በምስጋና ፍቅሩ
እኛ ኢትዮጵያውያን በሌሎች ሃገራት የሚደረግብን ጫና፣ ግፍ እና በደል የመሸከም አቅም የለንም። ለጠላት የመንበርከክ ታሪክም ከአባቶቻንን አልወረስንም። በሌሎች ሃገራት ሊሆኑብን፤ ሊደረጉብን የታቀዱትን ክፉ እቅዶች እንዲከሽፉ ለማድረግ በአንድነት ‹‹በቃ›› የማለት አቅማችንም የሚያስገርም እንደሆነ ማንም የሚመሰክረው ጉዳይ ነው። ከእኛ አልፈን በአህጉራችን የሚገኙትን ሃገራት በተለያየ መንገድ ለመቀራመት ለሚያስቡት ምዕራባውያን ከድርጊታቸው ገሸሽ እንዲሉ የ‹‹በቃ›› እንቅስቃሴውን በአህጉሪቱ እንዲቀጣጠል በማድረግ ትልቅ አቅም መፍጠር ችለናል ብለን ኮራ ብለን ብንናገር ማጋነን አይሆንም።
ይሁን እንጂ በሃገር ውስጥ በሚገጥሙን ችግሮች በአንድ ላይ ሆኖ ለመፍታት ብሎም ለመታገል ወደ ኋላ ስንል ይስተዋላል። ለዚህ ሃሳብ ማጠናከሪያ የሚሆኑ ብዙ ምሳሌዎች አነሳለሁ። በአሁን ወቅት ሃገራችን በብዙ ውስብስብ ችግሮች ተጠምዳለች። አንድ ጊዜ የኑሮ ውድነቱ፤ ሌላ ጊዜ ስግብግብ ነጋዴዎች የሚፈጥሩትን ችግሮች፣ ሠዎች በማንነታቸው በጽንፈኞች ሲጠቁ ለመመልከት በቅተናል።
በተለይም አሁን አሁን ከኑሮ ውድነቱ በተጨማሪ ዛሬስ ምን ይፈጠር ይሆን? የሚለው የብዙዎች ስጋት ከሆነም ሰነባብቷል። ይባስ ብሎም አንዳንዶቹ በሌሎች ሃገራት ሲሳለቁና በኢትዮጵያ ውስጥ ምንም ችግር እንደሌለ ሆኖ ለማሳየት የሚያደርጉት ጥረትም ሳንወድ በግዳችን ፈገግ እንድልን ያስገድደናል።
ሌላው ነገር ‹‹እኛ ኢትዮጵያውያንን የሚያሸንፈን አንዳች ኃይል አይኖርም። ›› ብለን እናስባለን ወይም እናምናለን፤ ምክንያቱ ደግሞ ጠላትን ለማንበርከክ በአንድነት የመነሳት አቅም፣ ፍላጎት፣ ሞራሉና ብቃቱ ስላለን ነው። በተቃራኒው ደግሞ በገዛ ወገኑ ሹመኛም ይሁን ነጋዴ አሻጥር ሲሠራበት በአንድ ላይ ሆኖ ‹‹በቃ›› ብሎ ከማጋለጥ ይልቅ ‹‹ሰው እንደሆነው እሆናለሁ›› በማለት በገዛ ራሱ ላይ ሌባ ቀማኛ ሲሾም ይታያል።
ከዚህ በተጨማሪም መረጃ በመስጠት የዜግነቱን መወጣት ሲገባው እና ጉዳዩ የት አደረስከው? ብሎ ከመሞገት ይልቅ ስለ አብዛኛው ሰው ስለ ውጭ ሃገር የኑሮ ውድነት ሊተነትን ሲጣጣር ሕዝቤን ምን ነክቶት ይሆን? የሚል ጥያቄ ያስነሳል። ከሰሞኑ ረገብ ይበል እንጂ በማኅበራዊ ሚዲያዎችም ይሁኑ በመደበኛው የመገናኛ ብዙኃን ስለ ሩሲያና ዩክሬን ጦርነት በስፋት መረጃዎች ሲሰራጩ ነበር። ይሁን እንጂ ሃገራችን ውስጥ ግን ምን እየከሰተ እንደሆነ መረጃው የሌለው ወይም እንዲኖረው የማይፈልግ ቁጥሩ ጥቂት የሚባል አይደለም።
እርግጥ ነው የሁለቱ ሃገራት ጦርነቱ ምን አልባት ብዙ አንድምታዎች እንደሚኖሩት የሚታወቅ ሲሆን፤ ይህንንም በመገንዘብ ከኢኮኖሚ አንጻርም ምን ችግር ሊያመጣ ይችላል? በሃገራችን ያሉትን ችግሮች እንዴት እንፍታቸው? መፍትሔውስ ምንድነው? ብሎ ስለ ራስ ከማሰብ ይልቅ ፤ ምንም ነገር በማይፈይዱበት እና ለውጥ በማያመጡበት ሁኔታ ውስጥ ሆኖ ከባለቤቶቹ በላይ ነገሩን ልተንትን ማለቱ ‹‹የራሷ አሮባት የሰው ታማስላለች›› እንደተባለችዋ ሴት መሳቂያ ነው የሚያደርገን።
ሃገራችን ኢትዮጵያ ከአግዋ መሰረዟ ይታወሳል። ይህንን ለመቃወም በርካታ የሕዝብ እንቅስቃሴ የተደረገ መሆኑ የሚታወስ ሲሆን፤ የሃገር ውስጥ ነጋዴ ግን በገዛ ወገኑ ላይ አሻጥር ሲሠራ እንዳላየ ታልፏል። ሌላም ምሳሌ እናንሳ፣ ጥቁር አሜሪካዊው የጆርጅ ፍሮይድ በዘረኝነት ምክንያት ሕይወቱ ማለፉን ተከትሎ ድርጊቱን ለማውገዝ ብዙዎች ‹‹አይካንት ብሪዝ›› በማለት በማኅበራዊ ሚዲያዎቻቸውም ይሁን ባላቸውና ባገኙት አማራጭ ሁሉ ድርጊቱን ከማውገዝ አልተቆጠቡም። ዛሬ ግን በእኛ ሃገር ሰው በቁሙ ሲቃጠል፤ ሰዎች ሲፈናቀሉ፣ የሃይማኖት ተቋማት ሲቃጠሉ ስናይ ድርጊቱን ለማውገዝ መጮህ የሚገባንን ያህል አልጮህንም፤ ድርጊቱንም ማውገዝ ባለብን መጠንም አላወገዝንም ።
እንደምናስታውሰው አሸባሪው የሕውሓት ቡድን የሚያደርስባቸውን እንግልት ሸሽተው ወደ አማራ ክልል የገቡ የትግራይ ክልል ተፈናቃዮች እንዴት የእለት ጉርስ ያግኙ? ስለሚለው ጉዳይ ከማሰብ ይልቅ ስለ ሶሪያና ስለ ሌሎች ሃገራት ጉዳይ ያሳስበናል። ይህ ማለት ስለሌሎች ስደተኞችም ይሁን በጦርነት ውስጥ ስላሉት ሃገራት ተፈናቃዮች እና ችግር ስለደረሰባቸው ሰዎች ሰብዓዊነት አይሰማን ማለት አይደለም። ይልቁንም በቅድሚያ ስለራሳችን ስናስብ እና ያሉብንን ችግሮች ላይ አተኩረን ከሠራን ከራሳችን አልፈን ለብዙዎች መትረፍ እንችላለን ከሚል ከቅንነት የመጣ ሃሳብ ነው።
እናም በወገኖቻችን ላይ የሚደርሰውን መከራ የሚወገዘውን እንደ ሰው ማውገዙ ተገቢ ቢሆንም፤ በራሳችን ችግር ላይ ግን ችግሩን ተመልክቶ ለማውገዝ ብሎም ለመተቸት እና ችግሩ እንዲፈታ የመፍትሔ አካል ስንሆን አንመለከትም። እንደውም ውጭ ላይ ሆኖ ለሚታዘብም ጉራማይሌ የሆነ ነገር ነው የገጠመን።
አንድ ሰሞን የሽንኩርት ዋጋ በከፍተኛ ዋጋ ንሮ እንደነበር ይታወሳል። አንዳንዶቹ ችግሩን ከመናገር ይልቅ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ችግሩን አሳንሰው ሲሳለቁ ለማየት ተችሏል ። ዛሬ ደግሞ ዘይትም ይሁን ሌሎች መሠረታዊ የሚባሉ የምግብ ፍጆታዎች ዋጋቸው ከዕለት ዕለት እየጨመረ በመሆኑ የኑሮ ውድነቱ ብዙዎችን እያንገዳገደ ይገኛል። በመሆኑንም በመገንዘብ መንግሥት ከሰሞንኛ ሥራዎቹ በተጨማሪ በዘላቂነት ችግሩን ለመቅረፍ መሥራት ይጠበቅበታል። ማኅበረሰቡም ሆን ብለው የዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ እንዲወሰድ መሥራት ይኖርበታል።
በአጠቃላይ በውጭ ሃገራት አማካኝነት የሚደርስብንን ጫና ‹‹በቃ›› ለማለት ይሁን በሌሎች ሃገራት ላይ የሚደርሱትን መከራ ግፍ እንዲያበቃ ድምጻችንን ለማሰማት እንደምንፈጥን ሁሉ ሃገራችን ውስጥ የሚከሰቱትን ሞት፣ መፈናቀል እርስ በእርስ ያለመከባበር ችግሮቻችን መፍትሔ እንዲያገኙ ፤የመፍትሔው አካል ሆኖ መሥራት ከሁላችን የሚጠበቅ የቤት ሥራ ነው።
አዲስ ዘመን ግንቦት 17 ቀን 2014 ዓ.ም