ስለዚህ መንግሥት ባሰብሁ ቁጥር ግርም ድንቅ የሚለኝን ነገር ላንሳ። ህልቆ መሳፍርት በሌለው ቀውስ ተከቦና እንደ ጎን ውጋት ተቀስፎ ተይዞ አይኑን ለአፍታ ከትልቁ ስዕል አለማንሳቱ ሰርክ ይገርመኛል። ይደንቀኛል። የኢትዮጵያ ታላቁ የህዳሴ ግድብ የገባበት ትብታብና ቋጠሮ ተፈቶ ከለየለት ክሽፈት ወጥቶ ኃይል ማመንጨት የጀመረው፤ የሸገርና የሃገር ፕሮጀክቶች አስገራሚ አፈጻጸም፤ የአረንጓዴ አሻራና የበጋ ስንዴ አበረታች ውጤት፤ የብር ለውጥና የተቋማት ግንባታ፤ የአግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታ እና ሌሎች እጅን በአፍ የሚያስጭኑ ፕሮጀክቶች ታቅደው በተቀመጠላቸው ጊዜ መሠረት እየተፈጸሙ ያሉት ሃገር በቀውስና በጦርነት በአራቱ ማዕዘናት እንደ ቆዳ ተወጥራ ባለበት መሆኑን ሳስብ መልሶ መላልሶ ይገርመኛል። ጊዜው በሃገሪቱ ዘመናዊም ሆነ ጥንታዊ ታሪክ እንዲህ ተፈትና የማታውቅበት መሆኑና ታላላቅ ሃገራዊ የሆኑ ፕሮጀክቶች የተጠናቀቁበትና እየተፋጠኑ ያሉበት መሆኑን ወዲህ ሳስብ ከአድማሱ ባሻገር ተስፋና ጽናት ይታየኛል። ምንም እንኳ ከቋጥኝ የገዘፉ የራሱ የብልጽግና ችግሮችና ውጫዊ ችግሮች ትልቁን ስዕል እንዳንመለከት ቢጋርዱንም።
ሰሞነኛ አኳኋናችንንና የኑሮ ውድነቱን እያብሰለሰላችሁ እየተከናወኑ ያሉ ግዙፍ አገራዊ ፕሮጀክቶች ያለምንም መደነቃቀፍ መቀጠላቸውን ስትመለከቱ እንደኔ ልትገረሙ ትችላላችሁ። አልያም ጽድቁ ቀርቶ በቅጡ በኮነን፤ መጀመሪያ በሰላም ወጥተን በሰላም እንግባ፤ የሕግ የበላይነት ይረጋገጥ፤ የአገር ሕልውና ይከበር፤ የኑሮ ውድነቱ ፤ ወዘተረፈ ይቀረፍ ልትሉ ትችላላችሁ። ይሁንና በሃገሪቱ ታሪክ እንደዚህ ቀውሶች፣ ችግሮችና ፈተናዎች በአንድ ላይ ግንባር ገጥመው ናዳ ሆነው መጥተው አያውቁም ። ቀውሶቻችን ምክንያትና ውጤት ከመሆናቸው ባሻገር ተወራራሽ፣ ተመጋጋቢና አንገብጋቢ ስለሆኑ አንዱን ዛሬ ሙሉ አቅማችንን አረባርበን ፈተን ሌላውን ደግሞ ነገ እንመለስበታለን የምንለው አይነት አይደሉም። ሕልውናችን፣ ሉዓላዊነታችን፣ የኑሮ ውድነቱ፣ የበጋ ስንዴው፣ አረንጓዴ አሻራውና ሌሎች እንዲህ በማዕቀፍ ታይተው በተመሳሳይ ጊዜና ሰዓት ምላሽ እንዲሰጣቸው ካልተደረገ ነገሩን ውሃ ቅዳ ውሃ መልስ ስለሚያደርገው መንግሥት ሚዛናቸውን አስጠብቆ ሁሉንም ለመፍታት የሰጠውን ያልተከፋፈለ ትኩረት አደንቃለሁ። አበውስ ህልም ተፈርቶ ሳይተኛ አይታደርም አይደል የሚሉት ።
“ኢትዮጵያ ታምርት”ን ከዚህ አንጻር ነው የምመለከተው። በነገራችን ላይ “ኢትዮጵያ ታምርት” ለኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ብቻ የሚተው ጉዳይ እንዳልሆነ ሁሉ፤ አረንጓዴ አሻራም ሆነ የበጋ ስንዴ ለግብርና ሚኒስቴር ብቻ የሚተው ጉዳይ አለመሆኑን የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ተገንዝቦ የ”ኢትዮጵያ ታምርት”ን አጀንዳ በሁሉም ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች ለማስገንዘብ የሄደበት እርቀት ይበል የሚያሰኝ መሆኑን በልኩ እውቅና መስጠት ያሻል። እንደ የህልውና ዘመቻው በሌሎች እንደ ኑሮ ውድነቱና የዋጋ ግሽበቱ ባሉ አንገብጋቢ አገራዊ ጉዳዮችም ተመሳሳይና ጉልህ ተሳትፎ ይኖረዋል ብዬ እጠብቃለሁ። የዚች ሀገር አጀንዳ በዜና፣ በመጣጥፍና በትንታኔ ብቻ ተሰልቆ አይልምምና። ዘ ኢኮኖሚስት ፣ ቢቢሲ ፣ አልጀዚራ ብሉምበርግ፣ ሲኤንኤንና ሌሎች ሚዲያዎችም በዚህ መንገድ ብዙ ይመላለሳሉና።
ወደተነሳሁበት ነጥብ ስመለስ፤ ሃገራችን በቀውስ ዳመና ተከባ እያለ የምን ኢትዮጵያ ታምርት ነው የሚል፣ የምን የበጋ ስንዴ ነው ፣ የምን የአረንጓዴ አሻራ ነው፣ ወዘተረፈ የሚለው ሕዝብ ቁጥር ቀላል ባይሆንም ሀቁ ግን ቀውሶቻችን ለማቀዳደም እድል ፈንታ የማይሰጡና በተመሳሳይ ጊዜ መፈታትን የግድ የሚሉ ናቸው። ሁሉንም እርግፍ አድርገን ትተን ሁሉም ነገር ወደ ጦር ግንባር ብለን ሕወሓትና ቡችሎቹ ላይ ብናተኩር ነገ ሌሎች ችግሮችና ቀውሶች የባሰ ተወሳስበውና ተጠላልፈው የከፋ አደጋ መደቀናቸው ሳይታለም የተፈታ ነው። “ኢትዮጵያ ታምርት”ን በአብነት ብንወስድ ፤ ሃገራችን ምርትና ምርትን በአጭር ጊዜ ውስጥ ማሳደግ ካልቻለች አሁን ከምትገኝበት ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ቀውስ ማለትም ከሥራ አጥነት ፣ ከኑሮ ውድነትና ከውጭ ምንዛሪ እጥረት ልትላቀቅ አትችልም። መዋቅራዊና ተቋማዊ ለሆኑ ችግሮች ዘርፈ ብዙና ዙሪያ መለስ ምላሽ ካልሰጠን ነገ እንደ ሃገር ትንፋሽ የሚያሳጡ ይሆናሉ። እንደ አገር ትንፋሽ ከሚያሳጡን ተግባራት “ኢትዮጵያ ታምርት “ዋነኛው ነውና በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የግብዓትና መሠረት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሺሰማ ገብረ ሥላሴ ከሪፖርተር ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ያነሷቸውን አንኳር አንኳር ነጥቦች ለዓምዱ እንዲመች አድርጌ አቅርቤዋለሁ።
“ኢትዮጵያ ታምርት” ንቅናቄ በዋነኛነት የአገር በቀል ኢኮኖሚ ሪፎርምና የአሥር ዓመቱን ብሔራዊ የልማት ዕቅድ መሠረት አድርጎ፣ በዚያ ላይ ለኢንዱስትሪ ዘርፉ፤ ከኢንዱስትሪ ዘርፉ ተነጥሎ ደግሞ ለአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉ የተቀመጡ ግቦች አሉ። እነዚህ ግቦች ምን ያህል ኢንዱስትሪዎች ይኖራሉ? ምን እናደርጋለን ? ይኼን ተከትሎ በዘርፉ የምናገኘው የውጭ ምንዛሪ ምን ያህል ነው? ምን ያህል የሥራ ዕድል ይፈጠራል? በዶላር የምናስገባቸውን የውጭ ምርቶችን በአገር ውስጥ ምን ያህል እንተካለን ? የመጨረሻ የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግር ይኖራል ተብሎ ተቀምጧል። እነዚህ እንደ ግብ የተቀመጡትን ጉዳዮች ዋነኛ የ”ኢትዮጵያ ታምርት” ንቅናቄ መነሻዎች ናቸው።
ሁለተኛ አሁን ባለንበት ሁኔታ ወስጥ የተለያዩ ጥናቶች አሉ። በራሱ በአሥር ዓመቱ ዕቅድ ውስጥም የዘርፉ ጉድለቶች ተብለው የተቀመጡ አሉ ። ከዚያ ውጪ በዓለም አቀፍም ሆነ በአገር ውስጥ በተለያዩ አጥኚዎች የተደረጉ ጥናቶችም ይገኛሉ። እነዚህ ጥናቶች አምራች ኢንዱስትሪዎች ባላቸው የማምረት አቅም እያመረቱ እንዳልሆነ፤ እንዲያውም አንዳንዶቹ ዘርፎች ከ20 በመቶ በታች እያመረቱ እንደሚገኙ፤ አማካዩ የማምረት አቅም ከ50 በመቶ በታች መሆኑ ተለይቷል ። ስለዚህ በተቻለ መጠን ሥራ ላይ ያሉት ኢንዱስትሪዎች በተሻለ አቅም ማምረት ይኖርባቸዋል። መቶ በመቶ ማድረስ ሊከብድ ይችል ይሆናል። ነገር ግን አሁን ካለው 46 እና 48 በመቶ አማካይ ወደ 60 እና 70 በመቶ ቢደርስ እንኳን የሚኖረው ትርጉም በጣም ብዙ ነው። በሥራ ዕድልም በውጭ ምንዛሪ ግኝትም፤ በገቢ ምርት በመተካትና በመሳሰሉት የሚኖረው ሚና ትልቅ ይሆናል።
በማደግ ላይ ያለ ኢኮኖሚ እንደ መሆኑ መጠን የውጭ ምንዛሪና የግብዓት እጥረት፣ የመሠረተ ልማትና የፋይናንስ ችግር ዋነኛ ማነቆ በሚል የተለዩ ናቸው። ይሁንና የሁሉም ኢንዱስትሪዎች ችግር ተመሳሳይ ሊሆን አይችልም። የአንዳንዱ የአመራር ፣ የሌላው የሰው ኃይል አጠቃቀም ወይም የፋይናንስ እጥረት ሊሆን ይችላል። አንዳንዱ ኢንዱስትሪ በውጫዊ ምክንያቶች የበርካታ ተቋማትን ድጋፍ ይፈልጋል። ምክንያቱም ከግብዓት እስከ ምርት ድረስ፤ ከምርት እስከ ገበያ ድረስ ተራ ዕቃ ገዝቶ እንደ መሸጥና የሆነ ቦታ ሄዶ አገልግሎት አግኝቶ እንደ መምጣት አይደለም። ኢንዱስትሪ ከጥሬ ዕቃ ግዥ አንስቶ እስከሚመጣ ድረስ ሎጂስቲክስ፣ መጋዘን፣ ማምረት ይፈልጋል። ከተመረተ በኋላ የገበያ ጉዳይ አለ። ይህንን ሁሉ ረዥም መንገድ የሚሄደው አምራች ኢንዱስትሪ ከመነሻ ጀምሮ፤ ለምሳሌ አዲስ ለመግባት የሚፈልግ አልሚ ካለ ከመሬት ዝግጅት ጀምሮ ወይም ባሉት የኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ገብቶ እንዲያመርት ማሽነሪ እንዲያቀርብ፤ የሰው ኃይል እንዲቀጥር፤ በዚህ ሁሉ ሒደት በርካታ የጥራት አረጋጋጮች፤ ድጋፍ ሰጪዎች፤ ብድር፣ የውጭ ምንዛሪና የሎጂስቲክስ አቅራቢ አለ። ከእነዚህ ሁሉ ጋር የሚሠራ እንደ መሆኑ እነዚህን ኃይሎች በተመለከተ የቱ ጋ ነው ችግሩ ያለው? ቀልጣፋ ነው ወይ? እያንዳንዱ ጋ ያለው አገልግሎት ግልጽ ነው ወይ? የሚሉት በጥናቶቹ ሲታዩ ኢንዱስትሪ ሚኒስቴርን ጨምሮ በእያንዳንዱ አካባቢ ችግር መኖሩ ታውቋል።
ችግሮቹ በአንድ ተቋም ወይም በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ብቻ የሚፈቱ ቢሆኑ ሌላ ተጨማሪ አካል ላያስፈልግ ይችል። በመደበኛ ዕቅድ ሊፈቱ ስለሚችሉ። በሌላ በኩል እያንዳንዱ ተቋም የራሱ ጉድለት አለው። የአገልግሎት ሰጪ ተቋሙም ሆነ አምራች ድርጅቱም በራሱ ጉድለት አለበት። እንደገና ዘርፍ ተሻጋሪ የሆኑ ለዚህ ዘርፍ እንዲያገለግሉ የተደራጁ በጣም በርካታ መሥሪያ ቤቶች አሉ ። ባንኮች የግልም ይሁን የመንግሥት፣ ብሔራዊ ባንክን ጨምሮ ጉምሩክ፣ ገቢዎች፣ ገንዘብና ንግድ ሚኒስቴሮች በጋራ መሥራት አለባቸው። ግብዓት ከሆነ ፍላጎቱ ከግብርና ጋር ሌሎች ግብርና አካባቢ ካሉ መሥሪያ ቤቶች ጋር የማዕድን ሚኒስቴርን ጨምሮ ከእነዚህ ሁሉ ጋር መሥራት ይጠይቃል። በአንዳንድ አካባቢዎች አላስፈላጊ ጣልቃ ገብነቶች ስለሚኖሩ ከፀጥታ አካላት ጋርም መሥራትንም ግድ ይላል።
እነዚህን ሒደቶች አልፈን እዚህ ብናመርትም እነዚህን ሁሉ ችግሮች ካለፉ አገሮች ምርት ጋር ነው የሚወዳደረው። የአምራች ኢንዱስትሪ የሚያመርተውን አንድ ሸሚዝም ሆነ ጫማ በዓለም አቀፍ ደረጃ በተሻለ ጥራትና በቀነሰ ዋጋ ማምረት የቻለ ሁሉ ይወዳደረዋል። ስለዚህ እዚህ ላይ ያለው ውድድር ከባድ እንደ መሆኑ ድጋፉም በዚህ ደረጃ መሆን አለበት። ከዚህ አንፃር የኢንዱስትሪ ፖሊሲው ምን ይመስላል? ትክክለኛውን አምራች ሲደግፍ ነበር ወይ? አምራችን እየደገፈም ከሆነ የተደገፈው ሰው ለትክክለኛው ዓላማ እያዋለው ነበረ ወይ? የሚለውንም ለማየት ተሞክሯል። ስለዚህ አንድ የሚያስፈልገው ነገር ራሱ የኢንዱስትሪ ፖሊሲውን መከለስ ሆኖ ተገኝቷል። ጉድለቶች መስተካከል ይኖርባቸዋል የሚል ነው።
ስለዚህ ከዚህ ጀምሮ አጠቃላይ አገር አቀፍና ዓለም አቀፍ ሁኔታ ከኮቪድ ጊዜ ጀምሮ እስካሁኑ የዩክሬይን ሩሲያ ጦርነት ድረስ የተፈጠረ ችግር አለ። እነዚህ ሁሉ ጫናዎች ካሉ ጫናዎቹን ተሻግረን፣ ይኼን ጊዜ አልፎ ወደ ተሻለ ደረጃና ኢንዱስትሪው የታለመለትን ዓላማ ማምጣት እንዲችል በሌላ መንገድ አቅሙ አለ። ያልተነካ በርካታ ዘርፍ አለ። ባለፉት ሁለትና ሦስት ዓመታት በጦርነትና በበርካታ ፈተናዎች ውስጥ ተሁኖ የተገነቡ የኢንዱስትሪ ማዕከላት አሉ። በጣም በፍጥነት ከላይ የተጠቀሱትን ፈተናዎች የሚቀንሱና ሰብሰብ የሚያደርጉ ወደ አንድ ማዕከል የሚያመጡ የአግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮችም አሉ፣ ሌሎች ፓርኮችም አሉ። ስለዚህ እነሱን በሙሉ አቅማቸው ወደ ሥራ ማስገባት የሚቻል ከሆነ፣ እነዚህን ዙሪያ መለስ ነገሮች በደንብ ከተነተንን በኋላ በአንድ መደበኛ ዕቅድ መፍታት ስለማንችል በንቅናቄ ተጀምሯል።
ንቅናቄ ስንል ብዙ ጊዜ በእኛ አገር ሁኔታ የሚነገሩ ነገሮች አሉ። ይኼ ግን እንቅስቃሴ ነው። የማይቋረጥ ነገር ማለት ነው። ዓላማውን እስኪያሳካ ድረስ የማይቆም ነው። ሌሎች አገሮች እንደዚህ ነው የሄዱት። ይኼ በበላይ አመራሮች የሚመራ፣ ረዥም ጊዜ የሚወስድ፣ አንዱን ጨርሰህ ወደ ሌላው የምታሸጋግርበት፣ የትምህርትና የምርምር ማዕከላት የሚሳተፉበት፣ የሰው ኃይል የሚያፈሩ ተቋማት የሚሳተፉበትና እነዚህን ሁሉ ሰብሰብ አድርጎ የሚመራ፣ ከኢንዱስትሪ ሚኒስቴርም በላይ የሆነ አመራር የሚጠይቅ ነው። ያንን በካውንስል ደረጃ ቀጥሎም በቴክኒክ ኮሚቴ ደረጃ እያደራጁ መሄድን ይጠይቃል። ስለዚህ ንቅናቄ ስንል እስከ ሰኔ 30 ድረስ ማለታችን አይደለም። እስከ የአሥር ዓመት የዕቅድ ዘመኑ በዚህ መንገድ መሄድ ከተቻለ፣ ለምሳሌ ‹‹ዱዊንግ ቢዝነስ›› የምንለው ለአምራች ኢንዱስትሪው የተመቸ የቢዝነስ ሁኔታ በየተቋሙ እስኪፈጠር ድረስ መቀጠል ያለበት ነው። በተከታታይ መመራት ያለበት ነው። ይኼ ከተደረገና ትንንሽ ቀዳዳ ተሰጥቶ ምቹ ሁኔታ ከተፈጠረ አምራች ኢንዱስትሪውም ቢሆን ለራሱ ትርፍና ጥቅም ስለሆነ የሚሠራው፣ ፈተናውንና አደጋውን ነው የሚፈራው እንጂ፣ ወደፊት ሊሄድ የሚችል የሰው ኃይል አለ፣ መሬቱ አለ። በተለይም ለአግሮ ኢንዱስትሪው በአገር አቀፍ ደረጃ በየአቅጣጫው ምቹ ሁኔታዎች አሉ። እነዚህን አቅሞች በደንብ ለመጠቀም ሚዛናዊ ነገር ያስፈልጋል ተብሎ ነው ንቅናቄው የተጀመረው።
አግሮ ፕሮሰሲንግ አንድ ክፍል ነው። ከሦስት እስከ አራት የሚደርሱት የአግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ሙሉ በሙሉ ወደ ሥራ ቢገቡ 450 ያህል አግሮ ኢንዱስትሪዎችን ሊይዙ ይችላሉ። ግን በየአካባቢውና በየሠፈሩ የአግሮ ኢንዱስትሪ ፕሮሰሲንግ የሚሠሩ ፋብሪካዎች አሉ። ዞሮ ዞሮ ካለን አቅም ጋር ማለትም የግብርና ምርት አለ፣ ይኼን ምርት ለምሳሌ ሦስት አካላት ይፈልጉታል።አንደኛው ከአርሶ አደሩ ጀምሮ ሸማች ይፈልጋቸዋል። ሁለተኛው ኤክስፖርተሮች ይፈልጉታል። ስለዚህ የኤክስፖርት ገቢ አለው ማለት ነው። ሦስተኛው የሚያቀናብሩ (ፕሮሰስ) የሚያደርጉ ተቋማት አሉ። ከዱቄትና ከዘይት ፋብሪካ ጀምሮ በጣም ብዙ የግብርና ውጤቶችን የሚጠቀሙ አሉ። ስለዚህ አግሮ ፕሮሰሲንግ አንዱ ክፍል (ኮምፖነንት) ነው እንጂ ዋናው አይደለም። በሁሉም ማለትም በብረት፣ በኮንስትራክሽንና በማዕድን ዘርፎች ቢታይ በርካታ ነገሮች አሉ። እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ እንደ ሴራሚክ ያሉት ዕቃዎች ከሩቅ አገር ነበር ተጭነው የሚመጡት። አሁን እዚህ አገር መመረት እየተጀመረ ነው። ገቢ ምርቶችን መተካት ማለት ይኼ ነው። በሁሉም ዘርፎች በተሻለ ጥራት እዚህ ተመርቶ ለሃገር ሊጠቅም የሚችልባቸው በርካታ ዕድሎች በየዘርፉ አሉ።
አግሮ ኢንዱስትሪ ላይ ማተኮሩ መጥፎ አይደለም፣ ዕድሎች አሉ። ለምሳሌ፣ አንድ ፋብሪካ 1 ነጥብ5 ሚሊዮን ኩንታል አኩሪ አተር ፈለገ፣ በመጀመሪያ ዙር 28 ሺሕ ኩንታል ብቻ ነበር ያገኘው፣ በሁለተኛው ግን የፍላጎቱን ግማሽ ያህል አገኘ። ከ28 ሺህ ወደ 700 ሺህ አካባቢ ማለት ነው። ፍላጎቱ በራሱ ምርት እንዲመረት አደረገ ማለት ነው። ቀጣይም መቶ በመቶ መድረስ ስላለበት ራሱ ወደ አርሶ አደሩ እየሄደ ምርጥ ዘር እያቀረበ፣ ኮንትራት ፋርሚንግ እየገባ አርሶ አደሩን ተጠቃሚ ያደርጋል፣ ፋብሪካውም ሳያቋርጥ ሥራውን ይቀጥላል፣ ገበያም አለው። ስለዚህ በየደረጃው ከአቮካዶና ከወተት ጋር የተያያዙት ፋብሪካዎችም ይኼንን ነው እያሳዩ ያሉት። የእሴት ሰንሰለቱ ረዥም ነው። ስለዚህ ማኑፋክቸሪንግ፣ ሁሉም ሰው በሥርዓት እስካስኬደው ድረስ ጠቃሚ ይሆናል። አላስፈላጊ ጣልቃ ገብነትና ጉልበትን መሠረት አድርጎ ክፈለኝ የሚል በረዥም መስመር ውስጥ ከገባ ደግሞ፣ ፋብሪካው እስከ መዘጋት አደጋ ላይ ይደርሳል።
ይኼንን እንቅስቃሴ ስንጀምር ቁጥራቸው ቀላል ያልሆኑ ፋብሪካዎችን ተዘግተው አግኝተናል። አሁን አንዳንዱ ክልል ላይ ሰላሳ፣ አንዳንዱ ክልል ላይ ሃያ እያለ ከዚህ እንቅስቃሴ በኋላ የተወሰኑ ችግሮቻቸው ተፈቶላቸው ወደ ማምረት የተመለሱ አሉ። ሰላሳ ፋብሪካዎችን ወደ ማምረት መመለስ ቀላል አይደለም። ቁጥራቸው ግን ቀላል የሚባል አይደለም። ከአጠቃላዩ ወደ አሥር በመቶ ቢሆን ነው። አሁንም መቀጠል ይኖርብናል። ክልሎችም በዚህ መንገድ እየሄዱ ነው። ሁሉም አካባቢ ቆም ብሎ እዚህ ጋ ትንሽ ከሌላው ዘርፍ የተለየ ድጋፍ ይፈልጋል የሚልና እያንዳንዱን ችግር በዝርዝር እየለዩ ወደ ሥራ ለማስገባት ጥረት እየተደረገ ይገኛል።
“ኢትዮጵያ ታምርት!”
አሜን።
በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)
fenote1971@gmail.com
አዲስ ዘመን ግንቦት 18 ቀን 2014 ዓ.ም