰኛል፤እኛም የፋሽን ተከታዮች አልያም ተጠቃሚዎች ሆንን ማለት ነው።
የፋሽን ዲዛይነሯ ሀና መከተ የፋሽንና ዘመን ቁርኝትን እንዲህ ትገልጸዋለች “ፋሽን ሊሰኝ የሚችል አልባስ ወይም መገልገያ የሆነ ዘመን ላይ የተወደደና ፋሽን ተደርጎ በብዙዎች የተወደደን በሌላኛው ዘመን ላሉ ፋሽን ተከታዮች እጅጉን የሚያስገርም ሊሆን ይችላል”። ምክንያቱም ፋሽን ሲፈጠር ዘመንና የማህበረሰቡን አጠቃላይ ሁኔታ መሰረት አድርጎ መሆኑ ታስረዳለች። ፋሽን ከዘመን ጋር የተገናኘ እሳቤና ትግበራ ውጤት መሆኑንም ታምናለች። ለዚህ ነው ብዙውን ጊዜ አልባሳት ላይ አስተያየት ሲሰጥ “ይህ እኮ ፋሽኑ አልፎበታል” እየተባለ በብዙዎች የሚነገረው። ይህ ነው የፋሽን ወቅታዊነት ትልቁ ማሳያም። ፋሽን ከተገኘበት ዘመን እና የአየር ንብረት ጋር ታርቆ ካልቀረበ ቀጣይነቱ ጥያቄ ውስጥ ይገባል።
ወቅታዊነት የፋሽን ዋንኛ ባህሪው ነው። ለዚህም ነው ፋሽን የተገኘበት ዘመን አሻራ ሆኖ፤ የተፈጠረበትና የተዘወተረበት ጊዜ ማሳያ ተደርጎ የሚወሰደው። አንድ ወቅት ላይ የነበረ ፋሽን ያንን ወቅት ተሻግሮና ተረስቶ ከዘመናት በኋላ ፋሽንነቱ ያልፍና በሌላኛው ዘመን “ያኔ ይዘወተር የነበረ ” ተብሎ ፋሽኑ እንደ ታሪክ ይነገራል። ለዚህም ነው የፋሽንና ዘመን መተሳሰር የአንድ ሳንቲም ሁለት ገፅታ ሆኖ ጎልቶ የሚታየው።
ፋሽን ሲታስብ ከንድፍ ጀምሮ ፋሽኑ የተፈጠረበት ዘመን የማህበረሰብ አስተሳሰብና ባህል፣ ፋሽኑ የተፈጠረበት ወቅትና ቴክኖሎጂ፣ የማህበረሰቡ ወይም የሆነ ቡድን ምርጫና የአየር ሁኔታን መሰረት ያደርጋል። በተለይም ቦታ፣ ጊዜና የአየር ሁኔታ ለፋሽን አልባሳት ዕውን መሆን ወሳኝ ቅድመ ሁኔታዎች ሆነው ይቀመጣሉ።
ፋሽኑ ልብስ ቢሆን ባለሙያው ከዘመኑ ሰዎች ፍላጎትና ተለምዶ በተጨማሪ በምን አይነት ቦታ ላይ ይለበሳል? የሚለው ጉዳይ ያሳስበዋል። ዘወትር፣ የበዓል ቀን አልያም ሁነቶችን መሰረት ሲያደርግ በምን አይነት ጊዜና ወቅት የሚለው ደግሞ ቀን፣ ማታ፣ፀደይ፣ በጋ ክረምት የመሳሰሉት እንደ አየር ንብረቱና ወቅቱ የሚለበሱትን ልንጠቅስ እንችላለን። ይህን ባገናዘበ መልኩ ተዘጋጀ ፋሽን ሁለንተናዊ የፋሽን መሰረታዊ ጉዳዮች አሟልቷልና ፋሽን ይሰኛል። ይህም ከዘመን ጋር የታረቀ በተገኘበት ዘመን የተወደደ ፋሽን ሆነ ማለት ነው።
ተገኝ ብሩ
አዲስ ዘመን ግንቦት 22/2014