እንደኔ አዲስ ሃሳብና ቃል ሲመለከት የሚደመም ሰው ብዙ ይሆን እያልኩ አስባለሁ። እኔ አዳዲስ ቃላት ጆሮዬን ያቆሙታል። ትርጉሙን እስካገኝ ነፍስያዬ መርምሪ ጠይቂ ጠይቂ ይለኛል። ይህ አዲስ ሃሳብና ቃል ግን ምን ማለት ነው? ለምን ዓላማስ የተሰዘነረ ነው? የሚሉ ጉዳዮችን መልስ እስካገኝለት እረፍት አላገኝም። ይህ ምናልባት የቃሉን ትርጉም ካለማወቅ ወይም ስለ ሃሳቡ ጭብጥ ካለመረዳት አይደለም። ይልቁንም የሃሳቡና ቃሉ ከሚነገርበት አገራዊ ወይም የሕዝብ ኑረት አውድ አኳያ ምን ይመስላል የሚለውን በወጉ ለማጤን፤ እንደ ግንዛቤዬም የራሴን አረዳድ በሚጠቅም መልኩ ለማዋጣት እንጂ።
ሰሞንኛው «ንግግርና ሃሳባችን በእውቀት ይቃኝ» ይሉት ውትወታም፤ አየሩን የሞሉት ፈር ለቀቅ ንግግሮች፣ መሠረት የለሽ ሃሳቦች፣ እውቀት የናፈቁ ቃላት መወራወሮችም የዚህ ዘመን ተጽዕኖ መፍጠሪያና መርህ አልባ ቅቡልነትን መፍጠሪያ ስለመሆናቸው አጥብቄ እንድመረምር አደረገኝ። እንደተረዳሁትም፣ ሰሞንኛው የአገራችን ጉዳይ ላይ ከየት እንደተነሳ የማይታወቅ ነገር ይዘው እዛም ብቅ እዛም ብቅ የሚሉ ሰዎችን እየተመለከትን ነው።
ይህ ጉዳይ እኔ ብቻ ይሆን የሚታየኝ ወይስ እናንተም ይታያችኋል? ሰሞኑን በጣም በሃሰት ወሬ የተጠመዱ ሰዎች አልበዙባችሁም? እንደ እኔ ግን እንደው አገኘሁ አማረልኝ ብለው እዚህም እዚያም የሚዘባርቁ ንግግራቸው የሌላውን ስሜት ባልጠበቀ መልኩ አንደበት እንዳመጣላቸው የሚለቅቁ ግለሰቦች የበዙበት ዘመን ላይ መሆናችንን ታዝቤያለሁ። ለራሱ ስሜቱን ከሞላ ስለሌላው ጉዳይ ጉዳዬ ሳይል ሌላውን ነገር ነገሬ ሳይል እዚህም እዛም ልታይ ልታይ የሚል ሰው በዝቷል።
አማረልኝ ብሎ አፉን ሲከፍት ባዶነቱ ጎልቶ የሚታይበት፤ ይባስ ብሎ የራሱን ጉድለት በወሬ ብዛት የሸፈነ መስሎት ከየምናምኑ የቃረማትን ቁንፅል እውቀት ይዞ የሚፋንን ሰው በርክቷል። ይሄን ሀሳብ ከየትኛው ሰው አንደበት ነበር የሰማሁት እስከሚያስብል ድረስ በየፖለቲካ አወዱና በየመገናኛ ብዙኃኑ ብቅ የሚሉ ንግግሮችን እየቀነጣጠበ የሚያወራ፤ የሱ የወሬ ጥማት ይርካ እንጂ ከአፉ የወጣው ቃል ሌላው ሰው ጋር ምን ያመጣል ብሎ የማያስብ የሃሰት መረጃ አዘዋዋሪ በዝቷል።
እስከዛሬም ድረስ ከታሪክ ባየነው፤ በመኖር ሂደት ውስጥ በድግግሞሹ ከልምድ በቀሰምነው፤ ጥል የሚጀመረው፣ ፍቅር የሚጠብቀው ሰላም የሚሰፍነው እና እርቅ የሚሰምረው ከአፍ በወጣ ቃል ነው። ቃሉን ያሳመረ ከአምሳያው ሰው ጋር የሚያግባባውን ቃል መርጦ የራሱን ስሜት ብቻ ሳይሆን የሌላውስ ምን ይላል? በሚል የልቡን ትርታ ያዳመጠ በጥበብ የተናገረ ሰላምን የመረጠው እሱ በእውነት ላይ ባልተመሰረተ መረጃ የሰውን ስሜት ከሚጎዱት ባይመደብም፤ ወቅትና ጊዜ አማረልኝ ብሎ አፉ እንዳመጣለት የአንድ ሰሞን ጭብጨባ ናፋቂ ደግሞ ሁሉንም አውቃለሁ ባይ ሁሉንም ልንካ፣ ሁሉንም ልናገር ባይ ነውና እዚህም ልናገር እዛም ልመስክር እያለ እውቀት አልባ ወሬዎችን ይዞ አደባባይ ይወጣል።
ሕዝቡ የኑሮ ውድነት ናላውን አዙሮት እዚህም ጭንቅ እዛም ጭንቅ በሆነበት በዚህ ዘመን ጆሮ አደንቋሪ ቃል፤ ባዶ ጠብ የማይል ግራ የገባው ወሬ፤ ወይ መሠረት የለው ወይ ለዛውን አያውቅ ዝም ብሎ ለአፉ ለከት ሳይበጀለት መልቀቅ፤ ካልተጠነቀቁ ልብ ካላሉለት ከአፍ የሚወጣ ቃል ሰላምን ለማወክ ከምንምና ከማንም ይልቃል። ልቦናን አቁስሎ ሰላምን ይነጥቃል። እናም በሃሰት ወሬ ታይታና ጊዜያዊ ጥቅምን ለማግኘት የምትጥሩ ዓለም የሁሉም ናት፤ በጋራ ቤታችን እንደሚመቸን እንድንኖር ለአፍህ ልጓም ማበጀቱ የተሻለ ነው እላለሁ።
በአብሮነት ሂደት ውስጥ ራስን ካልጠበቁ፣ ካልተጠነቀቁ፣ ንግግርን ቆጥቦ በወግ ካልከወኑ የአንደበት ወለምታ ከዱላ ያቆስላል፤ ከጥይት ያደማል፤ ሕሊናን ሲመታ የቁስሉስ ጥልቀት በምን ይታከማል? እጅግ ያስጨንቃል፤ ከመብረቅ ይጮሃል፤ ሕዝብ ሲያተራምስ፣ ሰላም ሲያደፈርስ ከሰይጣን ይከፋል። እናም የሃሰት ቃል ሰንዛሪው የአንደበትህ ጅራፍ ክፉ ክፉ ቃልህ እንደተባራሪ ጥይት አንዱንም አድምቶ ሌላውን አቁስሎ በጥልቀት ሲረብሽ ሕዝብን ከሕዝብ ጋር ወገን ከወገኑ ሲያተረማመስ አይነካኝም ያልከው እሳት ማጥፊያ ሆነህ ከውሃው ጋር እንዳትጨለፍ ለሰው የቆፈርከው አንተን እንዳይቀብርህ። ምንጭ የሌለው ወሬ መሠረተ ቢስ ትርክት ይዘህ ልታይ ልታይ ማለቱን አቁመህ ሕዝብ ሕዝብ ነውና እንደ ሕዝብህ እንድታድር እኔ እመክርሃለሁ።
ምክር አልሰማ ብለህ ንግግር ካዛባህ፣ ንግግርህም ካልጠራና አፍህ ክፉ ቃል ከተፋ፤ አፍም እንደ ጥይት ካቆሰለ በኋላ፤ የልብን አድርሶ ሆዴ ባዶ ነው ቢባል ከአፍ የወጣ አፋፍ ነውና ነገሩ መጠንቀቅ ግድ ነው። ይህ ሲሆንና መርህ አልባ ንግግር ሲጠፋ በቀዬውም በአገሩም ሰላም ይሆናል፤ ካልተጠነቀቁ አፍ ሲያድጥ ልጓም የለውም። ከብርሃን ይፈጥናል፤ በፀብ አጫሪ መንፈስ በጥል አድራሽ ክንፉ በቀል ያስነሳል። ሕሊናን አቁስሎ ቂም ወልዶ…. መርዝ አዝሎ…. ከትውልድ ትውልድ የበቀልን ቁርሾ ይዞ ይዋረሳል። ስለዚህ ይበቃል ለአንደበት ለከት ማበጀት ይበጃል።
ከዚህ ለጊዜያዊ ቅቡልነት ማግኛ ሲባል ያለ ማስተዋል ከሚሰነዘር ሃሳብና ንግግር አባዜ በተቃራኒው ደግሞ፤ ሰው ፍቅርን ሲያስብ ሰላም ብቻ ሲሻ በፍቅር አንደበት መልካም ቃል ሲያወጣ፤ ከፍቅር ልብ ሲማጥ በአዕምሮ ተፀንሶ ምላስ ውብ ቃል ሲመርጥ፤ ቃላቱንም በትህትና እና በአክብሮት ሲያወጣ ለሰው ልጆች ሃሴትና ሰላምን ያመጣል። ይህን መሰል የተቆጠበ አንደበትና የተገራ ምላስ የሚያወጣቸው ቃላት ከዓለም ሕግ በላይ ገዢ፣ ከጦር ኃይልም በላይ ማራኪ፣ ከሚያስፈራው ግርማና ከጠንካራውም በላይ ከሁሉም የቀደመና የበረታ ኃይል አለው። ታዲያ በዚህ ልክ አንድ ትሁት ቃል በቤታችንም በደጃችንም የሰላም አዝመራ እንድናጭድ ካደረገን፤ ለአንድ ሰሞን ሙገሳና ታይታ ስንል በግድ የለሽነት ቃላትን መወርወር ለምን አስፈለገን?
እናም እላለሁ፤ የአንድ ሀገር መሪዎች ብሎም ነዋሪዎች ለቃል ተጠንቀቁ፤ ነገርን ከሰሩ ውሃውን ከጥሩ ነውና፤ ነገርን መርምሩ፤ በደንብም አስተውሉ፤ ምክንያቱም፣ ተዋዶ ለመኖር ለአንድነት ማሰሪያ ለጠብ መጀመሪያ ለጥልም ለፍቅርም አንደበት ነው ሥሩ። እንዴት ከተባለም፤ ከአንደበት የወጣው አራራቂውም፣ አስታራቂውም ቃል፤ ከአፋችን ከመውጣቱ ነፍሳችንን ሊያጎሳቁልም ሊያለመልምም የሚችለው ከእኛው ወትቶ እኛኑ እንጂ ሌላ ማረፊያ የለውም። ሰው ክቡር ፍጥረት መሆኑን ተረድተን የዛሬው ክፉ ቃል ነገ ለራሳችን በሽታ ነው ብለን መለስ እናድርገው። ምላሳችንን ቆጠብ በማድረግ እርምጃችንም በማስተዋል ይሁን።
ለሀገሬ ምን ሠራሁ እንኳን ባንል፤ ምንም አላጠፋሁም ትውልድ አይወቅሰኝም፤ ወገንን ከወገን አላገዳድልኩም የሚለን ህሊና ሊኖረን ይገባል። ጥሩ ነገር መናገር ቢሳነን እንኳን ዝምታን ማን ይወስድብናል? መናገር የግድ ከሆነብን ደግሞ ለታይታና ለጊዜያዊ ቅቡልነት ስንል ያለ እውቀት መናገራችንን ትተን ታሪክን አጥንተን በጥልቀት ተረድተን ንግግራችን በእውቀት የተቃኘ ይሁን ብዬ አበቃሁ። ሰላም!
ብስለት
አዲስ ዘመን ግንቦት 18 ቀን 2014 ዓ.ም