ዛሬ ወቅታዊ ከሆኑ ጉዳዮቻችን መካከል አንዱ የሆነውን የኑሮ ውድነት በማስመልከት ʿሀገርና ታማኝ ልቦች ስል በአዲስ ሀሳብ መጥቻለው። ጽሁፌን በጥያቄ መጀመር እፈልጋለው ‹ለእናንተ ኢትዮጵያዊነት ምንድነው? በዚህ ታላቅ ጥያቄና መልስ ውስጥ ራሳችሁን አስቀምጣችሁ ተከተሉኝ። ሀገር የታማኝ ልቦች ነጸብራቅ ናት። ከጥንት እስከዛሬ ኢትዮጵያን የሳሉ እጆች ክፉ ሆነው አያውቁም። ኢትዮጵያን የደገፉ ክንዶች ራስ ወዳድ ሆነው አያውቅም። ኢትዮጵያዊነት ርህራሄ ነው። አለም ላይ ስለሌላው የሚያዝኑ ልቦች፣ ስለሌላው የሚያነቡ አይኖች ኢትዮጵያዊ ናቸው። በዚህ ተፈጥሮአዊ ባህሪያችን ውስጥ በርካታ አስቸጋሪ የሚባሉ ጊዜአትን በጋራ አሳልፈናል።
ኢትዮጵያዊነት ሲነሳ ሁሉንም የሚያስገርም አንድ የጋራ እውነት አለን፤ እርሱም ተካፍሎ የመብላት ባህላችን ነው። ለናሙናነት ይሄን አነሳሁ እንጂ ኢትዮጵያዊነት ሲገለጥ አብረው የሚገለጡ በርካታ የአብሮነት ታሪኮች ያሉን ህዝቦች ነን። ይሄ እኔና ሌላውን አለም የሚያስደንቀን ጥልቅ..ምጥቅ እሴታችን ነው። በዚህ ባህላችን ብቻ ከአለም እና ከታሪኳ ልዩዎች ነን። አለም እኔነትን ባስቀደመበት፣ ብቻ መብላትን እንደ ስልጣኔና እንደ ዘመናዊነት በያዘበት በዚህ ዘመን ላይ እኛ ኢትዮጵያዊያን ግን በጋራ በመቆም፣ በጋራ በመብላት የማንነጣጠል ህዝቦች መሆናችንን ስናሳይ ኖረናል..እያሳየንም እንገኛለን።
ይህ በየትኛውም የአለም ክፍል የሌለ የሚያኮራና የሚያስደንቅ ኢትዮጵያዊ መልክ ነው። ይህ ለሰው ልጅ ክብር የሰጠ፣ አንድነትን ያስቀደመ የስልጣኔ አሻራ ነው። ይህ የእኛ ብቻ የሆነ የድንቅ ስርዐት ውጤት ነው። ይህ የኢትዮጵያን ቀደምት ስልጣኔና የአብሮነት መንፈስ የሚገልጥ ሰነድ ነው። ሁሌም እንደምለው ስልጣኔ ራስን ከመውደድና የራስን እውነት ከመቀበል የሚጀምር ነው። ሁሌም እንደምለው ዘመናዊነት ከራስ እውነት ተነስቶ ወደ ሌሎች የሚተላለፍ የአስተሳሰብ ውጤት ነው። እኛ ኢትዮጵያውያን ደግሞ ቀደምት ስልጡን ህዝቦች ስለመሆናችን በርካታ ማስረጃዎች አሉ። ይሄ ሁሉ ባይሆን እንኳን አብሮ መብላታችን፣ አብሮ መቆማችን በደስታና በሀዘናችን ጊዜ መረዳዳታችን ቀዳሚነታችንን ከማሳየቱም በላይ የስልጣኔ ፈር ቀዳጆች እንደሆንን አንዱ አመላካች እውነታ ነው።
አሁንም የጥንቱን ሀያልነታችንን ይዘን እንቀጥል ዘንድ በዚህ ፈታኝ ጊዜ ላይ በመደጋገፍና በመረዳዳት አለኝታነታችንን ማሳየት ይኖርብናል። ኢትዮጵያዊነት የሚያምረው በመስጠት ነው። በመስጠት የከበረች ሀገር በስስት መርከስ የለባትም። አብሮ በመብላት የቆመች ሀገር ለኔ ብቻ በሚል ሴይጣናዊ አስተሳሰብ ልዕልናዋን ማጣት የለባትም። እንዳማረብን በአባቶቻችን የደግነት መንፈስ ወደ ፊት መጓዝ ነው የሚያዋጣን። ይህ ጊዜ በኑሮ ውድነት ህዝባችን የሚሰቃይበት ጊዜ ነው። ያለው በመስጠትና በማካፈል አጋርነቱን ሊያሳይ ይገባል።
ሰው ብዙ እውቀት፣ ብዙ ጥበብ፣ ብዙ ማስተዋል ሊኖረው ይችላል ሌላውን እንደማፍቀር፣ ለሌላው እንደ ማሰብ ግን እውቀት አይኖረውም። ሰው ብዙ በጎ ስብዕናዎች ሊኖሩት ይችላሉ፤ ሀገርን እንደመውደድና ለወገን ተቆርቋሪ እንደመሆን በጎ ስብዕና አለው አልልም። ይህ የታማኝና የእውነተኛ ሰውነት መገለጫ ባህሪ ነው። ሀገራችን ደግሞ ከትላንት እስከዛሬ በዚህ እውነት ውስጥ የኖረች ናት። እኔ መስጠትን የክብር ሁሉ ዘውድ፣ የጥበብ ሁሉ ምንጭ እለዋለው። እኔ በግሌ እንደ ኢትዮጵያዊነት ጥያቄና መልስ አላውቅም..እርግጠኛ ነኝ እናተም አታውቁም። ብዙ እውቀት፣ ብዙ ጥበብ፣ ብዙ ማስተዋል ሊኖረን ይችላል፤ እንደ ሀገርና ሰው፣ እንደ ታሪክና ባህል፣ እንደ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ጥበብና ማስተዋል ግን የለንም..አይኖረንምም።
እንግዲህ ይቺን ነው ኢትዮጵያ የምላችሁ። ይሄን ነው ኢትዮጵያዊነት የምላችሁ። ይሄን ነው ሀገርና ታማኝ ልቦች ስል የማወጋችሁ። ከነገርኳችሁ በላይ የምታውቁት ሀቅ አለ? ከሀገርና ሰው በላይ ምን ጥበብ ምን ልህቀት አላችሁ? ከዚህ እውነት በመነሳት የሰሞኑን ከኢትዮጵያ ባህልና አብሮነት ያፈነገጠውን ሰሞነኛ እውነት ላውጋችሁ። የሰሞኑ የኑሮ ውድነት ያላማረረው ማነው? እርግጠኛ ነኝ ሁላችሁም ተማርራችኋል። ከመማረርም ባለፈ የብዙዎቻችንን ህልውና የፈተነ እንደነበር እኔም እናተም ምስክሮች ነን። ይሄ እንዴት ሆነ? በማን ሆነ? ለምን ሆነ? ብለን ስንጠይቅ መልሱን እናገኘዋለን።
እንደነገርኳችሁ እንደምታውቁትም ኢትዮጵያዊነት ተካፍሎ መብላት ነው። ኢትዮጵያዊነት የታማኝ ልቦች አብራክ ነው። በዚህ እውነት ውስጥ ተወልደንና አድገን ነገር ግን በደጋግ ልቦች መሀል በበቀሉ የክፋት ልቦች የድሮ ጸዐዳ መልካችንን እያጣን ነው። ክፋትንና እኔነትን በለመዱ፤ ሌብነትንና ስግብግብነትን በተማሩ አንዳንድ ነጋዴዎች የጥንት ፍቅራችንን እየተነጠቅን ነው። ራስ ተኮር የሆኑ ወጪት ሰባሪዎች ሆን ብለው የኑሮ ውድነትን በመፍጠር በህዝቡ ላይ ግፍና በደልን እየሰሩ ነው። በተለይ ድሀው ማህበረሰብ በእነዚህ ውሸታምና አጭበርባሪ ነጋዴዎች እየተሰቃየ ያለበት ሁኔታ ጎልቶ ይታያል።
ይሄ ብቻ አይደለም የወቅቱን አስቸጋሪነት እንደ መልካም እድል በመጠቀም ድሀ አስጨንቀው በአቋራጭ ለመበልጸግ የሚሹ ሀላፊነት የማይሰማቸው ነጋዴዎች እንደ አሸን እየፈሉ ነው። ህዝብ ከማገልገል ይልቅ ያልተገባ ትርፍና ጥቅም ለማግኘት በሸቀጦች ላይ ያልተገባ የዋጋ ጭማሬ በማድረግ ጊዜውን ፈታኝ አድርገውታል። ምርት በመደበቅ፣ በማሸሽና ሌሎች ማጭበርበሪያ መንገዶችን በመጠቀም ከመንግስት እውቅና ውጪ በሆነ አሰራር ራሳቸውን ሲጠቅሙና ድሀ ህዝብ ሲበዘብዙ ማየት አዲስ ነገር አይደለም። ወቅታዊውን አለም አቀፍ ችግር እንደ ጥሩ አጋጣሚ በመጠቀም ሀብት ለማጋበስና የኑሮ ውድነትን በመፍጠር መንግስትና ህዝብን ሆድና ጀርባ ለማድረግ እየሰሩ ያሉ የክፉ ልቦች እዚም እዛም ተሰግስገው ይገኛሉ። የነዚህ ግለሰቦች ስውር አላማ የታወቀ ነው፤ እናም በአንድ ላይ ሆነን እኚህን ህገ ወጦች በማጋለጥና ለህግ በማቅረብ የኑሮ ውድነቱን ማስተካከል የሁላችንም ኃላፊነት ነው።
ለዘመናት አብሯቸው የኖረን ህዝብ በማገዝና በመደገፍ በዚህ ክፉ ቀን ላይ ውለታውን እንደመመለስ ዞሮ ጨካኝ መሆን ውለታ ከመብላት ባለፈ ነውረኛ ድርጊት ነው። አብረው የማይኖሩ ይመስል..ይሄ ክፉ ቀን የማያልፍ ይመስል እንዲህ አይነት ያልተገባ ግፍ መስራት ተገቢ ነው ብዬ አላምንም። ይሄ ጊዜ ያልፋል፤ ሁላችንም የምንናፍቀው አዲስ ቀን ይፈጠራል፤ በዚህ የንጋት ዋዜማ ላይ እንደ አባቶቻችን ስርዐት እርስ በርስ መተጋገዝ እንጂ ሆድና ጀርባ መሆን የለብንም። ይህ የኢትዮጵያዊነት መልክ አይደለም። ይህ ከአባቶቻችን የወረስንው የክብር ዘውድ አይደለም። ይህ ነውር ነው። ይህ በሰዎች መከራ ራስን የማኖር ሰይጣናዊ እሳቤ ነው። ይህ ኢትዮጵያዊነትን የሚያደበዝዝ የራስ ወዳድነት ስብዕና ነው። በዚህ ስርዐት ውስጥ አልመጣንው። ይሄን የጭካኔ ተግባር አናውቀውም። ስርአታችን አብሮ መብላት፣ አብሮ መጠጣት ነው። ስርዐታችን ተካፍሎ መብላት ነው፤ ያለው ለሌለው መስጠት ነው። ስርዐታችን እንደ አብረሀም ቤት በራችንን ከፍተን ለደግነት መንገደኛ የምንጠብቅ፣ ርሀብተኛ የምናጠግብ፣ የታረዘ የምናለብስ መሆኑ ላይ ነው። ነውር የምናውቅ ህዝቦች እኮ ነን፤ ይህስ የት ሄደ? ድሀን እንደማስጨነቅ፣ ከድሀ ላይ እንደመውሰድ እኮ ግፍና በደል፣ ሀጢያትና ነውር የለም። አብዛኛው የኢትዮጵያ ህዝብ ደግሞ ድሀ ነው፤ የሰሞኑ የነጋዴዎቻችን ሁኔታ ከዚህ የዘለለ አይደለም።
ለድሀ እየሰጡ እንጂ ከድሀ እየነጠቁ ማደግና መበልጸግ አይቻልም። ለድሀ ቸርነትን እያደረጉ እንጂ በድሀ ላይ በመጨከን ነገን ማየት አይቻልም። እድገት ያለው በመስጠትና በቸርነት ውስጥ ነው። ሀብትና በረከት የሚመጣው ለድሀ ቸርነትን በማድረግ እንጂ ድሀን በማስጨነቅ አይደለም። አካሄዳችንን እናስተካክል። ስራችን በእውነትና በእውቀት ህዝብን ማዕከል ያደረገ ይሁን። እኛ ስንሰጥና ስናካፍል እንጂ ስንዘርፍና ስናታልል አልኖርንም። እኛ በጋራ በመብላት በጋራ በመኖር እንጂ በውሸትና በማጭበርበር ራሳችንን ብቻ ስንጠቅም አልኖርንም። እኛ የሌላውን ጎደሎ በመሙላት ተያይዘን የመጣን ህዝቦች ነን ይሄን ኢትዮጵያዊ እውነት አትሳቱ። በዚህ ክፉ ጊዜ ላይ እንደ ባህላችን ለችግረኞች ልባችንን በመክፈት ይሄን ክፉ ጊዜ በጋራ መሻገር ይኖርብናል። ካልተጋገዝን የምንራመደው የብቻ መንገድ የለም። መንገዶቻችን ሁሉ በጋራ ተራምደን በጋራ የመጣንባቸው ናቸው። በእኔነት ስሜት የምንገነባው የብቻ መንገድ እኛን ከመጣል ባለፈ እርባና የለውም። እንደ አባቶቻችን በጋራ እየበላን በጋራ መኖር ነው የሚያዋጣን። እንደ አባቶቻችን በጋራ ሀሳብ የጋራ ስርዐት መገንባት ነው የሚጠቅመን።
ሰው ሀገር እንደሚፈልግ ሁሉ ሀገርም ሰው የምትፈልግበት ጊዜ አለ። ሀገር ሰው የምትፈልግበት ትክክለኛ ጊዜ ደግሞ አሁን ነው። ለዘመናት በሀገራችን ላይ ተዘባንነን ኖረናል። በህዝባችን ፍቅር ለዘመናት ታቅፈን ሳይበርደን ከትላንት ዛሬን አይተናል። አሁን ጊዜው በአንድነት መንፈስ ሀገር የምናቆምበትና በመረዳዳት መንፈስ ወገን የምንታደግበት ነው። ኮሮና ይዞት የመጣው ብዙ ነገር አለ። ከኮሮና ሳናገግም የሰሜኑ ጦርነት ተከሰተ። በሰሜኑ ጦርነት ተጎሳቁለን ሳይበቃን፤ ተጽዕኖው የኑሮ ጫናችንን ያከበደው የሩሲያና የዩክሬን ጦርነት ተከተለ። በዚህ ሁሉ ውስጥ ነን። ህዝባችን ከመቼውም ጊዜ በላይ በውስጥም በውጪም በተነሱ ችግሮች በኑሮ ውድነት እየተሰቃየ ይገኛል። በዚህ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ በሆነ ሁኔታ ውስጥ ለሚኖር ማህበረሰብ የእኛ ፍቅር፣ የእኛ ደግነት ዋጋው ምን ያክል እንደሆነ ለመገመት አይከብድም። እጆቻችን የሚሰጡበት፣ ልቦቻችን የሚያዝኑበት ሰሞን ላይ ነን። በደግነት ፈጣሪን የምናስደስትበትና የጽድቅ ስራ የምንሰራበት ሰሞን ላይ ነን። እንደ ሀገር ድሀ ነን፣ እንደ ህዝብ ደግሞ ችግረኛ። ከላይ የዘረዘርኳቸው ማህበራዊ ቀውሶች ተጨምረውብን ደግሞ የሚሆነውን አስቡት። እመኑኝ ካልተሳሰብን ይሄን ጊዜ አናልፈውም፤ አዲስ የተስፋ ማለዳ እናይ ዘንድ ልቦቻችንን ለሌላው ማራራት ይኖርብናል።
እንዘን ካልን የምናዝንላቸው ብዙ የማህበረሰብ ክፍሎች አሉ። በኑሮ ውድነቱ ሳቢያ ወርሀዊ ደሞዛቸው የወር አስቤዛ የማይገዛላቸው፣ ቤት ኪራይ ለመክፈል ያልቻሉ ብዙ ወገኖች በዙሪያችን አሉ። መማር እየፈለጉ በብዙ ምክንያት መማር ያልቻሉ፣ መለወጥ እየፈለጉ በአቅም ማነስ ወደ ኋላ የቀሩ ብዙ ናቸው። ለነዚህ ወገኖቻችን አለኝታነታችንን ማሳየት ይጠበቅብናል። ሰው ልቡ ቀናነትን ከተላበሰ የሚሰጠው አያጣም። መስጠት ሁልጊዜ ከኪስ አውጥቶ መስጠት አይደለም። ከኪሳችን ስናጣ ከልባችን የምንሰጠው ብዙ ነገር አለ። ከኪስ ይልቅ የልብ ስጦታ ተቀባይን ይባርካል ብዬ አምናለው፡ ኪሳችን ሲራቆት ብቻ ሳይሆን ኪሳችን በሞላ ጊዜም የልባችን ጓዳ መፈተሸ አለብን እላለው። ጊዜው ኢትዮጵያዊነት በራስ ወዳድነት የሚደበዝዝበት ሳይሆን በመስጠት የሚያብብበት ነው። ከመቼውም ጊዜ በላይ አንዳችን ለአንዳችን የምናስፈልግበት ጊዜ ላይ ነን። ወገኔ እየተራበ እኔ ጠግቤ ባድር ሰውነት ምንድነው? ጎረቤቴ ተቸግሮ እኔ ፍሪዳ ጥዬ ለብቻዬ ብደሰት እምነት፣ እውነት ዋጋቸው ስንት ያወጣል?
እንተጋገዝ..ይሄን ክፉ ጊዜ በመተሳሰብ ማለፍ እንጂ ስር በሰደደ ራስ ወዳድነት የምናልፈው አይደለም። ኢትዮጵያዊነት የተገመደበት ተካፍሎ አብሮ የመብላት ባህላችን ሊጎለብት ይገባል። ራስን ከሌሎች ማግለል ስልጣኔ አይደለም። በር ዘግቶ ለብቻ መብላት ዘመናዊነት አይደለም..ዘመናዊነት ነው ብንል እንኳን ኢትዮጵያዊነት አይፈቅድልንም። እኛ ሀበሾች ነን..አብረን በልተን አብረን የምንሞት። ከእውነታችሁ አትውጡ..ከስርዐታችሁ አትሽሹ..አዲሱ ትውልድ ከእናተ የሚማረው ብዙ ነገር አለና እባካችሁ መልካምነትን ተማሩ። ለድሀ ወገናችሁ የምትቆሙበት..አለኝታነታችሁን የምታሳዩበት ትክክለኛ ጊዜ ላይ ናችሁ። ርህራሄን የምትማሩበት፣ መልካምነትን የምትሹበት ሰሞን ላይ ናችሁ። በዚህ የጭንቅ ወቅት ከመቼውም ጊዜ በላይ ርህራሄአችሁ ያስፈልጋል። በጥቂት ራስ ወዳዶች መልካችን እየወየበ ነው፣ በጥቂት ስግብግብ ነጋዴዎች አንድነታችን እየተሸረሸረ ነው። ወደቀደመ አንድነታችን፣ ወደ ቀደመ ፍቅራችን እንመለስ ዘንድ ከእኔነት መውጣት ግድ ይለናል። ያለዛ ኢትዮጵያ ታዝንባችኋለች..ያለዛ ለተዋችሁት ስርዐት በልጆቻችሁ በኩል ዋጋ ትከፍላላችሁ። ይሄ እንዳይሆን ደጋግ ልቦችን የእኛ እናድርግ።
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)
አዲስ ዘመን ግንቦት 22 ቀን 2014 ዓ.ም