በዓለም አቀፍ ደረጃ ስለ ሴት ልጅ የነበረው እና ያለው ባህል፣ ወግ፣ አስተሳሰብ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ሴቶች ላይ ጫና እንዲበረታ አድርጓል። በዚህ ምክንያት ይመስላል በዓለም ላይ ከሦስት ሴቶች አንዷ በሕይወት ዘመኗ ቢያንስ አንድ ጊዜ ለጾታዊ ጥቃት ተጋላጭ እንደምትሆን ጥናቶች ያሳያሉ። ከሀገራችን መር ሆነ በሌሎች ሀገራት ከባህል አንጻር ሴቶች ጉዳትና ጥቃት ደርሶብኛል ብለው አደባባይ የመውጣት እድላቸው አነስተኛ መሆኑ እየታወቀም የተመዘገበው ቁጥር በራሱ ከፍተኛ ነው።
በሀገራችንም የኢትዮጵያ ሥነ-ህዝብና ጤና ጥናት እንደሚያሳየው፣ ከ15 ዓመት እስከ 49 የእድሜ ክልል ውስጥ ከሚገኙ ሴቶች 23 በመቶዎቹ በሕይወታቸው ውስጥ አካላዊ ጥቃት እንደደረሰባቸው፤ አስር በመቶዎቹ ወሲባዊ ጥቃት እንዳጋጠማቸው ያሳያል። ይሄ መረጃ የሚያሳየው ሀገር ሰላም በሆነበት ጊዜ የነበረውን ሁኔታ ነው። ሀገር ሰላም አጥታ ግጭትና ጦርነት ሲከሰት ችግሩ ከዚህም የከፋ ይሆናል።
ሊታወቅ የሚገባው ነገር ሀገር ሰላም ሆነም አልሆነ በርካታ ሴቶች የቤተሰብ ኃላፊነታቸውን ለመወጣት ደፋ ቀና ማለታቸው የተለመደ ቢሆንም፤ በችግር ጊዜ ለጥቃት የመጋለጥ እድላቸው ከፍ ያለ ነው። በቅርቡ አሸባሪው የሕወሓት ቡድን ወደ ሰሜኑ የሀገራችን ክፍል ለወረራ በተሰማራበት ወቅት፤ በርካቶች ቀዬና መንደሩን ለቅቀው መውጣታቸው ይታወቃል። ይሁን እንጂ በርካታ እናቶች ልጄን፣ ቤተሰቤን ሲሉ ጦርነት ቀጣና ውስጥ ቀርተዋል፤ አሁንም ይገኛሉ። በርካታ ታዳጊ ሴቶች ያለእድሜያቸው የቤተሰብ ጠባቂና መጋቢ ሆነው በችግሩ ውስጥ አሳልፈዋል።
ይህ ወቅት ታዲያ ወራሪው ቡድን በእነዚህ አካባቢዎች ከአንድ ኢትዮጵያዊ የማይጠበቅ አስነዋሪ ድርጊት ፈጽሟል። በሀገራችን ከተለመደው ውጭ አለም በቃኝ ብለው የመነኮሱ፣ ለአካለ መጠን ያልደረሱ ልጃገረዶች፣ ነብሰ ጡሮችና እመጫቶች በቡድን እና በቤተሰቦቻቸው ፊት ተደፍረዋል። በዚህም በርካታ ሴቶች በሆነባቸው ነገር ልባቸው ተሰብሮ፣ ማፈር የሚገባቸው ደፋሪዎች ሳያፍሩ እነሱ በሃፍረት አንገታቸው ተደፍቶ እርዳታ እንኳን ሳያገኙ አካላዊም ስነልቡናዊም ስብራታቸውን ይዘው ቀርተዋል።
ከተደፈሩት የተወሰኑት በሰቀቀን ውስጥ ሆነው እርዳታ ለማግኘት ቢወጡም፤ እርዳታ የሚሰጥ ባለሙያ፣ እርዳታ የሚሰጥበት የጤና ተቋምም ሆነ መድሃኒትና የህክምና ቁሳቁስ ማግኘት አልቻሉም። ከራሳቸው የተጣሉ ክፉዎች የፈጸሙባቸውን መቋቋም ያቃታቸው የጥቃቱ ሰለባ ሴቶችም እራሳቸውን ማጥፋትን እንደ አማራጭ መውሰዳቸውን በርካታ ማስረጃዎች ያሳያሉ።
ይህ ችግር ዓለማቀፍ የሴቶች ቀንን ዓመት እየቆጠሩ በማክበር የሚቃለል አይሆንም፤ በመንግስት መዋቅር ውስጥ ያሉ የሴት አመራሮችን ቁጥር በማብዛት ወይም የሴት ካቢኔዎችን ምጣኔ ከወንዶች እኩል በማድረግም የፈታነው ጉዳይ አይደለም። ይልቁንም እነዚህ ባሉበት ሁኔታ ነው ሴቶች ለዚህ አይነቱ የከፋ ችግር እየተጋለጡ ያሉት። ይህ መሆኑ ሴቶች የእኩልነታቸውን ማዕረግ እንዲያዩት አላደረጋቸውም፤ ከሚደርስባቸው ጾታዊ ጥቃትም አልታደጋቸው። ምንም እንኳን ጾታዊ ጥቃት በተለያየ መንገድ የሚፈጸም፤ መገለጫዎቹም ብዙ ቢሆኑም፤ ብዙዎች የፆታ ጥቃት ሲባል መደፈር፣ መደብደብ፣ በአጠቃላይ አካላዊ ጉዳት ላይ ብቻ የሚደርስ ይመስላቸዋል። ነገር ግን ጥቃቱ በግልጽ የማይታይ ስነ ልቦናዊ፣ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግርንም የሚያስከትል ነው።
አምነስቲይ ኢንተርናሽናል እ.አ.አ. በ2022 ባወጣው ሪፖርት በአማራ ክልል በጭና አካባቢ በሕወሓት የሽብር ሀይሎች የተፈጸመውን ጾታዊ ጥቃት በአስደንጋጭ የጭካኔ ደረጃዎች የተፈጸመ ሲል ገልጾታል። በሪፖርቱ ላይ ንጹሃን ዜጎች በገዛ ቤታቸው ተደብድበዋል፤ የግድያ ዛቻንና የዘር ተኮር ስድብ ተሰድበዋል። አምነስቲይ ቃለመጠይቅ ካደረገላቸው ሴቶች በቡድን እንደተደፈሩና የተወሰኑት በልጆቻቸው ፊት መደፈራቸውን ተናግረዋል።
ጾታዊ ጥቃት በቤተሰቡም ላይ ሳይፈጸም አስከፊነቱን ተረድቶ ከድርጊቱ መታቀብ፤ ሌሎች እንዳይፈጽሙም በመከላከል የሴቶችን ደህንነት የሚያስጠብቅ ወንድ ሴት ሳይል ይሄን የሚያደርግ ማህበረሰብ መፍጠር የተገባ ነው። ግን ምን ዋጋ አለው አብዛኞቹ የሴት መብት ማቀንቀኛ መድረኮች ወንዶችን አግልለው በሴት የተሞሉ ናቸው። ምንም እንኳን የግል ምልከታዬ ቢሆንም ጥቃት አድራሹን ሳናነቃ ሴቶች ላይ ብቻ ስለሰራን ለውጥ መጠበቃችን ስሕተት ይመስለኛል።
ከዚህም አለፍ ሲል መደፈራቸው ሳያንስ ይሄን አስታኮ የሰው መሸማቀቂያ እንዲሆኑ መደረጉ ሌላ በሽታ ነው። በቡድን የተደፈረች የ21 ዓመት የአማራ ክልል ነዋሪ ከአሜሪካ ድምጽ ጋር ባደረገችው ቆይታ የሕወሓት ሀይሎች አካባቢውን በተቆጣጠሩበት ወቅት በቡድን በመደፈሯ ለከፍተኛ አካላዊ ህመም በምትሰቃይበት ወቅት ፍቅረኛዋ እንደተዋት እና ማህበረሰቡ ስላገለላት መኖሪያ ቀይራ የቀድሞ መምህሯ ጋር ለመኖር እንደተገደደች ስትናገር መስማት ያማል። አንድ ሴት ያለፍላጎቷ በበርካታ ወሮበሎች ተደፍራ መልሶ እሷን የሚያሸማቅቅ ማህበረሰብ አካል መሆን፤ የደረሰባትን አካላዊና ስነልቦናዊ ጉዳት መመለስ ባንችል እንኳን እስካሁን ተበዳይን ከበዳይ አለመለየታችን ያሳዝናል። ደፋሪ በነጻነት ሲንቀሳቀስ ተደፋሪ አንገቱን መድፋት ማቆም አለበት።
እንደዚህ አይነት ከሰብአዊነት የወጡ ድርጊቶች በሀገራችን በስፋት መታየቱ ድርጊቱን ለማስቆም ከመስራት ይልቅ የሌሎችን ጥቃት እንዳናቀል ያሰጋኛል። ፍርሃቴ በዚህ ምክንያት የጾታዊ ጥቃትን ተለማምደን አንድ ሴት ብቻዋን በአንድ ወንድ ከተደፈረች ይሁን ከዚህ የባሰ ለስንት የተደፈሩ አሉ ብለን እንዳናቀልለው ነው። እስካሁን
“አካልህ ሴት ናት – ሴት ናት፣
አጋርህ ሴት ናት – ሴት ናት፣
እህትህ ሴት ናት – ሴት ናት
ሴት ልጅህ ሴት ናት – ሴት ናት
እናትህም ሴት ናት፣…” ብለን ማዜማችን ጥሩ ቢሆንም ችግሩ ከመቀነስ ይልቅ እየባሰ ሄዷል።
ስለ ሴት ልጅ ብዙ ጥበባዊ ሥራዎች ተሰሩ፤ የሴቶች ጥቃት እንዲቆም በሙዚቃዎች አማካኝነት ግንዛቤ ለመፍጠር በሚል ሃሳብ ብዙ ሙዚቃዎች ተሠሩ ፤ብዙ ድርጅቶች ስለሴት መብት እና የሚደርስባቸውን ጥቃት ሙሉ በሙሉ ማስቆም ባንችል እንኳን ችግሩን እንቀንስ ብለው በራሳቸው ወጪም ይሁን ከአጋር ድርጅቶች በጋራ በመሆን ቢሠሩም የሚጠበቀውን ያህል ለውጥ የመጣ አይመስልም። ለምን ለውጥ ማምጣት አልተቻለም? የሚለው ጉዳይ መሠረታዊ ነው።ብዙ ሥራዎች ተሰርተው ስለምን ብዙ ለውጥ አልመጣም? ሴቶች ላይ የሚሠሩ መንግስታዊም ይሁን መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት ሥራዎችን እየሠሩ ስለመሆናቸው ይነግሩናል፤ ግን ለምን ለውጥ ማምጣት አልቻሉም? ስለዚህም ማን ላይ? እንዴት እና መቼ መሥራት እንደሚገባቸው ቆም ብለው ማጤን የሚገባቸው ይመስለኛል።
ቤዛ እሸቱ
አዲስ ዘመን ግንቦት 20 ቀን 2014 ዓ.ም