ግለሶቦችን በመልካቸው ለመለየት እንደማያስቸግር ሁሉ፤ ሀገራትም የሚታወቁበት የራሳቸው መልክ አላቸው። የሀገራት ውበትም ሆነ የፊት እድፍ መገለጫው ብዙ፤ መከሰቻውም የዚያንው ያህል የትዬለሌ የሚባል ዓይነት ነው። የየሀገራቱ መልከ ብዙ ገጽታቸው የሚነበበው፣ የሚያያዘው፣ የሚሳለውና የሚቀረጸው በተፈጥሯዊው የጂኦግራፊ ውስን ክበብ ተቀንብቦ ብቻ አይደለም። በዋነኛነት የሀገር መልክ ማሳያ መስታወቱ የዜጎች መልክ ነው። ውበቱም ሆነ ጉድፉ የሚንጸባረቀው በዜጎች የአኗኗር ሰሌዳ ላይ ተስሎ ነው።
ብሂሉ “አብ ሲነካ፤ ወልድ ይነካ” እንዲል፤ የአገር ፊት የሚፈካውም ሆነ የሚጠይመው (የሚዳምነው)፣ የሚደምቀውም ሆነ የሚደበዝዘው በዜጎች አቋም ልክ፣ በአኗኗራቸውና በሥነ ምግባራቸው፣ በዓለም አደባባዮች ፊት በሚገለጸው የማንነታቸው መለያ ጭምር ነው። “ሀገር ማለት ሰው ነው፤ ሰው ነው ሀገር ማለት” የሚለው ረቂቅ ብያኔ (ተፈጥሯዊ መልክዓ ምድሩ ሳይዘነጋ) ከዚህ ዐውድ ጋር ቢጎዳኝ ትክክለኛ ቦታው እንደሚሆን ይታመናል። የኢትዮጵያ ስም ተነሳ ማለት ኢትዮጵያዊነትም አብሮ ስለሚነሳ አንዱ ያለ ሌላው ብቻውን መቆም አይችልም።
ከላይ የተጠቃቀሰውን ጥቅል የፍልስፍና ሃሳብ ዘርዘርና ፈታ አድርገን በማሳያ ምሳሌዎች እያጎለበትን በመልክ በመልኩ ለመሰደር እንሞክራለን። ትናንት ከትናንት ወዲያ የኢትዮጵያ በጎ ስም በዓለም መድረኮች ሲተዋወቅ የነበረው እንዴትና በእነማን ነበር? ሩቅ ምሥራቆች ኢትዮጵያን ከአበበ ቢቂላ ጋር ማያያዛቸው የተለመደ አልነበረም? የካሪቢያን አገራትና በርካታ የወቅቱ ምዕራባውያን አገራትም “ኢትዮጵያን” አጠይመው ሳይሆን አድምቀው ይስሏት የነበረው በማንና እንዴት እንደነበር ለብዙ ዜጎች የተሰወረ አይደለም።
የኢትዮጵያን መልክ በስፖርታዊ ውድድሮች ያደመቁት የቅርቦቹ ኃይሌ ገ/ሥላሴና ደራርቱ ቱሉን መሰሎች ቢጠቀሱም አግባብ ነው። የፊልም ጥበብ ባለሙያው ፕሮፌሰር ኃይሌ ገሪማ፣ በማሽላ ምርጥ ዘር አበርክቷቸው ዓለም ነዎሩ ያላቸው ፕሮፌሰር ገቢሳ ኢጄታ፣ የቢላሃርዝያ በሽታን ከቀንድ አውጣ ያፋቱት “የእንዶዱ ንጉሥ” ፕሮፌሰር አክሊሉ ለማ፣ የብዝሐ ሕይወት ሳይንቲስቱ ሎሬት ዶ/ር ተወልደብርሃን ገ/ እግዚአብሔር በርካታ የጦር ሜዳ ጀግኖችና ሌሎች በየዘመኑና በየጊዜው በተለያዩ ሙያዎቻቸው ለኢትዮጵያ ፊት መፍካት የክብር ወዝ የሆኑ ልጆቿና መታወቂያዎቿ ብዙዎች ናቸው፤ በርካቶችም ራሳቸው ተከብረው አገራቸውን እንዳከበሩ አልፈዋል።
የቅዱስ መጽሐፉ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “የእምነት አርበኞች” ብሎ የሰየማቸውን ሰማዕታት ስም መዘርዘር ጀምሮ ከብዛታቸው የተነሳ መዝለቅ ሲሳነው፤ “እንግዲህ ምን እላለሁ…እነዚህን የሚያህሉ ምስክሮች በዙሪያችን ከበውናል” ብሎ ሃሳቡን እንደጠቀለለው ሁሉ ይህ ጸሐፊም ይህንኑ አባባል ተውሶ “መልከ ኢትዮጵያን” ያፈኩት ሺህ ምንተ ሺህ ጀግኖቿን በሙሉ መዘርዘር ስለማይችል እንዲሁ ብቻ በበጎ ሥራቸው “እንደ ደመና ከበውን እንደሚኖሩ” ጠቅሶ ማለፍ ይቻላል። ክብርና ሞገስ ይሁንላቸው።
በድርቅና በረሃብ፣ በጦርነትና በዜጎች የእርስ በእርስ ግጭት ምክንያት መፈናቀል በተከሰተባቸው ዘመናትና ዓመታትስ “ኢትዮጵያ” በተቀረው ዓለም ፊት መልኳን ማድያት ወርሶት ትሳል የነበረው በምን ዓይነቶች የዜጎች ውክልና ነበር? “ከሰደበኝ መልሶ የነገረ ገደለኝ” እንዲሉ፤ ሀገራዊ ውርደታችንን ደግሞ ደጋግሞ ማስታወሱ ተገቢነት ስለማይኖረው እንዲሁ “በሾላ ድፍን” ቁጭት ጠቁሞ ማለፉ ይበጃል።
በሌላ አንጻርም መላው የዓለማችን ሀገራት ፈላስፎች፣ የታሪክ ተመራማሪዎች፣ የሃይማኖት ምሑራን፣ የየመንግሥታቱ ተወካዮችና ዜጎቻቸው ጭምር ኢትዮጵያን በበጎነት ሲገልጡ የኖሩባቸው በርካታ ማሳያዎች እንዳሉም ማስታወስ ይቻላል። ለአውሮፓ ቅኝ ገዢዎች ያልተንበረከከች የጀግኖች ምድር፣ ልዩ ልዩ ሃይማኖቶችን በፍቅር ተቀብላና አከባብራ የምትኖር አገር፣ ባዕዳን እንግዶችን ለመቀበል በሯንና ልቧን ያለስስት ወለል አድርጋ በፍቅርና በርህራሄ ለመክፈት የማትሰንፍ እንግዳ ተቀባይዋ የደጋግ ሕዝቦች መገኛ፣ የበርካታ ተፈጥሯዊና ታሪካዊ ቅርሶች ባለቤት፣ የውብ ባህሎች ሙዳይ፣ ቋንቋዋና ታሪኮቿ የሚያማልሉ ኢትዮጵያ፣ የአሥራ ሦስት ወራት የተፈጥሮ ፀጋ ባለቤት ወዘተ. እያሉም አይደል? ለዚህም ነው መልኳን ከገፀ ምድሯና ከልጆቿ ታሪክና ገድል መነጠል አይቻልም ያልነው።
የዛሬዪቱ ኢትዮጵያ መልክስ?
የአገሬ መልክ በተጀማመሩት አገራዊ ትሩፋቶች ምክንያት ለዓለም ማኅበረሰብ ፈክቶ ከመታየት ይልቅ በማድያት በሽታ እንዲጠይምና እንዲጠቁር ሰበብ የሆኑ በርካታ ወቅታዊ ፈተናዎችና ተግዳሮቶች ብዛታቸውም ሆነ ዓይነታቸው የተዥጎረጎረው ስለምንድን ነው? በተወሰኑ ፀረ አገርና ሕዝብ ቡድኖችና ግለሰቦች በመፈጸም ያሉት እነዚህን መሰል ክፋቶች ከእኛም አልፎ ተርፎ የዓለም ሕዝብም ሳይቀር ዐይኑን በዐይናችን ላይ ጥሎ ከእኛ እኩል ባለጉዳይ እስከ መሆን የደረሰ ይመስላል። አንዳንዱ ሳይጠሩት አቤት፤ ሳይልኩት ወዴት ባይ ጥልቅ ብዬ ከእኛ ከዜጎች በላይ ተቆርቋሪ መስሎ የሚታየው ከራስ አጀንዳ ጋር ተያይዞ መሆኑን በብዙ ማስረጃዎች ስናመላክት ሰንብተናል። በስመ ሰብዓዊነትና ድጋፍ ክብራችሁን ካልነጠቅን፣ በሉዓላዊነታችሁ ላይ ካልተሳለቅን የሚሉትን “የክፋት ደጋሾች” ደጋግመን አስተውለናል።
አንዳንድ ወዳጅ አገራትና ሕዝቦችም እውነቱን በመረዳትና የጉዳታችንን ልክ በመገንዘባቸው በክፉ ቀን ወዳጅነታቸው ውለታ እየዋሉልን እንዳሉም አይዘነጋም። እንደነዚህ ዓይነት ወዳጆቻችን ከእኛ ከዜጎች እኩል እያማጡና በድጋፋቸውም ሳይለዩን ጸንተው መቆማቸው በታሪካችን ገጾች ውስጥ ስፍራ ሊያሰጣቸው የሚችል ነው። ምሥጋናችን ይድረሳ ቸው።
“የልጅ ክፉ፤ ፈጥኖ አይነቀል ሰንኮፉ” እንዲሉ፤ የሀገራችንን መልክ ከሚያወይቡት መሠረታዊ ችግሮቻችን መካከል አንዱ የሀገር ምሰሷችንን ለመናድ እየተንፈራገጠ ያለው አሸባሪው ሕወሓትና ተቀጣሪ ጀሌዎቹ እየፈጸሟቸው ያሉት እኩይ ድርጊቶች እንደሆኑ ምክንያቶቹን እየነቀስን ስንሰልቅ ስለባጀን ደግመን አንዘረዝረውም።
ይህ ስር የሰደደው የአሸባሪው ቡድን “የተቀበረ ፈንጂ” ምን ያህል ጥፋት እያደረሰ እንዳለና ሰንኮፉ ሙሉ ለሙሉ ተነቅሎ ስላላቀ እንደምን ክፉ እባጭ እንደሆነብን ግን ዛሬም በእለት ተእለቱ ሕይወታችን ውስጥ እየተገለጠ ነው። ሕሊና አለኝ የሚል የሰው ፍጡር በወገኑ ላይ ቀርቶ በባእድ ምርኮኛ ጠላት ላይ እንኳን የማይፈጽማቸው የክፋት ጥግ ጭካኔዎች በእኛው ጉዶች ሲፈጸሙ እያስተዋልን ነው። እነዚህ የቤት ውላጅ ጉዶች በንጹሐን ዜጎች ላይ የፈጸሙት ወረራ፣ የፈጸሙት አረመኔያዊ ግድያዎች፣ ዘረፋና የሕሊና ቁስሎች እንኳን ብዛታቸው ዓይነታቸውና አተገባበራቸው ራሱ ገና ተዘርዝሮና ተለይቶ ለዓለም ማኅበረሰብ በአግባቡ አልተገለፀም።
በሕወሓት የሽብር ቡድንና በጀሌዎቹ የተፈጸሙትን ግፎችና ጭካኔዎች በተመለከተ “ሰይጣን ራሱ ቢጠየቅ” – “እኔ ከሕወሓትና ከጀሌዎቹ የበለጠ ምን የከፋ በደል ፈጸምኩ?” በማለት ከፈጣሪ ጋር መከራከሩ አይቀርም። የግፎቹንና የወንጀሎቹን ዓይነት አንድም ሳይቀር መዝግቦ ለማጠናቀቅ እንኳን ግፉ በደረሰባቸው ዘመን ለምንኖረው ለእኛ ቀርቶ ለመጻኢው ትውልድ ባለሙያዎችም ቢሆን ፈታኝ እንደሚሆን ይገመታል።
“የአባትህ ቤት ሲወረር አብረህ በዝብዝ” እንዲሉ፤ የአሸባሪዎቹን ዳናና ፈለግ እየተከተሉ በሀገር መልክ ላይ ተጨማሪ ማድያት እንዲፈጠር ምክንያት የሆኑ ሌሎች ተቀጥላ አበሳዎችንም በስፋት እያስተናገድን መሆኑ ሌላው ሀገራዊ ፈተናችን ነው። ከአሁን ቀደም ለመግለጽ እንደተሞከረው ጨለማን ተገን አድርገው ብቻ ሳይሆን በብርሃንና በአደባባይ ላይ ጭምር ሕዝብን የሚያማርሩና የአገርን መልክ የሚያጠይሙ በሌሊት ወፍ የሚመሰሉ ቡድኖች ከጊዜ ወደ ጊዜ ቁጥራቸው እያሻቀበ፣ ሴራቸው እየረቀቀ በመሄድ ላይ መሆኑ በግላጭ እየተስተዋለ ነው።
በመንግሥት ቢሮክራሲና በፖለቲካ ፓርቲ ዐይነ ርግብ ተሸፍነው ሕዝቡን የሚያስለቅሱ “የሰብዓውያን ተባዮች” ዓይነትና ቁጥርም እንዲሁ ከጊዜ ወደ ጊዜ “እየፈላ እንዳለ” በብዙ ማሳያዎች ማረጋገጥ ይቻላል። እነዚህን መሰል ሕሊናቸውን ለንዋይ፤ ክብራቸውን ለአስገባሪያቸው የሸጡ ቡድኖችና ግለሰቦች ሕዝቡ ተረጋግቶ የእለት ተእለት ሕይወቱን እንዳይመራና እፎይ እያለ ውሎ እንዳያድር በሽምቅ ውጊያ እያጣደፉ ያዋክቡታል።
በታሪካዊ ጠላቶቻችን ሴራ እና በአፍቅሮተ ራስ እየተሸነገሉ “ሆዳቸውን አምላካቸው፤ ክብራቸውን በነውራቸው” የለወጡ የማኅበረሰቡ አረሞች ብዙ ጉዳዮቻችንን ማናጋት ብቻም ሳይሆን አገራዊ ማድያቱም ጎልቶ እንዲታይ አቅማቸውና ኔትወርካቸው የፈቀደላቸውን ሁሉ እየፈጸሙብን ነው። “ሆዳም ቢሸከም የበላ ይመስለዋል” እንዲሉ “በተስፋ እያጀሉ የሚያልሷቸው አሞሌ” ለሀገርና ለሕዝብ ጥፋት ብቻ ይመስላቸዋል እንጂ ዞሮ ዞሮ ወጥመዱ አሰነካክሎ ጠልፎ የሚጥላቸው ራሳቸውን መሆኑን እንኳን ሊረዱ አልቻሉም።
እርግጥ ነው የሀገር መልክ በጊዜያዊ ፈተናዎች የወየበ ቢመስልም እንደገና ፈክቶ ለመድመቅ ጊዜው ሩቅ አይሆንም። የሀገራችንን ፊት እንደ ስራይ ያበላሸው መርዝም ሙሉ ለሙሉ ተነቅሎ መወገዱ አይቀሬ ነው። እስከዚያው ግን አገር በሠራዊት፣ መንደር በነዋሪ፣ ቤት በአባወራና በእማወራ እንደሚጠበቅና እንደሚመራ ሁሉ እያንዳንዱ ዜጋ በተሰለፈበት መስክ ሁሉ “የወር ተራ” ግዴታውን እየተወጣ አገሩን መታደጉ ውዴታ ብቻም ሳይሆን ግዜው የሚጠይቀው ትውልዳዊ ግዴታ ጭምር ነው።
መንግሥትም ቢሆን ሕዝብን ከማገልገል ይልቅ በእምባው ለመሳለቅ ማልደው የሚወጡትን አንዳንድ ሹሞቹን ካድሬዎቹንና፣ አቀባባዮችን አደብ እንዲያስገዛ የምንጠይቀው ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር የተያያዙ ብዙ በርካታ የችግር ጎርፎች ገደባቸውን እየጣሱ በመገንፈል ላይ መሆናቸውን ስለምናስተውል ነው። ጉቦ በድብቅ መሆኑ ቀርቶ በምስክር ፊት፣ አደራዳሪና አቀራራቢ ደላሎች ባሉበት ሲከወን ማስተዋል ተለምዷል። በዚህ ጉዳይ ላይ የሀገር መልክ ብቻ ሳይሆን የብዙ ዜጎች መልክም በድንጋጤ እየወየበ “መጨረሻችን ምን ሊሆን ይሆን” በማለት የማዲያቱ ግዝፈት እያስፈራ ያስበረግገናል።
የጸጥታውና የሰላሙ ጉዳይም በሕዝብ ትብብርና ተሳትፎ ተደግፎ እስካልጸና ድረስ በጸጥታ ኃይሎች ትከሻ ላይ ብቻ መጣሉ የሚፈለገውን ውጤት ላያስገኝ ይቻላል። “የመንግሥት ያለህ እያልን የምንጮኽበት መንግሥት” እለት በእለት የሕዝቡን ሃሳብ ማድመጥና “ሰምቻለሁ” ማለት ብቻም ሳይሆን ቁርጥ ባሉ ጉዳዮች ዙሪያ በእለት ውሎው ጠንከር የሚሉ የአደራ ኃላፊነቶችን ሊያሸክመው ይገባል።
በየአካባቢው ተደራጅቶና ተባብሮ “በዚህና በዚያ ጉዳዮች ዙሪያ ይንቀሳቀስ” የሚል አቅጣጫም ሊሰጥ ይገባል። ከሕዝቡ ጋር በቅንጅት የሚሠሩ በርካታ ጉዳዮች ስለመኖራቸው መንግሥታዊ መዋቅሮች ባይጠፋቸውም፤ የምርና ጨከን ብለው ሊተገብሩት ይገባል። የኢትዮጵያ ማድያት ጊዜያዊ ነው። ይፈወሳል። ብሩህ ገጽታዋም በአጭር ጊዜ ፈክቶ እናያለን። ይህ እስከሚሆን ድረስ ግን ጥቂት በጥቂት ችግሮቻችንን እየጨለፍን “ይድረስ” ለማለቱ አንሰንፍም። ሰላም ይሁን!
በ(ጌታቸው በለጠ /ዳግላስ ጴጥሮስ)
gechoseni@gmail.com
አዲስ ዘመን ግንቦት 20/2014