ኢትዮጵያ አገራችን ከጥንት ጀምሮ የራሷ የትምህርት ሥርዓት ያላት ሲሆን፤ በእሱም ብዙ ዘመናት ስትጠቀምበት ቆይታለች።በእርግጥ የትምህርት ሥርዓቱ በአብዛኛው የተመሠረተው በመንፈሳዊ ዕውቀት ላይ እንደነበር እንረዳለን:: ስለዚህም ሀገራችን በ19ኛው ምዕተ ዓመት መጨረሻና በ20ኛው መጀመሪያ ላይ በሯን ለውጭው ዓለም ክፍት ስታደርግ የውጭውን ተሞክሮ በግምት ውስጥ በማስገባት የትምህርቷን ሥርዓት ማሻሻል ነበረባት:: በዚሁ መሠረት የመጀመሪያ ዘመናዊ ትምህርት ቤት የሆነው የዳግማዊ ምኒልክ ትምህርት ቤትና ጥቂት የሚሲዮን ትምህርት ቤቶች በዚህ ወቅት ተከፈቱ። ከዚህ በኋላም የኢትዮጵያ የትምህርት ዕድገት ይህንኑ መንገድ በመከተል አሁን ከሚገኝበት ደረጃ ደርሷል:፡ የዚህ መጣጥፌ ዓላማም በአሁኑ ጊዜ በከፍተኛ የትምህርት ተቋም ውስጥ ያለውን ሁኔታ መመርመር ስለሆነ በቀጥታ ወደ ርዕሳችን ለመግባት እንገደዳለን::
በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሆነው በድሮ ስሙ የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ በአሁኑ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሚባለው በ1950ዎቹ አጋማሽ ላይ የተከፈተ ሲሆን፤ ከዚያም ከጥቂት ዓመታት በኋላ የአስመራ ዩኒቨርሲቲ ሕልውናውን አግኝቷል:: እነኝህ ሁለት ተቋማት ለረጅም ዓመታት ብቸኛ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በመሆን ለአገሪቱ የተማሩና የሠለጠኑ ባለሙያዎችን ሲያፈሩ ቆይተዋል። በዚህም በአገሪቱ ውስጥ የነበረውን የባለሙያ ፍላጎት በመጠኑም ያሟሉ ነበር ማለት ይቻላል:: በእርግጥ ከዚህ ጎን ለጎንም አገሪቷ ባለሙያዎችን በውጭ አገርም ታሠለጥን እንደነበር መረሳት የለበትም። በዚህ መልኩ እስከ ደርግ መንግሥት ውድቀት ድረስ በርካታ ተግባራት ሲከናወኑ፤ ትምህርት ተቋማቱም ቁጥራቸው በመጠን መጨመር ታይቶበት በዓይነትም ከፍ ብሎ ቆይቷል።
በአንጻሩ ኢሕአዴግ አገሪቷን ከተቆጣጠረ፣ በተለይም ከዘጠናዎቹ ዓመታት በኋላ በዚህ ዘርፍ ከፍተኛ ለውጥ መታየት ይጀምራል:: በአጭር ጊዜ ውስጥ የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ብዛት በብዙ እጥፍ የጨመረ ሲሆን እነዚህ ዩኒቨርሲቲዎችም በመቶ ሺህ ለሚቆጠሩ ተማሪዎች በራቸውን ክፍት አድርገዋል:: በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ ውስጥ ከ40 በላይ ዩኒቨርሲቲዎች የሚገኙ ሲሆን፤ እነሱም በየዓመቱም በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ የሰለጠኑ ባለሙያዎችን ያስመርቃሉ:: ከዚህ በተጨማሪም የግል ኮሌጆች፣ ኢንስቲትዩቶችና የተለያዩ ማሰልጠኛዎች በቀላሉ የማይገመቱ ባለሙያዎችን ያሰለጥናሉ:: ይህ ሁነት ግን በደፈናው ሲታይ እርምጃው ጥሩ ሊመስል ይችላል፤ ወጣቶች ለምን የዩኒቨርሲቲ ትምህርት አገኙ ብሎ የሚቃወም ሰው የሚኖርም አይመስለኝም::
ነገር ግን ውጤቱን በምንገመግምበት ጊዜ ይህ የከፍተኛ ትምህርት ፖሊሲ ከአገሪቱ የኢኮኖሚ ዕድገት ጋር የማይጣጣም መሆኑን ወዲያው እንገነዘባለን:: ለዚህም አንዱ ማሳያ የአገሪቱ የሥራ ቦታ ውስኑነት ነው:: ስለዚህም ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ስልጠናቸውን ጨርሰው ከሚመረቁ ባለሙያዎች ውስጥ አብዛኞቹ ሥራ የማግኘት ዕድል አልነበራቸውም። አሁንም የላቸውም:: አንዳንድ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ከተመረቁት ባለሙያዎች ውስጥ ሥራ የሚያገኙት አምስት በመቶ እንኳ አይሆኑም:: ነገሩ በጣም አሳዛኝ ነው፤ ይህ ዓይነቱ ሁኔታ የአገሪቷ ብሔራዊ ሀብት አላግባብ እንዲባክን የሚያደርግ ቢሆንም ዋናው ተጎጂዎቹ ወጣት ምሩቃኑ ናቸው:: በእነሱ ላይ የሚደርሰውን ኢኮኖሚያውም ሆነ ሞራላዊ ጉዳት በቀላሉ መገመት አይቻልም::
እነኝህ ወጣቶች ሥራ ይዘው አገራቸውንና ወላጆቻቸውን መርዳት ሲገባቸው፤ አብዛኛዎቹ የወላጆቻቸው ሸክም ሆነዋል:: ጥናት ባለመደረጉ ነው እንጂ “ቦዘኔ” ሆነው የቀሩ ወይም በሕገ ወጥ ተግባር ላይ የተሠማሩም እንደሚገኙ ጥርጥር የለውም:: ይህ ዓይነቱ ሁኔታ በወጣቶቹ ላይ ብቻ ሳይሆን በወላጆቻቸው ሥነልቦናና በኢኮኖሚ አቋማቸው ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ _ እንደሚያደርግና የኋላ ኋላም የብሶትና የተቃውሞ ምንጭ እንደሚሆን መረሳት የለበትም:: ከዚህም ሌላ ይህ ሁኔታ ሕዝቡ በዕውቀት ላይ እምነት እንዳይኖረው እያደረገ ነው:: ዕውቀት የሌለው ሕዝብ ደግሞ የመሻሻልና በመጨረሻው ሕልውናውን የማስጠበቅ ተስፋው የመነመነ ነው። ይህ ዓይነቱ ሁኔታ አገሪቷን ወደ ከፍተኛ ቀውስ ውስጥ ሊያስገባት የሚችል በመሆኑ መንግሥት ሊያስብበትና እርምጃ ሊወስድበት ይገባል::
ደግሞ በጣም የሚያሳዝነው በመንግሥት መሥሪያ ቤቶችም ሆነ አንዳንድ ድርጅቶች ውስጥ ክፍት የሥራ ቦታዎች ሲገኙ ቅጥሩ የሚፈጸመው በችሎታ ሳይሆን በዘመድ አዝማድ፣ በዘርና በሌሎች መስፈርት መሆኑ ነው። በዚህ ዓይነት ሙስና የሚቀጠሩ ሰዎች ለመንግሥትም ሆነ ለግል ድርጅቶች፣ ከዚያም አልፎ በጠቃላይ ለአገሪቷ የሚፈይዱት ነገር አይኖርም።
የአገራችን የከፍተኛ ትምህርት ሥርዓትና ሥራ አጥነትን የማስወገድ እርምጃ እንደዚህ ያለ አስከፊ ችግር ውስጥ ለምንድነው የወደቀው? ለእኔ እንደሚመስለኝ ለዚህ ዓይነቱ ሁኔታ መፈጠር ዋናው ተጠያቂ መንግሥት ነው:: መንግሥት ይሀን የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን ማስፋፋት ሥራ የጀመረው የአገሪቱን የኢኮኖሚ ሁኔታ ሳያገናዝብ ያለጥናት ነበር:: ዋናው ዓላማውም የፖለቲካ ጥቅምና የውጭ ዕርዳታ ለማግኘት እንደነበር ግልጽ ነው:: እዚህ ላይ የተባበሩት መንግሥታት የ21ኛው ምዕተ ዓመት የትምህርት ግብ የተባለው ፕሮጀክት ከፍተኛ ሚና የተጫወተ መሆኑን መጥቀስ ያስፈልጋል::
የኢሕዴግ መንግሥት አጋሮቹ የሆኑትን ምዕራባውያን ለማስደሰትና እግረመንገዱንም ዕርዳታ ለማግኘት ሲል ይህን ለአገር ብዙም ጠቀሜታ የሌለውን ፕሮጀክት ሳያንገራግር በተግባር አውሎታል:: ከዚህ በተጨማሪም መንግሥት በዚህ ዕቅድ አማካይነት የአንዳንድ ብሔረሰቦችንና የወጣቶችን ድጋፍ ለማግኘት ተጠቅሞበታል ማለት ይቻላል:: በአጠቃላይ ሲታይ ግን ፖሊሲው የሕዝብን ፍላጎት ሳያገናዝብ የፖለቲካ ጥቅም ብቻ ለማግኘት ሲባል እንደሚሰጡ ውሳኔዎች ሁሉ፣ ለአገሪቷና ለሕዝቧ የሚሰጠው ጥቅም የለም ብል አልሳሳትም:: መንግሥትም እንዳሰበው ወጣቱ ደጋፊው ሳይሆን ተቃዋሚው ነው የሆነው::
ከላይ እንዳየነው በከፍተኛ ትምህርቱ ዘርፍም አገሪቷ የምትገኘው አስቸኳይ መፍትሔ የሚፈልግ ከፍተኛ ችግር ውስጥ ናት ። ይህ ችግር ሊወገድ የሚችለው በትምህርቱ ዘርፍ ያለውን ችግር ላይ በማተኮርና እርምጃ በመወሰድ ብቻ ሳይሆን በተባበረ እርምጃ ነው:: ለምሳሌ ኢኮኖሚው ካላደገ የሥራ ቦታ መፍጠር አይቻልም፤ ሥራ ከሌለ ደግሞ ሰዎችን መቅጠር አይቻልም:: ስለዚህም አሁን ያለውን በሥራና በሠለጠነ የሰው ኃይል አጠቃቀም መሐከል ያለውን የተዛባ ሁኔታ ማስተካከል የሚቻለው በቀደምትነት የአገሪቱን ኢኮኖሚ በማሳደግ ነው:: የሰው ኃይል ሥልጠናው መካሄድ ያለበት ከኢኮኖሚው ዕድገት ጋር በተጣጣመ መልኩ ነው:: ያ ከሆነ የአገር ሀብትም በከንቱ አይባክንም፤ ወጣት ባለሙያዎችም አላግባብ አይጎሳቆሉም ስል ይህቺን አጭር ጽሑፌን እደመድማለሁ:: ሰላም!
በዛብህ ደምሴ (ዶ/ር)
አዲስ ዘመን ግንብት 21 ቀን 2014 ዓ.ም