ዶክተር ፍሬገነት ተስፋዬ ይባላሉ። አርማወን ሀንሰን የምርምር ኢንስቲትዩት (አህሪ) ውስጥ ተመራማሪ ናቸው። ተላላፊ በሽታዎች ላይ በተለይም ቲቢና ኤች አይ ቪን በተመለከተ የምርምር ሥራዎችን በማድረግ መፍትሄ አመላካች ተግባራትን ከውነዋል። ውጤታማነታቸው ደግሞ በየጊዜው በሚሸለሟቸው ሽልማቶች ይለካሉ። ሕይወታቸው በበርካታ አስተማሪ ልምዶች የተሞላች ናት። በተለይም በትምህርት ያሳለፏቸው ጊዜያት በርካቶችን የሚያስተምር ሆኖ አግኝተነዋል።
ልጅነት
ተወልደው ያደጉት በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ጣርማበር ወረዳ ደብረሲና ገነት ተብላ በምትጠራ ቀበሌ ውስጥ ነው። የዶክተር ፍሬገነት ቤተሰቦች ሴት ልጅ በቤት ውስጥ በሥራ ወላጆቿን እንድትረዳ እንጂ እንድትማር ብዙም አይፈልጉም ነበር። በተለይም የመጨረሻ ልጅ መሆናቸውና በትንሹም በትልቁም ታዛዥ መሆናቸው ብዙ ጫና እንዲፈጠርባቸው አድርጓል።
እናታቸው ቤት ውስጥ እንዲያግዟቸውና ሙያ እንዲማሩ ይፈልጋሉ። ትምህርት ቤት ከመሄድ በፊትና ከመጡ በኋላ ያሉትን ጊዜያት ምግብ የማብሰል ግዴታቸው እንደሆነ ያሳስቧቸዋል። በዚህም ቢደክማቸው እንኳን የታዘዙትን መፈጸም ግዴታቸው ነው። አባት ደግሞ የተማሩም ባይሆኑም ታላላቅ ልጆቻቸውን ስላስተማሩ እንዲማሩና እንዲያጠኑ ይፈልጋሉ። እናም «ታንብብበት» እያሉ፤ ባለቤታቸውን ይሟገቱላቸዋል። ባለታሪካችንም በሁለቱ ፍላጎት ውስጥ ለማለፍ የተቻላቸውን ሁሉ ያደርጉም ነበር።
«…..ቤት ውስጥ የተማርኩትን ነገር ማንበብ በጣም እፈልግ ነበር፤ ነገር ግን የቤቱ ትንሽ ልጅ ስለነበርኩ ትዕዛዞች ሁሉ እኔ ጋር ነበር የሚመጡት በዚህም በጣም ብናደድም በአካባቢያችን ባህልና ወግ መሠረት ግን እንኳን ለቤተሰብ ለዚያውም ለእናት ቀርቶ ለጎረቤትም መታዘዝ፣ መላላክና ሥራ ማገዝ ግዴታ ስለነበር የተቻለኝን ሁሉ በትዕግስት አደርግ ነበር» በማለት ሁኔታውን ያስታውሳሉ።
የልጅነት ፍላጎታቸው የሕክምና ዶክተር መሆን ነበር። ዶክተር ፍሬገነት አሁንም ከጤናው የሙያ ዘርፍ ባይርቁም ሀኪም መሆን ግን አልቻሉም። ይህም ቢሆን ህልሜ ስኬቱ ላይ አልደረሰም ግን አይሉም።
የገጠር ልጅ መሆን ሌላው ፈተና ማኅበረሰቡ ለሴት ልጅ ያለው አመለካከት ነው። ሴት ልጅ እናቷን አገልግላ ከዚያም ትዳር መስርታ ልጆች ወልዳ ቤቴ ቤቴ ማለት እንጂ ትምህርት ብሎ ነገር ተቀባይነት የለውም። በዚህ መካከል ደግሞ የእሷን ታታሪና ቅን ታዛዥነት እንዲሁም የቤተሰቡን የተከበረ መሆን ያየ ሌላ ወላጅ ልጅህን ለልጄ ማለቱ ደግሞ ወግም ባህልም ነው።
«….ያው ማኅበረሰባችን ለሴት ልጅ ያለው አመለካከት ከላይም ገልጬዋለሁ እኔም የገጠር ልጅ ከመሆኔ የተነሳ እኔንም ቤተሰቤንም ያየ ሁሉ ልጃችሁን ለልጃችን ማለቱ አልቀረም። አባቴና ወንድሜ ትምህርቴን እንድማር አጥብቀው ይፈልጉ ስለነበር ለዚህ ጥያቄ ቦታ አልሰጡትም፤ እንዲያውም ከጎኔ በመቆም አጋርነታቸውን ነበር ሲያሳዩኝ የነበሩት። እነሱ ያንን ባያደርጉልኝ ኖሮ ደግሞ የዛሬው እኔነቴ አይገኝም ነበር» ይላሉ።
አባታቸው ሴቷንና የመጨረሻዋን ልጃቸውን አስተምረው ለወግ ለማብቃት ከመጣር ጎን ለጎን በሥነ ምግባርም የታነጹ እንዲሆኑ ሰውን መውደድ፤ መታዘዝና ለሌላው ማሰብ ስንቃቸው እንዲያደርጉ ብዙ ሠርተዋል። ተካፍሎ መብላት ይህ አስተዳደጋቸው የሰጣቸው ሌላው ስጦታ ነው። መምህራንን ማክበርና የሚሉትን መስማት አዳማጭ መሆንም የልጅነታቸው ገጸ በረከት መሆናቸውን ያነሳሉ።
ነፍሰጡሯ ተማሪ
መምህራኖቻቸው ለዛሬ ማንነታቸው መሠረት የጣሉ ናቸው። ብዙ ነገራቸውን ለውጠውላቸዋል። አቅማቸውን በመመልከትም ብዙ ሽልማቶችና ማበረታቻዎች ሁልጊዜ ወደፊት እንዲራመዱ አድርጓቸዋል።
«…… በቤት ውስጥ ለማጥናት ምቹ ሁኔታ የለም፤ ቀን ሥራ ይበዛል፤ ሌላው እየሠራ ደብተር ይዞ መቀመጥ ደግሞ እንደ ንቀትም ሊወሰድ ይችላል። እናም አብዛኛውን ጊዜ ንባብን ካሰብኩ የማከናውነው ምሽት ላይ ነው። ይገርማል ምሽትን ብመርጥም የመብራት አለመኖር ደግሞ ሌላው ፈተናዬ ነበር» ይላሉ።
መብራት የለም አይታየኝም እንዴት አድርጌ ላንብበው ብለው ግን እጃቸውን አጣጥፈው አልተቀመጡም። ይልቁንም ኩራዝ ለኩሰው ጭሱ፣ የኩራዙን ብርሃን የሚያውለበልብባቸውን ንፋስ እየተቋቋሙ ከማሰንበብ ወደኋላ አላሉም።
አባታቸው በትምህርታቸው ጠንካራ የሚሆኑበትን መስመር ሲዘረጉላቸውም ይጠቀሙታል። በእነዚህ ወቅቶች ደግሞ የማይረሷቸው በርካታ አጋጣሚዎች አሉ። አባታቸው ለእሳቸው ትምህርት ብለው የሚከፍሉትን መስዋዕትነት በፍጹም ያልዘነጉት ታዳጊዋ ተማሪ ይልቁንም አባታቸውን ለማኩራት ኃይል ጨምረው የሚችሉትን ሁሉ በማድረግ በትምህርታቸው ግንባር ቀደም ለመሆን ችለዋል።
የትምህርትን ‹‹ሀሁ›› የጀመሩት በዚያው በቀያቸው ባለ ገነት አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ሲሆን፤ እስከ ስምንተኛ ክፍል ትምህርቱን ተከታትለዋል። ከዚያ በእግራቸው አንድ ሰዓት ተኩል እየተጓዙ ደብረሲና ከተማ ላይ ቀጣዩን ክፍል እንዲማሩ ሆነዋል። በእርግጥ የእግር ጉዞው እስከ 12ኛ ክፍል የዘለቀ አልነበረም። የዘጠነኛ ክፍል ተማሪ ሳሉ በዚያው በደብረሲና ከተማ ትዳር መመስረት ነበረባቸውና ትዳርን ተቀላቀሉ።
«…..የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ስሆን ያንን የፈራሁትን አባቴም ሲሟገቱልኝ ያቆዩልኝን ትዳር መመስረት ነበረብኝና ባል አገባሁ። አጋጣሚ ሆኖ አልያም ዕድለኛ ሆኜ ያገባሁት መምህሬን ስለነበር ትምህርት ማቋረጥ የሚለው ነገር አልመጣብኝም። በትምህርቴ ስኬታማ ለመሆኔ የባለቤቴ ድርሻ በቃላት የሚገለጽ አይደለም » በማለት የባለቤታቸውን ውለታ ያስታውሳሉ።
ከአባታቸው የተረከቧቸው ባለቤታቸው ባደረጉላቸው ያላሰለሰ እገዛም የልጅነት ህልማቸውን ዳር ሊያደርሱ ተቃረቡ። በተለይም የባለቤታቸው ሩቅ አሳቢነት በብዙ መንገድ እንዲጓዙ ምቹ ሁኔታን ፈጠረላቸው። ከዚህ አንጻርም ‹‹ትዳር የሚረዳ ሰው ከተገኘ ወርቅና የኑሮ ቅመም ብቻ ሳይሆን ስኬት ላይ የሚያደርስ ጡብ ነው›› በማለት ኑሯቸውን ይገልጹታል።
እርሳቸውን የሚረዳቸው የትዳር አጋር በማግኘታቸው ትምህርታቸውን እንዳያቋርጡ ሆኗል። በተለይ የከበዳቸውን የሚያግዛቸው አይዞሽ የሚላቸው ሰው ከጎናቸው መኖሩ የወደፊት ማንነታቸው እንዲያመር የራሱን ሚና ተጫውቷል።
«……እንዲህ እየተደጋገፍን እየኖርን 12ኛ ክፍል ደረስኩ፤ በዚህ ጊዜ ደግሞ ሕይወቴን ወደአዲስ ምዕራፍ የሚያሻግር ክስተት በቅ አለ፤ እንደእኛ ሃሳብ ትምህርቴን ሳልጨርስ ልጅ መውለድ አልፈልግም ነበር። የእግዚአብሔር ፍቃድ ሆነና የመጀመሪያ ልጃቸው ተጸነሰች። በሁነቱ ባልከፋም ትምህርቴ ላይ ጫና መፈጠሩ ግን አልቀረም። እንዳሰብኩትም ጥሩ ውጤት አምጥቼ ህልሜን ለማሳካት አልቻልኩም» በማለት የነበረውን ሁኔታ ይናገራሉ።
የ12ኛ ክፍልን ፈተና ሲወስዱ መውለጃ ቀናቸው ደርሶ ስለነበር፤ የፈተናውም ሆነ ከዚያ በፊት የነበሩት የዝግጅት ቀናት በእርግዝና ውስጥ ሆነው ነው ያለፉት። የመጀመሪያ እርግዝና ደግሞ አዲስም ነገር ስለሆነ ትንሹም ትልቁም ነገር ገዝፎ ይሰማልና ትንሽ መፈተናቸው አልቀረም። ያም ሆኖ ግን ከቀለም ትምህርቱ ጋር መፋለማቸውን አልተውም። በዚህም የህክምና ዶክተር የመሆን ህልማቸው ባይሳካም ቀድሞውንም የተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪ ስለነበሩ ዩኒቨርሲቲ ገብተው የጤናው ዘርፍ ጋር ተቀራራቢነት ያለው የትምህርት መስክ ለማጥናት አልተቸገሩም።
የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን የተማሩት በጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ የባዮሎጂ ትምህርት መስክን በመምረጥ ነው። በገቡበት መስክ ላይ ውጤታማ መሆን እንደሚችሉና ያሰቡት ላይ እንደሚደርሱ ያውቃሉ። ይሁን እንጂ ዩኒቨርሲቲው ገና ጀማሪ መሆኑ ግን አስፈርቷቸው ነበር። እንዲያውም መመደባቸውን ሲያውቁ ነው ስሙን እንኳን የሰሙት። ይህ ደግሞ ብዙ ነገሮች እንደሚያጎልባቸው ተሰምቷቸዋል።
«……ዩኒቨርሲቲው እንዳሰብኩት በደንብ ያልተደራጀ ነበር። ለመማር ማስተማሩ ሥራ ብዙ ነገሮችም ይጎድሉታል። ነገር ግን ስሄድ አስቤበትና ብዙ ነገሮችን ጠይቄ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን ሰርቼ ስለነበር ሁሉንም ነገር በየፈርጁ አስኪጀዋለሁ» ይላሉ።
ውጤት ለማያስገኝ ነገር መልፋት ትርፉ ንዴት ነው ብለው የሚያምኑት ባለታሪካችን ብዙ ሳይጨናነቁ የቻሉትን እያደረጉ ትምህርታቸውን ቀጠሉ። ትምህርቱን ሲጀምሩ ‹‹ኮንፒቴሽናል ናቹራል ሳይንስ›› በሚል መስክ ነበር። ከዚያ የባዮሎጂ ትምህርት መስክን መርጡ። በዚህም በከፍተኛ ማዕረግ ለመመረቅ በቁ።
ዶክተር ፍሬገነት ትምህርት ወዳድነታቸውን ከሚያጎድሉት ምክንያቶች መካከል ተፈጥሮ ጭምር ያልገደባቸው ሴት መሆናቸው ነው። እናት ለልጇ ስትል የማታደርገው ነገር የለም። ለልጅ መሳሳት እስከምን ድረስ መሆን አለበት የሚለው ካልተለካ ግን ዋጋ ማስከፈሉ አይቀርም። ስለዚህም ያ እንዳይሆን የለፉና ወደፊት እንጂ ወደኋላ የማይሉ ለዛሬ የልጆቻቸው ኩራት ናቸው።
ዶክተር ፍሬገነት «ከዛሬው የወደፊቱ ይበልጣል» የሚል እምነት አላቸው። በዚህም የሰባት ወር ጨቅላ ሕፃን ልጃቸውን ለቤተሰብ ትተው ለመማር ተጓዙ። ይህ የሆነው ደግሞ 12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተናን እንዳጠናቀቁ የመጀመሪያ ልጃቸውን ተገላግለው ነበርና ብዙም ሳይቆዩ ዩኒቨርሲቲ እንዲገቡ ተጠሩ። ስለዚህም ማቄን ጨርቄን ሳይሉ ወደተመደቡበት ዩኒቨርሲቲ ሄዱ። ነገር ግን ዩኒቨርሲቲ ከገቡ በኋላ እናትነታቸው በገቡበት ወኔ ልክ ሊያስሄዳቸው አልቻለም። የልጃቸው ጉዳይ የራስ ምታት ሆኖባቸዋል። በደንብ አይዟት ይሆን የሚለው ያሳስባቸው ጀመር። በዚህም የመጀመሪያ ዓመት ውጤታቸው ያሰቡትን ያህል አልሆነላቸውም።
ሰው ሰራሽ ፈተናውም በዚያው ልክ ቀላል አልሆነላቸውም። እረፍት በአገኙ ቁጥር መመላለስና የልጃቸውን ሁኔታ ማየታቸው ግን ሁሉን ነገር ቀየረላቸው። እፎይታ ተሰምቷቸው ትምህርታቸው ላይ እንዲያተኩሩም አደረጋቸው። ፈተናውን ሁሉ በድል በማለፋቸውም የማዕረግ ተመራቂነቱን መቆናጠጥ ቻሉ።
ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ሲጀምሩም ሥራ እየሠሩ በብዙ ትግል ውስጥ ነው ትምህርቱን የተከታተሉት። ይሁን እንጂ በውጤት አልተፈተኑበትም። ይልቁንም ከፍተኛ ውጤታማነትን አዋህደው የተሻሉ ለመሆን
የሠሩበት ጊዜ ነው። ‹‹….ራሴንና አቅሜን ያየሁበት ወቅት ነው። ሴት ልጅ መውለድ እንኳን ከትምህርቷ እንደማያስቀራት በተግባር አረጋግጫለሁ። ይህ ደግሞ አርአያ እንድሆንና ለልጆቼም እንዳስተምራቸው አድርጎኛል›› ይላሉ።
ወቅቱ በመውለድና ልጅን ትቶ ትምህርት ላይ ማተኮርን ጎን ለጎንም የተለያዩ ፈተናዎች የገጠሟቸው ቢሆንም በአይበገሬነት መንፈስ ትምህርታቸውን የተከታተሉበት ጊዜ ስለነበር ይደሰቱበታል። ለዚህም ማሳያው የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን እንዳጠናቀቁ በተማሩበት ዩኒቨርሲቲ የመቅረትን ዕድል አግኝተው ነበር አልፈለጉም እንጂ። ፔዳጎጂና መሰል የማስተማሪያ ሥነ ዘዴ ትምህርት ያስፈልጋል ተብለው ሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ ገብተው እየተማሩ ሳለ የሁለተኛ ዲግሪ የትምህርት ዕድል በማግኘታቸው አቋርጠዋል።
ያገኙት የትምህርት ዕድል በየዓመቱ ከፍተኛ ውጤት ለሚያመጡ ሴቶች የሚሰጥ ነው፤ ሰጪው ደግሞ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በስዊድን መንግሥት አጋዥነት ነበር። እናም እዚያ አመልክተው በማለፋቸው ለማስተማር የሚወስዱትን ትምህርት በማቋረጥ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን ተቀላቀሉ። በአራት ኪሎ ካምፓስ ውስጥም በባዮ ሜዲካል ሳይንስ የትምህርት መስክ የሁለተኛ ዲግሪያቸውን መማር ቀጠሉ ።
«……ብዙ ልምድ ያላቸው ሰዎች የሚገቡበት በመሆኑ በትምህርቱ የተሻለ አቅም ቢኖረኝም በሰው ፊት ቆሞ መናገር ይፈትነኝ ነበር። ነገር ግን እጅ ሳልሰጥ በሂደት ነገሩን ለመድኩት፤ ከዚያም በማዕረግ ተመርቄ ወጣሁ» በማለት ጥንካሬያቸውን ደግመው ደጋግመው ያስታውሳሉ።
ምርምራቸውን ለመሥራት መቸገራቸው የሁለተኛ ዲግሪ ትምህርታቸው ከባድ ፈተና ውስጥ አስገብቶት እንደነበር የሚያወሱት ዶክተር ፍሬገነት፤ ሙሉ ላብራቶሪ የሚያገኙበት አጋጣሚ ባለመኖሩ ተቸግረው ነበር። ችግሩ እንደ አገር ፈታኝ ቢሆንም ‹‹የትም ፍጪው ዱቄቱን አምጪው›› ዓይነት ነገር ነበርና ብዙ ቤት አንኳኩተው የዛሬውን መሥሪያ ቤታቸውን አገኙ። ተቋሙ አርማወን ሀንሰን የምርምር ኢንስቲትዩት ነው ዶክተር ፍሬገነት ተስፋዬ በየዓመቱ ጥሩ የሚባሉ የምርምር ሥራዎችን መርጦ የሚሠራበትን ሁኔታ ያመቻቻል። እርሳቸው በዚሁ የምርምር ተቋም ተወዳድረው በማለፋቸው የምርምር ሥራቸውን መሥራት ጀመሩ።
ጥሩ የሚባል የምርምር ሥራን ለማከናወን ብዙ ለፍተዋል። መጀመሪያ ይዘውት የሄዱት ሥራ ተቀባይነት ስላላገኘ ቶሎ በመቀየር በቲቢና ኤች አይ ቪ ላይ በዚሁ የምርምር ተቋም የሚሠራ አንድ የስዊድን አገር ፕሮጀክት በአማካሪያቸው አማካኝነት አግኝተው ምርምራቸውን ቀጠሉ። ይህ ደግሞ ፈተናውን ሁሉ በብቃት እንዲያልፉት አስቻላቸው። ምርምራቸውን የሠሩትም በተቋሙ አመቻችነት ባህር ማዶ ተሻግረው ነበር። ይህ ሁኔታ ሌላ የትምህርት ዕድል ይዞ ብቅ አለ – ሦስተኛ ዲግሪ፡፡
«…. ወደ ስዊድን አገር በመሄድ ሉንድ በተባለ ዩኒቨርሲቲ በክሊኒካል ኢንፌክሽየስ ዲዚዝ(Clinical infectious disease) ሜዲካል ሳይንስ/ የትምህርት መስክ ትምህርቴን ጀመርኩ ዶክተር ፍሬገነት ተስፋዬ ትምህርቱን የተማርኩት እየተመላለስኩ በሳንዱች ፕሮግራም ሲሆን፤ ኮርሱን እና የላብራቶሪ ሥራውን በሉንድ ዩኒቨርሲቲ እየተከታተልኩ ለላብራቶሪ የምርምር ሥራ የሚውል ናሙና ደግሞ ኢትዮጵያ መጥቼ በአዳማ ከተማ ባሉ ጤና ማዕከላት ውስጥ ነበር የሰበሰብኩት ከአራት አመት ከስድስት ወር በኋላም የሦስተኛ ዲግሪዬን አጠናቅቄያለሁ» ይላሉ ።
እንግዳችን ሦስተኛ ዲግሪያቸውን ሲጀምሩም እንደመጀመሪያው ነብሰጡር ነበሩ። ሁለተኛ ልጃቸውን አርግዘው ሥራ እየሠሩም እየተማሩም ነው ሕይወታቸውን የመሩት። ይሁን እንጂ በውጤት አልተፈተኑበትም። ይልቁንም ከከፍተኛ ውጤታማነት ጋር አዋህደው የተሻሉ ለመሆን የሠሩበት ወቅት ነው። እነዚህን ጊዜያት ሲያስታውሱም ‹‹ራሴንና አቅሜን ያየሁበት ነው። ሴት ልጅን መውለድ እንኳን ከትምህርቷ እንደማያስቀራት በተግባር የተረጎምኩበት ነው። ይህ ደግሞ አርአያ እንድሆንና ለልጆቼም እንዳስተምራቸው አድርጎኛል›› ይላሉ።
ህልም የመራው ሥራ
ለእርሳቸው መማርና መሥራት የተለዩና ተነጥለው የሚታዩ አይደሉም። በሽርፍራፊ ቁጥሮች እንኳን ለመለየት አስቸጋሪ ነው። ስለሆነም የሥራ ታሪካቸው ሁለቱንም ያቀፈ ነው። ከአንድ መስሪያቤትም አያልፍም። ከሥራው ይልቅ ብዙን ጊዜያቸውን ያሳለፉት በትምህርት እንደነበርም ያስታውሳሉ። ምንም እንኳን የሁለተኛ ዲግሪያቸውን የተከታተሉት በነፃ የትምህርት ዕድል (Scholarship program) ፕሮግራም ቢሆንም ፕሮግራሙ የሚሸፍንላቸው የወጪ መጋራት/cost sharing/ እና ትንሽ የኪስ ገንዘብ ነበር። እናም ባለታሪካችን እየተማሩ ተማሪዎችን በማስጠናት ተጨማሪ ወጪያቸውን ይሸፍኑ ነበር። በቤተሰቦቻቸውና በባለቤታቸው እገዛ ጊዜውን መግፋት ባይችሉ ኖሮ ዛሬን እንደማያገኙትም ያምናሉ። ሆኖም ብርቱ ሴት በመሆናቸውና መልካም አጋር ስላላቸው ነገሮችን ፈተዋል።
የሁለተኛ ዲግሪያቸውንም እንዳጠናቀቁ ሥራ ማግኘት ፈተና ሆኖባቸው ነበር። ያለሥራ መቀመጥ አይደለም ለተማረ ላልተማረም እጅግ ከባድ ነው። ጥገኛ መሆን ደግሞ ምቾት አይሰጥም። በእርግጥ ይህንን በሚገባ የሚረዳ የትዳር አጋር አላቸው። ሆኖም በብዙ ነገር ደስታቸው ይቀማ ነበር። ስለዚህም ሦስተኛ ዲግሪያቸውን ከመጀመራቸው በፊት ሥራ ማፈላለጉን ተያያዙት። ሆኖም የቱንም ያህል የትምህርት ብቃትና አቅም ቢኖራቸውም የሥራ ልምድ የላቸውምና ማንም ሊቀጥራቸው አልወደደም። ስለዚህም ተስፋ ቆርጠው ባህር ማዶ ተሻግረው ለመሥራት ወሰኑ። ይህንን ምርጫ ያገኙት ደግሞ አንድ አጋጣሚ በሰጣቸው ዕድል ነው።
«…… የምርምር ሥራዬ በአሜሪካ አገር በሚደረግ ትልቅ ኮንፍረንስ ላይ እንዲቀርብ ተመረጠ። ሙሉውን ወጪ ሸፍነውም ወደዚያ እንደምሄድ ተነገረኝ። እናም ያንን ቀን እየጠበኩ ነበር። ይሁን እንጂ ይህንን የሚሽር ሌላ ዕድል መጣ። ይህም ኢትዮጵያ ውስጥ የሚሠራ አዲስ የስዊድን፣ በሉንድ ዩኒቨርሲቲ የሚመራ የምርምር ፕሮጀክት ይፋ መደረጉ ነበር። ፕሮጀክቱን እንድቀላቀል ከፕሮጀክቱ ዋና ኃላፊ ጥያቄ ቀረበልኝ፤ ከልጆቼም ሆነ ከቤተሰቤ እንዳልነጠል የሚያደርገኝ ስለነበር ወደድኩት፤ ተቀበልኩት። ከአርማወን ሀንሰን እንዳልወጣ የሆነውም በዚህ ምክንያት ነው» በማለት ሁኔታውን ይገልጹታል።
ፕሮጀክቱ የቲቢ ኢንፌክሽንን በነብሰ ጡር እናቶች ውስጥ ማጥናትን አልሞ የሚሠራ ፕሮጀክቱ፤ ኤች አይ ቪንም ያካትታል። ስለሆነም ይህንን በሙሉ ኃላፊነት እየመሩና እየተመራመሩ አስቀጠሉት። ይህ የሆነው ደግሞ እ. ኤ. አ. በ2016 ነበር።
የሦስተኛ ዲግሪ የምርምር ሥራቸው መሠረት ያደረገው በዚሁ የጥናት መስክ ላይ ነበር። አሁንም በዚሁ የምርምር መስክ እየሠሩ ይገኛል። ይህ ሥራ ከኦሮሚያ ጤና ቢሮ እና በአርማወን ሀንሰን የምርምር ኢንስቲትዩት( አህሪ ) በተደረገ ስምምነት መሠረት በአዳማ ከተማ ውስጥ በሚገኙ የጤና ማዕከላት እየተከናወነ ሲሆን በአብዛኛው የላቦራቶሪ ሥራዎች ደግሞ በአዳማ ሪጅናል ላብራቶሪ ነው የሚሠሩት። በዚህም ቀጣሪዎቻቸው እምነት እስኪጥሉባቸውም ድረስ በትጋት አገልግለዋል። አዳዲስ የምርምር ውጤቶችን እንዲያወጡና በኢንተርናሽናል ጆርናል ላይ እንዲያሳትሙ ሆነዋል።
በሁለተኛ ዲግሪ የምርምር ሥራቸው በጤናው ዘርፍ መፍትሄ አምጪ ሰው በመሆናቸው በ አህሪ እ. ኤ. አ. በ2015 ‹‹የቶሬ ጎዳል›› ተሸላሚ የሆኑት ዶክተር ፍሬገነት፤ የጀመሩትን መጨረስ የሚወዱ ናቸው። አገር ወዳድም እንደሆኑ ይመሰከርላቸዋል። ለዚህም ማሳያው ብዙዎቹ አሜሪካ በሄዱበት ሲቀሩ እርሳቸው ግን ወደ አገሬ በሚል ተመልሰው አገራቸውን በማገልገል ላይ ናቸው።
ሴትነትና እይታቸው
‹‹ብዙ ሰው የሚረዳው ሴት ልጅ ፈተናዋ በቤተሰብ ላይ ሳለች ብቻ ይመስለዋል። ነገር ግን የራሷን ቤተሰብ መስርታ ስትኖር የበለጠ ጫናዋ ይበዛል። የሁሉንም ቤተሰብ ፍላጎት ማሟላት ይጠበቅባታል። በዚህም በብዙ መንገድ ጠንክራ ካልወጣች ትወድቃለች። በተለይም የትዳር አጋሯ ከእርሷ ጎን ካልቆመላት ጠንክራ ለመዝለቅ ትቸገራለች›› የሚሉት ዶክተር ፍሬገነት፤ ሁሉን ነገር እንዲጋፈጡና እንዲያልፉት ቤተሰብ ቤተሰብ መምሰል እንዳለበት ያስረዳሉ። ጣልቃ ገብነትን በትዳር ውስጥ መክተት ፈተናው ከባድ ነውና ወንዶች ይህንን ተጋፍጠው ከሚስታቸው ጋር ብቻ መመካከር ይኖርባቸዋል ባይ ናቸው።
በባለቤታቸው ቤተሰቦች ዘንድ እናትነታቸው ጥያቄ ውስጥ ገብቶ እንደነበር የሚያስታውሱት ባለታሪካችን፤ መማርን በማስቀደማቸው ብዙ ፈተናን አሳልፈዋል። ይህም ሆኖ በባለቤታቸው ብርታት ተሻግረውታል። እርሳቸውም ቢሆኑ አይበገሬ እንዲሆኑ አስችሏቸዋል። እናም ከዚህ የተነሳ ሴቶች እንዲህ ዓይነት ችግር ሲገጥማቸው ቶሎ ተስፋ መቁረጥ ሳይሆን የትዳር አጋራቸውን ይዘው ውሳኔ ሰጪ መሆን ይኖርባቸዋል ሲሉ ይመክራሉ። በሴቶች ላይ የሚደረጉ ጫናዎች እንደ ልማድ ብዙ ችግሮች ቢጥልብንም የምናልፍበት ጥበብ ተሰጥቶናልና ያንን መጠቀም ያስፈልጋል ባይ ናቸው።
ማኅበረሰቡ እኛን ሁሌ በጫና ውስጥ ማለፍ እንዳለብን ያስባል የሚሉት ባለታሪካችን ይህ መሆን እንደሌለበት ማሳየት ደግሞ ከእኛ ከተማርን ሴቶች ይጠበቃል ይላሉ። ስኬታማ ለመሆን ጫና መኖሩን አምኖ መጋፈጥ ተገቢ እንደሆነም ይናገራሉ። ማንኛዋም ሴት ጥቃቅን ነገሮች ተስፋ ሊያስቆርጧት አይገባም። ምንአባቱ የምትልም መሆን የለባትም። ከዚያ ይልቅ ነገሩን ተፋልሞ ከዛሬ ነገ እሻላለሁ ብሎ በማመን ወደፊት መጓዝ ይኖርባታልም ምክራቸው ነው።
‹‹….ልሞክረው ሳይሆን እችላለሁ ማለትን ማስበለጥ እንደሚያስፈልግ›› የሚያወሱት ባለታሪካችን፤ ለራስ ሁልጊዜ የነገን ተስፋ መንገር ከምንም በላይ ያስፈልጋል ብለው ያምናሉ። ሴቶች ይህንን ማድረግ እንዳለባቸውም ከተሞክሯቸው በማንሳት ይመክራሉ። እንዳንደክም ዕድሎችን ማየት፣ የተሰጠንን መጠቀምና ጊዜያችንን ከትምህርትና ከተፈጥሮ ጋር አዋህደን ወደፊት መገስገስ ይገባናልም ይላሉ።
‹‹ውሳኔ ከምንም በላይ ለሴት ልጅ አስፈላጊ ነው። በተለይም በልጆች በኩል የሚመጣውን ነገር መቋቋም መርህአቸው ማድረግ አለባቸው። እናትነታቸውን ፈተና ውስጥ በሚከት መልኩ ጭምር ችግር ይደርስባቸዋል። ሆኖም ጉዳቱ የማይበልጥና እነርሱን የማይነካ ከሆነ ወስነው አላማቸውን ከግብ ለማድረስ መትጋት ያስፈልጋቸዋል። እኔ ልጄን ለእናቴና ባለቤቴ ትቼ ዩኒቨርሲቲ ስሄድ እናት ሳልሆን ቀርቼ አይደለም፤ ለነገ የተሻለውን አቅጄላቸው ነው። ስለሆነም ሌሎች ሴቶችም ለልጆቻቸው የሚያስቀምጡት ነገር አርአያነታቸው፣ በትምህርት የተሻሉ መሆናቸውና ከዘመኑ ጋር የሚስማሙ መሆናቸው ነውና ይህንን ሊያደርጉላቸው ይገባል›› የሚመክሩት ነገር ነው።
የተማሩ ሴቶች ከላይ ያሉትን ብቻ ሳይሆን ከታች ያሉትንም መመልከት ያለባቸው። እነርሱ እንዲነሱ አርአያ መሆን ብቻ ሳይሆን ያሳለፉትን መንገድ ማሳየትና ከእነርሱ እንዲማሩ መምከር ይኖርባቸዋል። ብዙዎች ጥያቄ ለመጠየቅ እንኳን የሚያፍሩ ናቸው። እንዴት ህልማቸው ላይ መድረስ እንዳለባቸውም አያውቁም። በዚህም ማኅበረሰቡና ባህሉ የሚያደርስባቸውን ጫና ብቻ ተቀብለው ይኖራሉ። ማንም ሴት ዕድሎች ከተመቻቹላት ያሰበችበት ላይ ትደርሳለች። ያልታሰበውን ጭምር የማሳካት አቅም አላት። እናም በተለይም በገጠሪቱ የሚኖሩ ሴቶች ይህንን አምነው የሚሰጣቸውን ዕድል መጠቀም አለባቸው። በተለይም መማር የአሁንም የወደፊቱም ስንቃቸው መሆኑን ማሰብ እንደሚገባቸው ይናገራሉ።
መልዕክት
ማንም ሰው የተሻለውን ነገር በአለበት መስክ ላይ ለመሥራትና ለማለም የአገር ሰላም መሆን ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ ነው። ሰላም ሲፈተን ጤና ጭምር ይታወካል። ይህ ደግሞ የመኖርና ያለመኖር ጉዳይን ጥያቄ ውስጥ ይከታል። እናም አሁን ያለንበት ነባራዊ ሁኔታ ከምንም በላይ ስለሰላም የሚሠራበት ነው። ቀጣይ የሚታሰበው ነገር እንዲመጣ መጀመሪያ የሆነውን ሰላምን መሥራት ያስፈልጋል። ለዚህ ደግሞ ሴቶች ትልቅ ድርሻ አላቸው። ሰላሙን የሚያደፈርሰውን አካል ሀይ ማለት ይችላሉ። በተለይም ጦር የሚሰብቀው ወንዱ በመሆኑ በጥበባዊ ዘዴያቸው ይህንን ማስቀረት ይገባቸዋል ይላሉ።
ሌላው ያነሱት ሀሳብ ሴት ልጅ ልጅን በፈለጋት መስመር መምራት እንደምትችል ሲሆን፤ አትሂድ፣ አታድርግ፤ ይህንን ዓይነት ልጅ ሁን በማለት ከጨቅላነታቸው ጀምሮ በመሥራት አገር ወዳድና ሠራተኛ ዜጋ መፍጠር እንዳለባትም ይመክራሉ። መልካሙን ጎዳና ከአባት ይልቅ እናት የምትመራ ብቃት አላት። ስለሆነም ምሰሶነቷን በዚህ ጊዜ ማሳየት ይኖርባታል። እንደመንግሥትም ቢሆን የእርሱን ሥራ ከመወጣቱ ባሻገር መልካም ተግባራትን የሚከውኑ እናቶችን ማበርታትና ለሰላሙ አሻራቸውን እንዲያሳርፉ ማድረግ ይገባዋል ብለዋል።
እንደ ምርምር አሁን ባለንበት ሁኔታ በተለይም ተላላፊ በሽታዎች ማለትም እንደ ቲቪ ዓይነት በሽታዎች ብዙዎችን እያስቸገሩ ይገኛሉ። በተለይም ተፈናቃይ በሚበዛባቸው አካባቢዎች ይህ ዓይነቱ በሽታ እና ሌሎች ተላላፊ በሽታዎች በስፋት የመሰራጨት ዕድላቸው ሰፊ ነው። እናም ያንን ለማከም ከባለሙያው ባለፈ ስለሰው ልጅ ያገባኛል የሚል ሰው ሁሉ መረባረብ ይገባዋል። ሰው አሁን አጋዥን፣ ደጋፊንና አሻጋሪን ይሻል። አይዞህ ባይንም ይፈልጋል። እናም ሁሉም በቻለው ልክ መደገፍና ከችግሩ እንዲወጣ ማድረግ ይገባዋል! መልዕክታቸው ነው።
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን ግንብት 21 ቀን 2014 ዓ.ም