• የትግራይ እናቶች ልጆቻቸው ለሞት ሲመለመሉ እምቢ ማለት አለባቸው
በወላይታ ዞን አንጮጮ ከተማ ነው የተወለዱት። የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን በወላይታ ዞን በሚገኘው ጎላ በተባለ ትምህርት ቤት እንዲሁም አዲስ አበባ አመሐ ደስታ ትምህርት ቤት ተምረዋል። ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ደግሞ በአስፋ ወሰንና ልዑል መኮንን ትምህርት ቤቶች ነው የተከታተሉት። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን እንዳጠናቀቁ በቀጥታ ብሔራዊ ሀብት ልማት ይባል በነበረው መንግሥታዊ ድርጅት ውስጥ የተቀጠሩ ሲሆን በተለይም በፍልውሃዎች አስተዳደር በተለያዩ ኃላፊነቶች ላይ ተመድበው ለበርካታ ዓመታት ሠርተዋል። እንዲሁም በተለያዩ የመንግሥት ሆቴሎች መምሪያ ኃላፊ ደረጃ በመድረስ ሀገራቸውንና ሕዝባቸውን አገልግለዋል።
ከልጅነታቸው ጀምሮ ፍርድ ቤት ከሚሠሩት አባታቸው ስር በመሆን የፍርድ ቤቶችን ውሎ፤ የከሳሽና ተካሳሽ ክርክርን እየሰሙ፤ ክሶችን እየፃፉ ያደጉት እኚሁ ሰው የመማር እድሉን እንዳገኙ የተማሩት የሕግ ትምህርትን ነው። አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ገብተው ዲፕሎማቸውን ካገኙ በኋላ በዚያ ተቋም ውስጥ የሕግ ክፍል ኃላፊ ሆነው ሠርተዋል። በዚህም አልተወሰኑም፤ የትምህርት ደረጃቸውን በማሻሻል የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በሕግ አገኙ። እንግዳችን በነገረ ፈጅነትና በሕግ አማካሪነት ለረጅም ዓመታት ሕዝብና ሃገራቸውን ያገለገሉ ሲሆን በዚህም ምስራቅ አውሮፓ ሞስኮና ቼኮዝሎቫኪያ ተልከው በፖለቲካ ሳይንስ ዘርፍ ስልጠና ወስደዋል።
በመቀጠልም ቀድሞ ኢዲዲሲ ይባል በነበረው አሁን ደግሞ የኢንዱስትሪ ግብዓቶች በሚባለው ድርጅት ውስጥ የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ፤ የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያና ኃላፊ በመሆን ሠርተዋል። ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ደግሞ በንግድ አስተዳደር የሠሩት እኚሁ እንግዳችን በአሁኑ ወቅት በፌደራል ፍርድ ቤቶች የሕግ አማካሪ ጠበቃ ሆነው እየሠሩ ይገኛሉ። አቶ ካሳሁን ወርቄ በወቅታዊ ሃገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር ቆይታ አድርገዋል። እንደሚከተለው ይቀርባል።
አዲስ ዘመን፡- ለእርስዎ ኢትዮጵያዊነት ምን ማለት እንደሆነ ያንሱልንና ውይይታችንን እንጀምር?
አቶ ካሳሁን፡- ኢትዮጵያ ለእኔ ሕይወቴ፤ እናቴ፤ ቤቴም ናት። ምን ብዬ ልገልፃት እንደምችል አላውቅም። ለእኔ እዚህ መድረስ ትልቅ አስተዋፅኦ ያደረገችልኝ ኢትዮጵያ ሃገሬ ናት። ሕዝብ ሠርቶ በከፈለው ግብር ነው የተማርኩት። በሃገሬና በወገኖቼ የተደረገኝን ያህል ግን እኔ ሠርቻለሁ ብዬ አላምንም። ውለታዋንም አልከፈልኩም። ለሁላችንም ቢሆን ኢትዮጵያ መሰብሰቢያ ቤታችን ናት። ስለዚህ ኢትዮጵያዊ መሆኔ ከምን በላይ የሚያኮራኝ ነገር ነው። አሁን ያሉ ወጣቶች ለሃገራቸው ልዩ ክብር እንዲሰጡ እፈልጋለሁ። ኢትዮጵያ በዓለም ላይ ታሪኳ ያማረ፤ ብዙ ቋንቋ የሚናገሩ ብሔሮች ቢኖሩባትም አንድ ሆና የዘለቀች ሃገር ናት። ኢትዮጵያ ባትኖር እኛ ሁላችን ዛሬን ባላየን ነበር፤ እንደሶሪያ ዜጎች በየሃገሩ ስደተኛ ሆነን በኖርን ነበር። ስለዚህ እዚህ ላደረሰችን እናት ሃገራችን ሕልውና መቀጠል ከእኛ ምን እንደሚጠበቅ ቆም ብለን ልናስብ ይገባል።
እርግጥ ነው አሁን ላለው የሃገር ፍቅር ያለመኖር ችግር የትውልዱ ጥፋት ነው ብዬ አላስብም። ግን ትውልዱ ለሃገሩ እንዳያስብ፤ ግዴለሽ እንዲሆን፤ ጠያቂ እንዳይሆንና ለሆዱ ብቻ ያደረ እንዲሆን ሆን ተብሎ የተሠራ ሥራ አለ። ምክንያቱም ሆዱ ጠግቦ ካደረ ጥያቄ አያነሳም ተብሎ ስለታመነ ነው። ከዚህ ሴራ ያመለጠው ትውልድ ደግሞ እኔ እንደ ዕድለኛ ነው የምቆጥረው። ከዚህ ሴራ ያመለጡ ናቸው አሁን ላይ ጥቂትም ቢሆኑ ሀገራቸውን ከድህነት ለማውጣትና ለማሻገር እየታገሉ ያሉት። አሁን ላይ ለሀገራቸው የሚቆረቆሩ ወጣቶችን ሳይ እጅግ በጣም ነው የምደሰተው። ወጣቱ ሃገር ጠልና ሩቅ ናፋቂ የሆነው ባለፈው መንግሥት በተሠራበት ሴራ ነው። ወያኔ ከመጣ በኋላ ለስሙ ትምህርት ቤቶች እንዲስፋፉ ቢያደርግም ሆነ ብሎ ሥርዓተ ትምህርቱን በማበላሸት ሃገር ተረካቢ ትውልድ እንዳይኖር አድርጓል። ለፕሮፖጋንዳ ጥቅሙ ሲል በየክልሉ ዩኒቨርሲቲዎችን ቢከፍትም ውስጣቸው ባዶ ነው። ወጣቱ እውቀት አግኝቶ እንዲወጣ ከማድረግ ይልቅ ፊት ለፊታቸው ሺሻ እና ጫት ቤት በመክፈት ትውልድ ገዳይ ስትራቴጂ ነበር የተከተሉት። በዚህ የተነሳ አብዛኛው ወጣት አጫሽና ጠጪ ሆኗል። በዚህ የተነሳ ለሃገሩ ያለው አስተሳሰብ ደከም ያለ ነው። በመሆኑም አሁን ያለው መንግሥት ትውልዱ ላይ ሆን ተብሎ የተሠራው ገዳይ ሴራ ተገንዝቦ ወጣቱ ከገባበት ችግር የሚወጣበትን፤ ጠያቂ የሚሆንበትን፤ ለሃገርና ለወገን የሚጠቅምበትን ሁኔታዎች ማመቻቸት ይጠበቅበታል ብዬ አምናለሁ።
አሁንም ቢሆን ያንን ሥርዓት ሲያራምዱ የነበሩ ግለሰቦች እኔ ካልገዛኋት ኢትዮጵያ ትፍረስ በሚል አሮጌ ብሂል ሃገርን ለማተራመስ እየሠሩ ነው። በተወሰኑ አጥፊ ሰዎች ምክንያት የአንድ ክልል ሕዝብ መጎዳት የለበትም። አሁን ላይ የትግራይ ሕዝብ ክፉኛ እየተጎዳ ነው ያለው። እነሱ ደግሞ ለዚያ ሕዝብ ምንም የተለየ ነገር አላደረጉለትም።የትግራይ ሕዝብ በስሙ ብቻ የተነገደበት ሕዝብ ነው። በመሆኑም እነዚህ ሰዎች ከዚህ ድርጊታቸው በመታቀብ ላጠፉት ጥፋት ተፅፀተው ሃገራቸውን ለመገንባት ቢሠሩ ጥሩ ነው ባይ ነኝ። ከዚህ ጥፋታቸው ተምረው የኢትዮጵያን ሕዝብ ይቅርታ መጠየቅ መቻል አለባቸው።
አዲስ ዘመን፡- ሕገ-መንግሥቱ የጭቁን ብሔሮችን መብት አስጠብቋል ብለው ያምናሉ?
አቶ ካሳሁን፡- በወረቀት ደረጃ የሁሉም ዜጎች መብት ተቀምጧል። ማንኛውም ኢትዮጵያዊ የመናገር የመፃፍ የመደራጀት ባህሉንና ቋንቋውን የማሳደግ፤ ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሶ የመሥራት መብት እንዲሁም ያለበቂ መረጃ መታሰር እንደሌለበት በሕገ-መንግሥቱ ተደንግጓል።ከዚህ አንፃር በሕገ-መንግሥቱ የተፃፈው ሁሉ ችግር አለበት ባልልም ትልቁ ሻጥር ያለው ወረቀቱ ላይ የተፃፈውና በተግባር የሚታየው የተለያየ መሆኑ ላይ ነው። ለምሳሌ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በሕግ ፊት እኩል መብት እንዳለው ሕገ-መንግሥቱ በግልፅ ነው የሚደነግገው። በተመሳሳይም ማንኛው ዜጋ ፍትሕ የማግኘት መብት እንዳለው አንቀፅ 9 ላይ ተቀምጧል። ግን እንደተደነገገው ሁሉም ትክክለኛ ፍትህ የሚሰጥበት ሁኔታ እንዳልነበረ ሁላችንም ምስክር ነን። የእነሱ ደጋፊና አባል ያልነበረ ሰው፤ ፖለቲካቸውን የሚቃወም ሰው ፍትሕ አያገኝም፤ ይሄም በተግባር የታየ ነው።
እኔ ነፍስ ካወቅኩበት ጊዜ ጀምሮ ማንኛው ሰው በሃገሩ ሠርቶ የመኖር መብቱ እንዲከበርለት ታግያለሁ። በሃሳብ የበላይነት መታመን እንዳለበት ያኔም ሆነ አሁን የምከተለው መርሕ ነው። ማንኛው ሰው በጎሳው ወይም ባለው ሃብት የተለየ ቦታ ሊሰጠው አይገባም የሚል አቋም ነው ያለኝ። የሃሳብ ግጭቶች ቢኖሩም የበላይ የሆነው ሃሳብ ደግሞ ሊገዛን ይገባል። የሃሳብ ግጭት ውስጥ የተሻለውን በማመዛዘን ነው ልንተገብር የሚገባው። በመሆኑም ሕገ-መንግሥቱ ላይ የተደነገጉት አንዳንድ ሃሳቦች ጥሩ ቢሆኑም እነሱም ቢሆኑ በአግባቡ ተግባራዊ አልሆኑም። የነበረው መንግሥት ከሃሳብ የበላይነት ይልቅ በጎጥና በዘረኝነት እንዲሁም በጉልበት ነበር ሕዝቡን ሲመራ የነበረው። በእነዚያ 27 ዓመታት ሰዎች ዜጋ በመሆናቸው እኩል መብታቸው ተጠብቆላቸው የኖሩበት አጋጣሚ የለም። ይልቁንም የጥቂቶች የበላይነት የገዘፈበትና ብዙኃኑ ደግሞ መብቱ ተደፍጥጦ የነበረበት፤ ፍትህ በወረቀት ላይ ብቻ እንዲቀር ነው የተደረገው።
በመሠረቱ ሕገመንግስቱ ብዙ ችግሮች ያሉበት እንደሆነ ብዙዎቻችንን እናምናለን። የኢትዮጵያ ሕዝብ በብዙ ብሔሮች የተዋቀረ እንጂ አንድ ብሔራዊ ማንነት ያለው ሕዝብ ነው። ሆኖም ወያኔ ይህንን ሕገ-መንግስት ካፀደቀ በኋላ ግን ለሺ ዓመታት አንድ ሆኖ የኖረው ሕዝብ በጎሳና በጎጥ ከፋፍሎ እርስ በርስ እንዲባሉ ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል ባይ ነኝ። በእኔ እድሜ እንኳን ከዚህ ቀደም በነበሩት መንግሥታት የኢትዮጵያ ሕዝብ የጎሳ የእምነት ጉዳይ አሳሳቢ ሆኖበት ለግጭት የተዳረገበት ወቅት የለም። በጎሳ የመከፋፈሉ ክፉ ባህል ከ30 ዓመት በኋላ የመጣ በሽታ ነው። በዚህ መልኩ ሊቀጥል የሚገባው ግን አይደለም።
አዲስ ዘመን፡- ሕገ-መንግሥቱ ለክልሎች የሰጠው መብት የፌደራል መንግሥቱን ሕልውና አደጋ ላይ እንደጣለው አንዳንድ የሕግ ሰዎች ያምናሉ። እርስዎ በዚህ ሃሳብ ይስማማሉ?
አቶ ካሳሁን፡- በመጀመሪያ ደረጃ ማየት ያለብን የምንከተለውን የፌደራሊዝም ሥርዓት ነው። እያንዳንዱ ክልል ራሱን በራሱ ማስተዳደር እንዳለበት ይፈቅዳል። የፌዴራል መንግሥት ደግሞ በበላይነት ሁሉንም የሚያጠቃልል ለሁሉም የሚሆን አስተዳደር የሚፈጥር እንደሆነ ነው የሚታመነው። እያንዳንዱ ክልል የራሱን ሕዝብ የሚያስተዳድርበትና የሚመራበትን ሕግና ሥርዓት የማበጀት መብት በሕገ መንግሥቱ ሰጥቶታል። ሆኖም ይህንን ማድረግ የሚቻለው ከፌዴራሉ ሕግ እንዳይጣረስ በማድረግ ነው። እንደእኔ እምነት በቀና መንፈስ ከታየ፤ እውነት ለሕዝብ ከታሰበ ክልሎች ራሳቸውን በራሳቸው ማስተዳደራቸውን መደገፍ እንጂ መቃወም የለብንም። ነገር ግን የፌደራሉን መንግሥት በሚቃወም የሚያስችል መብት ሊኖራቸው ይገባል ብዬ አላምንም።
እኔ እንደሕግ ባለሙያነቴ እያንዳንዱ ክልል ሕግ የፌደራል መንግሥቱን ሕግ መቃወም ይገባዋል ብዬ አላምንም። ለምሳሌ ክልሎች የሚያወጡት ሕግ ከፌዴራሉ ሕገ-መንግሥት ጋር የተቃረነ ሊሆን አይገባም። እንደሚባለውም ኢትዮጵያዊ አንድነታችን ላይ መጥፎ
ጥላ የሚያጠሉ ሕጎችና አሠራሮች ካሉ ይህንን ማስወገድ ይገባል። ይህንን አጀንዳ ለሚያጠነጥኑ ግለሰቦችም ትክክል አለመሆኑን ማስረዳት ከመንግሥት ይጠበቃል። ጥላቻን የሚሰብኩ፤ አንድነትን የሚያፈርሱ የክልል መዝሙሮች ሊቀየሩ ይገባል። ይህንን እያየ ዝም ብሎ ያስቀጠለ የመንግሥት አካልም ተጠያቂ ሊሆን ይገባል ባይ ነኝ። እርግጥነው ላለፉት 30 ዓመታት ሆነ ተብሎ ልዩነት እንዲሰፋፋ መከፋፋል እንዲፈጠር ሲባል ጎሰኝነት አይሎ ሃገራዊ ኅብረት እንዲጠፋ ተደርጓል። የወያኔ መንግሥት ሆነ ብሎ ሕዝቡ እንዲገነጣጠል፤ እርስ በርሱ እንዳይተማመን፤ እንዲጠራጠር፤ እንዲፋጅ ያደረገው ሴራ ነው። ያንን እያደረገ እነሱ በሰላም ሲኖሩ ሕዝቡ በማያውቀው ሁኔታ እርስ በርስ እንዲባላ ተደርጓል። ይህንን ሴራ ደግሞ ሕዝቡ መንቃትና ማወቅ ነበረበት። አሁን ግን ይህ ነገር ታውቋል፤ ስለዚህ የነበረውን ቅራኔ የሚያጠፋ ሥራ ይሠራል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ። እንደሚታወቀው ደግሞ ሕጉን በማሻሻል ረገድ አሁን ስልጣን ላይ ያለው መንግሥት ከመመረጡ በበፊት እንደሚያሻሽለው ለሕዝቡ ቃል ገብቶ ነበር። እስካሁን ግን ምክር ቤቱ ሲወያይበት አላየሁም፤ ምንአልባት ቀዳሚ የቤት ሥራዎች ስላሉበት አዘግይቶት ሊሆን ይችላል። ግን በቀጣይ ጊዜ ሳይወስድ ሕጉ የሚሻሻልበት ሁኔታ ሊያበጅ ይገባል የሚል እምነት አለኝ።
አዲስ ዘመን፡- እንደሚያውቁት ዛሬ ግንቦት 20 ነው። ይህ ቀን ሁለት ወንድማማቾች ተጣልተው አንደኛው ድል ቀንቶት ስልጣን የተቀዳጀበት ቀን ከመሆኑ በዘለለ ላለፉት 27 ዓመታት ልክ እንደውጭ ወራሪ የነበረውን መንግሥት በጠላትነት ሲወገዝና ሁሉም በጎ ሥራው ሳይቀር በማንቋሸሽ ነው ሲከበር የነበረው። ለእርስዎ ይህ ቀን ምንድንነው? ቀኑስ በዚህ መንገድ እስከመቼ ነው መከበር ያለበት ብለው የሚያምኑት?
አቶ ካሳሁን፡- በመሠረቱ ደርግ ምንም እንኳን ወታደራዊ ሥርዓት ቢሆንም የሠራቸው በርካታ መልካም ሥራዎች አሉ። ከሠራቸው ሥራዎች በዋናነት የሚጠቀሰው ደግሞ ለአራሹ የኅብረተሰብ ክፍል የመሬት ባለቤት እንዲሆን ማድረጉ በዋናነት የሚጠቀስ ነው። በተመሳሳይ አዋጅ ቁጥር 47/67ም መኖሪያ የሌለው የከተማ ነዋሪም ቤትና መሬት እንዲኖረው ማድረጉ ሊመሰገን የሚያስገባው ነው። ሆኖም በሂደት ሥርዓቱ እየተበላሸ መጣ። ብዙዎቻችን እንደምናውቀውም ሁሉም ነገር ኃይል ቅልቅል በመሆኑ የሕዝብ ተቀባይነት ያጣበት ጊዜ ነበር። እኔ ራሴ ታስሬ ከሞት ለጥቂት ነው ያመለጥኩት። ግን ደግሞ ወያኔ ያኔም ቢሆን ሃገር ለማፍረስና መንግሥቱን ለመገልበጥ ሲል ብቻ ይሠራ የነበረው ሥራ ደርግ እንዲጠላ ምክንያት ነው ባይ ነኝ። ወያኔ እርስበርስ እንድንዋጋ ብቻ ሳይሆን ሱማሌን በመደገፍ ጭምር ሃገር ለማፍረስ የሠራው ሥራ ታሪክ የማይረሳው ነው።
ወያኔም ሲገባ መጀመሪያ ላይ ለሕዝብ የሚያስብ ይመስል ነበር፤ ብዙዎቻችንንም ደግፈነው ነበር። የደገፍነው ግን ውስጣዊ ዓላማውን በቅጡ ስላልተገነዘብን ነበር። በሂደት ነው እየተጋለጠ የመጣው። አካሄዱ ሲታይ ለአንድ ወገን የቆመ መሆኑን እያንፀባረቀ ሲመጣ፤ የሚቃወመውን እየገደለና እያሰረ ሲታይ ከሕዝብ ልቦና ወጣ። በዚህ የተነሳ እኔ በግሌ የዛሬውን ቀን ዘመኔን ሙሉ ስጠላውና ስረግመው ነው የኖርኩት። ያ ቀን ሲመጣ በጣም ይሰማኝ ነበር። የሚሰማኝ ወያኔ ያደርግ የነበረውን ድርጊት በማስታወስ ነው። ከገባ በኋላ ንፁሓንን በየቦታው እያሳፈነ ሲገድል፣ ኢትዮጵያን፣ ትውልዱን ለማጥፋት የሚያደርውን በማሰብ ነው። አስቀድሜ እንዳልኩሽ ለፖለቲካው በየቦታው ዩኒቨርሲቲ ይከፍታል ባጠገቡ ጫት ቤት እንዲከፈት ያደርጋል። በሰሜን አብዛኛው መሬት ጫት እንዲተከልበት ያደርጉ ነበር።
ይህ የሚያሳየው ሆን ተብሎ ወጣቱ በሱስ እንዲያዝ ለማድረግ ነው ። አብዛኛውን ወጣት በሱስ እንዲለከፍ፣ እንዲያብድ ተደርጓል፤ አብዛኛው ወጣት ብቻውን በየመንገዱ እየለፈለፈ ሲሄድ ይታያል። ስለዚህ ወያኔ ቢያንስ ሁለት ትውልድ እንዲጠፋ በማድረግ ወንጀል ፈፅሟል ባይ ነኝ። ለዚህም ነው ግንቦት 20 በመጣ ቁጥር መጥፎ ስሜት ነው የሚሰማኝ ያልኩሽ። የሚገርመው ደግሞ ወያኔ እስካዛሬ ዜጎቹ ላይ ሲፈፅም የነበረው በደል አልበቃ ብሎት ኢትዮጵያን ለመበታተን፣ ለማጥፋት አሁን እረፍት ማጣቱ ነው። አሁንም ቢሆን ግን የኢትዮጵያ ሕዝብ በወያኔ የቱንም ያህል ቢበደል ይቅር የሚል የተለየ ሕዝብ ነው። ስለሆነም ይህ ኃይል የሽብር ሥራውን በመተው ወደ ልማትና ግንባታ ቢገባ የተሻለ ነው ብዬ አስባለሁ።
ከዚህ በኋላ ይህ ቀን በምን መልኩ መከበር አለበት የሚለው ነገር መወሰን የሚችለው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ነው። ግን እኔ በግሌ ግንቦት 20 መከበሩን አልደግፍም። ምክር ቤቱ ይሄንን ተነጋግሮ ማስቀረት አለበት ብዬ አምናለሁ። በእኔ እምነት መከበር ያለበት የውጭ ወራሪዎችን ድል ያደረግንባቸው የአድዋ ድል የመሳሰሉትን በዓላትን ነው። እነዚህ በዓላት የኢትዮጵያ ታሪክ አካል ስለሆኑ በድምቀት መከበር አለባቸው። ለአዲሱ ትውልድ እነዚህ ታሪኮች መተላለፍ አለባቸው። እንደሚታወቀው እነዚህ በዓላት ኢትዮጵያውያንን አንድ የሚያደርጉ በመሆናቸው በትምህርት ቤት እንዳይማሩ ተደርጓል፤ ታሪክ ተዛብቶ ቀርቧል።
አዲስ ዘመን፡- ታሪክ ተዛብቶ የቀረበበትን ሁኔታ አብነት አድርገው ሊጠቅሱልን ይችላሉ?
አቶ ካሳሁን፡- ወያኔ ታሪክን አዛብቶ ያቀረበባቸው መንገዶች በርካታ ናቸው። ለምሳሌ ያህል ብንወስድ ወያኔ አንድ ወቅት ላይ ከአማራና ከቤኒሻንጉል ክልል በርካታ መሬቶችን ትግራይ ክልል ውስጥ በማስገባት የሠራው ካርታ ነበር። ለአንድ ጊዜ ሚዲያ ላይ ከታየ በኋላ ሕዝቡ ሲጮህ ነው መልሰው ያስቀሩት። የሚገርምሽ የጎንደርንና የቤኒሻንጉል ለም መሬቶችን በሙሉ በማካለል የራሳቸውን ግዛት አስፋፍተው ነው ያስቀመጡት። ይህንን ያደረጉት ከመጀመሪያውም ቢሆን ኢትዮጵያን የማጥፋትና የራሳቸውን ትልቅ ሃገር መፍጠር ዓላማ ስለነበራቸው ነው። አሁንም ቢሆን አካለው የያዙ መሬት አለ። ለዚህም ነው በእነዚህ መሬቶች ጉዳይ ጥያቄ እየተነሳ ያለው። በመሆኑም በዚህ ጉዳይ ላይ ምክር ቤቱ ትኩረት ሊመክርበትና እልባት ሊሰጠው የሚገባው።
አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ በጦርነትና በግጭት ውስጥ ትገኛለች፣ ሰላም ማስፈን አስቸጋሪ ሆኖ ይታያል፤ በመንግሥት በኩል ሰላምና ፀጥታ በማስከበር ሕዝቡ በሰላምና በነጻነት የመኖር መብቱ እንዲከበር ምን መጨራት አለበት?
አቶ ካሳሁን፡- በየቦታው የተከፈተው ሽምቅ ውጊያ የወያኔ ሴራ ነው። ሸኔ ቢባልም የወያኔ አሽከር መሆኑ ግልፅ ነው። በመጀመሪያ ደረጃ የኢትዮጵያ ሕዝብ ማወቅ ያለበት ኢትዮጵያ ከሌለች ሕልውና እንደሌለው መቁጠር አለበት። ሌላ ኃይል ከያዛት የሕዝቡ ታሪክ፣ ስማችን እንደሚጠፋ መገንዘብ አለበት። ወጣቱ ለሃገር እንዳያስብ ነው የተደረገው። ሃገር ምን እንደሆነ እንዳያውቅ፣ ፍቅር እንዳይኖረው፣ ጠያቂ እንዳይሆን በማድረግ ኢትዮጵያ ተረካቢ ትውልድ እንዳይኖራት ሆኗል። የሚገርመው በዚህ መልኩ ያደነዘዙትን አሁንም እየተጠቀሙበት ይገኛሉ። አርሶ የሚያድረውን፣ ኑሮውን ለማሸነፍ የሚታትረውን ሰው እያስፈራሩ ወደ ጦርነት እንዲገባ፣ እንዲፈናቀል እያደረጉት ናቸው።
ሸኔ ለኦሮሞ ሕዝብ ቆሜያለሁ ይላል ግን የራሱን ወገን እየገደለ ልማት እያጠፋ ነው። ሕዝቡ መሐል ያሉትን በማጋለጥ ሰላሙን ማስፈን ይኖርበታል። በመታለል፣ ባለማወቅ የገቡትን ሰዎች በማስተማር መመለስ ያስፈልጋል። ከጥፋታቸው ተምረው ለሃገር የሚሠሩበትን መንገድ እንዲማሩ ማድረግ ይገባል። በማስተማር ከጥፋት መንገዳቸው እንዲመለሱ ማድረግ ይገባል። አንመለስም ያሉትን ደግሞ ሕግ የሚፈቅደውን ማንኛውንም ርምጃ መውሰድ ይገባል ባይ ነኝ።
አዲስ ዘመን፡- ዳግም ወደ ጦርነት ለማስገባት የሚደረገውን እንቅስቃሴ እንዴት ይመለከቱታል?
አቶ ካሳሁን፡- የትግራይ ሕዝብ ጥሩ ሕዝብ፣ ታሪክ ያለው ትልቅ ሕዝብ ነው። በጥቂቶች ጠቅላላው የትግራይ ሕዝብ መወቀስ የለበትም። ሕዝቡ መታለል የለበትም፣ ዝም ብሎ ወደ ጦርነት መግባት አይገባውም። የትግራይ እናቶች ልጆቻቸው ለሞት ሲመለመሉ እምቢ ማለት አለባቸው። ሕዝቡ የወያኔ መሸሸጊያና መደበቂያ መሆን የለበትም። በተመሳሳይም የኦሮሚያ ሕዝብም ይህንን መገንዘብ ይገባል። ሸኔን አጋልጦ ሰላሙን ማስከበር ይጠበቅበታል። መንግሥትም ሕዝቡ እንዲነቃ ማስተማርና እነዚህን ፅንፈኛ ኃይሎች የሚታገልበትን ሁኔታ ማመቻቸት አለበት።
አዲስ ዘመን፡- ከሃገራዊ ምክክር ኮሚሽን ምን ይጠብቃሉ? ምን መሠራትስ ይኖርበታል?
አቶ ካሳሁን፡- በግሌ የኮሚሽኑ መቋቋም ጥሩ እንደሆነ ነው የማምነው። የእስካሁን የኮሚሽኑን አባላት የመምረጡ ሂደት መልካም የሚባል ነው። ከዚህ ጋር ተያይዞ ግን በማኅበራዊ ሚዲያው ኮሚሽኑን ለማጥላላት የሚደረገው ዘመቻ ትክክል እንዳልሆነ ተገንዝቤያለሁ። ሊታረም ይገባል። ወደ ጠየቅሽኝ ጥያቄ ስመለስ ግን ኮሚሽኑ ገና ተቋቋመ እንጂ በጣም ብዙ የቤት ሥራዎች እንዳሉበት እረዳለሁ። ታች ድረስ በመውረድ የሕዝቡን የልብ ትርታ ማዳመጥ ይጠበቅበታል። ኅብረተሰቡን በቀጥታ ማግኘት አለበት። እስከ ወረዳ በመውረድ ችግሮችን መዳሰስ አለበት። ሕዝቡን በማወያየት ስሜቱን መረዳት ይገባዋል። በዚህ መልኩ መላው ኢትዮጵያን ማዳረስ ከቻለ ኢትዮጵያን ያሻግራታል ብዬ አምናለሁ። መወያየቱ በራሱ አንድነቷን ያጠናክራል። የሕዝቡ ስሜትና የመንግሥት ስሜት አንድ የሚሆንበትን አጋጣሚ ይፈጥራል።
አዲስ ዘመን፡- የዋጋ ንረት፣ ሕገ ወጥነትና የኢኮኖሚ አሻጥር በተመለከተ የታዘቡትን ይንገሩኝ ምንስ መሠራት አለበት?
አቶ ካሳሁን፡- የኑሮ ውድነቱ ጣሪያ ነክቷል። አብዛኛው የኑሮ ውድነት የመጣው በአቅርቦት እጥረት አይመስለኝም። በንግዱ ውስጥ ያሉት እነማን ናቸው? አሁን ካለው መንግሥት ጋር ተስማምተው የሚሠሩ ናቸው ወይስ ሃገር እንዲበተን ሕዝቡ እንዲማረር የሚፈልጉ ናቸው? በንግዱ ውስጥ ካሉ አንዳንድ አመራሮች ሰጪዎች ጀምሮ ሻጥር እንዳለ አያለሁ። አጠቃላይ ሂደቱን በመፈተሽ መፍትሔ እንዲያገኝ በማድረግና ገበያው እንዲረጋጋ የሚደረገው ቁጥጥር በቂ አይደለም። ደግሞም ቁጥጥሩ የዘመቻ ሥራ መሆን የለበትም። እያንዳንዱ ሱቅ የሚሸጥበትን ዋጋ መለጠፍ አለበት። ግልጽ አሠራር መዘርጋት ይገባል። በየጊዜው የዋጋ ንረቱ እንደቀጠለ ነው፤ ቁጥጥር እየተደረገ እና እርምጃ እየተወሰደ ከሆነ ለውጥ መታየት አለበት። የመንግሥት መዋቅር ውስጥ ያለውን ችግር ፈትሾ ማጥራት አለበት። ካልሆነ የኑሮ ውድነቱ እየናረ ነው የሚቀጥለው። መንግሥት ሠራተኞች፣ ጡረተኞች ችግር ላይ ናቸው። ይህንን መንግሥት ሊመለከተው ይገባል። የተለያዩ ውጥረቶች ቢኖሩበትም የኑሮ ውድነቱን ማየት ይገባል።
በርግጥ ‹‹ሊነጋ ሲል ይጨልማል›› የሚባል ነገር አለ። አሁን እንደዛ ይመስለኛል። የውጭ ኃይሎች ምስራቅ አፍሪካ ላይ ኢትዮጵያ ካደገች እነ ግብፅ ስለሚወድቁ ኢትዮጵያ እንዳታድግ፣ እንድንበታተን፣ ከጥቅም ውጭ እንድንሆን የማያደርጉት ጥረት የለም። ይህንን ለመቋቋም መንግሥት ጥሩ እንቅስቃሴ እያደረገ ነው፣ ኅብረተሰቡ ይህንን እንዲደግፍ ማድረግ ያስፈልጋል። መንግሥትም የኅብረተሰቡን የኢኮኖሚ ችግር፣ የሚደርስበትን በደል መቅረፍ አለበት።
ከዋጋ ንረቱ ጋር ተያይዞ የዩክሬንና የራሽያ ጦርነት ዓለም ላይ ተፅእኖ ፈጥሯል ቢባልም እንደ ኢትዮጵያ ዓለም ላይ የኢኮኖሚ ችግር ያለ አይመስለኝም። ከዚህ ይልቅ መንግሥት የኅብረተሰቡን ኑሮ ለማሻሻል መሥራት አለበት። የገበያ ሁኔታውን መፈተሽ ይጠበቅበታል። ጥቂት ሰዎች ተንደላቅቀው የሚኖሩበት ሆኗል። ገበያው ካልተረጋጋ ኑሮ ውድነቱ የበለጠ እየጋለ ይሄዳል፣ በተያዘው መንገድ ከቀጠለም መንግሥትና ሕዝብ ወደ ግጭት ይሄዳሉ፣ ግጭት እንዲፈጠር ኢትዮጵያ እንድትበተንና እንድትፈርስ የሚፈልጉ ኃይሎችም ደስ ይላቸዋል። በመሆኑም በንግዱ ላይ መንግሥት በስፋት መሥራት አለበት።
በሌላ በኩል በከተማ ውስጥ ቀማኛ እና አጭበርባሪ በዝቷል፡ ታክሲ ትራንስፖርት ላይ ተደራጅተው ዝርፊያ ይፈፅማሉ፤ በሞተር የሚደረገው ወንጀልም እየጨመረ መጥቷል። በመሆኑም ፖሊስ የቁጥጥር ሥርዓቱን ማጠናከር አለበት የሚል እምነት ነው ያለኝ። አለበለዚያ ግን በኑሮ ውድነቱ ላይ ይህ ከተጨመረ ሕዝቡ የበለጠ የሚማረርበት ሁኔታ ይፈጠራል ብዬ እሰጋለሁ።
አዲስ ዘመን፡- ለነበረን ቆይታ በአንባቢዎቼና በዝግጅት ክፍሉ ሥም ከልብ አመሰግናለሁ።
አቶ ካሳሁን፡- እኔም እንግዳችሁ አድርጋችሁ ሃሳቤን እንድገልፅ እድል ስለሰጣችሁኝ አመሰግናለሁ።
ማህሌት አብዱል
አዲስ ዘመን ግንቦት 20 ቀን 2014 ዓ.ም