ይህ መጣጥፍ በአውድ/ኮንቴክስት/ ከ«ኢትዮጵያ ታምርት» ጋር ስለሚያያዝና ወቅቱም የግብርና እንዲሁም የአረንጓዴ አሻራ ስለሆነ ተመልሼበታለሁ። ዛሬ በዓለማችን ካሉ 20 ታላላቅ ኩባንያዎች ቀዳሚዎች ከበይነ መረብ / ኢንተርኔት / ፣ መረጃና ሶፍትዌር ጋር ተያይዘው የተፈጠሩ ናቸው። አፕል፣ አማዞን፣ ማይክሮ ሶፍት፣ ፌስ ቡክ፣ አሊባባ፣ ጉግልና ኡበር ዋና ዋናዎቹ ናቸው። የመጀመሪያዎቹ ባለ ትሪሊዮን ዶላር ወረት ኩባንያዎች አፕልና አማዞን ናቸው። የረቂቅ /ስማርት/ ስልኮችና ሌሎች ቴክኖሎጂዎች መፈጠር፤ የሰው ሰራሽ ክህሎት /አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ /፣ የአምስተኛው ትውልድ 5ጂ ወደ አገልግሎት መግባት የዘርፉን እድገት መጨረሻ ከፍታ ላይ ያደረሰው ይመስላል። ገበያው በአጭር ጊዜ ውስጥ ይጥለቀለቃል / ሳቹሬት / ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል። ወደፊት የዚህ ዘርፍ እድገት እየቀነሰ ቦታውን ለግብርና ኢኮኖሚ ይለቃል የሚሉ ትንበያዎች እየወጡ ነው።
ይህን ተከትሎ መጪው ዘመን ለግብርና ኢኮኖሚው ብሩህ እንደሆን እየተለፈፈ ይገኛል። የሰፋፊ የእርሻ መሬቶች፣ የተፈጥሮ ሀብት፣ የሰፊ ገበያ፣ በመልማት ያለ የሰው ኃይል፣ …፤ እምቅ አቅም potential ያላት አህጉር መሆኗ አይን ማረፊያ አድርጓታል። እ.አ.አ በ2050 የዓለም ሕዝብ ቁጥር 10 ቢሊዮን ይደርሳል ተብሎ ተተንብዮአል። የቻይናና የሕንድ የመሸመት አቅም መጎልበት ጋር ተያይዞ የሚያሻቅበው የምግብ ሸቀጦችን ፍላጎትን ለማርካት፤ በአመት ከ100 ትሪሊዮን ዶላር በላይ የሚያገላብጠው ግብርና የዓለም ኢኮኖሚ መሪነትን በቅርብ ከኢንፎርሜሽን ኮሚኒኬሽን ቴክኖሎጂ ይረከባል ተብሎ ስለሚጠበቅ፤ ትኩረቱ ባልታረሰው የአፍሪካ ድንግል መሬት ላይ መሆኑ ዘመኑን ይዋጃል። አገራችን ለግብርናውና ለአረንጓዴ አሻራ የሰጠችው ትኩረት ትክክለኛና ስትራቴጂካዊ ውሳኔ ነው።
የዓለም ሕዝብ ቁጥር እድገት አሁን ከሚገኝበት ሰባት ነጥብ አምስት ቢሊዮን፤ በክፍለ ዘመኑ መጨረሻ 11 ቢሊዮን ይደርሳል ተብሎ መተንበዩ፤ በዓለም በተለይ በቻይና፣ በሕንድና በሌሎች ታዳጊ አገራት እየተመዘገበ ካለው ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት ጋር የምግብ ፍላጎት እጅግ ጨምሯል። እድገቱን ተከትሎ የመግዛት አቅም ከፍ በማለቱ እና የመጣው የአመጋገብ ለውጥ ፍላጎቱን አንሮታል። ባለፉት 20 እና 30 አመታት በመቶ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ቻይናውያን፣ ሕንዳውያን፣ ብራዚላውያን ፣ ኢንዶኔዣውያን፣ ማሌዣውያን፣ ወዘተረፈ ከድህነት ወደ መካከለኛ ገቢ ማደጋቸው በግብርና ውጤቶች ፍላጎት ላይ መሠረታዊ ለውጥ አምጥቷል። በተቃራኒው የሚታረስ መሬትና የውሃ እጥረት እንዲሁም የአየር ንብረት ለውጥ በአናቱ ተጨምሮ ከአመት አመት ፍላጎቱን ማሟላት አዳጋች እያደረገው መጥቷል። የዓለም ሙቀት መጨመርና የደኖች መጨፍጨፍ፤ የአፈር መሸርሸርንና የመሬት መራቆት፣ በርሃማነት፣ ድርቅ፣ ሰደድ እሳት፣ ጎርፍ የግብርናውን ክፍለ ኢኮኖሚውን እያሽመደመደው ነው። በዚህ የተነሳ ፍላጎቱንና አቅርቦቱን ማጣጣም ከጊዜ ወደ ጊዜ አዳጋች እየሆነ መጥቷል። እንደ ኮቪድ 19 ያለ የተፈጥሮ አደጋ ሲከሰት ደግሞ ችግሩ ክፉኛ ይባባሳል።
የዓለም የምግብና የእርሻ ድርጅት በዚያ ሰሞን ይፋ እንዳደረገው ከወረርሽኙ ጋር በተያያዘ 265 ሚሊዮን ሕዝብ ለከፋ የምግብ እህል እጥረት ተዳርጓል። ከባድ ውሽንፍር፣ የጎርፍ መጥለቅለቅ፣ ድርቅ፣ የመሬት መንቀጥቀጥ ዓይነት የተፈጥሮ አደጋዎች በተከሰቱ ቁጥር የምግብ እህል እጥረት ከፍ ሲልም ርሀብ ይከሰታል። በመላው ዓለም አንድ ቢሊዮን ሕዝብ በምግብ እጥረት ሳቢያ ለተለያዩ የጤና እክሎች ተዳርጓል። ወደ አገራችን ስንመጣ 47 በመቶ የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን የከፋ የምግብ እጥረት እንዳለበት መረጃዎች ያትታሉ። ከወረርሽኙና ከድርቅ ጋር ተያይዞ ወደ 30 ሚሊዮን የሚጠጋ ወገናችን ለምግብ እህል እጥረት መጋለጡን መንግሥት ይፋ አድርጓል። ግብርና ለአገሪቱ ጥቅል ብሔራዊ ምርት ድርሻው 47 በመቶ ቢሆንም እድገቱ የሚጠበቀውን ያህል አይደለም። ከዚህ የርሀብና የምግብ እጥረት አዙሪት ቀለበት ሰብሮ ለመውጣት በቂ ምግብ ለማምረት በግብርናችን አካታችና ቀጣይነት ያለው ውልጠት /ትራንስፎርሜሽን ?/ እንደሚያስፈልግ በዘርፉ የተካሄዱ ጥናቶች ይመክራሉ።
አገራችን የወጣት፣ 85 በመቶ የሚሆነው ሕዝቧ በገጠር የሚኖር፣ አመቱን ሙሉ የሚፈስሱ ወንዞች፣ የሁለት ጊዜ የዝናብ ወቅት፣ የሚታረስ ሰፊ መሬት፣ ታታሪ ሕዝብ ያላት እና ቀደምት ከስድስት ሺህ አመታት የሚሻገር የእርሻና የግብርና ታሪክ ያላት ምድር ብትሆንም ራሷን እንኳ በቅጡ መመገብ አልቻለችም። በስንዴውና በዘይቱ ሲገርመን ሽንኩርትና ምስር ከውጭ እያስገባን ነው። በእኛው አባይ የለማ የግብጽ ብርቱካን በአለፍ ገደም ብቅ እያለ ነው። ካለፉት ሦስት አመታት ወዲህ ግን ከዚህ አዙሪት ለመውጣት በመንግሥት በኩል ፍላጎትና ቁርጠኝነትን እየተመለከትን ነው። ዛሬም ተረጂ ፣ ዛሬም ስንዴና ዘይት ከውጭ አስመጪ መሆናችን ቁጭት የፈጠረ ለለውጥ ያነሳሳ ይመስላል።
ቀድሞውኑም በኢኮኖሚያዊ አዋጭነትና በጥናት ባልተመሠረተ አግባብ ግብርናው የሚገባውን ያህል ድጋፍ ሳያገኝ ከፈረሱ ጋሪው እንዲሉ በግዕብታዊና በፖለቲካዊ ውሳኔ የዩኒቨርሲቲና የኢንዱስትሪ ፓርክ መዓት አግተልትለን ለምሩቃኑ ሥራ ለፋብሪካው ጥሬ ዕቃ ማቅረብ አልቻልንም። ለዚች አገር ነፍስ መዝሪያዋም መሞቻዋም ግብርና ነው። ግብርና ላይ ከተሳካልን ሌሎችን ዘርፎች ይዞ መውጣት ይቻላል። ለቀደሙት 27 አመታት ከፕሮፓጋንዳ ባለፍ የአገራችንን ስነ ምህዳር ታሳቢ ያላደረገ የዘመቻ ሥራ መሠራቱ ዛሬ ላይ ጥሎናል። ቆም ብለን ትንፋሽ ስበን የመጣንበትን መንገድ ገምግመን በግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ የሚስተዋለውን መዋቅራዊና ተቋማዊ ችግር ቀርፈን ትኩረታችን ግብርናው ላይ ሊሆን ይገባል።
ይህ እስኪሆን የለውጥ ኃይሉ እጁን አጣጥፎ አለመቀመጡና የህልውናችን መሠረት የሆነውን አየር ንብረታችን እንዲያገግም በአምስት አመታት ውስጥ ወደ 25 ቢሊዮን ችግኝ ለመትከል ግብ ጥሎ ካለፉት ሦስት አመታት ጀምሮ ወደ ተግባር መገባቱ የኑሮአችንና የኢኮኖሚያችን የጀርባ አጥንት ለሆነው ግብርና መልካም ዜና ነው። በሚቀጥሉት አምስትና አስር አመታትም የአገራችንን አየር ንብረትና ሥነ ምህዳር / ኢኮሎጂ / ፍጹም ይቀይረዋል። ይህ በግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ ላይ ተጨባጭ ለውጥ ለማምጣት መስፈንጠሪያ ነው። ይህ በሒደት እውን እስኪሆን የለውጥ ኃይሉ ስንዴን ከውጭ ማስገባትን ለማስቀረት፣ ግብርናውን ሜካናይዝድ ለማድረግ፣ መሬት ጦም እንዳያድር፣ የኩታ ገጠም አሠራርን ለማስፋፋት የሚያደርገው ጥረት ይበል የሚያሰኝ ሆኖ ወጥ በሆነና ስፋት ባለው አግባብ እንደየ ሥነ ምህዳሩ በመላ አገሪቱ ተግባራዊ ማድረግ ላይ ግን ይበልጥ ሊሠራ ይገባል።
እንደ አገር ያለን ሀብት የሚታረስ መሬት፣ ውሃና የሰው ኃይል ነውና ለግብርናው ቅድሚያ ሰጥተን ልንረባረብ ይገባል። ወደ ኢንዱስትሪ የሚደረግ ሽግግር ያለ ግብርናው ጽኑ መሠረት እውን ሊሆን አይችልምና። ስለሆነም ያለንን ሀብት ሁሉ አቀናጅተን ግብርናው ላይ ልንረባረብ ይገባል። የአረንጓዴ አብዮት በማቀጣጠል አንገታችንን ሲያስደፋን ሲያሸማቅቀን ከኖረው ርሀብ፣ ቸነፈርና ድህነት ይህን ተከትሎ ከማይለየን ተረጂነት መላቀቅ አለብን። ከ430ሺህ ሔክታር መሬት በላይ መሬት ላይ የበጋ ስንዴ ማምረት መቻሉ ዘርፉ ከድህነትና ከተረጂነት ማምለጫችን መሆኑን ያረጋግጣል።
ለመሆኑ የግብርና ወይም የአረንጓዴ አብዮት ምን ማለት ነው ? አገራችን ለአረንጓዴም ለአብዮትም እንግዳ አይደለችም። የማንነታችን ምልክት፣ መለያ የሆነው ሰንደቃላማችን አንዱ ቀለም አረንጓዴ ነው። ልማትን ልምላሜን ወክሎ የተቀመጠ ቢሆንም፤ ወደ ተግባር አልተረጎምነውም። አልኖርነውም። አላከበርነውም። ብናከብረው ከልማት ይልቅ በርሀብ በተረጅነትና በከፋ ድህነት ባላጠለሸነው። ከእኛ ይልቅ ከ1970ዎቹ እስከ 80ዎቹ መጀመሪያ የነበሩ እነ ሻምበል ምሩፅ ይፍጠር፣ ብርሃኑ ግርማ፣ ከበደ ባልቻና መሐመድ ከድር በዓለም የአትሌቲክስ መንደር ለተከታታይ አመታት ማንንም ጣልቃ ሳያስገቡ ከአንድ እስከ ሦስት በመግባት «አረንጓዴው ጎርፍ» በመባል ነገሰው አንግሰውናል። የሚያስቆጨው፣ እርር ድብን የሚያደርገው በአረንጓዴው ጎርፍ ከወጣንበት ማማ በ1980ዎቹ መጨረሻ በአገራችን በተለይ በደቡብና በኦሮሚያ ክልሎች በአረንጓዴ ልምላሜ ተደብቆ የተከሰተው ድርቅና ርሀብ «አረንጓዴው ርሀብ» መልሶ አውርዶ ጥሎናል። ይህ ክስተት ተምሳሌታዊ ነው። በጀግኖቻችን ደምና አጥንት ተከብሮና ታፍሮ የኖረው ሉዓላዊነታችን የሚደፈረው፣ የሚዋረደውና የሚንኳሰሰው በርሀብ ነው። ከዚህ ሀፍረት ከመላቀቅ የሚቀድም ምንም ነገር የለም። ብልጽግና ይሄን አበክሮ በመረዳት ለግብርናና ለአረንጓዴ አሻራ የሰጠው ልዩ ትኩረት ይበል የሚያሰኝ ነው ።
አብዮትም ብርቃችን አይደለም። አንድ ሁለት ጊዜ አብዮት ሁሉን ነገራችን ነቅሎ መቀመቅ አውርዶናልና። ለዚህ ነው ቃሉን ስንሰማ እንደ ኮሶ መድኃኒት የሚያንገሸግሸን። አረንጓዴ አብዮት ግን ርሀብን፣ ችጋርን፣ ቸነፈርን፣ ተመፅዋችነትን ከስሩ መንግሎ የሚጥል ዶዘር ነው። ከቀደሙት ሁለት የደም፣ የጥፋት ወይም የቀይ አብዮቶች አንዱ አረንጓዴ አብዮት ቢሆን ኑሮ የአገራችን መለያ ከሆነው ርሀብ እስከ ወዲያኛው በተለያየን። ዛሬ ለምንገኝበት የኑሮ ውድነትና የዋጋ ግሽበት ባልተዳረግን። አሁንም በሕዝብና በአገር ኢኮኖሚ እንዲሁም ገፅታ ላይ ስር ነቀል ለውጥ የሚያመጣውን የአረንጓዴ አብዮት ለማካሄድ አልረፈደም። እንግዲህ የ«አረንጓዴው አብዮት» ስርወ – ሀረግ ወደ ኋላ መለስ ብለን ስንቃኝ፤ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥቅም ላይ የዋለው የአሜሪካ የዓለምአቀፍ ትብብር ድርጅት / ዩኤስኤአይዲ / አስተዳዳሪ የነበሩት ዊሊያም ጋውድ እኤአ በ1968 የአብዮቱን አረንጓዴ ችቦ በለኮሱበት ሥነ ሥርዓት ፤ «… ይህ አዲስ አብዮት ነው። የሶቪየት ሕብረቱ ቀይ አብዮት አልያም የኢራን የሻህ ነጭ አብዮት አይደለም። አረንጓዴ አብዮት ብየዋለሁ። …»
የአረንጓዴ አብዮት የ2ኛውን የዓለም ጦርነት ተከትሎ የተከሰተውን የምግብ እና የአግሮ ኢንዱስትሪ ግብዓት እጥረት ለማሟላት በ1950ዎቹና 60ዎቹ ተለኩሶ የተቀጣጠለ አብዮት ነው። ምርጥ ዘርን፣ ማዳበሪያን፣ ጸረተባይ ኬሚካልን፣ አስተማማኝ የውሃ አቅርቦትን በማረጋገጥ በተለይ የስንዴንና የሩዝ ሰብልን ምርትን በእጅጉ ማሳደግ ያስቻለ አረንጓዴ አብዮት ነው። አረንጓዴ አብዮት በብራዚል፣ በሕንድ፣ በፊሊፒንስ፣ ወዘተረፈ ፈንድቶ ጎተራውን ሙሉ አድርጎታል። እኛም የአገራችንን ሥነ ምህዳርና ብዝሀ ሕይወት ከግምት ያስገባ አረንጓዴ አብዮት ያስፈልገናል። ርሀብን፣ ቸነፈርንና ችጋርን በቃ ! ልንለው ይገባል። ሁላችንም ከፖለቲካ ተንታኝነትና ከሴራ ፖለቲካ አራጋቢነት ወጥተን፤ ፖለቲካውን ለፖለቲከኞች ትተን ፤ አረንጓዴ አብዮትን እንቀላቀል። እናቀጣጥል። ግብርናውን እናግዝ ፤ በጓሮአችን አትክልት እናልማ ፤ የተከልናቸውን ችግኞች እንንከባከብ። ችግኝ እንትከል። የተገኘውን ውጤት ወደኋላ እንዳይመልሰውና የኑሮ ውድነቱን እንዳያባብሰው፤ እየተስተዋለ ያለው የማዳበሪያ ዕጥረትና አልቀመስ ያለው ዋጋ አፋጣኝ ምላሽ ይጠይቃል ።
ኢትዮጵያ ታምርት ! አሜን ።
በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን) fenote1971@gmail.com
አዲስ ዘመን ግንብት 21 ቀን 2014 ዓ.ም