ትውልዷ እና እድገቷ በጉራጌ ዞን እንድብር ጉመር ማዞሪያ ነው። በልጅነቷ አትሌት የመሆን ፍላጎት ስለነበራት ከወረዳ እስከ ዞን ድረስ ትወዳደር ነበር። አሁን ላይ የባህል ምግብ ቤት ከፍታ እየሰራች ትገኛለች። ድምጻዊ ሐና ተሰማ ትባላለች። የጉራጌኛ እና የአማርኛ ባህላዊ ሙዚቃ ሁለት የካሴት ሥራዎችን ብታሳትምም አብዛኛው ሰው በኪነጥበብ ባለሙያነቷ እንዳላወቃት ትናገራለች።
ለቤተሰቦቿ ብቸኛ ሴት ልጅ የሆነችው ሐና ትምህርቷን በየቀኑ የሁለት ሰዓት ጉዞ እያደረገች ትማር እንደነበር ታስታውሳለች። ከቤቷ ርቀው በሚገኙት ጀምበሮ እና አረቆት የተባሉ ትምህርት ቤቶች የአንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን ተከታትላለች። ከትምህርት መልስ የእንሰት ተክል ለምግብነት በማዘጋጀትም ሆነ በቤት ውስጥ ስራ እናትና አባቷ ጎን ታሳልፋለች። አምስት ወንድሞቿ ደግሞ እንጨት መፍለጡንም ሆነ ከብት ማገዱን ይከውናሉ።
ቅዳሜና እሁድ ደግሞ በአካባቢዋ በሚገኝ ገበያ ቆጮ እና የተለያዩ ምርቶችን ለገበያ በማቅረብ ለትምህርት የሚያስፈልጋትን ወጪ ትሸፍን ነበር። በትምህርት ቤት ቆይታዋ በሙዚቃ ክበብ ትሳተፋለች። በተለይም አትሌቲክስ ላይ ከፍተኛ ተሳትፎ ነበራት። ትምህርት ቤቷን ወክላ ከወረዳ አልፎ ተርፎም በዞን ደረጃ ወልቂጤ ከተማ የደረሰ የአትሌቲክስ ተሳትፎ አድርጋለች። ተሳትፎዋ እያደገ መጥቶ ወደሐዋሳ ከተማ የሚያስኬዳት ውድድር ሲመጣ ግን ቤተሰቦቿ ልጃችን ሯጭ አትሆንም የሚል ሃሳብ ያነሳሉ።
በወቅቱ ከጉዞዋ የተገታችው ሐና በቤተሰቦቿ ሐሳብ ክፉኛ ሀዘን ገባት። ከ10ኛ ወደ አስራ አንደኛ ክፍል እንዳለፈችም የፈለገችውን ስፖርት ለመቀጠል ብሎም በሙዚቀኛነትም ለመሳተፍ አስባ ከቤተሰቦቿ ጠፍታ ወደ አዲስ አበባ አቀናች። የዛሬ 15 ዓመት ያገኘቻት አዲስ አበባ ግን እጆቿን ዘርግታ በፀጋ አልተቀበለቻትም። ይልቁንም ለጎዳና ህይወት ዳረገቻት እንጂ። ገና ከተማዋን እንደረገጠች ልደታ አካባቢ አጎቶች እንደነበሯት ከማስታወስ በዘለለ አንድም የምታውቀው ዘመድ አልነበራትም። በመሆኑም ከአውቶቡስ ተራ ወደ ልደታ አካባቢ አቅንታ አጎቶቿን ስትፈልግ አውቃለሁ የሚል ሰው ጠፋ።
በዕለቱ ሐና ጎዳና ማደርዋ እንደማይቀር በመረዳቷ እንባዋን በመንገድ ስታዘራ ዋለች። ደንገዝገዝ ሲል ግን አንድ እናት አገኘችና ማደሪያ እንዳጣች ስትነግራቸው አንድ ኬሻ ሰጥተው የቤታቸው በረንዳ ላይ እንድታድር ያደርጋሉ። ብርድና የክረምቱ ወጨፎ ሲያሰቃያት ያደረችው ሐና ታዲያ በጠዋት ስትነሳ ከግቢው ውጪ ነጠላ የለበሱ ሴቶች ትመለከታለች። ነጠላ የለበሱት ሴቶች የሚያቀኑት ወደቤተክርስቲያን መሆኑ ገብቷት ተከተለቻቸው።
በአዲስ አበባ የሚገኘውን ልደታ ቤተክርስቲያን በማየቷ ኑሮዋን በራፉ ላይ ለማድረግ ወሰነች። በራፉ ላይ ከሚገኙ አዛውንቶች ጋር በመግባባቷ እነርሱ የሚበሉትን እየበላች ተጠግታ ማደሩን ተያያዘችው። በዚህ ሂደት ቤተክርስቲያኗ በር ላይ ሁለት ወር ያክል በጎዳና ህይወት አሳለፈች። በጎዳና ህይወት ቀን ከሌት ስታማርር እና ስታለቅስ ከዕለታት በአንዷ ቀን ሁለት ልጆችን ይዛ ቤተክርስቲያን ልትሳለም ከመጣች ሴት ጋር ትገናኛለች።
ሴትየዋም የሐናን እንባ አይተው ቀርበው ችግሯን ይረዳሉ። ከዚያም ሴትየዋ ልደታ «ቢሪም ሜዳ» የተባለው ቦታ ላይ የሚገኙ ጉሊት ነጋዴ ሴቶችን አሳይተዋት መስራት እንዳለባት ነግረው አበረታቷት። ሴትየዋ ሐናን ማታ ማታ በሳሎናቸው ውስጥ ኬሻ አንጥፋ እንድታድር ፈቅደው ቀን ቀን ደግሞ ጉሊት የምትነግድበት 10 ብር ሰጧት። ይህች 10ብር ነች እንግዲህ ለአሁኑ የንግድ ህይወቷ መነሻ የሆነቻት። ሴትየዋ ብሩን ሰጥተዋት ብቻ አላበቁም። ወደ ተክለሐይማኖትና ጭድ ተራ አካባቢ ወስደው ስኳር ድንች የምትገዛበትን ቦታ ጭምር አሳዩዋት። ከዚህ በኋላ ሐና ስኳር ድንቹን ቀቅላ እንዲሁም ጥሬውን ለንግድ ማቅረብ ጀመረች። ከዕለት ዕለት ገቢዋ በመጠነኛ ሁኔታ ማደጉ ቢያስደስታትም ለውጡ ግን እምብዛም ነበር።
አንድ ዓመት እንደሰራች ግን ባለውለታዋ አሳዳሪዋ ሴት በየአራት ቀኑ ከሚሰበሰብ የ4ብር ከ50 ሳንቲም ዕቁብ 180 ብር አስረከቧት። በገንዘቡ ጤፍ ገዝታ ላቀች ምድጃ በ60 ብር ካስገጠመች በኋላ በላስቲክ በተወጠረ የጉሊት ቦታ ላይ እንጀራ እየጋገረች ለሆቴል ቤቶቸ ማቅረብ ጀመረች።
አንድ እንጀራ በ50 ሳንቲም ቤታቸው ድረስ በማቅረብ ንግዱን ተያያዘችው። ሐና እንደምትናገረው፤ በወቅቱ ከሚገኘው ገቢ ላይ ለአሳዳሪዋ የሚሆን ቤት ኪራይ ከመደገፍ በተጨማሪ የዕለት ወጪያቸውንም መጋራት የቻለችበት ጊዜ ሆነ። አዕምሮዋ በትንሹም ቢሆን እረፍት ያገኘበት ወቅት ነበር። የእንጀራ ጋገራው ገበያ ፍላጎት እያየለ ሲመጣ ግን ከአቅም በላይ የሆነ ስራ መጣባት። በመሆኑም አንድ መላ ዘየደች። ልደታ አካባቢ ዳርማር የተባለ ቦታ የሚገኙ ሌላ እንጀራ ሻጭን ትነጋግርና እርሷ በ50 ሳንቲም ተረክባ ለሆቴሎቹ በ60 ሳንቲም ለማከፋፈል ወሰነች።
የ10ሳንቲም ትርፍ በመያዝ እራሷ እንጀራውን ተሸክማ ታደርስ እንደነበር ታስታውሳለች። ይሁንና ስራው ሊቋረጥብን ነው በሚል ሰበብ በዱቤ የወሰዱትን 600 ብር ሳይመልሱላት እብስ ብለው የጠፉት የሆቴል ደንበኞቿ ስራዋ ላይ እንቅፋት በመፍጠራቸው ንግዱ ተቋረጠ። ይህ ሁሉ የህይወት ውጣ ውረድ ሲከሰት ተስፋ ባለመቁረጥ መቀጠሏን የምታስረዳው ሐና እንጀራውን ትታ ሜክሲኮ አካባቢ ሻይ እያዞረች መሸጥ ጀመረች።
ከሻዩ በተጓዳኝ የፀጉር ጌጣጌጥ እና አበባዎችን ትሸጥ ነበር። በመንገድ ላይ ንግድ ከደንብ አስከባሪዎች ጋር መሯሯጡ ቢከብዳት ደግሞ ለገሃር አካባቢ የሚገኝ የእንግዳ ማረፊያ ቤት በ150 ብር የወር ደመወዝ የማስተናገድ ስራ መቀጠሩን መረጠች። ቀንና ሌሊት ጭምር በመስተንግዶ ቤቱ አንድ ዓመት እንደሰራች ስራው አዋጭ ባለመሆኑ አሁንም በስራ ወደ ንግዱ ለመመለስ ወሰነች።
በጥንቃቄ የቆጠበቻትን ብር በተጨማሪ ታገኝ ከነበረው ጉርሻ ጋር ደማምራ ሪቼ አካባቢ ቤት በመከራየት አነስተኛ ግሮሰሪ ከፈተችበት። አንድ ዓመት ሰርታ ቤቱ ሲለምድላት ደግሞ አከራዮቿ ልቀቂ በማለታቸው አነስተኛዋን ግሮሰሪ ለመዝጋት ተገደደች። ለስራ የተነሳሱ እጆችና አዕምሮዋ ሁልጊዜም በፈተና የተሞሉ በመሆናቸው ይብቃኝ ብላ አላቆመችም። ይልቁንም ወደተሻለ ደረጀ የሚያደርሳትን የክትፎ ቤት ስራ ጎተራ አካባቢ ተከራይታ ለመጀመር ወሰነች።
በአደገችበት አካባቢ ከልጅነቷ ጀምራ ስታይ ያደገችውን የስጋ እና የጎመን ክትፎ ለአዲስ አበባ ተጠቃሚዎች በማቅረብ ጥረቷን ቀጠለች። አያቶቿ በቤት ውስጥ ሲሰሩ የነበረውን የክትፎ ባህላዊ አዘገጃጀት በመከተል በጎተራው ንግድ ቤቷ ጣፋጭ የጉራጌ ባህላዊ ምግቦችን ማቅረቡን ተያያዘችው። አሁን ላይ ስድስት ዓመታትን ያስቆጠረው ክትፎ ቤቱ ጎተራ አካባቢ እና መስቀል ፍላወር አካባቢ ቁጥር ሁለት እና ቁጥር ሶስት የደረሱ ቅርንጫፎችን እንድትከፍት ረድቷታል።
በተለይ በቁጥር ሶስቱ የመስቀል ፍላወር ያዊዌ ክትፎ ቤት የምሽት ባህላዊ ጭፈራ እና በሙዚቀኞች የታጀበ ኪነጥበባዊ ዝግጅቶች ገበያ እየሳቡላት ይገኛሉ። የመስቀል ፍላወሩ ክትፎ ቤት በባህላዊ ዕቃዎች ያጌጠ እና የገጠሩን አካባቢ የሚያስታውስ ከመሆኑ ባሻገር ባህላዊ ጣዕማቸውን ያልለወጡ የተለያዩ የክትፎ አይነቶች ይቀርቡበታል። ምንም እንኳን ከንግድ ቤቱ ጋር ከኪራይ ውል ጋር በተያያዘ እስከ ፍርድ ቤት የደረሰ ችግር ቢኖርባትም ጉዳዩን ጊዜ በፈቀደ ወቅት አወጣቸኋለሁ ትላለች። ይሁንና ጥንካሬዋን የሚገታ ነገር እንዳላጋጠማት እና ለንግድ ስራው የሚሆናትን የምግብ ግብዓት በየጊዜው ከገበያ እየገዛች እራሷ አሰናድታ እንደምታቀርብ ታስረዳለች። በዚህ ምክንያት ደግሞ ሰራተኛ ቢለቅባት እንኳ እራሷ ምግቡን በማሰናዳቷ የክትፎ ጣዕሙ ሳይቀያየር ደንበኞቿን በደስታ እንድታስተናግድ እንደረዳት ትናገራለች።
ከጎዳና ተነስታ የተለያዩ ስራዎችን ስትሰራ የኖረችው ሐና አሁን ላይ በባህላዊ ቤቶቿ 35 ሰራተኞችን እስከመቅጠር ደርሳለች። ለንግድ ቤቶቿ 50 ሺ ብር የወር ቤት ኪራይ የመክፈል አቅምና የተወሰነ ጥሪትም ፈጥራለች። ከተሰራ የማይለወጥ ነገር እንደሌለ የሚያሳየውን የህይወቷን ልምድ በርካታ ወጣቶች እንዲማሩበት ፍላጎቷ ነው።
ሐና ከባህላዊ ቤቶቹ ስራ በተጨማሪ ሰርግ እና የተለያዩ ድግሶች ላይ አይቤ እና ጎመን እንዲሁም ክትፎዎችን ጨምሮ የተለያዩ ምግቦችን በማሰናዳት ታቀርባለች። በሰርግ ወቅት ለአንድ ሰው በ260 ብር ሒሳብ የምታስከፍለው የያዊዌ ባለቤት ባህላዊ ቡፌ በማዘጋጀት ደንበኞቿን ከማስደሰቷ በተጨማሪ ገቢዋንም እያሳደገች ትገኛለች። በድግስ ወቅት እስከ ሶስት ሺ ሰዎች ማስተናገድ የሚያስችል የምግብ እቃዎች እና ሰራተኞችን የማቅረብ አቅም መፍጠሯን የምትናገረው ሐና፤ በጥንካሬዋ ከዚህም በላይ መስራት እንደምትችል ማሳየት ፍላጎቷ መሆኑን ነው የምትገልጸው።
የአንድ ልጅ እናት ብትሆንም ቀን በጎተራው ያህዊዊ ክትፎ ቤት ንግዷን ስትከውን ውላ ማታ ደግሞ የቁጥር ሶስቱን ቤቷን ስራ ስትቆጣጠር ታመሻለች። አሁን ላይ የህይወት ታሪኳን የሚዳስስ የዘፈን ምስል ወድምጽ/ ከሊፕ/ ቀረጻ ማከናወኗን የምትናገረው ሐና፤ በድምጻዊነቱም ብዙም ሰው ባያውቃትም በሙያው የመግፋት ሃሳብ እንዳላት ነው ያጫወተችን። ከሁለት የሙዚቃ ካሴት ስራዎቿ ህትመት በቂ ገንዘብ አለማግኘቷ ወደኋላ እንዳላስቀራት እና አሁንም ጥረቷ መቀጠሉ ትናገራለች። ባህሏን የሚያስተዋውቁ ስራዎችን እና የተለያዩ ድምጻውያንን ስራዎች በባህላዊ ቤቷ ለታዳሚዎች ታቀርባለች።
ለወይዘሮ ሐና ስራና ሀብት ማለት ከጥረት ጋር የሚገኙ ጉዳዮች ናቸው። «አንድ ሰው በእጁ 500 ብር ይዞ ስራ የለም ይላል። አትክልት ተራ ሄዶ በአነስተኛ ዋጋ ገዝቶ ወደገበያ መቀየር ቢችል ግን ህይወቱንም መለወጥ ይችላል» ትላለች። በመሆኑም የሰው ልጅ ባለው ሙያ ሁሉ በአገሩ ላይ ቢሰራ ሊለወጥ እንደሚችል የእርሷ ታሪክ በቂ መሆኑን ትናገራለች። በቀጣይ ደግሞ የእራሷ የሆነ ቦታ ላይ የኢትዮጵያን ባህል እያስተዋወቀች ለመስራት አቅዳለች። ከዚህ በተጨማሪ እርሷ ያየችውን የጎዳና ህይወት በማስታወስ በመንገድ የሚገኙ ልጆችን እና አዛውንቶችን በቋሚነት የምትረዳበት መንገድ ላይ መስራት ደግሞ ህልሟ ነው። ይህ ህልሟ እንዲሳካ ዛሬም ነገም ሳትታክት እንደምትሰራ ትናገራለች።
አዲስ ዘመን መጋቢት 14/2011
ጌትነት ተስፋማርያም