ከእንቅልፏ ነቅታ ስልኳን ስታየው ማቲ አራት ጊዜ ደውሎ ነበር። ከዚህ በፊት እንዲህ እንደ አሁኑ በጠዋቱ ነቅታ ስልኳን ስታየው የምታውቀውም የማታውቀውም ብዙ ስልክ ተደውሎ ነበር የሚጠብቃት። አሁን ከማቲ በቀር ማንም የሚደውልላት የለም። እነዛ በውበቷ ተስበው ጠዋትና ማታ ስልኳን የሚያጨናንቁት ወንዶች አሁን ላይ ከውበት ሌላ ምንም እንደሌላት ሲያውቁ ሸሽተዋታል። ነፍስ ውበት ብቻ ከሆነች እንዲህ እንደ እሷ በትልቅ አለም ውስጥ ባይተዋር እንደሆነች አሰበች። ልብ ከትህትና እኩል ማፍቀርን ካልጨመረ፣ አእምሮ ከማሰብ እኩል ማገናዘብን ካልደመረ ሰውነት ትርጉም አልባ ነው ስትል ከአልጋዋ ላይ ተነሳች። ብዙ ሰዎች፣ ብዙ ታሪኮች፣ ብዙ መፈለጎች የከበቧት ነፍስ ራቁትነት ሲውጣት ህመሙ ምን ያክል እንደሆነ እያሰበች ወደ መታጠቢያ ቤት አመራች። ከሁሉም የሚበልጠው ህመሟ ግን ማቲም ውበት ብቻ ነሽ ብሎ ከተዋት ነው። ማቲ ፊት ውበት ብቻ ያላት ሴት እንዳትሆን የተቻላትን ሁሉ እየሞከረች ነው። አለም ላይ ውበት ብቻ እንደሆነች ሴት አስቀያሚ እንደሌለ ያወቀችው ሁሉም ከተዋት በኋላ ነው። ውበት ዋጋ የሚያወጣው በእውቀትና በምክንያታዊነት ሲታጀብ እንደሆነ የገባትን ያክል ምንም ገብቷት አያውቅም። ግን እንዴት ብላ ከውበት አስተሳሰብ መላቀቅ እንዳለባት አታውቅም። እንዴት ብላ ውበት ብቻ ያልሆነች ሴት መሆን እንዳለባት አታውቅም። እንዴት ብላ ውበቷ ውስጥ እውቀት፣ ሴትነቷ ውስጥ ትህትና ማብቀል እንዳለባት አታውቅም። የኖረችው ስለውበት ብቻ እያሰበች ነው። ያደገችው ውበቷ ሁሉን ነገር እንደሚሰጣት እየተነገራት ነው። ታዲያ ይቺ ሴት በአለም ላይ ለእሷ የሚሆን ምን ስፍራ አላት?
ከመታጠቢያ ቤት መልስ መስተዋቱ ፊት ተገተረች። ልቅም ያለች ቆንጆ ሆና ለምን መስተዋት እንደምትወድ ይሄም ይገርማታል። ፊቷን በመስተዋት ሳታይ፣ ጸጉሮቿ ላይ አርቴፊሻል ሳትቀጥል፣ አይኖቿን ቅንድቦቿን ሳትኳልና ሳትቀነደብ አንድ ርምጃ ተራምዳ አታውቅም። እንብርቷን ሳታሳይ፣ ገላዋን ሳትገልጥ ለብሳ አታውቅም። ታክሲ ላይ ሳትጨቃጨቅ፣ መንገድ ላይ ገፋኸኝ ብላ ከአንዱ ጋር ሳትሟገት ገብታ አታውቅም። ይሄ ባህሪዋ ከብዙ ጓደኞቿ ጋር ሲያጋጫት ነበር። ይሄ ባህሪዋ ቆንጆ ብቻ እንዳደረጋት ገና አልደረሰችበትም። ክብሯን ሀይለኝነት ውስጥ ነው ፈልጋ የምታገኘው። በትህትና መከበርን፣ በይቅርታ ከፍ ማለትን አታውቀውም። በመተው መብለጥን፣ አይቶ በማለፍ መላቅን አልደረሰችበትም። በቃ ከእውቀትና ከጥበብ የተኳረፈች ቆንጆ ብቻ ናት..
መስተዋቱ ፊት በምታየው በራሷ ውበት መደነቅ ጀመረች። ልቅም ያለች ቆንጆ ሆና ፍቅረኛ ማጣቷ ሳቋን አመጣው..እንደ ዛሬ አናዳጅ ሳቅ ስቃ አታውቅም። እየተናደደች ሳቀች። ማሽላ ሲያር ይስቃል እንደሚባለው እያረረች ሳቀች። ነፍስ በውበት ብቻ አትቆነጅም፣ ሰውነት በመልክ ብቻ አይጎመራም..ማሰብ የሌለበት ሰውነት ፍሬ እንደሌለው ዛፍ ነው ሲል ከየት እንዳመጣው እንጃ አእምሮዋ ሹክ አላት። ግን አትማርም..ግን ለመለወጥ አትዘጋጅም። ብትማር ኖሮ በውበቷ በኩል ገቡ በርካታ አስተማሪ ታሪኮች ነበሯት። ግን ራሷን መፈተሽ አትችልበትም።
መስተዋቱ ላይ እንዳፈጠጠች ራሷን ማሰማመር ጀመረች። አይኖቿን ኩላ፣ ቅንድቧን ስላ፣ እንብርቷን ያሳየ፣ ገላዋን የገለጠ ዘመነኛ ልብስ ለብሳ ማቲ ጋ ደወለች..
‹የኔ ፍቅር! ሲል ስልኩን አነሳው።
‹ስትደውልልኝ ተኝቼ ነበር..
‹እንቅልፋም..› አላት።
‹ቶሎ ነይልኝ ናፍቀሽኛል..
‹ምንም ብታወራ ከኔ የሚበልጥ ስሜት የለህም። የማፈቅርህ፣ የምናፍቅህ ከዚህ በኋላ በማይደገም ስሜት ነው› አለችው።
‹አንቺ በማይደገም እኔ ግን ሆኖ በማያውቅ የፍቅርና የናፍቆት ስሜት ነው የተጣበኩሽ› ሲል መለሰላት፡
‹ጉረኛ ነህ..
የኔ ፍቅር ቶሎ ነይልኝ…
‹እሺ እመጣልሀለው..እየወጣሁ ነው› ብላ ቶሎ ልትሄድለት ስልኩን ዘጋችው።
ዛሬ ቀኑን ሙሉ ከማቲ ጋር ነው የሚያሳልፉት። ቅዳሜ መጥቶ ሳይገናኙ ቀርተው አያውቁም። በተለይ ከሰአት ሲሆን ሁሉም ነገር ሌላ ነው። ከቤት ወጣች..ከቤት ስትወጣ ስለራሷ እያሰበች ነበር። በዚህ ቁንጅናዋ ፍቅረኛ ማጣቷ ይገርማታል። ቁንጅናዋ ብዙ ነገር ሲሰጣት ታማኝ ወንድ ግን አልሰጣትም። ወደ ህይወቷ የመጡ ወንዶች ሁሉ እያፈቀረቻቸው የተለዩዋት ናቸው። ከውበቷ እኩል፣ ከሽቅርቅርነቷ እኩል ወንዶችን ሁሉ የሚያሸሸ የሆነ ያልደረሰችበት ጉድፍ ያላት ይመስላታል። ከአለባበሷ እኩል፣ ከዝነጣዋ እኩል የቀረባትን ሁሉ የሚያርቅ የሆነ ገፊ ተፈጥሮ ያላት ይመስላታል። እንደዛ ባይሆን እማ በዚህ ልክ በፍቅር ርሀብ አትራቆትም ነበር። እንደዛ ባይሆን እማ በዚህ ልጅ በወንድ ልጅ አትቀጣም ነበር። ከሁሉ በኋላ የፍቅር ትርጉሙ፣ የመኖር እጣ ፈንታው ይሰወርባታል። ነፍስ ፍቅር ከሌላት ዋጋዋ ምንድነው? ስትል ራሷን ትጠይቃለች።
በግንኙነቷ በራሷ ላይም ሆነ በሌሎች ላይ ጥፋት ላለመስራት ሳትደነቃቀፍ በዝግታ ለመራመድ ሞክራ ታውቃለች። ግን ስህተት ላለመስራት በዝግታ የተራመደችባቸው መንገዶች ሁሉ ያዳለጧት ነበሩ። ወደ ህይወቷ የመጣን ወንድ ለማቆየት ስትል በዝግታ አስባ፣ በጥንቃቄ አውርታ ታውቃለች። በፍቅር ርሀብ የጠወለገች ነፍሷን ለማለምለም ስትል ሁሉንም እሺ፣ ሁሉንም ልክ ነው ስትል ተቀብላ ነበር። እየቀረቡ የሚሸሿትን ወንዶች ለማኖር ስትል ያልሆነችውን ሆና ነበር። እነዚህ ሁሉ ግን የምትፈልገውን ሊሰጧት አልቻሉም። ከብዙ ፍለጋና ከብዙ እንግልት በኋላ ማቲ ከሚባል ልጅ ጋር ተዋወቀች። ማቲ ወደ ህይወቷ እስከገባበት ጊዜ ድረስ የፍቅር ድርቅ መቷት ነበር። አሁን ማቲን ላለማስቀየም፣ ማቲን ላለማስከፋት ስትል ነው የምትኖረው።
የሰው ልጅ በውበቱ ውስጥ ጥበብ፣ በሰውነቱ ውስጥ ርህራሄ ከሌለው አውሬ ነው። የሰው ልጅ በልቡ ውስጥ ፍቅር፣ በአእምሮው ውስጥ በጎ ሀሳብ ከሌለው እንስሳ ነው። ሰው ከአካላዊ ስልጣኔ ርቆ አእምሮአዊ እስካልሆነ ድረስ ከውበት ባርነት መላቀቅ አይችልም ስትል በራሷ ነውር ራሷ ላይ ፈረደች። በቀጣይ ህይወቷ ሴት ሆና፣ በውበት ውስጥ ሳይሆን በእውቀት ውስጥ ለመፈጠር እየማለች ከቀጠሯቸው ቦታ ደረሰች። እዛ ስትደርስ ማቲ አልነበረም..ልትደውልለት ስልኳን ስትጎረጉር..
የሆነ እጅ ከኋላ በኩል ፊቷ ላይ አርፎ ‹ማነኝ? አላት:: ማቲ እንደሆነ አውቃለች…ደስ አላት። ለዚህ ሰው ስትል ራሷን አፍርሳ መስራት አለባት..ማቲ ከተዋት ሰው እንደማትሆን ታውቃለች። እጁን ከፊቷ ላይ አንስቶ ደረቱ ላይ ሲያሳርፋት አካሏን ጥላ በአእምሮዋ ለመኖር ለራሷ እየማለች ነበር።
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)
አዲስ ዘመን ግንቦት 19/2014