እንደምን ሰነበታችሁልኝ ውድ የአዲስ ዘመን ወዳጆቼ !! ሰነፍና አላዋቂዎች ስለትናንት፣ ብልሆች ስለአሁን፣ ሞኞች ደግሞ ስለነገ ብቻ ያወራሉ ይባላል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በዓለም መገናኛ ብዙኃን አማካኝነት የምንሰማቸው ዜናዎች ሁሉ የሚነግሩን ስለ ጦርነቶችና ግጭቶች በመሆናቸው የሰው ልጅ እልቂትና መፈናቀልን የኢኮኖሚ ውድቀትን የሚያስከትለውን አስከፊ ወሬ ተለማምደነው መሰል ብዙም ሳንደነቅ በቸልታ የምናልፈው ቀልድ ሆኗል::
በአገራችንም የሕወሓት «አጥፍተህ ጥፋ» ቅድመ ዝግጅት ሊጀመር እንደሆነ ሰሞኑን የሚጎሰመው የሶሻል ሚዲያው ከበሮ ሲጮህም ስለተለማመድነው ቅኝቱን እየሰማን እንዳልሰማን ዝም ብለን አልፈነዋል። ሕወሓት ግን ጦርነቱን አልጨረስኩም:: ያልተከፈለኝ ወይም ያልከፈልኩት እዳ አለብኝ….. ሒሳቤን አላወራረድኩም ወይም ታዝዤ ያልፈጸምኩት ተልዕኮ አለብኝ፣ ወዘተ. በማለት የጦርነት አታሞውን እየደለቀ፤ የበቀል ሰይፉን እየሳለ….. ክላሽኑን እየወለወለ በአውጫጭኝ የሰበሰባቸውን ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ለአቅመ አዳም ያልደረሱ ወጣቶችንና የደራጃቸውን ሚሊሻዎቹን በሽምቅ ውጊያ ሲያሰለጥን ቆይቶ አሁን በሁሉም ግንባር ለማጥቃት ተዘጋጅቻለሁ በማለት ፉከራና ቀረርቶውን እያስተጋባ፤ በትግራይ ዲጅታል ሚዲያዎች አማካኝነት ነጠላ ዜማውን ለቆ መጣሁ ቀረሁ እያለን ነው::
በቅርቡም የሕወሓት ከፍተኛ አመራሮች የተባሉቱ ከክልሉ ነዋሪዎች ጋር ባደረጉት ውይይት ከመንግሥት ጋር ችግሮችን በዲፕሎማሲ ለመፍታት ሲደረግ የነበረው ጥረት አለመሳካቱን ጠቅሰው፤ የትግራይ የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት ለማረጋገጥ የመጨረሻ የጦርነት ምዕራፍ ላይ መደረሳቸውን ጠቅሰው ውሳኔያቸውን አሳውቀውናል። በነገራችን ላይ እነዚህ ሰዎች የአንድ ሰው መጥፎ ሐሳብ በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ ሕዝቦች ትልቅ እልቂት ሊሆን እንደሚችል መገመት የቻሉ አልመሰለኝም።
ለምሳሌ፣ የሕወሓቱ መሪ ዶክተር ደብረፂዮን ገ/ሚካኤል በአንድ ስብሰባ ላይ ተገኝተው ያቀረቡትም ንግግር ውሀ የማይቋጥርና ለትግራይ ሕዝብ የማይመጥን መሆኑን ሳልጠቅሰው ባልፍ ደስ ባለኝ ነበረ። ነገርግን ታሪክ ነውና በሰነድ ይቀመጥ ዘንድ እንደወረደ ላቅርበው።
ዶክተር ደብረፂዮን በዚህ መድረክ ንግግራቸው «… በዚህ ሁኔታ መቀጠል አንችልም:: ከሰሜን ሸዋ በኋላ ለሰላም እና ዲፕሎማሲ ዕድል ሰጥተናል። ከጦርነት በፊት እና በጦርነት ጊዜ ዕድል ሰጥተናል። ሁሉም ፖለቲካዊ ችግር በሰላም እና በዲፕሎማሲ ብቻ አያልቅም። መብታችንን ለማስከበር ሪፈረንደም ማካሄድ አለብን፤ የትግራይ ሕዝብ የራሱን ዕድል በራሱ መወሰን አለበት፤» በማለት ለእነሱ የአጥፍቶ መጥፋት ተልዕኮ ሕዝብን እንደገና ጦርነት ውስጥ ለመማገድ ማነሳሳታቸው በቸልታ የማናልፈው፤ ዓለም አቀፍ ወንጀል መሆኑንም አስረግጠን ልንነግራቸው ይገባል።
በሌላ ዜና፣ የኤርትራ መንግሥት ኢንፎርሜሽን ሚኒስቴር ድረ-ገጽ ላይ የወጣው ጽሑፍ ራማ እና ባድመ አካባቢ ከሕወሓት ኃይሎች ጋር ግጭት አጋጥሞት ነበር ስለመባሉ አስተያየት ከመስጠት ቢቆጠብም፤ በድህረ ገፁ ላይ ባስተላለፈው መልዕክት በዓለም አቀፍ ሕግ የኤርትራ ሉዓላዊት ለመድፈርና ለመውረር ወያኔ በዝግጅት ላይ ይገኛል ሲል ለዓለም አቀፉ ኅብረተሰብ እወቁልኝ ብሏል። ከቀናቶች በፊትም የአማራ ክልል አስተዳደር ከሕወሓት በኩል ሊሰነዘር ይችላል ለሚለው አዲስ ዙር ወረራን ክልሉ እራሱን መከላከል እንዲችል፣ ሕዝቡ ዝግጁ እንዲሆን ትዕዛዝ አስተላልፏል::
ይህ በዚህ እንዳለ ደግሞ፣ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን (ኢሰመኮ) እያንሰራራ ያለው ግጭት መቋጫ እንዲያገኝ ለሁሉም አካላት የመፍትሄ ሀሳብ ያላቸውንም ቁምነገሮች በዝርዝር ጠቅሶ አቅርቧል። ኢሰመኮ- የግጭቱ ተሳታፊዎች፣ አገር አቀፍ ተዋናዮች ሲቪክ ማህበራት፣ መገናኛ ብዙኃን፣ የሃይማኖት አባቶች እና ሌሎች አካላት ገንቢ ውይይቶችን ጨምሮ እየተደረጉ ያሉትን ጥረቶችን በማደስ ግጭቱን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡም አደራ ብሏል:: ነገርግን ከጥፋታቸው ለመማር ፍላጎት የሌላቸውና ለለውጥ ያልተዘጋጁት ናፋቂ ግንቦት 20ዎቹ በእንቢ ባይነት አቋማቸው ፀንተው የትግራይን ሕዝብ ለእልቂትና ለጦርነት እንዲዘጋጅ እያስገደዱት ነው::
ምንም እንኳን ይሄን መሰል የሕወሓት ድርጊት ቢያሳዝነንም፣ ፍርዱን ለትውልድና ለታሪክ ትተን እኛ ለጋራ ነፃነታችንና ለለውጥ መዘጋጀት ይኖርብናል። በዚህ አጋጣሚ፣ የአንድ ሶሪያዊ ወጣት ታሪክ ትዝ አለኝ: : በ1943 ዓ.ም የተወለደ አንድ ሶሪያዊ ወጣት ለሚያስተምሩትና ለሚመክሩት አባቱ በ1983 ዓ.ም አንድ ደብዳቤ ፅፎ ነበር:: የደብዳቤውም ይዘት እንዲህ የሚል ነበር፡-
«እስከ 1970 ዓ.ም መልካም የሆኑ ሥራዎችን እሠራ ነበር። ይሄንንም ሌትም ቀንም ነበር የምከውነው:: ይህ ብቻም አይደለም፣ ሁል ጊዜም በሕይወቴ የመለወጥ ስሜት ነበረኝ፤ ለመማር የነበረኝ ልዩ ትጋት ትዝ ይለኛል:: ይሁን እንጂ በ1970 ዓ.ም የምሠራቸው መልካም ሥራዎች ሁሉ ባሉበት ቆሙ:: ድካምና መሰልቸት ሕይወቴን ተጫጫነው:: ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በማናቸውም ጊዜ ደብዳቤ ስፅፍ ዓመተ ምሕረቱን 1970 እያልኩ ነው:: ዘመኑ በእኔ አቆጣጠር እስካሁን ድረስ 1970 ነው:: ምክንያቱም ከ1970 በኋላ በኑሮዬ ውስጥ ምንም የተለወጠ ያደገ የተስተካከለ ነገር የለምና እባክዎት ብዙ የሚመክሩኝ አባቴ ምክርዎትን በመለገስ ወደ 1971 ያሸጋግሩኝ፤» በማለት የፃፈላቸው ነበር::
እሳቸውም ሲመልሱ፡- «መጀመሪያ አንተ ካልተለወጥክ ዘመኑም አይለወጥም፤» ብለው ነበር የመለሱለት ይባላል። በእርግጥም የአስተሳሰብ ለውጥ ያስፈልጋል:: የሰው ልጅ አንዱ የስልጣኔው መገለጫው ከራሱ ጋር የሚያደርገው ትግልና የአስተሳሰብ ለውጥ ነው:: ኋላ ቀር የሕይወት ዘይቤን ቀይሮ በአዲስ አስተሳሰብ በጋራ መስራትን በጋራ ማደግን አብሮነትን መለማመድ ሲጀምር ዘመኑም ወሩም ቀኑም ሰዓቱም አብሮ ይለወጣል:: የአስተሳሰብ ለውጥ ስንጀምር በድህነትና በድንቁርና ላይ አምፀን የቴክኖሎጂና የኢንዱስትሪ ባህል አብዮት ማካሄድ እንጀምራለን:: የአስተሳሰብ ለውጥ ስናደርግ የጎሳንና የዘር ኬላን እየጣስን ፍቅር ዘርተን ለሕዝባችን ፈጣን ለውጥ የማምጣት አቅም እንገነባለን። የአስተሳሰብ ለውጥ ስናደርግ አገራችንን በጥሩ ሁኔታ ለመለወጥ ሺህ ዕድሎች ይኖሩናል።
የአስተሳሰብ ለውጥ ብለን ስንል የበሰለና ያደገ አመለካከት፣ ሚዛናዊና አርቆ አሳቢ የፖለቲካ እውቀት ባላቸውና በተግባር በተፈተኑ የለውጥ አራማጆች የሚቀነቀን አስተሳሰብን ለአገር ፋይዳ እንዲሰጥ አድርጎ አስተማማኝ ፣ ዘላቂና ሠላም የሰፈነበት ልማትን በፅኑ መሠረት መገንባት ማለት ነው:: በዚህ ዓይነት አስተሳሰባችንን ቀይረን የማንጓዝ ከሆነ እንደ ሶሪያው ወጣት ዘመኑም በእኛ አቆጣጠር እስካሁን ድረስ 1970 ሆኖ ሳይለወጥ ይቀጥላል::
የአስተሳሰብ ለውጥ ስንጀምር ግን አሁን ካለንበት የበለጠ የተሻለ፣ ደስተኛ፣ ጤናማ፣ የተትረፈረፈ፣ ስኬታማ አገር እንዲኖረን መመኜት ብቻ ሳይሆን እንዲኖረን እናደርጋለን:: የአስተሳሰብ ለውጥ ስንጀምር ከመነጣጠል አብሮ መኖርን፣ አብሮ ማደግን መከባበርን… ይቅር ባይነትን ባህላችን አድርገን መለማመድና መኖር እንጀምራለን:: እኛ ካልተለወጥን ግን ከዓለማችን እርቀን ከዘመን ተኳርፈን ከወገን ተጣልተን እስካለንበት 21ኛው ክፍለ ዘመን ድረስ አመተ ምህረቱን የምንቆጥረው በዚያው ክላሽን ባነሳንበት…. ደደቢት በርሀ በገባንበት …1967 ላይ ነው የምንቆዝመው::
በመሆኑም አገርን ለመለወጥ በቅድሚያ የአስተሳሰብ ለውጥ ማድረግ ተገቢ ነው:: የተለወጠ ያደገ የተስተካከለ አብሮነትን ለመቀበል ዝግጁ የማንሆን ከሆነ ሰላምን ከመስበክ ይልቅ ዘወትር የጦርነት አዋጅ ነጋሪና የእልቂት ጡሩንባ ነፊ ተብለን በታሪክ ፊት የተመፅዋችነት ካባ አጥልቀን በትውልድ የፍርድ አደባባይ መቆማችን የማይቀር ነው። እኛ ግን እንደዜጋ አገራችንን ከሽብር አደጋ ለማዳንና ሕዝባችንን ለመታደግ ምን ማደረግ ይጠበቅብናል? በማለት እራሳችንን ጠይቀን በተረጋጋና በሰከነ አዕምሮ …ተደማምጠን መነጋገር ይኖርብናል:፡
ሕወሓት ከግማሽ ሚሊዮን በላይ የሽምቅ ተዋጊዎችን አሰልጥኖ ጨርሷል። ዝግጁም ነኝ ብሏል። በትግራይ ክልል ልጁን ያላዘመተ «ሴት» ነው የሚል ዲስኩር ይዟል። እራሱም ያልዘመተ ባንዳ ነው ተብሏል። የትግራይ ጠላት ተባባሪ ነው እያሉ ወጣቱን ከአባቱ እየለዩ ሲቀሰቅሱት፣ ከፍ ሲልም ሲያስገድዱት ከርመው አሁንም የትግራይ ወጣቶች ለዳግም የጦርነት ለዳግም እልቂት እንዲዘጋጁ ገፋፍተው ምሽግ ውስጥ አስገብተዋቸዋል።
ለአገራችን ችግር መፍትሔ የምንፈልግ ከሆነ ከእንዲህ ዓይነት የሕወሓት የጦርነት ዜማ ወተን ወደ ልማት መሸጋገር ይኖርብናል። በአብሮነት እንደ አገር እንድንቀጥልና ተጨማሪ ጦርነቶች እንዳይቀሰቀሱ ለማድረግ የበኩላችንን ማበርከት ይኖርብናል። መንግሥት የተናጠል የተኩስ አቁም ስምምነት ወስኖ የእርዳታ መተላለፊያ ኮሪደሮችን በመክፈት የሰላም ዋስትና የሚሆን መፍትሔ እያቀረበ ሰላም ወዳድነቱን ለዓለም ኅብረተሰብ በተግባር ከመግለፅ ያለመቆጠቡ ለዚህ ዓይነት መፍትሄ መልካም ጅምር ነው። ሆኖም ከሕወሓት እኩይ ባህሪ አንጻር ጦርነቱን ለማስቀረት ግን የሚችል አይመስለኝም::
ጦርነቱን አስቀርቶ ሂደቱን በሰላም ለመጨረስ የኢትዮጵያ መንግሥት የሚያደርገውን ጥረት ከሚታየው ጥረት በተጓዳኝ ሌላ ምን እየተደረገ እንደሆነ ለሕዝብ ግልፅ አድርጎ በይፋ ባይነግረንም፤ በስማ በለውና በወፍ በረር እስከ ሽምግልና መኬዱን ሰምተነዋል:: እውነት ከሆነም እሰየው !! ወደፊት የምናየው ይሆናል:: ሕወሓት ግን አሁንም ለሰላምና ለእርቅ ዝግጁ ባለመሆኑ እጅ አልሰጥም፣ ብሎ የሽብር ጦርነቱን እንደገና ለማወጅና ሕዝብን ለማስጨረስ ቀንና ሰዓት እየመረጠ መሆኑን መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ በንቃት እየተከታተለው ነው::
በእኔ እምነት ይህ ጦርነት ዳግም እንዳይቀሰቀስ መንግሥት ያለውን ትዕግስት አሟጦ የጨረሰ ይመስለኛል:: ከጦርነቱ የተሻለ ሰላምን መምረጥ ትርፋማነቱ ቢያዋጣም ወያኔ ግን ከእንግዲህ ለሰላም ድርድር ለመቀመጥ ዝግጁ እንደማይሆን መንግሥት ተገንዝቦ ጦርነቱን በተመለከተ ለዓለምአቀፉ ማኅበረሰብና ለኢትዮጵያ ሕዝብ በይፋ አሳውቆ ሕዝቡን ከጎኑ በማሰለፍ በተጠንቀቅ መቆም ይኖርበታል። እንዳለፈው ጊዜ በቸልተኝነት የሚደረጉ መዘናጋቶች አገርና ሕዝብን ካለፈው የባሰ ዋጋ ማስከፈል ብቻ ሳይሆን እንደ አገር እንዳንቀጥል ተፅዕኖ የሚያደርጉ አያሌ ምክንያቶች አሉ። ይህ ብቻም አይደለም ትልቅ የኢኮኖሚ ውድመት አድርሰን ከፍተኛ የእርሀብ እልቂት ሊያጋጥመን እንደሚችል በመንግሥት በኩል ሊታሰብበት እንደሚገባ አሁንም… ነገም …ከነገ ወዲያም …በጥብቅ እያሳሰብን መወትወታችን የማይቀር ነው::
ከዚህ ባሻገር በሌሎች አውዶች በተለይ ከጦርነት ባልተናነሰ ሊጋጥመን የሚችለው ሕወሓት የሚያሰራጨው የውሸት ፕሮፓጋንዳና የሶሻል ሚዲያ ጦርነት ቀላል እንደማይሆን እርግጠኛ ሆነን በጋራ ለመመከት መነሳት፤ ኃላፊነት የሚሰማቸው የሚዲያ ተቋማት እስትራቴጂ ነድፈው መዘጋጀት ይኖርባቸዋል:: ሌላው በዲጅታል ዲፕሎማሲ የሚደረገው እሰጥ አገባ በድል ለማጠናቀቅ ዳያስፖራውን ይመለከታል። ዳያስፖራው በትልቅ በትንሹ ኩሪፊያውን ትቶ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ሲል ከመንግሥት ጋር በቅንጅት ለመስራት ሎቢስቶችን በመያዝ ብሔራዊ ግዴታውን እንዲወጣ መንግሥት ግልፅነት ያለው ብሔራዊ ጥሪ ማቅረብ ይኖርበታል።
ያም ሆነ ይህ ሕወሓት ለአገራችን ችግሮች መባባስና መቀጠል ዋና ተጠያቂ ማድረግ ብቻም ሳይሆን ከበፊቱ ተሞክሯችን ልምድ በመነሳት የነበሩብንን ድክመቶቻችን አርመን መንግሥት እንደመንግሥት የተሻለ አሠራር በመዘርጋትና ለሰራዊታችን የሚደረገው ድጋፍ ከደም መስጠት ጀምሮ የተሟላ ስንቅና ትጥቅ እንዲያገኝ አብክሮ መስራት አለበት። እያንዳንዱ የመንግሥት ኃላፊ ዝግጅቱን በቀጠሮ ሳይሆን ዛሬውኑ መጀመር አለበት:: በመግቢያዬ ያነሳሁት ብሂል ይሄንኑ የሚነግር እንደመሆኑ፤ ልብ ያለው ልብ ይበል:: በሌላ ዝግጅት እስክንገናኝ ቸር ይግጠመን። ሰላም!
ከአለባቸው ደሳለኝ አበሻ (ለንደን)
አዲስ ዘመን ግንቦት 17/2014