አእምሯችን ነቅቶ ነገሮችን በጥልቀት እንዳን መለከት እንዳናስተውል የሆነ የተያዘብን ነገር ያለ ይመስለናል። ጠበብ ብለን ከአነሱት በታች ሆነናል። ዘር ጎጥ ቀበሌ መንደር እያለን በጥቃቅን ክፍልፋዮች ውስጥ የተቀበርን ስንቶቻችን ነን?። እኔ ዘረኛ አይደለሁም የምንልስ ከኔ ሀይማኖት የሚበልጥ የለም በሚል መታበይ የሌላውን የምንንቅ የምናንቋሽሽ ቤቱ ይቁጠረን። ግን ግን እውነት እንዲህ ተከታትፈን የአንድነት ስማችን ኢትዮጵያ የማትኖር ከሆነ የትኛው የተደበቅንበት ጉሬ ከመጥፋት ያስጥለናል?
ዛሬ ላነሳ የወደድኩት ሀሳብ ለመጠላቱም ለመታረቁም መጀመሪያ ሀገር ሊኖረን ይገባል የሚል ነው። ይህ ማለት አንድ ጦጣ መላ ሰውነቷ ላይ እሾህ ተሰክቶባት እሾኩን ሊለቅሙላት ለመጡት ባልንጀሮቿ መጀመሪያ መቀመጫዬን እንዳለችው ማለት ነው። ለመጣላትም ለመታረቅም፤ ለመደሰትም ለማዘንም፤ ለመሞትም ለመቀበርም መጀመሪያ መቀመጫ ያስፈልገናል። መቀመጫችንን ለማጥፋት የምንሯሯጥ ከሆነ ቁርጣችሁን እወቁ ኢትዮጵያ ሳትድን ማንም አይድንም።
ሀገራችን ፈርሳ፤ ሀገር ጠፍታ ብሄርህ አይድንም፤ ሀገር ሳትኖር ሀይማኖትህ አይድንም፤ እንደ ሰው መቆጠር ቀርቶ ሰው ሆኖ መቆምም ችግር ይሆናል። ስለዚህ ብሄሬን ብቻ አድናለሁ ብለን ከፍ ዝቅ የምንል፤ ሀይማኖቴን መሸሸጊያ አደርጋለሁ ብለን ደፋ ቀና ያለን የምንሰራው ስራ “ልፋ ያለው አንድ እንጨት ያስራል” እንደሚባለው አይነት ስራ መሆኑን አውቀን እንንቃ።
ኢትዮጵያ ሳትድን ኦርቶዶክስ የምትድን የሚመስለንም እንዲሁ ድከሙ ብሎን ነው እንጂ ኦርቶዶክስ ያለ ሀገር ከቶም አትኖርም። ጭራሽ ከሀገር ውጪ ኦርቶዶክስ አትታሰብም። ፕሮቴስታንት ነኝ፤ ካቶሊክ ነኝ እያልን ያደፈጥንም ሁሉ ጠንቅቀን ማወቅ የሚገባን ኢትዮጵያን ሊያጠፋ የመጣ አንተን ልጇን ለይቶ ሊተውህ የሚችልበት ምክንያት እንደማይኖር ነው። ኢትዮጵያ ሳትድን ከቶም የሀይማኖት ነጻነት ቀርቶ እንደ ሰው ቆሞ መኖር የሚታሰብ አይሆንም።
እውነተኛ ኢትዮጵያዊ ሙስሊሞችም ልብ ብላችሁ አስተውሉ። ሀይማኖታችን መደበቂያ ማምለጫ የሚሆነን ጊዜ የሚኖረው መጀመሪያ መቀመጫችንን ለማዳን አንድ ሆነን ስንቆም ነው። ያለበለዚያ አብሮነታችን ውበታችን፤ የመከባበር የሀይማኖት እኩልነት ሀገር ያልናት እኛ ከውስጥ ከተፈረካከስንላቸው እንደ ተራበ አንበሳ ሊውጡን አሰፍስፈው ዙሪያችንን እየዞሩ ያሉ ሀይሎችን ኑ ዋጡን ብሎ እንደመጋበዝ ይቆጠርብናል።
እናም ሀገራችሁ ኢትዮጵያ ዛሬ በመላው አለም ቢሊዮኖች የሚያመልኩትን የእስልምና እምነት በፍትህ እና በእውነት ከመጥፋት የታደጋቸው፤ በዚያን ዘመን የነበሩ ክርስቲያን ነገስታት በሀይማኖት እኩልነት እና ነጻነት የሚያምኑ ስለነበሩ ነው፡፡ እስልምናም ለሽህ ዘመናት በነጻነት በኢትዮጵያ በነጻነት ሲሰበክባትና ሲስፋፋባት የኖረባት ሀገር ስላላችሁ ነው። ዛሬ በመላው አለም ያሉ እውነተኛ ሙስሊሞች ወንድሞች በኢትዮጵያ እና በኢትዮጵያ ሙስሊሞች ታሪክ እንዴት እንደሚኮሩም ልብ ማለት ያስፈልጋል።
እናም እውነተኛ ኢትዮጵያዊ ነኝ የምንል ሁሉ አንድ ብቻ አላማ ይኑረን። በጋራ የምንቆምላትን የሁላችን ማረፊያ መቀመጫ የሆነችውን ኢትዮጵያን እናድን። አንድ ሆነን በተባበረ ክንዳችን ኢትዮጵያን እጃችን ውስጥ ካስገባን በኋላ በሜዳችን ችግራችንን እንፍታ። ኢትዮጵያን በመልመጥመጥ አድናለሁ ብለን እያሰብን ከሆነ ተሸውደናል፡፡ ቆፍጠን ብለን ህዝብና ህዝብ አንድ የሚሆነበት መደላድል መፍጠር ነው የሚያሻን። እውነተኛ ኢትዮጵያዊ የሆናችሁ ሁሉ ኢትዮጵያን ለማዳን በጋራ ቁሙ። አንድ ራዕይ አንድ አቋም ብቻ ይኑረን። እውነተኛ ኢትዮጵያዊ ከሆንን አንድ ሀገር ብቻ ናትና ያለችን እሷን ለማዳን የተቆራረጡ ክፍልፋይ አስተሳሰቦቻችንን ወዲያ ጥለን በአንድ እንጋመድ።
ጊዜ አምጥቶ በኢትዮጵያ ህዝብ መካከል የበተነው የጎሳ ፖለቲካ ለኢትዮጵያ ሰዎች ሁሉ መርገምት ሆኖበታል፤ ለጊዜው ይሄኛው ወይም ያኛው ጎሳ ያሸነፈ ይመስላል እንጂ በኢትዮጵያውያን መካከል ዘላለማዊ ፍጅት የሚያኖር የማይበርድ ቁርሾ ይዞ የሚያስቀጥል ነው። ታዲያ ያለፈ ታሪካችንን ለፍጅት መነሻ ሊሆነን አይገባም፤ ይልቁንም ካለፈው ተምረን የተሻለ አዲስ ታሪክ ልንጽፍ የተገባ ነው፡፡ ይህ እንዲሆን ደግሞ እስኪ ክፍፍሉን አሸንፈን በአንድ እንቁም፤ በቅድሚያም እምዬ ኢትዮጵያችን ትዳን።
የጎሳ ፖለቲካ ፓርቲዎች አብሮ መኖር ካልተቻለ ጎሳዎችን መገነጣጠል ይሻላል እንደሚሉት፤ አለዚያም ምዕራባውያን መንግስታት የራሳቸውን ፍላጎት ብቻ ለማንበር ኢትዮጵያን ሰፋ ብላ ካስቸገረች በእነሱ ፍላጎት መሰረት መገነጣጠል እና አነስ አነስ ያሉ ታዛዥ ሀገራትን መፍጠር የሚለው ስሌትም እንዳይሰራ ለማድረግ እውነት የሀይማኖቶች ደሴት የአማኞች ሀገር የሆነችን ኢትዮጵያ ሀገረ እግዚእብሄር ከአፍ በዘለለ የእውነት ውስጣችን የተተከለውን የጎጠኝነት ሰንኮፍ ነቅለን እናድናት። አባቶቻችን እንደሚሉትም ኢትዮጵያ ቅድስት ኢትዮጵያ ነች።
እናም ምርጫችን ኢትዮጵያዊ የሆንን ቅድስናችንን ተቀብለን፤ የጎሳ ፖለቲካን ስሩን ነቅለን፤ ኢትዮጵያዊነት ማንነታችን ሰገነት ማማ ላይ ማንበር ብቻ በቂ ነው። የተፈጠርነው ተባልቶ ለማለቅ አለመሆኑን ተገንዝበን ፈጣሪ አለም ላይ ሲያመጣን ለተፈጠርንበት ሀሳብ የተመቸን ፈጣሪ ሰውን በመፍጠሩ እንዳይፀፀት የምናደርግ የቅድስት ሀገር ልጆች ቅዱሳን እንሁን። ሌላ ምርጫ የለንም ይህ ካልሆነ ግን እየተቀጣቀጥን አብረን በክፋት እና በጎሰኝነት እየተባላን ከሰውም ከአለምም በታች ሆነህ እየተገዳደልን እየተፋጀን እንኖራለን።
አለበለዚያ ቅድስናችንን አምነን ቅድስት ኢትዮጵያን ጠቅልለን እናድናለን። ያኔ የሁላችን የሆነች አንድ ሀገር ይኖረናል ማለት ነው። እኛ ኢትዮጵያውያን በአንዲት የጋራ ሀገራችን አምነን እንዲሁም የኔ ብሄር ምረጥ የኔ ብቻ አንደኛ የሚለውን አመለካከት ወደጎን ትተን፤ የጎሳ ፖለቲካን ስሩን ቀጥቅጠን አድርቀን ወይም ከስሩ መንግለን በማቃጠል ኢትዮጵያውያን የቀደሙ ነገስታት አባቶቻችን እንዳስተማሩን አንዲት ሀገር ብለን መነሳት ካልቻልን የእውነት ከልቤ ነው የምነግራችሁ በዚህ በመከፋፈል አስተሳሰባችን ሀገራችን ጠፍታ ከቶም ማናችንም አንድንም።
የትኛውም ነገድ የትኛውም ሀይማኖት እረፍት አይኖረውም። ሀገር ሰላሟ ተነስቶ ከገደል አፋፍ ቆማ ተደላድለን የተቀመጥን ከገደል አፋፍ ላይ ካለችው ሀገር ውስጥ ነንና አንድ የሚያደርገንን መንገድ መርጠን ልዩነታችንን አጥበን ሀገራችንን እናድን። ለዚህም ነው፣ “ለፍቅሩም ለጠቡም እስኪ መጀመሪያ ሀገር ትኑር…” የምለው፡፡ አበቃሁ፤ ሰላም!
ብስለት
አዲስ ዘመን ግንቦት 22 ቀን 2014 ዓ.ም