ቅድመ – ታሪክ
ድንገት ሲጣደፉ ከፖሊስ ጣቢያው የደረሱት ግለሰብ ንዴታቸውን መቆጣጠር ተስኗቸዋል። ድንጋጤ፣ እልህና ቁጭት እያንቀጠቀጣቸው ነው። የምሽቱ ተረኛ ፖሊስ ጥቂት እንዲረጋጉ ጠይቆ ቃላቸውን ለመቀበል ተዘጋጀ ። ሰውዬው ሙሉ ስማቸውን «ጄኔራል ተስፋዬ ማሩ» ሲሉ አስመዘገቡ።
ጄኔራሉ መስከረም 26 ቀን 2004 ዓ.ም ምሽት ደብረብርሃን ስላሴ ቤተክርስቲያን ጀርባ ወሳኝ ቀጠሮ ነበራቸው። በሰዓቱ ለመድረስ ሱዚኪ ቪታራ መኪናቸውን እያሽከረከሩ ከአዲስ አበባ ሰሜን አቅጣጫ ፈጠኑ። በአንድ ትልቅና ጥቁር ቦርሳ ገንዘብ ይዘዋል። አንድ ሚሊዮን ዘጠኝ መቶ ሃያ ሺህ ብር።
የዛን ዕለታው ቀጠሯቸው መክረሚያቸውን ሲያፈላልጉት ለቆዩት ቦታ ግዥ ለመፈጸም ነው። ቦታውን ለማግኘት በወዳጅ ዘመድና በደላሎች ፍለጋ ሲባዝኑ ከርመዋል። አንዱን ሲመርጡና ሌላውን ሲያማርጡ የቆዩበት ጉዳይ ዛሬ እልባት በማግኘቱ ተደስተዋል። ጄኔራሉ ብቻቸውን እንደሆኑ ያውቃሉ። ለክፍያ የያዙት ገንዘብ በርከት ቢልም ውስጣቸው ፈጽሞ አልሰጋም። ከቦታው ሲደርሱ ከምሽቱ አንድ ሰዓት ከሰላሳ ሆኖ ነበር። የቤተክርስቲያኑን ዙሪያ ገባ መቃኘት ያዙ።
አካባቢው ጸጥ ረጭ ማለት ጀምሯል። ለማታ ጸሎት የመጡ ሰዎች ግቢውን እየለቀቁ ነው። አልፎ አልፎ ጭርታውን የሚሰብረው የጉልላቱ መርገፍት በንፋስ ግፊት ሲንሿሿ ይሰማል። ሰውዬው ሰዓታቸውን ደግመው ተመለከቱ። ከተባለው ጊዜ ቀድመው ተገኝተዋል። ባሻገር ፊታቸውን ዞር ከማድረጋቸው ከአንድ ወጣት ጋር ዓይን ለዓይን ተያዩ። ወጣቱ ለዛሬው ቀጠሮ ወሳኛቸው ነው። በከተማው ለሚገዙት የባዶ መሬት ሽያጭ ትልቁን ሚና ያበረከተ ደላላ።
ደላላው በለጠ ማንነታቸውን እንዳወቀ በፈገግታ ደምቆ ተቀበላቸው። ብቻውን አይደለም። አንድ ጎልማሳ ተከትሎታል። ወዲያው ሶስቱም በጄኔራሉ መኪና ተሳፍረው ወደ ቤተክርስቲያኑ ጀርባ አመሩ። በስፍራው እንደደረሱም ከነበሩበት ወርደው ሌሎችን መጠበቅ ያዙ። ይህ በሆነ አፍታ ጊዜ ውስጥ በለጠ በእጅጉ እንደበረደው ገልጾ መንቀጥቀጥ ጀመረ። ቅዝቃዜውን መቋቋም እንዳልሆነለት የተረዱት ጄኔራል ለመፍትሄው የመኪናውን የቀኝ በር ከፍተው ጋቢና አስቀመጡት።
ደላላው በለጠ ከወንበሩ እንደተቀመጠ መቁነጥነጥ፣ መንቆራጠጥ ያዘ። አይኖቹ ግራና ቀኝ ቃበዙ። እጆቹ ያገኙትን መያዝ መጣል ጀመሩ። ወዲያው ጣቶቹ አንድ ጥቁር ቦርሳ አስዳሰሱት። ቦርሳውን ጠበቅ አድርጎ ያዘው። ወዲያውም ገንዘቡ እንደሆነ እርግጠኛ ሆነ። አሁን ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ ከእጁ ገብቷል። ፈጣን አይኖቹ ወደ ውጭ ደጋግመው ተወረወሩ። ባልንጀራውና ጄኔራሉ ሞቅ ያለ ጨዋታ ይዘዋል። ከጓደኛው ጋር በምልክት ተግባቡ። ፈጥኖ በሩን ሲበረግድ ውጭ የቆመው ሰው ቦርሳውን ቀለበው። የሆነውን ሁሉ ያዩት ጄኔራል ተስፋዬ በድንጋጤ ብርክ ያዛቸው። ለቦታው መግዣ የያዙት ገንዘብ በደላላውና ግብረአበሩ ዓይን በዓይን እየተወሰደ ነው።
ንዴትና ድንጋጤ እንደዋጣቸው የአቅማቸውን ያህል ወደ ሰዎቹ ሮጡ። ከኋላቸው እየተከተሉም ሊይዟቸው ሞከሩ። ተጣጣሩ። ወዲያው ግን ድርጊታቸውን የሚያስቆም አስገዳጅ ሁኔታ ተከሰተ። አራት ጋቢ የለበሱ ሰዎች ዱላና ጩቤ እንደያዙ ከተደበቁበት ብቅ አሉ። በጩቤው እያስፈራሩም ወደሳቸው ቀረቡ። ይሄኔ ጄኔራሉ ካሉበት ሆነው የመኪናቸውን ሪሞት ተጫኑ። ለየት ያለ ድንገቴ ድምጽ የሰሙት አድፋጮችም በየአቅጣጫው ተበታተኑ።
ጀኔራሉ ነፍሳቸውን አትርፈው ወደፖሊስ ጣቢያ አመሩ። የደብረብርሃን ከተማ ፖሊስ የግለሰቡን አቤቱታ አንድ በአንድ ከመዘገበ በኋላ ተጠርጣሪዎችን ለመያዝ የሚያስችሉትን መረጃዎች ሰበሰበ። የሰዎቹን መልክና ቁመና መዝግቦም ሰውዬው ሲፈለጉ እንደሚቀርቡ አሳውቆ አሰናበታቸው። ጄኔራሉ ቃላቸውን ሰጥተው ከጣቢያው ሲወጡ በድንጋጤ እንደተዋጡ ነበር። አሁን ምሽቱ ገፍቷል። እዛው ማደር ግን አልፈለጉም። መኪናቸውን እያሽከረከሩ ወደ አዲስ አበባ የመልስ ጉዞ ጀመሩ። ወደ መሀል ሊደርሱ ጥቂት ሲቀራቸው ቴዲ ለተባለ ጓደኛቸው ደውለው የሆነውን ሁሉ ነገሩት። ቴዲ ከከተማው ዳርቻ የሚገኙትን ጄኔራል ያሉበት ድረስ ሄዶ አገኛቸው።
ምሽቱን አረጋግቶም ከአንድ ሆቴል አሳደራቸው። ሲነጋ ጄኔራል ተስፋዬ ጤናቸው ታወከ። ያጋጠማቸው ድንጋጤ ለህመም ዳርጎም ለሆስፒታል አልጋ አበቃቸው። ከቀናት በኋላ ጄኔራሉ ጥቂት አገገሙ። ከሆስፒታሉ እንዲወጡም ተፈቀደላቸው። የተፈጸመባቸውን ክፉ ድርጊት ግን እንደዋዛ መርሳት አልተቻላቸውም። ሽጉጣቸውን ጥይት እያቃሙ ውሎ ገባቸውን ደብረብርሃን ማድረግ ጀመሩ። ዕንቅልፍና ሰላም ላጡበት ጉዳይ በየቀኑ የፖሊስን በር ሳያንኳኩ አይውሉም።
የደብረብርሃን ፖሊስ ከተበዳዩ በደረሰው መረጃ ፍለጋውን ቀጥሏል። ድርጊቱ ሲፈጸም እማኝ ያለመኖሩ ጉዳዩን ቢያከብደውም ከጥረቱ አልታቀበም። የአባቱን ስም በውል ተለይቶ የማይታወቀውን ደለላ አስሶ ለማግኘት ሌት ተቀን ሲደክም ከረመ። ጄኔራል ተስፋዬ የሰውዬውን የሞባይል ቁጥር አስመዝግበዋል። ፖሊስም ህግና መመሪያው እንደሚፈቅደው ከኢትዮቴሌኮም ጋር ሆኖ አስፈላጊውን እንደሚፈጽም አሳውቋችዋል። ይህን እውነት የያዙት ተስፋዬ ከአዲስ አበባ ደብረብርሃን እየተመላለሱ ጉዳዩን ዳር ለማድረስ ሲባዘኑ ከረሙ።
ጄኔራል በቦታ ሽያጭ ሰበብ ገንዘባቸውን ከተዘረፉ ጊዚያት ተቆጥረዋል። እስካሁን ግን ወንጀል ፈጻሚዎቹን የበላው ጅብ አልጮኸም። ጠዋት ማታ በሀሳብ የሚብሰለሰሉት ሰው ከእልህ፣ ቁጭትና በቀል ጋር አድረው መነሳት ልማዳቸው ሆኗል። ላብ ያፈሰሱበት ንጹህ ገንዘባቸው እንደ ቀልድ ከእጃቸው መውጣቱ፣ እንደ ልጅ አታለው ያሞኟቸው ሰዎችም እንደዋዛ ጠፍተው መቅረታቸው ሁሌም ያበሽቅ ያናድዳቸው ይዟል።
መጋቢት 25 ቀን 2004 ዓ.ም
በጄኔራሉ ላይ የዝርፊያ ወንጀል ከተፈጸመ ስድስት ወራት ተቆጥረዋል። አሁንም ግን ተጠርጣሪዎቹን «አየን» ባይ እማኝ አልተገኘም። በተስፋና በብሽቀት መሀል የከረሙት ሰው ዛሬን በዚህ ቀን ላይ ቆመው የሆነውን ሁሉ ያብሰለስላሉ። ዛሬ ደግሞ ቪታራዋ መኪናቸው ከሀሳባቸው ጋር ወደቤት ይዛቸው እየገሰገሰች ነው። ምሽቱ ገፍቷል። ወደ ኮተቤና ካራ መንገድ የሚሄዱ ሰዎች ታክሲ ለመያዝ ይሯሯጣሉ።
ጄኔራል ብርሀኑ ለታክሲው ከሚሮጡት ሰዎች መሀል አንዷ ከአይናቸው ገብታለች። ሴትዬዋ ታክሲ ለመያዝ ስትጋፋ ቆይታ ባለችበት ቆማለች። አጠገቧ ደርሰው በ«ልሸኝሽ» ምልክት ሲያናግሯት አልተግደረደረችም። በሩን ከፍታ ከጋቢናው ተቀመጠች። ጉዞው በእሷ ምስጋና እንደተጀመረ ወዴት እንደምትሄድ ጠየቋት። ነገረቻቸው። መንገዷ መንገዳቸው በመሆኑ እንደሚያደርሷት ነግረው ወደፊት ቀጠሉ።
አለፍ እንዳሉ «ሻይ ቡና ልበልሽ »አሏት። ጥቂት አቅማምታ በሀሳባቸው ተስማማች። ሰዓቱ እየመሸ ቢሆንም በመኪናቸው መኖር ተማምናለች። ጉዞው እንደቀጠለ አንድ ሁለት ለማለት ቦታ አማረጡ። የሁለቱም ፍላጎት በአካባቢው ያለው የካራሎ ሆቴል ሆነ። ከሆቴሉ ግቢ እንደ ደረሱ ጄኔራሉ ከአንዱ ጥግ መኪናቸውን አቁመው ወረዱ። ሴትዬዋም ከኋላ ተከተለቻቸው። የሆቴሉ ሳሎን በጥቂት እንግዶች ተይዟል። በአንዱ ጥግ አንዲት ሴትና ወንድ ቢራ ይዘው ተቀምጠዋል። በሌላ አቅጣጫ ደግሞ በግል ጨዋታቸው የተጠመዱ ሰዎች ይታያሉ። አሁን ጄኔራሉ ሴትዬዋን አስከትለው ወደ ውስጥ እየገቡ ነው።
እግራቸው ወደ መሀል እንደ ደረሰ ግን ድንገት አይናቸው ከአንድ ሰው ላይ ተተከለ። ስለሰውዬው ማንነት ፈጽሞ አልተጠራጠሩም። ግንባር ለግንባር ሲፋጠጡ ከወራት በፊት የተፈጸመባቸው ማታለልና ዘረፋ አንደ በአንድ መጣባቸው። በንዴት እንደጦፉ ዓይናቸውን አፍጥጠው ተጠጉት። እጃቸው ይንቀጠቀጣል፣ ጥርሳቸው ይንገጫገጫል። አዎ! አሁን እያዩት ያለው ሰው በትክክልም ደላላው በለጠ ነው።
ወዲያው ሲንደረደሩ ሄደው የሸሚዙን ኮሌታ አንቀው ያዙ። «ፖሊስ ጥሩልኝ፣ጥሩልኝ ሲሉም መጮህ ጀመሩ። ጨኸታቸውን የሰሙ ፈጥነው ከቦታው ደረሱ። ግርግሩን ያስተዋሉ ለመገላገል መሀል ገቡ። ይሄኔ ደላላው በለጠ ወገቡን መዳሰስ ጀመረ። ወደ ኋላ ያለፈው የቀኝ እጁ ባዶውን አልተመለሰም። ነጣ ያለ ማካሮቭ ሽጉጥ ጨብጦ ነበር።
መሳሪያው በእጁ እንደታየ አብራው የነበረችው ሴት እየጮኸች ለመነችው። ለመገላገል የቀረቡ ሁሉ በድንጋጤ ገለል ማለት ጀመሩ። አጋጣሚው ለባለ ሽጉጡ መልካም የሆነለት ይመስላል። ወዲያው ዘቅዝቆ ያቀባበለውን ሽጉጥ አነጣጥሮ በጄኔራሉ ግንባር ላይ ተኮሰ «እግሬ አውጭኝ » ሲልም ተፈተለከ ።
የጄኔራሉን ተመቶ መውደቅ የተመለከተው የሆቴሉ ሂሳብ ሰራተኛ በለጠን በፈጣን ሩጫ ተከተለው። የኮቴ ድምጽ ሰምቶ ዞር ያለው ተኳሽ ሽጉጡን አልመለሰውም። ዳግመኛ ወደ ኋላ አነጣጠረ። የተተኮሰው ጥይት በሰውዬው ቀኝ እግር ላይ ተመሰገ። ይህን የተመለከቱ ሌሎች ደፍረው ሊከተሉት አልሞከሩም። በለጠ በሩጫ አጥሩን ጥሶ ወደ ቀጣዩ ግቢ ዘሎ ገባ ።
የፖሊስ ምርመራ
በሆቴሉ ሁለት ሰዎች በጥይት ተመተው ወድቀዋል። የሰራተኛው ጉዳት እግሩ ላይ በመሆኑ ለሞት አላበቃውም። የጄኔራሉ እስትንፋስ ግን ወዲያውኑ ጸጥ ብሏል። የምሽቱ የወንጀል መረጃ የደረሰው ፖሊስ ከሆቴሉ ደርሷል። የቆሰለውን ለህክምና፣ የሟችን አስከሬንም ለምርመራ ወደ ሆስፒታል ሲልክ በስፍራው የነበሩትን እማኞች ለጥያቄ ፈልጓቸዋል። ገዳይ ከባንኮኒው ትቶት የሄደውን ሞባይልም ተረክቧል።
በማግስቱ ፖሊስ ምርመራውን ቀጠለ። በመዝገብ ቁጥር 936/ 2004 የተከፈተው ፋይልም አስፈላጊ መረጃዎች ይሰፍሩበት ያዙ። ሁለቱ ሴቶች ከሟችና ገዳይ ጋር በነበሩበት አጋጣሚ «አየነው» ያሉትን ሁሉ ተናገሩ። በተለይ ምሽቱን ከበለጠ ጋር ያሳለፈችው ሴት ስለገዳይ ማንነት የሚጠቁም ፍንጭ ለመስጠት ፈቃደኛ ሆነች።
ሴትዬዋ ደላላው በለጠን ከዓመታት በፊት ታውቃዋለች። ባለትዳርና የልጆች አባት ነው። የራሱ ቤተሰብ ቢያፈራም ከትዳሩ ውጭ የመወስለት ፍላጎት ነበረው። ከዚህ ቀድሞ በሰው መግደል ወንጀል ተከሶ ለዓመታት በደብረብርሃን ማረሚያ ቤት መቆየቱን አጫውቷታል። ከአንድ ወር በፊት ሽጉጥ መያዙንና መኪና መግዛቱን፣ በማዕድን ሽያጭ ካገኘው በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ከሌሎች ጋር በጥቅም መጋጨቱን ሁሉ ነግሯታል።
በምክትል ሳጂን ያሬድ አለማየሁ የሚመራው ቡድን አሁንም ስራውን ቀጥሏል። ወንጀሉ በተፈጸመበት ምሽት ተጠርጣሪው አጥር ጥሶ ገብቶበታል በተባለው ትምህርት ቤት ግቢ ለማስረጃ የሚሆኑ መረጃዎች ተገኝተዋል። በወቅቱ የነበረ እማኝም ያየውን ሁሉ ተናግሯል። የዘረፋ ሙከራ በሚል በተደረገው ሪፖርት ግለሰቡን ለመያዝ በሞከሩ ጥበቃዎች ላይ ሽጉጥ ተተኩሷል። በቦታው የተገኘውን ቀለሀም ፖሊስ ለማመሳከሪያነት ተረክቧል። ፖሊስ ተፈላጊው መኖሪያ ቤት ደርሶ የተጠርጣሪውን ባለቤት በጥያቄ አፋጠጠ።
ሚስት ጉዳዩን እንደማታውቅ ለማድበስበስ ሞከረች። እንደማያዋጣት ስታውቅ ግን እውነቱን ተናገረች። የዛን ዕለት ምሽት ባሏ በስልክ እንዳገኛት፣ ከሰዎች ጋር መጋጨቱንና ማንም ቢጠይቃት አላውቅም ብላ እንድትመልስ ማስጠንቀቁን አልደበቀችም። ይህ ብቻ ያልበቃው መርማሪ የት እንደሚገኝ ደጋግሞ ጠየቃት። «በጭራሽ አላውቅም» ስትል ምላ ተገዘተች። ፖሊስ ያለችውን ሁሉ በዋዛ አላመናትም። ለተጨማሪ ጥያቄዎች ማረፊያ ቤት አደረሳት። የአዲስ አበባና የደብረብርሃን ፖሊስ በጥምረት መስራት ጀምረዋል። ቀደም ሲል በጄኔራሉ የተፈጸመውን የዝርፊያ ወንጀል የሚያውቀው የዞኑ ፖሊስ ያሉትን መረጃዎች ሁሉ ለኮሚሽኑ አድርሷል። የግለሰቡ የስልክ ልውውጦችም በቴሌኮም ጠቋሚነት በማስረጃነት ተያይዘዋል። አንድ ሰው ገድሎ ሌላውን አቁስሎ የተሰወረው ተጠርጣሪ ግን አሁንም ደብዛው አልተገኘም።
ፖሊስ የብርበራ ፈቃድ አውጥቶ መሳሪያው ተደብቆበታል በተባለ የቅርብ ጓደኛው ቤት ፍተሻ አካሄደ። የታሰበው ባይገኝም ጓደኛውን ይዞ ተመለሰ። ተፈላጊው ራሱን ለመሰወር ከሀገር እንዳይወጣ ከኢሚግሬሽንና ዜግነት ጉዳይ ዋና መምሪያ የተላለፈውን ትዕዛዝ ፖሊስ በእጁ ካስገባ በኋላ የተጠርጣሪውን ፎቶግራፎች አሰራጭቶ ፍለጋውን ቀጠለ ። ወንጀሉ በተፈጸመ ምሽት ሟች በሆቴሉ ግቢ ያቆሟትን ኮድ 2/87485 አአ የሆነች ቪታራ መኪና አስነስቶም ለቤተሰብ አስረከበ። ፖሊስ ተጠርጣሪው ሁሌም በስልክ ከሚያገኘውና አሁን አለም ገና ከሚገኘው ባልንጀራው ዘንድ ገሰገሰ።
ግለሰቡ መኖሪያው ደብቆታል የሚል መረጃ ስላለውም የፍርድ ቤት ማዘዣውን ይዞ ብርበራውን በታዛቢዎች ፊት አካሄደ። አሁንም የተገኘ መሳሪያና በቂ ማስረጃ አልነበረም። ውጣ ውረዱ ቀጥሏል። አሰሳና ፍለጋውም እንዲሁ። ፖሊስ ተስፋ አልቆረጠም። ከሆስፒታል የተገኘውን የሟች ህክምና ማስረጃን ጨምሮ ሌሎችን በማካተት ፍለጋውን ተያያዘ። አስቀድሞ በጄኔራሉ የተፈጸመው የዝርፊያ ወንጀል እልባት ሳያገኝ ሌላ ወንጀል መከሰቱ የቡድኑን አባላት እልህ ውስጥ ከቷል። የጄኔራሉ ድንገተኛ እይታ ህይወታቸውን እስከመንጠቅ ማድረሱ ሁለተኛ በደልና ግፍ መሆኑም የሰሙትን ሁሉ እያነጋገረ ነው።
አንድ ቀን የፖሊስ ሲቪል ክትትሎች ታዳኛቸውን በድንገት ከወጥመድ አስገቡት። ግለሰቡ በቁጥጥር ስር በዋለ ቀን የተጠረጠረባቸውን የዝርፊያና የግድያ ወንጀሎች ሁሉ አምኖ ቃሉን በፊርማው አረጋገጠ። ቀድሞ ስለተከሰሰባቸው ወንጀሎችና ስለቆየባቸው የእስር ዓመታትም በህይወት ታሪኩ መዝገብ ላይ አሰፈረ። አሁን ፖሊስ በበቂ ሰነድና የሰው ምስክሮች ያደራጀውን መዝገብ አጠናቋል። ጉዳዩን ለፍርድ በማቅረብም በአቃቤ ህግ በኩል ክስ መስርቷል።
ውሳኔ፦
ታህሳስ 26 ቀን 2006 ዓ.ም የአዲስ አበባ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ዳኞች በቦታቸው ተሰይመዋል። ችሎቱን የሚከታተሉ ታዳሚዎች፣ የሟችና የገዳይ ቤተሰቦችም በስፍራው ተገኝተዋል። ተከሳሹ በቀረበበት የወንጀል ድርጊት ጥፋቱን ማስተባባል ባለመቻሉ ለመጨረሻው የፍርድ ውሳኔ ቀርቧል። ዳኛው የክሱን አይነት በዝርዝር አነበቡ። ተከሳሹ በፈጸመው የግድያ ወንጀል ጥፋተኛ ሆኖ በመገኘቱ እጁ ከተያዘበት ቀን ጀምሮ በሃያ ስድስት ዓመት ጽኑ እስራት በማረሚያ ቤት እንዲቆይ ሲሉም የቅጣት ውሳኔውን አስተላለፉ።
አዲስ ዘመን መጋቢት 14/2011
መልካምስራ አፈወርቅ